በአብርሃም በዕውቀት
እርግጥ ነው ፕሮፌሰርን ለመተቼት የሚመጥን ቀርቶ ሊመጥን የሚጠጋ የዕውቀት ልክ ላይኖረኝ ይችላል፡፡ ለዚያውም ከፕሮፌሰርነታቸውም በላይ ሕይወት ያስተማራቸውንና በተቃውሞ ፖለቲካው ጫፍ የወጣ ዕውቅና ያላቸውን ፕሮፌሰር ጽሑፍ መንቀፍ በፌስቡክ ዳኞች በስቅላት ሁሉ ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ ኧረ ራሳቸውም ሊሰቅሉኝ ባይችሉም ሊያሳቅሉኝ ይችላሉ፡፡ በእርግጠኝነት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ለመተቼት መሞከር የሚያስከትለውን ዘለፋና ነቀፌታ በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ምክንያቱም እርሳቸው ከአገራችን ፊደላውያን መካከል ቁንጮ ናቸውና፡፡ ነገር ግን ፈርቶ ከመሞት ተናግሮ መሞት ይሻላል ብዬ ትችቴን ልቀጥል መሰለኝ? በቃ እንዲያውም ቀጠልኩ፡፡
ፕሮፌሰሩ ባለፈው ግንቦት ወር አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ የሚል መጽሐፍ ለገበያ አብቅተዋል፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር መስፍን በፈረንጅ ቋንቋ ሶስት አራት ‹‹ጆርናል›› ጽፈው የሚኮፈሱ ምሁራንን የሚያስከነዱ ቁጥራቸው በርከት ያሉ መጻሕፍትን ለኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቋንቋ የሚጽፉ ሰው ናቸው፡፡ በዚህ ሥራቸው በእጅጉ አመሰግናቸዋለሁ፤ አደንቃቸዋለሁ፡፡
ሌሎቹ የአገራችን ፊደላውያን ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ጥቂት ‹‹ጆርናሎችን›› በተለያዩ ርዕሶች ላይ ከመጻፋቸው ውጭ ለዚያውም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጭ አንባቢም ተጠቃሚም በሌላቸው ጭብጦች ላይ በአማርኛ ቋንቋ አንዳች ነገር ሲፅፉ አይታዩም፡፡ ለዚህም ነው ምሁራን ከማለት ተቆጥቤ ፊደላውያን የምላቸው፡፡ የፊደል እንጅ የተግባር ዕውቀት ስለሌላቸው፡፡
ወደ ተነሳሁበት የፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ ልመለስ፡፡ መጽሐፉ ዋነኛ ትኩረቱ ከዚህ በፊት ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚል ያሳተሙትንና በብዙዎቹ ዘንድ የተቃውሞ አቧራ ያስነሳውን መጽሐፍ ነቀፌታዎች ለማብራራትና አንዳንድ ተችዎችንም ልክ ለማስገባት የተፃፈ ይመስላል፡፡
በመጽሐፉ ገፅ 27 ሁለተኛው አንቀፅ ላይ ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክን ስፅፍ በኢትዮጵያዊነቴ መንፈስ ተይዤ ነው፤ ይህንን መካድ አልችልም፤ ከሰማይ እንደወረደ ሰው ሆኜ ስለኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ እችላለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ታሪክ ጸሐፊ (ወይም የታሪክ ተመራማሪ) ካለ የሚናገረውን የሚያውቅ አይመስለኝም፤ ከኢትዮጵያዊ ትውልዴ፣ ከኢትዮጵያዊ አስተዳደጌና ስሜቴ፣ ከበርበሬው መፋጄትና