Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የወያኔ ገመና ሸፋኝ…የኢትዮጵያ ደመኛ ጨቋኝ…መለስ ዜናዊ ሁለት ባህሪያት።

$
0
0

Melesኦባማ ኬኒያ በመግባት ከኬኒያው ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ግንኙነት የኬኒያ ፕሬዝዳንት ያሳዩት በራስ መተማመን ብቃት ኬኒያዊያኑን አልፎ እኛንም ጎረቤት አገራት አኩርቶናል። ይህንን ኩራትና ደስታ ባየንበት በቀናት ልዩነት ባራክ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ  ሲመጣ ከኩራት ይልቅ ውርደት ከክብር ይልቅ ሃፍረት ለብሰናል። የዚህ ግዜ ነው ምነው መልስ ዜናዊ በሆነ ያልኩት። መልስ ዜናዊ በውጪ አቋሙ ጥሩ ከሚባሉት ተርታ ነው። ባራክ ኦባማን መልስ ቢቀበለው ኖሮ የተሻለ አቀባበል ሊያደርግላቸው እንደሚችል እሙን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም መለስ ዜናዊን በውጪ አቋሙ ሳይሆን በውስጥ አቋሙ ነው ያልተቀበለው። መልስ ኢህአዴግ የሚባል መረብ ሲዘረጋ በውስጣዊ ተንኮል የተተበተበ፣ በክፋት የተሳሰረ፣ መሙስና የረካከሰ፣ በድድብና የበለጻጸገ አድርጎ  ነው። ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት በህይወት እስካለ  ድረስ መለስ ቢመራቸው ቢያንስ ማንነታቸው  እንደዚህ በተዝረከረከ መልኩ አደባባይ ወጥቶ  ፀሃይ አይሞቅም ነበረ። መለስ ለኢህአዴግ ገመናቸው፣ ክብራቸው፣ ንጉሳቸው ነበረ። ለዚህም ነው ከፍ አድርገው የሰቀሉት። የመለስ አለመኖር እንኳን በአገር ማስተዳደር ሂደት ውስጥ ይቅርና እንግዳ በመቀበል የፈጠረውን ክፍተት ቁልጭ ብሎ የአለም ህዝብ ያየው አሳፋሪ ክንውን ነው። ኢህአዴግ ውስጥ እንደዚህ አይነት ክፍተት ሊመጣ የቻለው ከምን የተነሳ ነው? በጥቂቱ እንይ

መልስ ዜናዊ ሁለት አይነት ባህሪ አለው። ውጪአዊ እና ውስጣዊ። ውጪአዊ እና ውስጣዊ ሁለት አይነት ናቸው። የመጀመሪያው ለውጪ መንግስታት ወይም ህዝብ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለው አመለካከት። ሁለተኛው ደግሞ በአፋዊ ወይም ለእይታ የሚናገረው እና በውስጥ የሚያስበው ወይም የሚሰራው ክንውኖች ናቸው።

