አበራ ሽፈራው /ከጀርመን/
ዛሬ አለማችን በከፍተኛ ስልጣኔ ላይ ትገኛለች። በዚህም ስልጣኔ ውስጥ በኢንተርኔትና ተያያዥ የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቅሞ የሰው ልጅ የሚፈልገውን መረጃ መፈልግ፣ማግኘት፣መለዋወጥና ማሳወቅም ሆነ ማወቅ የሚችልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ጊዜው ለውሸታሞች ፣ ለአታላዬች፣ ለግፈኞች እና ለበዝባዦች የሚመች አይደልም፤ ዓለም መድረስ ወደሚፈልግበት እየሔደ ነው፤ጊዜው ወደፊት መሄድን እንጂ እንደኃለኛው ዘመን ማሰብን አይፈቅድም፤ ስለዚሀ ከጊዜው ጋር አብሮ መሄድ ካልሆነም ውሸታሞች ውሸታቸውን ሊድብቁ የሚችሉብትን አዳዲስ መሳሪያዎችን መፈብረክ ይጠይቃል።አለመታደል ሆነና ህወሓቶች ስለእነሱና ስለተግባራቸው ማንም የሚያውቅ አይመስላቸውም። ትልቁ የሚያውቁትም ቃታን እየሳቡ ሰውን መግደል ብቻ መሆኑን ድርጊታቸው እያሳየን ነው፤ በዚህም ድርጊታቸው እንደ ትልቅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እራሳቸውን ከመሪዎቻቸው ጀምሮ ሲያጋንኑ፣ ከበሮ ሲያስደልቁ ኖርዋል አሁንም በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ግድያን መፈጸም፣መስረቅ፣መንጠቅ፣ማሸማቀቅ፣እያሰሩ ማሰቃየት፣በአጠቃላይ ግፍን መፈጸምና ማሸበር እንደትልቅ ሙያና ተግባር ተያይዘውታል።
ህወሃት /TPLF/ እ.ኤ.አ ከ1976-1991 በሰው ልጆች ላይ በፈጸማችው የሽብር ወንጀሎችና ጥቃቶች በአሸባሪነት ተመዝግቦ የነበረ ቡድንም ነበር። ህወሓት ሽብርን ለመፈጸም ለ39 ዓመታት ያካበተው ልምድ ቢኖረውም ከዚህ በላይ መሽበር ግን የህዝቡ ግዴታ ሊሆን አይግባም።
ህወሓት ዛሬ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ሽብር፣የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄን ሽብር፣ጋዜጠኝነትን ሽብር፣መደራጀትን ሽብር ፣ሃሳብን በነጻነት መግልጽን ሽብር በማለት ህዝብን ሲያሸብር ሲታይ ህወሓት ስሙንና ተግባሩን ለሌላ ለመስጠት የፈለገ ይመስላል።
በየጊዜዉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ድርጅት አማካኝንት የሚነዙትን ፕሮፓጋንዳ ላየና ለሰማ ሁሉ ሽብርተኝነት ህወሃትን ያስመረረው ይመስላል። ይልቁንም የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃት መሸበሩንና መማረሩን፤ የሽብርተኝንት ታሪክም የህወሓት የራሱ የ39 ዓመታት ታሪክ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ እንደልሆነ ለህወሓት ለራሱ ሊነገረው ይገባል።
- 1. ህወሓት መንግስት ከመሆኑ በፊት የፈጸማቸው የሽብር ተግባራት ምን ነበሩ ?