ከቡናው ትኩስነት ራሴን ሙሉ በሙሉ አግልዬ ስለኢትዮጵያ መናገር እችላለሁ ብዬ አልዋሽም›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ በእኔ ዕይታ የዚህ ዘመን ታሪክ ፅሐፊዎችም እንደ ድሮ ግለ-ታሪክ ፀሐፊዎች (chroniclers) ሁሉ ገለልተኞች (objective) አይደሉም እያሉ ነው የሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ ከስሜታዊነት አልፀዳም፤ ታሪክ አይደለም፤ ከሽፏል፡፡
በእርግጥ መጽሐፉ እርሳቸው ስለመክሸፍ የሰጡትን ትርጓሜና የክሽፈታችን ማስረጃዎች ናቸው ያሏቸውን ሀሳቦች በጥልቀት ለማብራራት ይሞክራል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት በተለይ ዓድዋ ላይ በዓፄ ምኒልክ ዘመን ድል ያደረግነውና ዓለምን ያስደመምንበት ጣሊያን ከአርባ ዓመታት ዝግጅት በኋላ በዓፄ ኃይለስላሴ ዘመን ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933ዓ.ም ድረስ ድል አድርጎናል፤ እኛ ግን በአርባ ዓመታት ውስጥ ከመሻሻል ይልቅ ስንበሰብስ ቆይተናል ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ለፕሮፌሰር ጥያቄ ላንሳ፤ ‹‹ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ያሸነፍነው በስልጣኔና በጦር መሳሪያ በልጠነው ስለነበር ነው?›› እንደኔ አይደለም፡፡ ይህ ለፕሮፌሰር ይጠፋቸዋል ብዬ ባልጠብቅም ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› በሚል ባሳተመው መጽሐፍ ገፅ 159 ጀምሮ እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያውያን ወደ ዓድዋ ዘመቻ ሲሄዱ 42 መድፎች ብቻ ነበሯቸው፡፡ ይህ ቁጥር ከኢጣሊያ ዘመናዊ የተራራ መድፍ ጋር አይወዳደርም ሲልም ይገልፃል፡፡ በሰራዊት ቁጥር ደረጃ በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን እጅግ ብዙ ነበሩ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ በመጽሐፉ እንዳስቀመጠው የኢጣሊያ ጦር ብዛት ከ20ሺህ የማይበልጥ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ግን ንጉሠ ነገሥቱ ዓፄ ምኒልክ የመሩት ጦር ብቻ 30ሺህ እግረኛ እና 12ሺህ ፈረሰኛ ነበረው፡፡ ራስ ሚካኤል ደግሞ ስድስት ሺህ አግረኛ እና 10ሺህ ፈረሰኛ ጦር ይዘው ዘምተዋል፡፡ በአጠቃላይ በዓድዋው ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል 120ሺህ እግረኛ እና 28ሺህ ፈረሰኛ ጦር ተሰማርቷል፡፡ በሰው ደረጃ ሲቆጠር ዓድዋ ላይ 148ሺህ ሕዝብ ዘምቷል፡፡ በንፅፅር ሲታይ ለአንድ የኢጣልያ ወታደር ቢያንስ ሰባት ኢትዮጵያውያን ተመድበው ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ያኔ ኢጣሊያን ያሸነፍነው በቴክኖሎጂና በወታደራዊ ስልት በልጠን ነበር ወይ? ካልሆነ የኋለኛው ሽንፈታችን እንዴት ክሽፈት ሊሆን ይችላል? ከዕድለ-ቢስነት ውጭ!
