እንዲህ ዓይነት ርዕስ እንኳን በኔ ጽሑፍ በሌላም የቅርብ ጊዜ ጽሑፍ ገጥሞኝ የሚያውቅ ስለመሆኑ ትዝ አይለኝም፡፡ ይህ ርዕስ በትንሹ ሦስት ነገሮችን ያስታውሰኛል – ዘና እያላችሁ እንድታነቡ ነውና እምፈልግ በቁም ነገሮች ብቻ የታጨቀ መጣጥፍ ልጀባችሁ አልፈልግም፡፡ ከሚታወሱኝ አንዱና ዋናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አያቸው የነበሩና አሁንም ድረስ በስፋት የማያቸው የጥናት ርዕሶች ናቸው – ለምሳሌ እንዲህ ሊገጥማችሁ ይችላል፡- The Vulgarism of Some National and International Article Contributors to the Ethiopian Opposition Websites that Claim to Play a Positive Role in the Emancipation of Ethiopia from the Roguish Ethnocentric Tyranny of Tigray People’s Liberation Front (TPLF): With Specific Reference to the Malignant and Insulting Articles Contributed by so Called Dagmawi Gudu Kassa who is Currently Working at MoFA in Addis Ababa, the Capital of Ethiopia . … ልብ አድርጉ ይህ ዓይነቱ ርዕስ ከ‹አጫጭር› ርዕሶች አንዱ መሆኑ ነው – ሁለተኛው የዱሮ ቤሣ ልቦለዶችን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ርዕስ ልታገኙ ትችላላሁ፡- “ ‹ድሃ ስለሆንኩኝ ጥጋበኛ ሀብታም እኔን በሽመል ነርቶ በማባረር እጮኛየን ቀማኝ አጭር ልቦለድ› – የስም መመሳሰል ቢኖር በአጋጣሚ እንጂ ሆን ብዬ አለመሆኔን በታላቅ ትህትናና አክብሮት እገልጻለሁ፡፡” እነዚህን ዓይነት ርዕሶች በራሳቸው ነጋሪ በመሆናቸው ማን ወደ ውስጥ ገብቶ እንደሚያነባቸው አንድዬና አላህ ይወቁት፡፡ ሦስተኛው ስም አወጣጥ ላይ ነው፡፡ በ‹ቤቶች› ድራማ በምናውቀው ስም ልጀምርላችሁና እውነተኛ ገጠመኜን ላስከትል፡፡ ‹እከደከን ማንችሎት በብልጠት ሆነ በጉልበት ሁሌም ከወንዶች በላይ አበጀ! አበጀ የአባት ስም ነው እንግዲህ፡፡ ሌላውና በቅርብ የማውቀው እውነተኛ የሰው ስም፡- ሺህ ማጫሽ ሺህ መገመቻሽ፣ አባይ በደጅሽ ተከዜ በጅሽ አበጀ – የሚል ነው፤ አሁንም እንደአጋጣሚ ሆኖ አበጀ የአባቷ ስም መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ጊዜ ያላችሁ በርዕስና ስም አወጣጥ ላይ እስኪ ተጨማሪ ጥናት አድርጉና አስነብቡን እባካችሁን፡፡ ለመግቢያ ያህል ይህችን ካልኩ ወደሌላ አንቀጾች ልውረድ፡፡
[ሰበር ወሬ! የዚህ የቅንፍ ወሬ ከምሽት የአምስት ሰዓት የኢሳት ዜና በኋላ የተጨመረ ነው ፤ ቅድም እየጻፍኩ ሳለ እንደሁልጊዜው ሁሉ መብራት ድርግም አለ፡፡ ተናድጄ ወደምሄድበት ሄድኩ፡፡ አሁን ስመለስ ደግሞ መብራት መጥቶ አገኘሁ፡፡ ተመስገን ነው፡፡ በቀን ዘጠኝና አሥር ሰዓት መብራት ማግኘት በራሱ እሰዬው ነው፡፡ በየደቂቃው እኮ ነው ድርግም የሚልብን - እሚጠየቅ አካል የለ፤ ጠያቂ የለ፤ እንዲያው ባጭሩ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የለዬለት ዳፍንት ውስጥ ገብተንላችኋል፡፡ ሥራው በኮረንቲ ላይ የተመረኮዘ ሰው ሁሉ ጉድ ፈልቶበታል፡፡ ለሚደርስበት ኪሣራ ማንን ይጠይቃል? ማንንም! በዚህ ችግር ብቻ ስንቱ ባለድርጅት ሥራውን እየቀነሰ ወይ እየዘጋ ብዙዎች ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው እንደሚሰናበቱ ይነገራል፡፡ ጉዳችን እየተንተከተከ ነው ጎበዝ! እናማላችሁ በአሁኑ ዜና የርዕዮት ዓለሙን የርሀብ አድማ በድጋሚ ከሰማሁ በኋላ ይቺን ቅንፍ መጨመር አሰኘኝ፤ አሰኝቶኝም እንዲቀር አልፈለግሁም፡፡ ያበጠው ይፈንዳ - ኢትዮጵያ በሰላማዊ ትግል ነጻ አትወጣም - እህል ብትተው መኖ ቀነስክላቸው እንጂ ምናቸውም አይጎዳም፡፡ ይህ ዓይነቱን ትግል የምታደርገው አእምሮ ባላቸው በሰለጠኑ መንግሥታትና ሕዝቦች መካከል ነው - እንደኛ ባለው ግዑዛን የመንግሥት ‹ሰዎች› ዘንድ አይደለም፡፡ ምድር ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢሉ ኢትዮጵያ በወያኔ ፈቃድ ነጻ ወጣች ማለት በትንሹ አዜብ ጎላ ሰው ሆነች የማለት ያህል ነው - አዜብ ሰው አይደለችማ! የርሷን የባህር ዳር የድህነት ንግግር ያደመጠ መቼም እሷን ሰው ነች ብሎ የሚቀበል ከሆነ ራሱም ሰው ስለመሆኑ የሀኪም ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል - ይህች ዮዲት ጉዲት ያለችበት ድርጅት አመራር እንዴት ሰው ሆኖ እንደሰውም አስቦ ለሕዝብ ሰቆቃ ቅድሚያ ሊሰጥ ይችላል? እንግባባ - ዋናው ነገር ወያኔ በድርድርና በሰላማዊ ትግል