Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ያለፉት ስህተቶች ትምህርት እንጂ ማነቆ አይሁኑ –ግርማ ካሳ

$
0
0

ግርማ ካሳ  

እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር፣  ኖቬምበር 17 ቀን 1996 ነበር። በሰርቢያ (የቀድሞ ዩጎስላቪያ) ፣  የክልል ምርጫ ይደረጋል።  በቩክ ድራስኮቪች የሚመራዉ SPO ፣ በቬስና ፔሲች የሚመራዉ GSS እና ሌሎች ድርጅቶች በአንድ ላይ ሆነው አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ። ነገር ግን  በወቅቱ የነበሩ አምባገነን ባለስልጣናት፣ እነ ስሎቦዳን ሚሎሶቪች አጭበረበሩ።  ከኖቬምበር 17 1996 እስከ ፌቡሩያሪ 11 1997 ድረስ፣ «ያጄድኖ» የሚል፣  ሕዝባዊ ተቃዉሞዎች በስፋት ተደረጉ። ባለስልጣናቱ፣  የሕዝቡ ሰላማዊ ተቃዉሞ አይሎ መምጣቱን ሲያዩ አፈገፈጉ። የተቃዋሚዎች ስብስብ በክልል ምርጫዉ ያገኙትን ምርጫ፣ ተቀበሉ። ሊበራል ዴሞክራቱ ዞራን ጂንጂች የአገሪቷ መዲና የቤል ግሬድ ከንቲባ ሆኑ።

 

ብዙም አልቆየም፣ በተቃዋሚዎች መካከል ችግር መታየት ጀመረ። በቩክ ድራስኮቪች የሚመራዉ ፓርቲና  በዞራን ጂንጂች በሚመራዉ ፓርቲ መካከል ልዩነቶች ተፈጠሩ። መካረር መጣ። የሕዝብን ጥያቄ አንግቦ በጋራ መቆም ተሳናቸው። በአደባባይ መወጋገዝ ጀመሩ። በአመቱ አገራዊ የፕሬዘዳንት ምርጫ ሲደረግ የሚሎሶቪች የሶሻሊስት ፓርቲ በቀላሉ ስልጣኑን ጨበጠ። የተለፋበት፣ የተደከመበት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከሸፈ። አምባገነኖች አሸነፉ። በሕዝብ ትግል የተገኙ ዉጤት እንደገና ተቀለበሱ። ዞራን ጂንጂችም ከናካቴዉ ከተመረጡበት የቤልግሬድ ከንቲባነት ተነሱ።

 

በ1998 በየክልሉ ተማሪዎች «ኦትፖር» ( በሰርቢያን ቋንቋ እምቢተኝነት) በሚል ስም ከታች ወደ ላይ የሆነ እንቅስቃሴ ጀመሩ። የተከፋፈሉ የፖለቲካ ደርጅቶች በአንድ ላይ እንደገና ተሰባሰቡ። ካለፉት ስህተቶች በመማር፣ ፍጹም ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለሚቀጥለው ምርጫ መዘጋጀት ጀመሩ። ከፍተኛ ጫና እየተደረገም ዝግጅቱ ተጧጧፈ። የገዥዉ ፓርቲ ደጋፊዎችን የመሳብ ሥራ በስፋት ተሰራ። በዚህም ምክንያት በርካታ የገዢዉ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ተቃዋሚዎችን መቀላቀል ጀመሩ። ኢቫን ስታምቦሊች ፣ የሚሎሶቪች አጋር የነበሩ ፖለቲከኛ ፣ ተቃዋሚዎች በመቀላቀላቸውም በሚሎሶቪሽ የደህንነት ሰራተኞች ታፍነው ተገደሉ።

 

