ግርማ ጌታቸዉ ካሳ
Muziky68@yahoo.com
ኅዳር 11 ቀን 2006 ዓ.ም
ኢሕአዴግን እንደ አንድ የሚመለከቱ፣ ሁሉን አባላቶቹን በጅምላ የሚፈርጁ ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን ኢሕአዴግ ዉስጥ የተለያዩ ቡድኖች አሉ። አንዱ የገነባዉን አንዱ ያፈርሳል። አንዱ ሲያነሳ አንዱ ይጥላል። አንዱ ሰላማዊ ሰልፍ ሲፈቅድ፣ አንዱ በጎን የዜጎችን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ይጋፋል። አንዱ የታሰሩ የሕሊና እስረኖች እንዲፈቱ ሲፈልግ፣ ሌላዉ «እዚያዉ ቃሊቲ ይበስብሱ» ይላል። አንዱ በጎና ቀና ሕሊና ሲኖረዉ፣ ሌላዉ ደግሞ የጠመመና የጫካ አስተሳሰብ ያለው ሆኖ ይገኛል።
በኢሕአዴግ ዉስጥ ያለው ተቃርኖ ሰሞኑን በጉልህ ለማየት ችያለሁ። ነገሩ እንዲህ ነዉ። በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ግፍ ለመቃወም፣ በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያዉያን ወደ ሳዉዲ ኤምባሲ ያመራሉ። ወዲያዉ የደህንነት ሰራተኞች ባዙቃቸዉንና እና ዱላቸውን ይዘው፣ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከማድረግ ይልቅ፣ ሰልፈኞችን መደብደብ ጀመሩ። ብዙዎች ታሰሩ።
ሰልፉ፣ የደህንነት ሰራተኞችና ፖሊሶች ሳይቀሩ ሊቀላቀሉት የሚገባ ሰልፍ ነበር። በሰልፉ የተነሳዉ ጉዳይ፣ ኢትዮጵያዉያንን በሙሉ ያዋረደ ጉዳይ ነዉ። ነገር ግን ፣ የዜጎቻችን መብት ተረግጦ በሳዉዲ የተፈጸመዉን ድብደባ ለመቃወም፣ በአገሩ የወጣዉ ሕዝባችን ተደብድቦ ተመለሰ።
በዚህ ጉዳይ ላይ ፣ አልጃዚራ እንደዘገበው፣ የኢሕአዴግ መንግስት ቃለ አቀባይ፣ አቶ ሽመለስ ከማል፣ አስተያየት ሰጥተዉበታል። «ሰላማዊ ሰልፉ ሕገ ወጥ ነዉ። ፍቃድ አልተሰጣቸውም። በኢትዮጵያዊያን መካከል ፀረ-አረብ ስሜት (anti-Arab sentiments) እንዲኖር ለማድረግ እየሞከሩ ነዉ። ስለዚህ ፖሊስ እርምጃ ወስዷል» ነበር ያሉት።
አቶ ሽመልስ እንዲህ ማለታቸውን ከአልጃዚራ ዘገባ ሳነብ፣ ልክ ወላፈን በፊት ያለፈ ይመስል በጣም ደነገጥኩኝ። ለማመን አልቻልኩም። ደቂቃዎች እያለፉ፣ ፍም ላይ እንደተጣደ ምጣድ፣ ዉስጤ መንደድ ጀመረ። የኢትዮጵያዉያን ስሜት ተጎድቶ ባለበት ወቅት፣ ቆስለን ባለንብት ወቅት፣ ግፍ ለፈጸሙብን አረቦች ስሜት የምንቆረቆርበት ጊዜ ነዉን ? ይህ አይነቱ የኢትዮያዉያንን ስሜት ክፉኛ የሚጎዳ አስተያየት ከአንድ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል፣ ያዉም የመንግስት ባለስልጣን፣ ይጠበቃልን ? በእዉኑ እንዲህ አይነት፣ ለሕዝብ ስሜትና ክብር ፍጹም ደንታ የሌላቸው ሰዎች ናቸዉን የሚገዙን ?