ሥልጣኑን አይለቅም - አራት ነጥብ፡፡ በሙስና በተካበተ የሀብት ባህር የሚዋኙ ሰዎች፣ በሚሊዮኖች የደም ውቅያኖስ ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች፣ በጥላቻና በፀረ-ኢትዮጵያ ልክፍት የተመቱ ሰዎች እንዲህ በቀላሉ ለሰላማዊ ትግል ይንበረከካሉ ብሎ ማሰብ ከጅልነትም በላይ ዕብደት ነው፡፡ ወያኔ ማለት ባልጩት ራስ የማፊያዎች ቡድን ማለት ነው፡፡ ማፊያ እንዲያውም ከወያኔ ይሻላል፡፡ ማፊያ በተወሰነ ደረጃ መደማመጥና መግባባት ያውቃል፡፡ ወያኔ ግን ደነዝና በዘረኝነት የሰከረ የወሮበሎች ጥርቅም ነው፡፡ ወያኔን የማያውቅ ብቻ ነው በሰላማዊ ትግል ታግዬ ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ የሚል፡፡ ለመሆኑ ከአንበሣ መንጋጋ ሥጋን መንጠቅ የሚችል ማን ነው? ዮሤፍ መርሻ ከግብጽ ለምን ተመለሰ? ያኔ በ84 እነየማነና ገነት ግርማ ለምን ከርቸሌ ወረዱ? ፕሮፌሰር አሥራት፣ አሰፋ ማሩ፣ ተስፋሁን ወርቁ፣… ለምን ተገደሉ? ከ22 ዓመታት በላይ የተሞከረው “ሰላማዊ” ትግል የውኃ ሽታ ሆኖ በህልም ደረጃ የቀረውና የነጻነታችን ጥያቄ እየፈጩ ጥሬ እሚሆነው ለምን ሆነና? በሰላማዊ ትግል ለምን ይቀለዳል? ሰላማዊ ትግል ቢሠራ ኖሮ ዳግማዊ ጉዱ ካሣ ሣሪስ በሚገኝ የኪራይ ቤቱ ተደብቆ እንዲህ ይንጨረጨር ነበር ወይ? ለምን ይዋሻል ነው ያለው ያ ራሱ ዋሽቶ ሰውን ውሸታም የሚል ቀልማዳ ባለመድረክ መላ-ያጣ ሰውዬ? ጎበዝ አንወሻሽ! ወያኔ በምንም መንገድ በሰላማዊ ሰልፍ ወደሚሄድበት አይሄድም፡፡ ጊዜያችሁን አታባክኑ፡፡ ዓለም የማን ሆነችና! ዓለም የውሸታሞችና የአስመሳዮች ናት፡፡ ወያኔ በሰላማዊ መንገድ ቢወርድ ኖሮ ከግንቦት 97 ወዲህ የወያኔ ታሪክ ልክ እንደቀዳማዊ ወያኔ ታሪክ በታሪክ መዘክር ብቻ በተወሳ ነበር፡፡ አይ፣ የለም፣ ቀልድ በልክ ሲሆን ያምራል፡፡ እንኳንስ በተበጣጠቀ የከበደና የአምባቸው የተለያዩ ቀናት ሰላማዊ ሰልፎች ይቅርና በተባበረ የሚሊዮኖች ሰልፍም ወያኔ ሥልጣኑን ለድርድር አያቀርብም፡፡ ታዲያ መፍትሔው ምን ሊሆን ነው ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው፡፡ እንደኔ መፍትሔውም ቢሆን ቀላል ነው - ልክ እንደ አሁኑ በዘርና በጎሣ፣ በብሔርና በአገር ልጅነት ተደራጅተው ሲያበቁ ወታደራዊ ሥልጠና በመውሰድ ጎጣዊና ዘውጋዊ ጦር መዝዞ ወያኔን ‹በሚገባው ቋንቋ ማናገር›፣ በሃይማኖትና በንዑሳን የሃይማኖት ክፍሎች(sectarian divisions) እየተዋቀሩ ወያኔን በየዱር ገደሉ ማርበድበድ፣ በፖለቲካ ፓርቲ ረገድም በ33 ቦታ፣ በ66 ቦታ፣ በ99 ቦታ እንዳስፈላጊነቱም ከነዚህም በላይ እየተቧደኑ በሣምንታዊና በወርኃዊ ፕረስ ኮንፈረንሶችና በራሪ ወረቀቶች አማካይነት ወያኔን በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ለቀጣዮቹ 1000 ዓመታት እርቃኑን ማውጣት፣ የት አባቱንስና! ስበሳጭ የመፍትሔ ሃሳብ እንዴት እንደሚዥጎደጎድልኝ አትጠይቁኝ… የቅንፍ ሰበር ወሬ እዚህ ላይ አበቃ፡፡ ቀድሞ ወደተጻፈው እንውረድ፡፡]
- በተለይ በተረገመችዋ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሚሠራ ሰው ሁልጊዜ ይታማል፡፡ ከሞትክና ካልሠራህ አትታማም፡፡ ሥራህ የሚያሳማ ሆኖ ብትታማ፣ የሚያስወቅስ ሆኖ ብትወቀስ መልካም ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን ልትወቀስበት በሚገባህ ትሞገስበታለህ፤ ልትሞገስበት በሚገባህ ደግሞ ትወቀስበታለህ፡፡ የሀገራችን ነገር ግራ አጋቢ ነው፡፡ ለዚህ ነው በርዕሴ ላይ የጠቀስኩትን ነገር የጠቀስኩት፡፡ ብትወፍር ዕዳ ነው፡፡ ብትከሳም ዕዳ ነው፡፡ ባትወፍርም ባትከሳም እንዲሁ ዕዳ ነው፡፡ ዝቅ ብለህ፣ ወደታችኛው የማኅረሰብ ክፍል ወርደህም ይሁን ወጥተህ ሁኔታዎችን ስትታዘብ የምታየው አብዛኛው ያሳዝንሃል፡፡ ብዙ ከመማርና ከማወቅም ይሁን ከተቃራኒው የተነሣ ብዙውን ጊዜ የምትታዘበው ነገር ወዴት እየሄድን ነው ያስብልሃል፡፡ መተማማት – ሲለዩ ቡጭቅ ይባላል – መጨቃጨቅ፣ በረባ ባልረባው መጣላት፣ መከዳዳት፣ በማያገባ እየገቡ በሃሜትና በአሉቧልታ ‹ወርቃማ ጊዜ›ን ማባከን … በጣም የተዘወተረ መሆኑን ትረዳለህ፡፡ ብትወፍር ‹ከየት አባቱ አምጥቶ በላና ተመቸው› ትባላለህ፤ ብትከሳ ‹ያ ነገር ገዝግዞ አሰለሰለው› ትባላለህ፤ ባለህ አቋም ብትገኝ ‹ይሄ ሰው እየበላ እየጠጣ ለውጥ የማያመጣው የገደሉ አይቶት ይሆን ?› ትባላለህ፡፡ በሥራህም አለሥራህም የምትታማበት ሀገር ቢኖር የአፍሪካ ቀንድ ነው – ሊያውም ኢትዮጵያ፡፡ ሰው የተጠመደው በሥራ ሳይሆን በወሬ ነው ብለህ እስክታምን ብዙዎቻችን በዚህ አጥፊ መንገድ እየተመምን እንገኛለን፡፡ ጥቂቶች እየሠሩ ሚሊዮኖችን የሚያኖሩባት ሀገር – ኢትዮጵያ፡፡ ሁላችን ብንሠራ የት እንደርስ ነበር?
