Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ይድረስ ለጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም፡ ማስረሻ ላይ የተፈፀመው በእርስዎ የበኩር ልጅ ዮሐና ላይ ቢፈፀም ምን ይሰማዎታል?

$
0
0

ይድረስ ለአቶኃይለማርያም ደሳለኝ እና ለኢህአዴግ አመራሮች!

ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com,
addismediab@gmail.com

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ፤ ምንም እንኳ እናንተ ብዙውን ሰላም እየነሳችሁ ብታስቸግሩም፡፡ ዛሬ ግን እስኪ በእናንተ እና በቤተሰባችሁ ላይ እንዳይፈፀም የምትፈልጉትን በሌላው ላይ ስላደረጋችሁት ከብዙው አንዲት እውነት ብቻ አንስቼ ልጠይቃችሁ ወደድሁ፡፡ የጥያቄው መልስ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለህሊናችሁ፣ እናንተ በምትመሩት አስከፊ፣ አፋኝ እና ጨቋኝ ስርዓት ሰለባ ለሆኑ እንዲሁም አሁንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተለመደውን እኩይ ተግባር ለምትፈፅሙባቸውና ለቤተሰቦቻችሁ ይሆን ዘንድም አበክሬ እጠይቃለሁ፡፡
hailemariam and Yohana hailemariam
ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እርስዎ ተወልደው ባደጉበት የደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ቦለሶ ሶሬ ወረዳ መዲና በሆነችው አረካ ከተማን መቼም የሚረሷት አይመስለኝም፡፡ እርስዎ አሁን የደረሱበት የይምሰልም ይሁን ተግባር የጠቅላይሚኒስትርነት በትረ ስልጣን ከመጨበጦ በፊት እዛው አረካ ከተማ አካባቢ እንደ አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ በግብርና እርሻ ሙያ ዕየተዳደሩ ነው እንበል፡፡ ታዲያ በዚህ ሙያ ሳሉ ልክ አሁን እንዳሉት ባለትዳር እና የ3 ልጆች አባት ሆነው፤ እርስዎ በሚመሩት ኢህአዴግም ይሁን 24 ሰዓት በምትኮንኑት ደርግ ስርዓት አርዓያ “ሞዴል” አርሶ አደር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተብለው የትውልደ ቀዬዎትን ወክለው በደቡብ ክልል መንግስት ቢሸለሙ ምን ይሰማዎታል? ያው ደስታ እንደሚሉኝ አልጠራጠርም፡፡

አለበለዚያም ገበሬ ሆኜ አላውቅም ካሉም፤ ያኔ አርባምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ተቋም (የአሁኑ አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተመረቁበት ሲቪል ምህንድስና(Civil Engineering) አሊያም ከፊንላንድ በተመረቁበት የአካባቢ ንፅህና ምህንድስና(Sanitory Enegineering) እስተማሩና እያስተዳደሩ ሞዴል መምህር ተብለው በወቅቱ ገዥ ስርዓት ቁንጮዎች ቢሸለሙ ምን ይሰማዎታል? አሁንም ያው ደስታ ነው እንጂ ሀዘን ሊሉኝ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው በሙያው ጥሮ ግሮ ላበረከተው አስተዋፅዖ እና ለሌሎች መልካም አርዓያ በመሆኑ የሚጠላ አይኖርምና፡፡ ይሄንን ምሳሌ ለራስዎ መቀበል ካልቻሉም ከቤተሰብዎ እጅግ መልካም ነው ብለው አብልጠው የሚወዱት ወንድምዎ ካሉም በእርስዎ ምትክ እርሳቸውን ተክተው እርስዎን በታዛቢነት ያስቀምጡ፤ ስሜቶንም ያሰላሱ፣ ይግለፁ፡፡

