Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የሚያስቅ እና የሚያሰቅቅ ጉብኝት –በኢትዮጵያ!

$
0
0

ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ- ጆርጂያ)

ይህ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት፤ ድንገት ትላንት የመጣ ሳይሆን – ቀደም ሲል ሲገነባ በቆየው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው። የትላንት ታሪካችንን ማየት የተሳናቸው የዘመኑ ገዥዎች ይህንን ላያውቁ ይችላሉ። ነገር ግን ታሪክ ሊፋቅ የማይቻል ሃቅ በመሆኑ፤ ደግመን ደጋግመን በእውነት በትር አናት አናታቸውን መቀወር ያስፈልጋል።
ADF6D103-B2F3-45BA-BEC7-4DA0AC962E4A_w640_r1_s
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በኦፊሴል ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከጀመሩ 112 አመታት ተቆጠሩ። በታህሳስ 1903 ከአጼ ምኒልክ ጋር የተነጋገሩት ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት የተላኩት፤ ሮበርት ስኪነር ነበሩ። ከአጼ ምኒልክ ጋር የተደረገው ስብሰባ ዘጠኝ ቀናትን የፈጀ ነበር። የሁለቱም አገር ህዝቦች በነጻነት እንዲዘዋወሩ፣ የንግድ ግንኙነት፣ እና አሜሪካ አባይን ለመገደብ እውቀቱ ያላቸውን ሰዎች እንድታበረክት ነበር። በኋላ ላይ ሃኪም ወርቅነህ እሸቴ (ዶ/ር ቻርልስ ማርቲን) በ1927 ወደ አሜሪካ መጥተው ሃርለምን ሲጎበኙ፤ የራስ ተፈሪን መልእክት አስተላለፉ። ወደአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመሄድም፤ በአጼ ምኒልክ ዘመን ስምምነት ላይ የተደረሰበትን የአባይን ግድብ ጉዳይ ተነጋገሩ። በእርግጥም አሜሪካውያን ጥናቱን ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ግድቡንም ለመስራት ስምምነት ላይ ተደረሶ ነበር። እነዚህን ነገሮች በደምሳሳው የምንጠቃቅሰው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት ወይም የአባይ ግድብ ሃሳብ ጭምር ትላንት የተጀመረ አለመሆኑን ለመግለጽ ነው። አንድ አንቀጽ እንጨምርና ወደ ዋናው ጉዳይ እንሄዳለን።
እንዲህ እንዲህ እያልን… ጥቁሮች ዩኒቨርስቲ መግባት በማይችሉበት ወቅት እነመላኩ በያን ኦሃዮ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ያደረጉትን የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዋረን ሃርዲንግን ጭምር ማንሳት አስፈላጊ ነው። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች ልባቸው ኢትዮጵያን ሲያስብ ኖሯል። በኢትዮጵያ እና ጣልያን ጦርነት ወቅት አለም ሁሉ ፊቱን ሲያዞርብን፤ የጣልያንን ወረራ ካልተቀበሉት አምስት አገሮች ውስጥ አሜሪካ አንዷ ነበረች። በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፉን አየር መንገድ እና የቀድሞውን አውራ ጎዳና መስሪያ ቤት የመሰረቱት አሜሪካኖች ናቸው። በ1963 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አሜሪካንን ሲጎበኙ፤ ፕሬዘዳንት ጆን.ኤፍ.ኬኔዲ ተቀብለው አስተናግደዋቸዋል። ኋይት ሃውስ በክብር የገቡትም የመጀመሪያው ጥቁር መሪ፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሆነዋል። አሜሪካኖች ከመልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን በተጨማሪ ተዋጊ መርከቦችን ጨምሮ፤ የሰጡን የጦር መሳሪያ እና የጦር ልምድ የትየለሌ ነው። ይህን ሁሉ ወደ ጎን ብንተው እንኳን፤ በ19ሰማንያዎቹ የድርቅ ዘመናት ከሌላው ህዝብ በላይ “We are the world” ብለው የታደጉንን ከቶ አንረሳውም። አለም በአውሮፕላን መቀራረብ ከጀመረች በኋላ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች ጂሚ ካርተር፣ ቢል ክሊንተን እና ጆርጅ ቡሽ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። አሁን ደግሞ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ጎበኙ። ከዚያስ? የሆነውን አብረን እንከታተል።

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በኦፊሴል ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከጀመሩ 112 አመታት ተቆጠሩ። በታህሳስ 1903 ከአጼ ምኒልክ ጋር የተነጋገሩት ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት የተላኩት፤ ሮበርት ስኪነር ነበሩ። ከአጼ ምኒልክ ጋር የተደረገው ስብሰባ ዘጠኝ ቀናትን የፈጀ ነበር። የሁለቱም አገር ህዝቦች በነጻነት እንዲዘዋወሩ፣ የንግድ ግንኙነት፣ እና አሜሪካ አባይን ለመገደብ እውቀቱ ያላቸውን ሰዎች እንድታበረክት ነበር። በኋላ ላይ ሃኪም ወርቅነህ እሸቴ (ዶ/ር ቻርልስ ማርቲን) በ1927 ወደ አሜሪካ መጥተው ሃርለምን ሲጎበኙ፤ የራስ ተፈሪን መልእክት አስተላለፉ። ወደአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመሄድም፤ በአጼ ምኒልክ ዘመን ስምምነት ላይ የተደረሰበትን የአባይን ግድብ ጉዳይ ተነጋገሩ። በእርግጥም አሜሪካውያን ጥናቱን ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ግድቡንም ለመስራት ስምምነት ላይ ተደረሶ ነበር። እነዚህን ነገሮች በደምሳሳው የምንጠቃቅሰው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት ወይም የአባይ ግድብ ሃሳብ ጭምር ትላንት የተጀመረ አለመሆኑን ለመግለጽ ነው። አንድ አንቀጽ እንጨምርና ወደ ዋናው ጉዳይ እንሄዳለን።

