15.08.2015 /ሲወዘርላንድ – ዙሪክ/
ምዕርፍ ሁለት ….
እንደ መግቢያ በር – እንዴት ናችሁ የኔዎቹ? ደህና ናችሁ ወይ? የአንድ ሃሳብ ዕድሜ ዘላቂነት ሆነ ታላቅነት መለኪያው ዬተግባሩ ሥነ -ምግባሩ ብቻ ነው። አቅጣጫ ቢሱን፤ መደምደሚያ ቢሱን፤ ማለቂያ – አልቦውን እስከ ትብትባዊ ዝክትንትሉ፤ እንዲሁም በብዙ ቋሳ የዘለበውን ችግር – እስከ ጉስቁሉ ጥንዙል ተስፋችን፣ እንደአለ በሙሉ ፈቃደኝነት፤ ለዛውም ከነገመናው ለመሸከም መፍቀድ ብቻ ሳይሆን፤ መፍትሄ አመንጭነቱንም መሬት ያሳያዝ፤ በተጨማሪም ኃላፊነት የሚሰማውን ጥንቁቅ ብልሃትን የሰጠን፤ አቤቱታችነን በተጠያቂነት – ያዳመጠ፤ በነጠፈ ሌማት የራህብ መና ላዘጋጀልን፤ በምድረበዳ የጥማት ማርኪያ የምንጭ ውሃ ያፈለቅልን ፈጣሪ አምላካችን ልዑል እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን – አሜን!
እንዲህ ሆኖ ነበር። ያን ክፉ ዘመን ይቋቋሙ ዘንድ ቤተ – እስራኤላውያን አምላካችን ያዘጋጀላቸው የሚገዛ አለቃ አልነበረም የነብያትን መሪነት ነበር መርቆ የሰጣቸው። እኛስ በእግዚአብሄር መንበር ፊት እንደ እስራላውያን አምሳል አይደለንም? ፈጣሪ አምላክ – አያዳላም። በፈጣሪያችን ዘንድ ዕንባችን እኩልነት አለው። ከሰማዩ ችሎቱ ፊት – ለፊት ለመቆም ሙሉ ዕውቅና – አለው። በዛ የሱራፌል ዙፋን አቤቱታው ለመደመጥ ሙሉ አቅም አለው።
ያለንበትን የረረበት ዘመን ፈጣሪያችን – ያውቃል። ጽናታችን ሊፈትን ነው። ከመከራው በስተጀርባ ትልቅ ክብር አለና። ይህ ዘመን …… ሽምግልና የታሰረበት – ዘመን! መፍትሄ የተገነዘበት – ዘመን። ዬእርቅ ጥያቄ የተወገረበትና የተቀጠቀጠበት ጠቀራማ ዘመን ነው። የሃይማኖት አቨው እንደ አልባሌ እቃ የተወረወሩበት – የተንዘገዘጉበት – ከትቢያ በታች የታዩበት ዘመነ፤ ዘመነ – ጉግ ማንጉግ … ዘመነ – ሲዖል፤ ዘመነ – ረመጥ —-
የኔዎቹ – ወገኖቼ። ምዕራፍ አንድ የምዕራፍ ሁለት ዋዜማ ነውና …. ማወራረስ እንዲቻል ምዕረፍ አንድን የከወንቡበት ፍሬ ነገር እንዲህ ይል ነበር።
„በማህሌት ደጋፊነት በትጋት ማዕለተ – ተሌሊት ሰዓታት የቆሙት የ24 ዓመታት ዬቅዱሳን የዕንባ ሱባኤ፣ ጻድቅ የዕንባ ዘጉባኤ፤ …. መልክ ያዘ። ዘመነ – ሱባኤው በድል – ይሰክናል። ተግባርን የሚረታው በእኩል የተግባር ወቄት ቢሆንም ፈቃዱም ታትሞበታል።የኔዎቹ – የማከብራችሁ ዛሬም ውስጤ የሚሰማውን ላጋራችሁ ነውና፤ በተመቻችሁ ሁኔታ ትምረምሩት ዘንድ በትህታና ገልጬ …. መብቱም ፈቃዱም የውዶቼ ነውና የቤት ሥራውን ለእናንተው ለውዶቼ – ልተዎው።
እርግጥ ነው ቅዱሳን አባቶቼ የሐገሬ ዬአንድምታ ሊቀ ሊቃውንታት ትርጓሜውን ሆነ ሚስጢሩን መፍታት ሰማያዊ ጸጋ ባለቤቶች ናቸውና ይህን ለደጋግ አቨው ለአባቶቼ ትቼ ፤ እኔ ሳይገባኝና ሳልመቸው ግን ውስጤ አስጨንቆ ያስገደደኝን እገልጸው ዘንድ የፈቀደልኝ ጌታ አምላኬን – አመሰግነዋለሁ፤ እኔ ትቢያዋና ደካማዋ የሥላሴ ባርያ ንባቡን ብቻ አንዲህ ልሂድበት። ሸበላ የመደማመጥ ጊዜ ተመኘሁ – ለክብሮቼ – ለጹሑፌ ታዳሚዎች።
