ኢቲቪ ስለትህዴን መክዳት የለፈለፈው፣ አቶ ሞላ ስለ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ስለተቃዋሚዎቹ፣ የሻብያን ጦር “እየደመሰሱ” ስለመምጣት በግነት የተናገረው፣ ሌላው የትሄዴን ጊዜያዊ ሃላፊ ኮማንድር መኮንን ተስፋዬ ስለከዳው የትህዴን ጦር እና ስለውጊያው የተናገረው እና የተለያዩ ሌሎች አስተያየቶች ሰሞኑን በማህበራዊ ድህረገጾች ተለቀዋል፣ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ተወያይተውባቸዋል። እኔም ውይይቱን መልሼ መድገም አልፈልግም፥ የእኔ አላማ የአቶ ሞላ አስገዶም በተለያዩ አካላትና ሁኔታዎች መዳፍ ስር ቢወድቅ ኖሮ በጥትቅ በሚታገሉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች፣ በኢትዮጵያ መንግስትና፣ በኤርትራ መንግስት ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች በአጭሩ መዳሰስ ነው።
አቶ ሞላ በኤርትራ ትግል ሜዳ ውስጥ ቢቆይ ኖሮ
አቶ ሞላ በኤርትራ ውስጥ በትግል ላይ መቆየት፣ ለነጻነት የሚደረገውን ትግል እጅግ ረጅም እና እልህ-አስጨራሽ ያደርገው ነበር። ብዙ የሰው ህይወትና እልቂት ሊከተልም ይችላል። ትግሉም ወደኋላ ይጎተት ነበር። አቶ ሞላና አብረውት ወደኢትዮጵያ የተጓዙት በትግሉና በህብረቱ ያልተደሰቱ “አርበኞች” እነሱ እንደሚሉት ከሆነ ሰነድ በመሸጥና፣ የስለላ መረብ በመዘርጋት ለኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የውስጥ አርበኝነት ስራ መስራት በቻሉ ነበር። እነዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ባንዳዎች በሁለት ልብ ሆነው ጦርነቱን በቁርጠኝነት ሊያካሄዱ አይችሉም። ስለዚህ በህወሃት ላይ ነፍጥ ያነሱት የህብረቱ አባል ኢትዮጵያውያን በህወሃት ካሊበር ጥይት መታጨዳቸው አይቀርም ነበር። በሌላ አነጋገር አቶ ሞላ አሁን ከነበረው የስልጣና የዕዝ ሃላፊነት አንጻር እያንዳንዷን የአማጺያንን እንቅስቃሴ ለህወሃት አለቆቹ አሳልፎ መስጠቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ በተቃዋሚው ላይ የሚያደርሰውን እልቂት እድግ ከባድ ያደርገዋል። ከዚያም የኤርትራና የተቃዋሚ ሃይሎች “ከተደመሰሱ” በኋላ አቶ ሞላና ግብረ-አበሮቹ የ”ጀግኖች ጀግና” ተብለው በተወደሱ ነበር። በመሆኑም አቶ ሞላና ግብረ-አበሮቹ ከትጥቅ ትግል ሃላፊነት ገለል ማለት በነፍጥ ለሚታገሉ ተቃዋሚ ሃይሎች ከፍተኛ ድልና እፎይታ ነው። ተቃዋሚዎች አንድ ከፍተኛ የ”ወገን” ጠላት ነው የተገላገሉት! አቶ ሞላ በመሸሹ አሸናፊዎቹ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችና የኤርትራ መንግስት ናቸው።
አቶ ሞላ ኤርትራ ውስጥ ቢገደል ኖሮ!
