ይህን 77 እስሩት በገመድ፣
ወደ 78 እንዳይረማመድ።
ይህች አነስተኛ ስንኝ የሰማኋት እንደ ሃገራቸን አቆጣጠር በ1978 ዓ.ም ላይ ነበር። መቼም የማይረሳ የለም አሥረኛው የአብዮት በዓልም ተረሳ። ያኔ እነ “ጓድ መንግሥቱ“ ድርቁን ደብቀው አሥረኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን ለማክበር ውስኪ በመርከብ ያስገቡበትና የተራጩበት ዘመን ነበር። ያኔ እነ “ብጻይ መለስ“ በድርቁ ስም በተገኘው ገንዘብ ጠብመንጃ የገዙበት ዘመን ነበር። የማይረሳ የለም በዚያ ዘመን በድርቅ ያለቀው ወገናችንም ተረሳ። የሕዝብ ገንዘብ ለውስኪና ለጠብመንጃ ያዋሉት ትንሽ ቆይተው ስልጣን ተቀያየሩ። 1977 ማሰር አቅቶን 1983 ከድጡ ወደ ማጡ አነጎደን።
በደርግ ዘመን የደረሰውን ድርቅ ለመከላከል በሰሜን የሚኖሩትን ዜጎቻችንን(ከሰሜን እየታፈሱ የመጡት ዜጎቻችን በድርቁ ምክንያት ይሁን በሌላ ወደፊት አዋቂዎች ይጽፉት ይሆናል) ወደ ምዕራብ ማስፈር ተጀምሮ ነበር። ማስፈሩ ሁለት መልክ ነበረው። ሠፈራ የሚባለው ሰው ባልሰፈረበት አካባቢ ወስዶ ማስፈር ሲሆን ስግሰጋ የሚባለው ደግሞ በሕዝብ ቁጥር የሳሱትን ወረዳዎች በሰፋሪዎች መሰግሰግ ነበር። ሠፈራና ስግሰጋ የራሱ የሆነ በሰፊው የሚተረክለት ታሪክ አለው።
ከሰሜን ኢትዮጵያ ለሠፈራና ለስግሰጋ ወደ ኢሉባቡር የመጡ አንድ ሽማግሌ ገበሬ ነበሩ ይህችን ከላይ የሰፈረችውን ስንኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገሩኝ። ይህች ስንኝ ሁለት ትርጉም ይዛለች። አንደኛው 1978 ከ 1977 ይብሳልና አይሸጋገር የሚል ሲሆን ሁለተኛው 1977 ያየነው ችግር ወደ 1978 እንዳያልፍ የሚል ነው። ሽማግሌው እንዳስረዱኝ የመጀመሪው ነው ትክክሉ። ከጊዜ በኋላም አንድ የምቀርበው የወረኢሉ ሰው ስለነ መንግሥቴ ደፋር ፣ ስለነ ብሩኬ ስንጫወት ይህችን ግጥም አስተወሰኝና ማስታወሻ ላይ ጽፌ ይዣት ቆይቼ ለዛሬው መነሻ ሆነችኝ። (መንግሥቴ ደፋርና ብሩኬ በወረኢሉና ሰሜን ሸዋ ሃገር ያንቀጠቀጡ “ሽፍቶች“ ነበሩ። ቀን ሲሞላ የሚጻፍ ታላቅ ታሪክ አላቸው።)
ድርቅ ከሳይንስ በተቃረነ መልኩ በአገራቸን ሁል ጊዜ ዱብ እዳ ነው የሚሆነው። 1966 የደረሰውም ይሁን 1977 የተደገመው ድርቅ እንደው ሳንሰማው ነው በድንገት ያየነው። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 80ኛ ዓመት በተከበረ ማግሥት ድርቅ “ሳይታሰብ“ መጣ። ደርግም ሕዝብ ሲራብ የንጉሡ ባለሥልጣናት ኬክ ይበሉ ነበር በማለት ቅስቀሳ አድርጎ ነበር ወደ ስልጣን የመጣው። ደርግ ይባስ ብሎ የአሥረኛውን አብዮት በዓል እስከሚያልፍ ድርቁን ደብቆ፣ በዓሉ ባለቀ ማግስት ድርቅ እንደ ዱብ እዳ፤ እንደ ተምች ከሰማይ እንደወደቀ ነገረን። በ1966 ዓ.ም. እንደ ሃገራችን አቆጣጠር የደረሰው ድርቅ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ 60ዎቹን ባለሥልጣናት የገደለው መንግሥቱ በእሱ ዘመን ለተደበቀው ድርቅ ራሱን ሳይገድል መቅረቱ ፍትህ አልባነት ነው ማለት ይቻል ይሆን?