obama
እንዲህ እንዲህ እያልን… ጥቁሮች ዩኒቨርስቲ መግባት በማይችሉበት ወቅት እነመላኩ በያን ኦሃዮ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ ያደረጉትን የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዋረን ሃርዲንግን ጭምር ማንሳት አስፈላጊ ነው። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች ልባቸው ኢትዮጵያን ሲያስብ ኖሯል። በኢትዮጵያ እና ጣልያን ጦርነት ወቅት አለም ሁሉ ፊቱን ሲያዞርብን፤ የጣልያንን ወረራ ካልተቀበሉት አምስት አገሮች ውስጥ አሜሪካ አንዷ ነበረች። በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፉን አየር መንገድ እና የቀድሞውን አውራ ጎዳና መስሪያ ቤት የመሰረቱት አሜሪካኖች ናቸው። በ1963 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አሜሪካንን ሲጎበኙ፤ ፕሬዘዳንት ጆን.ኤፍ.ኬኔዲ ተቀብለው አስተናግደዋቸዋል። ኋይት ሃውስ በክብር የገቡትም የመጀመሪያው ጥቁር መሪ፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሆነዋል። አሜሪካኖች ከመልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን በተጨማሪ ተዋጊ መርከቦችን ጨምሮ፤ የሰጡን የጦር መሳሪያ እና የጦር ልምድ የትየለሌ ነው። ይህን ሁሉ ወደ ጎን ብንተው እንኳን፤ በ19ሰማንያዎቹ የድርቅ ዘመናት ከሌላው ህዝብ በላይ “We are the world” ብለው የታደጉንን ከቶ አንረሳውም። አለም በአውሮፕላን መቀራረብ ከጀመረች በኋላ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች ጂሚ ካርተር፣ ቢል ክሊንተን እና ጆርጅ ቡሽ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። አሁን ደግሞ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ጎበኙ። ከዚያስ? የሆነውን አብረን እንከታተል።

ምን ያህል ሰው ልብ እንዳለው ማወቅ ያስቸግራል። የፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማን የእራት ምሽት ንግግር ልብ ይበሉ። በአማርኛ ቋንቋ “እንደምን ዋላቹህ?” ብለው ነው ንግግራቸውን የጀመሩት። “የኢትዮጵያ ታሪክ የ200 አመት ታሪክ ነው” ሲሉን ለነበሩ ሰዎች ነው – ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን እና ጥንታዊነቷን የመሰከሩት።
የአጼ ምኒልክን ወራሪነት ለሚሰብኩት ሰዎች ነው፤ “ኢትዮጵያ – ከጥቁር አሜሪካውያን በፊት ለነጻነቷ የተዋጋች አገር ናት” ብለው ያሞገሷት። ሌላው ቀርቶ የንጉሥ ሰለሞን እና የንግሥተ ሳባን ግንኙነት፤ “ተረት ተረት ነው” ሲሉን የነበሩ ሰዎች በብሄራዊ ሙዚየም፤ የንግሥተ ሳባን ስዕል እያዩ እና እያሳዩ ስናይ፤ የታሪክን አሸናፊነት ተገነዘብነ።
ሌላው ቀርቶ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የሉሲን አጽም በመገረም ሲመለከቱ፤ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ “የዚህ አጽም ብሄር ምን ይሆን?” ብለው… ሆዱን ቁርጠት ይዞት ፊቱን ቅጭም ያደረገ ህጻን ልጅ መስለው ነበር።
በአጠቃላይ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በዝርዝር ያቀረቧቸው የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች፤ በሰዎቹ የፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ “የነፍጠኞች ታሪክ” ተብሎ የተመዘገበ ነው። ኢህአዴግ አገሪቱን እንደተቆጣጠረ ሰሞን፤ “በብሄራዊ ሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙት የአጼ ምኒልክ እና የሌሎች ነገስታት አልባሳት መቃጠል አለባቸው” ሲሉ የነበሩትን ወገኖች በሙዚየሙ ጉብኝት ወቅትአላየናቸውም። ቢያንስ ተወካያቸው ግን በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን ታሪክ የተማረ ይመስለናል። እናም “በፕሬዘዳንት ኦባማ ጉብኝት ወቅትት፤ ጎልቶ እና አሸንፎ ለወጣው የኢትዮጵያውያን ታሪክ ዘላለማዊ ክብር ይሁን!” አልነ።
በነገርዎ ላይ… የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በእራቱ ግብዣ የመጨረሻ ንግግራቸው ላይ፤ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት፣ ቀስተ-ደመና ለተወለደባት ለኢትዮጵያ እንዲሁም “ለጤናችን” ብለው ፅዋቸውን ለማንሳት ሲዘጋጁ፤ (የአስተናጋጁን ነውር አይታችኋል?) አተናጋጁ በግራ እጁ መለኪያውን ሰጥቶ ሂድት ይላል። የሱ ገርሞን ሳያበቃ… የኛው ሰውዬ ደግሞ በምላሹ፤ ከጽዋው ባይጎነጩም (ምናልባት በሃይማኖት ምክንያት ይሆናል)፤ “እኛም እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን” ብለዋል። በቅሌት ላይ ቅሌት ሲደራረብብን፤ ከአንድ ቀን በፊት ቦሌ ላይ የነበራቸውን ሁኔታ አስታወሰን። ቦሌ ላይ እጅ ዘርግቶ መቀበል ብቻ ሳይሆን፤ ተንበርክከው መቀበል ቢኖርባቸው የሚያደርጉት ነው የሚመስለው። ለዚህ አባባል ምስክር እንዲሆነን፤ በፊልም ደንብ Flash back ሂደት ወደ ኋላ በማጠንጠን፤ ለፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ቦሌ ላይ የተደረገላቸው አቀባበል፤ “ኧረ የፕሮቶኮል ሹም ያለህ!” የሚያሰኝ ነውና – እስኪ ትንሽ እንጨዋወት።