ሀ. ህወሓት አሸባሪ ድርጅት የነበረና የተመዘገበም መሆኑ፡-
በዩ.ኤስ.ኤ አሜሪካ በአገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት አማካኝንት በሜሪላንድ ዩንቨርስቲ በአለም አቀፍ ደረጃ የአሸባሪዎችን እንቅስቃሴና ድርጊታቸውን የሚመዘግበውና የሚተነትነው የመረጃ ማዕከል ማለትም The National Consortium for the study of Terrorism and Responses to Terrorism/START/ ለመረጃ መሰብሰቢያ ባዘጋጀው ዳታ ቤዝ ወይም GTD/Global Terrorism Data Base/ ክፍት በሆነው የመረጃ ፍልሰቱ ውስጥ እ.ኤ.አ ከ1976-1991 ድረስ አሥር/10/ ልዩ ልዩ የሽብር ጥቃቶች በህወሓት/TPLF/ መፈጸማቸውን መዝግባል፤ በነዚህ የሽብር ድርጊቶቹ ህወሓት አሸባሪ ድርጅት ተደርጎ ተመዝግባል። ይህ የመረጃ ማዕከል ህወሓት የፈጸማቸውን የሽብር ድርጊቶች የዘረዘረ ሲሆን በዚህ መረጃ ላይ ድርጊቱ የተፈጸመበት ቀን፣ ቦታ፣የአደጋው ብዛት፣ የአደጋው አይነት፣የተጠቀማቸውን የመሳሪያ ዓይነት ለመመዝገብ ሞክሯል፤በዚህ መረጃ መሰረት በራያ ቆቦ፣በትግራይ ቦታዎች፣በላሊበላ፣በጅሬ፣በኮረም፣በወርቅ አምባ፣በአክሱምና በሌሎች ቦታዎችም የሽብር ድርጊቱ የተፈጸመ መሆኑን ጽፋል፤በነዚህም ጥቃቶች የሃይማኖት ተቃማትና መሪዎች፣በግለሰብ ህይወት እና ንብረት ላይ፣ በመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ፣በንግድ ተቃማት ላይ ፣በጋዜጠኞች እና ሚዲያዎች ላይ ሽብሩ መፈጸሙን ዘርዝሯል። ስለዚህ ህወሓት አሸባሪ ድርጅት እንደነበረና ተግባሩም ሽብር እንደነበረ ለማወቅ ይቻላል። ለበለጠ መረጃ http://www.start.umd.edu/start/ ይመልከቱ።
ለ. ህወሓት ልዩ ልዩ ሽብሮችን ሲፈጽም እንደነበረ አባሎቹ የነበሩ መመስከራቸው፡-
የህወሃትን እኩይ ተግባር በማጋለጥ የሚታወቁት አቶ ገብረመድህን አርአያ ስለ ህወሓት ያለፈው ታሪክ ላይ በጻፋቸው ጽሁፎች ላይ ህወሓት ግልጽ አሸባሪ መሆኑን በተደጋጋሚ ከመግለጻቸውም በላይ አሁንም ካዩትና ከሰሙት እዉነታዎች ተነስተዉ ይህንን አሽባሪ ድርጅት እያጋለጡም ይገኛሉ።
ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ የተነሳው የራሱን የህወሓትንና የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ለማስጠብቅ ሳይሆን ጥቂቶች በስውር ይዘዉት የተነሱትን ስውር የዘረኝነት፣የብዝበዛና የጭቆና ዕቅዶቻቸውን ከግብ ለማድረስ እንደህነ ተግባራቸው ያሳየና፤ ይህንንም ግባቸውን ለመፈጸም የትኛውንም ሽብር ከመፈጸማቸው ጋር ተያይዞ ህወሓቶች በዓለም ከሚታወቁ የሽብርተኛ ቡድን ተርታ ተሰልፈው የነበረ ቢሆንም ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ጋርና ከደርግ መንግስት መንኮታኮት ጋር ተያይዞ አገራችን በአሸባሪዎች እጅ ወደቀች፤ ደርግና ባለማሎቹም እንዲሁም ዋና ዋናዎቹም የዓለም መንግስታትም ህዝቡንና አገራችንን አሳልፈው ለሽብርተኞች ሰጡ ። ይለወጣል ብለው ብዙዎች ቢጠብቁትም ተግባሩ ያለቀቀው ህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከሆነም በኃላ ከቡድናዊ ሽብርተኝንት ወደ መንግስታዊ ሽብርተኝነት ተሸጋገረ።
- 2. የህወሓት/ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣን ከያዘ በኃላ ወደ መንግስታዊ ሽብርተኝነት መቀየር /State Terrorisim/
ሀ . ለመሆኑ የመንግስት ሽብርተኝንት/ State Terrorisim/ ምንድ ነው?
ጸሃፊዎች የሽብርተኝነት መሰረታዊ ዓላማ ሽብርተኞቹ የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ልዩ ልዩ መንገዶችን ተጠቅመው በህዝቦች ላይ ከሚገባው በላይ ፍርሃትን በመፍጠርና በማስገደድ ዓላማቸውን ከግብ ማድረስ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በ acadamia.org ላይ የመንግስት ሽብርተኝነትን እንደዚህ ጽፎታል፡- State terror refers to the use or threat of violence by the state or its agent or supporters,particularly against civilian individuals and population,as a means of poletical intimidation and control.
