Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የማለዳ ወግ …ስደተኛው ዘፋኝ በሳውዲ በርሃ …(ነቢዩ ሲራክ)

$
0
0

ነቢዩ ሲራክ

Bekah

   የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ … እንደጨው ተበትነናልና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወገኖቸን በየሔድኩበት ከተማ ፣ እግር በጣለኝ የሳውዲ የቀለጡ በርሃዎች ወንድም እህቶቸን አገኛለሁ ። ላፍታም ቢሆን ጊዜ ሰጥቸ እየኑሩት ስላለው ኑሮ ፣ እየገፉት ስላለው ክፉም ደግ ተሞክሮ እጠይቃቸዋለሁ አንድም ሳይደብቁ የሆድ የሆዳቸውን ያጫውቱኛል …
እለተ ቅዳሜ በማለዳው ያቀናሁት በያንቦና በጅዳ መካከል በምትገኝ የዋዲ በርሃ ዙሪያ ነበር ። አየሩ ተቀያይሯል ፣ ከዚህ ቀደም ወደዚህ ቦታ ሳመራ እንደ እሳት ነበልባል የሚጋረፈው ሙቀት ዛሬ የለም ። ለስራ ወዳቀናሁበት በድቅድቁ በርሃ ላይ በተሰራው የድንጋይ መከስከሻ ፋብሪካ እንደደረስኩ አንድ መልከ መልካም ወንድም የግቢውን በር ከፍቶልኝ ለመግባት ወዴት መሄድ እንደምፈልግ ጠየቀኝ  ፣ ወጣቱ \ሃበሻ ለመሆኑ ቅንጣት ያህል አልተጠራጠርኩምና የሚጠይቀኝን ትቸ እኔው ጠየቅኩት “ሃበሻ ነህ! ” ነበር ያልኩ ። ይህን ስጠይቀው እንደ መሽኮርመም እና እንደመሳቅ እያለ “አዎ ሃበሻ ነኝ ፣ ኢትዮጵያዊ ! ” ሲል መለሰልኝ !  ብዙ ሃበሾች አላችሁ?  ስል ጥያቄየን ቀጠልኩ “አዎ አምስት ሃበሾች አለን! ” አለኝ ፈገግ እያለ … በአሻጋሪ መምጣቴን የሚጠብቀው የፋብሪካው ሃላፊ “አስገባው ፣ አስገባው! ” ሲል ፍልቅልቁ ወደ የት እንደምሄድ የጠየቀኝ ወንድም ተደናግጦ በወራጅ ብረት እንደነገሩ የተዘጋውን የግቢ ብረት አጥር ከፍቶልን እኔና የስራ ባልደረባ ረዳቴ የፊሊፒን ዜጋው ግላዲ ወደ ግቢው ገባን ፣ ወጣቱን ወንድም በመስኮት በኩል አንገቴን ወጣ አድርጌ ስራየን ከዋውኘ እንደማገኘው ቃል ገብቸለት ወደ ውስጥ ገባሁ  …

  unn2343     ሱዳኑ የፋብሪካ ሃላፊ ከድንጋዩ መፍጫ የቅርብ ርቀት ካለው ጋራጅ አጠገብ ከተሰራች ባለሁለትና ሶስት ዛኒጋባ ቆርቆሮ ቤት ወጥቶ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጥቶ ተቀበለን ። ድንጋዩን እየከሰከሰ ጠጠር የሚያደርገው ፋብሪካ ነጭ አመድ ወደ ሰማይ እየተፋ የጓራል …ዲንጋው እየተፈጨ ጠጠር እየተሰራ መሆኑ ነው! የመንገድ መደልደያ ፣ የምንገድ መጥረጊያ እና የመንገድ ማለስለሻ ዳምጤ ከባባድ የኮንስትራክሽን መኪኖችን ጨምሮ ጥገና የሚያስፈልጋቸው መኪኖች ጋራጁን አጨናንቀውታል  … ከጋራጁ ጀርባ ደግሞ እኛ መመርመር ያከብን የተሽከርካሪ ጎማ መአት ተከምሯል። …አምስት የተባሉትን ሃበሾች አግኝቸ እስካዎጋቸው ቋምጫለሁ …የፊት የፊቱን እያስቀረብኩ ፊሊፒኑ አጋሬ ምን መስራት እንዳለበት አሳወቅኩት ፣ ስራውን አጣድፊ ግን በአግባቡ መርምሬ እንደጨረስኩት ሌሎች ሁለት ሃበሾች ሃበሻ ወንድማቸው መምጣቴን ሰምተው ኖሮ በፈገግታ እየተፍለቀለቁ መጥተው ሰላምታ ተለዋዎጥን …