ጁላይ 26 ቀን፣ 2015 የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው የብዙዎች ግምት ነበር። ሆኖም ምስቅልቅሉ በወጣ እና ፕሮቶኮሉን ባልጠበቀ፤ አሳፋሪ ግርግር የአቀባበሉ ስነ ስርአት ተበላሸ። እዚያ የተገኙት ጥቂት የኢህአዴግ ሹመኞችን ብንጠላቸውም እንኳን፤ እንደሰው መጠን አሳዝነውናል። ከሃዘናችን በላይ ግን ሰዎቹ ኢትዮጵያን ወክለው ሲቆሙ፤ ክብራችንን ዝቅ በሚያደርግ ደረጃ እንዲያዋርዱን መፍቀድ የለብንም። ለፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የተደረገውን አቀባበል የተመለከተ ማንም ሰው፤ በአገሪቱ የፕሮቶኮል ሹም ወይም የእንግዳ አቀባበል ስነ ስርት እንደሌለ ሊስማማ ይችላል።

እናም ቦሌ ላይ… “ኤርፎርስ አንድ” አውሮፕላን ካረፈ በኋላ፤ የመውረጃውን መሰላል የተሸከመው መኪና ግራ እንደተጋባ ያስታውቅ ነበር። መኪናው መሰላሉን ተሸክሞ ወደ ፓይለቱ መውረጃ ገሰገሰ። ሆኖም ቁመቱ አልደርስ ብሎት እየታገለ ሳለ፤ በአውሮፕላኑ ያልታሰበ ክፍል፤ ባራክ ኦባማ ከውስጥ በሩን ከፍተው ብቅ አሉ። መሰላሉ ግን በስፍራው የለም። ሰውየው ባራክ ኦባማ መሆናቸው በጀ እንጂ፤ ሌላ ቀልቃላ ፕሬዘዳንት ቢሆን ከአውሮፕላኑ ላይ ሊፈጠፈጥ እንደሚችል አትጠራጠሩ። እናም እንደአለም ዋንጫ ሂደቱን በቴሌቭዥን እያየን፤ “ኧረ ቆይ ክቡርነትዎ” እያልን ሰጋን። ሆኖም አትሙች ያላት ነፍስ ተመልሳ ወደ ውስጥ ገባች። ባራክ ኦባማ ከፍተው ሊፈጠፈጡበት የነበረው በር ተመልሶ ተዘጋ። ያ – የመውረጃ መሰላል የተሸከመውና በፓይለቱ መውጫ በኩል ለማስጠጋት ይጥር የነበረ ሹፌር… በፍጥነት አነዳድ ተከፍታ ወደተዘጋችው በር ሄደ። (ትዕይንት አንድ አበቃ)
ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ቀይ ምንጣፍ ተዘጋጅቶ አልጠበቃቸውም። ትንሽ ቆይተው ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀይ የቃልቻ የሚመስል ጃንጥላ ተይዞላቸው ወደ አውሮፕላኑ መጡ። ከሳቸው በፊት ቆመው የሚጠብቁትን ጥቂት ሚንስትሮቻቸውን ቀና ብለው እንኳን ሳያዩ ወደ አውሮፕላኑ ስር ተጣድፈው ደረሱ። ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ከአውሮፕላኑ ወርደው ሳይጨርሱ፤ ህጻናቱ አበባ ለመስጠት አሰፈሰፉ። አንድ ሳይሆን ሁለት አበባ ይዘዋል። ሁለተኛው አበባ ለማን እንደሆነ አምላክ ይወቀው። (ትዕይንቱ ቀጥሏል)
አቀባበል ሊያደርጉ ከሄዱት ሚንስትሮች መካከል፤ ፌስ ቡክ ላይ ፎቶ በመለጠፍ የሚታወቁት የውጭው ጉዳይ ሚንስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባራኪ ስልካቸውን ይዘው፤ ለፌስ ቡካቸው የሚሆን ፎቶ ለማንሳት ቢሞክሩም የአሜሪካው ሴኩሪቲ ኮስተር ብሎ ሲያያቸው፤ የሚገቡበት ጠፋቸው። ሌሎቹ ሚንስትሮች እንደምንም ተጋፍተው ወደ ባራክ ኦባማ ሲሄዱ ዶ/ር ቴድሮስ ከኋላ ተሸፍነው ቀሩ። ነገሩ ቅጥ አምባሩ ጠፋ። ፕሮቶኮል ትሁን ምን ያላወቅናት ሴትዮ፤ ከህጻናቱ ጋር አብራ ትጋፋለች። ተጋፍታ ሄዳ ፕሬዘዳንት ኦባማን ትጨብጣለች። የህወሃቱ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ጎንበስ ብሎ የሚሆነውን ሲመለከት፤ ሌሎቹም እሱን ተከትለው ሲያጎነብሱ – በሁኔታው ሃፍረት የተሰማቸው በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ግርማ ብሩ፤ የብርሃነ ገብረክርስቶስን ጀርባ ደልቀው፤ ስነ ስርአት እንዲይዙ ለማድረግ ይሞክራሉ። ትርኢቱ እያሳቀ ያሳቅቃል።

