Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

በውኑ ድብኝት ይታጠባልን? በገለታው ዘለቀ

$
0
0

ኣንድ ጊዜ ታዋቂው የሰነ ጽሁፍ ሰው ጋሽ ስብሃት ገብረ እግዚኣብሄር ኣንዱን እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል::

“ስራህ ምንድነው?”

“ኤዲተር ነኝ ጋሽ ስብሃት”

“ኣየ ጉድ! ድብኝት ኣጣቢ ነኝ ኣትለኝም”

ኣገላለጹ በተለይ የኤዲቲንግ ስራ ለሚሰሩ በደንብ ይገባቸዋል፣ ያስቃቸውማል:: ዛሬ ታዲያ ይህቺ ኣገላለጽ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ስራ ጥሩ ማሳያ ሆና ኣገኘኋትና ነው መግቢያ ያደረኳት። የጸረ- ሙስና ኮሚሽንም ድብኝት ኣጠባ ላይ መሆኑን ነው የምናየው።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትም ሳይቀሩ ተጠያቂ እየሆኑ ነው የሚል ዜና እየተሰማ ነው። መቼም ለየዋሆች ግራ ለተጋቡ ማለቴ ነው ኣይ ይሄ መንግስት ሳይቆርጥ ኣይቀርም ባለስልጣኑን ሁሉ ተጠያቂ እያደረገው ነው ሊሉ ይችላሉ። እውነቱ ግን ጸረ- ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ  ከ2001 ወዲህ ሙስና በተቃራኒው ቀጥ ብሎ እያደገ ነው የመጣው። ይህ ተቋም በርግጥ በሃገሪቱ የተንሰራፋውን ከፍተኛ ሙስና ሊቀንሰው ያልቻለበት ኣንዱ ትልቁ ምክንያት የሙስናው ባህርይ የተለየ በመሆኑም ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ  ያለው የሙስና ኣይነት ከዚያም ከዚህም ትንሽ ትንሽ ቦጭቅ(competitive) ኣይነት ሳይሆን ጎልቶ የሚታየው የጠቅልል ሙስና(monopolistic corruption) ኣይነት  ነው። በብዙ ኣገራት የሚታየው የትንሽ ትንሽ ቦጭቅ (competitive-like) ሙስና በኢትዮጵያ ውስጥ ጎልቶ ኣይታይም። አንደሚታወቀው በተለይ በታችኛው ርከን ላይ ያሉትን ባለስልጣናት ኢህኣዴግ በከፍተኛ ኣውጫጭኝ ( “ግምገማ” ) ወጥሮ የያዛቸው ሲሆን ቢቻል ኣንድም ሳንቲም እንዳይነኩበት ይታገላል። እነዚህ ሰዎችም በኣብዛኛው በፍርሃት የሚኖሩ እንዴውም ኢህኣዴግ ኣንድ ቀን ብሽ ሲለው በቀላሉ የሚወረውራቸው በመሆናቸው ለሙስና የሚደፍሩ ኣይደሉም።ለነሱ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ናት። በመካከል ያሉትም ቢሆን እንዲሁ በግምገማ ተወጥረው የተያዙ ናቸው።

ኢህኣዴግ ይህን የሚያደርገው ለሃገር ሃብት ኣስቦ ሙስና እንዳይስፋፋ ተጨንቆ ኣይደለም። ይልቁን የሙስናው ባህሪ ሞኖፖሊስቲክ በመሆኑና ሁሉንም እኔ ላጋብሰው ከሚል ስሜት የመነጨ ነው።ይህ ኣይነቱ የሙስና ኣይነት ደግሞ  በኣንድ ልፍስፍስና ነጻ ባልሆነ ተቋም ከቶውንም ሊጸዳ ኣይችልም። ምክንያቱም የሙስናው ባህርይ ራሱ ተቋማዊ ይዘት ስላለው የሚደፈር ኣይሆንም።

በመሰረቱ ይህ ተቋም ሲቋቋም ጀምሮም ሙስናን ለመቀነስ ሲሰራም ኣይታይም።ከፍ ሲል አንዳልነው እንዴውም የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኣመታዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ይህ ተቋም ከተመሰረተ ጀምሮ ሙስና ማደጉን ነው የሚያሳየው። ይህ የሚያሳየው ደሞ በርግጥ እውነተኛ ስራው ላይ እንዳልሆነና ይልቁንም መንግስት ያበሸቀውን ሰው ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ የሚቀጣበት ኣንድ ተጨማሪ ተቋም ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ያለው የጠቅል ሙስና በሌሎች ሃገሮች እንዳለ የሙስና ኣይነት ጉዳቱ ኣንድ ኣቅጣጫ ብቻ ኣይደለም ያለው። ይህ የሙስና ኣይነት ሲጠናከር ኣንድ ከፍተኛ የመጨቆኛ መሳሪያ ይሆናል። ኣብዛኛውን ማህበረሰብ በኢኮኖሚ ከመጉዳቱም በላይ ለውጥ እንዳይመጣ የህዝብን ድምጽ ለማፈን ትልቅ መሳሪያ ነው። ከሁሉ የከፋው ጉዳትም ይሄ ነው።

መንግስት ራሱ የጦፈ ነጋዴ በሆነበት ኣገር፣ቡድኖች ያገኙትን ሃብት የባህላዊ ቡድናቸው ሃብት ነው ብለው በሚያስቡበት ኣገር ይህ ኣይነት የሙስና እድገት ከፍተኛ ችግር ነው። ዛሬ ኤፈርት ነው ኣንዱ የሃገሪቱን ሃብት ይዞ ያለው። ይህ ድርጅት በፊት በጦርነቱ ጊዜ በኢትዮጵያዊያን ስም የተገኘ፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች የተዘረፈ ሆኖ ሳለ ንብረትነቱ የኣንድ ቡድን ብቻ ነው መባሉ ራሱ በራሱ ሙስና ነው። ዋናው ጥያቄ ኤፈርትን ኣንዳንድ ሰዎች እየበዘበዙት ነው ሳይሆን ራሱ ድርጅቱ በተፈጥሮው

ሙሰኛ ነው። የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመሩት፣ የኢትዮጵያዊያን ሃብት መሆኑን የካደ ድርጅት የሙሰኛች ሙሰኛ ነው።

ችግሩ እዚህ ድረስ ብቻ ሳይሆን ኤፈርትን ለዚህ ያበቃው ደሞ የታችኛው የፖለቲካው ቅርጽ(deep structure) ነው። ፖለቲካው ራሱ መገንጠል ዋስትና ነው ብሎ የሚያምን፣ ሁሉም ወደየጎጡ እንዲሮጥ የሚገፋ በመሆኑ የሙስናው ወለል ይህ የፖለቲካ ቅርጽ ነው። ይህ ደሞ በጸረ ሙስና ኮሚሽን የሚፈታ ሳይሆን በስርዓት ለውጥ ነው የሚፈታው።  የኢትዮጵያ የሙስና ጥያቄ ጉዳይ እከሌ ይህን ያህል ብር ወስዱዋል እከሊት ይህን ያህል በሚል ሳይሆን ራሱን የበሰበሰውን ለሞኖፖሊስቲክ ሙስና በር የከፈተውን ስርዓት መለወጥ ነው ፈውሱ።እነዚህ በከፍተኛ ሙስና የተመሰረቱና የሚኖሩ ድርጅቶች ደግሞ ከግለሰብ ብልጽግና ፍላጎት የዘለለ የቡድንተኛነት ስሜት ያላቸው በመሆኑ ሲበዛ ስግብግብ ኣድርጓቸዋል። የሃገሪቱ ኣጠቃላይ ሃብት GDP ሲታይ በየኣመቱ እድገት የሚታይ ሲሆን ይህ እድገት ግን በሲቪል ሰርቫንቱ፣ በገበሬው ባጠቃላይ በኣብዛኛው ህዝብ ላይ ኣለመታየቱ የሚያሳየው ነገር ሙስናው ጠቅልል መሆኑን ነው። እንደ UNDP የኢትዮጵያ GDP  በየኣመቱ ያድጋል። በኣንጻሩ የሙስና መለኪያዎች ደግሞ ሙስና በያመቱ እያደገ መሄዱን ያሳያሉ። የነፍስ ወከፍ ገቢም ሲባል መኖሪያ የሌለውን ጦሙን ኣዳሪውን ዜጋ  በሙስና ሰማይ የደረሱ ሰዎች ገቢ ጋር ይደመርና ለሁለቱም ተካፍሎ ለጭቁኑ ይህን ያህል ነው የነፍስ ወከፍ ገቢህ ተብሎ ይፈረድበትና ቁጭ ይላል።ያላየውን ያልበላውን ድሃ እንዲህ ይፈረድበታል።ይሄ የራሱ የቀመሩ ውሱንነት ሳይሆን ዋናው ችግር የስርዓቱ ሙሰኛ መሆን ነው። በሙሰኛ ስርዓት ውስጥ ከባድ የገቢ ልዩነት በመኖሩ ይህ የነፍስ ወከፍ ገቢ መለኪያ ከ እውነቱና ከፍትህ ደጅ በጣም ይርቃል።

የተስፋፋው የሞኖፖል ሙስና የግሉን ሴክተር ኣክርካሬ ኣድቆ ይታያል። በሌላ በኩል ስለ ሙስና ስናወራ በገንዘብ ብቻ ኣይደለም የሚገለጸው። የመሬት ነጠቃው ራሱ ኣንዱ ከፍተኛ የሙስና ስራ ነው። ዜጎች በማያውቁት ውል መንግስት ብቻውን እየተዋዋለ ሰፋፊ እርሻዎችን እየሰጡ ነው። ባንድ በኩል ተርበናል እየተባለ ስንዴ ከውጭ እየለመንን በሌላ በኩል ኣገር ቤት እህል እየተመረተ ወደ ውጪ ይሄዳል። ይሄ ነው እንዴውም ከባዱ ሙስና።

ለመንግስት የምንለው ይህንን ነው። ኢትዮጵያዊያን ለውጥ እንፈልጋለን፣ ድብኝት ኣይታጠብም! ይህን የተበላሸ ሙሰኛ ፖሊሲ የሚያጥበው ደግሞ የህዝብ የተቃውሞ ጎርፍ ነው። ይህ ጎርፍ ሲመጣ በርግጥ ስርዓት ለውጦ በተሻለ ስርዓት ይተካል። በኢትዮያም ይህ ነገር በቅርቡ እውን መሆኑ ኣያጠያይቅም።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

geletawzeleke@gmail.com

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>