እዚህ አሜሪካ – በሀገረ ማርያም – በጊዚያዊ ቤቴ – ጊዚያዊ በረንዳ
ቆሜ ሳነጣጥር
አየሁኝ መንገድ ዳር – ተገትሮ ያለ የቆሻሻ ገንዳ
ዳቦው እንደ ጉድፍ
ወተቱም እንደ እድፍ
ልብሱም እንደ ቅጠል
በገንዳው ከርስ ውስጥ ይረግፋል እንደ ጠል ::
ያሜሪካ መልኳ
አይደለም ህንፃዋ ሰማይ የሚነድለው
አይደለም መንገዷ – እንደ ቆለኛ ቅል የተወለወለው
አይደለም ፖሊስዋ – ዝሆን የሚያህለው
ያሜሪካ መልኳ ጎልቶ የተሳለው
በገንዳዋ ላይ ነው እመንገድ ዳር ባለው
ባገሬ ሰማይ ስር
ሰው ጠኔ ገፍትሮት ሲውድቅ በመደዳ
ያሜሪካ ንስር
ላንዲት ስኒ ሆዱ በጋን እያስቀዳ
እዚያ ማጣት እዳ
እዚህ ማትረፍ እዳ
እዚያ ባዶ መሶብ
እዚህ ሙሉ ገንዳ
ከእለታት አንድ ቀን
በሰማያት እና በምድሪቱ ድንበር
ከእኛ ጎታ አጠገብ የቆሻሻ ገንዳ ተቀምጦ ነበር
የሰማይ አማልክት አላጋጭ ቀልደኛ
“ራበን መግቡን” ስንላቸው እኛ
ብዙ መና ጋግረው ሲያዘንሙ ከሰማይ
የእኛን ጎታ ስተው ከተቱት ገንዳው ላይ::
ከቶ ለምን ይሆን
ያፍሪቃ ህፃናት በደቦ ሚያልቅሱ
የወተቶች አዋሽ – የርጎ ሚሲሲፒ – በበዛበት ዓለም – ጤዛ የሚልሱ
የሹራብ ተራራ – የቡልኮ ጋራ – በበዛብት ዓለም – ጭጋግ የሚለብሱ
የምድር ጠቢባን
ለዚህ ግዙፍ ምስጢር – መልስ አገኝ ብላችሁ – ጠፈር አታስሱ
አሜሪካ ያለው – የቆሻሻ ገንዳ – ግጣሙ ሲከፈት – ወለል ይላል መልሱ::
- በእውቀቱ ሥዩም (September 16, 2013. Maryland | USA)
↧
ገንዳው –በእውቀቱ ሥዩም (አሜሪካ እንደመጣ የፃፈው)
↧