በደርብ ከፈለኝ
አዋቂ መስሎኝ ሰምቼዉ
ትልቅ ሰዉ መስሎኝ ተጠግቼዉ
በቃኝ . . . በቃኝ አወቅኩትና ናቅኩት
ለካስ ወዳጄ ኖሯል ፈረስ እየናቀ አህያ የሚጋልብ
በሬ እያቀጨጨ ጅብና ድብ የሚያደልብ
ከላይ አያ ተክሌ ብዬ የጀመርኩህ ተሳስቼ ነዉ። ከአሁን በኋላ ግን አቦይ ተክሌ ብዬ ነዉ የምጠራህ። አይዞህ “አቦይ” ያልኩህ እንደ አቦይ ስብሐት አርጅተህብኝ አይደለም። አወቃለሁ አንድ ፍሬ ልጅ ነህ . . . አዎ ልጅ ነህ . . . አሁንም ልጅ! “አቦይ” ብዬ ሹመት የሰጠሁህ አነጋገርህ፤ አስተሳሰብህና እንዳዉ አኳኋንህ ሁሉ ከአቦይ ስብሐት ጋር ስለተመሳሰለብኝ ነዉ፤ ወይም እንደ አቦይ ስብሐት ቀላማጅ ነህ ትቀለማድለህ ማለቴ ነዉ። አቦይ ተክሌ ምንም ቢሆን የቅርብ ጓደኛዬ ነህና የጓደኝነቴን ምክር ቢጤ ልሰጥህ እስኪ ስማኝ። አቦይ ስብሐት ሃያ ሁለት አመት ሙሉ ቀላምደዋል፤ ከአሁን በኋላ ልቀላምድ ቢሉም አንድ ሐሙስ ነዉ የቀራቸዉ። አንተ ግን አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፤ እንግዲህ ይታይህ 35 አመት፤ 40 አመት፤ 50 አመት፤ ስልሳ አመት እያልክ ወዳጅና ጠላት፤ዘመድና ባዳ ፤ ጎረቤትና የማዶ ሰዉ ሳትለይ ይህንን ሁሉ አመት እየቀላመድክ ልትኖር ነዉ . . . ያዉም በዚህ እንደ አሞራ በሚበርረዉ የዳያስፖራ ኑሮ። ምነዉ ተክሌ ቢቀርብህ! መዶሻ የያዘ ሰዉ ሁሌም የሚመለከተዉ ሚስማር ብቻ ነዉ ሲባል ሰማሁና መዶሻ የያዘ ሰዉም መሰልከኝ፤ አሁን ግን በደንብ አድርጌ ሳይህ መዶሻ የያዘ ሰዉ ሳይሆን ጭራሽ መዶሻዉን እራሱን መሰልከኝ።
“ዬት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ታየ” . . . አያ ተክሌ . . . ይቅርታ አቦይ ተክሌ ማለቴ ነዉ . . . ይህ ስንኝ የተቋጠረዉ ለሌላ ለማንም ሳይሆን ላንተ ብቻ ይመስለኛል። እስኪ ንገረኝ ተክሌ ምነዉ የነካሄዉ ነገር ሁሉ አይበረክት ወይ አንተ አትበረክት። እስኪ መለስ ብለህ አስበዉ ECADF፤ EHSNA፤ ESAT TV ፤ ESAT Radio ሁሉንም ነካ ነካ ግን አንዱንም ሳታረካ አንተም ሳትረካ እንዳዉ ዉኃ ላይ እንደተንሳፈፈ ኩበት ባክነህ ቀረህ። ምነዉ ወንድሜ ተክሌ እንዲህ ነበር እንዴ እኔና አንተ የምንተዋቀዉ? ምን ላድርግ እንደዛ ማታ ማታ እንደምንጫወትበት ካርታ ተበዉዝክብኝኮ። ምነዉ ተክሌ የተደበቀዉ ጸባይህ እየወጣ ነዉ ወይስ ድሮ ሳዉቅህም እንዲህ ወናፍ ነበርክ? ተክሌ ከሁሉም ከሁሉም የምታናድደኝ ደርሶ አዋቂ ለመመሰል ቱግ ቱግ ስትል ነዉ፡፡ ዉድ ጓደኛዬ ተክሌ እባክህ ተረዳኝ እኔ አዋቂ አትሁን ማለቴ አይደለም፤ ግን አዋቂ ለመሆን አዋቂ ሁን እንጂ አዋቂ አትምሰል። ደግሞም ቱግ ቱግ እንኳን ባንተ በእንደኔ አይነቱ አንድ ክንድ ከስንዝር በማትሞላዉ ባንተ በሸበላዎቹም አያምርም። ስለዚሀ ተክሌ እባክህ እንዳቅምህ . . . አዎ እንዳቅምህ!