ሴፕቴምበር 2000 ዓ.ም ምርጫ ተደረገ። የሚሎሶቪች ምርጫ ቦርድ፣ አሁንም የተጭበረበረ የምርጫ ዉጤት ይፋ አደረገ።  ያንን አስከትሎ  ኦክቶቦር  2000 ዓ.ም ፣ ትልቅ ተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ። ምርጫ ቦርድ የምርጫዉን ዉጤት ወደ ነበረበት እንዲመልስ ተገደደ። የተቃዋሚዎች እጩ የሆኑት  ኮስቶኒሳ እንዳሸነፉ ተገለጸ። የሚሎሶቪች ስልጣን ፍጻሜ ሆነ። የሰርቢያ ሕዝብ የማይቀለበስ ድል ተቀዳጀ።

 

ይሄንን ያለ ምክንያት አይደለም ያመጣሁት። በሰርቢያ፣ በመጀመሪያዉ ምርጫ  የተከሰተው፣ በኢትዮጵያም በምርጫ ዘጠና ሰባት ከተከሰተው ብዙ የሚለይ አይደለም። ያኔ በቅንጅት ጊዜ የሕዝብ ጉልበት አያሎ የወጣበት ወቅት ነበር። ነገር ግን በተቃዋሚዎች መካከል በተፈጠሩ ልዩነቶች፣ በቀላሉ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ስልጣን ላይ ለመቆየት ቻለ። (በገዢው ፓርቲ የደረሰው ወከባ፣ ግድያ፣ እሥር፣ እንግልትን ጫና ቢኖርም፣ በዋናነት የተቃዋሚዎች ችግር ነው አገዛዙን ያቆየው ብዬ ነዉ የማምነው)

 

ሰርቦች ጠመንጃ አላነሱም። ሰርቦች ለዉጥ ማምጣት አይቻልም ብለው አላወጁም። ሰርቦች ተስፋ አልቆረጡም። እኛ ኢትዮጵያዉያን ግን ተስፋ ቆረጥን። ፎጣችንን መሬት ላይ ጥለን፣ አምባገነንነትን አሜን ብሎ የመቀበል አዝማሚያ አሳየን። «ተቃዋሚዎች አይረቡም። ያኔ ደግፈናቸው ጉድ አላደረጉንም እንዴ ? አርፎ መቀመጥ ይሻላል፣ ሰላማዊ ትግል አይሰራም ….» የሚሉ ጨለምተኛና የሽንፈት አባባሎችን ማሰማት ጀመርን።

 

የገዢዉ ፓርቲ ሰዎችም፣ ስልጣን ላይ ለመቆት የሚያስችላቸው፣  ይሄዉ የተቃዋሚዎች መከፋፈልና የሕዝቡም ተስፋ መቁረጥ ስለነበረ፣  በሚቆጣጠሯቸው ሜዲያዎች፣ ሕዝቡ በተቃዋሚዎች ላይ የበለጠ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ ከፍተኛና ሲስቴማቲክ፣  ተቃዋሚዎች የማጥላላትን የማሳነስ ዘመቻቸዉን አፋፋሙ። ጠንካራ የሚሏቸውን የተቃዋሚ መሪዎችና ጋዜጠኞች ያለ ርህራሄ አሰሩ። ብርቱካን ሚደቅሳን አሰቃይተውና ሰባብረው (ለስድስት ወራት ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር ጨለማ ቤት ዉስጥ እንዳስቀመጧት) ለስደት ዳረጓት። «እነርሱን ያየህ ተቀጣ» በሚል፣  በአንዱዋለም አራጌ፣ በእስክንደር ነጋ፣ በርዪት አለሙ፣ በዉብሸት ታዬ፣ በበቀለ ገርባ እንዲሁም በሌሎች ..ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ፣ በተራ የዉሸት ሽብር ክስ፣  ኢፍትሃዊነትና ኢሰብአዊነት የተሞላበት ግፍ መፈጸማቸዉን ቀጠሉ። በሕዝቡ  አይምሮ ዉስጥ፣ እነርሱን ማንም ሊነካቸው የማይችሉ፣  ግዙፎች (ኢንቪሲብል) እንደሆኑ ለመሳል መሞከርና፣ ሕዝቡ እርስ በርስ ተፈራርቶ እንዳይደራጅ፣ እንዳይነጋገር፣ እንዳይተማመን፣ በዘር፣ በኃይማኖት በጥቅም እንዲከፋፈል፣  ማድረጉን ተያያዙት።

