ቫቲካን ከሙሶሊኒ ጋር ስለ ነበራት ሕብረት
ስለ ዴሽነር መጽሐፍ፤ በኪዳኔ ዓለማየሁ
ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው ዋናው ምንጩ በሆነው፤ እ.አ.አ በ2013 (2006 ዓ/ም) ታትሞ ለንባብ በደረሰው፤ ካርልሔንዝ
ዴሽነር (Karlheinz Deschner) “እግዚአብሔርና ፋሺሽቶቹ – የቫቲካን ሕብረት ከሙሶሊኒ፤ ፍራንኮ፤ ሒትለርና ከፓቬሊች
ጋር” “God and The Fascists – The Vatican Alliance with Mussolini, Franco, Hitler, and Pavelic” በተሰኘው
መጽሐፍ በተካተተው ማስረጃ ላይ ነው። የጽሑፌ ዓላማም በፋሺሽቶች ኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው እጅግ መራር የጦር
ወንጀል፤ የቫቲካንና የሙሶሊኒ ግንኙነት ምን ይመስል እንደ ነበር ደራሲው ተመራምሮ ያቀረበው ማስረጃ በኢትዮጵያውያን
ዘንድ ሰፊ ግንዛቤ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው። ስለዚህ፤ ደራሲው ቫቲካን ከሒትለር፤ ከፍራንኮና ከፓቬሊች ጋር ስለ ነበራት
ግንኙነት ያቀረበውን ማስረጃ በዚህ ጽሑፌ አላካተትኩትም።
እንደሚታወቀው፤ በሙሶሊኒ ትመራ የነበረችው ፋሺሽት ኢጣልያ፤ በቫቲካን ያልተቆጠበ ድጋፍ፤ ኢትዮጵያ ላይ
በፈጸመችው የጦር ወንጀል አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከመጨፍጨፋቸው በላይ 2 000 ቤተ ክርስቲያኖችና 525 000
ቤቶች ወድመዋል። ሌላም እጅግ አስከፊ ግፍ ተፈጽሟል።
በዓለም-አቀፍ ሕግ በተከለከለ የመርዝ ጋዝ ጭምር በመጠቀም ፋሺሽቶች በፈጸሙት የጦር ወንጀል፤ ቫቲካን ስለ ነበራት
ሚና በተለይም መሪዋ ስለ ነበሩት ፖፕ ፓየስ 11ኛና ፋሺሽቱ ሙሶሊኒ ሕብረት በብዙ ማስረጃ ተረጋግጧል። በበኩሌ ከዚህ
ቀደም ባቀረብኳቸው መጣጥፎች፤ እነአልቤርቶ ስባኪ (Alberto Sbacchi, “Ethiopia Under Mussolini”) አቭሮ
ማንሐታን (Avro Manhattan: “The Vatican in World Politics”), ሥዩም ገብረእግዚአብሔር (“The Symphony of
My Life”) ወዘተ. መጽሐፎች እንዲሁም ታዋቂ በሆኑ ጋዜጦች (New York Times) እና (Manchester Guardian)
የቀረቡትን አስተማማኝ ማስረጃዎች አካፍያለሁ። በተገኙት ማስረጃዎች ሁሉ ፖፕ ፓየስ 11ኛ ከሙሶሊኒ ጋር በነበራቸው
ፖለቲካዊ ቅርበትና የመጠቃቀም ሥልት፤ “ላተራን” (Lateran) የተሰኘ ውል ተፈራርመው ሲደጋገፉ እንደ ነበር፤ ፖፑ
ራሳቸው የኢጣልያን ንጉሥ፤ ኡምቤርቶን “የኢጣልያ ንጉሥና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት” ብለው የባረኳቸው መሆኑን፤
የቫቲካን መሪዎችና ካሕናት የፋሺሽቱን ጦር መባረካቸውን በተጨባጭ ማስረጃ ፍንትው ብሎ ቀርቧል።
ፖፕ ፓየስ 11ኛና ሙሶሊኒ እጅና ጓንት ሆነው እንዲተባበሩ ያመቻቸላቸው ዋናው መሠረታዊ ምክንያት ሁለቱም መሪዎች
ለዲሞክራሲ፤ ለሕብረተ-ሰብዓዊነትና ለኮሙኒዝም ይጋሩት የነበረው ጥላቻ ነበር። በአበው አነጋገር፤ “የጠላቴ ጠላት፤ ወዳጄ
ነው” በሚለው ሰንካላ መርሆ ይመሩ ነበር ማለት ነው።
የ”እግዚአብሔርና የፋሺሽቶቹ” ደራሲ፤ ካርልሄንዝ ዴሽነርስ ምን ብሏል?