ሁለተኛውን የኢጣሊያ ወረራ ስንመለከት ደግሞ አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል-ኒየችኮ ጽፈውት አለማየሁ አበበ ወደ አማርኛ የመለሰው ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጄመሪያው እስከ አሁኑ ዘመን›› የሚለው መጽሐፍ ላይ ከገፅ 508 ጀምሮ እንደተብራራው የኢጣልያ ጦር ብዛት ተጠባባቂውን ጨምሮ 500ሺህ ያህል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም በእርግጥ 600ሺህ ያህል የሰው ኃይል ለጦርነቱ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ኢጣሊያዎቹ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ፣ ታንክና በበርካታ የጦር አውሮፕላኖች የሚታገዙ የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ ግን ከግማሽ የማያንሱት ቆመጥ የታጠቁ ነበሩ፡፡ እንግዲህ በሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ወቅት የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችን ደረጃ ማወዳደሩን ትተን በሰው ኃይል ብቻ እንኳ ብናወዳድረው ንፅፅሩ አንድ ለአንድ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዓድዋው የአንድ ለሰባት ጥምርታ በጣም ያነሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ መሸነፍ መክሸፍ ነው ፕሮፌሰር? ሌላው ለፕሮፌሰሩ ማንሳት የምፈልገው ጥያቄ ከዓፄ ቴዎድሮስ ሽንፈትና ከዓፄ ዮሐንስ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በመጀመሪያ ግምቴን ሳስቀምጥ ፕሮፌሰር መስፍን ለዓፄ ዮሐንስ 4ኛ ያላቸው አመለካከት ግብዝነት ያለበት (stereotype) ይመስለኛል፡፡ የውጫሌ ውል እ.ኤ.አ ግንቦት 2 ቀን 1889 ቦሩ ሜዳ አጠገብ በምኒልክና በኢጣሊያ መካከል ተፈረመ፡፡ ዓፄ ምኒልክ ውሉን መፈረማቸው ስህተት መሆኑን እ.ኤ.አ መስከረም 27 ቀን 1890 የአንቀፅ 17ን የጣሊያንኛ ትርጓሜ ስህተት መሆን በመጥቀስ ለኢጣሊያ ስህተት መሆኑን በደብዳቤ ጽፈው አሳወቁ፡፡ ውሉን እንደማይቀበሉት ለአውሮፓ መንግስታት ይፋ ያደረጉት ግን አምስት ዓመታትን ዘግይተው ነበር፡፡ ከዚያ ዓፄ ምኒልክ የውጫሌ ስህተታቸውን ያረሙት ስህተቱን ከፈፀሙ ከ8 ዓመታት በኋላ አሁንም በአውሮፓውያኑ መጋቢት 01 ቀን 1896 ዓድዋ ላይ ባስመዘገቡት ድል ነበር፡፡
ነገር ግን ፕሮፌሰር መስፍን ዓፄ ዮሐንስን በመጽሐፋቸው (አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ) ገፅ 15 ላይ ሲነቅፉ ‹‹አጼ ምኒልክ በውጫሌ ውል የሠሩትን ስህተት በአድዋ ላይ አርመውታል፤ አጼ ዮሐንስ ግን ከእንግሊዞች ጋር ባደረጉት ውል የተሠራውን ስህተት ማረም አልቻሉም፡፡›› ይላሉ፡፡ አሁንም ጥያቄን ላንሳ፤ ዓፄ ዮሐንስ ከእንግሊዝ ጋር እ.ኤ.አ በሰኔ 03 ቀን 1884 ዓድዋ ላይ የተፈራረሙትን ውል ስህተት ለማረም እንደ ምኒልክ 8 ዓመት ነበራቸው ወይ? ሌላው ጥያቄ ደግሞ እንግሊዞች ቴዎድሮስን ለመውጋትና ዜጎቻቸውን ለማስፈታት ወደ መቅደላ ሲመጡ የተባበሯቸው ብቸኛ የቴዎድሮስ ጠላት ተደርገው በፕሮፌሰሩ የቀረቡት በዝብዝ ካሳ (በኋላ ዮሐንስ 4ኛ) ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ ዋግሹም ጎበዜን (በኋላ ተክለ ጊዮርጊስ) ረስተዋቸው ነው? ቀደም ሲል አለማየሁ አበበ ወደ አማርኛ መልሶታል ባልኩት የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ገፅ 282 ላይ እንደተገለፀው እንግሊዞች ወደ መቅደላ ሲገሰግሱ ዋግሹም ጎበዜ 60ሺህ ወታደሮች በስራቸው ነበሩ፡፡ ነገር ግን በእንግሊዞች ላይ ኮሽታ አላሰሙም፤ ለዚህ ውለታቸውም የወቅቱን መዲና መቅደላን በስጦታነት አግኝተዋል፡፡ ታዲያ ፕሮፌሰሩ ስለዓፄ ዮሐንስ 4ኛ ግብዝነት የጀቦነው ጥላቻ ባይኖርባቸው ኖሮ ስለምን እንግሊዞችን የደገፉ ብቼኛ ተጠያቂ ያደርጓቸዋል?