 

ነገር ግን ኢትዮጵያዉያን መንቃት ያለብን ይመስለኛል። ከሰርቦች መማር ያለብን ይመስለኛል። አምባገነኖች ኃይለኛ የሆኑ ይመስላሉ እንጂ ሁልጊዜ ባዶ መሆናቸዉን መረዳት አለብን። ሕወሃት/ኢሕአዴግ የሕዝብ ድጋፍ የሌለው፣ በሙስና የተዘፈቀ፣ ለሕዝብና ለዜጎች ከበሬታ የማያሳይ፣ ዜጎችን ሽብርተኞች እያለ የሚያሸብር፣ የበሰበሰ ድርጅት እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነዉ።

 

እንግዲህ «ትላንት ወድቀናል ብለን፣ የትናንቱ ጠባሳችንን እያየን ወደፊት ከመራመድ መቆጠብ የለብንም» እላለሁ። ከስህተቶቻችን ተምረን፣ ያለፈው ታሪካችን በአይምሯችን እየፈጠረ ካለው ጎታች ጫና ተላቀን፣ ይሄንን ዘረኛና አምባገነን ስርዓት ለመቀየር በቁርጠኝነት መነሳት የግድ ነዉ። ቁልፉ በእጃችን ነዉ። በርግጥ ለዉጥ ማምጣት እንችላለን። ጥያቄው «ፍላጎቱ አለን ወይ?» የሚል ነዉ።

 

እያንዳንዳች ወደ ራሳችን እንመልከት። እራሳችንን እንጠይቅ። «እስከመቼ ነዉ፣  በአገራችን እንደ ባይተዋር ፈርተን እና አንገታችንን ደፍተን የምንቀመጠው ?» ማለት እንጀመር። በየወረዳችን፣ በየአካባቢያችን፣  ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ድርጅቶችን እንቀላቀል። የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፣ ጠንካራና አገር ሰፊ የኢትዮጵያዊትነትና የሰለጠነ ፖለቲካ የሚያራምድ ድርጅት ነዉ። በመቀሌ፣ አርባ ምንጭ፣ ጂንካ፣ አዳማ ፣ አሶሶ …በአገርቷ ክፍሎች ሁሉ ብትሄዱ አንድነት በዚያ አለ። አንድነትን እንቀላቀል። አንድነትን እንደግፍ። የሰማያዊ ፓርቲ ፣ መኢአድ፣ ኤዴፓ፣ አረና ..ሁሉም በፊናቸው የሕዝብን ጥያቄ እያሰተጋቡ ነው። እንቀላቀላቸው። እንደግፋቸው። ልዩነቶቻቸውንም አጣበው ፣ የበለጠ ኃይልና ጉልበት ኖሯቸው ሰላማዊ፣ የኢትዮጵያዊነት የሰለጠነን የፖለቲካ ትግል ይመሩ  ዘንድ፣ እንዲሰባሰቡ፣ እንዲዋሃዱ እናበረታታቸው።

 

ፈረንጆች ኒው ዪር ሬዞሉሽን (የአዲስ አመት ዉሳኔ) ይሉታል። እንግዲህ፣ በዚህ የ2014 አዲስ አመት፣ የሁላችንም ምኞት፣ ጥረትና ዉሳኔ፣  በአገራችን መልካም ለዉጥ እንዲመጣ፣ የድርሻችንን በሃሳብ፣ በገንዘብ፣ በጸሎት ለማገዝ ይሁን። የሌሎች ሕመምና ስቃይ ይሰማን። ዝምታን በቃ እንበል። እግዚአብሄር አምላክም ረድኤቱን ያብዛልን!

 

comment pic


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>