የግል አስተያየት
“አዲሱ” የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ግዛቸው ሺፈራው ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ስለመጪው የፖለቲካ እርምጃቸው እንዲህ ይላሉ ፦
” ከኢሕአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት (Constructive Engagement) እንዲኖረን እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥላቻ ፖለቲካ ማብቃት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የሚያያቸው እንደ ጠላት ከዚያም አልፎ እንደ ሽብርተኛ ነው. . . በእኛም በኩል ኢሕአዴግን የምናየው እንደ አውሬ ነው፡፡ ምናልባት የሠራውን ሥራ ሁሉ ዋጋ (Credit) ያለመስጠት አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካችን ኢሕአዴግን መቃወም ብቻ ሆኖአል፡፡ ያ መቆም አለበት፡፡ ትልቁ ኳስ ያለው ኢሕአዴግ ዘንድ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ወደፊት በማደርገው እንቅስቃሴ ገንቢ ግንኙነት አድርገን ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ለሁላችንም እኩል ማድረግ አለበት፡፡”
ይህ መንገድ፣ ካልተሳሳትኩ ” ሶስተኛው መንገድ” ( The Third Way) የሚባለውና አቶ ልደቱ አያሌው የ1997 ምርጫ አጣብቂኝ በገባበት ወቅት አምጥተው የደነጎሩት፣ በሌላ አነጋገር “መሀል ላይ መቆም” የሚባለው የፖለቲካ አካሄድ ነው። አሪስቶትል “መሀል ላይ መቆምን” ወርቃማ የፖለቲካ አካሄድ ነው ይለዋል ( The Golden mean- ) ። መሀል ላይ ቆመው የሚታገሉ ፖለቲከኞች ጫፍ እና ጫፍ ከቆሙት የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ሳይጋጩ ፣ ሁለቱንም መስሎ በመኖር ወይም ከሁለቱም ጫፎች የተወሰኑትን አስተሳሰቦች በመውሰድ የራስ አድርጎ በመታገል ያምናሉ ። “የመሃል ፖለቲካ” ምን ያክል ርቀት እንደሚወስድ በዚህ ዙሪያ የተሰሩ ትምህርታዊ ጥናቶችን ባላነብም፣ ሀሳቡን ሲያራምዱ የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንም ሆኑ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠ/ሚ ቶኒ ብሊየር ብዙ ርቀት እንዳልሄዱበት የሁለቱንም መጽሃፎች አንብቤ ተረድቻለሁ ። ዛሬም ቢሆን ዲሞክራቶችና ሪፑብሊካኖች ዳር እና ዳር ቆመው የአሜሪካን ፖለቲካ ይዘውሩታል፣ በእንግሊዝም ሌበርና ኮንሰርቫቲቮች ዳር እና ዳር ቆመው ይተያያሉ።
“መሃል ላይ የቆሙ” ፖለቲከኞች የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም የላቸውም ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ብዙውን ጊዜ በወላዋይነት ይከሰሳሉ፣ በምርጫ ጊዜ ድል የሚቀናቸውም አልፎ አልፎ ነው። ዲሞክራሲ በሆኑ አገሮች “መሀለኞች” የመመረጥ እድል የሚያገኙት ህዝቡ ጫፍና ጫፍ በቆሙ ፖለቲከኞች መሰላቸት ሲጀምር ብቻ ነው ፤ አምባገነንነት በሰፈነባቸው አገሮች ደግሞ መሀል ላይ የሚቆሙ ፖለቲከኞች ፈሪዎች ተደርገው ስለሚቆጠሩ ብዙም አይወደዱም። መሀል ሰፋሪዎች መሀል ላይ የሚቆሙት ከመንግስት የሚወርደውን ዱላ ስለሚፈሩ ነው ተብሎ ይታማሉ። አቶ ልደቱ አያሌው በ97ቱ ምርጫ “መሀል ላይ የመቆምን” ፖለቲካ ማራመድ ሲጀምሩ ደጋፊዎቻቸው በሁለት ምክንያቶች አልተቀበሉዋቸውም ነበር ፤ አንደኛው ምክንያት ምርጫውን ያሸነፉት “ዳር” ላይ ቆመው ባራመዱት የፖለቲካ አቋም እንጅ በሁዋላ ላይ ባመጡት “የመሀል ፖለቲካ” አስተሳሰብ ስላልነበረ፣ ደጋፊዎቻቸው አዲሱን ባህሪ ለመቀበል አልቻሉም ። አቶ ልደቱ የጨዋታውን ስልት ወደ ምርጫ ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ቢያስታውቁ ኖሮ ሁዋላ ላይ የደረሰባቸውን አይነት ውግዘት አይደርስባቸውም ነበር፣ በምርጫውም ላያሸነፉ ይችሉ ነበር።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ አቶ ልደቱ የጨዋታውን ህግ የቀየሩት በደህንነት ሃይሎች ብዙ እንግልትና ማስፈራሪያ ከደረሳቸው በሁዋላ በመሆኑ የአቋም ለውጡ ከፍርሃት ጋር ተያይዞባቸዋል። ጀግንነትን የሚያወድሰው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንገዱ ትንሽ ሸርተት ያለን ሰው በወላዋይነትና በፈሪነት ፈርጆ ይጠለዋል ።