“አዳፍኔ፣ፍርሃትና መክሸፍ›› እርስ በእርስ የሚቃረኑ ሀሳቦችም አሉበት፡፡ ለምሳሌ በመጽሐፉ ገፅ 63 የመጨረሻው አንቀፅ ላይ ‹‹ትምህርት የአዳፍኔ ፀር ነው፤ ስለዚህም አዳፍኔም የትምህርት ፀር ነው›› ይላሉ፡፡ ገፅ 68 መካከለኛው አንቀፅ ላይ ሲደርሱ ደግሞ ‹‹በአጠቃላይ አዳፍኔ ባለበት የትምህርት መሣሪያነት በመጀመሪያ ለአዳፍኔ፣ ቀጥሎም ለቤተ ሃይማኖት ነው፤›› ይላሉ፡፡ መጀመሪያ ነገር አዳፍኔ ለትምህርት፣ ትምህርትም ለአዳፍኔ ፀር ከሆኑ አንዱ ለአንዱ እንዴት መሳሪያ ሊሆን ይችላል? አንዱ ለአንዱ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው እኮ በሁለቱ መካከል የለበጣም ቢሆን ፍቅር ሲኖር ነው? ፕሮፌሰር መስፍን ሲቀጥሉ በገፅ 114 ላይ ‹‹ወደጥሩው ለውጥ የሚወስደውን አቅጣጫ ለመያዝ የማያስችለው ጋሬጣ አዳፍኔ ነው፤ የአዳፍኔ ዋናው ሥራ ጤንነት፣ ዕውቀት፣ ትብብር፣ ብልፅግና፣ ማኅበራዊ ጥንካሬ እንዳይፈጠሩና ሕዝቡ ወይም ሕብረተሰቡ ደካማና ተስፋ ቢስ ሆኖ በቀላሉ ለመገዛት የሚመች እንዲሆን ነው›› ይላሉ፡፡ ለእኔ በገባኝ ልክ ፕሮፌሰሩ ‹‹አዳፍኔ›› የሚሉት ስርዓተ-መንግስቱን ወይም ገዥውን አካል ይመስለኛል፡፡ አሁን ወንዝ በበራፉ ዓመቱን ሙሉ የሚያልፍበት ሰው በንፅህና ጉድለት በሚመጣ በሽታ ቢጠቃ ስለምን አዳፍኔ ተጠያቂ ይሆናል? ወንዝ ዳር እየኖረ ጳጉሜን ጠብቆ የሚታጠብ ሰው ቢኖር ንፅህናውን አለመጠበቁ የግለሰቡ ድክመት እንጅ ‹‹የአዳፍኔ›› እጅ ነው ለማለት ምክንያት የለኝም፡፡ ለብዙዎቻችን እኮ ተንኮልና መጠፋፋትን የሚያስተምሩን ወላጆቻችን ናቸው፡፡ መሪዎችም እንደኛው ሰለሆኑ ወላጆች አሏቸው፤ የወላጆቻቸው የአስተዳደግ ውጤትም ናቸው፡፡ የብዙዎቻችን ወላጆች እኮ የሚመክሩን ‹‹ከጠላትህ ሳይሆን ከወዳጅህ ተጠንቀቅ›› ብለው ነው፡፡ ፀሎታችንም ‹‹አንተ ከወዳጄ ጠብቀኝ፤ ጠላቶቼን እኔ ነቅቼ እጠብቃለሁ›› የሚል ነው፡፡