በቃሉ።
„እግዚአብሄርም፣ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፣ – ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፣ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከዬአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር ከአለቆቻቸው ከዬአባቶቻቸው ቤት „አሥራ ሁለት በትሮች“ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ሥም በዬበትሩ ላይ ፃፍ፤ „አንድ በትርም ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ ይሆናልና፤“ „በሌዌ በትር“ ላይ ያሮንን ስም ፃፈ። እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት „በመገናኛ ድንኳን“ ውስጥ „በምስክሩ ፊት አኑራቸው።“ እንዲህም ይሆናል። „የመረጥኩት ሰው በትር ታቈጥቈጣለች።“ በእናንተም ላይ „የሚያጕረመርምባችሁን“ የእስራልን ልጆች „ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።“ ሙሴም ለእስራል ልጆች ተናገራቸው፤ አለቆቻቸው ሁሉ አሥራ ሁለት በትሮች እያንዳንዱም አለቃ በዬአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች። ሙሴም በትሮቹን በእግዚአብሄር ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው። እንዲህም ሆነ „በነጋው“ ሙሴም ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ። እነሆም „ለሌዊ ቤት“ የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፤ ለመለመችም፤ አበባም አወጣች፣ የበሰለ ለወዝም አፈራች። ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከእግዚአብሄር ፊት ወደ እስራል ልጆች አወጣቸው፤ „እነርሱም አዩ፤“ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ“ ኦሪት ዘኊልቍ ምዕራፍ 17 ቁጥር 1 እስከ 9“
እንደ – ቃሉ!
- „በመገናኛ ድንኳን“ ሥህነ – ቤዛ በባዕቱ ሆኖ የነፃነት ፍላጎቱ ስኬታማ – አልሆነም። ፈቃዱ አልነበረምና። ምልክት ግን ታይቷል፤ ምልክት ነውና። ተሰዶም በተሟላ ኑሮ መንፈሱ መጠለያ – አላገኘም። ከእሱ የቀደሙም ወገኖቹ በቦታው – ተገኝተውበታል። /ሳይንቲስቱም ሆነ ፕሮፌሰሩም/ ሳይቀሩ ግን ያ መንፈስ ባልተሰበ ሁኔታ መቋረጥ – ገጥሞታል። ፈጣሪ አምላካችን የሚጠብቀው ልዩ ማዕዶት ነበረው። የተመረጠ ዬቀን አገልግል ነበር። እንሆ ሌላ ሚስጢር እግዚአብሄር – ገለጠ። እግዚአብሄር የፈቀደለትና የመረቀለት „በድንኳኑ ቤት“ ብቻ ሆኖ ራዕዩን ማነጋገር እንዲችል – ነበር። ለዚህም እንዲህም ሆነ — ድንኳኑን እንደ አምላኩ ፈቃዱ መረጠ – ድንኳኗ ስንት ሰማያዊ ገድል የተቀዳበት የቀዩ ባህር ክፍለ አካል ጋር በተአምር – ተወዳጀ። በድንኳኑ ትንቢት – ተተከለ፤ ሊጸድቅ። …. የተለያዩ እትብታዊ ልጆቹ መገናኛ! ነገም ብሩኽ ነው። በቃሉ ስለቃሉ ለቃሉ – አትጠራጠሩ! መገናኛ ዘመን – መጣ። ዬስጋትን አንጥሽት ውሃውን የሚያፈሰው መዳህኒዓለም ነውና።
- „በምስክሩ ፊት አኑራቸው።“ የኢትዮጵያ ህዝብና የኤርትራም ህዝብ ለዳኝነት የተሰጠው ክህሎት ብቃቱን – ይገልጣል፤ እነሆ ብዙዎቹ ቃሉን – ፈቀዱት ጥጋቸው አደረጉት። ወደዱት፤ አከበሩት። ከበከቡት፤ተከተሉት = በፍቅር ሞሸሩትም።
- „የመረጥኩት ሰው በትር ታቈጥቈጣለች።“ ይሄው በዬደቂቃው የመንፈስ ለውጥ አብዬት ላይ – እንገኛለን። የብዙዎች ውስጥ ታጠበ – ንጹህ ህሊናን አበራከተ። የተመረጠችው ቅድሰት በትረ በሁሉም መስክ በዬደቂቃው ማቆጥቆጥ ጀመራለች እና … ከእኛ ይልቅ ብላቴናዎቹ ቀድመውን አዳመጡ – ከልብ ሆነው። ታቦሩ ላይ ሊያበራ! ዓለምም አዳመጠ – በማስተዋል ሆኖ፤ አደብ ግዙ! ፍለጋው የነፃነት ነው በማለት በዓለሙ መሪ አንደበት ተከፍቶ ማህተም – ታታመ። መንገዱ ዬነፃነት ቅኔ ነው ተብሎ ዕውቅና አገኘ። እግዚአብሄር ሲመርጥ መግቢያውንም መውጫውንም በር በቅድስና ከፍቶ ነውና።- … መንገዱ ዬቀና ነው ….. ተስፋ በዜማ ይዘምር … ራዕይ ማህሌት ይቁም፤ ናፍቆትም በሰዓታት ፈጣሪውን ያመስግን፤ ፍቅርም ድዋ ይያዝ …. የኔዎቹ – አትጣራጠሩ ስለክብሩ መገለጥ አመስግኑ እንጂ …
- „አሥራ ሁለት በትሮች“ ከ80 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ቤተ ነገዶችን ያመልክታል …. ሁሉንም በእኩልነት መርምሯል አምላካችን። የመረጠውን ሥጦታ በመረጠበት አምላካዊ ሚዛኑ እንሆ – ቀብቶታል። ፈጣሪያችን ከሁሉ በላይ ንጡህ ልቦናን፤ መንፈሱ ቤተመቅደሱ ሊሆን የሚችለውን እንደ ትእዛዙ የፈቀደውን ቅን አልቆ በሰማያዊ ሥነ ጥበቡ ይመርጣልና ….. እንሆ በፈጣሪ ቃል በፈተና የነጠረው ወርቅ ያበራል – ያነጋል …. መርሁ እግዚአብሄርም ለእኔ ተውሉኝ ብሎታል። የኔ ነው ብሎታል፤ ከዬነገዶቹ አልተቆጠረም ለማዕከላዊ እርስተ መንፈሱ ብቻ የታጨ ስለሆነ። ለታላቅ ተልዕኮ – ለኢትዮጵያዊነት!
- „የሚያጕረመርምባችሁን“ ከቃልህ በመራቃችን ብቻ ማስተዋሉን አዘገዬነው እንጂ አዎን! ነጠል ብለው ተለይተው ወጠተው ወገኖቻችን ሲያጉረመርሙ – አይተናል። እነሱም የእኛ ናቸውና ምህረትህ ጎብኝቷቸው የቃልህን ድምጽ ያደምጡ ዘንድ አንተ – ፍቀድላቸው። ለንሥኃም አብቃቸው። ዕዝነ ልቦናቸውን በምርቃት – ክፈትላቸው። እኛም የቂም በቀል ደጀን አንዳንሆን ልቦናችን አቤቱ! – ጥረግልን። የጨለመውን ሥነ -ልቦናችን አንጋልን። አቤቱ! በቃችሁም በለን።
