ከዚህ ጽሁፍ ጋር አያይዤ የለጠፍኳቸውን የባቡር ጣቢያ ስሞች ስመለከት አዲስ አበባ ወደ መቀሌ የሄደች መስሎ ተሰማኝ። መቀሌ ብዙ ድርጅቶች ከትግርኛ ይልቅ በአማርኛ ማስታወቂያ መለጠፍ ይቀናቸዋል። መቀሌ ውስጥ አማርኛ የቢዝነስ ማስታወቂያ መጻፊያ ቋንቋ ነው። መቀሌ በአማርኛ የቢዝነስ ማስታወቂያ እንደመጻፏ መጠን ለቃላትና ለሆሄያት ግድፈት ግን ግድ የላትም። መቀሌን ለአመታት ለሚያቃት ሰው የአማርኛ ሆሄያትን በማሳከር ባለሁለት ዲጂት እድገት እያስመዘገበች ያለች ከተማ ልትመስለው ትችላለች።
ምስጉን ተስፋይ የሚባል ጎበዝ የአዲግራት ልጅ አንድ የግጥም መድበል አሳትሟል። የግጥም መድበሉን ያሳተመው በአማርኛ ነው። የምስጉንን ግጥሞች አንብቦ መረዳት የሚችል ቢኖር እንደኔ አይነት በአማርኛ አፉን የፈታ ሳይሆን የትግራዋይ አማርኛ [Tigrian Amharic ] የሚችል ሰው ብቻ ነው። ምስጉን ተስፋይ መጽሀፉን ሲጽፍ አማርኛውን በማረም ያገዘውን ወንድሙን አመስግኗል። ግን ወንድሙም ልክ እንደ ምስጉን የትግራዋይ አማርኛ ተናጋሪ በመሆኑ የተነሳ የግጥም መድበሉ የአማርኛ እርማት የተደረገለት ሳይሆን የአማርኛ መፋለስ ተደርጎለት ለመታተም የበቃ ነው የሚመስለው። ሁለቱም የትግራዋይ አማርኛ ጽሁፍ «ጸሀፊዎች» በመሆናቸው ለምስጉን ያልታየው የአማርኛ እርማት ችግር ለወንድሙ ሊታየው አይችልም።
መቀሌ ከተማ በየንግድ ተቋሙና በየአደባባዩ ከተለጠፉ የንግድ ማስታወቂያዎች መካከል ባልተሳካ አማርኛ ከተጻፉት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤«ሞቫይል ቆፎ ንሸጣለን»፤ «ካራ ቡላ ናጫወታለን»፤ «ሞቫይል ካርድ አሎ»፤ «ሞቫይል ቆፎ ንጠግናለን» «ተራንስ ፎርሜሽኑ ይሳካል» «ኤመይል ንከፍታለን»፤ «ፍስ ቡክ ናስጠቕማለን»፤ «ባለማጮሶ ንመስግንናለን»፤«ዃረንቡላ አንጫወታለን»፤«የተዘጋ ዋሃ ንሸጣለን» [የታሸገ ውሀ እንሸጣለን ለማለት ነው] ወዘተ።
መቀሌ በአማርኛ ለሚጻፉ ማስታወቂያዎች ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋም ለሚጻፉ ማስታወቂያዎች ግድ የላትም። የቢዝነስ ማስታወቂያዎችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፈው የሚለጥፉት አብዛኛውን ጊዜ የአውሮፓን የእግር ኳስ ጨዋታዎችን የሚያሳዩ የDSTV ቤቶችና ፊልም የሚያከራዩ ሙዚቃ ቤቶች ናቸው። «Prison Break» የተሰኝውን የእንግሊዝኛ ፊልም የሚያከራዩ አራት መደዳውን የተሰደሩ ሙዚቃ ቤቶች ማስታወቂያውን የሚያስቅ እንግሊዝኛና አማርኛ ቀላቅለው ጽፈውት ተመልክቻለሁ። የመጀመሪያው «ድንኳን [በትግርኛ ሱቅ ማለት ነው» ማስታወቂያውን <«prison brike» ዚህ ይገኛሉ> ብሎ ለጥፎታል። ሁለተኛው ቪዲዮ አከራይ ደግሞ <«perison braik» በዝካረ ይገኛሉ> ይላል። ሶስተኛው ቪዲዮ ቤት ሙሉ በሙሉ «የእንግሊዝኛ» ቃላትን ተጠቅሞ «price break four rent» ይላል። አራተኛው ነጋዴ ደግሞ በፋንታው <«prisim brek» ፊልም ናከራያለን> ሲል ለጥፏል።