ለውጪ መንግስት ወይም ህዝብ የሚያሳየው ክብር ለየት ያለ ነው። ንግግሩም በጣም የተለሳለሰ ነው። በውጪው ማንነቱ አይተውት ጥሩ ግምት የሚሰጡት አሉ። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ኢትዮጵያ ኬኒያ  እና ሱዳን ሊገነቡት ላሰቡት ትልቁን የነዳጅ ማጣሪያ መሰረት ለመጣል በሄደበት ግዜ የሱዳንን እና የኬኒያ ህዝቦችን እጁን እያውለበለበ በቅርብ ሰላምታ ይሰጣቸው ነበረ ይሄንን ሰላምታ ግን ኢትዮጵያ  ውስጥ አንድም ቀን አድርጎት አያውቅም። በምረቃው ወቅት የውጪ ማንነቱ የውጪ ዜጎችን ያስደሰተ  ቢሆንም ውስጣዊ ማንነቱ ግን ኢትዮጵያዊያንን ያናደደ ነበረ። አገርን እመራለው የሚል መሪ የአገሩን ባንድራ ገልብጦ ይዞ ከአቻው አጎራባች አገር መሪዎች እኩል ተሰልፎ መታየቱ ህዝባችንን ያሳዘነ ጉዳይ ነው። ይህ ጉዳይ ያጋጣሚ ጉዳይ አይደለም ምክንያቱም አንድ የአገር መሪ በዙሪያው ብዙ አይኖች ስላሉት መለስ ሳያየው ነው ቢባል በዙሪያው ያሉት አላዩም ማለት ግን አይቻልም ይህ የሚያሳየው ለውጪ አገር ያለው ክብር እና ቅርበት ምን ያህል እንደሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ያለውን ጥላቻ እና ንቀት ምን እንደሚመስል ያንጸባረቀበት ነው። በተለይ እንደ መለስ አይነት ጠንቃቃ ሰው ያለ ምክንያት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማውን ዘቅዝቆ ያዘው ለማለት አይቻልም።

ሰላም መጣ፣ ዲሞክራሲ መጣ፣ ነጻነት መጣ፣ እኩልነት መጣ፣ የሚለው ቃል የውስጥ ተንኮሎች ሊሰሩበት ሽፋን የሆነ ተግባር ላይ ያልዋለ የማስመሰያ ቃላቶች እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ክልሎች በራሳቸው ሰው ይመሩ በሚልም ሽፋን ወደ ስልጣን የሚመጣው ባለስልጣን እንዲሁም ሌሎች በሚንስትር ደረጃ የተሰየሙት ሁሉ ሁለት ነገሮችን የሰሩ ናቸው ወይም ከሁለት አንዱ ያደረጉ ናቸው። እነርሱም ሙስና  እና የእውቀት ማነስ። ከኢህአዲግ ባለስልጣን ጥቂት የተማሩ ቢኖሩም እንኳን ሙስና ውስጥ ያልገባ  ግን ማግኘት አይቻልም። የግል ማህደራቸው የሚያሳየውም ይሄንኑ ነው። ወደዚህ የዘቀጠ ተግባር ወይም የጥፋት ስራ ባለስልጣኑ በሙሉ ወደው ነው የገቡት ወይስ ተገደው የሚለውን ለማየት ሌላ ጥናትና ትንታኔ ይፈልጋል ለአሁኑ ወደዚህ ጉዳይ ውስጥ አልገባም ነገር ግን ሁሉም ባለስልጣን የዚህ በሽታ ተጠቂ ያደረጋቸው መለስ ዜናዊ እንደሆነ ግን ይታወቃል።