1ኛ/ እ.አ.አ ከ1922 በፊት፤ ቫቲካንና የኢጣልያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተጻራሪዎች ነበሩ። ቫቲካን ባንድ በኩል ስትሆን
በሌላ በኩል፤ የሶሺያሊስትና የኮሚዩኒስት ፓርቲዎች ሐገሪቱን ለመቆጣጠር ይፎካከሩ ነበር። በተለይ ሙሶሊኒን
በተመለከተ፤ በጊዜው እሱ በእግዚአብሔር የማያምን፤ እንዲያውም ስለ ክርስቶስ ተገቢ ያልሆኑ ቃላት በጽሑፍ ያቀርብ
እንደ ነበረና ይህንን ሁኔታ የተገነዘቡ ሌሎች ጸሐፊዎች በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና በፋሺሽቶቹ መሀል ምሕረት የሌለው
ግጭት ሊከሰት እንደሚችል ይተነብዩ ነበር። (ገጽ 28-29)
“Mussolini was certainly an atheist. His first essay, published in 1904 and titled “There is No
God.” was about the nonexistence of God…..” (p 28) (ትርጉም፤ ሙሶሊኒ በእርግጥ በእግዚአብሔር
የማያምን ሰው ነበር። (እ.አ.አ.) በ1904 ያሳተመው “እግዚአብሔር የለም” የተሰኘው የመጀመሪያ ጽሑፉ ስለ
አምላክ አለመኖር ነበር።)(ገጽ 28)
2ኛ/ እ.አ.አ በ1921 ግን ሊከሰት የሚችለው ግጭት ቀርቶ ፋሺሽቶቹ ባወጡት መግለጫ፤
“…the Fascist leader announced “that the only universal idea that exists in Rome today is
the one that emanates from the Vatican.” (p. 29) (ትርጉም፤ የፋሺሽቱ መሪ (ሙሶሊኒ)፤
“ባሁኑ ጊዜ በሮም የሚገኘው ዓለም-አቀፋዊ አስተሳሰብ ከቫቲካን የሚመነጨው ነው።” በማለት
አስታውቋል። (ገጽ 29)
ስለዚህ፤ አኪሌ ራቲ (Achille Ratti) በመባል ይታወቁ የነበሩት የካቶሊክ ካርዲናል እ.አ.አ የካቲት 5 ቀን 1922
(February 5, 1922) ፖፕ ፓየስ 11ኛ (Pope Pius XI) ተሰኝተው እንደ ተመረጡ ሙሶሊኒ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር
በእለቱ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ የቫቲካን አደባባይ በመሔድ የተሰማውን ጥልቅ ስሜት አንጸባርቆ ነበር። ከጥቂት ጊዜ
በኋላም ሙሶሊኒ በጻፈው ደብዳቤ ለፖፕ ፓየስ የነበረውን አድናቆት እንዲሁም በፖፑና በኢጣልያ መሀል
የነበረው ግንኙነት እንደሚሻሻል አስተያየቱን ገልጾ ነበር። (ገጽ 29፤ ምንጭ (Neisser Zeitung, March 12, 1929)
የሙሶሊኒ ድርጊት ግን ሃይማኖተኛ ወይም ካቶሊካዊ በመሆኑ አልነበረም። እንዲያውም፤ ሃይማኖት ንጉሦችና
ጨቋኞች ለሥልጣናቸው የሚጠቀሙበት መሣሪያ መሆኑን ያምን ነበር።
“But on the other hand, Mussolini knew that religion, as he had himself stated in his
first atheist piece of writing, is “a trick of kings and oppressors to keep their subjects
and slaves under control” (p. 30) (ትርጉም፤ በሌላ በኩል፤ በሙሶሊኒ እውቀት፤
በመጀመሪያው የኢአማኝ ጽሑፉ፤ “ሃይማኖት ንጉሦችና ጨቋኞች ሕዝቦቻቸውንና
ባሪያዎቻቸውን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ የሚጠቀሙበት ማታለያ” መሆኑን አትቶ ነበር።)(ገጽ 30)
3ኛ/ ካርዲናል አኪሌ ራቲ፤ ለፖፕነት ከመመረጣቸው በፊት እ.አ.አ. በ1921 ስለ ሙሶሊኒ የነበራቸውን ከፍ ያለ
አድናቆት እንደሚከተለው ገልጸው ነበር፤
“ Mussolini is making quick progress and will crush everything that gets in his way with
elemental force. Mussolini is a wonderful man. Did you hear? A wonderful man!…..