በያ ሰሞን በየድረ ገጹ እየገባሁ ያገኘሁትን ሁሉ ሳነብ አንተም የሞነጫጨርከዉን አገኘሁና አንብቤዉ በጽሁፍህ ሳይሆን በጓደኝነትህ አፈርኩ። እስኪ ንገረኝ ተክሌ ምን ይሁን ብለህ ነዉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዉን ፖለቲካ አትተንትን ያልከዉ፤ እናስ ምን ይተንትንልህ? እኮ ንገረኝ ተክሌ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ፖለቲካ ካልተነተነ ሌላ ምን ይተንትን? ለመሆኑ ያልተተነተነ ፖለቲካ ምን አይነት እስትራቴጂ ነዉ የሚወጣለት? ምነዉ ተክሌ “አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት” የምንላትን ሴትዮ ሆንክብኝ! የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሆኖ የአገሩን የፖለቲካ ሁኔታ የማይተነትንና መጻኢዉን እዉነት በስዕል ቀርጾ የማያሳየን ከሆነ ምኑን የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሆነ . . . እንደሱ አይነት የፖለቲካ ፓርቲ መሪማ ካንተ ጋር የዋለ ሰዉ ማለት ነዉ። አይዞህ ተረት ጎበዝ ነህ ብዬ ነዉ (ከአህያ ጋር የዋለች . . . ) አቦይ ተክሌ ችኩልነትህን ድሮም አዉቀዋለሁ፤ ከተናገርክ በኋላ የምታስብ ሰዉ መሆንህም ለእኔ አዲስ አይደለም፤ ግን ምነዉ ተክሌ . . . ያንተ እዉነት የሰዉ ሁሉ እዉነት ይመስልሃል እንዴ? እንደዚህማ ከሆነ እዉነት የሚባል ነገር ምድር ላይ የለም ማለት ነዉኮ! ተክሌ እባክህ በዚህ “ካፍ ከወጣ አፋፍ” በሆነበት አለም ከመናገርህና ከመጻፍህ በፊት አስብ። ፈረንጆቹ (Think twice before you speak once) ይላሉ። ተክሌ አንተ ግን የሚጽፈዉ እጀህ ደራሽ የሚናገረዉ አፍህ ነካሽ ነዉና እባክህ እንዳዉ በዚያች በምታከብራት በወላዲት አምላክ ይዤሃለሁ ከመናገርህ በፊት አምስቴ አስብ (Think five times before you speak once).