የፖለቲካ የበላይነትን ለመያዝና ጫናን ለመፍጠር በተለይም በሰላማዊ ግለሰቦችና ህዝቦች ላይ ተገቢ ያልሆነን ጥቃትን በራሱ በመንግስት፣በተወካዮቹና በደጋፊዎቹ ሲፈጸም ይህንን ጥቃት መንግስታዊ ሽብር ብሎታል።
እንግዲህ ህወሓት/ኢህአዴግ ምንም እንካን የመንግስትን ሥልጣን የያዘ ቢሆንም ሌሎች አሸባሪ ድርጅቶች የሚፈጽማቸውን ተግባራት በግልጽና በአደባባይ ይፈጽማል። ከነዚህም ውስጥ ፍንዳታን ይፈጽማል ፣ያፍናል፣ህጋዊ ያልሆኑ እስራትን ይፈጽማል፣በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ የማይፈጸሙ ድብደባዎችን፣ በወንዶችም ሆነ በሴቶች የመራቢያ ብልቶች ላይ አደጋን ማድረስ፣አካለ ስንኩል ማድረግ፣ ቤተሰቦች እንዲለያዩ ማድረግ፣ ስውርና የአደባባይ ላይ ግድያዎችንና ሌሎችም ተግባሮችን ይፈጽማል።ከዚህም ድርጊቱ አንጽር ህወሓት/ኢህአዴግ ከአሸባሪነት መገለጫዎች የዘለሉ ተግባሮችን የሚፈጽም ቡድን መሆኑን ያሳያል።
ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጽመውን የሽብር ጥቃቶችን ኢትዮጵያውያን በግልጽ የሚያውቁት ጉዳይ መሆኑ ፣የልዩ ልዩ ሃገራት መንግስታትና በኢትዮጵያ የሚኖሩ የልዩ ልዩ ሃገራት አምባሳደሮችም ሳይቅሩ በግልጽ የሚያውቁት መሆኑና ይህንንም የሚያግዙ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ መሆናቸው፤በተለይም የዩ.ኤስ.ኤ አሜሪካንና ሌሎችንም መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በማጋለጥ የሚታወቀው ዊኪሊክስ ይፋ ባደረጋቸው መረጃዎች መሰረት እነዚህ እውነታዎች ግልጽ እየሆኑ መምጣታቸውና በተለይም ህወሓት የራሱን የሽብርን ጥቃት ለመፈጸም እንዲያግዘው ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ጥቃት እንዳለ ለማስመሰል ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የማታለያ እንቅስቃሴዎች ማለትም የሽብር መሳሪያዎችን በራሱ ወታደሮችና የደህንነት ሰዎች በልዩ ልዩ ቦታዎች በማስቀመጥ መልሶ በራሱ የደህንነት ሰዎች እንደተገኙ በማስመሰል ያደርገዉ የነበረውን ተግባር አጋልጧል፤ እነዚህም ድርጊቶቹ አስቀድሞም ብዙዎች የነበራቸውን ጥርጣሬም አጠናክሮታል።
ለ. ህወሓትኢህአዴግ የፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶችስ ምንድ ናቸው?
ህወሓት/ኢህአዴግ የመንግስትን ሥልጣን ከያዘ በኃላ መጠነ ሰፊ የሽብር ጥቃቶችን በህዝቡ ላይ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታ የፈጸመ ሲሆን ዋና ዋናዎቹን በጥቂቱ እንመልከት፡-
- በወልቃሪት ጠገዴ ህዝቦች ላይ የተፈጸሙት የዘር ማጥፋት ዘመቻና የዚህንም ህዝብ ህልዉና በማጥፋት የራሱን መስፋፋት ከግብ ለማድረስ በህዝቡና በትውልዱ ላይ የተወሰደዉ የዘር ማጥፋት ተግባር እጅግ ዘግናኝ ተግባር የሆነና ጉዳዩ ገና መፍትሄ ያልተገኘለት ይልቁንም ገና ብዙ ቀውስን ሊፈጥር የሚችል ተግባር መሆኑም እራሱም ህወሃትም ያልተረዳው ግፍ ነዉ።ለበለጠ መረጃ http://ethio-wolqait.blogspot.de/. እና ሌሎችንም ተያያዥ ጽሁፎችን ይመልከቱ::