«በቂ የጥበቃ ኃይል እንዲኖር ዝግጅት ስላላደረግን፣ ሕዝቡም በንዴት ዉስጥ ስለሆነ ፣ የሳዉዲ ኤምባሲን የማቃጠል ተግባር ሊፈጸም ይችላል» የሚል ስጋት ኖሯቸው ሊሆን ይችላል፣ ሰልፉን በኃይል ያስቆሙት። ነገር ግን አንድ የዘነጉት ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ሕዝብ መሆኑን ነዉ። ላለፉት 5 ወራት በተለያዩ የአገራችን ግዛቶች በርካታ ሰልፎች መደረጋቸውን ማስታወስ እፈልጋለሁ። አንድም ድንጋይ አልተወረወረም። አንዲትም ንብረት አልጠፋችም። እንደዉም በደሴ ሰልፈኞቹ ለፖሊስ አበባ ያድሉ ነበር። በርግጥ ሕዝባችን የተከበረ፣ የሚያኮራ፣ ጨዋ ህዝብ ነዉ።
አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች ሰልፍ ለማድረግ፣ በሕጉ መሰረት ባለስልጣናት ቢያሳዉቁም፣ አሁንም ሕገ መንግስቱ ተንዶ፣ ሰልፍ ማድረግ እንደማይችሉ ነዉ በደብዳቤ የተነገራቸው። እንኳን ሌሎች ድርጅቶች ሰልፍ ሲጠሩ መከልከል ቀርቶ፣ በዚህ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳይ፣ እራሱ ኢሕአዴግ ሰልፍ መጥራት ነበረበት። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲክ ሳይንስ መምህር የሁኑት አቶ ሰይፉ ኃይሉ፣ በቅርቡ በለቀቁት ጽሁፍ « why not the government has arranged even public demonstration at least in our major cities to condemn the event and send message to the world?» ሲሉ ነበር የጠየቁት።
አሁን ደግሞ ወደ ሌላ የኢሕአዴግ ባለስልጣን ልዉሰዳችሁ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶር ቴዎድርስ አዳኖም። ኅዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም ዶር ቴዎድሮስ፣ ከሳዉዲ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ጊዜያዊ ማረፊያ ድረስ በመሄድ እንዳጽናኑና እንዳበረታቱ ፋና ዘግቧል። በርግጠኘንት ማረጋገጥ አልቻልኩም፣ ግን ዶክተሩ፣ ስደተኞች፣ የአገራቸውን መሬት በአይሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው እንደተቀበሏቸው የሚገልጹ አንዳንድ አስተያየቶች ፌስቡክ ላይ አንብቢያለሁ። ከአጥር አልፎ ሕዝብ ጋር መቀላቀል ማለት ይሄ ነዉ !!