መቼም የኛ ነገር “አፍ ያለዉ ጤፍ ይቆላል” ነዉና አንድ ሰሞን ይችኑ የምትንጣጣዉን አፍህን አይተዉ ኢሳቶች ወያኔ ላይ ብትንጣጣላቸዉ ብለዉ አስጠጉህ አንተ ግን ጠላትና ወዳጅ ሳትለይ ሁሉም ላይ የምትተኩስ ጉድ ነህና ኢሳቶች ላይ እሳት ሆንክባቸዉና እሳት አደጋ ጠርተዉ በግዜ ተገላገሉህ። ተክሌ ልክ እንደ ቁመትህ ምን ያህል ትንሽ ሰዉ እንደሆንክ ያየሁት በስራ አጋጣሚ የምታዉቀዉን ነገር ሁሉ ድረ ገጽ ላይ እንዳላዋቂ ሳሚ መለቅለቅህ ነዉ። አሁን ይህ ምን ይባላል? አዋቂነት ወይስ ጅልነት? መልሱ ቀላል ነዉ፤ ተክሌ አንተ አዋቂነት የሚባል ነገር በአጠገብህ ያለፈም አይመስለኝም። ጅልን ለማወቅ ደሞ ጅል መሆን የግድ ይላልና እስኪ እዚያ የሞነጫጨርከዉ መጣጥፍ ላይ የከተብከዉን ዝባዝንኬ እንዳለ ላሳይህ
“ይሁን እንጂ፤ የኢሳት አስተዳዳር የሆነው ወዳጄ ነአምን ዘለቀ የዛሬ አመት አካባቢ እንዲህ ያለው ተመሳሳይ ስብሰባ ሲዘጋጅ፤እባክህን መሪዎቹ ንግግር ያሳጥሩና ለሰዉ እንዲተነፍስ ግዜ ይስጡት ብዬ አሳስቤው ነበር። ነአምን አንዳንዴ አይሰማም። ወይም ቢሰማም አያደምጥም” አቦይ ተክሌ
“ነአምን አንዳንዴ አይሰማም። ወይም ቢሰማም አያደምጥም” . . . ወይ ጉድ! አንተንስ ምን እንበል? . . . ተክሌ የሚባል ስም ከተሸከምክ ጀምሮ ሰምተህም አዳምጠህም የማታዉቀዉን ጆሮም አፍም የሌለህ እንግዳ ፍጥረት! ለካስ አለምክንያት መዶሻ አልተባልክም! ነአምንማ እንተም እንደመሰከርክለት አንዳንዴ ነዉ እንጂ አብዛኛዉን ግዜ ይሰማልኮ፤ እንደዚህ ብዙ ግዜ የሚሰሙ ኢትዮጵያዉያን ደግሞ ብርቅዬ ናቸዉ . . . የሉማ! እስኪ ንገረኝ ተክሌ ምንድነዉ እየነገርከን ያለኸዉ፤ አንተ ሁሉን ነገር አዋቂዉ ተናግረህ ነአምን አላዋቂዉ አለመስማቱን ነዉ ወይስ ከዚህ ሌላ የምትለን ነገር አለ? ደሞኮ ከብዙ ጉድ ያዳነን የነአምን አንዳንዴ አለመስማት ነዉ እንጂ ሰምቶህማ ቢሆን ኖሮ የዛሬዉ ትግላችን ከወያኔ ጋር መሆኑ ቀርቶ አንተ የቀደድከዉን ቀዳዳ መቋጠር ላይ ይሆን ነበር። ችግሩ ዲሲ ላይ አትቅደድ ብለዉ ሲያባርሩህ ቶሮንቶ ሄደህ ደሞ እንደገና ትቀድዳለህ . . .እስኪ ንገረን የሚቀደድ የሌለበት ዬት አገር እንስደድህ?