- ዛሬ ጧት ኢሳትን የተመለከትኩት በልቅሶ እየተነፋረቅሁ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ተወልደ በየነ የሚያቀርበው የመዝናኛና የማስተማሪያ ‹የጥበብ ቃና› እሚባለው ዝግጅት ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅቱ የቀረበው ታማኝ በየነ በጥላሁን ገሠሠ የህመምና የጥበብ ሕይወት ዙሪያ ያሰናዳው በትዝታ ማዕበል የሚያላጋ ግሩም ዝግጅት ነው፡፡ ይህን ፕሮግራም ስመለከት ሰሞኑን ያነበብኳቸው የድረ ገጽ ጽሑፎች ትዝ አሉኝና በተለይ በኢሳት ላይ የሚደረጉ ዓላማቸው ያልገባኝ ዘመቻዎች ላይ እኔም አንዳች ነገር መናገር አለብኝ ብዬ ተነሳሁ፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ ሆኖ አለመፈጠር ምን ያህል ፀጋ ነው ጎበዝ! ‹ያውጡብሽ እምቢ፣ ያግቡብሽ እምቢ› ዓይነት ጉራማይሌ ዘመን፡፡ ይህን ብቻ ብዬ አላበቃም፡፡
- ኢሳትን ሰዎች ለምን ጠምደው ያዙት? ይህን ብርቅዬ የሀገር ልጅ ታማኝ በየነን ለምንድን ነው ሰዎች እንደወገብ ቅማል ሰቅዘው የያዙት? ግራ እሚያጋባ ነው ነገሩ፤ ለእኔ ግራ ገባኝ፡፡ ለነገሩ ግራ አያጋባም፡፡ በበኩሌ ቀናሁ፡፡ ምነው እኔም እንደታማኝ አንዳች ነገር ሠርቼ ሰዎች ትኩር ጥምድ አድርገው በያዙኝ አልኩና እውነቴን ነው ለመግለጽ ቃል እስኪጠፋኝ ድረስ በጣም ስቅስቅ ብዬ ቀናሁ፡፡ በኢትዮጵያ ከሠራህ ትወነጀላለህ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብን የሚያነቃቃ (የሚያነቃንቅ?) ነገር ከሠራህ ትጠመዳለህ ማለት ነው፡፡ ‹በእግርዎ ገብቼ በራስጌ ብወጣ፤ ከትርንጎ በቀር የለብሁም ጣጣ› ያሉት ሼህ ማን ነበሩ? አዎ፤ በኢሳትና በታማኝ እግር ገብቼ በጭንቅላታቸው በኩል ብወጣ ሰዎችን እንዲህ ሊያንጨረጭር የሚችል አናዳጅ ነገር አጣሁ – መቼስ ኢቲቪን ትቼ እዚያው ተጎልቼ ነው እምውልና ስተኛ ወይም ሥራ ላይ ስሆን ካላመለጠኝ በስተቀር ኢሳትና ታማኝ ይህን ያህል ሀገርን የሚያናውጥ መጥፎ ድርጊት ፈጽመዋል ወይም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጨራርስ ዐዋጅ አስነግረዋል ለማለት የሚያስችል አጋጣሚ አጣሁ – ባገኝባቸው ከኔም በላይ ተሳዳቢ ላሳር ነው ብዬ የምታበይ ነኝና በወረድኩባቸው – በዚህችስ ማንም አይስተካከለኝ – ዱሮውንስ ሰው በስንቱ ይበደላል – ከሥልጣን ሥልጣን የለኝ – ከሀገር ሀገር የለኝ – ከሀብት ሀብት የለኝ – በድራቦሹ ታዲያ የመሳደብ ችሎታም ልጣ? … ነገር ግን በሌላ አቅጣጫ ስናይ አናዳጅ ነገር ምን ማለት ነው? አናዳጅ ነገር ሲባል በወርድና በቁመት ተለይቶ ሊታወቅ ይችላል ወይ? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ሁሉንም የሚያስማማ የወል መደላድል ላይ መድረስ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ ለኔ የሚያስደስትኝ ነገር አንተን ሊያናድድ ከቻለ የተለያየንበት ነገር ተፈጥሯል ማለት ነውና ቁጭ ብለን መነጋገር ይኖርብናል ማለት ነው – መነጋገራችን ጥቅም ካለው – ከሌለው ግን እልህን፣ ጊዜንና እንዳስፈላጊነቱም ስድብንና ዘለፋን በማይሆን ዒላማ ላይ በከንቱ ማባከን ነው ትርፉ፡፡ ከዘመድህ ጋር ብትወቃቀስ ተገቢ ነው – በማከያው ትታረቅና ትስማማለህ፡፡ ልትግባባው ከማትችለውና ዐይንና ናጫ ከሆንከው ሰው ጋር መናቆር ግን ኪሣራ እንጂ ትርፍ የለውምና አይመከርም – በግዕዝ ‹ኢይጥዕም መዓር ለአድግ ዘእንበለ እንጉስታር› ይባላል፡፡ አንድ ሰው የሚጥመውን ነገር ቀድሞ ከወሰነና ከውሳኔው ውጪ ምንም ነገር ላይጥመው ምሎ ከተገዘተ ያ ሰው እጅግ አስቸጋሪ ነው፤ ከዚያ ዓይነቱ ሰው ጋር በፍጹም መግባባት ቀርቶ በቅጡ አለመግባባትም እንኳን ላትችል ትችላለህ – በአለመግባባታቸው የሚግባቡ ብፁዓን ናቸውና፤ ሊያጠፋህስ ቢችል ምን ይውጥሃል? በመሠረቱ ዓለማችን የተሞላችው በዚህ ዓይነቱ የተቃርኖዎች ተቃርኖ ነው – አንዳንዱ የተቃርኖ ተቃርኖ ግን የጅል ፍቅር ሆድ ይገትር ዓይነት ከተፈጥሯዊ የግጭቶች ሂደት ወጣ ያለ ነው – እምልክ – ለምሳሌ ሴትና ወንድ አብሮ ቢተኛ ተፈጥሯዊ መሳሳብና ያን መሳሳብም ተከትሎ የሚከሰት ብዙ ነገር አለ፤ ሴትና ሴት ወይም ወንድና ወንድ ቢተኙስ? ዝርዝር ውስጥ መግባት አይገባም፤ ከግትርና መንቻካ ሰው ጋር የመከራከር ሂደት እንግዲህ ከሁለተኛው የምሳሌየ ነጥብ ጋር የሚገናኝ ትርጉም የለሽ ልፋት ነው ማለት ነው፡፡ በመሠረቱ ይህች ዓለም በ‹binary opposition and polarization› ከአፍ እስከ ገደፏ ጢም ብላ ሞልታ በምትገኝበት በአሁኑ ሁኔታዋ እኔ የምወደውን ሌላው ሰው ሁሉ በግድ ይውደድልኝ ብሎ መሟገት ወይ መጠበቅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እንዲያማ ባይሆን ኖሮ የአንዲት ሀገር የሦርያ ዜጎች እንዲህ ዓለምን ጉድ ባሰኘ አሣፋሪ ሁኔታ በኬሚካል መሣሪያ ሳይቀር ሊጨራረሱ ባልቆረጡና ባልተገባቸውም ነበር፡፡ እዚህ እኛው ጋ መለስን በክፉ ስታነሳበት እሚያለቅስና ጦር እሚመዝብህ አለ፤ መንግሥቱን በበጎ ስታነሳበት ጩቤ ሊሰካብህ የሚያሯሩጥህ አለ – በደስታ ጮቤ እሚረግጥም ሞልቷል፤ አፄ ቴዎድሮስን በጥሩ ስታነሳ ገደል ግባ የሚልህ አለ፤ አፄ ዮሐንስን ካማህበት በቴስታ የሚያጋጭህ አለ፡፡ የዚህ ሁሉ መሠረት የዓላማና የጥቅም መለያየት መሆኑ ባይካድም መነሻው እውነትነት አለው ማለት ግን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለምን ቢባል እውነት ከጥቅምና ከቡድናዊ የጋራ ዓላማ በእጅጉ ትለያለችና፡፡…