- „ለሌዊ ቤት“ ከቤተ ነገዶች ለእረኝነት የተመረጠው አንዱ ቤተ – መዳፍ ብቻ መሆኑን – ይሄው አዬን፤ በድረጊት ሲከበር ተመለከትን፤ ፈቃደ እግዚአብሄር ነውና አብሮነት በአኃቲነት ዕርገት አደረገ። በዚህ መሥመርም የቆሸሸ ስብዕና ያልታዬበትን ንጡህ መንፈስ ቤቱ አደረገ – ፈጣሪው ….. መረቆታልና እረኛውን፤ ስኬት መንገዱ ይሆናል፤ ለእኛ ብቻ አይደልም እንሆ አፍሪካም …. ምስብክህ …. አፍሪካኒዝምን – ያልቃል። የቆዬ ሰው ይይው። እንደተመኘነው – ይሆናል። ጧፉ ይበራል በእማዋይሽ – አፍሪካ። – ያበራል – ይመራል – ተስፋችን – ይሠራል።
- „ ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።“ ጕርምርታው ጽንስ ጎልቶ የወጣው፤- – የተነሳው በአዋጅ ተናጋሪዎች በመለከት ቤተሰቦች ላይ – ነበር። ሳሎኑም መኝታ ቤቱም ኮሪደሩም ከማህል አስከ ጠርዙ እነዛው አውታራዊ ዘርፎች ነበሩ። በአንድም በሌላም መንገድ። ህውክቱ ሰላምን ጠጥቶ ችግሩ ፍቺ አግኝቶ ካለ ይግባኝ በአሸናፊነት የሰከነውም በዕወጃው ቤተ መንበር ላይ – ነበር። ጉርምርምታውን በግነት በለው እያለ – „አዲስ ድምጽ“ ጀመረው፤ ከዛው ላይም ምህረት ወርዶ እንደ ንሥኃ አበበ እያለ ደግሞ እንሆ – አዳመጥን። ተመስገን አንተ የሰማይና የምድር ንጉሥ አልን። የጉዞውን መልካም ምኞትም ተከታዩ ቀላጤ – ብራና ላይ ተነበበ፤ አሁንም የሁሉን ጌታ አንተን – አመሰገን። ሁሉንም የምሥራች አዳመጥን – ሐሴትም አደረግን።
እንዲሁም በልዕልት ሀገራችን በኢትዮጵያ ፈቃደ እግዚአብሄር ታምሩን ይገልጥ ዘንድ ከሹክሽክታ ወጥቶ የተመረጠችው በትር ታቆጠቆጥ – ታንቆጠቁጥም ዘንድ የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ዬተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን አነሳስቶ ለምክንያት በምድሯ ወስዶ በምድሯ ጥልቅ ታምሩን – ገለጠ። እኛ ግን ከፈጣሪ ገድለ ረቂቅ ምርቃት ውጪ ነበርን። በዕወጃ ጉባኤ በኢትዮጵያ መሬት ከሁሉ የቀደመው ጥያቄ የታወከው ጀውጃዋ መንፈስን አዝሎ ሊያዝል ፀላዬ ሰናይ ሲነሳ ከዛው ላይ በሽንፈት – ከነሸንኮፉ በዓለም አዳባይ – ከሰመ – ምኞት መቃበር ሲሰምጥ – አስተዋልንበት።
የፈጣሪ ጥበብ እንዲህ ነው። ከተወረወረ ቀስት እንድን ዘንድ ቃሉ አናገረ …. ቃሉ አሸናፊ ሆነ። ቃሉ ገዢ መሬቱን ተቆጣጠረ …. ቃሉ ነገን አናገረ …. ተመስገን!