- በጋምቤላ በአኟኮች ላይ እ.ኤ.አ በዲሴምበር 13/2003 በጋምቤላ ከተማ የተደረገው የጅምላ ግድያ/Gonocide/ 424 ስዎችን በጅምላ በመግደል ታሪክ የማይረሳው የመንግስት ሽብር የተፈጸመ ሲሆን ብዙዎችም አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፣የአኟክ ሴቶች በወታደሮች ተደፍረዋል፣በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመዋል፣የሚመገቡአቸው ምግቦችና የቤት እንሥሣቶችም እንዲወድሙ ተደርጓል።ይህ ሽብር ህወሓት በዚህ ክልል ውስጥ ለመስፋፋት ብሎ በህዝብ ላይ የተፈጸመ ግልጽ ሽብር ነው።ለዚሀም ድምዳሜ ላይ ያደረሰኝ ጉዳይ አብዛኛው የጋምቤላ ሰፋፊ መሬቶች በህወሃቶችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ቁጥጥር ውስጥ መሆኑና እየተበዘበዘ መሆኑ ነው። በዚሁ ክልል ስለተፈጸመው ጅምላ ግድያና ህወሓት በዚሁ ክልል ስለሚፈጽማቸው የሃብት ብዝበዛ ለማውቅ ከፈለጉ የአኟክ የፍትህ ካውንስልን ዌብ ሳይት “http://www.anuakjustice.org/” ይመልከቱ።
- የሲዳማ ህዝቦች ሰላማዊ ጥያቄዎች በማንሳታቸው እና ህገ-መንግስታዊ መብቶቻቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በመነሳታቸው ብቻ ከ 11 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ ሜይ 24/ 2002 በአዋሳና አካባቢው ከ100 በላይ የሲዳማ ተወላጆችን በጅምላ በመግደልና ከ250-300 የሚሆኑትን በማቁሰል የተፈጸመው ዘግናኝ ሽብር ለታሪክ የማይረሳና የህወሓትን ግልጽ ሽብርተኝነት የሚያሳይ ሌላው ሀቅ ነው። ለበለጠ መረጃ http://sidamaliberation-front.org/ ይመልከቱ።
- በኢትዮጵያ አቆጣጥር ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኃላ በህዝብ ምርጫ የተሸነፈው ህወሓት/ኢህአዴግ ከህጻናት እስከ አዋቂ በጠራራ ጸሃይ በመቶዎች የሚቆጠሩትን ንጹሃን ግንባር ግንባራቸውን ብሎ በመግደል፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩትን አካለ ስንኩል በማድረግ፣በሽዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ በእሥር ቤቶች ውስጥ በማሰርና በማሰቃየት በኢትዮጵያ ህዝብና በዓለም ማህበረሰብ ፊት ግልጽ ሽብር የፈጸመ ቡድን መሆኑ የቅርብ ግዜ እውነታዎች ናቸው።
- በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ውስጥ በተወሰኑ በኦሮሞና በትግራይ ተማሪዎች መካከል በተደረግ ግጭት ግልጽ በሆነ መድሎና በማን አለብኝነት በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ከትምህርት ገበታቸው እንዲባረሩ ተወስኖ የነበረውን ውሳኔ ሰንመለከት እጅግ የሚያሳዝን ተግባር መሆኑና ድርጊቱ በአዲሱ ትውልድም ላይ የተቃጣ ሽብር ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን በአገራችን በግልጽ መድሎ ውስጥ መሆናችንን ያሳያል።
- በኦሮሞ ህዝቦች ውስጥ የሚደረጉትን ትግሎች በሙሉ ከኦነግ ጋር በማያያዝ የኦሮሞ ህዝቦች በእስር ቤቶች ውስጥ እንዲማቅቁ መደረጉና አብዛኛው የአገሪቷ እስር ቤቶች ኦሮሚኛ የሚነገርባቸው እስከ መሆን መድረሳቸውን ከፖለቲከኞች አፍ መስማታችን እጅግ ከባድ ችግሮች በህዝቡ ላይ መኖራቸውንና በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሽብር እየተፈጸመ መሆኑን ያሳየናል።
- ህወሓት/ኢህአዴግ ሊፈጽመው የሚፈልገውን ሽብር በሽብር ህግ ድጋፍ እንዲደረግለት በህዝቡ ሳይሆን ለህወሓት የብዝበዛና የጭቆና መሳሪያነት በሚያገለግለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት አጽድቆ የሽብር ጥቃቱን እየፈጸመ ሲሆን በዚህ ጥቃትም ልዩ ልዩ አካላት የህወሓት የሽብር ጥቃት ስለባዎች ሆነዋል። በዚህም ውስጥ ጋዜጠኞች፣የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ የነጻነት ተማጋቾችና ልዩ ልዩ ግለሰቦች በሙሉ በዚሁ ጥቃት ውስጥ ወድቀዋል።