አቦይ ተክሌ . . . ዶ/ር ብርሐኑ በሐይማኖት ጉዳዮች ላይ የጻፉት ሰፋ ያለ ጽሁፍ አልገባህ እንደሆነ መጠየቅ አንድ ነገር ነዉ፤ አለዚያ ስምም፤ሀሳብም ጸባይም እንደምትጋራቸዉ እንደ አቦይ ስብሐት ህዝብ አንዳለ ባኮረፈበት አገር “ያኮረፉ ሰዎች እንጂ ያኮረፈ ህዝብ የለም” ብትል አባባሉ ለግዜዉ ሊያምርልህ ይችል ይሆናል፤ እመነኝ የሚሰማህ ግን አታገኝም። የዶ/ር ብርሀኑ ጽሁፍ ላይ ገጽ 16 መጨረሻና ገጽ 17 መጀመሪያ ላይ የቀረበዉ ሃሳብ ጥልቅ ወይም ሐቀኛ አይደለም ብለሃል። እስኪ ንገረኝ ተክሌ ምንድነዉ መለኪያህ? ጥልቀቱን ባንተ ስንዝር ሐቀኝነቱን ባንተ ሚዛን ነዉ የለካኸዉ? ከሆነ… አብረን ስለኖርን ዝንዝርህንም ሐቅህንም በሚገባ አዉቃለሁና አልፈርድብህም። አቦይ ተክሌ እንዳዉ ያንተ ነገር “አህያ ማር አይጥማት” ሆኖብህ ነዉ እንጂ እስኪ አሁን ምኑ ላይ ነዉ ያ ጽሁፍ ጥልቀት ያጣዉ ምኑስ ላይ ነዉ ሀቅ የጎደለዉ? አንድን ሰዉ ደደብ ነዉ ብሎ አንድ ሙሉ መጽሐፍ መጻፍ ይቻላልኮ፤ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገዉ ብዙ ጥረትም አይደለም አንድ ያንተ አይነት ጭንቅላት ይበቃል። ችግሩ የሚመጠዉ የሰዉየዉን ደደብነት ዋቢ ጠቅሶና መረጃ አስይዞ ማቅረቡ ላይ ነዉ፤ እንደዚህ አይነቱ መረጃ ደግሞ እንኳን አንተ አያገባዉ ይገባል ያልከዉ ሰዉ ላይ ቀርቶ የእርጎ ዝንብ የሆንከዉ አንተ ላይም ማቅረብ አስቸጋሪ ነዉ። አይህ ወንድሜ ተክሌ አንተም እንደዚሁ ነህ። ሰዉን “ደደብ” ለማለት አፍህ ይቀድማል መረጃ ተብለህ ስትጠየቅ የምታሳየን ግን ያንኑ የምናዉቀዉን ባዶነትህን ነዉ . . .እሱ ደግሞ ሰለቸን . . . አዎ ሰለቸን! ሰማህ ተክሌ ሰለቸን።
አቦይ ተክሌ ደሞ ብለህ ብለህ አንተም እንደ ወያኔ ምሁራን ተቃዋሚዉን ሁሉ “ሊብራል” ልትለዉ ነዉ እንዴ! መቼም አንዳንዴ ነካ ሲያደርግህ እንደ ዕብድም መሆንም ያምርሃል እንጂ በወያኔነት እንኳን በፍጹም የምትታማ ሰዉ አይደለህም፤ ግን . . . ግን ጠንቀቅ በል ልጄ ዉኃኮ ሲወስድ እያሳሳቀ ነዉ . .. እንግዲህ ይታይህ ተክሌ ባንተ መንቀዥቀዥኮ መወሰድህ ነዉ! ብሉይን በመቀበል ከዚያ ክርስትናን፤ ከዚያ እስልምናን፤ ከዚያ ካቶሊክን፤ ከዚያ ፕሮቴስታነንስዝምን፤ በመቀበልና በማቻቻል የኖረች አገር ናት ብለሀል አገራችን ኢትዮጵያን። እርግጥ ነዉ፤ ግን ለመሆኑ ብሉይ የሚባል ሐይማኖት አለ አንዴ ወይስ አንተዉ ወደኋላ ሄደህ ልትጀምር ነዉ? ደግሞስ ክርስትና፤ ካቶሊክና ፕሮቴስታነንስዝም ስትል ካቶሊክና ፕሮቴስታንት ምን መሆናቸዉ ነዉ? ክርስትና አይደሉም እንዴ? ወይስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከምንም ተቋም ጋር የማይገናኝ “ክርስትና” የሚባል ሐይማኖት አለ? አየህ ተክሌ ምን አይነት የተበላሸ ጭንቅላት እንዳለህ የሚያሳየዉ እንደዚህ አይነት ቆሻሻና ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ትንተናህ ነዉ። ይልቅ ምነዉ እንዲህ አይነቱን ጭንቅላት የሚፈልገዉን ትንተና ለዚያ አትችልም ላልከዉ ሰዉ ብትተዉለት! ማቻቻል የሚል ቃልም ተናግረሃል፤ ምን ማለትህ ነዉ? ኢትዮጵያ ዉስጥኮ ማን ማንን ችሎ እንደኖረ ግልጽ ነዉ . . . እና አሁንም በዚያዉ እንቀጥል ነዉ እንዴ የምትለን? ዶ/ር ብርሀኑኮ በዚያ ጸሁፉ ዉስጥ ያስነበበን የተለያየ ሐይማኖት ቢኖረንም እንዴት ሁላችንም ያሰኘንን ሐይማኖት ባሰኘን መንገድ እያመለክን (ይግባህ መቻቻል አይደለም) በእኩልነት ተከባብረን መኖር እንደምንችል ነዉ። ይህንን ደግሞ ሊብራል ዲሞክራሲ በሚገባ ተንትኖ አስቀምጦታል። አየህ ተክሌ ፖለቲካ ተንትን ተብሎ ስራ ሲሰጥህ አንደጋይኮ ኮሜርሻል ነገር ትደባልቃለህ፤ አዋቂ ሲተነትን ደሞ አትተንትን ብለህ ትወርድበታለህ፤ ምነዉ ተክሌ . . . “ያግቡብሽ እምቢ ያዉጡብሽ እምቢ” ሆንክሳ!
