Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የእብዶች ስብስብ –ይገርማል ታሪኩ

$
0
0

TPLFየእብዶች ስብስብ የምለው ወድጀ አይደለም:: አገርን ያህል ነገር እመራለሁ: ኢትዮጵያውያንን ያህል ታሪካዊና ኩሩ ሕዝብ አስተዳድራለሁ ብሎ ከተቀመጠ ቡድን ውስጥ ለቁምነገር የሚፈለግ: ለጠበቃነትና ለዋስነት ሊጠራ የሚችል አንድ እንኳ ለህሊናውና ለፈጣሪው ተገዥ የሆነ ፈሪሀ እግዚአብሐር የፈጠረበት ሰው ሲጠፋ ታዲያ ምን ልበል!

እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1990 ዓ.ም ክረምት ካንድ ሰው ጋር ሆስፒታል ውስጥ ተገናኘን:: ሁለታችንም የምናስታምማቸው ሆስፒታል ውስጥ የተኙ ሰወች ነበሩን:: አንዳችን ያንዳችንን ጭንቀት የመረዳታችን ምክንያት ይመስለኛል ተግባብተን ለመጨዋወት ያበቃን::

ታማሚው ምንህ ነው? ህመሙ ምንድን ነው? ከሚለው ተነስተን ወደህይወትና ፖለቲካ ዝባዝንኬ ገባን:: ሲያዩት ቀናና ግልጽ ይመስላል:: ታሪኩን ቃል በቃል ባላስታውሰውም ጭብጡን በነገረኝ ልክ ላካፍላችሁ:: እንዲህ አለኝ

“የገጠር ልጅ ነኝ:: ትምህርት ቤት ገብቸ 12ኛ ክፍልን አጠናቅቄአለሁ:: ቤተሰቦቸ የኑሮው ሸክም የከበዳቸው ስለሆኑ ከትምህርት መልስ አንዳንዴም ከትምህርት ቤት እየቀረሁ በስራ አግዛቸው በተጨማሪም ያገኘሁትን የጉልበት ስራ  እየሰራሁ በማገኛት ጥቂት ገቢ ቢያንስ የት/ቤት ጣጣየን እሸፍን ነበር:: ስራ ለማግኘት ስል ይሁን ወይም ተፈጥሮየ ሆኖ እንጃ ብቻ ባህሪየ ጥሩ የሚባልና የሰው መውደድ ያደለኝ ነበርሁ:: ት/ቤት የምሄደው በአካባቢየ ያሉትን ወጣቶች ለመምሰል እንጅ የትምህርት ጥቅሙ ገብቶኝ አልነበረም:: ያም ሆኖ አንድም ጊዜ ሳልደግም 12ኛን ክፍል አጠናቀኩ::

ከ12ኛ ክፍል በላይ ሊያስቀጥል የሚችል ነጥብም ሆነ የኢኮኖሚ አቅም ስላልነበረኝ ስራ ፍለጋ ስባዝን ፖሊስ እንቀጥራለን የሚል ማስታወቂያ አየሁና ሄጀ ተመዘገብኩ:: የቅጥሩን ፎርማሊቲ አሟልተው ለፖሊስነት ከተመለመሉት ውስጥ አንዱ በመሆኔ የሰፈሬን አድባርም አምላኬንም አመሰገንሁ:: ስልጠናውን ከጨረስሁ በኋላ ከዚያው ከወረዳየ እንድሰራ ስለተመደብሁ ደስታየ ወሰን አልነበረውም:: በፍትህና በሰላም እጦት የሚሰቃየውን ወገኔን ልረዳ የምችልበት እድል ሳገኝ እንዴት አልደሰት!

ደስታየ ግን ብዙም አልቆየ:: ከበላይ የሚሰጠኝን ትእዛዝ ብቻ መፈጸም እንዳለብኝ ይነገረኝ ጀመር:: ለማነሳቸው ጥያቄወች የሚሰጡኝ መልሶች ስራየንና እራሴን እንድጠላ አደረገኝ:: ‘ለምን? እንዴት? የሚሉ ጥያቄወች ማንሳት ፖሊሳዊ ባህል አይደለም: አድርግ የተባልኸውን ብቻ ፈጽመህ መገኘት ነው የሚገባህ’ እየተባልሁ በግምገማ ተወጠርሁ:: ቤተሰቤ: ዘመዶቸ: ጎረቤቶቸና መላው የወረዳችን ህዝብ ከአይን ያውጣህ እንዳላሉኝ የፖሊስ ስራ ከጀመርሁ በኋላ ግን ያም ያም አይንህ ይጥፋ ይለኝ ያዘ::