ከጋዜጠኞች መካከልም፡- ርዮት አለሙ፣ውብሸት ታዮ፣እስክንድር ነጋ፣ በተለያዩ ጊዜያት በፍርድ ቤት የሚመላለሰው ተመስገን ደሳልኝ እና ሌሎችም ከሃገር ውስጥ ፣ የስውዲን ጋዜጠኞች ጀሃን ፕርሰን/Johan person/ እና ማርቲን ሽብዮ/Martin Schibbye/ ከውጭ ይገኙባቸዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትም ውስጥ አንዱዓለም አራጌ ፣በቀለ ገርባ፣ኦርባና ሌሊሳና ሌሎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በእሥር ቤቶች የሚማቅቁ ይጠቀሳሉ።
በተለይም ተዋቂ ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት ሰበብ አስሮ ሌሎች በአገራቸው በሚደረገው የነጻነት እንቅስቃሴ ላይ ምንም እንዳይናገሩ በማድረግ በነጻው ሚድያ ላይ ግልጽ የመንግስት ሽብር እንዳለ ሁሉም የሚያውቀውና እ. ኤ. አ ከ2007-2012 ድረስ ብቻ 49 የሚሆኑ ጋዜጠኞች በዚህ የህወሓት የሽብርተኝነትን ድርጊት በመፍራትና በግዳጅ ከሃገር መሰደዳቸውን ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከረው ሲፒጄ/Commitee to Prtect Jornalists / በተለያዩ ጊዜያት ገልጸዋል፤በዚህም ምክንያት አገራችን ለጋዜጠኞች ህይወት አደገኛ አገር መሆናንና ከሱማሊያና ከኢራቅ ቀጥላ ለጋዜጠኞች የስደት ምክንያት በመሆን ታዋቂ ሆናለች ።
- በተለያዩ ጊዜያት በአፋር፣በሶማሊያና በጋምቤላ ክልሎች የህወሓት የመሬት መስፋፋትን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የእነዚህን ህዝቦች የመሬት ሃብት ተጠቃሚነትን በመንጠቅ የህወሓት የብዝበዛ ቡድን አባላትና ጀሌዎቻቸው በህዝቦች ህይወት ላይ ተደጋጋሚ አደጋ በመፍጠርና በማፈናቀል አስከፊ ተግባር እየተፈጸመ ያለው በዚሁ ተስፋፊ የህወሓት/ኢህአዴግ ቡድን አሸባሪነት መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።
- በአማራ ተወላጆች ላይ ከደቡብ ከጉራፈርዳ፣ከቤንሻንጉል ጉምዝና ከሌሎችም ክልሎች በማፈናቀል፣መሬት በመንጠቅና በማሳደድ የዘር ማጽዳትን ተግባርን የሚያቅደው እራሱ ህወሓት መሆኑንና ከትግሉ ጀምሮ ይዞት የመጣው በማኔፌስቶውም ላይ በግልጽ ያስቀመጠውና እየተገበረ ያለው ተግባር ነዉ፤በዚህም ብዙ ጭቁን አማሮች የሚከላከልላቸው አጥተው የዚሁ የሽብር ጥቃት ሰለባ ሆነው ተቀምጠዋል።
- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይም ከአንድ ዓመት ወዲህ በሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚፈጸመው የአደባባይ ላይ ድብድባ፣እስራትና ግድያዎች የህወሓት/ኢህአዴግ ሌላው ህዝብን የማሽበር ተግባሩ አካል እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
- በሃገር ውስጥ ባሉ ሰላማዊ ትግልን አማራጭ ትግል በማድረግና ህግን ተከትለው የሚታገሉትን የተቀዋሚ ፓርቲዎች አመራርና አባላት ላይም እየደረሰ ያለው ወከባና እንግልት ሰላማዊ ትግሉን እጅግ መራራ አድርጎታል፤ለዚህም ማስረጃ ይሆን ዘንድ በቅርቡ በሰማያዊ ፓርቲ ላይና በአንድነት ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ህወሓት/ኢህአዴግ በፍጹም ማን አለብኝነት መቀጠሉንና ሰላማዊ ትግሎችንም ጭምር ለማጥፋት መቀጠሉ ይህ ሥርዓት በግልጽ በመንግስታዊ ሽብርተኝነት መቀጠሉን ግልጽ አድርጎልናል።
- 3. ህወሓት/ኢህአዴግ የሽብር ጥቃትን ለምን ይፈጽማል ?