በዛ ዘመን ካለ መንግሥቱ አመራር ምንም ነገር የሚሆን አልነበረምና በዓሉ ካለቀ በኋላ ሁላችንም ስለድርቁ ተነግሮን ዝግጅት እንድናደርግ ታዘዝን። ከግብርና ሚኒስቴር እስከ ታች እስከ ወረዳ ድረስ ከግብርና ጋር ግንኙነት ያለን በሙሉ ክተቱ ተባልን። የኢሠፓ አባላት መሪዎቻችን ሆነው እኛ የእርሻ ኤክስፐርቶቹ ተመሪ ሆነን ሥራውን ጀመርን። ቀርፋፋዋ ኢሊባቡር ከአዝጋሚነት ወጥታ እንቅስቃሴ በእንቅስቃሴ ሆነች። በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ መኪናዎች ከእኛ ተወስደው ለኢሠፓዎቹ መጓጓዣ ሆኑ። እኛ ወደ ሞተር ባይስክልና ወደ ትራክተር ተዘዋወርን።
በዚያ ወቅት ኢሊባቡር ነበርኩና እኔም ለዚህ “ሳይታሰብ በድንገት“ ከሰማይ የመጣብንን እዳ ለመቋቋም በየቦታው መራወጥ ጀመርን። በጋምቤላ ለሰፋሪዎች ቦታ መዘጋጀት ጀመረ። በሌላ በኩል ደግሞ በሕዝብ ቁጥር የሳሱ የገበሬ ማህበራት ውስጥ ከሰፋሪዎቹ ውስጥ እየተወሰዱ ይሰገሰጉ ጀመር። እኔ ጎሬ አካባቢ በሚገኝ ወረዳ ለሚሰገሰጉት ገበሬዎች ጎጆ ለመስራት ተመደብኩ። ዛሬ ያገኘሁት ትንሽ የየቀኑን ሁኔታ የምዘግብበት ማስታወሻ አንዲት ጎሬ ለምትኖር አንዲት ወይዘሪት የተጻፈ ደብደቤ ላይ የደብዳቤውን ብዙው ዝባዝብኬ ተቀንሶለት እንዲህ የሚል የተጠቀሰ ጉዳይ ይገኝበታል። ።
ውዷ
ጓጆ ቤት መሥራት ቀርቶ ጎጆ ቤት ውስጥ አድሬ አላውቅም። ይህ የምሰራው ጎጆ (ጎጆ ከተባለ) የሚገርም ነው። ከላይ ሳር ጣል ተደርጎ ይከደንና ግንድግዳው በዘንባባ ይሸፈናል። የኛን አዛዥ አላፊ ካድሬዎችን ለመሆኑ ይህ የምንሰራው ቤት ከምን ይከላከላል? ብዬ ጠይቄ ነበር። የተሰጠኝ መልስ ለጊዜው ማረፊያ ካገኙ ሰፋሪዎቹ ሲመጡ ያሻሽሉታል የሚል ነበር። በድርቅ የተጎዳ ሰው እውን ቤት መስራት ይችል ይሆን? የሚገርም ነው። ለማንኛውም ሥራውን እያጣደፍነው ነው። ስራው አልቆ ጎሬ ለመምጣት ቸኩያለሁ።
ይላል። በዛ ወቅት የነበረውን ጥድፊያ አጉልቶ ነው። ከሁሉ የሚገርመው በትንሽ ቀን ያንን ሁሉ ሕዝብ ማጓጓዝ እንዴት አስከፊ ነበር። በችኮላውና በሕዝብ ብዛቱ ምክንያት ከአንድ አውቶቡስ ውስጥ የነበሩ ቤተሰቦች በምደባ ይለያዩና አንዱ ጎሬ ሌላው ጋምቤላ ይደርሰው ነበር። ማንም ጥንቃቄ የሚያደርግ አልነበረም። ብዙ ቤተሰቦች ሳይገኛኑ ይቀሩ ነበር። ልጆች በረሃብም ይሆን በጉዞው አድካሚነት ይረግፉ ነበር። ይህንን ያልተጠና ሰፈራ የመንግሥቱ መመሪያ ነውና ማንም ባለሥልጣን፣ ማንም የእርሻ ኤክስፐርት ሊቃወም አልሞከረም።