በሙያዎ ለብዙ ዓመታት ሰርተው ለሌሎች አርዓያ ተብለው ሽልማት፣ እውቅና እና ሙገሳ ከተሽጎደጎደልዎ 3 ወር ሳይሞላ፤ ከትዳር አጋርዎ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እና የበኩር ልጅዎን ተማሪ ዮሐና ኃይለማርያምን ጨምረው ከሌሎች ልጆቾ ጋር አምላኬ በሰላም አሳድረኝ ብለው ተቃቅፈው ተኝተው በሸለሞት አካል አሸባሪ ተብለው ሌሊት በቤትዎና በቤተሰብዎ ላይ በ 16 “የፀረ-ሽብር” ግብረ ኃይል የጥይት እሩመታ ሲሰሙስ ምን ይሰማዎታል? አሁን ልክ እንደቅድሙ ደስታ ሊሉኝ አይችሉም፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ እርስዎን በቤተሰብዎ ፊት በሸለሞት አካል በ 16 ግብረ ኃይል ሽፍታ ነው ተብለው በክብር አርፈው ከተኙበት ቤት በሚተኮሱ የጥይት ናዳዎች በቤተሰብዎ ፊት ህይወትዎ እስከወዲያኛው ቢያልፍ እና እንደው ግማሽ ነብስ የለም እንጂ በከፊል ድርጊቱን ቢታዘቡት ምን ይላሉ; ከእርስዎ በተጨማሪ ለፍተው ጥረው ግረው ያቆሟት ቤት፣ ያፈሯቸው ላሞች ፣በጎችና በሬዎች በማያውቁት ነገር የጥይት ናዳ ሲያርፍባቸውስ; ከላይ በተጠቀሱት ሳያበቃ ግብረ ኃይሉ አሁን የሰው ህክምና ሳይንስ የምታጠናው የበኩር ልጅዎ ተማሪ ዮሐና ሌሊቱን ገና በ8 ዓመቷ ከእቅፎ ተኝታ እርስዎ ሲገደሉ እርሷ የምትፅፍበት፣ አሊያም በትርፍ ጊዜዋ ከብቶች የምታግድበት ወይንም እንደሌሎች ህፃናት ከአቻዎቿ ጋር ለመጫወት የምትጠቀምበት የቀኝ እጇ ሙሉ ለሙሉ በጥይት ቢቆረጥስ ምን ይሰማዎታል? በዚህም ደስታ እንደማይሉኝ ግልፅ ነው፡፡ ልክ በውጊያ አውድማ እንዳለ ወታደር ከወላጆቿ እቅፍ ሳለች ቀኝ እጇ የተቆረጠችው ልጅ ስታድግስ ምን ይሰማት ይሆን? ፍርዱን ህሊና ላለው ሁሉ ልተወው፡፡

ልክ እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች እና አባላት ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ቢፈፀም ምን ይሰማችኋል; እናንተም ደስታ እንደማትሉኝ አልጠራጠርም፡፡ ይህንን ሁሉ የጠቀስኩት በማንም የሰው ሰብኣዊ የሰው ልጅ ላይ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ድርጊት እንዲፈፀም ፈልጌ ይደለም፤ ይሄንንም አቶ ኃይለማርያምም ሆኑ ሌሎች ግብር አበሮእዎ በቅን ልቦና እንድትረዱልኝ እሻለሁ፡፡

ክቡርነትዎ፤ ከላይ ብእርስዎ የጠቀስኩት ምሳሌ በሌላ ኢትዮጵያዊ ላይ በእናንተ ስርዓት አመራር የተፈፀመ እውነተኛ ድርጊት መሆኑንን ከዚህ እንደሚከተለው በአጭሩ ልነግሮት እወዳለሁ፡፡

ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ አረቦር ቀበሌ ልዩ ቦታው ደቀፉቀር በሚባል ስፍራ ከሌሊቱ 12 ሰዓት ከነ መላው ቤተሰቦቻቸው አምላኬ በሰላም አሳድረኝ ብለው የተኙ፤በእነ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስርዓት ሞዴል አርሶ አድር ተብለው የተሸለሙ ታታሪ ገበሬ አቶ ማስረሻ ጥላሁን በ 16 የፀረ ሽብር ግብረኃይል በተተኮሱ የጥይት ናዳዎች እዛው እቤታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ የሚያሳዝነው ለግድያ የተላከው ግብረ ኃይል አቶ ማስረሻን ከገደሉ በኋላም በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ተከታታይ የጥይት ናዳ በማውረድ ቤታቸውን የጥይት ጌጥ ሲያደርጉት ጥረው ግረው ያፈሯቸው ከብቶችንም ከመግደል እና ከማቁሰል አልቦዘኑም ነበር፡፡