አቶ ሞላ በሽሽት ላይ እያለ ሱዳን ሳይደርስ ቢገደል ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር? ያው እንደተለመደው የህወሃትም ይሁን አብዛኞቹ የተቃዋሚ ሃይል አባላት አቶ ሞላን የኤርትራ መንግስት እንደገደለው ማውራታቸው አይቀሬ ነበር። ይህም ኤርትራ ላይ ከፍተኛ ጥላሸት ከመቀባቱ በተጨማሪ ኤርትራ የገባ ተቃዋሚ ሁሉ እንደሞተ ለሚቆጥሩ ተቃዋሚዎችና ለህወሃት አገዛዝ ልሂቃን ከፍተኛ የዕልልታ ዜና ፍጆታ ይሆን ነበር። “ኤርትራ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እንዲጠነክሩ አትፈልግም፣ ህወሃትና ሻዕቢያ አንድ ናቸው” ለሚሉ ተቃዋሚዎችና ጥርጣሬ ውስጥ ላሉ ወገኖች የሰውየው ኤርትራ ውስጥ መገደል አስተማማኝ የመረጃ ፍጆታ ይሆን ነበር። በተለይም ለእነ አቶ ኤሊያስ ክፍሌ ዜናው አስደሳች ይሆን እንደነበር ጥርጥር የለኝም። በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ መንግስት የትህዴንን የመሰለ “ጠላት” ስለተገደለላቸው ደስታቸው ወደር አይኖረውም፥ ህወሃት ስለግድያው ኤርትራን መውቀሱ ግን አይቀርም። እናም አቶ ሞላ አስገዶም ወደ እናት ፓርቲው ህወሃት በሰላም መቀላቀሉ ለተቃዋሚው ትግል ስኬት ቀላል የማይባል ፋይዳ ይኖረዋል። አቶ ሞላ በመቶ የሚቆጠር ሃይል ይዞ ወደሱዳን ያለምንም ችግር መሄድ መቻሉ የሚያሳየው በኤርትራ ያሉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ያለምንም ገደብ የመንቀሳቀስ መብት እንደተቸራቸው ነው። የአቶ ሞላ ኤርትራ ውስጥ መገደል ለተቃዋሚዎችም፣ ለኤርትራ መንግስትም ከፍተኛ ኪሳራ ይሆን ነበር። ከዚህ አይነት ድርጊት አትራፊው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ይሆን ነበር።
አቶ ሞላን ህወሃት ኤርትራ ውስጥ ቢገለው ኖሮስ?
አቶ ሞላን የህወሃት መንግስት ቢገድለውስ ኖሮስ? ይህም ሁኔታ በትግሉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥር ነበር። በፊት አቶ አንዳርጋቸውን ከየመን ጠልፎ ያመጣ የህወሃት ቡድን፣ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ላይ ግድያ ቢፈፅም ለህወሃት ከፍተኛ ድል፣ ለተቃዋሚዎች እና ለኤርትራ መንግስት ግን አንገት የሚያስደፋ ሽንፈት ይሆን ነበር። በሉዓላዊት አገር ኤርትራ የጠላት አገር ሃይል ገብቶ ተቃዋሚ ፓርቲ ሃላፊን ከገደለ፣ ኤርትራ በደህንነት ጥበቃ ንዝህላልነት ተጠያቂ መሆኗ አይቀርም። ያ ሳይሆን ቀርቶ ህወሃት አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለተቃዋሚ ትግል ስኬት ከፍተኛ እገዛ ሊያደርግ የሚችል ስራ ሰርቷል። የአቶ ሞላ ኤርትራ ውስጥ በህወሃት ደህንነት አለመገደል ለአማጺው ሃይልና ለኤርትራ መንግስት ከፍተኛ እፎይታ ነው።
አቶ ሞላ ወደ ኢትዮጵያ ባይመለስስ?
አቶ ሞላ ሱዳን ወይም ሌላ አገር ውስጥ ጥገኝነት ቢጠይቅስ ወይም ወደሌላ አገር ተላልፎ ቢሰጥስ? ይህ ድርጊት ለህወሃት ከፍተኛ ጥቅም ይኖረው ነበር። ህወሃት ጥሩ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻም ይሰራበት ነበር። በተለይም ኤርትራ አሁን ካላት አለም አቀፋዊ ተሰሚነት አንጻር፣ ሁኔታው ለተቃዋሚዎች አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረው ነበር። አቶ ሞላም ቢሆን ከህወሃት ጋር ሳይወግን፣ ተቃዋሚ ሃይሎችንና የኤርትራ መንግስትን ማውገዝና በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችል ነበር። ሰውየው ኤርትራ ውስጥ በትግል ካሳለፈው ጊዜ አንጻር እሱ ሊናገር የሚችለው አብዛኛው ነገር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተአማኒነት ይኖረው ነበር። ያም ሆነ ይህ፣ አቶ ሞላ ይህንን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
አቶ ሞላ በተቃዋሚዎች ኤርትራ ውስጥ ቢታሰርስ/ ቢገደልስ?