  ሃበሻ ዝር በማይልበት በርሃ ያገኙኝን ወንድም እነርሱም ሊያስተናግዱ ሊያጫውቱኝ እንደቋመጡ አልጠፋኝም … በተንቀሳቃሽ ኮንቴነር በፋይዚት ግሩም ሆና የተሰራቸው ማረፊያ ቤት  ከጋራጁ የቅርብ ርቀር ትገኛለች ። አቧራ የጎረሰውን እጀን ሳልተጠብ በበርሃው ወዳገኘኋቸው ወንድሞች ማረፊያ ቤት አመራሁ … ረመድ ረመድ እያልኩ ከመድረሴ ወንድሞቸ በደስታ እየተፍለቀለቁ ግማሽ መንገድ ላይ ተቀበሉኝ ! ጠባቧ ቤት ማረፊያ ቤት ብቻ እንዳልሆነች ከበር የተደረደሩትን ጫማዎች ስመለከት ገባኝና ጫማየን አውልቄ “ቤት ለእንቦሳ! ” ብየ ዘው ብየ ገባሁ…  ቤቷ ጽድት ያለች ናት … ሶስት አልጋዎች ሶስቱን ማዕዘኖች ጥግ ይዘው ተዘርግተዋል ። የተቀበሉኝ ወንድሞቸ ሶስት ሲሆኑ ዘግየት ብሎ ሌላ ወንድም ገባ … አምስተኛው ወንድም የት እንዳለ ስጠይቅ እሱ ስራ ላይ እንደሆነ ገለጹልኝ። ሁላችንም የምናወራው ከአልጋዎች ላይ ተቀምጠን ነው ።  እንደገባኝ ከሆነ አልጋዎች ይተኛባቸዋል ብቻ ሳይሆን በመቀመጫነት ያገለግላሉ!  … ጫዎታችን ከመጀመራችን በፊት እጀን ለመታጠብ ውሃ ቢጤ ስጠይቅ ድምጹ ጎርነን ያለው “ሸዋንግዛው እባላለሁ!” ብሎ የተዋወቀኝ ወንድም በእጅ ከምትያዝ ማቀዝቀዣ ውሃ ይዞ ወደ ” በር ላይ ላስታጥብህ! ” ብሎ ግማሽ ጎኔን ከበሩ ወጣ አድርጌ እንደነገሩ ጣቶቸን ውሃ አስነካሁ ብል ይሻላል ፣ ብቻ ታጠብኩ !

  unnajgj6    ወጋችን  የጀመርነው በድፍኑ አበሻ ሁኘ እንጅ ማንነቴን የተረዳ ሰው የለም! ብዙ የህይወት ልምዳቸውንና ስለስራቸው ስለተመለከቱት የቴክኒክ ስራየ ፣ ሱዳኑ ሲጠራኝ ስለሰሙት የእንጀራ ስሜና ስለ አጠቃላይ የሳውዲ ህይወት እንዳንፈራራ ፣ እንዳንደባበቅ ፣ እንደ መተዋወቂያ አወራን … ጋዜጠኛ መሆኔን ትንፍሽ ሳልል “ራዲዮ ትሰማላችሁ ፣ ኢንተርኔት ፊስ ቡክ ትከታተላላችሁ? ” በማለት ደጋግሜ ጠየቅኳቸው!  አዎንታቸውን ገለጹልኝ ። ስሜን የእኔ ነው ሳልል ታውቁታላችሁ?  ስላቸው አዎንታቸውን በዝርዝር ገለጹልኝ!  ስገባ በር የከፈተልኝ እያሱና የቀሩት ሁለት ያህሉ በአካል የማያውቁት  ግን ማንቴስ ተብሎ የተዋወቃቸው “የነቢዩ “  የፊስ ቡክ ጓኞች እንደሆኑ በኩራት ገለጹልኝ :) አክለውም በቅርቡ የለቀቃቸውን የራዲዮ መጠይቆች እያነሱ የሚያውቁትን ሰው ስም ስላነሳሁላቸው በደስታ ብዙ አወሩኝ !  … እንዲህ ጥቂት ከቀጠልን በኋላ ግን እነርሱ እዚህ ስላደረሳቸው መንገድ መጠየቅ ጀመርኩ !  ሁሉም የሆነውን ሁሉ ሲያጫውቱኝ  ” አበባ ተሸልሜ በጭብጨባ የተሸኘሁ ዘፋኝ ነበርኩ !” ያለኝ  ድምጸ ጎርናናው የሸዋንግዛው ታሪክ ልቤን ነካው …  ብዙም ሳልቆይ ግን የእውነተኛው አለም  ማንነቴን ገላልጨ ለወንድሞቸ ሳጫውታቸው ነገሮች ተቀያየሩ!  … በጣም ተገረሙ !  ብዙ ተጫወትን … ለዛሬ እንዳላደክማችሁ በሚል በሳውዲ በርሃ ስላገኘሁት ዘፋኙ ወንድም ትኩረቴን ላድርግ  …

