Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ማስታወሻ በቸግራችን ለደረሳችሁልን ኢትዮጵያውያን በሙሉ

$
0
0

በሣዑዲ ዓረቢያ የምንኖር ወገኖቻችሁ

illegals_web_0በሳዑዲ ዓረቢያ ከግማሽ ሚለዮን በላይ የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተን እንገኛለን፡፡ ከሃገር ያስወጣንን ድህነት ለማሸነፍ ብዙውን ግዜ ከአቅም በላይ የሆኑ የጉልበት ስራዎችን እና ስነልቦና የሚጎዱ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ በሆኑ የስራ መስኮች ተሰማርተን እስከአሁኑ ግዜ ደርሰናል፡፡ በሺዎች የምንቆጠር ደግሞ ባለንበት ሃገር ቤተሰብ መስርተን እና ሃብት ንብረት አፍርተንና ለአመታት በአንፃራዊ ሰላም ስንኖር ቆይተናል፡፡ የሃገሪቱ መንግስት ህገ ወጦች ናችሁ በሚል ሰብአዊ መብትን በጣሰ መንገድ በዜጎቻችን ላይ የሚፈፅመው አሳዛኝ ድርጊት እስከተፈጠረበት ግዜ ድረስም በሃገራችን ያጣነውን የስራ ዕድል ሳዑዲ ዓረቢያ ላይ ተፈጥሮልን በሃበሻነታችን ተፈልገን የምንሰራ እንጂ ሃበሻ በመሆናችን እንድንሸማቀቅ የተደረግንበት አጋጣሚ የጎላ አልነበረም፡፡ አሁን ባለው ወቅታዊ አሳሳቢ ችግር በአስር የሚቆጠሩ ትናንት አብረውን የነበሩ ወንድምና እህቶቸችንን የመቅበር እድል እንኳን ሳናገኝ ተሰናብተናቸዋል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩት ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በጤና ጥለዋት የወጧትን ሃገራችንን በበሽታ ሊመለሱባት እየናፈቁ ነው፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ይዞታው ከግዜ ወደግዜ እየተባባሰ በሚመጣ ማቆያ ክፍል እና እስር ቤት ውስጥ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡

ውድ ወገኖቻችን፡ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ በሌላቸው ኢትዮጵያውያን ላይ እየተወሰደ ባለው ኢ-ሰብአዊ እርምጃ መነሻ በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን ልብ ምን ያህል እንደተነካ እና ለችግራችን ደራሽ መሆናችሁን ማሳየታችሁ እዚህ ያለንበትን ስቃይ እንድንረሳ የሚያደርግ ትልቅ ማፅናኛ ነው፡፡ ይህ የወገን መተባበር ካለንበት ችግር ተላቀን ሁላችንም ከስደት ተመልሰን ሃገራችንን  ለማልማትም ትልቅ አቅም እንደሚሆን አንጠራጠርም፡፡

ውድ ኢትጵያውያን፡ በመላው ዓለም በምታደርጓቸው የተቃውሞ ሰልፎች እና የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች ብሶታችንን ለአለም ማሰማታችሁ የማይተካ ሚና አለው፡፡ ይህ አጋርነታችሁ እንዲጠናከር እየጠየቅን ጥቂት ነጥቦችን ለማስታወስ ወደድን፡፡ ቀዳሚው ነጥብ ኢ ሰብአዊ ድርጊቶቹ የሚፈፀሙት በውል በሚታወቁ ጥቂት አካባቢዎች እና ግለሰቦች በመሆኑ ሃገርን እና ህዝብን አጠቃላይ በጅምላ የመፈረጁ አካሄድ ችግራችንን ከመቅረፍ ይልቅ በቀጣይነት ያልታሰበ ጉዳት እንዳያስከትል ሊታሰብ ይገባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የምንሆን ኢትዮጵያውያን የምንገኝ ስንሆን ሃገርን እና ህዝብን በጅምላ የመፈረጁ አካሄድ ከገፋ ህጋዊ ሁነው በሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅእኖ እጅግ ከባድ ነው፡፡ በተለይ ምንጫቸው ባልተረጋገጡ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች በዚያ የሚኖሩ ህጋዊ ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመጠላት እና የመገለል አደጋ እያመጣ ይገኛል፡፡ ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ የጎላ ባይሆንም አገርን በአገር ላይ ህዝብን በህዝብ ላይ የማነሳሳት አዝማማያ ያላቸው አካሄዶች  የሃገራቱን እና የዜጎች ለዜጎች ግንኙነት ታሪካዊ እና ቀጣይ ግንኙነትን  ታሳቢ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ የአንድን ሃገር ሉአላዊነት ማክበርም እኛ ከሌሎች የምንጠብቀው በመሆኑ ለሌሎችም ልንሰጠው ግድ ይለናል፡፡ በተጨማሪም የችግሩን መነሻ እና ለዚያ የሚመጥን አፀፋም እኛኑ ሚዛናዊ የሚያስብለን የብስለት አካሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም ሚዛናዊነት በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ በሁሉም ጉዳይ ከኛ ይጠበቃል፡፡

በስተመጨረሻም ለማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን እያደረጋችሁ ያላችሁት ድጋፍ እና ጫና የሃገራችን መንግስት ዘግይቶም ቢሆን የማዳን ጥረት እንዲጀምር አስገድዶታል፡፡ በሳዑዲ መንግስትም ይደርሱ የነበሩ የመብት ጥሰቶች ጥቂትም ቢሆን ጋብ እንዲል አድርጎታል፡፡  በቀጣይ የምታደርጓቸው የአጋርነት ድጋፎች ለችግር የተጋለጡ ሁሉም ዜጎቻችን በሰላም ወደ ሃገራቸው ገብተው የስነልቦና ስብራታቸው ተጥግኖ አምራች ዜጎች እስኪሆኑ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡ በሃገራችን ፍትህ እና ልማት መጥቶ በሰው ሃገር የሚፈሰው ላብ እና እውቀት ለሃገራችን የሚውልበት ቀን እንዲመጣም በፀሎትም በሰላማዊ ትግሉም እንድትጠነክሩ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

በሣዑዲ ዓረቢያ የምንኖር ወገኖቻችሁ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>