ኢ/ር ግዛቸውም የመሀሉን ቦታ ይዘው እንደሚታገሉ አስታውቀዋል። እዚህ ላይ ሁለት ነጥቦችን እናንሳ። አንድነት ፓርቲ ከኢህአዴግ ጋር መልካም ግንኙነት ከማድረጉ በፊት በቅድሚያ በኢህአዴግ በኩል የሚቀርበውን ቅደመ ሁኔታ መቀበል አለበት፣ ያም ቅደመ ሁኔታ “የምርጫ ስነምግባር መመሪያ” ውን መፈረም ነው። መድረክና አንድነት ይህን መመሪያ አንፈርምም ብለው ላለፉት 6 ዓመታት በአቋማቸው ጸንተው ቆይተዋል። በ2002 ምርጫ ወቅት ኢ/ር ሀይሉ ሻውል ይህን መመሪያ በመፈረማቸው ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ይመስለኛል፤ በወቅቱ አቶ ሃይሉ ፊርማውን የፈረሙት “ድጋሜ እንዳይታሰሩ ፈርተው ነው፣ ከፍተኛ ሀብት ያፈሰሱበትን ቢዝነስ እንዳይቀሙ በመስጋት ነው” እየተባሉ ይታሙ ነበር፤ ኢንጂነር ሃይሉ በገደምዳሜም ቢሆን፣ የአማካኙዋን ቦታ ይዘው ለመታገል ፈልገው ነበር። ኢ/ር ግዛቸውም ይህንን “የስነምግባር መመሪያ” ካልፈረሙ ከኢህአዴግ ጋር ቁጭ ብለው እንደማይነጋገሩ ያውቃሉ። ላለፉት 5 አመታት የስነ ምግባር መመሪያውን “አልፈርምም” ብሎ ጠንካራ አቋም ያራመደ ድርጅት፣ በአዲሱ አመራር አቋሙን እንደገና ለመፈተሽ ያሰበ ይመስላል። ፓርቲው መመሪያውን አልፈርምም በሚለው አቋሙ ከጸና ግን አዲሱ ሊቀመንበር ከኢህአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት ለመመስረት የሚቸገሩ ይመስለኛል፣ ሌላ መንገድ አዘጋጅተው ከሆነ አላውቅም።
ኢ/ር ግዛቸው በመሀል መንገድ ለመጓዝ ከመረጡ ከእርሳቸው በፊት በዚሁ መንገድ ተጉዘው የተሰባበሩ ፖለቲከኞች እጣ ፋንታ እንደሚገጥማቸው ለመናገር ነብይ መሆንን አይጠይቅም ፤ የፓርቲው ህልውና አደጋ ውስጥ መውደቁም አያጠራጥርም። የያዙት አላማ ለበጎም ይሁን ለክፉ፣ አዲሱ መንገዳቸው ከፍርሀት ጋር ሊያያዝባቸው እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ለዚህ ማጠናከሪያ የሚሆኑ ምክንያቶች ደግሞ አሉ። ሊቀመንበሩ ቀደም ብሎ፣ ከሌሎች የቅንጅት መሪዎች ጋር ታስረው በነበረበት ጊዜ የፈረሙት የይቅርታ ሰነድ አለ። ሊቀመንበሩ ገዢውን ፓርቲ የሚያስከፋ ነገር ከተናገሩ ይህ ፋይል በማንኛውም ጊዜ እንደሚመዝባቸው ይታወቃል፤ እንደ አንዱዓለም አራጌ የታሰሩበትን ገመድ ለመበጠስና ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ምን ያክል ተዘጋጅተዋል የሚለውን ለመመለስ እቸገራለሁ፣ ከምርጫ 2002 ልምድ እንዳየሁት ግን የእስር ገመዳቸውን ለመበጠስ መዘጋጀታቸውን እጠራጠራለሁ። እንዲያውም የመሀሉን መንገድ አማራጭ ” የታሰሩበትን ገመድ ሳይበጥሱ፣ በገመዱም አጥብቀው ሳይታሰሩ ለመጓዝ ከመፈለግ የመጣ” ይመስለኛል። ፓርቲው ቀድሞውንም በረጅም ገመድ የታሰረን ሰው በመሪነት መምረጥ አልነበረትም፣ ከመረጠም ገመዱን ለመበጠስ የተዘጋጀ መሆን አለበት።
የሊቀመንበሩ አካሄድ በእስር ላይ በሚገኙት አንዱለአም አራጌና ናትናኤል መኮንን ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም፤ አንዱዓለም ከሚታወቅባቸው ባህሪዎች አንዱ በአቋሙ የሚጸናና ላመነበት ነገር ህይወቱን ለመስጠት የተዘጋጀ ሰው መሆኑ ነው፤ ደስ ሲለው ወዲህ፣ ደስ ሳይለው ወዲያ የሚረግጥ ሰው አይደለም። ፓርቲው ለስድስት አመታት የተጓዘበትን መንገድ ቀይሮ መሀል ላይ ለመቆም ከወሰነ ፣ አቋማቸውን ለማሳወቅ እድል በማያገኙት አንዱአለምና ናትናኤል ላይ የስነልቦና ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። አዲሱ መሪ ይህን ያሰቡት አይመስለኝም፣ ካሰቡበትም የእነ አንዱአለምን ሁኔታ ከግምት ያስገቡ አይመስለኝም፣ ከግምት ውስጥ አስገብተውት ከሆነም ፣ አንድ ነገር አስበዋል ማለት ነው። ለማንኛውም መጪው ጊዜ ለአንድነት ፓርቲ ፈተና የሚሆንበት ይመስለኛል።