- ባለፈው ሰሞን ሰይጣን አነሳስቶ ባስጀመረኝና እኔው በጨረስኩት አንድ መጣጥፍ ብዙ ሰው አስከፍቻለሁ፡፡ እኔ የምጽፈው በመሠረቱ ሰውን ለማስከፋትም ሆነ ለማስደሰት አይደለም፤ ስትጽፍ የሆነ መንፈስ ይመጣብሃል ወይም ይመጣልሃል፤ ያ መንፈስ ሳትወድ በግድህ በምትዘባርቀው ነገር አንዱን ልታስከፋ ሌላውን ልታስደስት ትችላለህ – ይህ ደግሞ የሚጠበቅ ነው፤ ሰዎች ዘንድ ልዩነት አይጠፋምና ልዩነቶችን በቀናነትና በገራምነት ለማቻቻል ወይንም ለመረዳዳት መሞከር ብልህነት ነው – ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ጥሩ አይደለም፤ ዛሬን የሚሳሳት ሁሌ እንደተሳሳተ አይኖርምና አንድ ቀን ወደፊት ወይም በቅርብ እንደሚመለስ ማመን ይኖርብናል – ጠላ እምትጠምቅ ሴት ሁልጊዜ ለሁሉም እኩል የሚጥም ጠላ መጥመቅ አይቻላትም፤ ያኔ ታዲያ ብዙም ሳይከፉና ሳይቆጡ እንደ አለቃ ገ/ሃና ‹አይ አንቺ ሴት፣ ዛሬስ ምነው አይጥም ጠላሽ!› ብሎ ቀልዶ ማለፍ ነው፡፡ እኔ እውነት የመሰለኝን እጽፋለሁ፡፡ የምጽፈው ደግሞ ከስሜት እንጂ ከእውነት ብቻ እንዲሆን አይጠበቅም – መጣጥፍ እንጂ የጥናትና ምርምር ዘገባ አይደለምና፡፡ የሀገር ጉዳይ ደግሞ ይበልጡን የሚቆራኘው ከስሜት እንጂ ከእውነት ብቻ አይመስለኝም፡፡ ስሜትና እውነት ደግሞ ለየቅል ናቸው፡፡ በዚያ ልጅ ላይ የጻፍኩት ተናድጄበት እንጂ ግንቦት ሰባትን ወድጄው አይደለም፡፡ ግንቦት ሰባትንም ብወደው የግሌ ጉዳይ ነው፡፡ ማንም ሊከለክለኝ ወይም ሊፈቅድልኝ የማይችል ነገር ነው፡፡ አንዳንዶች በመጣጥፉ አስተያየት መስጫ ላይ እንዳሉኝ ግንቦት ሰባትን አዝየው ብዞር የኔ የግል ጉዳይ ነው – ዋናው ነገር ግን እንዳዝለው የሚያሳምነኝ በቂ ምክንያት የመገኘቱና የት አግኝቼም ላዝለው እንደምችል ማወቁ ነው፡፡ በተረፈ ግንቦት ሰባት ይሁን ጳጉሜ ስምንት የሚያስወድዳቸው ነገር ካለና ቢወደዱ ምን አለበት? የብዔልዘቡል መለያ ከሆኑት ቁጥሮች መካከል 11 ቁጥርን በማፍቀር የሚከንፉለት አሉ አይደለምን? ቀልዱ በቀልድነት ይቀመጥና የሀገራችን ጉዳይ ግን እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተገንዝቤያለሁ፡፡ … ሆዳችንን ግን ሰፋ እናድርግ ጎበዝ!
- ግንቦት ሰባት ለምን ይጠላል? እንዲህ በአንዳንዶች ክፉኛ እንዲጠላ ያደረገውና እኔንም በደራሽ ወንዝ አስተኔ አጣልፎ የግንቦት ሰባት ፍቅረኛ እንደሆንኩ ያስመሰለብኝ ምክንያት ምን ይሆን? ይህ ድርጅት እየሠራው ያለው አንዳች ጠቃሚ ነገር ይኖር ይሆን ወይንስ ሌላ ይህን ታዳጊ ድርጅት እንደማይወዱት በሚነገርላቸው ወገኖች አካባቢ የተደበቀና ለእንደኔ ዓይነቱ ሞኝ ዜጋ ያልተገለጠ አንዳች አጀንዳ ይኖር ይሆን? አንዱ የማውቀው ጸሐፊማ ትናንት ባወጣው አንድ ጽሑፉ ታማኝን በትልቅዬ ውሃ እማያሰኝ ብዕር ሲወግረው ሳይ ‹እንዴ! እንታይ ኢዩ ጉዱ?› አልኩና በጣም ተረበሽኩ፡፡ እነዚህን ሰዎች(እነታማኝን) አላውቃቸውም ማለት ነው? አልኩ፡፡ ታማኝ በርግጥም የትግራይን ሕዝብ በነቂስ ወይ በጅምላ በዕንቁላል ሻጭነት ፈርጆ ከሆነ እኔም በግማሽ ትግሬ በመሆኔ በቁማችን ገድሎናል ማለት ነውና የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ግን አይመስለኝም፡፡ ልጁ ትሁት መሆኑን እረዳለሁና ይቺ ከዐረፍተ ነገር እንደደሮ ብልት እየተገነጠለች የምትወሰድ ነገር ተቃጥታበታለች ማለት ነው – ሰዎች ስንባል የምንጠላውን ሰው በቃላት እሩምታ ድባቅ ለመምታት በማቀድ ምን ያህል ወንጀል ልንሠራ እንደምንችል ሳስበው ይገርመኛል – እንዲህ ስል እኔንም ጨምሮ ነው ታዲያ፤ ከዚያች ቆረጥ እዚያች ላይ ወስደን ለጠፍ እናደርግና ሰውዬው ማለት ያልፈለገውን ወይም ጭራሽ ያላሰበውን እንደተናገረ አስመስለን በሰዎች ዘንድ እናሳጣዋለን – ክፋት ነው፤ ሰይጣናዊነትና ወንጀልም ነው፡፡ Dearest fellow Ethiopians [who are soaked in such nasty game of distortion], please let us begin to be genuine and let us stop harassing words and phrases by detaching them from their context and applying them for the enhancement of an insincere intention to harm innocent people; let us resort to other plausible mechanisms and deploy them to our offensive side if we are overzealously keen to smear the names on our black list. Misusing the meanings of words out of their original context is an abuse of moral principles and it is satanic as well. በዚህ ቃልን በመገነጣጠልና ለሸረኛ ዓላማ ሲባል ከዐውዳቸው ውጪ በማዋል ረገድ ብዙዎች ለጥቃት ዒላማ ሲዳረጉ ይስተዋላል – ፕሮፌሰር መስፍን በዚያ የፋብሪካ ዕቃ ነው ምርት ብለው በተናገሩት ስንትና ስንት ተብለዋል፤ በ97 የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አቶ በድሩ አደም እንዲሁ ተቦጫጭቀዋል፡፡ ይህ የተንኮል አካሄድ ይቅርብን please!