     ሸዋንግዛው እና ከቀሩት ጓደኞቹ ሃገር ቤት አይተዋወቁም ። ዳሩ ግን ድህነት ፣ የኑሮ ውድነት ፣ የማደግ የመመንደግ ፍላጎት በቁንጮዋ ነዳጅ አምራች ሀገር በሳውዲ በርሃ ላይ አገናኝቷቸዋል ! … ከሁሉም ወንድሞች ይልቅ ዘፋኙን ስደተኛ  ሸዋንግዛውን እዚህ ያደረሰ መንገድ ለማወቅ ጓጉቻለሁ !  እናም ላፍታ ከዘፋኙ ወንድም ጋር የሆድ የሆዳችን ላፍታ አወጋን … ሸዋንግዛው ንጉሱ ይባላል ፣ እድሜው በአርባወቹ  ውስጥ እንጅ ከዚያ አይዘልም! ዘፋኝ መሆኑን ካጫወተኝ ታሪክ አልፎ በበርሃው ሲያንጎራጉር ከተቀረጻቸው ድምጾች እና የተለቀቀውን ነጠላ ዜማ ሰምቸ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም … “ዘመኑ የዘፋኝ ነው” በሚባልበት ዘመን ድምጸ መረዋውን  ዘፋኝ ወደ ሳውዲ ምን አመጣው ?  በሚል ባለጉዳዩ ስደተኛ ዘፋኝ ጠየቅኩት  … መልሶልኛል ….

    ሸዋንግዛው ንጉሴ በቀድሞው የአርሲ ክፍለ ከሃገር ሎዴ ኤዶሳ በሚባል አከቀባቢ በአንድ መንደር ተወለደ። የሙዚቃ ጥበብ ገና በብላቴና እድሜው የለከፈችው ሸዋንግዛው በሎዴ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ሲከታተል ጥበብ አብራው አደገች ። ገና ከጅምሩ የጥበቡ ምሳሌ ከልብ የሚወደውን ክቡር ዶር ጥላሁን ገሰሰን ጥሩ ምሳሌ አድርጎ ገሰገሰ።  ሎዴ የትምህርይ ቤት ኪነት ለመመረጠረም ተሰጥኦ ያደለው ተርገብጋቢ ድምጽ ተሰጥኦና ፍላጎቱን ደገፈው ፣  የቀደሙትን ዜማ እያነሳሳ ሲለው የራሱን እየገጠመና እያንጎራጎረ ህይወት በፈለገችው መንገድ ትጓዝ ዘንድ ሸዋ ብርታት አገኘ። ብዙም ሳይቆይ ታዳጊው ሽዋንግዛው ከትምህት ቤት ወደ ወረዳ ኪነት ከፍ እያለ ሄደ … ከወርቁ ቢቂላ ( በኋላ ከሃይሌ ገ/ስላሴ ጋር አለም አቀፍ ሩጫን ይሮጥ ነበር) ታዳጊ እያለ የሙዚቃ ዝንባሌ ስለነበረው በአርሲ ሎዴ የወረዳ ኪነት አብረው እንደሰሩ ሸዋ ሩቅ ተጉዞ ዘርዘር ያለ ትዝታውን አዎጋኝ ። ሸዋ ብዙ ትዝታ አለው ። በአስደሳቹ ፈገግ ፣ በአሳዛኙ ትክዝ  እያለ አጫውቶኛል …