ኦባማ ሲመረጥ ምሁር ነበር ብለሃል. . . . አይደለም ብዬ ብከራከርህስ? ምነዉ ተክሌ የማታዉቀዉ ዉስጥ ገብተህ ትፈተፍታለህ! አባማ ፕሬዚዳንት ሆኖ ሲመረጥ የፖለቲካ ሰዉ (ሴኔት) ነበር፤ ዛሬም የፖለቲካ ሰዉ ነዉ። በእርግጥ ኦባማ የምሁር ችሎታዉም ተሰጥኦዉም አለዉ፤ ግን በምሁርነት የሚበልጡት ሺዎች አሉ፤ ኦባማን አባማ ያሰኘዉ በምሁርነት ችሎታዉ ላይ አዳብሎ የያዘዉ ከፍተኛ የፖለቲካ ችሎታዉ ነዉ (ይህ ችሎታ የፖለቲካ ትንተናዉንም ያጠቃልላል)። አለዚያ ለምሁርነቱማ ሀርቨርድና ፕሪንስተን ዉስጥ አባማን የሚያስከነዱ ብዙ ምሁራን አሉኮ። ተክሌ አንተኮ አንዳንዴ የምትናገረዉንም የምታዉቅ አይመስለኝም፤ ለዚህ ይመስለኛል ‘ተክሌ’ ከተናገረ በኋላ ነዉ የሚያስበዉ እየተባልክ የምትታማዉ። ምሁር ምሁርነቱ ሲቀንስ ወደ “ቡሽነት” ይለወጣል ነዉኮ ያልከዉ? የፈጣሪ ያለህ! . . . ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ፤ ዕድሜ ላንተ ዘንድሮ ሊጣባ ነዉ። አየህ ተክሌ በዚህ አንተ ባልከዉ ስሌት ከሄድንኮ ኢሳት ዉስጥ ዜና ያነበበ ሰዉ ሁሉ ወናፍነቱ ሲጨምር ‘ተክሌ’ ይሆናል ማለት ነዉኮ . . . እንዴ! እኛ አነተ አንዱም አላስቀምጥ ብለኸናል ደሞ ስንት ተክሌ ሊኖረን ነዉ? ከዚህስ ቸሩ ፈጣሪ ይጠብቀን!!
