Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ገድሎ ለቅሶ የሚደርሰው ስርዐት ሞቶ ቀብር የምንወጣለት አዲስ አመት ይሁልን

$
0
0

Melak addis  ametመቸም የዘመን ዑደት ማለት አሮጌው አልፎ አዲሱ የሚተካበት፣ ዘር አፈር ቅሞ ወሀ ጠጥቶ በቅሎና አብቦ የሚያሸትበት መስከረም ማለትም አይደል? አዎ አዲስ ዘመናችን ምድሪቱ ጭጋግን ለብሳ፣ አራዊቱ ያጠራቀሙትን ስብ እያቀለጡ የሚኖሩበት፣ አእዋፍ ስደት የሚጀምሩበትና የሰው ልጅ አንደ በቆሎ በልብስ የሚጠቀለልበት የበረዶ ወቅት ባለመሆኑ እርግጥም አዲስ አመት ነው። በምንም መስፈርት በማንም መለኪያ ዘመን አቆጣጠራችን ለኛ ተገቢም ትክክልም ነው። አዲስ አመት ማለት ለኛ ለኢትዮጵያውያን ተስፋ ማለትም ነው።

ታድያ ተስፋ ላይ ለቅሶና ቀብር እንዴት ርዕስ ሆነ ማለታችሁ አይቀርም። አዎ ሸፍጥ ሞቶ ሀቅ ቀብር ቢወጣና ለእውነት ኖረን ስለ ዕውነት ብናልፍ፤ በዚህ የአመታት ቅብብሎሽም እንደ አደይ አበባ ሁሉ የተስፋ ብስራት ቢያሸትልን ምን ይለናል? የሚል መንደርደርያ ነው የዚህን አይነት ርዕስ ያስመረጠኝ። አዎ እነዚህ አዲሶቹ ገድሎ ቀብር ወጪዎች ‘ተረትና ማቅራራት’ የአማራ ነው እንዳለው አስተኳሻቸው ገድለው አያቅራሩም። በፊት በረሃ እያሉ እርግጥ ነው በአንድ ጥይት 10 ሰው መደዳውን እንደሚገድሉ ተራራው እንደሚንቀጠቀጥላቸው ነግረውን ነበር። ‘ፍሬንድሊ ፋየር’ የምትለውን ብልጥ ቃል መጠቀም የጀመሩት ግን ያኔ ‘ፍሬንዶቻቸውን’ እያጋደሙ ሲያርዱ ነበር። እድሜ ለገብረመድህን አርአያ አስገድሎ አሸርጦ ማልቀስን በሜጋ የፊልም ቅንብር ሀውዜን ላይ መተወናቸውን ነግሮናል። አተረፉበት ነው የሚባለው! ከበሩበት እንጂ ሸገር ይዞአቸው የገባው ሞት የሀውዜኑም አይደል? ከዚያ በሁዋላ ያፈነገጠውን ሁሉ እርድ ያደርጉና ጉድ ተሰራን? ገዳዩን ለማግኘት የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም ብለው አደባባይ ይምላሉ።

በሁዋላ ግን የፈነቀሉትን ድንጋይ መቃብሩ ላይ ቆልለው ወሬውንም ያጠፉታል። አይንአውጣ ስለሆኑ ለቅሶ ሁሉ ይደርሳሉ። ስፍስፍ ብሎ የሚያለቅስና ሁዋላ አደጋ የሚያመጣ የሚመስላቸውን መንጥረው ለማባረር የሚጠቀሙበትም ይመስላል። ይህ ወንጀላቸው ወደ ህግ ባይመጣም እንኳ ሕሊናን መበጥበጡና ነገም ለኔ አይመለሱም የሚለው ፍርሀት መኖሩን ከሰዎቹ ፊት ማንበብ ይቻላል። ይህ ጥርጣሬና ፍርሃት ፊታቸውን አበላሽቶታል።

የሆነ እርኩስ መንፈስ የተጠናወተው የሚመስል ቅብዝብዝ ዐይኖች አላቸው። የተሸበረ ፊ የሌለው ባለስልጣን እኮ የለም። አዎ የሰው ደም ያቅበዘብዛል። እነዚህ በጎደለ የተተኩ ከበረሀኞቹ በላይ በረሀኛ የሚመስሉትም ቶሎ የደለበ ግን መታረጃውን ያየ ሰንጋ መስለዋል የሚሉም አሉ። አሁን በቀደም ሼክ ኑሩን መስዋዕት ሲያደርጓቸው ገድሎ አልቃሾቹ መስጊድ እንደጧፍ ሲነድ ቤተክርስትያን እንደ ደመራ ቦግ ሲል ሕዝቡ ሲተራረድና እነሱ ገላጋይ ሆነው ሲወጡ የሚያሳይ ባለቀለም ሕልም አይተው ነበር። ሕዝቡ ግን አረ ቀልዳችሁን አቁሙ ብለው ‘የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ’ የሚል የአማራ ተረት ተረተባቸው ሲባልም ሰምተናል። አዎና አርባ አመት ሙሉ ገድሎ ማልቀስ እንዴት ይቻላል? ማነው ስሙ አንድ አስለቃሽ ጋዜጠኛ ወደ ወሎ ሄዶ የ’አይዶል ሾው’ ቢሆን “ለዛሬው አልተሳካልህም” የሚያስብል ሳይጀመር ያለቀ ዘገባ አቅርቦ ነበር። ከዚህ የበለጠ ጭካኔ መቸም የለም።

ለቅሶ ላይ መፈክር ሲያሰሙ እንዲውሉ አደረጋቸው። ውሸታቸው ወንዝ የመሻገር አቅም ስለሌለው ውሸቱን በውሸት ለመሸፈን አሁን መዘዙ ለሼኩም ልጅ አልቀረለት መታሰርና መጋዝ ውስጥ ወስጡን ሌላ ሞት መደገስ ሆነ። የሰለቸንም ይኸው ነው! ዘዴውም ጃጀ እንደ ተሰነጣጠቀ ሽክላ በድምጽ ሲፈርስም አየነው። አሁን አስተኳሹ ብቻ ሳይሆን ስርዐቱም ሞቱን በጸጋ ሊቀበል ይገባዋል። ብዙ የለቅሶን ወሬ ወደ የመልካም ምኞት መግለጫ እንቀይረውና በሚቀጥለው አመት ገድሎን ለቅሶ የሚወጣው ጎጠኛና ወሮበላ ስርዐት ሞቶ ቀብር የምንወጣለት ይሁን ብለን እንመራረቅ። እንዲህ እያልን ምክርም እንምከር “ከነሱ ጋር በልቶ በሰላም ተኝቶ ማደር የለምና በቁልቋል የተመሰልክ ተላላ ሆይ ይህንን አጋም ተጠግተህ እድሜ ልክህን አታልቅስ።” ብለን። የፍቅር አደይ አበባ የተነጠፈባት፣ የተስፋ ቀስተ ደመና የተዘረጋባት፤ ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነት መለያዋ የሆነች ውብ ኢትዮጵያ የመልካም አዲስ አመት ምኞታችን ትሁንልን እውነትም እናድርጋት።
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
biyadegelgne@hotmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>