ከዳዊት ሰለሞን
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም‹‹የኢትዮጵያ መንግስት በሳውዲ መንግስት ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ ገለጹ››
አሪፍ ሀሳብ ይመስላል፡፡ግን ምንድን ነው ተመጣጣኝ እርምጃ?እወስዳለሁ የሚሉንን እርምጃ ተመጣጣኝነት የሚለኩት በደረሰብን ውርደት ከሆነ ሳውዲዎች የሚከፍሉት ዋጋ ከዚሁ ጋር የሚስተካከል መሆን ይኖርበታል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን መንግስት በሳውዲ ኢትዮጵያዊያኑ ስለደረሰባቸው ወይም እየደረሰባቸው ስለሚገኘው ሰቆቃ እንኳን ትክክለኛ መረጃ የለውም፡፡የሞቱት ሰዎች ቁጥር ሶስት ብቻ ነው በማለትም ቴድሮስ ለሚዲያ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ለዚህ ምስቅልቅል መፈጠር የቀድሞው የጤና ባለሞያ ጣታቸውን በደላሎችና በኤጀንሲዎች ላይ መቀሰራቸውም ለጉዳዮ የቀረበ ምልከታ እንደሌላቸው አስረጂ ነው፡፡
አስቂኙ ነገር ቴድሮስ ስለሚወስዱት ተመጣጣኝ እርምጃ ተጠይቀው ‹‹ወደፊት ምን እንደሚሆን እናጠናለን›› ብለዋል፡፡እስኪ በዚህ ጉዳይ ኢህአዴጎች/በማህበረሰብ ገጾች ደጋፊነታቸውን ያወጁ/ ሁሉ ምላሻቸውን ይስጡን፡፡
በሳውዲ ወገኖቻችን ኢህአዴግ፣ተቃዋሚ፣ትግሬ፣አማራ፣ኦሮሞ፣ክርስቲያን ሙስሊም ሳይባሉ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡አሁን ቴዲ ተመጣጣኝ እርምጃ እወስዳለሁ ሲሉ በሳውዲ ዜጎች ላይ ምን መዓት ሊያወርዱ ይሆን ?
እንበልና ከሳውዲ ጋር መንግስት ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት አቋረጠ፡፡ይህ እንዴት ተመጣጣኝ እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ግኑኝነቱ በመቋረጡስ ተጎጂ የሚሆነው ማን ነው?
ሳውዲ ስታር የተባለው በሼህ አላሙዲን ስር የሚገኝ ኩባንያ ቤልጂየምን የሚያክል መሬት በአንድ የሲጋራ ፓኮ መግዣ ዋጋ ተከራይቶ ከሳውዲ መንግስት በሚደረግለት የገንዘብ ድጋፍ ሩዝ እያመረተ ለሳውዲ ይልካል፡፡ይህንን መንግስት አቋርጣለሁ ቢልም የሚጎዱት ሼሁ ብቻ ናቸው ፡፡ሳውዲዎቹ ሌላ መሬት ፍለጋ ገንዘባቸውን ይዘው እብስ ይላሉ፡፡እናስ ቴድሮስ ምን አይነት ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወስዱ ይሆን?
የ1997ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት ከ200 ሰው በላይ መገደሉ አይዘነጋም፡፡አጣሪ ኮሚሽኑ ለፓርላማው ባቀረበው ሪፖርት ወታደሮች በተሰላፊዎቹ ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ መውሰዱን ተናግሮ ነበር፡፡ወዳጄ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ወታደሩ ምን ተረደገ?ምንም፡፡ቴድሮስ ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን ብለው የሳውዲን ኢምባሲ ቢዘጉ ምን እንላቸዋለን?ምንም፡፡