“የፖለቲካ ተንታኝ የምለው፤ በፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ በአድራጊ-ፈጣሪነት ሳይሳተፍ ወይም መሳተፍ ሳይጠበቅበት፤ የአንድን ፖለቲካዊ ስብስብ/ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ሁኔታ እየቃኝ፤ ከአካባቢያዊና አለማቀፋዊ ሁነቶች ጋር እያጣቀሰ የሚናገር ነዉ” ብለሀል። ለመሆኑ ይህ የተናገርከዉ ነገር ያንተ ህግ ነዉ ወይስ የሁላችንም? ያንተ ከሆነ ያንተ ነገር ሁሉም ግራ የተጋባ ነዉና አልፌሃለሁ። ግን ምነዉ ተክሌ ሰሜን አሜሪካ ዉስጥ እየኖርክ ፖለቲካ በምሁርና በፖለቲከኛዉ ሲተነተን ልዩነቱ አልገባህ አለ? እስኪ የሚገባህ ከሆነ ምሳሌ ልስጥህ . . . ፕሮፌሰር ላሪ ሰባቶ (ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቨርጂኒያ) አንተ ያልከዉ አይነት የታወቀ ምሁርና ፖለቲካ ተንታኝ ነዉ፤ ግን ፖለቲካ አድራጊም፤ፈጣሪም አይደለም ። ተሳትፊ ግን ነዉ። አንተ ከዬት እንዳመጣኸዉ አላዉቅም አንጂ ሰዉ ሆኖ ፖለቲካ ላይ የማይሳተፍ የለም፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ፖለቲካ አድራጊም፤ፈጣሪም ተሳታፊም ናቸዉ፤ ዋናዉ ስራቸዉ ፖለቲካ መተንተን ላይሆን ይችላል፤ ግን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአሜሪካንን ፖለቲካ ተንትነዉ ለህዝብ ማቅረብ ግዴታቸዉ ነዉ። ህዝቡም ጆሮዉን በአብዛኛዉ የሚሰጠዉ ለፖለቲካ ኤክስፐርቱ ለላሪ ሰባቶ ሳይሆን ለፖለቲከኛዉ ለኦባማ ነዉ። አየህ ተክሌ ባንተ አባባል ፕሬዚዳንት ኦባማ ፖለቲካ ትንተናዉን ለላሪ ሰባቶ መተዉ አለባቸዉ ማለት ነዉ፤ ወይም የኦባማ ፖለቲካ ትንታኔ ያልጠራ የላሪ ሰባቶ ትንታኔ ግን የጠራ ነዉ ማለት ነዉ . . . እንዴት ሆኖ! እርገጠኛ ነኝ ይህንን ጽሁፍ አንብበህ ስትጨርስ በራስህ ቅዠት ይምትስቅ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያም ፖለቲካ እንደዚሁ ነዉ፤ ጋዜጠኛዉም፤ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩም፤ ሌላ ሌላዉም ሊተነትነዉ ይችላል፤ ግን ህብረተሰቡ (አንተን ላይጨምር ይችላል- አዋቂ ነሃ!) በብዛት ጆሮዉን የሚሰጠዉ ፖለቲካዉን የፖለቲካ መሪዎች ሲተነትኑት ነዉ። ደሞ ማነዉ ምሁር ሁሉ ፖለቲካ መተንተን ይችላል ብሎ የነገረህ? አቦይ ተክሌ ሌላዉ ትልቁ ችግርህ ሰዉ ያለማክበር ነቀርሳ አለብህ፤ ለምሳሌ ዶ/ር ብርሀኑን አንዴ ዲባቶ ብርሀኑ ፤ አንዴ ብርሀኑ ነጋ፤ ሌላ ግዜ ደግሞ ልክ እንደ ቆሎ ጓደኛህ “ብሬ” ብለህ ጠርተዋኸል። ዶ/ር ብርሀኑ በዕድሜ ይበልጥሃል ደግሞም አስተማሪህ ነዉ፤ ስለዚህ አጠገቡ ስትሆን ዶ/ር ብርሀኑን እንዳሰኘህ መጥራት ትችላህ እሱ ያንተና የሱ ጉዳይ ነዉ፤ ለኛ ስትጽፍልን ግን ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነዉና ማክበር ግዴታህ ነዉ። ይህንን ታላቆችህን የመዘርጠጥ ነቀርሳ በግዜ ካልታከምከዉ ብዙ ታዳጊ ልጆቻችንን ታበላሻለህና አንተዉ ጽሁፍህ ላይ በጠቀስካት በእመ ብርሀን የዤሃለሁ እባከህ ታላቆችህን አክብር።