ታመርህ ምንኛ ድንቅ ነው። እረኛው አምላክ ወደ ጠራው የሱባኤ ድንኳን የተጓዘው ሰሞናቱም ይሄው የታምራትህ መገለጫ ወቅታት ነበሩ፤ የዓለሙ መሪም እረኛው ደልቶት ከሚኖርበት ቦታ ተነስተው እረኛው ባዕቱን በግፍ ወደ ተቀማበት እትብቱ ከተቀበረበት ቦታ – ተገኙ። ረቂቅ ታምሩ እንዲህ ነው። የታላቋ ሐገር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዬኢትዮጵያዊነት ቤተሰብነታቸውን በልበ ሙሉነት – አረጋገጡ። በእምቤት ኢትዮጵያ … ትንግርት ተመሳጠረ፤ ገድል በቅኔ – ተቀዳ። …. እያንዳንዷ ቀንና ጉዞ በሚስጢር የተቃኘች የቅኔ ቤተኛ ሆነች። የሆነው ሁሉ ለምክንያት ነበር። ስለ ተከደነውን ሲሳይ ስለ ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ ዘለግ ብለን በአርምሞና በተደሞ እንድናስተውል – ሆነልን። ስለሆነም ጥበቃው የላይኛው ነውና በቅቶ ግን ተከድኖ የኖረው ቀለም የሥርዬት መንገድ እንሆ። ይቻላል በሚያስችለው አምላክ። የድህነት ትልም ነው። የፍውሰት መርኽ ነው። መርኹ ደማችን እንሆ – ሆነ።
አሁንም ሰላምንና ፍቅርን – ይሰብካል። „ግራ ቀኙ የኔ ናቸው አለ“ ለዚህ ያበቃን አምላክ ክብር ምስጋና ለእሱ ይሁን። ስጋት ያለባችሁ ወገኖቼ አቶ እገሌ፤ ጄኒራል እግሌ፤ የውቅያኖስ ያህል ብራናው በቀለም ቢለቀለቅ ከዚህ ከጸደቀው ታዕምር ጋር መቀባትን የማጉበጥ አቅም – የለውም። ህውከት ፈጣሪ ወጀቦች ማረፊያ ብትን አፈር – የላቸውም። ይባናሉ። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት በደጅ ጥናት ነው የሚገኘው። የሸፈተው ልብ ሁሉ የሚመለሰብት ጊዜ ነው ወደ ውበቱ። ኑ እዩ ኢትዮጵያዊነት ሲያበራ! በብርሃኑ መንገድ ሁኑበት። በውስጣችሁ በክብር ኑሩበት! አንድዬን – እመኑ! ድሉ ለተመረጠው እረኛ እሱ አዶናይ – ሰጥቶታል። ይህን ትብትብ እጅግም ውስብስብ ፈተናዎችን ለመሸከም የመከራ ዘመን ለመታደግ፤ ይህን የውርዴት ዘመን ይፍታህ ለማለት መመረጥም – ነብይነት ነው። ሐዋርያነት ነው። ሰማዕትነት ነው። ሃገሬ መከራዋ ብዙ ነው፤ ግን ቁልፍ አለኝ ብሏል – አማኑኤል። የተመረጠው ቀኑን ቀን ማድረግ የሚችለው በተሰጠው የፈጣሪ ምርቃት ብቻ ነው። አቅሙ ከሰማዬ ሰማይት ነው የሚቀዳው። ከገሃዱ ዓለም ሳይሆን ከመንፈሳዊው ቅዱስ አለም። እሱም እራሱ ሱባኤ ይያዝ – ሥጦታውን ያክብር። ፈጣሪውን ተንበርክኮ ያመስግን። መጠነ ሰፊውን ፍቅር ይሰነብትለት ዘንድ – አምላኩን – ይማጠን። ፈጣሪው መንገዱን ጠርጎለታልና …. የተሰጠውን በረከቱን አብዝቶ ይጠንቀቅለት። ከምድር ሃብታት ሁሉ እጅግ የላቀ ነውና የዕንባ መዳህኒትነት – በፍቅራዊነት (Loveism) ሲሞሸር።
- „ለሌዊ ቤት“ ቤተ መዳፍ ተመረጠ። ይህ ቃለ ምህዳን የሆነው የቤተ – መዳፍ በትር አቈጠቈጠች፤ ለመለመችም፤ አበባም አወጣች፣ የበሰለ ለወዝም አፈራች ይላል ቃሉ።። ጥርጣሬን የሚፈውሰው የመዳህኒት ቃል ነው። ሥጋትን የሚበትነውም እሱ ቃሉ ነው። መሻሪያው ቃሉ ነው። ልሳናችን ሳይሆን ልባችን ለፈጠረው ፈጣሪ – ከሰጠነው። ቢያንስ ለመዳህኒተ – ዓለም ቃለ ወንጌል መንፈሳችን ካላሸፈትናው። እባካችሁን! በፈጣሪ ሥጦታ አትቅኑ! የድርሻችሁን የተገባችሁን በልካችሁ ሰጥቷችኋል ፈጣሪያችን። – ፈቃዱን አትተላለፉ ….. የኔዎቹ ውዶቼ።
- „በነጋው“ ወገኖቼ አስተውለን እንዬው ይህን ቃል። በቃሉ መሃከል ጠባቂ ዘቦች አሉ። ጠበቂ ዘቦች ‚በ‘ እና ው‘ ናቸው። በመሃላቸው ያለው ኃይለ በትረ ሥም „ነጋ“ ነው። ተልዕኮውም ጉምን ገፎ – ምህረትን፣ ልዩነትን እረትቶ እርቅን፤ ጥላቻን ንዶ – ስምምነትን፤ ቂምን ሸኝቶ – ሥርዬትን፤ ጨላማን ገፎ የትውልድን ተስፋ ማብራት አዎን ሊያነጋ ….. ነው፤ ፍቅርን አውጆ ተስፋን – ሊያሰብል። በዚያ ወቅት አሸናፊው ቃሉ ብቻ ነው። ድሉ የባለቃሉ የህዝብ ልጅ ነው። „በ ሆነ ው“ አብረውት የተጓዙት ምርጦቹ ናቸው። እነሱም የተመረጡ ዮሴፎች – ናቸው። ጠባቂዎቹን ሳይቀር መርጦለታል። ሥህን – ቤዛን የእኔ ነው ብሎታልና ለአደራ ይበቁ ዘንድ በፀሎት – ይትጉ። የረገጣት መሬት ሁሉ ብሩክ ናት። የተጠጋት ትልም ለምለም ናት። የጀመራት ተከታይ ፍጻሜም አላት።
- „ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከእግዚአብሄር ፊት ወደ እስራል ልጆች አወጣቸው፤“ ሁሉም የተሰጠውን የተፈቀደለትን ብቻ ይከውን ነው ቃሉ የሚለው። ድርሻ አለን ሁላችንም። የድርሻችን ደንበሩን የወሰነው የሰማዩ ዳኛ አምላከችን ብቻ ነው። ይህ ሰው ሰራሽ – አይደለም። ምድባችን ሰማያዊ ነውና። በዬተመደብንበት አቅማችን ለጥሪያችን – እናውል።
- „እነርሱም አዩ፤“ አዎን! አቤቱ አምላኬ ሆይ! እኔም ባሪያህ እነሆ በአንተ ፈቃድ ዓይኖቼ ከበፊቱ በበለጠ ጉልላታማና ብቁ አድማጭ ሆነው ቦግ ብለው – ተገለጡ፤ ለዐይኔ ውሃዎች ለጠረናቸው ሆነ ለጥራታቸው በድርጊት የተባን ተስፋን – ሸልምካቸው። አቤቱ ጌታዬ ሆይ! – አመስግንሃለሁ። አባ ቅንዬንም ይምራሽ ብለህ ከነ መክሊቱ ስልፈቀድክልኝ አቤቱ – ሰገድኩልህ። የኢትዮጵያዊነትን መዳኛ እግዚአብሄር ሰጥቶኛል። አምላኬንም ክብሬን ስለሰጠኝ ደግሜ – እንሆ አመስግናለሁ። ፍለሰቲትን ሆነ ተከታትዬም ፆመ ጽጌንም ሥጦታውን – አክበርበታለሁ። ለዛሬም ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም የተመረጠው „ባለ ቅብዕ በትር“ ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ ሌላ መዳህኒት እኔ አልጠብቅም። ሥህነ ቤዛን ዘመንና አምላኬ ሰጥተውኛል እና። ተስፋዬን ከ24 የህልም ጉዞ በኋላ – በዕውን አግኝቻለሁ። „ጊዜ ገቢረ ለእግዚአበሄር“ እንሆ አሁን ሆነ። አዎን ሆነ። ይቻላል ሆነ። ማድረግን ሆነ። ነፃነት የራባቸው አንስት እህቶቼም በተሰጣቸው ድርሻ ብቻ – ይትጉ! ተግተውም ጥላ ከለላ ሆነው – ይርዱት! ወንድማቸውን – ይገዙትም። አባታቸውን አለንልህ ይበሉት። አማንያን ተግተው በፀሎት አጥር ይጠብቁት ዘንድ በትህትና እኔ ሎሌያቸው ዝቅ ብዬ አሳስባለሁ። እግዚአብሄር ይመስገን። አቤቱ መዳህኒታችን የተሰደዱ መንፈሶችን ሁሉ ዬቃልህ ሚስጢር፤ የፈቃድህ ትንግረት ጉልበት አለውና – ይሰብሰብልን። አሜን!
