Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የኛ ነገር፤ ከኔ ማእዘን፤ ክፍል 14 (ከተክለሚካኤል አበበ)

$
0
0

ከተክለሚካኤል አበበ

የግንቦት ሰባት ርእሰ-አንቀጽ
1. ከግንቦት ሰባትና የግንቦት ሰባት አመራር አባላት የማደንቅላቸው ድንቅ ነገር ቢኖር ሌሎችን ያለመተናኮስ ባህርያቸው ነው። ሌሎች ቢተነኩሷቸውም እንኳን፤ ምንም ምላሽ ያለመስጠት አቋማቸውን አደንቅላቸዋለሁ። እስካለፈው ሁለት ሳምንት ድረስ። ባለፈው ሁለት ሳምንት ግን፤ በራሳቸው አነሳሽነት አገር ቤት ያሉትን ድርጅቶች ወደመተንኮስ ያዘነበሉ ይመስላል። በተለይም ሰማያዊ ፓርቲን። ስለዚህም ጥያቄ ተነሳብኝ።
2. ግንቦት ሰባት፤ ነሀሴ መጨረሻ ላይ፤ http://www.ginbot7.org/2013/09/02/በሰማያዊ-ፓርቲ-አባላት-በደረሰው-ወያኔያ/ አንድ ርእሰ አንቀጽ ጽፏል። ርእሰ አንቀጹ የሚቆጣም የሚያላግጥም ይመስላል። ድሮ ልጆች ሆነን አባቶቻችን የሚሉንን አይነት ለዛ አለው። “ሀሳብህ ጥሩ ነው፤ ጥረትህንም እናደንቃለን፤ ነገር ግን ልጅ ስለሆንክ ነው” አይነት ነገር።
3. የኢህአዴግ አገዛዝ የሰማያዊ ፓርቲ ለጠራው ሰልፍ ሲዘጋጁ በነበሩ አባላት ላይ ያደረሰውን ድብደባ ያወገዘው ግማሽ ገጽ ርእሰ አንቀጽ፤ በግማሽ ገጽ ላይ ሰባት ግዜ “ወጣቶች ወጣቶች” እያለ ወርዶ (ትንሽ አጋንኜ ነው እንጂ አምስት ግዜ ብቻ ነው)፤ ወጣቶቹን ተስፋ ለማስቆረጥ የታለም የሚመስል መልእክት ይሰነቅራል። እንዲህ ይላል።