በአገራችን ያሉ የተለያዩ የፈውስ መድኃኒቶችን የሚያውቁ የባሕል ሐኪሞች በብዛት ነበሩን፡፡ ነገር ግን እነዚህ አዋቂዎች በዕድሜ በጣም ሲገፉ ለአንድ በጣም ለሚወዱት ልጅ ከሚነግሩት በቀር ለማንም ቀርቶ ለሁሉም ልጆቻቸው መድኃኒቱን አያሳዩም፡፡ ይህ ዓይነት ግላዊ የተተበተበ የምቀኝነት አባዜ ባሕል በሆነበት ህብረተሰብ ውስጥ ያደገ አዳፍኔ ያልሆነ መሪም ሆነ ስርዓት እንዴት ሊገኝ እንደሚችል ፕሮፌሰሩ የጠቆሙት ነገር የለም፡፡ በእኔ እምነት ከማኅበራዊ ችግሮቻችን ተኮትኩተው የሚያድጉ ችግሮቻችንን ፖለቲካዊ ያደረጓቸው ይመስለኛል፡፡ አዳፍኔ ሕዝብን ተስፋ ቢስ ቢያደርግ ኖሮ ስለምን በደርግ የጭፍጨፋ ዘመን ሕዝቡ ተስፋ ቆርጦ ፀጥ ረጭ ብሎ አልተገዛም፡፡ እንዲያውም ሕዝብ እንደሕዝብም ተስፋ አይቆርጥም የሚል አቋም አለኝ፤ ተስፋ መቁረጥ የሚመነጨው ከአዕምሮ ስለሆነና የወል የሆነ ሕዝባዊ አዕምሮ ስለሌለ፡፡ አዕምሮ ያለው በግለሰብ ደረጃ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ የሚቆርጠውም ተስፋ የሚያደርገውም ግለሰብ ነው፡፡
ሌላው ፕሮፌሰር መስፍን ስለታሪካችን ሲፅፉ በገፅ 117 ላይ ‹‹ማርቲን በርናል የተባለ ሊቅ የተማርነውን ሁሉ ገለበጠው፤ የሴም ቋንቋዎች ከኢትዮጵያ ወደ ባሕር ማዶ ተሻገሩ እንጅ ከዚያ ወደዚህ አልመጡም አለ›› ይሉና ‹‹ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ የበርናልን ፈር ተከትሎ የኢትዮጵያን ታሪክ ተከትሎ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመከለስ የሞከረ አንድም ባለሙያ መኖሩን አልሰማሁም፤ የታሪክ ተመራማሪ የሚባሉ ግን አሉ›› ሲሉ ይደመድማሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት በርናል ጥናቱ የፈጄበት 10 ዓመት ነው፡፡ አስፈላጊና ትክክለኛ ሆኖ ካገኙት የሚያስኬድም ከመሰላቸው ስለምን እርሳቸው ሳይሞክሩት 27 ዓመታትን አሳለፉ? የታሪክ ተመራማሪ ከሚባሉት ውስጥ አርሳቸው የሉበት ይሆን ይሆን?