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያነሱትን የመብትና የነፃነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ ኢትዮጵያዉያን፤ የምንደግፍ ግን ንቅናቀዉን በጥርጣሬ አይን የምንመለከት ኢትዮጵያዉያንና ጭራሽ ንቅንናቄዉን የምንቃወም ኢትዮጵያዉያን አለን። አቦይ ተክሌ አንተም የሙስሊሙን ህብረተሰብ እንቅስቃሴ መጠራጠር መብትህ ነዉ፤ ያ እዚያ ሙንጭርጭርህ ላይ የወረድክበት የፖለቲካ ተንታኝም አትጠራጠሩ አላለምኮ! መቼም ያንተ ዱላ ልክ እንደ ወያኔ ፌዴራል ፖሊስ ዱላ ያገኘዉ ሁሉ ላይ ይመዘዛል እንጂ ዶ/ር ብርሀኑማ እንድያዉም የሙስሊሙን እንቅስቃሴ የሚጠራጠሩ ሰዎችን በመንግስት ፕሮፓጋንዳ የተደለሉና የሐይማኖት አክራሪነትን የሚፈሩ ብሎ በሁለት ከፍሎ ነዉ ያስቀመጣቸዉኮ። አንተ ግን በዚያ በተከፈተ ቁጥር አንደ “ታድፋለች ቅጥ” በሚሰፋዉ አፍህ “ብሬ አድበሰበሰው” ብለህ አረፍከዉ። መቼም በባህላችንም ቢሆን ነዉር ነዉና አደባባይ ላይ “ባለጌ” ብዬስ አልሰድብህም!
ምንም ቢሆን ተሰድደህ ዳያስፖራዉን የተቀላቀልከዉ ለትግል ነዉና አስኪ አንድ ነገር ልጠይቅህ . . . . ክርስቲያኑ የሙስሊሙን የመብትና የነፃነት ጥያቄ በጥርጣሬ የጎሪጥ ከተመለከተዉ፤ ሙስሊሙ ደግሞ ይህንን እሱን በጥርጣሬ የሚለከተዉን ክርስቲያን በትግል አጋርነቱ ካላመነዉና ካልተቀበለዉ እንዴት ሆኖ ነዉ የኛ ትግል ግቡን መትቶ አገራችን የምንገባዉ? ይሄዉልህ ተክሌ በዚያ አስቀያሚ የፖሊስ ዱላህ ደጋግመህ የጨረገድከዉ ሰዉ እንዲህ አይነቱን አንተ አይቶ ለመረዳት አመትና ሁለት አመት የሚፈጅብህን ነገር እሱ በግዜ አይቶና ተንትኖ ለህዝብ ያቀረበ ሰዉ ነዉኮ! ምነዉ የልጅነት ገደኛዬ እንዲህ ገብስ ሆንክብኝ ከገብስም የነፈዘዉ! ለመሆኑ ጽሁፉን በደምብ አንብበኸዋል ወይስ ለትችት የሚመችህን ቦታ ብቻ ነዉ እየመረጥክ ያነበብከዉ፤ ለዚያዉምኮ አንተኑ ለትችት የሚያጋልጠዉን ቦታ ነዉ የመረጥከዉ። ለነገሩ አንተ መምረጥ መች ታዉቅበታለህ? ብታዉቅ ኖሮ አንዳቅምህ ትኖር ነበር። ዶ/ር ብርሀኑኮ እንደ ማንም ሰዉ የሚተች ሰዉ ነዉ፤ እንዳዉም እንደሱ ለትችት የተጋለጡ የፖለቲካ መሪዎች በጣት የተቆጠሩ ናቸዉ፤ በየቀኑ እንደሰሩ ነዋ! አንተ ግን ወይ አትሰራ፤ ወይ አታሰራ እንዳዉ “ዝናር በቅፌን” ይመስል መናኛ መናኛዉን ኮተት ተሸክመህ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር ትቀላቀላለህ። አሁን እስኪ ተክሌ በሞቴ ንገረኝማ . . . ተክሌ እንዴት ጎበዝ ነዉ፤ ዶ/ር ብርሀኑን እኮ አገኘዉ፤ ልክ ልኩን ነገረዉ ብለዉ ያንተ ብጤ ጥቅት ወናፎች ቢያናፍሱልህ እዝያ ቁመትህ ላይ ስንዝር ይሚጨምሩልህ ይመስልሃል? ቢጨምሩስ?