ሰፋሪዎቹ መጥተው በሰራው ቤት ከተመደቡ በኋላ እየተመላለስኩ እጠይቃቸው ነበር። ይህንን ግዜ ነው አንድ ሽማግሌ ስለዚህ አባባል ያጫወቱኝ። አዎ ገበሬዎቹ ነገሩ ገብቷቸው ኑሮ በ1978 ከ 1977 እንደሚብስ ገምተው ነበር።
የፈረንጆቹ ዓመት ከ2013 ወደ 2014 ሲቀየር የተመኘሁት ይህንን ግጥም ነበር። የሃገራችንን ጉዳይ በጥሞና ሳስበው፣ በየቀኑ እየባሰ የሄደውን የወያኔን ግፍ ስንገምተው፣ የደሃውና የሃብታሙ ልዩነት እየገፋ መምጣቱን ስመለከተው፣ ችግርን በመሸሽ በየበርሃው በየባሕሩ የሚያልቀው ወጣት ዜጎችቻን ቁጥር መጨመርን ሳሰላው፣ በእየእስር ቤቱ የሚማቁትን ዜጎቻችንን ሳስታውሳቸው፣ ለሃያ ዓመት በነጃዋር፣ በነ ተሰፋዬ ግብረ አብ፣ በእነ ብርሃኑ ዳምጤ መሰሎቹ የተዘራው የዘር ፖለቲካ ስሞኑን የደረሰበትን ደረጃ በጣም ያሳስበኛል።
ሃገራችን አንድነቷን ጠብቃ የመኖሩዋ ሁኔታ ጥርጣሬ ውስጥ ሲገባ፣ ጠንካራ የሆነ ተቃዋሚ ለመፍጠር ያለውን ችግር ስንገመግመው፣ በትግሉ ውስጥ ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ ሳጣበት 2014 ከ 2013፣ የሚብስ መሆኑን ስንረዳው ያኔ እንደ ገበሬዎቹ፡ -
ይህን 13ትን እሰሩት በገመድ
ወደ 14ቱ እንዳይረማመድ ።
ለማለት ተገደድኩ።
የሃገራችንን ሁኔታ ልብ ብለን ስንመከተው ይህ ዘመን ከመቼውን ጊዜ ይበልጥ የሚያስፈራ ሆኖ ይታሰበኛል። በተለይ 2013 መጨረሻ ላይ የተመለከትነው ሁኔታ ስንገመግመው፣ በተለይ እነዚህ በዘር የተለከፉ አጋንቶችን እዚህ ማን አደረሳቸው የሚለውን ስንመለከተው፣ በወያኔ ቀጥሎ ራሳችንን እንድንገመግም ይጠይቀናል። ሞኝ ብቻ ነው ቤቱ ሲቃጠል የሚስቀው። ለሚቃጠለው ቤቱ ቤንዚል የሚያቀብለው። ሞኝ ብቻ ነው ፎቅንና ጥልፍልፍ መንገድን ተመልክቶ እየፈረሰ ያለውን የሃገሩን አንድነት የሚዘነጋው። ሞኝ ብቻ ነው ሃገርን ለሚፈርሱ መድረክ እየሰጠ ሃገሩን የሚያፈርሰው። የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ የሚለው በሃገር አይሰራም።