ይሄ ሁሉ ሲሆን… ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ፤ ስለህጻናቱም ስለሚንስትሮቻቸውም ግድ ሳይሰጣቸው፤ ከሁሉም በላይ ተንሰፍስፈው ወደ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ አመሩ። (እኛ በቲቪ እያየን “ኧረ አትንሰፍሰፉ” እንላለን) ጠ/ሚንስትሩ – ፕሬዘዳንቱን ጨብጠው ምን እንዳሏቸው ባናውቅም፤ አቶ ኃይለማርያም በደስታ የሚይዙት እና የሚጨብጡት ጠፍቷቸው ፍንድቅድቅ አሉ። እግር ኳስ ጨዋታ ሲጀመር፤ የቡድኑ ካፒቴን ግዜ ወስዶ – ሌሎቹን ተጫዋቾች የሚያስተዋውቀውን ያህል እንኳ አልተጨነቁም – አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ። ሚንስትሮቹን በስርአት ሳያስተዋውቁ፤ ወደ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ መኪና አብረው ሄዱ። ልክ ወደዛ እየሄዱ ሳለ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ለፌስቡክ የሚሆናቸውን ፎቶ ለማንሳት ስልካቸውን ይዘው ፎቶ ለማንሳት በድጋሚ ታዘብናቸው። ሆኖም በዚያች ቅጽበት ፕሬዘዳንት ኦባማ ወደመኪናቸው ገብተው፤ በፍጥነት ቦሌ አየር ማረፊያን ለቀው ሄዱ። እናም ለታላቁ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የተደረገው አቀባበል እዚህ ላይ አበቃ። ለጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያምም፤ ለቃልቻ የሚያዘው ቀይ ባለ አዝራር ጃንጥላ ተይዞላቸው አየር መንገዱን ለቀው ወጡ።

እንደ እብድ ቡድን የተዘባረቀ ሱፍ የለበሱትን ሚንስትሮች ትተን አበባ እንዲሰጡ የተደረጉትን ልጆች እንቃኝ። ልጆቹ አበባውን ከሰጡ በኋላ ፕሬዘዳንቱን መኪናቸው ድረስ ተከትለው፤ የማናውቀውን ነገር ያወሯቸዋል። እነዚህ ልጆች እንደባህላችን ጸጉራቸውን ሽሩባ ተሰርተው… ደግሞም የአገር ባህል ለብሰው አልቀረቡም። ጭራሹን ከአራቱ አንዷ… ጸጉሯን ጨበርኛ ተሰርታ፣ ካኪ ኮት እና ጥቁር ሱሪ አድርጋ… ከታች ሸራ ጫማ ሸብ አድርጋ እንድትቀበል ነው የተደረገው። እንደዚህ አይነት አለባበስ ኢትዮጵያውያንን ሊወክል አይችልም። እንጨምር ከተባለ ሌላም ማለት ይቻላል።