- „አንድ በትርም ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ ይሆናልና፤“ ሥህነ – ቤዛ የቃለ እግዚአብሄር ሥጦታ ነው። ሁሉም ነገር እስከ ዛሬ የሆነው ለምክንያት ነበር። „ስለምን ቅንጅት ተመረጠው ህዝቡን መልሰው እንግባ አንግባ ብለው ጠዬቁ ወዘተ… ፤“ እንደ ትልቅ ወንጀል ዛሬ ድረስ እንደ አዲስ የሚነሳሱ ነገሮ አሉ ነው። የመርኽ ጉዳዮች ነበሩ። በጠጨማሪም ያ ፈቃደ እግዚብሔር ምልክቱን ለማሳየት ብቻ ያመሳጠረበት ሂደት ነበር። የቀደመውን የመንገድ ጠራጊውንም የፍላጎት እትብትንም በማስተዋል እዩት። የፍቅር ሚዛኑ – የተቀባይነት ልኩ – የፈተና ተቀባይነት አቅሙን – በዬትኛው በትር ላይ እንደሆነ ሚስጢሩን ይገልጥበት ዘንድ የሆነ ነው። እርግጥ አይደለም ያን ጊዜ አሁንም ጥቂቶችች ሊያሰተውሉት – አልፈቀዱም። ልባቸውን – ስለቆለፉት። ክብር „ከእኔ“ ይጀምር፤ ተቀባይነትም በእኔ ይጽደቅ የሚለውን መታበይ ተሸናፊ ማድረግ – ስላልቻሉ። እሩቅ ከማሰብ፤ የማይቻልን ከመተለም በፊት ከግንባር ካለው መጀመር ብልህነት ነው። እሱም ራስን ማሸነፍ። ሁሉም ለምክንያት ነበር፤ አፍላነቱን በምልሰት ጉልምስናውን በተደሞ ሁሉ ለመልካም ነበር።
- ሌላም ሚስጥር ተቀና። የዓለሙ መሪ በቅኔ ዘጉባኤ ቅኔውን ዘረፉልን የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የዚያን የቅኔው ንጉሥ የብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ትንቢት ተቃኙት፤ ጋሼ ጸጋዬ እኮ ነብይ ነበር። ለዚህም ነው ለእኔ ህይወት አባቴ እጬጌዬ – የሆነው። የቅዱሱና የሰማዕቱ አባት የአቡነ ጴጥሮስ „ምድሪቱ ለፋሽስት አንዳትገዛ ግዝት“ ሰማዕትነት ጉባኤም በሰሞናቱ ነበር በሃምሌ 22 ቀን ነበር። አሁንም ድህነትን መሬታችን ጠይቃለች! የጸሐፊ ምስብዕከ ወርቁ „ዴርቶ ጋዳ” ራዕያዊ ጥበብ፤ የቅኔው ዕንቡጥ ዬቴዲ አፍሮ „ፍቅር ያሸንፋል” አንዲህ ቀስተ ዳመና ላይ በክብር – ሰከነ። ተባረከልን። የቀስተዳመና ፓርቲ መሥራች መርኹ ትንቢቱን እንዲህ – አገናኛው። የመክሊት መገናኛ። የቅኔ ትንቢት መዳረሻ። “Here is the land where the first harmony in the rainbow was born. We walk on the bed rock of our planet’s first continent. Here is the root of the Genesis of Life; the human family was first planted here by the evolutionary hand of Time….We walk on the footprints of the evolutionary ancestors of Man.”
ይሄ ነው ቃሉ። በቀስተዳመናችን ሥር የፈጣሪያችን ፍላጎት ስለመሆኑ – እናዳምጥ። አቅማችን – ፍላጎታችን – ሰብስበን ለብሄራዊ ነፃነታችን – እናውል። የሐገሬ ልጆች ስጋትን – ወርውሩት። የፈጣሪ ቃል ሁሉንም የማሸነፍ አቅም – አለው። የአምላካችን ምርቃት ሁሉንም መርታት – ይችላል። የፈርዖን ልብ በፈጣሪ ቃል አልተገራንም? ኢትዮጵያ ሁልጊዜም መንበር ናት – የዕምነት ንጥህና – ቅድስና ሀገር! ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተመረጠ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ ሐገር ናት። ለሁላችሁም አቅም ላላችሁ ሙሁር ሊቅ ልጆቿ – ትበቃለች። ብዙ ብዙ መጠነ ሰፊ አቅምን የሚጠይቁ ክፍት ቦታዎች አሉ። ቅንነትን እንዳ እዬብ ከታጠቃችሁ – የብሩኽ ዕውቀት ባለድርሻ ወገኖቼ።
