Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“አና ጐሜዝ አሁንም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ይቆረቆራሉ” –አቶ አስራት ጣሴ (የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ)

$
0
0

ከአቶ አስራት ጣሴ (የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ)

ከአና ጐሜዝ ጋር ከአንድ ሠዓት ተኩል ለማያንስ ጊዜ ነው የቆየነው፡፡ የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ከእኛ ጋ የተገናኙት ገለፃ ለማድረግ አስበው ሣይሆን የእኛን አስተያየት ለመስማት ነበር፡፡ ውይይቱ፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን የሚዳስስ ነበር፡፡ በወቅቱ ከሞላ ጐደል ተደጋጋፊ እንጂ የሚቃረኑ ሀሣቦች አልተነሱም፡፡ በእኔ በኩል፣ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል በከፍተኛ ችግርና አደጋ ላይ እንደሚገኝ፣ ኢትዮጵያም መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደሆነች፣ ከፊታችን አሳዛኝና አስጊ ሁኔታዎች እንዳሉ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ ሰላማዊ ትግሉን አስመልክቶ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታዎች እያሣየ መሆኑን ገልጫለሁ፡፡
Ana Gomez
“ሰላማዊ ትግል” የሚለው “ሰላማዊ እንቅልፍ” የሚል ደረጃ ላይ ለመድረሱ ዋነኛ ምክንያቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትከሻቸውን ታስረው ለመንቀሣቀስ ያለመቻላቸው ነው፡፡ የህዝባዊ ስብሰባዎች እና የሰላማዊ ሰልፎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ መታገድ፣ የአዳራሽ መከልከል፣ ልሳናችንን እንዳናሳትም መታገድን ጨምሮ በርካታ ሕገ መንግስታዊ ጥሰቶች እየተፈጸሙብን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕገ መንግስቱን እየጣሱ ነው እየገዙን ያሉት፡፡ ሕገ መንግስቱ እየተተገበረ ነው የሚያስብል ሁኔታ የለም፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ እየገባ ነው ያለው፡፡ ነገሮች ተባብሰዋል፡፡
የስልጣን ኃይል ሚዛኑ በማን እጅ ላይ ይገኛል ብሎ መጠየቅ እስኪያስፈልግ ድረስ ሁሉም ነገር ተወሳስቧል፡፡ በሚኒስትር ደረጃ የተቀመጡት ሲቪሎቹ ናቸው ወይስ ከጀርባ የሚያስተዳድሩን አሉ? ሂደቱ ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ ቀውስ ሊወስዳት የሚችል ትልቅ አደጋ ነው፡፡
ከአና ጎሜዝ ጋ በተተወያየንበት ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ አንድ ተወካይ ብቻ በፓርላማ እንደሚገኝን ተናግሬያለሁ፡፡ አስቀድመውም ያውቁታል፡፡ በ1997 ዓ.ም. የተቀማውን ድምጽ ትተን 180 የሚሆኑ ተቃዋሚዎች በፓርላማው መቀመጫ ነበራቸው፡፡ አሁን ግን ወደ አንድ ወርዷል፡፡
ኤልሳቤት ሃይኒ የተባለች የቢቢሲ ጋዜጠኛ ያነሣችውን ጥናት ለአና ጎሜዝ አሳይቻቸው ነበር፡፡ አንድ ፓርቲ በምርጫ ከ51-59 ፐርሰንት አግኝቶ ካሸነፈ ታላቅ ድል ነው፡፡ ከ60-69 አምጥቶ ካሸነፈ “ዝረራ” የሚባል ውጤት ነው፡፡ ከ70-79 አምጥቶ ካሸነፈ ደግሞ የሕዝቡን ጥያቄዎች የመለሰ ፓርቲ ነው፡፡ ከ80-89 የሚያገኝ ፓርቲ ግን የሚፈራ፣ አምባገነን፣ ጉልበተኛ ፓርቲ ነው፡፡ ከ90-99 ፐርሰንት ከተገኘ ደግሞ ምርጫ አልተካሄደም ማለት ነው ይላል፡- ጥናቱ፡፡ በኛ ሀገር ይኸው “99” አልፎ ዜኀር ነጥብ ስድስት ሁሉ ተጨምሮበታል፡፡ ስለዚህ ይሄ በግልፅ የሚያሣየው ፍፁም የዴሞክራሲ ስርዓት መጣሱን ነው፡፡ ምህዳሩ ተዘግቷል፡፡ ተደፍኗል፡፡