የውስጥ ማንነት የሚባለውም ይሄ ነው። እንደዚህ አይነቱ መረብ በጣም ከባድ እና አጣብቂኝ ነው። ወደዚህ መረብ ውስጥ የገባ ሰው በሙሉ ወደደም ጠለም አድርግ የተባለውን ያደርጋል አታድርግ የተባለውን አያደርግም ምክንያቱም ሌላ አማራጭ ስለሌለው። ሙስና የሰራ በአገሪቱ ህግ መሰረት ከፍተኛ ቅጣት ያስቀጣል። ከአገርም ውጪ በአለም ህግ መሰረት ሙስና የሰራ እና የሰው ነፍስ ያጠፋ ወደ ሁለተኛ አገር ሄዶ መደበቅ አይችልም። የሄደበት አገር አሳልፎ ይሰጠዋል። ቢሰወር እንኳን በኢንተርፖል ታድኖ ይያዝና ይመለሳል። ባለስልጣኖች በሙሉ በተለያየ እና በድብቅ ወይም ባልተረዱት  መንገድ ወይም ልማት በሚል ሽፋን ወደሙስና እንዲገቡ ወይም ሙስናውን እንዲፈጽሙ ከተደረጉ በኋላ ድብቅ እቅዱን በግልጽ ይነገራቸዋል። ከዚህ በኋላ እንደ ባሪያ ማገልገል እንጂ የፈለጉትን ማድረግ  የማይችሉ ተደርገው ይቀረጻሉ። መለስ ከሚላቸው ውጪ ማሰብም ወይም መናገርም የማይችሉት ለዚህ ነው። መለስ በፓርላማው ውስጥ ከሳቀ የማያስቅ ቢሆን እንኳን ሁሉም ይስቃሉ ምንድነው የሚያስቃችሁ ተብለው ቢጠየቁ መለስ ስቋል እኮ ብለው የሚመልሱም አይነት የመስለኛል። ለዚህ ነው አሁን ያሉት ባለስልጣናት በሙሉ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ ውሳኔ ሰጪ ያልሆኑት። በእንደዚህ ብቃት በሌላቸው እና ወሳኝ ባልሆኑ ሰዎች አገር መመራት አደገኛ ነው። ምክንያቱም የሰሩትን ስራ ከህዝብ የሚያሸሽ ወንጀል ስለሆነ ሽሽታቸውን በብቃት መወጣት ስለማይችሉ ህዝብን በመጉዳት፣ አገርን በማፍረስ፣ ስራ ውስጥ ይገባሉ። የዚህ ሁላ መሰረት ጥቂት ሰዎች እንደሆኑ ይታወቃሉ። ጥቂቱን በማጋለጥ አገርን ከሙስና የጸዳ እና ብቃት ያላቸው ዜጎች ወደ ስልጣን ማምጣቱ የሁላችንም ትግል ወሳኝ ነው። ያኔ እውነተኛ፣ አገርን ወዳድ፣ ህዝብን አክባሪ እና አስከባሪ ባለስልጣኖች ይኖሩናል።