የፖሊስነት ስራየን ‘ሀ’ ብየ መስራት በጀመርሁበት ጊዜ ህገወጥ መሳሪያ የያዙትን ሰወች ትጥቅ አስፈቱ የሚል መመሪያ መጣ:: ይህን ተከትሎ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ማስፈታት በሚል ሰበብ መሳሪያ ደብቋል ተብሎ የተጠረጠረን ሰው አስሬ እየገረፍሁ እንዳዋጣው ጫናው በረታብኝ:: አንድም እንጀራየን ብየ ሌላም የፖለቲካውን ተንኮል ባለመረዳት ተታልየ ህገወጥ መሳሪያ የታጠቁ ህገወጦች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩትን ሰወች የደበቁትን መሳሪያ እንዲያመጡ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቸ ጋር ተባብሬ አይሰሩ ስራ ሰራሁ::

ወገን ያለው ታሳሪ ያልደበቀውን መሳሪያ እሽ አስገባለሁ እያለ ወገኖቹ ዳር አገር ድረስ አፈላልገው መሳሪያ ገዝተው እያስረከቡ እንዲለቀቅ ሲያደረጉ ወገን ያጣና ያልቻለው ግን የሲኦልን ፍዳ በምድር ተቀበለ:: ማንም የብአዴን አባልና ደጋፊ ነኝ የሚል ሁሉ ህገወጥ መሳሪያ የያዘን እንዲጠቁም የተሰጠውን  መመሪያ ተመርኩዞ አንዳንዱ ህሊና ቢስ በትንሽ በትልቁ የተጣላውን ሰው ሳይቀር በሀሰት መሳሪያ ደብቋል በማለት እየጠቆመ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ተፈጸመ::

ፖሊስ ጣቢያወች የንጹሀን እንባና ደም የሚፈስባቸው የመከራ ካምፖች ሆኑ:: ወገን: ሀገር: እየተቀባበለ” እሪው” ብሎ ጮኸ:: የጩኸቱ መበርከት ስማችንን ያጎድፋል ብለው የሰጉ የብአዴን ባለስልጣኖች  አለ የተባለውን ችግር የሚያጠና ሰው ልከናል በማለት ሌላ ዙር የተንኮል ቀልድ ቀለዱ:: ከዞንና ከክልል የመጡት ሹመኞች የተሰጣቸው ተልእኮ እኛን የገና በግ ማድረግ ነበር::

በአንድ የሰንበት ቀን በየቀበሌው ያለው ህዝብ በየቤተክርስቲያኑ እንዲገኝና ተፈጠረ በተባለው ችግር ዙሪያ ውይይት ተደርጎ የማያዳግም መፍትሄ እንዲሰጥ ቅስቀሳ ተደረገ:: በእለቱ የወረዳው ፖሊስ አባላትም አብረን እንድንገኝ ትእዛዝ ደርሶን ስለነበር ሁላችንም ቀድመን ከስፍራው ተገኘን:: እኔ በተገኘሁበት የስብሰባ ቦታ የተገኘውን ህዝብ ሳይ ለቤት ጥበቃ እንኳ የቀረ ሰው ያለ አይመስልም ነበር:: የፖለቲካ ተዋናዩ የመንግስትን አቋምና ለህዝብ ያለውን ወገንተኝነት ካብራራ በኋላ ብአዴን የቆሰለበትና የሞተለት የዜጎች የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት መጣስ ከምንም በላይ እንደሚያሳስበው ገልጾ የደረሰባችሁን በደል አስረዱ ሲል ተሰብሳቢውን ጋበዘ:: ምን ይባላል! አንዱ በአንዱ ላይ እየተረባረበ ደረሰብን ያለውን ጉድ ይዘከዝከው ጀመር::

‘መንግስት ባለበት ሀገር እንዴት እንዲህ ያለ የውንብድና ግፍ ይፈጸምብን’ ሲሉ በስም እየጠቀሱ: በጣታቸው እየጠቆሙ እያሳዩ: ለህዝብ ተቆርቋሪ የሆነው መንግስት ሳያይና ሳይሰማ መአት አወረዱብን ያሉንን እኛን በጥርሳቸው ሊነክሱን በጥፍራቸው ሊቧጥጡን አሰፍስፈው ተነሱ:: ‘ባትደርሱልን ኖሮ አንዳችንም አንተርፍም ነበር’ ሲሉ እንባ እየተናነቃቸው ብሶታቸውን አጎረፉት::