ታዳጊው ሸዋንግዛው በወረዳው ኪነት ቡድን  ተግቶ እየሰራ ባለበት ወቅትም ወደ ክፍለ ሃገር ኪነት ቡድን ለመምረጥ በተደረገ ውድድር ከወረዳ ወደ አርሲ ክፍለ ሃገር ቢመረጥም የወረዳው ሃላፊዎች በቅንነት “ልጃችን አሰልጥለን አንሰጥም !” በማለታቸው ወጣቱ በሙያው ርቆ የመሄድ ስሜቱ ተጎዳ !  እናም በብስጭት ወደ ውትድርና አለም ገባ ። ሸዋንግዛው ማንጎራጎሩን ባንድ በኩል በሌላ በኩል ሳይወድ በተጎዳ ስሜት ገፋፊነት የገባበትን የውትድርና ስልጠና ወሰደ። ቀን ቀንን ሲወልድ ግን ውትድርናው ወደ ጦር ሜዳ ሳይሆን ወደ አሳደገው የሙዚቃ ጥበብ ዶለው !  ሸዋ በብስጭት የተጎዳኘው የውትድርና ስልጠና እንደጨረሰ የባሌ ሸዌ የጦር እዝ ማዕከል የኪነት ቡድን አባል ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም ።

     በጦሩ የኪነት ቡድን በመስራት ላይ እንዳለ የደርግን ስርአት የሚታገለው የኢህአዴግ ጦር ወደ ከተማዎች እየገፋ ሲመጣ የኪነት ቡድኑ ወደ ሲዳሞ በመሄድ ሌላ ተጨማሪ የመከላከል ስልጠና እንዲያደርግ ሲታዘዝ ሸዋንግዛው  ከጓዶቹ ጋር ስልጠናውን ወሰደ። ከዚያም ድልድሉ ወደ ሞያሌ ሆነና ወደ ዚያው አመራ። በጭንቁ ቀን ያልተለየው የጥበብ አውሌ ተጭኖት ማንጎራጎሩን ስላላስቆመው እንቅስቃሴውን ያዩ የሰራዊቱ አባላት ሸዋንግዛው የደቡብ እዝ ኦርኬስትራ ቡድን እንዲቀላቀል ግፊት አድርገው እንዲመረጥ ቢያደርጉም አሁንም የጦር አዛዡ ” ሸዋግዛውን ወደ ደቡብ እዝ አልለቀውም! ” በማለታቸው እድሉ ተጨናገፈ። ይህም ሲሆን ዳግም እክል የገጠመው ዘፋኙ ወጣት ተስፋ አልቆረጠም። ሙዚቃው እንቢ ቢለው በልጅነት ወደ ሚወደው ሌላ ሙያ አጋደለ። ባለበት ብርጌድ የእግር ኳስ ብቃቱን አስመስክሮ እግር ኳስ መጫወቱን በደስታ ተቀላቀለ  ! በወቅቱ ኳሱም ተሳክቶለት ኮከብ ኳስ አግቢ በመሆን ተመርጦ እንደነበረ ሲያጫውተኝ ህይወት በትግል እንደምትፈተን አሸንፎም መውጣት ግዴታ እንደሆነ ሸዋንግዛው በፈገግታ እየገለጸልኝ ነበር ። ኢህአዴግ መላ ሃገሯን ሲቆጣጠር ጦሩ ፈረሰና ከሞያሌ ወደ ኬንያ የገባው ሸዋንግዛው እና የቀረው ስደተኛው በቀይ መስቀል ትብብር ወደ ሃገር ቤት ሲገባ ቤተሰቦቹን ከጠየቀ በኋላ ወደ  አዲስ አበባ ገባ…

  232 አዲስ አበባ ለአርሲው ተወላጁ ለሸዋንግዛው የተመቸች ነበረች። በተለይም በልጅነት የተለከፈባት የሙዚቃ ጥበብ ተሰጥኦውን  የሚያጎለብትበት ብቸኛ እድል አገኘ ። እናም በየምሺት ቤቶች “ከተፋ ቤቶች” ተሰማርቶ ምሽቱን እያደመቀ እና ራሱንና ቤተሰቦቹን በመርዳት መስራት ጀመረ ። ባለትዳር የሆነው ሸዋንግዛው በምሽት ስራው በአሁኑ ሰአት ታዋቂ ከሆኑ ዘፋኞች ጋር እኩል ድምጽ ማጉያን ተጋርቶ በጥበብ ተናኝቷል !