ህወሓት/ኢህአዴግ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰና ለእውነተኛ ዲሞክራሲና ፍትህ የቆመ ቡድን ሳይሆን በጥቂቶች ጠባብና ዘረኞች የተዋቀረ የማፍያ ቡድን መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያውቃል። የህወሓት ዓላማና ግብ በእርግጥም የነጻነትና የዲሞክራሲ ሳይሆን ጥቂቶች የአገሪቷን ወታደራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅሮችን በሙሉ ተቆጣጥረው ለዓመታት የተመኙትን የኢኮኖሚና የመሬት መስፋፋትን ዕውን ለማድረግ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አካልና፤በኢትዮጵያ ህዝብ ደምና ሀብት ለመክበር በሚቋምጡና በሚተገብሩ የህወሓት መሪዎችና ጀሌዎቻቸው አማካኝነት ይህንን ስውር ተግባር ለማስፈጸም የሚፈጸም የሽብር ተግባር ነው።
የዚህን እውነታዎች ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ አሁን በተጨባጭ የሚታየውን እውነታን ማየት ይቻላል።አጠቃላይ የኢኮኖሚው ክፍል በሙሉ ማለት ይቻላል በህወሓት ቁጥጥር ስር መውደቁና፤ የህወሓት የንግድ ድርጅቶች ሙሉውን የአገሪቷን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ለመቆጣጠር ሩጫ ላይ መሆናቸውና፤ እነዚህን ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ የመንግስት መዋቅሮች በእነዚሁ በህወሓት ሰዎች እጅ ቁጥጥር ስር መዉደቁ ግልጽ ማስረጃ ሆኖ ይገኛል፤ለምሳሌ ኢፈርት በሁሉም የአገሪቷ የንግድ ሴክተሮች ተጽዕኖን እንዲፈጥርና ሌሎችን ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ የሚያደርገው እንቅስቃሴና በብሄራዊ ባንክ፣በግሙሩክ፣በአየር መንገድ፣በአገር ዉስጥ ገቢ መስሪያ ቤቶች፣በወታደራዊ ተቋማት፣በፖሊስና ደህንነት መስሪያ ቤቶች ተሰግስገው አገሪቷን ለመበዝበዝ የሚያስችሉአቸውን ሁኔታዎች በቁጥጥር ውስጥ ያስገቡ በመሆኑ፤ ይህንን ብዝበዛ የሚቃወምም ሆነ የሚነካ ሃይል በሙሉ የጥቅሞቹ ተቀናቃኝ አድርጎ በመቁጠሩና፤ ይህንን የህወሓትን ቡድን ስውር ዓላማን ለማስፈጸመ መንግስታዊ ሽብርን አንዱ አማራጭ አድርገው የያዙት መሆኑ፤ ህወሓትን የሚያሳስበው የፍትህና የዲሞክራሲ ጉዳይ ሳይሆን ይህንን የብዝበዛ መዋቅራቸውን የሚነካ ሃይል ሁሉ በአሸባሪነት በመፈረጅ የብዝበዛ ተግባራቸውን ከግብ ለማድረስ የመንግስት ሽብርተኝነትን እያቀጣጠሉ መሆኑ ነው።
- የህወሓት/ ኢህአዴግ የሽብር ተግባራት በህዝቡ ላይ የፈጠራቸው ችግሮች ምንድን ናቸው ?
የህወሓት/ኢህአዴግ ቡድን በሚፈጥራቸው የሽብር ተግባራት የተነሱ በህዝቡና በአገሪቷ ላይ የፈጠሩት ተጽዕኖዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
- በህዝቡ ላይ ፍርሃት መንገሱና በብዙዎች ላይ የስለልቦናም ችግር ያስከተለ መሆኑ፤
- ስደትና በስደትም የተነሳ ወጣቶች በጎረቤት አገራትና በየበረሃው ለሞት መዳረጋቸው፤
- እስራትና ሞት፤
- ግልጽ የህወሓትንና የጥቅም ተጋሪዎቻቸውን ልዩ ልዩ ብዝበዛዎችን ከፍርሃት የተነሳ በዝምታ ማየት፤
- በህዝቡ ላይ ሰብዓዊ ጥሰቶች በብዛት እየተፈሰሙ መምጣታቸው፤
- የመሬትና የተፈጥሮ ሃብቶች ብዝበዛ መቀጠሉ፤
- የሃገሪቷ ሃብቶች በጥቂቶች እጅ እየወደቁ መምጣታቸው፤
- ህዝቡ መብቶቹን እንዳይጠይቅ መገደዱ፤
- የስራና የትምህርት እድሎች መድሎዎች መፈጠራቸው ይህንንም መድሎ በዝምታ ለመቀበል መገደድ፤
- የስራና የመኖሪያ ቦታዎች ችግር መፈጠሩ፤
- የሙስና መስፋፋት መባባሱ፤
- የህግ የበላይነት ቀርቶ የህግ መድሎ መፈጠሩ፤
- ግልጽ የንግድና የስራ ቦታዎች መድሎ መኖሩ፤
- ህዝቡ ከተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንዳይቀላቀልና መብቶቹን እንዳያስከብር መሆኑ፤
- በንሮ ውድነት መማቀቅ፤
- ህዝቡ በሃገሩ ላይ የበይ ተመልካች መሆኑ፤
- የንብረት መነጠቅ ችግሮች መደራረብና ሌሎችም:-
- 5. ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ከስቪክ ማህበራትና ከኢትዮጵያ ህዝብ አጠቃላይ ምን ይጠበቃል ?