ቅዳሜ ኅዳር 7 ቀን ዶር ቴዎድሮስ ፣ አዲስ አበበ በተደረገ ሶስተኛዉ የአለም ቀፍ ፋሚሊ ፕላኒንግ ኮንፍራንስ ላይ ያደረጉትን ንግግርም ማንሳት እፈልጋለሁ። «ዜጎቻችን ወደ አገር ሲመለሱ፣ ነገሮች በተስተካከለ ሁኔት እንዲሄዱ ለማድረግ እንሞክራለን። ሳዉዲዎች ሕገ ወጥ ናቸው (ከአገር ዉጡልን) ቢሏቸው፣ ግድ የለም፤ የሚሄዱበት አገር አላቸው። አጠንክሬ ላረጋግጥላችሁ ፣ ዜጎቻችን በአክብሮት እንቀበላቸዋለን» ነበር ያሉት። ከአንድ ጨዋ፣ የተማረ፣ በሳል መሪ የሚጠበቅ ግሩም ንግግር ! በአቶ ሽመልስ ከማል አይነቶቹ የደማዉ ልቤ ትንሽ ታደሰ።
ምን አለ ኢሕአዴግ እራሱን ከሽመልስ ከማሎች አጽድቶ ቴዎድሮስ አዳኖሞችን ቢያበዛ ? ምን አለ ባለስልጣናቱ የሚሰብርና ለሕዝብ ንቀት የሞላበት ንግግር ከሚናገሩ፣ የሚያሰባብስ፣ የሚያነጽ፣ የሚገነባ ንግግር ቢናገሩ ? ምን አለ ዜጎችን በማሰቃየት፣ በመደብደብ ፣ ሽብርተኞች እያሉ በማሰር፣ በማንገላታት ከሚደሰቱ፣ ዜጎች ሲጠቁ ማዘን ቢጀመሩ ? ምን አለ እንደ እንስሳ ከሚሆኑ እንደ ሰዉ ቢሆኑ ?
እንግዲህ እነቴዎዶሮስ አዳኖም የሚያረጉትን እያበረታታን፣ የተለየ ትእዛዝ እየላኩ፣ ዜጎችን የሚያስደበድቡ ፣ የዜጎችን መብት የሚረግጡና በዜጎችን መቆሳቆል የሚደሰቱ፣ የአገዛዙ ባለስልጣናትን ለማጥራት ሁላችንም ተባብረን መስራት ይኖርበናል። እነዚህ ግለሰቦች ለኢሕአዴግም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እርግማን ናቸው!!!! አገራችንን እንዲያምሱና እንዲያወኩ ሊፈቀድላቸው አይገባም።በተለይም የኢሕአዴግ ደጋፊዎች እነዚህ ሰዎች የድርጅታቸው ጠንቅ፣ ድርጅታቸው የበለጠ እንዲጠላ የሚያደርጉ መሆናቸውን አዉቀቁ፣ እነርሱ ላይ ዘመቻ እንዲጀምሩ አሳስባለሁ።
በመጨረሻ አንድ ነገር ጣል ላድርግና ላቁም። በዚህ ወቅት የ«ጠቅላይ ሚኒስቴራችን» ኃይለማሪያም ደስ አለኝ መሰወር ነዉ። እኝህ ሰው ዝምታን ለምን መረጡ ? ጋዜጠኛ ወሰን ሰገድ፣ «አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ “እስረኛ” ናቸዉ» በሚል አዉራምባ ታይምስ ላይ ባወጣዉ ጽሁፉ፣ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የሕዝብን ትረታ እንዲያዳምጡ፣ ከአማካሪዎቻቸው አጥር እንዲወጡ፣ እንደመሪ አገር መምራት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርቧል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማሪያም በ3ኛዉ የአፍሮ-አረብ ስብሰባ ላይ ለመገኘት (ሳዉዲዎችም ያሉበት) ወደ ኮዌት ትላንት ኅዳር 10 2006 ዓ.ም ቀን አመርተዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በቀጥታ የተባበሩት መንግስት ክላይሜት ቼንጅ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ዋርሶዉ ፖላንድ ያመራሉ።(የአለማችን የአየር ሁኔታ በወገኖቻችን ላይ ከደረሰዉ ግፍ በልጦ ማለት ነዉ)
አቶ ኃይለማሪያም የተማሩ ሰው ናቸው። በዚህ ወቅት ከአገር ምንም አይነት መግለጫ ሳይሰጡ፣ ሕዝቡን ሳያበረታቱ፣ ከአገር ዉጭ መዉጣታቸው፣ ምን ያህል ተሰሚነታቸውን እንደሚጎዳ ያጡታል ብዬ አላስብም። ታዲያ ምን ነክቷቸው ነዉ እራሳቸዉን እንደዚህ የሚያገምቱት? ወደፊት በስፋት የምንነጋገርበት ይሆናል።