አስራት ጣሴ

አስራት ጣሴ

የተቃዋሚ ፓርቲዎች በየጊዜው የምናቀርባቸው የውይይት እና የእንደራደር ጥያቄዎች ከስልጣን ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡ ሀገራዊ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ብሔራዊ ውይይት፣ ብሔራዊ ንግግር ይከፈት ብለን ደጋግመን ብንጠይቃቸው ባለሥልጣናቱ አሁንም ያሾፋሉ፡፡ “የምርጫ ስነምግባር ደንብ” ፈርሙ እንባላለን፡፡ እንኳን “የምርጫ ስነምግባር ደንብ” ይቅርና የማንወደውን፣ እየተጐዳንበት ያለውን “የፀረ ሽብር አዋጅ” ተቀብለን ነው የምንተዳደረው፡፡ ምክንያቱም በሕግ የተደነገገ ነው፡፡ እንዴት ተደርጐ ነው “የምርጫና ስነምግባር ህግ” በምክር ቤት ጸድቆ በነጋሪት ጋዜጣ በወጣ ህግ ለይ ዳግም ፈርሙ የምንባለው? የሚል ሀሳብም አንስቻለሁ፡፡
መንግስት “ፀረ ሽብር” አዋጁን የማጥቂያ መሣሪያ አድርጎታል፡፡ ሽብርተኝነት የአውሮፓም፣ የአሜሪካም ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ የፀረ ሽብር ህግ አውጥተዋል፡፡ ወደ እኛ ሃገር መለስ ስንል የፀረ ሽብር ሕጉ የወጣው ሽብርተኞችን ለመቅጣት ብቻ ሳይሆን፣ ሰላማዊና ሕጋዊ ፓርቲዎችን ጭምር ለማጥቃት ነው፡፡
ሽብርተኝነትን በማንኛውም መልኩ፣ በየትኛውም ገፅታው እንቃወመዋለን፡፡ ሽብርተኝነት ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ በኢራቅ፣ በናይጄሪያ /ቦኮ ሀራም/ እናውቀዋለን፡፡ እዚህም በሕዝብ፣ በህፃናት፣ በእርጉዝ ሴቶች፣ በሽማግሌዎች፣ በወጣቶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እናውቀዋለን፤ እንቃወማለንም፡፡ ኢትዮጵያውያን በባህላችን፣ በአስተዳደጋችን፣ በኃይማኖታችን፣ በእምነታችን… ለሽብርተኞች የተጋለጠ ስነ ልቦና የለንም፡፡ “ሽብርተኝነት” ይምጣብን የሚል ልመና ካልተያዘ በቀር ኢትዮጵያዊ ሽብርተኝነት የለብንም፡፡ የ“ጸረ ሽብር” አዋጁ በሽብርተኝነት ከፈረጃቸው ፓርቲዎች መካከል… ለአብነት ግንቦት 7፣ ዋና መቀመጫው በአሜሪካና አውሮፓ ከተማዎች ነው፡፡ ይሄ እንቆቅልሽ ይሆናል፡፡ አወሮፓውያን ከተማዎቻቸውን ለአሸባሪዎች ምሽግነት መርጠዋል ማለት ይሆን?
ሌላ እንቆቅልሽም አለ፡፡ ስርዓቱ “ሽብርተኛ” ብሎ ያሰራቸው ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶችን እና ክብሮችን እያገኙ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት አለሙ፣ አንዱአለም አራጌ… ወዘተ በፀረ ሽብር አዋጁ ነው የታሰሩት፡፡ በ”ሽብርተኝነት” የተፈረጁት ግን በአሜሪካና፣ አውሮፓ ከተማዎች እንደፈለጋቸው እየተዘዋወሩ ነው፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ሽብርተኞችን እየደገፉ ነው ማለት ነው?
የፖለቲካ ምህዳሩ ከድጡ ወደ ማጡ እየገባ ነው፡፡ የሕዝብን ችግር፣ እሮሮ በሳዑዲ አረቢያ በዜጐቻችን ላይ የሚደርሰው እልቂት፣ የስራ አጥነት፣ በስታቲስቲክስ ማሣየት ይቻላል፡፡ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሙስና መንገስ፣ የስርዓቱ መገለጫ ሆኗል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የአውሮፓ ህብረትን ትኩረትና ዕይታ ሊስቡ ይገባል፡፡ ይሄን የምንለው ግን ትግሉን ታገሉልን ለማለት አይደለም፡፡ ትግሉ የራሣችን ነው፡፡ ትግሉ የኢትዮጵያውያን ትግል ነው፡፡ ነገር ግን እናንተም ደግሞ ባላችሁ ደረጃ፣ ባላችሁ የግንኙነት መስመር፣ የሚደረገውን ነገር ለማድረግ ጥረታችሁን ቀጥሉ ብለናቸዋል፡፡ የተወሰነ ድጋፍ ካልተደረገ ወደፊት ሊመጣ የሚችለው ችግር ሁላችንንም ጉዳት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ጉዳቱ ስርዓቱን የሚመሩት ሰዎችንም ጭምር የሚምር አይደለም፡፡