ህወሓት/ኢህአዴግና የጥቅም ተጋሪዎቹ ይዘው የተነሱትን የኢኮኖሚ፣የንግድና የመሬት መስፋፋት ከግብ ለማድረስ በሚያደርጉት የብዝበዛና የዝርፊያ እንቅስያሴ ዉስጥ ማናቸውንም ሰላማዊና ህጋዊ ትግሎች ሳይቀሩ በሽብርተኝነት ሰበብ መግደል፣ማሰር፣ማሳደድ፣ማሸማቀቅና ማስፈራራት የህወሓት የየዕለት ተግባር ሆኗል። ይሁንና ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ እራሳችን ለመታገል ካልቆረጥንና መሰዋዕትነትን ለመክፈል ካልተነሳን ችግሩ ማብቂያ እንደማይኖረው ሊሰመርበት ይገባል።
በሃገራችን ታሪክ ህዝብንና አገርን በማሽበር በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በዓለም የሽብርተኝነት መዛግብት ውስጥ የተመዘገበውን ይህንን ሽብርተኛን የህወሓትን ቡድን ከድርጊታቸው እንዲያቆሙ ማድረግ ወይም እራስን የመከላከል ተፈጥሮአዊና ህጋዊ መብቶችን ተጠቅሞ ወደ መከላከል መግባት፣ የህወሓት ፍጹም አምባገነንነት እንዲያበቃና የአገራችንና የህዝቦቻ ነጻነት እንዲረጋግጥ ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
በእርግጥም ህዝብን በማሸበር ህወሓት ለዓመታት በህዝቦች መብቶችና ህይወት ላይ የሚፈጽማቸው የሽብር ጥቃቶች እንዲያበቁ አስፈላጊዉ ሁሉ ባለመደረጉ ዛሬ ህዝባችን በመከራ ውስጥ መሆኑ ለሁሉም የተሰወረ አይደለም።ትግሉ አሁን የመንግስት ስልጣን ይዘው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ግፍን ከሚፈጽሙ የመንግስት ሽብርተኞች ጋር እንጂ ከህገ መንግስት ጋር አይደለም፤ህግ በትክክል እየተጣሰ ያለው በእነዚህ እኩይ ተግባርን በሚፈጽሙ የህወሓት/ኢህአዴግ በዝባዥ ሥርዓትና የሥርዓቱ መሪዎች ነው፤ ይህንን አስከፊ ሥርዓት ለማስወገድ መነሳት፣ መታገልና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍሎ በድል ማጠናቅቀ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
በሃገራችን የበይ ተመልካች ሆነን መቀጠል ያብቃ፤ጥቂቶች ብዙሃኑን የሚዘርፉበትና የሚጨቁንበት ሊያበቃ ይገባል፤የተወለድንባቸውና ያደግንባቸው ቦታዎች የራሳችን እስር ቤቶች ሊሆኑ አይገባም፤ወታደሩ፣ፖሊሱና የደህንነት ሀይሉ ኢትዮጵያውያንን የሚወክል መሆን ይኖርበታል እንጂ ለጥቂት ዘረኞች ቅጥረኛ ሆኖ የሚያገለገለበት ጊዜ ሊያበቃ ይገባል።
ህወሓት/ኢህአዴግን መታገልና ማስወገድ የተቀዋሚ ፓርቲዎች፣የስቪክ ማህበራት፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ለእውነት የቆሙ ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ሁሉ ትግል ሊሆን ይገባል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ የሚከተሉት ሁኔታዎችን ማየት ይኖርብናል ብዮ አስባለሁ፡-
- ነጻነቱን የተነጠቀዉ ሁሉም መሆኑና ነጻነቱን ማስመለስ የሁሉም መሆኑ፤ ስለሆነም ትግሉም የሁሉንም ተሳትፎና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም በመረጠዉ የትግል መንገድ ወደ ትግሉ መቀላቀል ይጠበቅበታል።ድልን የሚጠብቅ ሁሉ የትግሉም አካል ሊሆን ይገባል፤
- የህዝቦች መቀራረብና በጋራ ጠላት ላይ የጋራ ትግልን ማፋጠን ለነገ የማይባል መሆኑ፤
- የተማሩና የህዝባቸው ሮሮ የሚሰማቸው ሁሉ ዛሬ ህዝቡ የሚፈልጋቸው በመሆኑ ያስተማራቸውን ህዝብ ለማገልግል የሚቆርጡበት ጊዜ መሆኑ፤
- የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነቶችን በማጥበብና ለትዉልዱ በማሰብ በጋራ ጠላት ላይ በጋራ መነሳት መቻልና ለህዝቡ የትግል ፍላጎት መዳረሻ ሊሆኑና ሊያታግሉ ይገባል፤
- የስቪክ ማህበራትም ያላቸዉን ትስስር በማጠናከር ትግሉን ማገዝ ይኖርባቸዋል፤
- አዲሱ ትውልድም ለራሱ ሲል ወደ ትግሉ መቀላቀል ይኖርብታል፤