  ይህም ሁሉ ሆኖ ፣ ይህንን የከበደ መንገድ ተጉዶ ሸዋንግዛው ከልጅነት እስከ እውቀት ሙጥኝ ያላትን ጥበብ አዳብሮ የራሱን ወጥ ዘፈን ለማውጣት አቅሙ አልገደደውም። ያም ሆኖ ግን  በማይቆጣጠረው እክል ስራውን ለሃገር መናኘቱ አልሆንልህ እያለው መቸገሩ አልቀረም። ሸዋንግዛው እንዲህ እየሆነ ህይወትን ሲገፋ ለማደግ የሚያደርገው ግብግብ ባያሸበርከውም ሩጫው አልፎ አልፎ  እንዳደከመው ሳይደብቅ አጫውቶኛል።  የጥበብ አውሌ ብቻዋን ከተዘፈቀበት ድህነት ራሱን ቀና አላደረገችውም!  ይህ እንዳይሆን ፣ በሰው ሰራሽ ምክንያት በጥበብ ላይ የሚሰራ ደባ እየደሰቀው መፈናፈኛ እንዳሳጣው ሸዋንግዛው ይናገራል ! በተለይም “ከከተፋው” ዘፋኝነት ጎን ለጎን ብዙዎችን ዘፋኞች ያሳወቀውን ነጠላ ዜማ ግጥምና ዜማውን ራሱ ደርሶ ቢያወጣም ሃገር ስራውን እንዳያውቅለት ጫና ፈጣሪዎች አላገዙትምና ድንቅ የባህል ዘፈኑ ሳይደመጥለት እንደቀረ ዜማዋን እንድሰማት በመጋበዝ ሸዋ ብዙ አጫወተኝ።  በሙዚቀኞች መካከል ውስጥ ለውስጥ የሚሰራውን “የቲፎዞ ” ድጋፍ ፣ አንዳንድ የሃገር ቤት ጋዜጠኞች በተለይም  የኤፍ ኤም ራዲዮ ጋዜጠኞችን ድጋፍ ማጣቱ አውኮተ አሰናክሎታል። ሸዋ ባለሙያዎች ሙያቸውን በሙስ አርክሰው የሚሰሩትን በገደምዳሜም ቢሆን አጫውቶኛል። እኔም በሙስናው ዙሪያ ያለውን አበሳ ወገንተኛ ዘመም የቲፎዞ አካሄድ ግልጥልጥ አድርገው ካወሩት ጉዳዩ ብዙ እንደሆነ ከዚህ በፊት የማውቀውን ታሪክ ሸዋንግዛው አስታወሰኝ …

ሸዋን ሳውዲ አረቢያ ስላደረሰው መንገድ እና የወደፊት ህልሙ እንዲያጫውተኝ ጠይቄው እንዲህ አለኝ ” ነጠላ ዜማው አልሳካ ሲለኝ ድህነቱንና የኑሮ ውድነቱን ለማሸነፍ እንዳልቻልኩ የገባት ጅዳ የምትኖረው እህቴ በኮንትራት ስራ እንድመጣ አመቻቸችልኝ። ተሳክቶም ልክ የዛሬ 11 ወር ወደ ሳውዲ አረቢያ በኮንትራት ስራ መጣሁ ።  በዘፈን ብዙዎች ይሳላካላቸዋል ። እኔ የእድል ጉዳይ ሆኖ አልተሳካልኝም ። ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ። የመጣውን መቀበል እንጅ አላማርረውም። አሁን የምሰራው “ሮለር ” በሚባል የኮንስትራክሽን ተሽከርካሪ ላይ ነው። በሃገራችን ዳምጤ ይባላል። ዳምጤን እየነዳሁ በርሃውን ማቅናት ነው የአሁን ስራየ ። በቃ ! ህይዎት እዚህ አድርሶኛል! እንደኔ ሃሳብና ህልም ከሆነ እንደ ምንም የሁለት አመት ኮንትራቴን ጨርሸና ገንዘቤን ሰብስቤ እግዚአብሄር ብሎ የሙዚቃዋ አድባር ከጠራችኝ ወደ ሙዚቃው መመለስ ነው ሃሳቤ፣ ካልሆነ የማገኛትን ይዠ ቤተሰቤንና ራሴን እየረዳሁ በሃገሬ መኖር ነው የምፈልገው!  ለእስካሁኑ  እግዚአብሔር ይመስገን! ወደፊትም እሱ ያውቃል! ” በማለት ሸዋንግዛው መልሶልኛል…