ሌላ መቀሌ የማውቀው የንግድ ድርጅት በተለምዶ ሀውዜን አደባባይ ከሚባለው የከተማይቱ አነስተኛ አደባባይ በስተቀኝ አቅጣጫ በግምት አንድ መቶ ሜትር ያህል ገባ ብሎ በግራ በኩል «ናቲ ምሿለኪያ ካፌና ሬስቶራንት» ይሰኝ የነበረን ቤት ነው። እኔና ጓደኛዬ «ናቲ ምሿለኪያ ካፌና ሬስቶራንት» በተደጋጋሚ እየተገናኘን የቤቱን «ስፔሻል ምግብ» ተመግበናል። አዲስ አበባ ላይ «ምሿለኪያ» የሚል የባቡር መተላለፊያ ተጽፎ ሳነብ ቀጥታ ወደ ጭንቅላቴ የመጣው መቀሌ ከተማ የማቀው «የናቲ ምሿለኪያ ካፌና ሬስቶራንት» ነበር። ለዚያም ነው የጽሁፌን ርዕስ «የመቀሌ አማርኛ በአዲስ አበባ» ብዬ የሰዬምሁት።
የመቀሌን «ድድ ማስጫዎች» ተዘዋውሮ ለጎበኘ በመቀሌ ከተማ የንግድ ማስታወቂያዎችን ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ «ባነር» መለየት ይቸግረዋል። በተለይ ዋናው የህወሀት ጽህፈት ቤት አካባቢ በሚገኙ የንግድ ቤቶች ላይ የሚለጠፉ የንግድ «ማስታወቂያዎችን» ላስተዋለ ንግድ ቤቶቹ እቃና አገልግሎት መሸጣቸውን ትተው ፕሮፓጋንዳ መሸጥ የጀመሩ ነው የሚመስሉት። ሰላሳ ዘጠነኛው የህወሀት ልደት መቀሌ ከተማ ሰማህታት አዳራሽ ሲከበር ህወሀት ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ባለ አንድ ካፌ ደጅ ተቀምጠን እኔና ጓደኛዬ ሻይ ቡና እያልን ባካባቢው የሚካሄደውን እንቅስቃሴ እየታዘብን ነበር። ሻይ ቡና በምንልበት ካፌ በር ላይ «መለስ ጅግና እዩ፤ጀግና አይሞትም» ከሚል መፈክር ስር «Meles is alive» የሚል የእንግሊዝኛ ፍቺ ተሰጥቶት መፈክሩ ተሰቅሎ ነበር። ይህ መፈክር ዋናው ህወሀት ጽህፈት ቤት ውስጥም ተሰቅሎ እንደነበር ለማወቅ ችያለሁ።
በአጠቃላይ መቀሌ የተቀመጠ አንድ ለአቅመ ፖለቲካ የደረሰ ሰው ትናንትና የተለቀቁትን የአዲስ አበባ ባቡር ጣቢያ ስሞች ሆሄያት መጣመምን ሲመለከት አዲስ አይሆንም። ይልቁንም ድርጊቱ አዲስ አባባ ላይ ሊፈጸም የቻለው አንድም የባቡር ጣቢያ ስሞቹ መቀሌ ሄደው የተጻፉ መሆን አለባቸው ብሎ ሊያስብ ይችላል፤ አልያም የመቀሌን ማስታወቂያዎች የሚያትሙ ባነር ጻፎች አዲስ አበባ መጥተው የጣቢያ ስሞችን ለመጻፍ የተደረገውን ውድድር «አሸንፈው» ከመቀሌ ይዘው በመጡት የሆሄ መቅረጫ የአዲስ አበባን የባቡር ጣቢያ ስሞች ወደ ማተሙ ገብተዋል ብሎ ያስባል።
በአዲስ አበባና በመቀሌ በተፈጸሙ የሆሄያት ግድፈቶች መካከል ግን አንድ ልዩነት ይታየኛል። የመቀሌ ማስታወቂያዎች ግድፈት የአማርኛ ሆሄያት ብቻ አይደለም፤ የመቀሌ ማስታወቂያዎች ለእንግሊዝኛ ፊደሎችም ግድ የላቸው። የአዲስ አበባዎቹ ግን የአማርኛ ሆሄያቱ ስህተትም ቢሆኑ የእንግሊዝኛ ስሞች ግን በስህተት የተጻፉትን የተሳከሩ የአማርኛ ሆሄያት ተከትሎ በትክክል የተቀረጹ ናቸው። አዲስ አበባ በተሳከረ አማርኛ ተጽፈው ወደ እንግሊዝኛ ሲለወጡ ግን ወጥነት የሚባል ነገር ገደል ገብቷል። ሲያሻቸው ሙሉውን በupper case letters ሌላ ጊዜ ሲፈልጉ ደግሞ በsentence case ጽፈውታል። ይህንን መፋለስ አጸደ ህጻናት ያሉ ልጆች እንኳ አይፈጽሙትም።