- በውጭ የሚገኙም የዚህን ዘረኛና አሸባሪ መንግስታዊ ቡድን ተግባር በማጋለጥና በዲፕሎማሲው ዘርፍ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ በማድረግ ዕርቃኑን ማስቀረትና አገራትና መሪዎቻቸው ከተጨቆነው ህዝብ ጋር እንዲወግኑ ጥረት ማድረግ፤
- በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፣ በስቪክ ማህበራት መካከል፣ በሰብዓዊ ድርጅቶች መካከል በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉት የእርስ በእርስ ግንኙነቱን በአህጉራት መካከልና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጠናከር የህወሓትን የመከፋፈል አቅምን መስበር መቻል፤
- በውጭ ያሉ ምሁራንም የተለያዩ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማበረታታትና ተነሳሽነት መፍጠር፤
- የህወሓት የንግድ ድርጅቶች ምርቶችን ባለመግዛትና የንግድ አገልግሎቶቹን ባለመጠቀም ጭምር የህወሓትን የብዝበዛ መስመሮች መዝጋትና
- ልዩ ልዩ ትግሎችን በሃገር ውስጥና በውጭ ማቀጣጠልና ተግባራዊ ማድረግ ግድ ይላል።
እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም ይህንን ሽብርተኛ ቡድን ከሃገራችንና ከህዝባችን ላይ ማንሳት ይጠበቅብናል።
- 6. ማጠቃለያ
ከላይ ከተዘረዘሩትም ሆኑ ሌሎች በዚህ ጽሑፍ ካልተጠቀሱ የህወሓት/ኢህአዴግ ተግባራት ስንነሳ ግዜው መሰባሰባችንን ይጠይቃል። ከራሳችን ይልቅ ለደሃው ህዝባችን ልናስብና የመከራውን ግዜ ልናሳጥር የሚገባን ሰዓት ላይ ነው ያለነው፤ ስልሆነም አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበናል።
ህወሓት/ኢህአዴግ በሰላማዊ ትግል ላይ ባሉ የሰላማዊ ትግል አራማጅ ፓርቲዎች ላይም ሳይቀር መንግስታዊ ሽብርን ቀጥሏል። ይህንን የፓርቲዎችን ትግል ማገዝና ችግራቸውን መጋራት ለነገ የሚባል ሳይሆን ዛሬ የሚተገበር ተግባር ነዉ። በሩቁ ሆኖ ፓርቲዎቹ ብቻቸውን እንዲታገሉ መፈልግ ትግሉን ይጎዳዋል እንጂ አይጠቅመዉም፤ ስለሆነም ትግሎችን መደገፍና ከውጤት ላይ ማድረስ የሁሉም ተጠቂ ሁሉ ሃላፊነት ነው ።
በመጨረሻም አንድ ነገርን ሳልል አላልፍም ይኽውም ትግሎቻቸን ግቦቻቸውን እውን የሚያደርጉ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችንና አስተሳሰቦችንና ፖሊሲዎቻቸውን ማየት ይኖርባቸዋል ፤ እነዚህም ቢሆኑ የብዙሃኑን ተሳትፎ ይጠይቃሉ ። ይኽንን ያልኩባቸው ምክንያቶችን ለመመልከት ያህል በዓለማችን እንደሚታየው አብዛኞች ትግሎች ግባቸውን እንዲስቱ የሚደረጉበት አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፤ ትግሎች በልዩ ልዩ ምክንያት በድሎቹ ዋዜማና አስቀድሞ የራሳቸው ስውር ግብ ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እጅ በመውደቃቸው ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለባቸው ትግሎች ግቦቻቸውን እየሳቱ ሌሎች ትግሎችን የሚጠይቁበት ሁኔታዎች ታይተዋል።ለምሳሌም በሃገራችን የተደረጉት የተማሪዎች ትግል በደርግ እጅ መውደቅና የኢህአዴግ ትግል በጥቂቶች የህወሓቶች እጅ መውደቁ፣አሁን በአረቡ ዓለም የሚደረጉ ትግሎችንም ስንመለከት ደግሞ እንዲሁ ብዙ መስዋዕትነት ከተከፈለባቸው በኃላ ባልታሰቡና ወይም ያልተጠበቀ ግብ ባላቸው እጅ እየወደቁ ሌላ ተጨማሪ መከራን ሲፈጥሩ ተስተውላል፤ስልሆነም ትግሎች ግቦቻቸውን የሚተገብሩ ሰዎችንና ቡድኖችን ማንነት ማወቅ ይኖርባቸዋል ለዚህም የብዙሃኑ ተሳትፎዎች ወሳኝነት ይኖረቸዋል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።
aberashiferaw.wordpress.com