የኦባም አቀባበል ግዜ የታየውን የተዝረከረከ የውስጥ ማንነታቸው ሚንስትሮችም ሆኑ የወያኔ ካድሬዎች ወይም ደጋፊዎች መለስ ቢኖር ኖሮ  ብለው የተቆጩበት ብሎም በጥልቅ ያሰቡበት ሰዓት ነበረ። ምክንያቱም ገመናቸው በሙሉ የተሸፈነው በአንድ ሰው ነበረና። ወያኔ ውስጥ ትልቅ ችግር የፈጠረው የድርጅቱ ድብቅ አላማ እና የድርጅቱ የአቀራረጽ ሁኔታ ነው። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ሰዓት ጀምሮ  አብሮ ታግለው የመጡትን አሉ የተባሉ ታጋዮችን ኃየሎም አርኣያን ጨምሮ ሰላሳ ስድስት ሺ (36.000)ንጽኋን ታጋዮችን በተቀረጸው ህግ ያልተስማሙ ስለነበሩ በቀጭን ትእዛዝ እንዲገደሉ ተደርጓል። በአሁኑ ሰአት ያሉት ባለስልጣን በሙሉ ሊወጡ በማይችሉበት መረብ ተተብትበው ተቀርጸው የተቀመጡ እና የእውቀት ብስለትም ሆነ በራስ መተማመን የጎደላቸው ናቸው። አሁን ላለው የእርስ በእርስ ያለመተማመን በወስጣቸው መንገስ፣ እርስ በራሳቸው መጠላለፍ፣ በውስጣቸው መደማመጥ መጥፋቱ፣ መሪና ተመሪ ማን እንደሆነ አለማወቃቸው፣ እርስ በራሳቸው አለመተማመን  በማህከላቸው መንገስ፣ በማይቀረፍ መልኩ በወያኔ ውስጥ ሊኖር የቻለው ድርጅቱ ሲቀረጽ ሰዎችን ጥያቄ እንዳያነሱ እና ተሸማቀው እንዲኖሩ የሚያደርግ አሳሪ ህግ ተሰርቶለት ስለሆነ ነው። ወደ ስልጣን ወንበር ሲመጡ ታስረው እንደመግባት ማለት ነው። አሳሪውም ደግሞ አንድ ሰው ነው። መለስ ዜናዊ ያሰረውን የጥልፍልፎሽ የሞት ቋጠሮ መፍታት የሚችሉበት አቅሙ ስለሌላቸው እርስ በራሳቸው የጎንዮሽ እየተያዩ  ከሞትንም አብረን እንሙት ከኖርንም አብረን እንኑር በሚል ህሳቤ ያለብቃታቸው አገር እያተራመሱ እነሱም እየተተራመሱ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት የኢህአዴግን ባለስልጣን እያስጨነቀ እና እያተራመሰ  ያለው ሁኔታ ስርዓቱ አብቅቶለት ስለመውደቁ አይደለም የውድቀታቸው ቀን እንደሚመጣ ጠንቅቀው ያውቁታል። ኢህአዴግ የተያያዘው መፍጨርጨር የሰሩት ከፍተኛ ወንጀሎች በዝርዝር ስለሚቀርብባቸው ይህ እንዳይገለጽባቸው ስልጣን ላይ መቆየታቸው ብቸኛው አማራጫቸው ስለሆነ ነው። ከዚህ የተነሳ  እርስ ባራሳቸው እየተተራመሱ አገርን እያተራመሱ ያለ ሙያቸው እና ያለ አቅማቸው ትላልቅ ቦታዎችን ይዘው የህልውናቸው ጉዳይ በመሆኑ የመጨረሻ አቅማቸውን እየተጠቀሙ ያሉት። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ  አቅጣጫ ስርዓቱን የሚከዱ በዝተዋል። ከመለስ ሞት በፊት ስርዓቱን የሚከዱ አንድ ወይም ሁለት ሰው ነበረ። ከመለስ ሞታ  በኃላ በብዛት ሆነው ስርዓቱን መክዳት ተጀመረ  ሌላው ቀርቶ ተዋጊ ሄሊኮፕተር ጭምር ይዘው እስከመሰወር ተደርሷል። ከጥቂት ግዜ በኋላ ደግሞ ሙሉ ወለጋ ስርዓቱን ከዱ፣ ሙሉ ጎጃም ስርዓቱን ከዱ፣ ሙሉ ጎንደር ስርዓቱን ከዱ፣ ሙሉ ጅማ ስርዓቱን ከዱ፣ ሙሉ ሸዋ፣ሐረር፣ሐዋሳ …. ለወያኔ  አልገዛም በማለት ወያኔዎችን ከሞተው ስርዓታቸው ጋር ከውስጣቸው በማስወጣት እራሳቸውን ነጻ አድርገዋል የሚለው ግዜ  ይመጣል። ይሄ እንደሚመጣ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ከፍተኛ ጭንቅ ላይ ናቸው። በዚህ ሰዓትና ግዜ  ከወያኔ የሚተላለፈውን ሃሳብ ማንም መስማት አይገባውም። ከህዝቡ ነጥቃችሁት የበላችሁትን፡ ከናተ ተነጥቆ ለህዝቡ የሚደርስበት ስራ እየተሰራ ነው። ህዝቡን አደህይታቹ እራሳችሁን በሃብት ወንበር ላይ የተቀመጣችሁ የወያኔ ተላላኪዎች ህዝቡን ወደተሻለ ሃብት እና ወደ ሚፈልገው ሰላም ለመመለስ በኢትዮጵያ ልጆች እየተሰራ  ነው። ግዜው ሳይረፍድ ተፀፅቶ የተመለሰ ማንም ባለስልጣን ቢሆን ንስሃውን የማይቀበል ማንም ኢትዮጵያዊ የለም። ህዝባችን ይቅርታ አድራጊ ነውና ። ከነበደል መሞት ግን ሁለተኛ ሞት ነው።

ከተማ ዋቅጅራ

08.09.2015

Email- waqjirak@yahoo.com

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>