በንጋታው ቡና ሲፈላ የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ቡና የሚያፈሉት ሴቶች ‘ለምን አሮጊቶች ሆኑ ብሎ መከራከር ወይም ለምን የትግሬ ሹሩባ ተሰሩ?’ ማለት አግባብ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ቡና ሲፈላ፤ በሙቀጫ የተወቀጠ የሚመስል – ጋቢ አይሉት ነጠላ አድርጎ ቡና ማስተናገድ ምን የሚሉት ባህል ነው? ባህል ለማሳየት ከሆነ ያስፈለገው እጣኑ በገል፣ ስኒው በረከቦት፣ ቄጤማው ተጎዝጉዞ፣ ፈንዲሻው ተበትኖ፣ ቁጢጥ ከሚሉም በርጩማ ላይ ቁጭ ብለው – አቦል ቶና በረካ ቢጠጡ ደስ ይል ነበር።
በዚያ ላይ ለዳንኪራ የተጠሩት ልጆች እንደድሮ የቀበሌ ኪነት፤ አራምባ እና ቆቦ ሲረግጡ አይተን… “የአገር ፍቅር ቴያትር ቤት ተወዛዋዦች ባይኖሩ፣ የማዘጋጃ እና የብሄራዊ ልጆች ወዴት ሄዱ?” ብለን አዝነናል። በዚያ ላይ ልጆቹ እስክስታቸውን ሲጨርሱ፤ አበባየሆሽ ለማለት እንደመጡ ህጻናት እየተገፈታተሩ ሲወጡ አይተን… “ምን እየተካሄደ ነው?” ማለታችን አልቀረም።
አቀባበሉን ከኬንያው ጋር ማነጻጸር አይቻልም። ኬንያዎቹ ሽር ጉድ ሳያበዙ ዘና ብለው ነው አቀባበል እና አሸኛኘት ያደረጉት። በሬድዮ እና በቴሌቭዥን ብዙ በጣም ብዙ ሲባል ነበር። በየመንገዱ ሳይቀር የፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ፎቶ ተለጥፏል። ከፎቶውም ስር በትላልቁ፤ “Thank you for vesting Ethiopia!” ተብሎ ተጽፏል። የዚህ ቀጥታ ትርጉም “ኢትዮጵያን እንዳሻዎ ስለሚያደርጓት እናመሰግናለን” የሚል ነው። ይሄን እንዲጽፍ ሃላፊነት የተሰጠው ሰው visiting ለማለት ፈልጎ vesting ማለቱ እውነት ነው። “Thank you for visiting Ethiopia” ለማለት ነበር የተፈለገው። እንግዲህ ዲግሪ በገንዘብ በሚገዛበት አገር ይህ ነገር መፈጸሙ ሊገርመን አይገባም፤ ሆን ተብሎ ቢደረግም አይደንቀንም።

ወደ እንግዳው አቀባበል እንመለስ። በአገራችን ከአጼ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ትላልቅ እንግዶች ሲመጡ፤ ለክብራቸው 21 ግዜ መድፍ ይተኮሳል። እ.አ.አ በ1903 በአሜሪካው ፕሬዘዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የተላከው የመጀመሪያው ዲፕሎማት ሮበርት ስኪነር፤ አዲስ አበባ ገብቶ ከአጼ ምኒልክ ጋር ከተገናኘ በኋላ፤ ለክብራቸው 21 ግዜ መድፍ እንደተተኮሰ እና የንጉሠ ነገሥቱ የሙዚቃ ባንድ አጅቧቸው ወደ ራስ ወልደጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት ለማረፍ መሄዳቸውን ጽፏል። ከመቶ አመት በፊት አጼ ምኒልክ ለአሜሪካ ልዑካን ቡድን ያደረጉትን ያህል አቀባበል ማድረግ ሊያቅተን አይገባም ነበር። ይህችን አጋጣሚ በመጠቀም በወቅቱ የምኒልክን ፎቶ አንስቶ ነበር እዚህ ላይ ፎቶዋን አናካፍለናቹህ ወደ ጉዳያችን እንለፍ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለሰማይ እና ለምድር የከበዱ ሰዎች ሲመጡ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በዘመኑም ሆነ አሁን ጭምር በአለም ህዝብ ዘንድ ከፍ ብለው የሚታዩት የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ከአዲስ አበባ አልፈው ጢስ አባይን ጭምር ጎብኝተዋል። ከማርሻል ቲቶ ጀምሮ የብዙ አገር መሪዎች በክብር ተስተናግደዋል። የኩባውን ፕሬዘዳንት ፊደል ካስትሮን ጨምሮ በርካታ ፕሬዘዳንቶች ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በጥሩንባ ጭምር፤ ህዝቡ በነቂስ እንዲወጣ ተደርጎ ነው አቀባበል ያደረገላቸው። ይሄን ማንሳታችን እንኳን፤ አንዳንድ ግዜ እራሳችንን እስከሚገርመን ድረስ፤ ከዚህ ዘመን በፊት አንድም ታዋቂ የአለም መሪ ኢትዮጵያ መጥቶ እንደማያውቅ ተደርጎ ስለተነገረን – በቁጭት አይነት ያነሳነው ጉዳይ ነው።

የደቡብ አፍሪቃው ኔልሰን ማንዴላ ለአፍሪካ አንድነት ስብሰባ አዲስ አበባ ሲገቡ፤ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ፕሬዘዳንት የነበሩት መለስ ዜናዊ ጃኬት አድርገው ያደረጉት አቀባበል ገርሞን ሳያበቃ፤ የአሁኖቹ ደግሞ ሙሉ ሱፍ ልብስ አድርገው ይበልጥ አሳቀቁን። የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሬሳ ቦሌ ሲገባ የተደረገለትን ያህል አቀባበል፤ ለፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ማድረግ ተስኗቸው፤ እንደገመሬ ያለስርአት ሲግበሰበሱ አይተን ተገረምነ። እንደው… ‘ወደፊት ገና ብዙ የምንሸማቀቅበት ጉዳይ ይኖራል’ ብለን በማሰብ፤ ‘የባሰ አታምጣ’ ብለን በመጸለይ፤ ሃፍረታችንን ዋጥ አድርገን ትዕይንቱን ያለቁጥር መቁጠር ቀጠልን።

