Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

መሰረታዊ ግንዛቤ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ! (ዘነበ በቀለ)

$
0
0

   ዘነበ በቀለ

music-notesሙዚቃዊ ፍልስፍና እንቆቅልሹ የሚፈታው ህዝባዊ በሆነው መሰረታዊ ግንዛቤ ላይ ተመርኩዞ ነው። ህዝባዊ ግንዛቤ ስንል ደግሞ ሙዚቃው የሚሰጠውን ስሜትም ሆነ መልዕክት የገባውና አሰራሩን የተረዳው ክፍል ወሳኝ መሆኑን ለመጠቆም ነው።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ማለት በብዙ ዘመናት የህዝቡ አብሮ የመኖር ስልት መሰረትነት የተገነባ የጋራ ግንዛቤን የፈጠረ የባህሎችን ልዩነት አቀናብሮ የያዘ አንድ ወጥ ቅርስ የሆነ ማለት ነው። እነዚህን የቅርርብ ሁኔታዎች ለመገንዘብ ሶስት መሰረታዊ የሆኑ የዜማ መዋቅሮችን መመልከት የተገባ ነው። እነዚህም

1ኛ/ የዜማ ስልት

2ኛ/ ሪትም/ምት

3ኛ/ ቋንቋ

ሲሆኑ ከመመርመሪያቹ መንገዶች መሃል ዋነኞቹ ናቸው።

 

የዜማ ስልት ስንል ሙዚቃው የተገነባበትን መሰላል/ስኬል ማለታችን ነው።

ሪትሙ ደግሞ በየአካባቢው የአኗኗር ዘይቤ ላይ ተመርኩዞ በረገዳ፣ በዘፈን፣

በእስክስታ፣ በጭፈራ የሚተረጎም መሆኑን የሚገልፅ ነው።

ቋንቋውም ቢሆን እንደየአካባቢው የአነጋገር ፈሊጥ የሚታይ በመሆኑ ለምሳሌ ያህል – በጎንደር አማርኛና በጎጃም አማርኛ፣ በሸዋ አማርኛና በወሎ አማርኛ መሃል ልዩነት አለ። በኤርትራ ትግሪኛና በትግራይ ትግሪኛ መሀል ልዩነት አለ። ይህ ሁኔታ በዜማው ላይ ተፅዕኖ አለው’ የዜማው ስሪት ደግሞ ጭፈራውን ይወስነዋል።  ለምሳሌም የሸዋው ኦሮሞ ጎፈር አጥልቆ ረገዳ ሲጫወት ይስተዋላል። የወሎ ኦሮሞ ግን ጭፈራውን  በእስክስታ አጅቦ ነው የሚያቀርበው። የወለጋና የጂማ ኦሮሞ በጭፈራው ላይ እጅን ማርገብገቡ ተመሳሳይ ቢያደርጋቸውም ያርሲ ኦሮሞ አንገትን ማሽከርከር ይጠቀማል። በሁሉም ዘንድ የዜማ ባህሪያቸውና ሪትሙ የተለያየ ነው። ስለዚህም መለኪያው ሁሉንም ነጥቦች የዳሰሰ መሆን ይገባዋል እንጂ! የኦሮሞ ባህላዊ ሙዚቃ አንድ አይነት ነው ከማለት ይልቅ ኢትዮጵያዊ ትርጉም ያለው ለመሆኑ የበርካታ ባህሎችን ተመሳሳይ አሰራር መገምገም ያስፈልጋል።

 

የወያኔ ፖለቲካ የተቀነበበው በነገድ ማንነት ዙሪያ በመሆኑ ሙዚቃን በተለይም ኢትዮጵያዊ ፀባይ ያለውን ክፍል ለመተርጎም በርካታ ችግሮች ሲደነቀሩ ይስተዋላል። የሙዚቃን ምንነት በራሳቸው ፍላጎት ላይ ተመርኩዘው የሚተረጉሙ ግለሰቦች መኖራቸው ተገቢውን ግንዛቤ ያልጨበጡ አድማጮችን ለመፍጠር ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም የሙዚቃ ግንዛቤ ፈሩን የለቀቀ ማንኛውንም ነገር በምርታማነት/ሽቀላ ስሌት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ፣ የሙዚቃ ሰዎች በስራቸው ላይ ከጥራት ይልቅ ብዛትን እየመረጡ  በመምጣታቸው መካለስና መደለዝ፣ መደባለቅና መዋዋጥ፣ በተለይም በስታይል/ አሰራር ዘይቤው/ እንዲጨፈለቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸው ይስተዋላል። በዚህም ምክንያት ከላይ የተጠቀሱትን ማገናዘቢያ ነጥቦች ያላሟሉ ሙዚቃዊ ስራዎችን በተናጠል በማቅረብ፣ በቋንቋ ላይ ብቻ የተመረኮዘ ግምገማን በመሰንዘር ይኸ ሙዚቃ የእከሌ ጎሳ/ነገድ ባህል ነው ብሎ መደምደም ፈሊጥ ሆኗል። ይሁን እንጂ! የየነገዱን አኗኗር ከቋንቋው ውጭ ተመልክቶ መገምገም አስፈላጊ ነው። ከሙዚቃው ጥበብ ባህርይ የወጣ ግምገማ ለሙዚቃው ምንነት ጠቃሚ አይሆንም።