በነገራችን ላይ የፕሮፌሰር መስፍን አዳፍኔ የአርትኦት ችግሮችም አሉበት፡፡ መጽሐፉ በጥድፊያ የታተመ ይመስላል፡፡ በጥድፊያ አርትኦት ሳይሰራለት ለመታተሙ የሚያሳብቁ በርካታ የፊደል ግድፈቶች አሉበት፡፡ የፊደል ግድፈቶቹን እንተዋቸውና ያልተሟሉ መረጃዎችን እንኳ ለማሟላት ፕሮፌሰሩ ትዕግስት አልነበራቸውም፡፡ ለአብነት በገፅ 129 ላይ ሰንጠረጅ 2 (በሰንጠረጅ 1 ላይ የተመሠረተ) ተብሎ ዓመተ ምህረትና ክፍለ ሀገር (ጠቅላይ ግዛት) የተፃፈበት ነገር ግን ‹‹በሰንጠረጅ 1 ያለው የአርበኞች ስርጭት በመቶኛ›› ተብሎ ባዶ ሰንጠረዥ ታትሟል፡፡ መቼም ይህ ስህተት ለሕትመት ከመቻኮል ካልመነጨ በቀር አይከሰትም፡፡ ወይም ደግሞ ፕሮፌሰሩ ‹‹ከእኔ በላይ ላሳር›› ብለው ለማንም አርታኢ አላሳዩትም ማለት ነው፡፡ ምናልባት እንደርሳቸው በዓፄው ዘመን የተማሩ አርታኢዎች አጥተው ይሆን? እነማዕረጉ በዛብህ የእርሳቸው ዘመን ተማሪዎች አይሆኑ ይሆን?
ወደ መጨረሻ ማንሳት የምፈልገው ነጥብ ደግሞ ፕሮፌሰሩ ‹‹ከእኔ በላይ አዋቂ የለም›› ባይና ዘላፊ መሆናቸውን በመጽሐፉ ማንፀባረቃቸውን ነው፡፡ በመጽሐፋቸው ገፅ 73 ላይ ፕሮፌሰር ባሕሩን እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አንድ አስተማሪ ያስታጠቀውን ጉዳይ ይዞ አንድ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡›› በተለይ በ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› መጽሐፍ ላይ አስተያዬት የሰነዘሩ ሰዎችማ የስድብ ናዳ ወርዶባቸዋል፤ ዳግመኛ ለሂስ ብዕራቸውን የሚያነሱም ሆነ አንደበታቸውን የሚከፍቱ አይመስልም፡፡ ብርሃኑ ደቦጭ የተባለውን ተች ‹‹እንግሊዝኛን በአማርኛ ፊደል መጻፍ የሚችል መሆኑን አወቅሁለት›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ እርሳቸው ታምራት ነገራን ሲወርፉ ከገፅ 214 ጀምሮ ‹‹ፓራግራፍ›› እያሉ እንደጻፉት የሚጽፍ ለማለት ፈልገው ይመስለኛል፡፡
ዳንኤል ክብረት በፕሮፌሰር መስፍን ከገፅ 222 ጀምሮ እንደወፍጮ በተደጋጋሚ የተወቀረ ተች ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ‹‹ያውቃል እንዲባል የሚፅፍ እንጅ አውቆ የሚጽፍ አይመስልም›› በሚል ውረፋ የጀመሩት ፕሮፌሰር ‹‹የዩኒቨርሲቲን ዓለም የማያውቁ ሰዎች ሌላ ትርጉም በመስጠት እንዳይሳሳቱ ማስጠንቀቅ ያስፈልጋል፣ በአካል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆነው ልባቸው ከደብተራ ተንኮል ላልፀዳም ቀናውን የእውነት መንገድ እንዲያመለክታቸው እመኛለሁ›› ሲሉም አስከተሉ፡፡ ‹‹ይህ ሰው አንብቤአለሁ ሲል በመሀይም ድፍረት ነው›› የሚል ውረፋም ተመርቆለታል፡፡ የዳንኤል ክብረት የዲቁና ማዕረግም በፕሮፌሰር መስፍን ስልጣን ተገፍፏል፡፡ ምክንያት ያሉት ደግሞ ‹‹እኔ እንደማውቀው ዲያቆን ሶስት ደረጃዎች ሲኖሩት የዲያቆኖች አለቃ ሊቀ ዲያቆናት ይባላል፤ አቶ ዳንኤል ሊቀ ዲያቆናትም አልሆነም፤ የአቶ ዳንኤል ዲያቆንነት የቱ ዘንድ እንደሚወድቅና ምን ማለትም እንደሆነ አላውቅም›› ይላሉ፡፡ ዲያቆንነት ሶስት ደረጃዎች ካሉት ዳንኤል ክብረት ሊቀ ዲያቆን ካልሆነ ቀሪዎቹን ሁለት ደረጃዎች ሊሆን እንዳማይችል ግን ፕሮፌሰር መስፍን ግልፅ አላደረጉትም፡፡ በነገራችን ላይ ዳንኤል ብቻ ሳይሆን የዳንኤል ደጋፊዎች የተባሉትም በአዳፍኔ ስድብ ተዳፍነዋል፡፡
የአንተ አሽከር፣ የአንተ ቡችላ፤ ኩፍ ኩፍ ይላል እንደጉሽ ጠላ!