ስብሰባው የተጠራው እኛን ለማስገምገም መሆኑን ባለማወቃችን ምንም ዝግጅት ሳናደርግ ስለመጣን እራሳችንን መከላከል የተሳነን ፍጹም ምዑታን ሆነን በጋለ ብረትምጣድ ላይ እንደተጣለ ላስቲክ ተጨራመትን:: ለመናገር አፋቸውን በደመነፍስ ያላቀቁትን ጓደኞቸን ሊናገሩት ያሰቡትን መልሰው እንዲውጡት በሀይለቃል ሲነገራቸው ስሰማ ውስጤን ድብልቅልቅ ያለ ግራ የተጋባ መንፈስ ወረረው:: ሆኖም ቃል አልወጣኝም: የምናገረው ቃል ቢኖረኝስ እንዴት አድርጌ!

ተባለ ተባለና መጨረሻ ላይ ‘ታዲያ እኒህን በህግና በህዝብ ላይ ያመጹትን ወንበዴወች ምን እናድርጋቸው ሲሉ’ ሰብሳቢው ምልአተ ህዝቡን ጠየቁ:: ማን ምን እንደሚናገር ማወቅ  አስቸጋሪ ሆነ:: ሁሉም እየጮኸ ተመጣጣኝ ነው የሚለውን ፍርድ ይሰጥ ጀመር:: ‘እድሜ ይፍታህ ይታሰሩ!  እንደገረፉን እነሱም በተራቸው 80 ይገረፉ:  ይሰቀሉ:  በጥይት ይገደሉ ——::

ቤተሰቦቸን በአይኔ ፈለኳቸው:: አባቴ አንገቱን ሰብሯል: እናቴ በድንጋጤ ጭብጥ አክላ አይኗ ፈጦ እኔን እኔን ታያለች:: ምነው ባልተወለድሁ! በመጨረሻም አስገምጋሚ ፖለቲከኛው የህዝብ ተቆርቋሪነትና ደም መላሽነት በተላበሰ መንፈስ ተሞልተው ከጩኸት ባልተናነሰ ድምጽ ‘በቃ! በቃ! ሀሳባችሁን ለግብአትነት እንጠቀምበታለን:: የተወሰደውን እርምጃ ወደፊት ትሰማላችሁ:: ማንም እንደፈለገው ህግን ተላልፎ የሰወችን የማይገሰስ መብት ሊገስ አይችልም:: ስለትብብራችሁ እናመሰግናለን: ደህና ሁኑ’  አሉና ግምገማውን አጠናቀቁ::

የተወለድሁበት ቀየ… ያሳደገኝ ህዝብ — ሁሉንም ደግሜ ላላያቸው ፊቴን ሳዞር አንዱ ከሹመኞቹ ጋር የመጣ ፖሊስ እጆቸን በሀይል ወደኋላ ጠመዘዛቸውና ካቴና አጠለቀባቸው:: ድንጋጤ: ፍርሀትና ግራ መጋባት የፈጠረብኝ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ከእኔ ጋር የተገመገሙትን ጓደኞቸን ሁኔታ እንዳላስታውስ ጋረደኝ:: ያም ሆኖ ግን ወደዞኑ ከተማ ስንጓዝ አብረውን እንዳልነበሩ አስታውሳለሁ:: ከዞኑ ዋና ከተማ ስንደርስ ‘ከእንግዲህ በኋላ በስራህ አትቀጥልም: ወደፈለክበት መሄድ ትችላለህ’ ተብየ ካቴናው ወለቀልኝ:: የኔ ነገር በዚሁ አበቃ:: እኔም ሆንኩ ህዝቡ የማንፈለግ: አንዳችን በአንዳችን እንድንጠፋ መንገዶች የሚመቻቹልን አላስፈላጊ አረሞች ነን:: አስገምጋሚወቸ ተራው እስኪደርሳቸው ድረስ የተሰጣቸውን ስራ አከናውነው ባገኙት ሙገሳ ተደስተው ረክተው ይሆናል: እኔ ግን ያለምሁት ሳይደርስ ያሰብሁት ሳይሳካ አግዘዋለሁ ብየ ያሰብሁትን ወገኔን አሰቃይቸ ከማንም ሳልሆን ከቆሰለ ህሊና ጋር ተሳዳጅ ሆንኩ” አለኝ::