የዘር ፖለቲካ የደረሰበትን ደረጃ ያልተረዱ ብዙ ናቸው። ክምር ፎቅ፣ ጥልፍፍ መንገድ፣ ዳንኪራ መደለቂያ ቡና ቤት ብቻ ለሃገር አንድነት የሚበቃ የሚመስላቸው የዋሆች እየበዙ ነው። ዛሬ በድሎት የሚንደላቀቁ ዘመናዮች በየጥጉ በረሃብና በበሽታ የሚልቁት ዜጎቻችንን እንዳያዩ የየክለቡ አብለጭላጭ መብራት ዓይናቸውን ሽብቧቸዋል። በዓለም ታሪክ በቅርብ እንኳን ስንት የሚያምሩ ፎቆች በዘር ክፍፍል እንደፈረሱ የማይረዱ አሉ።ትንሽ ዘርን ተመርኩዛ የምትንሳ ሁኔታ የእርስ በእርስ መተላለቅን እንደምታስከትል፣ የተከመሩ ፎቆችም ሆነ ፣ጥልፍለፍ መንገዶች በቀናት ሊፈርሱ እንደሚችሉ ያልተረዱ የዋሆች የአንድነት ኃይሎችን እየተዋጉ ጭንብል ላጠለቁ ዘረኞች መድረክ ፣ እውቅና እየሰጡ እንዳሉ ሊረዱት ይገባል።
ከወያኔ ተፋተናል ያሉን ሁሉ መለያየታቸው መልካም ነው። ለምን ከወያኔ እንደተፋቱ አሳማኝ ምክንያት ሳያቀርቡ ሰው እንደጠፋ በየቦታው የፖለቲካ ተንታኝ . . . የኮሚቴ አባል . . . የመድረክ የክብር እንግዳ፣ . . . ወዘተ. እያደረጉ መካብ በተሰፋዬ ገብረአብም ይሁን በጃዋር የከሸፈ ነው። ነገም በብርሃኑ ዳምጤ ቢደገም የሚያስደንቅ አይደለም። ከወያኔ ወጥተው ተቃዋሚ ሆንን ሲሉ ወያኔ ውስጥ ሆነው የሠሩትን ጥፋት ለሕዝብ እንኳን ይቅርታ እንዲጠይቁ አይደረግም። ብቻ የሰሞኑን ፖለቲካችንን ይደግፉልን እንጂ በሃገር ላይ የሚያመጡትን ጥፋት አይታየንም።
ለሃገራቸው የሠሩ፣ የሞቱ እየተወገዙ፣ ሃገራቸውን የገደሉ ወደፊትም ሊገድሉ የተዘጋጁ ትላንት የወያኔ አሽከር የነበሩ፣ አሁን ተቃዋሚ ነን የሚሉ እነ ጃዋር፣ እነ ብርሃኑ ዳምጤ (ደቡር) ጀግና ተብለው እየተዘፈነላቸው ነው። ሲሞቅ ኦ.ፒ. ዲ. ኦ.(OPDO) ሲቀዘቅዝ ተቃዋሚ፣ ትላንት የወያኔን ቀንደኛ ደጋፊ ሥልጣን ሲከለከል ተቃዋሚ መሆን የዘመኑ የፖለቲካ ገጽታ ነው።
እንደነ ጃዋር አይነት የዘር ፖለቲከኞች አቋም በቀየሩ ቁጥር አብረን ዳንኪራ የምንረግጠው ምን እንባል? አንድ ሰሞን ፓልቶኩም ፣ ራዲዮኑም ጃዋር ፣ ጃዋርና ሲልና የፖለቲካ ተንታኝ የሚል አዲስ ስም ተሰጥቶት በባልና ሚስት ጥል ላይ እንኳን ሳይቀር(እንደ ቀልድ ውሰዷት) ሃሳብ እንዲሰጥ ሲጠየቅ እንዴት ያላገባ ሰው የትዳር ሊቅ ሊባል ይቻላል የሚል ተቃውሞዬን አቅርቤ ነበር። ይኸው ዛሬ ጃዋርን ተቀምጠቀው የሰቀሉ ካስቀመጡበት ቆመው ማውረድ አቃታቸው። ሕዝብን የሚከፋፍለውን ጥያቄ ይዞ ለኢትዮጵያ የሚመኝላትን የእርስ በእርስ ጦርነቱን ይቀሰቅስ ጀመር። ጃዋር ትንሽ ሲፍቁት ኦፒዲኦ(OPDO)፣ በጣም ከፋቁት ወያኔ(TPLF) መሆኑን አጥተነው ነው። አይመስለኝም ለሰሞነኛ ፖለቲካ ከጠቀመን ስለሃገራቸን ግድ ስለማይኖረን ይመስለኛል።
