ከያሬድ አይቼህ – ጁላይ 15፥2013
አቶ ጃዋር መሃመድ የኢስላምና የኦሮሞ ትግል አይነጣጠሉም የሚል ሃሳብ ያቀረበበትን ቪዲዮ ተመለከትኩ። ሀጂ ነጂብም “80% የኢትዮጵያ ሙስሊም ኦሮሞ ነው” ማለታቸውንም ሰምቻለሁ። እነዚህ ወገኖቻችን ሃሳባቸውን የመግጽና የእምነት መብታቸውን አከብራለሁ። ያሳሰበኝ ጉዳይ ግን የዲያስፓራው ኢትዮጵያውያን ፓለቲካ ሊሂቃን ለኦሮሚያዊነት ተገቢውን እውቅናና ክብር ባለመስጠቱ ፡ የኦሮሞን ጥያቄ ፅንፈኛ ሙስሊሞች ሊጠቀሙበት መዘጋጀታቸው ነው።
የዲያስፓራ ሊሂቃን በተደጋጋሚ የኦሮሞን ጥያቄ በማንጓጠጥ ፡ በማሽሟጠጥ ፡ በመናቅና ችላ በማለታቸው የተነሳ የኦሮሚያዊነት ማንነትን እንጀ ጭንብል ተጠቅመው በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ውጥረትን መፍጠር የሚፈልጉ ፅንፈኛ ሙስሊሞች ብቅ ማለት ከጀመሩ ቆይቷል። ይሄንን ስል ጃዋርም ሆነ ሀጂ ነጂብ ፅንፈኛ ናቸው ማለቴ አይደለም። የነገሩ ዝንባሌ ግን ወደፅንፈኝነት የሚንደረደር ይመስላል።
የአገራችን ሊሂቃን ፡ በተለይ የአማራ ሊሂቃን ፡ አሁን አገራችን ላለችበት የፓለቲካ ቅርጽና ይዘት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የተጫወቱት ሚና ግን ሁሉ የሚያስመሰግን ብቻ ሳይሆን የሚያስወግዝም ጭምር ነው። ለምሳሌ ለኤርትራ መገንጠል ዋናው ተጠያቂ የአማራ ሊሂቃን ናቸው። ኤርትራን በኮንፌደሬሽን ከመያዝ ይልቅ በጉልበት እና በሞኝነት ኤርትራን ከ’እናት አገሯ ጋር ትቀላቀል’ ብለው አሁን የኤርትራ ህዝብ ለገባበት ስቃይ እና መከራ የዳረጉት የአማራ ሊሂቃን ናቸው።
ከዛ ትልቅ ስህተት ያልተመረው የዲያስፓራ ሊሂቃን (አማራና ሌሎች ብሄሮችን ያካትታል) ኦሮሚያዊነትን በመናቅ የኦሮሞን ጥያቄ በፅንፈኛ ሙስሊሞች እንዲጠለፍ አሳልፈው እየሰጡት ነው። የኤርትራዊነትንና እና የኢትዮጵያዊነትን ማንነቶች አብሮ የመኖር አቅም ያልተገነዘቡት የአጼው ሊሂቃን ፡ ኤርትራን አስገነጠሉ። አሁን ደግሞ የአጼው ሊሂቃን ልጆች እና የልጅ ልጆች ለኦሮሚያዊነት እና ለኢትዮጵያዊነት በቂ የማንነት ምህዳር ከመፍጠር ይልቅ ፡ “ኦሮሚያ የሚባል አገር የለም” በሚል የሞኝ ዘፈን ኦሮሚያን ለፅንፈኞች እየዳረጓት ይመስላል።
ኦሮሞን መናቅ የኤርትራውን አይነት ሁኔታ እየፈጠረ ነው። ኤርትራውያንን በመርዳት ኢትዮጵያን ማዳከም የፈለጉ ባዕዳን ሃይሎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ወገናችን የሆነውን የኤርትራን ህዝብ ከኢትዮጵያዊው ወገኑ ለይተው ለፋሽስት ስርዓት ዳርገውታል። ኦሮሚያውያን ወገኖቻችንንም ካላከበርናቸው ፡ ለማንነታችው ሙሉ እውቅና ካልሰጠን ፡ ጥቂት ኢስላሚስት ኦሮሚያውያን በባዕዳን ተደግፈው ወደ አስከፊ ነውጥ እና ቀውስ አገራችንን መዳረጋቸው አይቀሬ ነው።
ለኦሮሚያዊነት እውቅና መስጠት የኦሮሞን ህዝብ ማክበር ነው። እውቅና መስጠቱ የተከፈተውን ቀዳዳ ይደፍነዋል። ካልሆነ ግን ቀዳዳው እየሰፋ ፡ ኢስላሚስት ኦሮሚያ መመስረቷ አይቀሬ ነው። ከታሪክ እንማር ፡ ከስህተታችን እንማር።
- – - –
ጸሃፊውን ለማግኘት፦ yared_to_the_point@yahoo.com