ግርማ ካሳ
የእግዚአብሄር ሰላምና ጸጋ ከርስዎ ጋር ይሁን። ከአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ፣ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ብዙ ያበረከቱ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ኖት። በተለይም ደርግ ሊወድቅ አካባቢ፣ ከነዶር ሰለሞን ተርፋ፣ ዶር ስብሀት ጋር ሆነዉ አቅርበዉት የነበረው የእርቅ ሰነድ መቼም የማልረሳው ነዉ። «ይቅር ለእግዚአብሄር» በሚል መንፈስ፣ ከኢሰፓና ከሽምቅ ተዋጊዎች ከተወከሉ፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች የተወጣጣ፣ የሽማግሌ መንግስት እንዲቋቋም ነበር ሃሳብዎት። መንግስቱ ኃይለማሪያም ፈርጥጦ ሊጠፋ ፣ «የአገር ጉዳይ የባልና የሚስት ጉዳያ አይደለም በይቅር ለእግዜር የሚፈታዉ» ብሎ፣ በአራት ሰዓቱ ባዶ ዲስኩር አደንቁሮን፣ ሃሳብዎትን ዉድቅ አደረገዉ እንጂ።
አሁንም ያኔ በርስዎ ዘንድ የነበረዉን የማስታረቅና የማቀራረብ መንፈስ ነዉ ማየት የምፈልገዉ። እንደሚያወቁት በምርጫ ዘጠና ሰባት፣ ቅንጅት ዉስጥ ነበሩ። ከዚያም በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራዉን የአንድነት ፓርቲን ተቀላቀሉ። መድረክ የሚባል ስብስብ ተፈጠረ። በመድርክ ዙሪያ አንዳንድ ልዩነቶች ጎልተዉ ወጡ። እርስዎም በወቅቱ «ዝም አንልም» ከዚያም «መርህ ይከበር» ከሚሉ ወገኖች ጋር በመሆን በአንድነት ፓርቲ አመርሮች ላይ ከፍተኛ ተቃዉሞ አሰሙ። (ዴሞክራሲያዊ መብቶትን ተጠቅመው) በተለይም በመድረክ ዙሪያ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ያላችሁ ልዩነቱ መፍትሄ ሲያጣ፣ ሰማያዊ ፓርቲ የሚባል ድርጅት አቋቋማችሁ። ባልሳሳት እርስዎ የመጀመሪያው መሪ ሆኑ። ይኸው የርስዎ ድርጅት ሰማያዊ ፓርቲ፣ አገር ቤት ጥሩ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ድርጅቶች ከጥቂቶቹ መካከል አንዱ ሆኗል። ምንም እንኳን አሁን የድርጅቱ አመራር አባል ባይሆኑም፣ ትልቅ ተሰሚነት ያልዎት፣ የሰማያዊ ፓርቲ «አባት» መሆንዎ ግን የማይካድ ነዉ።
የአንድነት ፓርቲ፣ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤዉን አድርጓል። የቃሊቲ ወዳጅዎ ኢንጂነር ግዛቸው፣ ሊቀመንበር ሆነዉ ሲመረጡ፣ 65% የሚሆኑ የአመራራ አባላቱ ከሰላሳ አምስት በታች የሆኑ ወጣቶች ሆኑ። ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ፣ ድርጅታቸዉ አንድነት፣ ከሰማያዊ፣ መኢአድ፣ አረና፣ ኤዴፓ ጋር ለመዋሃድ ፍላጎት እንዳለው፣ ለዚያም ተግቶ እንደሚሰራ ተናገሩ።
እንደሚያወቁት በሰማያዊና በአንድነት መካከል፣ ይሄ ነዉ የሚባል የጎላ የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት የለም። ሁለቱም አሁን ያለዉ በዘር ላይ ብቻ የተመሰረተ ፌደራል አወቃቀር መቀየር አለበት ይላሉ። ሁለቱም ብሄረሰቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸው የማስፋፋት መብት እንዳላቸው፣ ኢትዮጵያ ዉበቷ ብሄረሰቦቿ እንደሆኑ ያማናሉ። ሁለቱም «የብሄረሰብ ሆነ የቡድን መብቶች መከበር አላባቸው» ይላሉ። የቡድን(ብሄረሰብ) መብቶች ከግለሰብ መብት ጋር ከተጋጨ ቅድሚያ የሚሰጠው ለግለሰብ መብት እንደሆነ ሁለቱም ያረጋግጣሉ። በመሬት፣ በጸረ-ሽብርተኘነት ሕግ እንዲሁም በርካት ፖሊሲዎች ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም አላቸው።