አና ጐሜዝ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያላቸው ግንዛቤና የመቆርቆር አቅም አሁንም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተረድቻለሁ፡፡ በውይይቱ ወቅት እንኳ ከሌላ የአውሮፓ ፓርላም አባል ጋር ያለመስማማት ሁኔታን አይቼባታለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና፣ ኢትዮጵያ ልታከብራቸው ከሚገቡ በዓለም ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ስብዕና ካላቸው ሰዎች መካከል አንዷና ትልቋ አና ጐሜዝ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጐሜዝ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርብ ይከታተላሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ያላቸው ተቆርቋሪነት ከ1997 ዓ.ም. ከነበረው የበለጠ ነው፡፡ የሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ዛሬም ለኢትዮጵያ ሽንጣቸውን ገትረው እንደሚከታተሉ ያመላክታሉ፡፡
በውይይቱ ወቅት “እኔ እኮ ዛሬ ኢትዮጵያ ለመግባት የቻልኩት አቶ መለስ በሕይወት ባለመኖራቸው ነው፡፡ በሕይወት ቢኖሩ እዚህ ሀገር አልገባም” ነበር ያሉን፡፡ ከፍተኛ ጥንካሬና ተቆርቋሪነት ነው ያየሁባቸው፤ ውይይታችን የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞችን ጭምር የሚመለከት ነበር፡፡
የአውሮፓ ፓርላማ ልዑካን ቡድን ኃላፊ በስብሰባው ላይ አልተገኘችም፡፡ እና ምክትሏ ሆና ነው ስብሰባውን የመራችው፡፡ “ኃላፊዋ በአሁኑ ሰዓት እዚህ ስብሰባ ላይ ያልተገኘችው ቃሊቲ እስረኞችን ለመጠየቅ ሄዳ ነው” ብላን ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተወካዮች መጥተው፣ ጠ/ሚኒስትሩ ከፈቀዱ በኋላ “ቃሊቲ” ሄደው ተከልክለው ሣይገቡ ነው የተመለሱት፡፡ እርሷም በዛው እለት በዚህ ጉዳይ ተበሣጭታ ወደ ሃገሯ ተመልሣ ለምክትሏ ስለሁኔታው ገልጻላት ነበር፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የእስረኞቹን ጉዳይ በበቂ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡
የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያላቸው እውቀት አናሳ ነው፡፡ የሚያውቁት ጥቂቱን ነው፡፡ ግንዛቤ አላቸው ከተባለ ደግሞ ብዙ ትክክል ያልሆነ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ ለምሣሌ ሀገሪቱ በልማት እየተራመደች መሆኗን፣ ኢትዮጵያ የአውሮፓ የፀረ ሽብር ከፍተኛ አጋር መሆኗን፣ የአፍሪካ መዲና መሆኗን… ይሄም የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ እንሚያሣይ የሚገልፁ አሉ፡፡ የአና ጐሜዝን ሩብ ያህሉን የማያውቁ አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ከኛ ለመስማት ስለነበር ፍላጐታቸው የሚያውቁትን ለኛ ለመናገር አስፈላጊ አድርገው ላይመለከቱት ይችላሉ፡፡ በውይይቱ ወቅት ሁሉም ጊዜ ሰጥተው በጥሩ ሁኔታ ነው ያዳመጡን፡፡ በትኩረት ያነሱት ግን በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መብዛት ነው፡፡

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>