- እውነቴን ነው የምለው አንዱ የምር ወዳጄ በኔ የግንቦት ሰባትና መሪው ዶር. ብርሃኑ ‹ጠበቃነት› ምክንያት ግራ መጋባቱን፣ ከእንግዲህ ማንን ማመን እንደሚቻልም ውዥንብር ውስጥ መግባቱን በአንድ ወዳጄ አማካይነት ስረዳ እኔም ለተወሰነ ጊዜ ግራ ተጋባሁ፤ ዓላማየ ያ ወጣት ብዕሩን እንዲገራ ሆኖ ሳለ ለካንስ ሰዎች ባላሰብኩት መንገድ ተረድተውኛል ማለት ነው፡፡ እኔ በመሠረቱ ተክሌን የተቃወምኩት አካሄዱን እንጂ ተቃውሞውን አልነበረም – እዚያም ላይ ገልጫለሁ – ‹መቃወምን እኔ ቀርቼ ማንም ምድራዊ ኃይል አይከለክለውም› ብያለሁ፡፡ ምናልባት በአነጋገሬ ከራርነት ተክሌን አስቀይሜው ከሆነ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ የግንቦት ሰባትን ገመና ለመሸፈን ወይም ከአግባብ ውጪ ለመደገፍ ያደረግሁት ጥረት ግን በጭራሽ የለም እላለሁ፡፡ በተቃዋሚዎች ጎራ በትግል ሥልት ረገድ ልዩነት መኖሩን አውቃለሁ፡፡ አንድ ሰው ወደሂልተን ለመሄድ ፈልጎ ወደዚያ ከሚወስዱ መንገዶች መምረጥ ቢፈልግ የምርጫው ጉዳይ የራሱ የግሉ ብቻ ይመስለኛል፡፡ በአየር ዘልዬ እደርሳለሁ፤ በመሬት ውስጥ ለውስጥ ቆፍሬ በዋሻ ውስጥ ተጉዤ እደርሳለሁ፤ በሌላ ረጂም አቋራጭ ተሹለክልኬ እደርሳለሁ… ብሎ ራሱ ይመርጣል እንጂ እኔ በፈቀድኩልህ መንገድ ብቻ ወደሂልተን ተጉዘህ ካልደረስክ መንገድህም የመንገድህ ውጤትም ዜሮ ነው ቢባል እንደ አካሄድ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ የ‹የትም ፍቺው ዱቄቱን አምጪው› ይትባሃላዊ የመፍትሄ ፍለጋ መንገድ ጭፍን ተከታይ እንዳይደለሁ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ I would rather prefer the means to justify the end instead of the end to justify the means. ይሁንና ለወጣት ድርጅት ጊዜ መስጠት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ እኔ ደግሞ ብዙ የማውቀው ነገር የለኝም – አውቃለሁ ብዬ ብገምትም እንኳን በደምባራ ብዕር ብዙ የማይገባኝን (የማያገባኝን አላልኩም!) የፖለቲካ አካሄድ እየዘነኮርኩ አንባቢን የማደናበር ፍላጎት እንዲኖረኝ አልሻም፡፡ ዘመን እየተለወጠ ነው – ታሪካዊ ጠባሳዎችና ጨፍጋጋ ሥነ ልቦናዊ ዳራዎች በዘመኑ ፖለቲካ ላይ ምን ያህል አሉታዊ ጥላቸውን እንደሚያጠሉ ለመረዳት በትንሹ ዝምታንና ትዕግስትን እንደሚጠይቁ እንዲሁ በመንፈስ ይገባኛል፡፡ ለነገሩ ማንም ጮኸ አልጮኸ ሁሉም በመሰለው እየታገለ ባለበት ሁኔታ ትርፉ ትዝብት ማትረፍ እንጂ በዚህ ሂድ በዚያ አትሂድ ብሎ ምክርም ሆነ ተግሣፅ መስጠቱ የሚያዛልቅና ትርጉም ያለውም አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ነጥብ አንጻር ስለእንትና ይህን መናገርህ ወይ አለመናገርህ ጥሩ ነው ወይ ጥሩ አይደለም ማለቱና በፍሬፈርስኪ ነገር መበሳጨቱ ያንኑ ያህል ብዙ ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡ በበኩሌ ስለሚባለው ሁሉ ተጨባጭ ነገር ባውቅ ኖሮ ብዙ በጮሁ – በዚያ ላይ በመታገያ ሰነዱ ላይ ‹ማንኛውንም ዘዴ ተጠቅሜ አምባገነኑን የወያኔ ሥርዓት እጥላለሁ› ብሎ የተነሣን ድርጅት ባይሆን እሱም በለስ ቀንቶት ሥልጣን ሲይዝ ልቡን ያራራልንና የምንናፍቀውን ዴሞክራሲ ያጎናጽፈን ብሎ ከመጸለይ ውጪ የትግል ሥልት ምርጫህ ተሞክሮ የከሸፈ ነው እያሉ ከወዲሁ ማጣጣል ከሁሉም ሳይሆኑ የመቅረት ያህል ተስፋ አስቆራጭ ይመስለኛል – የግንቦት ሰባት መንገድ መጥፎ ሊሆን ይችላል – ግን በማን ዐይን? ከሰሜን የመጣ ዝናብ ሁሉ አጥፊ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ ወገኖች እንደሚኖሩ ባውቅም ገሣ ቢጤ ለመግዛት መጣር እንጂ በአድማስ ክልል ውስጥ ባልታዬ ችግር ያን ያህል መሸበርም ለጊዜው የሚገባን አይመስለኝም – ቢያንስ እኔ ልሸበር አልፈልግም፡፡ … ብዙዎች ሲጮሁ ግንቦት ሰባት ዝም ማለቱ ግን ብዙም እንዳላስደሰተኝ በዚች አጋጣሚ መጠቆም እወዳለሁ፡፡ ያቺ የኢሕአፓ የብረት ዲስፕሊን ወይም የእባብን ያዬ በልጥ በረዬ ዓይነቷ ነገር ለፀጥታው መስፈንና ለምሥጢሮች መጠንከር አስተዋፅዖ ሳያደርጉ እንዳልቀሩ እገምታለሁ – ዝምታ ደግሞ ሰውን ይረብሻል፤ ያኔ መጯጯህ ቢበዛ አይገርምም፤ እንደኔ ችግሩ ያ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ሁሉም ከልኩ አይዘልም፡፡ ግንቦት ሰባት ምን ያህል ለጦርነት ቢሰናዳና ወያኔን በ‹ሚያውቀው ቋንቋ ለማነጋገር ቢዘጋጅ›፣ ፀረ-ግንቦት ሰባቶችም የፈለጉትን ያህል ቢያብጠለጥሉትና በቃላት እሩምታ ቢዋጉትም የታሪክ ሂደት እንደሆነ ከላይ በተወሰነለት ጊዜና ከታች በተመደበለት የሰውና የማቴሪያል ኃይል መጓዙ፣ የመጨረሻውን የወያኔ ግብአተ መሬትም በቅርቡ ማየታችን የማይቀር ነው፡፡ ትዝብት እንዳናተርፍ ግን ሁላችንም ብዙ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ ባላልፍ ደስ ስለሚለኝ ነው እንዲህና እንደሚከተለው የምለው፡፡