እርግጥ ነዉ በአንድነትና በመድረክ ግንኙነት ዙሪያ የተንጠላጠሉ ችግሮች አሉ። ነገር ግን የአንድነት ፓርቲ በሶስት ወራት ጊዜ ዉስጥ የመድረክን ጉዳይ እልባት እንዲሰጠው ጠቅላላ ጉባዔው ወስኗል። ወይ የመድረክ አባል ድርጅቶች፣ ልዩነቶቻቸውን አጣበው፣ ዉህደት ይመሰርታሉ፤ አሊያም አንድነትና መድረክ ይለያያሉ። ስለዚህ ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድነት ጋር የዉህደት ንግግር እንዳይጀመር ፣ መድረክ መሰናክል ሊሆን አይችልም።
እርስዎ እንዴት እንደሚያዩት አላውቅም፣ እኔ ግን የሰማያዊ ፓርቲና አንድነት መዋሃድ ድርጅቶቹን ብቻ ሳይሆን፣ ትግሉን ይጠቅማል ባይ ነኝ። በ2007 ዓ.ም የሚደረገዉ ብሄራዊ ምርጫ አንድ አመት አካባቢ ነዉ የቀረው። በ547 ወረዳዎች ተወዳዳሪዎችን ማሰለፍ የግድ ነዉ። አንድ ድርጅት ብቻ ሊሰራዉ አይችልም። የግድ አቅምና ጉልበትን ማስተባበር ያስፈልጋል። እርስዎም ይሄን ያጡታል ብዬ አላውቅም፤ የሰማያዊና አንድነት አብሮ አለመሆን የሚጠቅመው አገዝዙን ብቻ ነዉ ።
እንግዲህ እንደ አባት ሁሉን እየተቆጡና እየመከሩ፣ ዘንድሮም እንደ ከዚህ በፊቱ ቁም ነገር እንዲሰሩ እማጸንዎታለሁ። የፖለቲክ መሪዎች ከራሳቸው ስሜት አልፈዉ፣ ከድርጅታቸው በላይ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም እንዲችሉ፤ የትላንቱ ልዩነቶች ገመድ ሆነው እንዳይጠልፏቸው እንዲጠነቀቁ፣ ከግትርነት እንዲወጡ ፣ ይቅር ለእግዚአብሄር እንዲባባሉ ያስፈልጋል። ያላጠፋ የለም። ያልተሳሳተ የለም። እርስዎም ቢሆኑ፣ ሁላችንም ያጠፋነው ጥፋት አለ። ነገር ግን ትልቅ ሰው ከስህተቱ ይማራል። ትልቅ ሰው በትላንቱ ስህተቶቹ እግሮቹን አስሮ ወደፊት ከመጓዝ አይቆጠበም። ትልቅ ሰው ይቅር ይላል።
ከላይ እንዳልኩት የአንድነት ፓርቲ የዉህደት ጥሪ አቅርቧል። መኢአድና እና አራና ከአንድነት ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እንደጀመሩ የሚገልጹ ዘገባዎችን አንብቢያለሁ። አቶ ልደቱ አያሌዉ ለአድምስ ጋዜጣ ጋር ከሰጡት ቃለ መልልስ አኳያ፣ ኤዴፓም ከነአንድነት ጋር አብሮ ለመሆን የመፈለግ አዝማሚያ ሳይኖረው እንደማይቀር አስባለሁ። የቀረዉ ሰማያዊ ነዉ። እንግዲህ የሰማያዊን ነገር ለርስዎ ጥዬዋለሁ። ያሳምኗቸዉና ያግባቧቸው ዘንድ እጠይቅዎታለሁ።
ምክርዎትን አልሰማ ብለው የተናጥል ጉዟቸዉን ከቀጠሉ ግን፣ ምንም ማድረግ አይቻልም፣ ምርጫዉ የነርሱ ይሆናል። ጉዳዩ የፌዝና የቀልድ፣ ወይንም የግልሰቦች ተክለ ሰውነት የመገንባት ሳይሆን፣ የአገር ሕልዉናና ደህነት ነዉ። ይሄንንም ጠንቅቆ የሚረዳው፣ በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ፣ ሁሉንም ያታዘባል። ትልቁ ነገር ቅንነት ነውና፣ እግዚአብሄር ለሁላችንም የቅንነትን እና የትህትናን መንፈስ ያላብሰን ! «እኔ ለምን ተነካዉ» ብለን የምንቆጣና የምንቀየም ሳይሆን ይቅር ባዮች ያድርገን !
እግዚአብሄር ያክብርልኝ።