 

የሙዚቃ አሰራር በተለያዩ መልኮች በህዝብ ውስጥ መተላለፉ ሀቅ ነው። በጉርብትና፣ ገበያ፣ ጦርነት፣ ራድዮ ማሰራጫ ወዘተ. ዋና ዋና የመተላለፊያ መንገዶቹ ናቸው። በመሆኑም

የኢትዮጵያ ህዝብ ባህል በነዚህ ሁሉ መልኮች የመተላለፍ ዕድል ስለገጠመው አንድ ወጥ የሆነ ሙዚቃዊ መሰረት ይዞ እንዲወጣ ዕድል አግኝቷል። ይህም የአምስት ድምፅ መሰላል ተከታይ መሆኑ አንዱና ዋናው ነው። በጣም ጥቂት የሆኑ ባህላዊ ሙዚቃዎች ከዚህ ባነሰ /ቶናል ሬንጅ/ ወይም የድምፅ ገደብ ውስጥ ያሉና በኦሮምኛ እንጉርጉሮ ሙዚቃ ውስጥ ከሚታየው ሄክሳቶኒክ/ ወይም ስድስት ድምፅ መሰላል እንዲሁም በአደሬ ክሮማቲክ ታይፕ/ የግማሽ ድምፅ ግንባታ ያለው ሙዚቃ መሰላል ውጭ፣ አብዛኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ማለትም የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ የወላይታ፣ የጉራጌ ወዘተ. የነገድ ሙዚቃዎች በአምስቱ መሰላል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በመሆኑም አንድ አይነት ሳይኮሎጂካል ሜክአፕ/ ፈጥረዋል።

 

የአምስቱ መሰላል ቶን የፈጠረው ሜላንኮሊክ ጠባይ የአድማጩን ሙዚቃዊ ግንዛቤ በመወሰኑና አንዳንድ ሁኔታዎችን ተመርኩዞ የሀዘን ስሜት የሚፈጥር በመሆኑ በተለይ እንዳሁኑ አይነት ህዝብ ያዘነበት የተከዘበት ዘመን ሲከሰት ለቅሶንና ሙሾን በመድረስ የሙዚቃውን አጠቃላይ ግንዛቤ ለውጦ እንባ አባሹ እንዲበራከት የሙዚቃው ይዘት  አንድወጥ ትርጉም ብቻ እንዲይዝ የሚያደርጉ ሙያተኞች ምክንያቶች ይሆናሉ። ሙዚቃ ደስታና ሀዘን የሚገለፁበት ጥበብ ብቻ አይደለም። ትምህርትንም ማስተላለፊያ እንደመሆኑ ሁሉ ፖለቲካም ጓዙን ጠቅልሎ በጥበቡ ታዛ ስር እንደሚጠለል ታሪክ መስክሮልናል።  ትክክለኛ ሁኔታዎች ከተለዋወጡ አጉል ቦታ የሚደነቀረው አሰራር ብዙ ትርጉሞችን ያዛባል። ለምሳሌ የቀረርቶ ዜማን  ያለቦታው መደባለቅ “ሳይገድሉ ጎፈሬ…” የሚሉት አይነት ትርጉምን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ወቅታዊ የሆነ የመነሳሳት ስሜት ፈጣሪ የነበረውን የጦርነት ሙዚቃ ማዕረጉን ቀንሶ ለዳንስ እንዲውል ያደርገዋል።

 

የኢትዮጵያ ሙዚቃ በጊዜው ያልተዋዋጡ የተለያዩ የአካባቢ ባህሎችን ልዩ አሰራር የሚያከብርና በጋራ የሚታዩ ሙዚቃዊ እሴቶችንም አቅፎ የሚጓዝ የህዝብ ባህል ነው። የኢትዮጵያ ሙዚቃ በእንጉርጉሮና በዘፈን በመዝሙርና በመንፈሳዊ ዜማ መንገዶች መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ በመረዳት የሚጓዝ መሆኑ መታወቅ ይገባዋል።

 

ቸር ይግጠመን!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles