Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያነበው የሚገባ መጽሐፍ! (የመጨረሻ ‹መጣጥፍ›)

$
0
0

ይነጋል በላቸው (yinegal3@gmail.com)

የመጽሐፉ ርዕስ፤   “የካድሬው ማስታወሻ”

“በደርግና በኢሕአዴግ አገዛዝ ውስጥ ከተራ ወታደርነት እስከ የጦር መኮንንነትና የፖለቲካ ካድሬነት የተደረገ ትግል …”

ደራሲ፤                   አስረስ ገላነህ ብዙነህ (ሻምበል)
የኅትመት ዘመን፤    ሐምሌ 2005ዓ.ም
የገጽ ብዛት፤            271
አርታዒ፤                በስም ያልተጠቀሰ (ግን እጅግ በጣም ጎበዝ ሰውዬ!)

 
የካድሬው ማስታወሻበሀገራችን የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሣትና የትኩሣቱ መንስኤዎች ላይ በርካታ መጻሕፍት ረዘም ካለ ጊዜ ጀምሮ ለኅትመት እየበቁ ናቸው፡፡ ጊዜ ያለን ሰዎችም እንደየፍላጎታችንና እንዳለን ጊዜ ማንበብ የምንችለውን ያህል እያነበብን በ‹ጉድ ነው!› አጃኢበትም እየተደመምን አለን፡፡ ከመሳጭነቱ የተነሣ በዛሬዋ ዕለት በግማሽ ቀን ብቻ አንብቤ የጨረስኩት ከፍ ሲል የተገለጸው መጽሐፍ ከቅርብ ዓመታት የመጻሕፍት ንባቤ በስሜት ቆንጣጭነት ወደር አላገኘሁለትም፡፡ ጸሐፊውም አርታዒውም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፤ ዘራቸው ይለምልም፡፡ የዘመናችን ወያኔ-ወለድ ፖለቲካ ያመጣብንን መርገምት አብዛኛውን የሚያጋልጥ በመሆኑ በታሪካዊ መዝገብነት መጪው ትውልድ ሊዘክረው የሚገባው ድንቅ ሥራ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉ አማርኛ ቋንቋን ማንበብ የሚችሉ የሀገሬ ዜጎች ሁሉ ባሉበት ይህን መጽሐፍ እንዲያነቡት ወገናዊ ጥቆማየን በታላቅ አክብሮትና ትህትና አቀርባለሁ፡፡ ብዙዎቻችን በአነስተኛ መጣጥፎችና ጦማሮች ስናትተው የከረምነውን ፀሐይ የሞቀው እውነታ በመጽሐፍ መልክ – ሊያውም ፈረንጆቹ “from the horse’s mouth” እንደሚሉት ከራሱ ገጠመኝ ጨልፎ ከሚያቀርብልን ተንከራታች ዜጋ በሚጥም አቀራረብ ታገኙታላችሁና በጥቆማየ እንደምትደሰቱ አልጠራጠርም፡፡ ብዙ የተደከመበት የአእምሮ ውጤት በመሆኑ መነበብ የሚገባው ነው፡፡ (ይህ ጽሑፍ የይነበብ ጥቆማ እንጂ የመጽሐፍ ቅኝት ወይም ትችት አይደለም!)

 

የምንገኝበት የእርግማን ዘመን እያበቃ እንደሆነ በበኩሌ ይሰማኛል – በዚያውም ላይ ‹ስድስተኛውን የስሜት ሕዋስ› በከንቱ ተሸክሜ የምዞር ገልቱ እንዳልመስላቸሁ!! አቅል አጥተን እንዲህ  በሀብትና በሥልጣን ራሳችን ያበድንበትና ሌሎችን ያሳበድንበት ዘመን ሊያከትም የቀረን ጊዜ በጣም ጥቂት ይመስለኛል፡፡ ሊነጋ ሲል መጨላለሙን በገሃድ እየተመለከትን ነው – በአሁኑ ወቅት ጨለማው ከፍቷል፤ ዐይንን ቢወጉ ጭራሽ የማይታይ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነን፡፡ አቅጣጫውን በውል ለይቼ አላውቅም፤ ነገር ግን እየነጋና የብርሃን ብልጭታ እየታየኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በታትኖ በዓለም ሕዝብ ዘንድ መሣቂያና መሣለቂያ ያደረገውን የወሮበሎች መንጋ ፈጣሪ ከአናት ጀምሮ ቀስ በቀስ ግን በፍጹም ሊጨናገፍ ወይ ሊስተጓጎል በማይችል ሁኔታ ብትንትኑን እያወጣው የሚገኝ መሆኑን መረዳት የሚከብደው ሰው ቢኖር ዐይነኅሊናው የታወረና ዕዝነልቦናው የደነቆረ ዓሣማ ወያኔ ወይም አጋሰስ ጥገኛ መሆን አለበት፡፡

ሮም በአንድ ቀን አዳር አልተገነባችም፤ ባግዳድና ደማስቆም በአንድ ቀን ጀምበር አልወደሙም፤ የቀን ጉዳይ እንጂ ወያኔዎች በሚያሣዝን ሁለንተናዊ አገባብ እየጠፉ ነው – በሥነ ልቦናም፣ በኅሊናና አእምሮም፣ በአካላዊ ጤንነትም፣ በቤተሰባዊ የጤናማ ትውልድ አለመቀጠልም … ብቻ በሁሉም ዘርፍ የተሣካ ውድቀት ውስጥ ተዘፍቀው እየተንፈላሰሱ እንደሚገኙ መገንዘብ ከጀመርን ውለን አድረናል , እንዳባታቸው ቃለ ቡራኬም “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችው” ብለን መርቀናቸዋል፡፡ ይህን እያደረገ ላለው የኢትዮጵያ አምላክ ምሥጋና ይድረሰው፡፡ አንድ ጥይት ሳይተኮስባቸው በትንቢቱ መሠረት እንደጉም እየተበታተኑና እንደጪስ እየበነኑ ነው – በዚህ ነባር አባባል አላፍርበትም ልድገምላችሁ – በትንቢቱ መሠረት ወያኔዎች እስከወዲያኛው ብትንትናቸው ሊወጣ ጊዜው ቀርቧል – ሃሌ ሉያ፤ በሰው ስቃይ መደሰት አግባብ ባይሆንም የፈጣሪን ፍርድ ማጣጣል ተገቢ ባለመሆኑ የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀረው ፈጣሪ ለሚሰነዝረው ለዚህ ፍትሃዊ ብያኔ አኮቴት ማቅረብ ይገባል – እንደጥፋታቸው ከባድነት ደግሞ በሰው አምሳል የሚንቀሳቀሱ አጋንንት እንጂ እንደሰው ሊቆጠሩ የማይገባቸው ነገሮች በመሆናቸው በነሱ ላይ በሚወርድ ፍርድ ማዘን ጌታን ማስቀየም ነው፡፡ “ወይ ፍረድ ወይ ውረድ” ካልን በኋላ “እንዳይፈርድም እንዳይወርድ”ም ደንቃራ ልንሆን አይገባምና በርሱና ከርሱ ለሚመጣ የመጨረሻ ፍርድ እንቅፋት መሆን የሚዳዳን ዜጎች ብንጠነቀቅ አይከፋም፡፡ ማንም ደግሞ ሊያድናቸው አይችልም፤ የተፈረደን ፍርድ ዝምብሎ እንዳመጣጡ መቀበልና መኮምኮም እንጂ እኔ ነኝ ያለ ምድራዊ ኃይል ከዚህ ከተደገሰላቸው የመከራ ድግስ አያስጥላቸውም – “አንቺም ጨካኝ ነበርሽ ጨካኝ አዘዘብሽ፤ እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብሽ” እንደተባለው እነሱም በሠፈሩት ቁና እየተሠፈረላቸው ነው፡፡ አስቡት፡- ከመለስና ገብረ መድኅን ሞት በኋላ ማን ይመስላችኋል እንዲህ ምንቅርቅራቸውን እያወጣ የሚገኘው? ለመሆኑ ማን ጻዲቅ ማንስ ኃጥዕ ሆኖ ነው እንዲህ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ማጎሪያ ቤቶቻቸውን ሊሞሉ የደረሱት? ሥርቆትና ሙስና የሁላቸውም የሕይወት እስትንፋስ ያልሆነ ያህል አንዳቸው አንዳቸውን ካለምንም ሀፍረት እንደጅብ የሚዘረጥጡት እንደባቢሎንያውያን በክፋት ለክፋት እንዳይግባቡ እግዜር ስለፈረደባቸው አይደለምን? ይህን የማያውቅ ማን አለ? ጭካኔያቸው ወደር የሌለው እንደመሆኑ የግብ ዕዳ ክፍያቸውም ያንኑ ያህል ተወዳዳሪ የማይገኝለት እየሆነ ነው፡፡

ይህን ሂደት እነሱ ዐወቁት አላወቁት ምንም ለውጥ ስለማያመጣ ምሥጢር አይደለምና አጠፋፋቸውን ደግመው ደጋግመው ይስሙት – ይህንን ነባራዊና መለኮታዊ ፍርድ ኅሊናቸውም ቀድሞ ያውቀዋል፡፡ ፈጣሪ ሥራውን ዘንግቶ አያውቅም፤ ወደፊትም ሆነ አሁን አይዘነጋም፡፡ የሰውና የእግዜር የጊዜ አለካክ ለዬቅል በመሆኑ ግን ብዙዎቻችን ተስፋ እየቆረጥን ወዳልሆነ አቅጣጫ እንዞርና ከሁለት ያጣ ጎመን ወደመሆን ደረጃ እናጋድላለን፤ ያኔ በሁለት ጌቶች መካከል ስንመላለስ ወይ ከሥጋችን ወይ ከነፍሳችን ሣንሆን እንዲሁ በመሀል ቤት እንደተቅበዘበዝን እንቀራለን፡፡ በአቋማቸው የሚጸኑ ግን መጨረሻቸው ያማረ ይሆናል፡፡ “ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክብ አምላክነ” አልነበር ቅዱስ ገብርኤል የተናገረው – ሰይጣን “አምላካችሁና ፈጣሪያችሁ እኔ ነኝና ለኔ ስገዱ” ብሎ የእግዚአብሔርን ኅልውና በተገዳደረበት ፈታኝ ወቅት? አዎ፣ እኛም በዚያ ዓይነት ከባድ ፈተና ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ እውነተኛ እናታችንን እስከምናገኝ ድረስ ታዲያ መረታት የለብንም፡፡

ለማሣጠር … በበኩሌ ከ2007ዓ.ም መጠናቀቅ በፊት ብዙ እናያለን የሚል ታላቅ የተስፋ ስንቅ ቋጥሬያለሁ፡፡ … ያልተነገረ የተፈጸመ፣ የተፈጸመ ያልተነገረ ነገር ፈጽሞውን አላስታውስም፡፡ ሁሉም ተነገረ፤ ሁሉም ተፈጸመ፡፡ ዘመነ መንሱት ወደታሪክ ሰገባ ገብቶ በብረት ክፈፍ ሊጠረቀም፣ በምትኩ ደግሞ ወርቃማው ዘመነ ፍስሐ ወሃሤት ሊብትና እምዬ ኢትዮጵያ ከሞት ልትነሣ የተሰደዱ ልጆቿም በ‹ጉሮ ወሸባየ› የድል ብሥራት ዘፈን ታጅበው ሊመለሱ፣ የሚሊዮኖች የዘመናት ሰቆቃም በፈጣሪ ዕልባት ሊያገኝ ተቃርበናል፤ ዕድሜ ለዕንባችን አሁን ዕፁብ ቅንቅ ተዓምራትን እያየን እንዳለን ሁሉ የመጨረሻውን ልዩ ትንግርት ልናይ ተቃርበናል፡፡ እነሱ ለእራት ሲያመቻቹን አንድዬ በብዙ አቅጣጫ ቀስፎ ይዟቸዋልና የነጻነታችን ቀን መቅረቡን መጠራጠር አይገባም፡፡ መተማመኛችንን እርሱን ያደረግን አናፍርም፡፡

ግን ለፈጣሪያችን ማድረስ ከሚገባን ልባዊ ጸሎትና ምህላ በተጓዳኝ ከቂም በቀለኝነትና ከክፋት መራቅ አለብን፤ እንደወያኔ በተመሳሳይ የክፋት ቅኝት የምንነጉድ ከሆነ ነጻነታችን የማይቀር መሆኑ በታሳቢነት ተይዞ ፈረሰኛው ጎርፍ እንዳይጠራርገን ያሰጋል፡፡ ልብ እንበል፡- እንደወያኔ እያሰቡ፣ እንደወያኔ እየሆኑ፣ እንደወያኔ እያደረጉ፣ እንደወያኔ እየሞሰኑ ወያኔን ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት አንድ ስንዝር ማባረር አይቻልም፡፡ ይህን ስል ወያኔን በሚገባው ቋንቋ ማነጋገር መጥፎ ነው ወይም ‹ኃጢኣት› ነው ለማለት ፈልጌ እንዳልሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ጥፋተኛን ከንፁሕ የማይለይ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በባህል ተመሳስሎ መገኘትን እንደወንጀል የሚቆጥር፣ በብዕር የመጣን ወገን በታንክ የሚጨፈልቅ፣ ዳቦና የንግግር ነጻነትን የጠየቀ በአሸባሪነት ፈርጆ ዘብጥያ የሚወረውር፣ አማላይና ማራኪ የመንግሥትን ሕግና የፈጣሪን ትዕዛዝ የማይከተል ወያኔዊ አሠራር ማስወገድ ለዘለቄታዊ ድል እንደሚበጅ መረዳት ይገባል – እውነትን በመደፍጠጥ የሚገኝ አብረቅራቂ ድል የውሸትና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በጎመን ጥጋብ የሚያስፏልል መሆኑን ከዚህ ዘመን በላይ አስረጅ የለም፡፡

የሐጎስን ስህተት አምባቸው ቢደግመው፣ የስንሻውን ግድፈት ፈይሣ ቢሰልሰው ታጥቦ ጭቃ እንጂ የምንፈልጋቸውና የምናልማቸው ፍትህና ርትዕ እንዲሁም በዜጎች ሃቀኛ እኩልነት ላይ እንዲመሠረት የምንጠብቀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕልምና ቅዠት እንደሆኑ ይቀራሉ፡፡ ለታደለና አንጎል ላለው ሰው ያለፈ ስህተት ከዩኒቨርስቲ በሚበልጥ ሁኔታ ከፍተኛ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው፡፡ እንደኛ ላልታደለ ሕዝብ ግን ያንዱን ስህተት ሌላው እያዘመነና በተንኮል እያጠናከረ የሚቀጥልበት የመሠሪዎች የጭቆና አገዛዝ አዙሪት ነው፡፡ ከእንስሳት ያነሱ ሰዎች ስለራሳቸው ብቻ ይጨነቃሉ፤ ሌሎችን መቅ ይከታሉ፡፡ ለሆዱ የሚያድር ጅብና ዓሣማ ነው፡፡ ወያኔዎች መነሻቸው ምንም ይሁን ምን ከዓሣማና ከጅብ ያልተሻሉ እንዲያውም የባሱ ሆዳሞችና በአንጎል ሣይሆን በከርሳቸው የሚያስቡ አውሬዎች ናቸው፡፡ ከባድ ዋጋ እያስከፈላቸው የሚገኘውና ገና አንዲትም ጥይት ሳትተኮስ እንዲህ ፍርጠጣና ሽሽት ውስጥ የገቡት ከሰውነት ተራ ባወጣቸው ሆዳቸው አማካይነት የሠሩት ወንጀል ከአሁኑ እያቃዣቸው ነው – የሰው ዋና ጠላቱ ሆዱ ነውና በዚህ በቀዳዳ በርሜል በሚመሰል ሆዳቸው ጦስ ወያኔዎች ገና ብዙ አሣር ይገጥማቸዋል፤ ሱቅ ውስጥ እንደገባ ሕጻን ሁሉንም ለራሳቸው የማድረግ አባዜ የተጠናወታቸው እነዚህ በጎደሎ ቀን የተፀነሱ ይሉኝታቢስ ዜጎች አወራርደው የማይጨርሱት ውዝፍ ሒሳብ አለባቸው፡፡ ከአሁኑ በነሱው ቋንቋ መላቅጡ በጠፋበት ውስጣዊ “ህንፍሽፍሽ” ገብተው እንዲህ የተራወጡ ዋናው የፈጣሪ ማዕበል ሲነሣማ ዕድሜውን ይስጠን እንጂ እንዴት እንደሚሆኑ የምናየው ይሆናል፡፡ አለ ነገር!

የአዲስ አበባን ነገረ ሥራ ብታዩ ከ‹አለ ነገር› በላይም ትላላችሁ፡፡ የምፅዓት ማወጃ ፊሽካው ብቻ የቀረ ይመስላል፡፡ ርሀቡ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ ሙስናው፣ የፍትህ ዐይን መጥፋት፣ የነጋዴውና ባለሥልጣኑ እምብርት ማጣት፣ የዘረኝነቱና ጎጠኝነቱ መንሠራፋት፣ የድህነቱ አለቅጥ መስፋፋት፣የወንጀሉና ወንጀለኛው አበዛዝ፣ የኃጢኣቱ ከላይ እስከታች መዛመት … የጥቂቶች አለልክ መንደላቀቅና መዘባነን፣ የተያዘው አሥረሽ ምቺው፣ የተወሰኑ ዜጎች ገንዘባቸውን እምን እንጣለው በሚል በእሳት የማቃጠል ያህል አልባሌ መርጨት፣ የለፋና የደከመ እየደኸዬ አጭበርባሪውና የአየር ባየር ደላላና መልቲ ዜጋ በደቂቃዎች መክበር  … በአንዲት ጠባብ ከተማ ሲዖልና ገነት፣ ገሃነምና መንግሥተ ሰማይ ባልተፈረመበት ውል እየተጎሻመጡ ይኖራሉ – ጎን ለጎን እየተያዩ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ በድብቅ ሚስቶቹን አግብቶ እየወለደ እያስተማረ አሳድጎም ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ለወግ ለማዕረግ ሲያደርስ ብታዩ ልትደነቁ አይገባም – “አንተን በዚህ ምን አገባህ – እነሱው ይኮነኑበት” የማለት መብታችሁን አከብራለሁ – እየተገረፍንበት ስለምንገኘው የሀሰተኛ ነቢያት ዘመን ተጨባጭ ሁኔታ የመናገር መብት እንዳለኝ ደግሞ በግልጥ ማሳወቅ እወዳለሁ ፡፡ እኔ ይህን መሰል ታሪክ በጣም በቅርብ አውቃለሁ፡፡ ካህናት የነፍስ ልጆቻቸውን ሚስቶች ‹እየቀሙ› ቢያባልጉ አትገረሙ፤ ብዙ ወንጀሎችና ኃጢኣቶች ይሠራሉ፡፡ መንግሥተ እግዚአብሔርና መንግሥተ ሕዝብ የዱርዬዎችና የወሮበሎች መናኸሪያ ሆነው መልካም ዘመንን መጠበቅ ታዲያ የዋህነት ነውና በሚደርስብን ዕኩይ ነገር ሁሉ በቀላሉ መደናገጥ አይኖርብንም፡፡ እንደሥራችን ይህም ሲያንሰን ነውና፡፡ የእንግልታችን ሁሉ መንስኤ ይሄው ለመንግሥትና ለእግዚአብሔር ሕግጋት አለመታዘዝ ነው – ከጫፍ እስከ ሥር ድረስ – ከፓትርያርክ እስከ ዲያቆንና ከጠ/ሚኒስትር እስከተራው ዜጋ፡፡ ካልተወሻሸን በስተቀር ከሞላ ጎደል ሁላችንም ጠፍተናል፡፡

አሁንና ዛሬ ለምን አይፈርድ? ለምን ሶዶም ወገሞራዊ ብያኔውን አይደግም? ሚሊዮኖች በርሀብ አለንጋ እየተገረፉ በጠኔ ጣር ሲሞቱ ጥቂቶች በዘረፉት ወይም አግባብ በሌለው የንግድና የሙስና ተራክቦ ባገኙት ገንዘብ ዳንኪራና ጮቤ ሲረግጡ እያዬ እስከወዲያኛው የሚያስችለው ፈጣሪ ምን ዓይነት ፈጣሪ ነው? ንጉሥ ዳዊት ቢጨንቀው፤ “እስከማዕዜኑ ትረስዓኒ ሊተ” በማለት ጌታን ወቅሷል፡፡ እኛንስ እስከመቼ የረሳን እንደመሰለ ሊቆይ ይችላል? ሁሉም መጠን አለው፤ እሺ? እናም የኛ ነገር አሁን አሁን ያለቀ ይመስላል፡፡ ማለቁን ለማወቅ አዲስ አበባን ኑና ጎብኙ፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ሣትሆን ሀገራችን ባጠቃላይ ከካምሱሩ የተላቀቀ ቦምብ ሆናለች፡፡ “የጨው ተራራ ሲናድ ብልኅ ያለቅስ፤ ሞኝ ይስቅ” እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ አንድ ሐሙስ ከሚቀራት የማስፈራሪያና የማስጠንቀቂያ ደረጃ ወጥታ መጥፋት ከተገባት ጊዜ ብዙ ሐሙሶችን እንዳለፈች ልብ ልንል ይገባል – እንደእግዚአብሔር ፈቃድና ጥበቃ ግን ይሄውና ጠላቶቿ ሊያጠፏት ከውጪም ከውስጥም በተቀናጀ ሁኔታ በተደጋጋሚ ቢሞክሩም እስካሁን አለች፡፡ ነገም ትኖራለች፤ ለጊዜው ልጆቿ ተንገላታንባት እንጂ እርሷማ ሳለ ፈጣሪ ተመልሳ ታሪካዊ የክብር ሥፍራዋን እንደምትይዝ ጥርጥር የለውም – ሁሉም ነገር የሚፈራረቅባት ሁሉንም እንድታየው ነው፡፡ እነዚህን የታሪክ ወበሎዎችና አስካሪ እንክርዳዶች አቧራ ላይ ጥሎ የሚያንደባልልላት አምላክ አላትና በቅርብ የምናየው ልዩ ታሪካዊ ክስተት አለ፡፡ “stay tuned!” የሚሏት የጋዜጠኞች አባባል እንዴት ደስ እንደምትለኝ! አዎ፣ ተርፎ ከሚቀር ዕድሜና ጤናው አይንፈገን እንጂ ብዙ ድንቅ ነገሮችን በግምባር ማየታችን አይቀርም፡፡ ይህ የቅዠት ዘመን ሲያልፍ የሚጠሉን ይወዱናል፤ የሚንቁን ያከብሩናል፤ ያዋረዱን እግራችን ሥር ይወድቃሉ፤ … ለማንኛውም “stay tuned!”…

 

በደርግ ዘመን አንድ እንግሊዝኛ የማይችል የቀበሌ ለፋፊ “ነገ ሜይ ዴይ ስለሆነ በአብዮት አደባባይ ለሠልፍ እንድትወጡ!” የሚለውን ትዕዛዝ “ነገ መሄዴ ስለሆነ በአብዮት አደባባይ ለሠልፍ እንድትወጡ ” በማለት ጡሩንባውን እየነፋ ሲያውጅ “የቀበሌው ነዋሪ እመት ጠንፌ “እንዴ! አሁኑኑ ጥርግ ለምን አትልም፤ ላንተ ደግሞ የምን ሠልፍ ነው” አሉት አሉ፡፡ ይህንን ቀልድ አለነገር አላስታወስኩትም – የስንብት ሰላምታዬን ለማቅረብ ዳር ዳር እያልኩ ስለሆነ አንዳንድ ወዳጆቼ “ጥንቅር በላ!” ሲሉኝ እየታየኝ ነው ከወዲሁ ለፈገግታ ያህል ወደአብዮቱ ዘመን የኋሊት በመጓዝ ያቺን ጨዋታ የመዘዝኩት፡፡ እናም ማንንም የማትጠቅም ወይም የማትጎዳ አንዲት የግል መልእክት ቢጤ አለችኝ፤ ከ‹ጨዋ› መጣጥፈኛ ልንጠብቃት የሚገባን መሰነባበቻ ናት – ሌሎች ስለማይሉ እኔም አልልም አልልም፡፡ እናም ፈጣሪ ጨርሶ ፊቱን እስኪያዞርልንና የነጻነትን ብርሃን እስኪፈነጥቅልን ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ‹ያመት ፈቃድ ሞልቼ› ማረፍን ወድጃለሁ፡፡  እግር ኳስ ተጫዋች ጫማ ይሰቅላል፤ አጫዋቹ ወይም ሪፌሪው ደግሞ ምናልባት ፊሽካውን ሊጨምርበት ይችላል፡፡ እኔም ስለቴ እስኪሰምርና በጉጉት የምጠብቀው የነጻነት ቀን እስኪብት በዚያውም እውነተኛ የመደማመጥ ቀን እውን እስኪሆን ድረስ ብዕሬን ሰቀልኩ፡፡ ምክንያቶቼ ብዙ ናቸው፡፡ በጣም ጥቂቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደገዳም መቁነን በቀን ለጥቂት ሰዓታት ብቻ የሚለቀቅልንና የሚንቀራፈፈው በኢንሳ አሰለጦችም እንደሚጠለፍና እንደሚፈተሸ የሚነገርለት የወያኔ ኢንተርኔት እንዳለ ስለማይቆጠር ያበሳጫል፤ የመብራቱ በቀን ሠላሣ ጊዜ መቆራረጥም ያበሳጫል፤ ኑሮውም ያበሳጫል፤ የሰው ‹ትግስት› ገደብ ማጣትም ያበሳጫል፤ የራሴው ፍርሀትም ያበሳጫል፤ ተናግረህ አለመደመጥም ያናድዳል፤ የማይቀረው የፈጣሪ ፍርድ መጓተትም እንደሰው ሆነው ሲታዘቡት ያናድዳል፤ የሃይማኖት መጥፋት ያናድዳል፤ የሞራል መላሸቅ ያቃጥላል፤ የትውልድ በትምህርትና በዕውቀት መምከን ያቃጥላል፤ የራሴ የምትለው ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር አጥተህ የማታምንበት የነተበና የተቀዳደደ ባንዴራ ተመልካች አጥቶ 24 ሰዓት እንደተሰቀለ ሲውለበለብ ማየት ራሱ ያቃጥላል፤ የምታየው ወታደር ያንተን ጥቅምና ፍላጎት የማያስጠብቅ መሆኑን ስትረዳና ባንተ ገንዘብ በተገዛ የጦር መሣሪያና አንተው በምትከፍለው ደሞዝ ፀረ-አንተና ፀረ-ሀገርህ በሆነ መንግሥታዊ ተቋም እየታዘዘ አንተን ሊገድል መሠማራቱን ስታይ አንጀትን ያሳርራል፤ ሃይማኖት የለሽ የመንግሥት ሹመኛ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ የሚጠላ፣ ሥልጣንንና ገንዘብን ግን በእጅጉ የሚያፈቅር ሆኖ ስታይ ያናድዳል፤ ሀገርህ ውስጥ ሆነህ ሀገርህ ስትናፍቅህ በብስጭት ኮረንቲ ያስይዛል፤ በየምትሄድበት ቢሮ ካለገንዘብ መብትህ የማይጠበቅ ሆኖ ስታገኘው ያናድዳል፤ … ባጭሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የማያበሳጭና የማያናድድ ነገር የማግኘት ዕድልህ በጣም አናሳ ነው፡፡ ስለዚህ … ለነገሩ ምን ስለዚህ አለው፡፡ ያው ለጊዜው ዝምብሎ መናደድና መበሳጨት ነው፡፡

እስካሁን በድረገፆችና በሌሎች የመገናኛ መንገዶች የምሰዳቸውን መጣጥፎችና የብሶት ጦማሮች በማስተናገድና በማንበብ ከ24 ለማይበልጡ ጥቂት ዓመታት አብረን የዘለቅን ወገኖቼን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ምናልባት – እንዲያው ጠባብ ዕድል አግኝቼ ከጎርፉ በማምለጥ በነጻነት ቀን በአካል የምከሰት ከሆነ እንደስካሁኑ በብሶት ሣይሆን በወያኔና በጋራ ‹ጥረቶቻችን›ም ጭምር የጠፋውን ትውልድ ለማነፅ በሚደረግ ርብርብ ዘልዛላው ዕድሜየና ሙያዬ በሚፈቅዱልኝ ለመሣተፍ ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡ እስከዚያው ወኔው ላላችሁ መልካም የጭቅጭቅና የንትርክ ዘመን ይሁንላችሁ፤ ለሀገራችን ደግሞ ፈጣን የነጻነት መባቻ ይሁንልን!(መለያየት ሞት ነው … የሚለውን የጥላሁን ገሠሠን ጣዕመ ዜማ ከዚችው ጊዜያዊ ስቱዲዮ ልጋብዝና ልለያችሁ፡፡ እናንተዬ … ከአሁኑ ሆዴን ባር ባር አለኝሳ! ውይ እውነትም መለያየት ለካንስ ክፉ ሰው ነው፡፡ … )

“ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር”


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>