አቶ ሞላ በራሱ በትህዴን ሰዎች ቢታሰር ወይም ቢገደል ኖሮ ለተቃዋሚዎቹ ለራሳቸው ጥሩ ሁኔታ አይፈጥርም ነበር። እስሩን ወይም ግድያውን የፈጸሙት ጓዶቻቸው ሳይሆኑ የሻዕቢያ መንግስት እንደፈጸመው በመገመት ዳር ላይ የቆሙ ሰዎች ብዙ ሊያወሩ ይችሉ ነበር። እንግዲህ በትጥቅ ትግል የሚያምኑ የተቃዋሚ መሪዎች የኢሳያስን መንገድ በመከተላቸው በጥርጣሬ መታየታቸው፥ በዋነኝነትም የሻቢያን ጉዳይ በማስፈጸም መታማታቸው አይቀርም። ሞላ አስገዶምና ግብረ-አበሮቻቸው በራሳቸው በትሂዴን ሰዎች በጣም ሊወደዱ የሚችሉበት፣ በውጭ የሚኖረውም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው ተቃዋሚ እንደጀግናም ሊቆጥራቸው የሚችልበትን ሁኔታ ሳይሆን ቀርቷል። የእሱ መታሰር በትጥቅ ትግሉ ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ ነበር። አቶ ሞላ አስገዶም ብቸኛ ጀግና ተደርጎም ሊቆጠር ይችል ነበር።
አቶ ሞላ ወደ ኢትዮጵያ መግባትስ?
የአቶ ሞላ ወደህወሃት ጉያ መግባት ለኢትዮጵያ መንግስትና፣ ለራሱ ለሞላ አስገዶም ከፍተኛ ኪሳራ ነው። አቶ ሞላ የዘር ካርድ በመምዘዝ እንደቀድሞ ጓዶቹ ተመልሶ ወደህወሃት አፎት ገብቷል። አሁን በአገርም በውጭም ያለ ተቃዋሚ ሁሉ አቶ ሞላ “ጓደኞቹን ጥሎ የፈረጠጠ” ከሃዲ አድርገው ያየዋል። አስራ አራት አመት ሙሉ ራሱ የመለመላቸውንና ያሰለጠናቸውን ወታደሮች በኤርትራ በረሃ በትኖ ነፍሴ አውጪኝ ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ሸሽቷል።
አቶ ሞላ ይህን አስነዋሪ ድርጊት በማድረጉ ከህዝቡ ያገኘው ንቀት እንጂ ጀግንነትና ክብር አይደለም። ክህደት የራስ ወዳድነት መገለጫ ነው። እሱ ወደ ኢትዮጵያ ሸሽቶ ገባ፣ በእሺ የሚቆጠሩ ጓዶቹስ? የሚል ጥያቄ በብዙሃን ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲብላላ ቆይቷል። እንግዲህ አቋም የሌለው ሰው በህዝብ ኪሎ በጣም ትንሽ ይመዝናል፥ ሞላም ከዚህ አላመለጠም።
የህወሃት ሃላፊዎችም የሰውየውን ወደ ኢትዮጵያ መኮብለል እንደጥሩ የፖለቲካ ትርፍ ማየታቸው የሚገርም ነው። የፖለቲካ ትርፍ የሚገኘው አማጺ የነበረን ሰው አበባ ይዞ ምንጣም አንጥፎ በመቀበል አይደለም። የፖለቲካ ትርፍ የሚኖረው ማህበራዊ ችግሮችን በመቅረፍ፣ የፖለቲካ ምሕዳር በማስፋት፣ ለዜጎች ዴሞክራሲና ነጻነት በማጎናጸፍ፣ የስልጣንና የሃብት ከፍፍል በማመጣጠንና እኩልነትን በማስፈን እንጂ፣ አንድ ያውም መሳሪያው ሱዳን ውስጥ አስረክቦ የመጣን ሽፍታ የንጉሳን አቀባበል በማድረግ አይደለም። አሁን አቶ ሞላ ምንም የፖለቲካ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም የለውም። ምናልባት የውጊያ ልምድ ሊኖረው ይችል ይሆናል፥ ለ14 አመት ግን አልተዋጋም። በመሆኑም፣ አቶ ሞላም በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ንቀት አስመዘገበ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም እንኳን የፖለቲካ ትርፍ መሳሪያ እንኳን ሳያገኝ ቀረ። የኤርትራ መንግስት አማጺያንን በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በመፍቀድ፣ ከኢትዮጵያውያን ከፍተኛ አክብሮት ተቸረ። አማጽያንም ትግሉን በተጠናከረ፣ በተዋሃደ መንገድ ጀመሩት!