- አንድ ገበሬ እርሻ ውሎ ሲመጣ ዛፍ ላይ የነበረች አንዲት ጦጣ ‹ገበሬ፣ ምን ዘርተህ መጣህ?› ብላ ትጠይቀዋለች፡፡ ገበሬውም ምኑ ሞኝ የዘራው ባቄላ መሆኑን ልቡ እያወቀ ‹ ተልባ!› ይላታል – እሷ የማትለቅመውን የሰብል ዓይነት መርጦ ማለት ነው፡፡ እርሷስ ብልጥ አይደለች? – ‹ ወርደን እናየዋለና!› ትለዋለች፡፡ እንግዲህ ‹ቂጣም ከሆነ ይጠፋል፤ ሽልም ከሆነ ይገፋል› ነውና ሰሞኑን እየሰማነው ያለነው ነገር የምር ከሆነ ‹ወርደን የምናየው› ይሆናል፡፡ እንደኔ እንደኔ ግን ሁላችንም የአንዲት ሀገር ልጆች እንጂ ባዕዳን ስላልሆንን – አሁንም ልድገመውና – በከንቱ አንጠላላ፤ በከንቱ አንጠላለፍ፡፡ ዘርን መሠረት ያደረገ ወይም ሌላ ሥልጣንንና ጥቅምን መነሻ ያደረገ ጥላቻ ወይ ሥጋት ካለብን ያን በምክክር ለማስወገድ እንሞክር፡፡ መረጃን በመሸቀብ የምንታወቅ ድርጅቶችም ሆንን ግለሰቦች በወቅቱ ተገቢውንና በሕዝብ ዘንድ ቢደርስ ለክፉ የማይሰጥ መረጃን እንስጥ – እርግጥ ነው – ሁሉም መረጃ አይዘከዘክም – ይህንንም በጨዋነት ማስረዳት ይቻላል፡፡ በፍርሃትና በሥጋት የተቀነበበ እጅግ የጠነነ ምሥጢራዊነት ለምሥጢራውያን ዓለም አቀፋዊ የጥፋት ድርጅቶቸም አልበጀም፡፡ ይሄውና ከ500 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ያከማቹት ሀብትና ንብረት የዓለምን ቅርጽ እነሱ በፈለጉት መጠን ሊያስገኝ አልቻለም፡፡ ጥፋት ላይ ጥፋት እየተደረበ፣ ምሥጢር ላይ ምሥጢር እየተደረበ፣ ገብጋባነት ላይ ገብጋባነት እየተደረበ በተደረገው የምዕተ ዓመታት ጉዞ … የዓለም ምጽዓት ቀረበ እንጂ … የዓለም አንጡራ ሀብት በጥቂቶች እየተግበሰበሰ በባንኮቻቸውና ጎተራዎቻቸው ውስጥ አላግባብ ሲከማች በሌላ ወገን ግን ቢሊዮኖች እጅግ ለሚያማቅቅ ድህነት ተዳረጉ እንጂ… ዓለማችን የጅምላ ጨራሽ ጦር መሣሪያ መሞከሪያ ሆነች እንጂ፣ … ምንም እንኳ የሰው ልጅ ጨረቃንና ሕዋን ቢዳስስም ጉንፋንን እንኳ ማሸነፍ አቅቶት ይሄውና አጠቃላይ ዕልቂቱን እየተጠባበቀ ነው፡፡ ሰው በወደደው ይቆርባልና በሠራነው ልንጠፋ የቀረን በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፡፡ እመኑኝ፡፡ የምታውቁትን ስነግራችሁ አትዘባበቱ፡፡ የኛ ቀን ግን ይመጣል፡፡ ከንፍሮ ጥሬ የሚያወጣ አምላክ ሀገረ ኢትዮጵያን የሰው ዘር መሸሻ ሳያደርጋት አይቀርምና ይልቁንስ ከእስካሁኑ ስህተታችን እንማር፡፡
- እናም ምቀኝነታችንን አሁኑኑ እንተው – በአንዴ ልንተው ባይቻለን እየቀነስነው እንሂድ፤ መተሳሰባችንን እንመልስ – የሚሻለን እርሱ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ገንዘብ ለማግኘት ሲል በተለይ ወጣቱ ትውልድ አቅሉን ስቶ እየተራወጠ ነው – በህጋዊ መንገድ ሠርቶ እንዲያልፍለት ቢተጋ እሰዬው ነው፡፡ ግን ብዙው ዜጋ የሰው ሥጋ የመጋጥ ያህል በህገወጥ ንግዶችና በስንጥቅ ትርፍ የድሃውን ገንዘብ እየቀማ ኢትዮጵያ ለአንዱ ገነት ለሌላው ሲዖል እየሆነች ነው፡፡ መተያየትና መተሳሰብ ቀርቷል፡፡ ኑሮው በየቀኑ እያሻቀበ አብዛኛው ዜጋ በመኖርና ባለመኖር የሕይወት ውጣ ውረድ ተወጥሮ ይገኛል፡፡ ዱሮ ለበዓል በግና ዶሮ ይገዛ እንዲሁም ቅርጫ ይገባ የነበረ ዜጋ ዛሬ የዶሮና የዕንቁላል ስዕልም መግዛት የሚያስችል ገንዘብ የለውም፡፡ የገንዘቡ የመግዛት አቅምም ላሽቆ አንድ መቶ ብር እንደክፍልፋይ ሣንቲም የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፤ አንዳንድ ዜጎች ግን ብሩን ከጓሮ ባህር ዛፍ ይሸመጥጡት ወይም ከቻይና በኮንቴነር ያስመጡት እስኪመስል ድረስ ሲመነዝሩት ሲታዩ ለጉድ ነው፡፡ የስሙኒ ዶሮ 200 ብር፣ የስሙኒ ቤንዚን ሃያ ብር፣ የስሙኒ ቢራ ሃያና ሠላሳ ብር፣ የስሙኒ ቲማቲም 30 ብር፣ የስሙኒ የሉካንዳ ቤት ሥጋ 150 ብር፣ የስሙኒ ዕንቁላል 100 ብር፤ የስሙኒ የምግብ ቅቤ 200 ብር፣ የስሙኒ ጋዝ 15 ብር፣ የስሙኒ ክትፎ 100 ብር፣ የስሙኒ ቀይ ወጥ 70 ብር፣ የስሙኒ የምግብ ዘይት 80 ብር(ሃቱም የሚሉት)፣ የስሙኒ ታክሲ አሥር ብር፣ የስሙኒ ባለ18 ካራት ወርቅ 300 ብር(ማነጻጸሪያየ ግራም ሳይሆን ስሙኒ መሆኑን ልብ አድርጉልኝ) …. ይህ ሁሉ ውርጅብኝ በሀገር የታወጀው በእኛ ስግብግብነትና ከፈጣሪ ትዕዛዛት መውጣት እንጂ ሀገራችን የጎደላት ነገር የለም፡፡ ፈጣሪ ፊቱን ቢመልስልን የአንድ ላም ወተት ለሀገር የሚበቃበትን ጊዜ ለማየት የማንችልበት ምክንያት የለም፡፡ …
- ወያኔን ለማስወገድ ከመነሳታችን በፊት ከላያችን ላይ ገፍፈን መጣል ያለብን ብዙ ደካማ ጎኖች አሉብን – በግለሰብም በማኅበረሰብም ደረጃ፡፡ አንድ ሕዝብ ከሚገባው በታችም ሆነ በላይ መንግሥት አያገኝም የሚባለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አባባል እውነት መሆኑን የምናረጋግጥባቸው በርካታ ምልክቶች በሀገራችን በስፋት ይታያሉና እነሱን ከሁሉም በፊት ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፡- ‹በራስህ ዐይን ውስጥ የሚገኘውን ዕርፍ እሚያህል ጉድፍ ሳታወጣ በጓደኛህ ዐይን ውስጥ የሚገኘውን ስንጥር እሚያህል ጉድፍ ለማውጣት አትሞክር›፡፡ ከመጠን ባለፈ ጥላቻ የተጠማመድን ዜጎች ሞልተናል፤ የምንጠላው ሰው ምንም ዓይነት መልካም ነገር ቢያደርግ የማይጥመን ዜጎች በሚሊዮን እንቆጠራለን፡፡ ጥላቻን በፍቅር ካልለወጥነው ባለንበት እየረገጥን አንዱን ወያኔ ሸኝተን ሌላውን ወያኔ እንቀበላለን እንጂ የምንመኘውን መልካም አስተዳደር አናገኝም፡፡ ጥላቻ ለብዙ ነገሮች እንቅፋት ነው፡፡ ጥላቻ በፈረንጅኛው arrogance, ignorance, bias, prejudice … ከምንላቸው የኔጌቲቭ ኢነርጂ ምድብ የሚወለድ የዕድገት ፀር ነው፡፡ የሰው ልጅ ከአካላዊ የሦስተኛ ዳይሜንሽን ኑባሬው ወደመንፈሣዊ ልዕልናው እንዳያቀና የዕድገቱ ፀር የሆኑትን እነዚህን ደንቃራዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ያሸነፈ አንድ ሰው ነበር – በ33 ዓመቱ ገደሉት፡፡ ገዳዮቹም አልተጠቀሙም ፤ እኛም በተጨናገፈው ዕድገታችን ምክንያት ተጎዳን፡፡ ከዚያ ሰው ኅልፈት በኋላ በተለያዬ ጊዜና ዘመን የመጡ ጥቂት ብፁዓንና ንዑዳን ሰዎች ቢኖሩም የፖለቲካ ሥልጣንና የሀብት ጉጉት በማረካቸው የሰው ልጆች አሰናካይነት ምክንያት መልካም ምኞታቸው ሳይሳካና ወደሚገባቸው የአመራር ደረጃም ሳይወጡ በአጭር ተቀጭተዋል ወይም ሃሳባቸው ተቀባይነት ሳያገኝና ዳር ሳይደርስ ወደሌላው ዓለም አልፈዋል፡፡ እነ ማኅተመ ጋንዲ፣ እማሆይ ተሬዛና ኔልሰን ማንዴላ በዚህ የብርቅዬ ዜጎች ማዕቀፍ ውስጥ ይካተታሉ፡፡