የሚገርመው እንዴት የአንድ ሰው መኖሪያ ቤት የቀድሞ የአድዋ ወይም ባድመ፣…የውጊያ ስፍራ ሊመስል እንደቻለ ግልፅ አይደለም፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ እጅግ የሚዘገንነው እና የሚያሳዝነው በተመሳሳይ ሰዓት የአቶ ማስረሻ ጥላሁን የ 8 ዓመት ልጅ ስለእናት ማስረሻ እዛው በሞት ከተነጠቀው ወላጅ አባቷ እና በፀረ ሽብር ግብረኃይል ከተሸበሩ ምስኪን ቤተሰቦቿ እቅፍ ሆና ሲነጋ ጥቅምት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ከአቻዎቿ ጋር ትምህርት ቤት ስለመሄድ እና ስለመጫወት ስታልም ብዙ ስራዎችን የምትሰራበት ቀኝ እጇ በግብረ ኃይሉ ጥይት ሙሉ ለሙሉ ተቆርጧል፡፡

አቶ ኃይለማርያም በእርስዎ እና በግብር አበርዎ የሚመራው ኢህአዴግ ሞዴል አርሶ አደር ያላችኋቸውን አቶ ማስረሻ ጥላሁንን በ 16 “የፀረ ሽብር” ግብረ ኃይል ለማስገደል በወረዳውና በዞኑ አመራሮች ሽፍታ ነው የሚል ለባለቤታቸውና በህይወት ለተረፉ ልጆቻቸው መልስ ተሰጥቶ ፍትህ እንጦርጦስ ገብቷል፤ ቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግ እስካለ ፍትህ እና ርትዕ ከማግኘት ሰማይ ቤት ደርሶ መመለስ የቀለለ ይመስል ሰው ተስፋ ቢቆርጥም፤ ለወጉም ቢሆን ፍርድ ቤት መኳተኑ አልቀረም፡፡ ነገር ግን እሮጣ ያልጠገበች፣ክፉና ደጉን የማታውቅና ቂም በቀል የሌለባት፣ ዓለማችንንም ይሁን ሀገራችንን ኸረ እንደውም አካባቢዋን በቅጡ ለይታ የማታውቅ የ 8 ዓመቷ ህፃን ስለእናት ማስረሻ ጥላሁንን ምን ብላችሁ ይን እጇ እንዲቆረጥ የተደረገው? ነው ወይስ ይህቺን ህፃንም ሽፍታ ነች ልትሉን ነው? ኸ…ረ…ረ..የፍትህ ያለህ፣…የህፃን ልጅ ያለህ፣…ቢያንስ ሰብዓዊነት እንኳ እንዴት ይሳናችኋል?

እስኪ አቶ ኃይለማርያም ስለእናት ማስረሻ ላይ የተፈፀመው በእርስዎ የበኩር ልጅ ዮሐና ኃይለማርያም ላይ ቢፈፀም ምን ይሰማዎታል? ስለ እናንተ ልጆች እንደምታስቡ ሁሉ ስለሌሎች ህፃናት ያላችሁ አስተሳሰብና አመለካከት ወይም ግንዛቤ የት ድረስ ነው? ዛሬ በዚህ ግፈኛ ስርዓት ቀኝ እጇ የተቆረጠው ስለእናት ማስረሻ ነገ እንደማንኛውም ልጅ አራሷን፣ ቤተሰቧን፣ ሀገሯን ብሎም የዓለምን ማኀበረሰብ ልታገለግል ምትችል፣ ብዙ ተስፋ የሰነቀች ነች፡፡