ginbot 7
“ወጣቶች ምን ትላላችሁ? ጥንካሬያችሁን እናደንቃለን፤ ሆኖም የያዛችሁት መንገድ የባላንጣችንን ባህሪይ እግምት ውስጥ ያስገባ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለን። … ባርነትን ትቀበላላችሁ ወይስ አማራጭ የትግል ስልቶችን ለመመርመር ትደፍራላችሁ? ባዶ እጆቻችሁን እያሳያችሁት እየረገጠና እያዋረደ “መንግሥት” ነኝ ብሎ የሚኮፈስ እኩይ ጋጠወጥ ጋር ሰላማዊ ትግል ያዋጣል ትላላችሁ?”
4. ርእሰ አንቀጹ ሀቀኛ አይደለም። ርእሰ አንቀጹ፤ መልሱን ለናንተ እንተወዋለን ቢልም፤ መልሱን ግን ዝቅ ብሎ ይመልሰዋል። መልሱ፤ ባንድ በኩል “የሰላም ትግል ከእኛ ወዲያ አልቆለታል” የሚል መልእክት ያለው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ሁለቱም ተያይዘው ይሄዳሉ” የሚልም ለዛ አለው። አንዱ ያላንዱ፤ ሰላማዊው ከአመጽ፤ የአመጹም ከሰላማዊው ተለይተው ህይወት ይላቸውም ይላል። አንዱ መንገድ ያለሌላው ህይወት ከሌላቸው የራሳቸውን ጠበቅ አድርገው ሌሎቹም የራሳቸውን ጠበቅ እንዲያደርጉ መምከር ሲገባ፤ ወያኔ ከዚህም የከፋ ድብደባና ውርደት ስለሚያከናንባችሁ፤ መንገዳችሁን መርምሩና፤ ዛሬውኑ ወስኑና እኛን ተቀላቀሉ ምን የሚል ግብዣ ነው ያቀረቡት።
Tekele5. እነሱማ ወስነዋል። የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወስነው፤ የለም ጠብመንጃ መሸከም አንችልም፤ ዳገት ቁልቁለቱን መውረድ፤ እሾህና ጋሬጣውን መቋቋም፤ አውሬውንና መከራውን እንደምን መሸከም አይቻለንም፤ መሸከም ብንችልም፤ የትጥቅ ትግል ተገቢ አይደለም ብለው በሰላም፤ ነገር ግን በመጋፈጥ እዚያው አገር ቤት ሊፋለሙ ወስነዋል። ግንቦት ሰባት አንዳቸው ያላንዳቸው ህይወት የላቸውም ካለና፤ የራሱ የመለመላቸው ጫካ የገቡ ሀይሎች ካሉት፤ ለሰላሙ የቆሙትን ደግሞ ባላችሁበት በርቱ ማለት ሲገባው፤ እንደገና ደግሞ ከወያኔ ጋር የሰላማዊ ትግል አያዋጣምና እኛን ተቀላቀሉ ምን የሚሉት ጅልኛ አነጋገር ነው።
6. የዚህ ርእሰ አንቀጽ መንሸዋረሩ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ድግግሞሹም የሚገርም ነው። የዛሬ ዘጠኝ አስር አመት ሰላማዊ ትግል ብቸኛው ምርጥ መንገድ ነው የሚሉት የግንቦት ሰባት መሪዎች ነበሩ። እነ ኢህአፓ አገር ቤት በሰላም የሚታገሉትን ድርጅቶች ወያኔዎች ናቸው ወይም ለወያኔ ህጋዊነት ያሰጡታል እያሉ ሲከሱ ሁሉ ብርሀኑ ነጋ (ዲባቶ) አውሮፓና አሜሪካ መጥቶ በፍጹም ብቸኛው መንገድ ሰላማዊ መንገድ ነው እያለ ይሰብክ ነበር። የዛሬው ርእሰ አንቀጽ ግን ልክ እነሱ ከአገር ሲወጡ የሰላማዊ ትግል ከነሱ አብሮ እንደተሰደደ ነው የሚነግረን። የሰላማዊ ትግል ከነሱ መሰደድ ጋር እንዳበቃለት ይሰብካሉ።
7. እንደኔ እንደኔ አስተያየት፤ የግንቦት ሰባት ርእሰአንቀጽ፤ በሰላም እንታገላለን የሚሉትን ሁሉ እነሱን እንደሚያሳጡ አድርገው ከማሰብ የመነጨ ይመስላል ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ፤ የዛሬው የግንቦት ሰባት አቋም፤ ትናንት እነሱ ቅንጅት በነበሩበት ግዜ፤ ኢህአፓና ወዳጆቹ ሲያራምዱት የነበረውና እነሱ የግንቦት ሰባት ሰዎች ሲዋጉት የነበረው አቋም ነው። ርእሰ አንቀጹ፤ “ያለን ምርጫ ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው ሲል የደነገገልን ማነው?” ብሎ ይጠይቅና፤ ሰላማዊ ትግል ከትጥቅ ትግል በላይ መስዋእትነት ሊያስከፍል እንደሚችል፤ እንደውም ሰላማዊ ትግል ብቻውን ድል ማቀዳጀት እንደሚችል ማረጋገጫ እንደሌላ ይናገራል። እንዲህ ያለው ያልጠራና የተደባለቅ አካሄድ ነው ቀደም ሲልም በቅንጅት ዘመን ድል ያሳጣን።
8. ግንቦት ሰባት የሚያዋጣውን መንገድ መርጦ ከገባ በሁዋላ፤ የሌሎችን መንገድ ባደባባይ መተቸትና መጠየቁ አግባብነቱ አይታየኝም። የራስን የትጥቅ መንገድ መተንተን አንድ ነገር ነው፤ የሌሎችን የሰላም መንገድ ማጣጣል ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ይሄ ርእሰ አንቀጽ፤ ቀደም ሲል ግንቦት ሰባት የተናገረውን፤ በምንም መልኩ ሌሎችን አንነካም የሚል መርህ የሚጣረስም ነው። በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የደረሰውን መከራ ማውገዝ አንድ ነገር ነው። ከዚያ አልፎ ግን ይሄ የደረሰባችሁ ሰላማዊ ትግል የሚባል የፖለቲካ ደዌ ስለአዛችሁ ነው ብሎ በሌሎች መንገድ ላይ መፈትፈትና ማላገጥ ፋይዳው አይታኝም። ስለዚህ ግንቦት ሰባት ርእሰ አንቀጹንም፤ ርእሰ ነገሩንም ይመርምር።
9. በመጨው አርብ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቃለምልልስ ላይና፤ ብርሀኑ ነጋ (ዲባቶ) ጎበዝ የዴሞክራሲ ጊዜ መሪ ስለመሆኑ፤ በምንም መልኩ ግን ውጤታማ የትጥቅ ትግል መሪ ሊሆን ስላለመቻሉ እጽፋለሁ። የማደንቀውና የማከብረው የግንቦት ሰባት ዋና ጸሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ እኔ አምስት ስድስት አመት በተደጋጋሚ የጻፍኩበትን ከኤርትራ በቅርበት የመስራት ነገር ደግፎ መናገሩ ቢያስደስተኝም፤ ያቀረበት መንገድና ትንተናው በጣም የሚዘለዘል ነው። ባለፉት አራት ቀናት በቶሮንቶና ኦታዋ ስለከረመው አቶ ግርማ ሰይፉም ትንሽ እቀዳለሁ። ከአቶ ግርማ ጋር ያደረግነው ይፋ ህዝባዊ ስብሰባ በቪዲዮ ስለተቀዳ፤ ለኢሳት እንልከውና ኢሳት ካልገገመና መልካም ፈቃዱ ከሆነ በኢሳት ትመለከቱታላችሁ። በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ በግልና በቡድን ከአቶ ግርማ ጋር ስለተጫወትናቸው አንኳር ጨዋታዎች እጽፋለሁ። ኢንሽ አላህ አለ ሀሰን ኡመር አብደላ። እግዚአብሄር ያውቃል እንደማለት ነው።
እኛው ነን፤ ከቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ መስከረም፤ 2006/2013


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>