    ሸዋንግዛው “ይሻላል እንደሁ! ” ብሎ በኮንትራት ከመጣ ቀን ጀምሮ ስራውን የበርሃውን ቃጠሎ ተቋቁሞ ከጓደኞቹ ጋር እየሰራ ቢሆንም በደመወዝ አከፋፈሉ ላይ ቅሬታ እንዳለውና ይህም ፈተና እንደሆነበት ገልጾልኛል።  ከሸዋንግዛው ጋር በነበረን ቆይታ በበርሃው ውሎ አዳር ስለሚለከታቸው በእረኝነት ተቀጥረው ስለሚገፉ ኢትዮጵያውያን ይዞታ ሲያጫውተኝ እንዲህ ነበር ያለኝ ” የእኛን ተወው ደህና ነው ፣ የእረኛ ወንድሞቻችን ህይወት ብታየው ያሳዝናል፣ ሃበሾችን ከሩቅ ታውቃቸዋለህ። ስናናግራቸው ደስተኛ እንዳልሆኑ ይገልጹልናል። ወደ ሃገር ቤት እንዳይመለሱ ከድህነትና ኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ ያላቸውን ቅሪት አንጠፍጥፈው ተሰደዋልና ምን ይዘን እንግባ ?  ይሉሃል ! ምን ትላቸዋለህ? ያ ያ ስላለ እንጅ ከኢትዮጵያ መጥተህ በበርሃው ውሃ እየተጠማህ የመንጋ በግ ፣ ፍየልና ግመል እረኛ ሆነህ ኑሮን መግፋት ይከብዳል። ታለቅሳለህ! ” ሲል ፊቱን በሃዘን ክችም አድርጎ ዘፋኙ አዝኖ አሳዘነኝ …

    አዎ እኔም በአካል ተገኘቸ ያየሁትና ዛሬ በርሃ ላይ ባገኘሁት ዘፋኝ የተገለጸልኝ ህይወት በእርግጥም ያሳዝናል!  ያማል!  ማለቱ ብቻ ስሜትን የሚገልጸው አይሆንም …ብቻ በባለጸጋ አረቦች ሃገር ከአረቦቹ ጓዳ ፣ እስከ ደራው ከተማና በርሃው የእኛ ህይዎት ሲሰሙት ውለው ቢያድሩ ተነግሮ አያልቅምና በዚሁ ልግታው እና ወደ በርሃው ውሎ የመጨረሻ ምዕራፍ ላቅና…

    ከሸዋንግዛውና ከጓደኞቹ የነበረኝ አጭር ቆይታ ታላቅ የጽናትን እና ዥጉርጉሩን ህይዎት የተረዳሁበት መልካም አጋጣሚ ሆኗልና እዚያው ውየ ባድር ደስታየ በሆነ ነበር … ያ እንዳይሆን የእንጀራ እና የህይወት ጉዳይ አልፈቀደልኝም!  እናም መለያየት ግድ ሆነ  ! በሳውዲ ራብቅ በርሃ ላይ ያገኘሁትን ዘፋኙን ሸዋንግዛውንና  ጓኞቹን ስለያቸው በፍቅር ተሳስቀን እና ተቃቅፈን ተሳስመን ነበር …ደግሜ ልጎበኛቸው ቃል በመግባት …

     ሸዋንዳኝን ስለየው ያቀበለኝን ባንድ ወቅት ሰርቷት በህዝብ ጀሮ ያልደረሰችውን “ሸዋ ጥበብ ያውቃል! ” ነጠላ ዜማው እየኮመኮምኩ በርሃውን ለቅቄ ወደ ጅዳ መገስገስ ጀመርኩ  …

” ከወዲያ ከወዲህ ስታንገላታኝ
ይህች የመንዝ ልጅ አስራ ልትፈታኝ
ቃሌ አይታጠፍም የመጣው ቢመጣ
እንዳሻት ታድርገኝ አላበዛም ጣጣ ” ይለዋል  ሸዋ… በጥበቡ የሸዋን ጉብል የከበደ ፍቅር ሲገልጸው ….
የሙዚቃው የደመቅኩት ምንጃርኛውን ሞቅ ደመቅ ባለው ቅንብርና ዜማ የታጀበ ብቻ በመሆኑ አይደለም!  የሸዋ ግጥሞች መልዕክት አላቸው …

     የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ ፣ እጓዛለሁ … እንደ ጨው ተበትነናልና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወገኖቸን በየሔድኩበት ከተማ  ፣ በቀለጡ በርሃዎች እና መንደሮችም ወንድም እህቶቸን አገኛለሁ ! እንዲህ በማለዳ ወጌ ወጋወጉን ለተሞክሮ ሳካፍላችሁ ደግሞ ደስታ ይሰማኛል ! ህይዎት እንዲህ ይኖራል …

ሰላም

ነቢዩ ሲራክ

YeMaleda Weg


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>