አየህ አቦይ ተክሌ ጽሁፍኮ ፊደልና ፊደል ማገናኘት ስለምንችል ብቻ የምንገባበት የጨረባ ተዝካር አይደለም። መጻፍ ማሰብ፤ ማሰላሰል፤ ማንበብና ነገሮችን የማመዛዘን ችሎታን የሚጠይቅ ትልቅ ስራ ነዉ፤ አንተ ደሞ ነገሮችን መቀላቀል ነዉ እንጂ ከእነዚህ እሴቶች ጋር በተለይ ከማሰብና ከማመዛዘን ጋር ጭራሽ የምትተዋወቅም አይመስለኝም። እዩኝ እዩኝ ትላለህ፤ አወቅኩ አወቅኩ ታበዛለህ። አንዳንዴማ ጭራሽ ካንተ በላይ የሚያዉቅ ሰዉ ያለም አይመስልህም። የሰዉ ልጅ የማዉቁ ትልቁ ምልክት አለማወቁን ማወቁ ነዉ። ኦይ ተክሌ ላንተ ግን ይህ የጠቢባን አባባል ተረት ነዉ የሚመስልህ። እባክህ የማታዉቀዉን ነገር አላዉቅም በል። በተለይ በተለይ የማተዉቀዉ ነገር ላይና በደምብ ያልገባህ ነገር ላይ አትጻፍ፤ አትተች አስተያየትም አትስጥ። ዉድ ጓደኛዬ ተክሌ አንግዲህ አንድም ገና የምታድግ ሰዉ ነህና ደሞም ሰዉ እፈር ተብሎ የሚነገረዉ ዉድቀቱን ሲረዳ ስለሆነ “እፈር “ ብዬህ አፌን አላበላሽም። እስከዛሬ እንዳየሁህ አንተም እንጣጥ እንጣጥ ማለት ነዉ እንጂ እፍረት የሚሰማህ ሰዉ አይደለህም። እንጣጥ የሚያበዛ ሰዉ ደግሞ ያመለጠዉ ለታ ዕድሜ ልኩን ያፍራል። እንግዲህ ይህ መጥፎ ቀን ሳይመጣብህ ከአቅምህ በላይ መዝለሉን አቁም። እርግጠኛ ነኝ ተክሌ ይህንን ጽሁፍ አንብበህ “ዲሞክራሲ” የማይገባቸዉ ሰዎች ሀሳቤን የመግለጽ መብቴን ሊቀሙኝ ነዉ እንደምትል፤ ሆኖም የዚህ ጽሁፍ ጥረት የዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ አንዲገባህና ከሰዎች ጋር በቡድን ስትሰራ ሌሎችን ሳትጋፋና ሳታስቀይም ሀላፊነት ተሰምቶህ ግዴታህን እንድትወጣ ነዉ እንጂ የሁላችንም ትግል ለመብት መከበር ነዉና መብትህን የነካም የደፈረም የለም። የፖለቲካ መሪዎቻችንን መተችትና ስህተት ሲሰሩ ተከታትሎ ማጋለጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነዉ፤ ነገር ግን የሌለ ስህተት እየፈጠርክ፤ ያልተጻፈ እያነበብክና ሰዎች ደፋር ተቺ ነዉ እንዲሉህ ብቻ የሚሰሩ ሰዎችን ባትቦጫጭቅ ጥሩ ይመስለኛል። አንድ ሰዉ ባጠፋዉ ጥፋት የሚያዝነዉ ለሌሎች ካለዉ ክብርና ፍቅር ነዉና . . . ተክሌ እስኪ እባክህ ለህዝብ ክብር ስትል ጥፋትህን ተረዳና ከራስህም ከወገንም ጋር ታረቅ። የምትመኘዉን ትልቅ ሰዉ ለመሆን ከፈለግክ የትልቅነት መንገዱ ይህ ነዉ። እግዜር ይርዳህ!