አሁን ግን ገና የ !ኛ ክፍል ትምህርቷን በጀመረች አንድ ወር ከአስር ቀን የመመህሮቿን የፊደል አጣጣል ትዕዛዝ የምትቀበልበት ቀኝ እጇ ገና ከጅምሩ ተቆርጧል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰኞ ማክሰኞ እያለች ትምህርቷን መከታተል ሲገባት ፍትህ አጥታ ከምትኖርበት ዳባት ወረዳ፣ ሰሜን ጎንደር ዞን ከዚያም የአማራ ክልል ፍትህ ፅፈት ቤት እስከ ህፃናት ጉዳይ በጥይት ናዳዎች ከተረፉ ቤተሰቦቿ ጋር ፍትህን ፍለጋ እየተንከራተተች ትገኛለች፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ልጅ ዮሐና ኃይለማርያም በተደላደለ ሰላም፣ ጤናና እና ሁኔታ የህክምና ትምህርት ትከታተላለች፣ የብአዴኑ ሊቀመንበር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ልጆችም የተሻለ ትምህርት ቤት ከዚሁ ደህ ህዝብ በሚገኝ ገንዘብ ይማራሉ፣ የአቶ በረከት ስምዖንን ፣ የዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ የአቶ ሙክታር ከድር፣ የነ ሀሰን ሽፋ፣ የነ ጌታቸው አሰፋ ፣ የነ አያሌው ጎበዜ፣ የነ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የነ ግዛቱ አብዩ እና የሌሎች የኢህአዴግ ሹማምንት ልጆች በህዝብ ሃብት ተንደላቀው በተመቻቸ ሁኔታ ይማራሉ፡፡ የዳባት ወረዳ ነዋሪዋ ህፃን ስለ እናት ማስረሻ ደግሞ ለትምህርት ባልተመቻቸ ሁኑታ እንኳ የጀመረችውን ትምህርት እንዳትማር ቀወላጅ አባቷን በግፍ ከማጣቷ በተጨማሪ ቀኝ እጇን ተቆርጣ ፍትህን ፍለጋ ትኳትናለች፡፡

ታዲያ ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎች የኢህአዴግ ሹማምንት ሆይ፤ የምትመሩት ስርዓት በህፃናት ስም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረብጣ ዶላሮችን እንደሚያገኝ የምትዘነጉት አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ በህፃናቱ ስም የሚመጣው እርዳታ ቢያንስ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል ባይችል እንኳ ለምን አንዲትን ህፃን በፀረ-ሽብር ግብረኃይል በጥይት ለማስመታት ዋለ? በዚህች ህፃን ልጅ እና ወላጅ አባቷን ጨምሮ በቤተሰቦቿ ላይ የተፈፀመው ግፍ የት ድረስ ያስኬዳችኋል? ይህችን ደብዳቤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አቶ ኃለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ይህቺ ደብዳቤ ደረሳችሁ ሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች ፤ ስለ ህፃናት ልጆቻችሁ፣ ስለ እናቶቻችሁ ፣ ስለሚስቶቻችሁ እና ስለራሳችሁ ብላችሁ የዚህቺን ህፃን እና ቤተሰቦች ጊዜ ሳትሰጡ ፍትህን ፍለጋ እየደከሙ ነውና ፍትህን ይሻሉ፡፡

እነ አቶ ኃለማርም ደሳለኝ የእውነት ከልብ አዝናችሁና እና ተሰነምቷችሁ ፍትህን መስጠት ከቻላችሁ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ብዙ በምታወሩበት ኢቴቪና በሌሎች መድረኮች ሌሎች አመራሮችም ሆኑ ህዝብ እንዲማሩበት ጭምሩ ተገቢው ፍርድ በግልፅ በአደባባይ ሊሰጥ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ የሴቶች እና ህፃነት ጉዳይ ቢሮዎች፣ አቃቤ ህግ፣ ጠበቆች ፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሌሎች የሚመለከታችሁ አካላት የድርሻችሁን ትወጡ ዘንድ ተግባሩ የት አለ? ስል መልሳችሁን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

ታህሣሥ 2006 ዓ.ም. ተፃፈ

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>