ወያኔን ለማስወገድ በቅደሚያ ከወያኔ በኋላ እንዲመጣ ለሚፈለገው ማኅበራዊ ሥርዓት ዝግጁ የሆነ ስብዕናን መላበስ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ አሮጌውን ወይን በአዲስ አቅማዳ እንደመጨመር ዓይነት ይሆንና አዲሱ አቅማዳ በአሮጌው ወይን ተቦጫጭቆ ከጥቅም ውጪ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ወጡ ሳይወጠወጥ በስደትም ሆነ በሀገር ቤት ውስጥ በሚገኙ ተቃዋሚዎች ዘንድ ይህን ያህል ፉክቻና የጥላቻና የንትርክ አባዜ የሠፈነው እንግዲህ አሮጌው አስተሳሰባችን ወደአዲሱ አስተሳሰባችን ለመስረግ ያለውን ቆራጥ አዝማሚያ ያሳያል፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ግንቦት ሰባትና ኢሕአፓ ወይም አርበኞች ግምባርና ሌሎች የተቃዋሚ ኃይላት ለምን አብረው አይሠሩም? ይሄ ሁሉ መቶና መቶ ሃምሳ የፖለቲካ ስብስብ ለምን አስፈለገ? በሬው ባልተገዛበት ሁኔታ በረቱ በሌቦች መወረሩ ምንን ያመለክታል? የሥልጣን ጉዳይ ነው ወይንስ የዓላማ? የዓላማ ልዩነት አለ ከተባለ እስኪ ይነገረንና እንወቀው? ሀገር በመዥገር ተወርራ በስደት ላይ ይህን ያህል የተቃዋሚዎች መወራከብ ምን ይባላል? እንበልና ወያኔ በራሱ ፈቃድ ሥልጣኑን ቢያስረክብ የአሁን ተቃዋሚዎች የነገ ሥልጣን ተረካቢዎች አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሳይደርሱ መስቀል አደባባይ አካባቢ እርስ በርስ ይጨራረሳሉ ማለት ነው? ምን ዓይነት መርገምት ነው? ይህን የብልጥነት ይሁን የሞኝነት ፈሊጥ ምን እንበለው? … እጅግ ብዙ ተቃዋሚዎች፣ እጅግ ብዙ የሲቪክ ማኅበረሰብ ማኅበራት፣ እጅግ ብዙ ታዋቂ ግለሰቦች፣ እጅግ ብዙ ፎረሞች፣ እጅግ ብዙ እንትኖችና እገሌዎች በየቀኑ እየከረረ ከሚሄድ ጭቆናና የሀገር ውድመት መች ነጻ አውጡን? የምን በሀገር መቀለድ ነው? ለመሆኑ ተቃዋሚዎች ሕዝቡን ያውቁት ይሆን? እርግጠኛ ነኝ – ከእኛ ችግር ይልቅ የነሱን መናቆር ነው በሚገባ የሚያውቁትና ዋናውን ትኩረታቸውንም የሚሰጡት፡፡ ስለዚህ ለውጥ ከመሻታችን በፊት አስቀድመን እኛ ሰው ለመሆን እንሞክር የምለው ለዚህ ነው፡፡ አንድ ሰው፣ ሰው ከሆነ በኋላ – ማለትም እንደሰው ማሰብ ከጀመረ በኋላ የሚያጣው ነገር የለም፡፡ አሁን ግን እኛ ተጨቋኝ የምንባለውም እነሱ ጨቋኝና በዝባዥ የሚባሉትም ሁላችንም ሰው መሆን ስላቃተን ይሄውና ድንበር ለሌለው መሪር አገዛዝና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ተዳርገን እንገኛለን፡፡ ወያኔዎችም ተመችቷቸው የሚኖሩ እንዳይመስለን፡፡ ከእኛ የበለጠ በጭንቀትና በፍርሀት እንዲሁም በሰቀቀን እየተሰቃዩ የሚኖሩት እነሱው ናቸው፡፡ የመጨረሻውን የታሪክና የፈጣሪ ፍርድ ያውቃሉና፡፡
አሁን ሕዝቡ እንዴት ነው እየኖረ ያለው? በብዙ ነገሮች አፍራለሁ፡፡ ብዙዎቻችን ከሰውነት ተራ ወጥተናል፡፡ ከሞራልና ከእምነት ወይም ከሃይማኖት መርሆዎች ወጥቶ እንደልቡ እየፈነጨ የሚኖረው ዜጋ ቁጥር የትዬለሌ ነው፡፡ አብዛኛው ወጣት ለሱሶች ተዳርጎ የነገይቷ ኢትዮጵያ አየር ላይ ተንሳፍፋ እንዳትቀር ያሰጋል – በሁሉም ረገድ ተረካቢ የሚሆን ጤናማ ዜጋ እየጠፋ ነው፡፡ ማይምነቱ አናታችን ላይ ወጥቶ እየፈነጨብን ነው፡፡ ስግብግብነትና ሆዳምነት የጊዜያችን ፋሽን ሆነው በሀገር ሲወረር አብረህ ውረር ፈሊጥ የምትበላ ነገር ስትገኝ ሁሉም እየተረባረበ የሀገር ሀብት እየተመናመነ ነው፡፡ መሬት ተቸብችቦ ሊያልቅ ምንም አልቀረው፡፡ ባለሥልጣናት ብቸኛ ዘመዳቸው ሆዳቸው ሆኗል፡፡ ያለ ጉቦ የሚፈጸም አንድም ነገር የለም፡፡ የሀብት ምንጩ ምን እንደሆነ ባላወቅኸው ሁኔታ የማይናቅ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በአንድ አዳር እንደሮኬት ሲወነጨፍ ታያለህ፡፡ የመኪናውን ብዛት ስታይ፣ የንግዱን እንቅስቃሴ ስትመለከት፣ የጮማ ቆራጩን የውስኪ ጨላጩን የዳንኪራ ረጋጩን ምዕመን ዕለታዊ የአሥረሽ ምቺው ሕይወት ስትታዘብ በ‹የት ነው ያለሁት?› ክፉኛ ልትጨነቅ ትችላለህ፤ አዲስ አበባ እየኖርክ ፓሪስ ላይ ያለህ ሊመስልህ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የዕንቆቅልሽ ሀገር ሆናለች፡፡ በሌላ ወገን በየአደባባዩ የሚርመሰመሰውን ድሃና ቁርስ በልቶ ምሣና እራት የማይደግም ምሥኪን ዜጋ ስታይ ጭንቅላትህ በጭንቀት ሊፈነዳ ይደርሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ህልም-እውናዊ ዕንቆቅልሽ ልትወጣ የምትችለው ታዲያ ዜጎች ቁጭ ብለው ‹በርግጥ እኔ ሰው ነኝን? በእውነቱ የቀድሞዎቹ ትሁታንና እርስ በርስ በመተዛዘን የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ትውልድስ ነኝን? ብለው ማሰብ ሲጀምሩ ነው፡፡ ልክ እንደ እስካሁኑ በራስህን አድን የአህያ ፍልስፍና ከተመራን በሰውኛ አስተሳሰብ ሀገሪቱ መቅኖ አጥታ እንደምትቀር መገንዘብ አይቸግርም፡፡ ስለዚህ ሀገራዊ ነጻነትን ከማሰባችን በፊት እያንዳንዳችን ነጻ መውጣት አለብን፤ ነጻ ያልወጣ ስብዕናና አስተሳሰብ ተይዞ ስለነጻነት ማሰብ አይቻልም፡፡ የምቾቱ ባሪያ የሆነ ሰው ነጻነትን አያውቅም፤ ነጻነት ሊኖረውም አይችልም፡፡ በጥቅም የተከፋፈለን ሕዝብ፣ በአመለካከት የተወነዣበረን ሕዝብ፣ በማይምነት ጥቁር መጋረጃ የተሸበበን ሕዝብ ነጻ የምታወጣው ከምንድን ነው? ነጻ አውጪውስ ማን ነው? ነፍስንና ኅሊናን በሚያቆሽሹ ተግባራት የበሰበሰና ሰውነቱ በሙስና የጨቀዬ ሰው – ተጸጽቶ ከልቡ ንስሃ ካልገባ በስተቀር – ራሱ የክፋት ባሪያ ሆኖ ሳለ ሌላን ሰው ነጻ ሊያወጣ አይቻለውምና በዚህ ረገድ መጠንቀቅ የሚገባን ወገኖች ጊዜ ሳናባክን ወደዬኅሊናችን እንመለስና ለኛም ለሀገርም የሚበጀውን እናድርግ፡፡ ለማንኛውም ከከሃዲነት፣ ከሀሰተኝነት፣ ከሌብነት፣ ከመረንነት፣ከዋልፈሰስነት፣ከሸፍጠኝነት፣ ከጨካኝነት፣ ከመተተኝነት፣ ከጠንቋይና አስጠንቋይነት፣ ከፍቅረ ንዋይ፣ ከጥላቻ፣ ከሃይማኖት የለሽነት፣ ከዘረኝነት፣ ከኋላቀር አስተሳሰብ፣ ከሆዳምነት፣ ከሙሰኝነት፣ ከማይምነትና ከአላዋቂነት፣ ከግብዝነት፣ ከግልብነት፣ ከሸረኝነት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከአስመሳይነት፣ከአድርባይነት፣ ከምቀኝነት፣ከአጭበርባሪነት፣ ከቅናት፣ ከህገ-ወጥነት፣ ከህግ-አልባነት፣ ከወንዘኝነት፣ ከጎጠኝነት፣ ከሥርዓት አልበኝነት፣ ከትምክህት፣ ከትዕቢት፣ ከዕብሪት፣ ከጉረኝነት፣ከዝምድና አሠራር፣፣ ከንፉግነት፣ ከስግብግብነት፣ ከሞራለቢስነት፣ ከአመፀኝነት፣ ከሴሰኝነት፣ ከአመንዝራነት፣ ከሰካራምነት፣ ከቃሚነት፣ ከዕፀኝነት፣ ከስንፍና፣ ከግዴለሽነት፣ ከባዶነት ስሜት፣ ከግልፍተኝነት፣ ከተሳዳቢነት፣ ከአሽሙረኝነት፣ … ከነዚህ እሥር ቤቶች ባፋጣኝ ራሳችንን ነጻ ካላወጣን አይደለም ወያኔ አፄ ቦካሣና ኢዲያሚን ዳዳም ሲበዙብን ነው – ለወያኔ ሌባ ጣታችንን ስንቀስር ሦስቱ ጣቶቻችን ወደኛ ማመልከታቸውን ልብ እንበልና ከአርቲፊሻል ሕይወት ወጥተን እውነተኛ ሰውኛ ሕይወት ለመኖር የፈጣሪን ረድኤት እንጠይቅ፤ አለበለዚያስ አልጠፋንም ብለን ልንዋሽ አይገባንምና ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በሚገባ ጠፍተናል፤ ተለያይተንማል፡፡ ተለያይቶና ጠፍቶ ደግሞ ነጻነትን መመኘት የሚቻል አይደለም፤ ህልምና ቅዠት ነው፡፡ የሚመጣው መሪ ሁሉ የኛ ነጸብራቅና የማንነታችን ቅጂ መሆኑን አንርሳ፡፡ ያልዘሩት አለመብቀሉ የታወቀ ነው፤ እናም ወያኔን ማማረራችንን ወደጎን ትተን ራሳችንን እንፈትሽና የንጹሕ ኅሊና ባለቤቶች ለመሆን እንትጋ፡፡ ‹ቤታቸውን ከፍተው ሰው ሌባ ይላሉ› አለ አሉ አንዱ ሣተና ሌባ፡፡ ቸር ያሰንብተን፡፡
የሚከተለውን ቆንጆ አባባል ያገኘሁት አንድ ጽሑፍ ሳነብ ነው፡፡ ደስ አለኝና ከነአማርኛ ትርጉሙ ከዚህ በታች አስቀመጥኩት፡፡ ተመልከቱትና አንዳች ግንዛቤ ጨብጡበት፡፡ ማንበብ ሙሉና ጎደሎ ሰው ያደርጋል – እንዳንባቢውና እንደተነባቢው ጽሑፍ፡፡
Here is to the crazy ones, the misfits, the rebels, the trouble makers, the round-pegs in the square holes… the ones who see things differently – they are not fond of rules… you can quote them, disagree with them, glorify or vilify them, but the only thing you can’t do is ignore them because they change things … they push the human race forward, and while some may see them as the crazy ones, we see genius, because the ones who are crazy enough to think that they can change the world, are the ones who do.
Steve Jobs, US Computer Engineer and industrialist
በማኅበረሰባችን ውስጥ ዕብዶች የምንላቸውን፣ በጋጠወጥነት የምንፈርጃቸውን፣ በአማጊዶነት(ወሮበልነት) የምንኮንናቸውን፣ በችግር ፈጣሪነታቸው ምክንያት የምንታወክባቸውን፣ ነጭን ጥቁር ጥቁርን ነጭ ብለው ድርቅ ካሉ የሚመለልሳቸው አንዳችም ምድራዊ አመክንዮ የማናገኝላቸውን መንቻካና ልበ ሥውራን ወገኖቻችንን፣ … እኚህን መሰል ነገሮችን በተለዬና በራሳቸው አቅጣጫ ብቻ ማየት የሚፈልጉ አፈንጋጭ ዜጎችን በሚመለከት መናገር የሚቻለው የሚከተለውን ነው፡- ሕግና ደንብ አያከብሩም – የሕግጋት መኖር አለመኖርም ደንታቸው አይደለም፡፡ … ብዙ ዋቢዎችን እየጠቀስክ ልትከራከራቸው ትችላለህ፤ በዚህ ጥረትህም ላትግባባቸው ትችላለህ፤ ይህን ጥረትህን በተመረኮዘም ልታከብራቸው ወይም ልታንቋሽሻቸው ትችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ልታደርገው የማትችለው ነገር ቢኖር እነሱን ችላ ብለህ ማለፍ ወይም በተራ አነጋገር ‹መዝጋት› ነው፤ ምክንያቱም የነገሮችን ሂደት በመለወጥ ረገድ ያላቸው ተፅዕኖ የወሳኝነት ያህል የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነውና፡፡ (የናቁት ‹ወንድ› ያስረግዛል ዓይነት መሆኑ ነው፡፡) … ከነዚህ አፈንጋጭና ወፈፌ መሰል የማኅበረሰብ አባላት መካከል የተወሰኑት የሰውን ዘር በክፉም ይሁን በበጎ ነገር ከነበረበት ሁኔታ ወደተለዬ አቅጣጫ የመግፋት አቅምና ችሎታ አላቸው፤ ምንም እንኳን አንዳንዶች እነዚህን ዜጎች እንደዕብድና ወፈፌ ቢቆጥሯቸውም ከነሱው ውስጥ ዓለምን መለወጥ እንደሚችሉ የሚያምኑና በርግጥም መለወጥ የሚችሉ የታላቅ አእምሮ ባለቤቶችንም ማግኘት ይቻላል፡፡