የሚገርመው ግን… ይሄን ሃፍረት የተመለከተ አምላክ አሳፍሮ አላሳፈረንም። ለአቀባበል በሚመስል መልኩ… በአዲስ አበባ ላይ ትልቅ ቀስተ ደመና ታየ። ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ታላቅ አቀባበል ያደረገላቸውን ቀስተ ደመና ለማስታወስ ይመስላል። የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን፤ “Here is the land where the first harmony in the rainbow was born…” በማለት በእራት ግብዣ ንግግራቸው ላይ ታዳሚውን አስጨብጭበዋል።

ከጭብጨባው ወጥተን ወደ ከተማው ከሄድን ደግሞ ብዙ ሹክሹክታ አለ። የቱን ይዘን የቱን እንደምንተው ግራ ይገባናል። “የብአዴን ሰዎች ለምን የሉም?” የሚሉ ሰዎች አሉ። በረከት ስምኦን ኦባማን እንደማይቀበል ሲያውቅ ወዲያው ነው የታመመው አሉ፡) “ግን እነአዲሱ ለገሰ? ተፈራ ዋልዋ? ከኦህዴድ የተጠራ ማንም የለም እንዴ? አባ ዱላ፣ ኩማ ደመቅሳ የታል? ከህወሃት ሰዎች እነአሞራ አልተጠሩም? የመለስ ሚስት የት ገባች? እነብሃት ነጋ? ስዩም መስፍን?” ይሄ ሁሉ ጥያቄ የውስጥ ለውስጥ ሹክሹክታ ነው። ከነዚህም ሰዎች አልፎ፤ በትክክለኛው ፕሮቶኮል መሰረት፤ “ፕሬዘዳንትን የሚቀበለው ፕሬዘዳንት ነው” ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ሃሳባቸውን ለአንድ ደቂቃ እንጋራና፤ “እውነት ግን… ለመሆኑ የኢትዮጵያው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የት ናቸው?” ማለታችን አይቀረም። (እንደ’እውነቱ ከሆነ… ብዙ ኢትዮጵያውያን ፕሬዘዳንቱን ቀርቶ፤ የፕሬዘዳንቱን ሙሉ ስም አያውቁም።)

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 71 የፕሬዘዳንቱ ሚና ውሱን ቢሆንም፤ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ቢያንስ እንግዳ ለመቀበል የሚያንስ ትከሻ እንደሌላቸው ይታወቃል። እናም አንዳንዶች ‘ፕሬዘዳንቱ ቢያንስ ቦሌ ሄደው ባራክ ኦባማን ሊቀበሉ ይችላሉ’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል… ቦሌ ላይ ሲያጧቸው ደግሞ ‘ብሄራዊ ቤተ መንግስት አቀባበል ያደርጉላቸዋል’… ብለውም አስበዋል። ሁለቱም ግን አልሆነም። ህገ መንግስቱ እንደማይከበር ብናውቅም፤’ ፕሬዘዳንቱን በእድሜ እንኳን አክብረው ለዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ትንሽ ሚና ይሰጧቸው ይሆናል’ ብለን ብናስብም… ሰውየው የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ። ከዚያው ጋር ግን አንድ ቀልድ ሰማነ። ነገሩ እንዲህ ነው።

ፕሬዘዳንት ኦባማ አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት የብሄራዊ ቤተ መንግስት በር ተንኳኳ። ፕሬዘዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋቢያቸውን እንዳደረጉ፤ ‘ምን መጣ?’ ብለው በሩን ሲከፍቱ፤ ከአሜሪካ ኢምባሲ ከተላኩ ሰዎች ጋር ይፋጠጣሉ።
“ምን ልታዘዝ?” ፕሬዘዳንቱ ናቸው።
“ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ሲመጡ፤ ስለአቀባበላቸው ለመነጋገር ነበር።” አሜሪካኖች ይመልሳሉ።
“ታዲያ እኔ ምን አውቃለሁ? ሰዎቹን አናግሯቸው እንጂ።” ይላሉ ፕሬዘዳንት ተሾመ።
“እርስዎ በዚህ ጉዳይ መነጋገር አይችሉም?” አሜሪካኖቹ ገርሟቸው ጠየቁ።
“እኔ ቤት ጠብቅ ተብዬ ነው። አሁን ሰዎቹ የሉም።” ብለው በሩን ዘጉባቸው – አሉ።