እነ ጃዋር እኛን የሞቀው ላይ የምንጣደውን ሲፈለጉ ደጋፊያቸው አድርገው ያጫጩናል፣ ሲደብራቸው ደግሞ የዘር ፖለቲካቸውን አምጥተው ያምሱናል። ዛሬ ወያኔ ፣ ነገ ተቃዋሚ ፣ ተነገ ወዲያ ደግሞ ተመልሰው ወያኔ እንደፈለጉ መሆን ይችላሉ። በተቃዋሚው መድረክ ላይ ከወያኔ ለተመለሱት ሁሉ እግራቸው ሥር እንድንነጠፍ የሚፈልጉ ብዙ ናቸው።
እድሜ “ለነጻ ሜዲያ ጋዜጠኞች“፣ እድሜ ለኛ በሞቀበት ለምንጣደው፣ ሃገራችንን ሊበትኗት ሲራወጡ አብረን ልንበትናት እየሮጥን ነው። እንግዲህ ፍላጎታችን ይህ ከሆነ አሁን የምናየው ደስ ሊለን ይገባል። ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ስንት አንጋፋ አሮሞዎች እያሉ ይህ ስንዝሮ ፖለቲከኛ ጃዋር ይጋበዛል። ስለ እስልምና ስንት የተማሩ የበሰሉ ሊቀ ሊቃውንቶች እያሉ ጃዋር ሁሉም ቦታ የሃይማኖት ተንታኝ ሆኖ ይቀርባል። ጥፋቱ ጃዋር ጋር አይደለም ጥፋቱ ለሃገራቸን አንድነት እንዋጋለን ብለን ግን ለክፍፍል በምንሰራው ላይ ነው። እነ ጃዋር በኛው መድረክ፣ በኛው ገንዘብ አላማቸውን ሲስፈጽሙ እንደሞኝ የሚቃጠለውን ቤታችንን እያየን እንስቃለን። በነጻ ፕረስ ስም እውቅና እንሰጣለን።
ትላንት የወያኔ ደጋፊ ሆኖ ዛሬ ከወያኔ ተጣላሁ ካለን ምራን ብለን እግሩ ሥር እንነጠፋለን። ይህ ደግሞ ለምዶብናል። 1997 ምርጫ ዋና የወያኔ አቀንቃኝ የነበረውና የነ ሽብሬን መገደል ትክክል ነው ብሎ ሲያቀነቅን የነበረው፣ አሁን በግል ጥቅም ምክንያት ከወያኔ የተጣላው ብርሃኑ ዳምጤ (ደቡር፣ አባ መላ) ዛሬ በየሃገሩ የክብር እንግዳ፣ በመገናኛ ዘዴው ተንታኝ ከሆነ ሰነበተ። ለአንዲት የሰሙኑ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል ብርሃኑ ደቡርን እላይ የሰቀላችሁት በኋላ እንደለመደው ሲክዳችሁ ስትንጫጩ መስማታችን አይቀርም። ትንቢት እንዳይመስላችሁ ደቡርን በደንብ አድርገን እናቀውቀዋለን። ቆዳችሁን ገፎ ይሸጠዋል፣ ደቡር ሃገሩን አይደለም እናቱንም ቢሆን ይደልላል። አታውቁት እንደሆን መርካቶ ላይ ሄዳችሁ የተሰራውን ግፍ ጠይቁ። እንኳን የቀይ ሽብሩን ፣ እነ ሽብሬን ረስተን የለም እንዴ !! ምን ይደንቃል።
እድሜ ለኛ ብጻይ ብርሃኑ ዳምጤ ከወያኔ ጋር የምናደርገውን ትግል ይምሩልን ብለን . . . ሁሉንም እናስረክበው . . . እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ ብርሃኑ ዳምጤ ደቡር ይክደናል። ከዛም አሁን ከሰማይ ሰማየት የሰቀልነው እንደ ድመት እግሩ ስር እናለቅሳለን። ብርሃኑ ደቡር ቆዳችንን ገፎ ሥጋችንን ለአሞራ ይበትነዋል። በጨረታው አይገደድም ለበለጠው ይሸጠናል። ኢሕአፓ ነው ፣ ግንቦት 7 ነው ፣ መኢአድ ነው . . . እያለ እንደፈለገ ይከፍለናል። ምን እንሆናል ለመሸጥ የተዘጋጀን በጎች አይደለንም እንዴ? በሉ የዘመኑ ፖለቲከኞች ከጃዋር ፣ ከብርሃኑ ዳምጤ ጥፋት መፈለግ ትታችሁ ከነቴዲ አፍሮ ጥፈት ፈልጉ። መቼም፣ የምታሸንፉት አይደለም የምታጠቁ ወያኔን ከመቃወም ቴዲን መስደብ ይሻላል። ጃዋርን ከመቃወም ቴዲን መስደብ ለዝሙት ቱሪስቶች ፣ ለዘመኑ ኢንቨስተሮች ፣ የደደቦች ሸንጎ አባሎች የሚሻል ነው ።
2013 ተቀይሮ 2014 ሲገባ ተስፋ የሚሰጥ ራዕይ ያለው ፖለቲካ እያከተመ እንጂ እያበበ መሆኑ አይታይም። ጠብ አጫሪ፣ እኔ እኔ በሚል የተቃኘ የግለሰቦች ፍላጎት የሕዝብን ራዕይ ሸፍኖ ጎልቶ ወጥቶ ስንመለከት የዴሞክራሲ ትግል የመጨረሻው ቀን ርቆ ይታየናል። ከነገ ደህና የሚጠብቅ ትንሽ ነው።
ዓመትን ማሰር ቢቻል የምናስራቸው ዓመታት ብዙ ይሆኑ ነበር። ከዛ በፊት ግን ሕዝብ ለክፍፍል የሚጠሩ ምክንያቶችና እነዚህ አጀንዳዎች ለግል ጥቅማቸው ከፍ የሚደርጉ ፖለቲከኞች ከፖለቲካው መድረክ ሊሸበቡ ይገባል። እነ ተስፋዬ ግብረ እባብ፣ እነ ጃዋር ፣ እነ ብርሃኑ ዳምጤ . . . ነገም ብዙዎች ይመጣሉ። ተቃዋሚ መሆናቸውን መከልከል አይገባም ምሩን ማለት ግን ደደብነት ነው።
ወያኔዎች ሃገራችንን ለማፍረስ የማይጠቀሙበት መንገድ የለም። በማካከላችን አንቀላፊዎች(Sleepers) ያስቀምጡብናል። ቀኑ ሲደርስ ያነቋቸዋል። ሰሞኑን በእነ ጃዋር ያየነው ይህንን ነው። እነ ጀዋር ሲነቃባቸው ሌሎች ይላካሉ። እኛም ምሩን ብለን እንቀበላቸዋለን። ለወራት ካመሱን በኋላ ያደረሱትን ጉዳት አድርሰው ተልዕኳቸው ተፈጽሟልና ይሸሸጋሉ። ሌሎች በምትካቸው ይመደቡልናል . . . እንዲህ እንዲህ እያልን ዓመት እንቆጥራለን . . .። መቼ ይሆን እያየን አለማየታችንን የምንገነዘበው? መቼ ይሆን ከተኛንበት የቁም እንቅልፍ የምንነቃው? መቼ ነው ሰው ነኝ ወይስ በሰው ምስል የቆምኩ “ሰው“ ብለን ራሳችንን የምንመረመረው። ብልህን አንዴ ያሞኙታል፤ ሞኝን ግን ዘንተለት እንዲሉ ነውና ከእንቅልፋችን እንንቃ።
በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ስለ ሃገራችን አንድነት የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ!
ለንደን ታህሳስ 2006