በመጨረሻ ከማስታወቂያ ሆሄያቱ ግድፈት ጀርባ ስላለው እውነት አንድ ሞያዊ ቁምነገር ላክል። አንድ የመሰረተ ልማት አውታር ተሰርቶ ሲጠናቀቅ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት የጥራት ፍተሻ [ Quality Control] ይካሄድበታል። ፍተሻው የመሰረተ ልማቱ ፊዚካል ግንባታ ደረጃውንና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ መካሄዱን ብቻ ሳይሆን በየቦታው የሚሰቀሉ የአውታሩ ምልክቶችና የማስታወቂያ ሄሆያትን ትክክለኛነትም ያካትታል። በአንድ ባቡር አውታር ላይ የሚካሄድ የማስታወቂያ ሆሄያትና የምልክቶች ፍተሻ የመጨረሻው ደረጃ ፍተሻ ነው። ይህንን ደረጃ ያላለፈ አውታር የጥራት ደረጃ ፍተሻውን እንዳላለፈ ይቆጠራል። በዚህ መሰረት ትናንትና ስራ ጀመረ የተባለው የአዲስ አበባው ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የመጨረሻውን የጥራት ፍተሻ ምዘና አላለፈም ማለት እንችላለን። የመጨረሻውን የጥራት ፍተሻ ምዘና ያላለፈ አውታር ማስተካከያ ተደርጎበት ካልሆነ በስተቀር እንዳለ በቁሙ ስራ እንዲጀምር አይደረግም። ይህ ምክረ ሀሳብ የEconomics of infrastructure ሀ ሁ ነው። ትናንትና ኢትዮጵያ የሳተችው ይህንን ምክረ ሀሳብ ነው። ለነገሩ በኢትዮጵያ የሚሆን ነገር እንዳይሆን ሆኖ መደረጉ አዲስ ነገር አይደለም። በኢትዮጵያ እውቀት ከትምህርት ቤት ሳይሆን ከወያኔ ወንበር ስለሚፈልቅ መቆርቆዝና መዝቀጥ ባህላችን ከሆነ ውሎ አድሯል።
እኔን የገረመኝ ግን ከውጭ ማንም ሰው አይቶ የሚለየውን የሆሄያት ግድፈት እንኳ ተመልክቶ ማስተካከል ያልቻለ የጥራት ማረጋገጥ ምዘና፤ ውስብስብ የሆነውን፣ ጥልቅ ሞያዊ ክህሎት የሚጠይቀውን፣ ባይን የማይታየውንና ከባዱን የባቡሩን መስመር ፊዚካላዊ ጥንካሬ ጉድለት ፈትሾ የባቡር መስመሩ ግንባታ ደረጃውን መጠበቁን አለመጠበቁን እንዴት ብሎ ማረጋገጥ ይችላል? በእውነት ስራ ጀመረ የተባለው የባቡር መስመር ፕሮጀክት የጥራት ፍተሻ ተካሂዶበታልን? እንዴት ተብሎ ስንት መሀንዲሶች ባሉባት አገር ውስጥ የባቡሩ አውታር በአይን የሚታየውን የጥራት መመዘኛ [ማለት መስመር አመላካች ሆሄያት በሚገባ ያልተሟሉለት ሆኖ ሳለ] ፈተና ማለፍ ሳይችል በአይን የማይታዩ የጥራት ፍተሻዎችን እንዳለፈ ተቆጥሮ የመጨረሻውን የጥራት ደረጃ ምዘና ባላሟላ ሀዲድ ላይ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀመር ይደረጋል?
በወያኔ ዘመን ሁሉ ነገር ፖለቲካ ሆኖ እውቀት፣ጥራትና ልቀት የሚባል ነገር ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር አፈር ድሜ በላ። አውሮፓና አሜሪካ ቀርቶ የትም ሶስተኛ አለም ውስጥ የመጨረሻውን የጥራት ምዘና ደረጃ ያላሟላ የባቡር አውታር እንደኛ አገር ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ስራ እንዲጀመር አይደረግም። በእውነት የባቡሩ አውታር ላይም የተደረገ ፍተሻ በተሰቀሉ የአውታሩ ምልክቶችና የማስታወቂያ ሄሆያት ልክ ከሆነ፤ ከጣራው በላይ ዳንኪራ የተደለቀለቱ የባቡር ትራንስፖርት በቅርቡ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ሰባራ ሀዲድ ብቻ ታቅፈን እንቀራለን። ይህንን እድሜ ያለው ያያል!