የሚል ስንኝም ተቋጥሮላቸዋል፡፡ ብቻ በአዳፍኔ ብዙ የተዳፈኑ ነገሮችንም አንብቤያለሁ፡፡ ፕሮፌሰሩ እንዲህ ተሳዳቢ መሆናቸውን አላውቅም ነበር፡፡ ከደርግም ሆነ ከኢህአዴግ አባላትም ሆነ ደጋፊዎች አንድም ምሁር ሰው አለመኖሩንም ፕሮፌሰሩ በልበ-ሙሉነት ያስረዳሉ፡፡ ምሁራኑ በአዳፍኔ ተዳፍነዋል፤ አዳፍኔና ዕውቀት ተፃራሪ ናቸውና፡፡ ሁለት ትልልቅ ትምህርቶችንም በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ ውስጥ አግኝቻለሁ፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስናን ማስቀረት ከባድ መሆኑን፤ ገፁንና ቃላቱን አንድ ባንድ ባላስታውሰውም ‹‹ኢትዮጵያውያን ፈጣሪያቸውን ጭምር በሙስና ውስጥ ለመክተት ስለት የሚሳሉ ሰዎች ናቸው›› ያሉትን የፕሮፌሰር ሀሳብ በጣም ወድጄዋለሁ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተራደሁት ነገር ቢኖር ሰዎችን አንድ ባንድ እያነሱ በመሳደብ መጽሐፍ ማሳተም እንደሚቻል ነው፡፡ ሶስተኛ ቁም ነገር ልጨምር ካልኩ ምሁር ለመባል ወይ በንጉሱ ዘመን መማር አሊያ በፕሮፌሰር መስፍን ጽሁፎች ላይ እንደነማዕረጉ በዛብህና ማስረሻ ማሞ የፕሮፌሰሩን ሀሳብ ደጋፊ አስተያዬት ብቻ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ የዳንኤል ክብረት፣ የኢህአዴግና የደርግ ምሁራን እጣ ፋንታ ገጥሞህ ከ8ኛ ክፍል አላለፈም ትባላለህ፡፡
በመጨረሻም በእርግጥ ይህንን በማለቴ ፕሮፌሰር መስፍን እንደ ዳንኤል ክብረት በስድብ ናዳ መቀመቅ ሊያወርዱኝ ይችላሉ፤ እንደምንም የተማርኳቸውን ሁለት ዲግሪዎችም ወደ ሁለተኛ ክፍል ሊያወርዷቸው ይችላሉ፤ ለነገሩ ከመጀመሪያውም የዚህን ዘመን ተማሪዎች ዕውቅና አልሰጡንም፤ ማን ያውቃል የአዳፍኔ ማዳፈኛ ብለው ሌላ የስድብ መጽሐፍ እንዲጽፉም መነሻ ልሆናቸው እችል ይሆናል፤ ምናልባት ፌስቡክ ላይ እንደኔ አይጣዱ እንደሆነ ደግሞ ላያነቡትና ምንም ላይቀየሙኝም ይችላሉ፡፡ የመጨረሻው ምኞቴ በሆነልኝ እንዳልል ‹‹ይኸው ፈራህ፤ ከሽፈሀል!›› ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የፈለጉትን ይበሉ፡፡