ስንት ነገር አዬን – ሙሉ ተስፋ ሰንቀን ኢዲህቅን – አማራጩንም – ህበረቱንም – ቅንጅቱንም – አንድነቱንም – መድረኩንም – በዬቤት ቤታቸው የተደራጁትንም – /ሰማያዊውንም ገና ለጋ ወጣት ነው/ አዬን፤ አዎን! ተመለከትን። አዳመጥን። ተሳተፍን። ግን ተከፍተን – ኖርን። ግን በሃዘን ተቆራምድን ኖርን። አሁን ግን ለቀኑ ቀኑ ተክሊል – ደፋለት። ቤተ መዳፍ በክፉ ቀን ቀልጦ እንዲያበራ – ተፈቀደ። ለሠርግ እኮ አልሄደም። ለሽርሽርም አይደለም። ለጉብኝትም አይደለም። እናስተውል ከልብ ሆነን ሞትን ወዶ ፈቅዶ እጅግ አጣብቂኝና አስጊ እርምጃን ነው የወሰደው። አዎን በሰከነ ብልህ እርምጃው አውሎ እረፍት አደረገ – በረዶውም ተግ አለ። ወጮፈውም ቢሆን በመጣበት – ተመለሰ። ነጕድጓዱም እግሬን አውጪኝ አለ። ነፋሻማና ሳቂተኛ፤ ባለ ሙሉ ልብ በቃሉ ውሎ ውሉን አዬን። ኪዳኑን በተግባር ቀለበት – አሰረ፤ ስለቃሉ ሙሉ ቃል ሆነ። እኛም – ተመስገን አለን።
ተስፋዬን ቀለብኩት
ይሁንልኝ ብዬ አምላኬን —- ለመንኩት፤
የልቤ እንዲሆን እንዲህ — ተማጸንኩት፤
ተስፋዬ ነውና – ተስፋዬን — ቀለብኩት
የመሆን ነውና – በውስጤ አኖርኩት
ቤዛዬ ነውና መንፈሴን – ሸለምኩት!
እርገት ይሁን አይደል – የኔዎቹ?! ለእኛ ቁርባናችን – ታቦታችን – ጸሎታችን – ስግደታችን – ሳላዳችን – የወልዮሽ የባህል ዝክረ ነገራችን – የሃይማኖት ማዕዳችን – ቤተ አምልኳችን ንግሥት ኢትዮጵያ ናት። ለነፃነት ፍላጎታችን ማደሪያ የተመረጠው ደግሞ ሥህነ – ቤዛ ነው። እሱ የአርቅ ጉባኤን ከአድማስ ወዲህና ባሻገር መሳላል – የሥርዬት መክሊት መገናኛ መርከባችን አንባችን – ነው።
በተረፈ – በአጋጣሚው ትንሽ ነገር ልከል፤ ከመሆን በላይ ሌላ የመሆን ፍሬ ነገር መጠበቅ እራስን ማተለል መሆኑን አብክሬ መግለጽ እሻለሁ። እራሱን የሸነገለ ህውከት፤ ጦሮ ንፋስን ፈቅዶ አምላካችን ያስከፋ፤ የውስጥ ሰላምን መንጠቅም እንዳለ ይገንዘብ። ለተግባር ገበሬ፤ – እራሱን ችሎ ለግለግ ብሎ ለወጣ ዬዕውነት የቀስተዳመና ዓላማ፤ ምስክርነት – ያስፈልገዋል። አለንልህ ልጆችህ፤ አለንልህ የአብነት ተማሪዎችህ፤ አይዞኽ ማለትም በልበሙሉነት – ይገባል። እግዚአብሄር ይስጥልኝም ማለት – የተገባ ነው። ልዑል እግዚአብሄር ሚስጢሩን ገልጦ ይህን ለመሰለ ለተምሳሌነት ያበቃ አምላክ ጥንካሬውን ብርታቱን፤ ጥበቃውን ይስጥልኝ – ለአርበኞቼ! ድንግልዬ ድስስ ታድርግ፤ የጎደለውንም ትሙላ – እናት!
መሸቢያ ሰንበት – ለእኔዎቹ። ውድ ዘሃበሻ ኑሩልኝ – የመንፈስ ጥሪቶቼ። ምዕራፍ ሦስት ይቀጥላል።
ማሳሰቢያ – አባቱ የእኔ ጀግና ናትናኤልሻ እሺ – እኔ ሎሌህ ነኝ። በጹሑፎቼ ሁሉ መልእክትህን እለጥፋለሁ። በራዲዮ ፕሮግራሜም በድምጽ መልእክትህን ሙሉውን – አስተላልፋለሁ። http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45527
ፈጣሪ አምላክ እኛን ስለሰጠን እናመስግን!
ወስብሃት ለእግዚአብሄር።