ሲናገር ጸጸት ባህር አንጀቱ ገብቶ እያንሰፈሰፈው: ንዴት ቆሽቱን እያደበነው እንደሆነ አጠቃላይ ሁኔታውን ላየ ስሜቱን ከመረዳት አልፎ ይጋባበታል:: “የመንግስት የውስጥ መመሪያ” ማለትት ምን ማለት እንደሆነ ያልተረዳ ሰው ከዚህ ድርጊት ጥቂትም ቢሆን ግንዛቤ ሊጨብጥ ይችላል ብየ አስባለሁ:: ምንም አይነት የጽሁፍ ትዕዛዝ ሳይደርስህ አንድ የሚፈለግ የጥፋት ተግባር እንድትፈጽም ትታዘዛለህ:: ስለጉዳዩ ምንነት ካወቅህ በኋላ እሽም ሆነ እምቢ ብለህ አትተርፍም:: ሚስጥር ካወቅህ በኋላ ከነሚስጥርህ ማን በሰላም ይለቅሀል:: ብቻ ከንጹህ ህሊናህ ጋር መቀበር ከፈለክ የህገወጥ ድርጊት ተባባሪ ወይም ፈጻሚ አልሆንም ብለህ የነገውን ሞት ዛሬ መቀበል ነው:: እንደታምር ሆኖ ይህ ከ18 አመት በፊት ያገኘሁት ወጣት ለወሬ ነጋሪነት ተርፎ ይህን ያጫወትኋችሁን እውነት ለመተንፈስ በቃ:: እኔም ዘግይቸም ቢሆን የዚያን ወጣት የቁም ኑዛዜ ለናንተ አደረስኩ::

የወያኔ አላማ ግልጽ ነው:: አልገባን ብሎ ወይም ፈርተን እንደሆነ እንጅ ወያኔ እንደሆነ ገና ጫካ እያለ ጀምሮ በአማራው: በኦርቶዶክስ ሀይማኖትና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያለውን ጥላቻ በሰነድ አስፍሮ ‘በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቡራኬ በጉልበት በአማራው በተፈጠረችው የመቶ አመቷ ኢትዮጵያ የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ነው የምንታገለው’ እያለ ሁሉንም ለማጥፋት አልሞ ነው የመጣው::

ስለዚህ “እሾህን በእሾህ” ነው እንዲሉ ወያኔወች አንዱን አማራ በሌላው አማራ እያጠፉ: እነርሱ ከደሙ ንጹህ ነን እያሉ በነርሱ ምጡቅ ዐዕምሮ ተኩራርተው በሌሎች ጅልነት ተሳልቀው ቀጥለዋል:: ከአማራው አብራክ የተገኘን ነን የሚሉት የብአዴን ሰዎች እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ በያለበት የጥቃት ሰለባ ሲሆን ምንም ሳይቆረቁራቸው እንዲያውም የወንጀሉ ተባባሪና ፈጻሚ ሆነው ሲገኙ ምን ይባላል! ሌሎች የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶችስ ቢሆኑ የወያኔ ዱላ ሆነው ህዝባቸውን በሆነ ባልሆነው እየገረፉ እያቆሰሉት አይደለም! መቸ ነው ወደህሊናቸው ተመልሰው የህዝባቸውን ስቃይ ለማስቆም የሚሰሩት! ጅል ጅሉ እየተመረጠ ከስልጣን ላይ ወጥቶ የታዘዘውን እየፈጸመ እንዲቀጥል የሚደረገው የወያኔ ሴራ ሊከሽፍ የሚችለው ነፍስ ያወቀው ዜጋ አንገቱን ካቀና ብቻ ነው::

ወያኔወች እንደሆኑ “የላም አሸናፊ” ናቸው:: ፈርተው ቢሸሿቸውም እየተከታተሉ መውጋታቸውን አይተውም:: በተለያየ ሱስ የተለከፉ: በቂምና በጥላቻ የተበከሉ: የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ በመቻላቸው ተደስተው የሚኖሩ ከራሳቸው ውጪ ለሆነ ለማንም ለምንም ግድ የሌላቸው ወፈፌወች ናቸው:: ታዲያ እኒህን ጊዜ ከስልጣን ማማ ላይ ያስቀመጣቸውን የጉዶች ስብስብ ምን ብየ ልጥራው? የእብዶች ስብስብ ብል አይገልጸው ይሆን! ወገን እንንቃ!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>