የ’ነዚህ ሰዎች ነገር… አንዳንዱ ድርጊታቸው ቢያስቅም፤ ኢትዮጵያን ወክለው የሚያደርጉት ተግባር ግን እያሳቀቀን ነው።
የሆነው ሁሉ ሆኖ ግን በአንድ ነገር እንጽናናለን። ልብ በሉ። ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ኢህአዴግ ለ17 አመታት አደረኩት ስላለው የጀብድ ትግል አላወሩም። ነገር ግን 130 አመታት ወደ ኋላ ተመልሰው፤ አጼ ምኒልክ አድዋ ላይ ያደረጉትን ድል አወደሱ። አጼ ምኒልክን የሚጠሉ ሰዎች አንገታቸውን ሊደፉ ይችሉ ይሆናል። ፕሬዘዳንቱ ግን… ደግመው ደጋግመው የኢትዮጵያውያንን ተጋድሎ ሲተርኩ፤ የምኒልክ ዘመን ሰዎችን ገድል ነው – የነገሩን። ሌላው ቀርቶ በአፍሪቃ ህብረት ንግግራቸው ላይ… በአፍሪቃ የሚገኙ አምስት ዲሞክራቲክ አገሮች ብለው፤ እነናይጄርያን፣ ጋና፣ ታንዛንያ የመሳሰሉትን አገሮች በምሳሌነት ሲጠቅሱ ኢትዮጵያ በዝርዝሩ ውስጥ የለችበትም። ይሄ ለነአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዱብ’ዳ መሆን አለበት።
እንዲህም ሆኖ ግን… ኢህአዴግ መራሽ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች አሁንም “ለፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።” ሲሉ ‘የት? መቼ?’ ማለታችን አይቀረም። የቦሌው ሲገርመን… በንጋታው በብሄራዊ ቤተ መንግስት ሲደርሱ፤ በጃንሆይ ግዜ አሎን ሲነጠፍ የምናውቀውን ምንጣፍ ውጪ አውጥተው ዘረጉት። ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፈውን ኢሳት እና ሌሎች ድረ ገጾች ለማፈን በቀን ብዙ ሚልዮን ዶላር የሚያባክን አምባገነን መንግስት በDust mite የነተበ ምንጣፍ ለባራክ ኦባማ ክብር ዘረጋላቸው። በጣም የሚያስቀውና የሚያሳቅቀው ደግሞ “Welcome” የምትል፤ ከWal Mart በ$3.99 ገዝተን ውጪ የምናቀምጣት አይነት፤ መናኛ እግር መጥረጊያ ተደረገላቸው። ከዚያም ለ20 ሰከንድ ያህል የቆየው የማርሽ ሙዚቃ አስደመመን። ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማም… እንደ”አሳ በለው በለው” ዳንስ አራት መአዘን ሆኖ በተነጠፈ ምንጣፍ ላይ፤ ሲሽከረከሩ፤ ‘ነገሩ የህጻን ጨዋታ ነው እንዴ?’ አልነ። በዚያ ላይ ከዳይኖሰር አፍ የወደቁ ፓስታ የሚመስሉ ቀጫጭን ሰዎች ተሰልፈው ስናይ፤ የድሮ ት/ቤታችንን ባንድ አመሰገንን። ካልሲያቸውን ሱሪያቸው ላይ ገድግደው፤ ወይም ገምባሌያቸውን በሱሪያቸው ላይ ለብሰው ቆመው ስናይ፤ “የቤተ መንግስቱ የክብር ዘቦች እነዚህ ናቸው?” ብለን ተገረምን።
ሌላ ትዝብት እንጨምር። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተሻለ እንግሊዘኛ ቢችሉም፤ አሜሪካም ሆነ የተባበሩት መንግስታት ፊት በአገራቸው ቋንቋ ነበር የሚያወሩት። ይቺን ጫፍ ይዘን ወደ ጋዜጣዊ መግለጫው እናምራ። “ፕሬዘዳንት ኦባማ – ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ።” ከዚያ በኋላ… አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንግሊዘኛውን እያነበቡ ሳለ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ ትርጉሙን ባማርኛ ያስነብበን ጀመር። የሚገርመው ታድያ አቶ ኃይለማርያም በእንግሊዘኛ የሚሉት እና ባማርኛ ተተርጉሞ የሚጻፈው አረፍተ ነገር ፈጽሞ የሚገናኝ አልነበረም። ይሄ ገርሞን ቀና ስንል ደግሞ፤ ኦባማ ማናገሪያ ላይ ኮከቧን ለጥፈዋታል። “ይሁን” ብለን ስናልፈው ደግሞ የማይታለፍ ነገር ገጠመን። ከሁለቱ ሰዎች ጀርባ አይናችንን የሚስብ ነገር አየነ። የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ባንዲራ በስቴፕለር ሽቦ አንድ ላይ ተሰፍተዋል። የኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ ሲንከረፈፍ አልታይ እያለ የሚያስቸግረውን፤ አምባሻ መሰል ሰማያዊ ኮከብ ለማሳየት ሲሉ፤ እንደሰፈር ልጆች… የኢትዮጵያን ባንዲራ በግድ ወደ ጎን ወጥረው ከአሜሪካ ባንዲራ ጋር ሰፍተውት ብንመለከት፤ መግለጫውን በደንብ ሳናጣጥመው አለቀ። በኋላ ላይ እንደሰማነው ግን፤ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ አንዳንድ ቁም ነገሮችን ተናግረዋል – አሉ። በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አለመኖሩን በዘወርዋራ፤ በኤርትራ በኩል ዘልቀው የሚዋጉት አርበኞችም አሸባሪዎች አለመሆናቸውን በቀጥታ ማሳወቃቸውን ሰማነ።
ከዚያ በኋላ፤ “ፕሬዘዳንት ኦባማ ቡና ጠጡ። እስክስታ መቱ።” ይሄ ሁሉ እልል ሊያስብል ይችል ይሆናል።
እንግዲህ ሁሉም ነገር አበቃ። ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ጽዋቸውን ሲያነሱ፤ ‘የኛ ሰውዬ’ ደግሞ እጃቸውን ዘረጉ። ከዚህ በኋላ ያለውን ታሪክ ለመጻፍ፤ የታሪክ መዝገቡ ክፍት ሆኖ እየጠበቀን ነው። እዚህ መዝገብ ላይ፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘው ሃይል በአዲስ ምዕራፍ… የራሱን ታሪክ ጽፎ ማለፍ አለበት።

ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ያመኑበትን ጉብኝት አድርገዋል። ያላመኑበት ነገር ደግሞ አለ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰብአዊ መብት እንደማይከበር ገብቷቸዋል። የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር አበክረው ገልጸዋል። ይህ አቋማቸው አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት በመነባረቁ ነበር፤ ከሳቸው ጉብኝት በፊት የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በከፊል እንዲፈቱ የተደረገው። በአፍሪቃ አንድነት አዳራሽ ውስጥ፤ “ምርጫ ማድረግ ማለት፤ ዲሞክራሲያዊ አያሰኝም።” ሲሉ በአዳራሹ ከላይ የተቀመጡት ሰዎች በጭብጨባ እና በሆታ ሃሳቡን ተቀበሉት። በነገራቹህ ላይ እነዚህ ሰዎች ብዙዎቹ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰሩ ናቸው። ደሞዝ የሚከፍላቸውን መንግስት ቢወክሉም፤ የኢህአዴግ መንገድ ትክክል ስላልሆነ ነው – “ምርጫ ማድረግ ማለት፤ ዲሞክራሲያዊ አያሰኝም።” ሲባል፤ ሆ ብለው በደስታ የጮሁትም እነሱ ነበሩ። (አሸባሪ ተብሎ ከመከሰስ ያድናቹህ)

ፕሬዘዳንት ኦባማ በሌሎች አገሮች ጉብኝት ሲያደርጉ፤ ለመሪዎቹ የሚሰጡትን አክብሮት እርግፍ አድርገው በመተው፤ አምስት ካሏቸው ዲሞክራቲክ አገሮች ውጪ የኢትዮጵያን መሪዎች ጨምሮ ሙልጭ አድርገው ነው የነገሯቸው። መሪዎች በስልጣን ላይ የመቆየታቸውን በሽታ አስመልክቶ ትዝብታቸውን ከገለጹ በኋላ… ከአፍሪቃ ኔልሰን ማንዴላን፤ ከአሜሪካ አብርሃም ሊንከንን እንደጥሩ ምሳሌ አድርገው አቅርበዋል። ስልጣን ላይ የሚቆዩትን የአፍሪካ መሪዎች አምርረው ወቅሰዋል። የፕሬስ ነጻነትን ቀጫጫነት፣ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ኢትዮጵያ ውስጥ በበቂ መጠን እንዳልጎለበተ አምነዋል። የኤርትራን ድንበር አቋርጠው ለነጻነት የሚታገሉ አርበኞች አሸባሪዎች አለመሆናቸውን በቃላቸው መስክረዋል። ይህንን የበለጠ ማጉላት ያስፈልጋል።

ፕሬዘዳንት ኦባማ ከአፍሪቃ መልስ ኋይት ሃውስ ከገቡ በኋላ፤ “Shame on you” ከማለት ይልቅ (ብዙም ደስ የማይል ቃል ነው)፤ መልካም ጅምራቸውን አድንቆ፣ እውነቱን በመመስከራቸው አመስግኖ፤ ንግግራቸውን የሚያጠናክር ተጨባጭ መረጃ ማቀበል ያስፈልጋል። ያለበቂ ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች እና የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ፤ ንብረታቸውም ሊመለስላቸው እንደሚገባ፤ ደግመን ደጋግመን ለአሜሪካ መንግስት መግለጽ አስፈላጊ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሚዲያ – የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ጉብኝትን አመልክተው ብዙ ብለዋል። ብዙ የተባለው በሙሉ ግን፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ያህል ጥቅም ላይ የዋለ ነው። የዚያኑ ያህል የፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ ቆይታ፤ በአሜሪካ ትላልቅ ሚዲያ ምንም አልተባለለትም – ማለት ይቻላል። ይህ ምን እንደሚያሳይ ግልጽ ነው። ከዚህ በመነሳት ወደ ቀጣዩ የታሪክ ምዕራፍ ራሳችንን ማሸጋገር ይኖርብናል።

በመጨረሻም ስንበት። ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በተደረገላቸው የእራት ግብዣ ላይ፤ የኢትዮጵያዊነት መአዛ ያለውን የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን አንቀፀ-ቃል ትንሽ አቃምሰው ነበር። ፕሬዘዳንቱ ሙሉውን አላሉትም። ሙሉው አንቀፀ-ቃል ከዚህ የሚከተለው ነው።

“Here is the land where the first harmony in the rainbow was born. We walk on the bed rock of our planet’s first continent. Here is the root of the Genesis of Life; the human family was first planted here by the evolutionary hand of Time….We walk on the footprints of the evolutionary ancestors of Man.” ፕሬዘዳንቱ ይህን ብለው ሲያበቁ፤ እኛም ጽዋችንን በቀኝ እጃችን አንስተን፤ “እነሆ በረከት” እንኳን ደህና ወጡ – ብለናቸዋል – ፕሬዘዳንታችንን።

የፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማን የኢትዮጵያ ቆይታ በወፍ በረር ቃኝተናል። ጉብኝታቸውም ተጠንቆ ተሸኝተዋል። እኛንም ሸኙን። እነሆ ለስንብት “አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ” ብለን ጽዋችንን አንስተናል። በያላችሁበት አሜን በሉ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>