The future belongs to him.” (p 30)(ትርጉም፤ ሙሶሊኒ በፍጥነት እየገሰገሰ ነው፤ የሚጋረጥበትንም ማንኛውንም ነገር በኃይል ያወድመዋል።
ሙሶሊኒ ግሩም ሰው ነው። ሰማችሁኝ? ግሩም ሰው!…..መጪው ዘመን የሱ ነው።” (ገጽ 30) (ምንጭ፤ Paris,
The Vatican, 69)
4ኛ/ አኪሌ ራቲ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ በመባል ከተመረጡ በኋላ ከፈጸሟቸው ለሙሶሊኒ እጅግ ጠቃሚ ተግባሮች
አንደኛው እ.አ.አ. ጥር 20 ቀን 1923 (January 20, 1923) የቫቲካን ዋና ደጋፊ የነበረውን “ፓርቲቶ ፖፑላሬ” (Partito
Populare) የተሰኘውን የካቶሊክ ፓርቲ ማውደም ነበር። የዚህም ዋናው ምክንያት ለቫቲካን የፋሺሽቱ ፓርቲ የተሻለ ጥቅም
የሚያስገኝ መሆኑን በማመን ነበር።
5ኛ/ ሙሶሊኒ ለቫቲካን ያበረከተው የመጀመሪያው አገልግሎት 1.5 ቢሊዮን ሊሬ በማበርከት ነበር፤
“The first service the ex-socialist rendered to the Holy See was a financial one. He saved the
“Banco di Roma” to which the curia and many of its prelates had entrusted large amounts of
money, from bankruptcy by stepping in with approximately 1.5 billion lire at the expense of the
Italian state.” (p31-32) (ትርጉም፤ የቀድሞው ሶሺያሊስት (ሙሶሊኒ) ለቫቲካን ያበረከተው የመጀመሪያው
አገልግሎት የገንዘብ እርዳታ ነበር። በኢጣልያ መንግሥት ወጪ፤ 1.5 ቢሊዮን ሊሬ በማበርከት ቫቲካንና
መንፈሳዊ መሪዎቿ ብዙ ገንዘብ ያስቀምጡ የነበረበትን “ባንኮ ዲ ሮማ”ን ከክስረት አዳነው። (ገጽ 31-32፤ ምንጭ፤
Manhattan, 112)
በሙሶሊኒና በፖፕ ፓየስ 11ኛ መሀል የነበረው ግንኙነትና ሕብረት እጅግ የተጠናከረ ስለ ነበረ፤ ፋሺሽቶች
ተቃዋሚ ካቶሊኮችን ሲያሰቃዩና ሲገድሉ ፖፑ ምንም ተቃውሞ አላሰሙም ነበር። እንዲያውም፤ የካቶሊክ ካሕናት በሙሉ
ከካቶሊክ ፓርቲ ራሳቸውን እንዲያገልሉ በማዘዝ ለፋሺሽት ፓርቲ ከፍተኛ እንቅፋት የነበረውን ሁኔታ አስወገዱለት። ከዚህ
በተጨማሪ፤ ከዚህ በታች ያለውን መግለጫ ለዓለም አስታወቁ፤
“Mussolini has been sent to us by Providence.” (p. 33) (ትርጉም፤ ሙሶሊኒ በፀጋ (በአምላክ) የተላከልን
ነው።) (ገጽ 33፤ ምንጭ፤ Manhattan, 115)
6ኛ/ ሌላው ሙሶሊኒና ፖፕ ፓየስ 11ኛ የተጠቃቀሙበት እጅግ ከፍተኛ ጉዳይ፤ “ላተራን” (Lateran) የተሰኘውን
ውል በመዋዋል ነበር። በዚህ ውል መሠረት፤ ቫቲካን መንግሥታዊ ልዑላዊነት እንዲኖራት ከመደረጉ በላይ የኢጣልያዊ
ብሔራዊ ሃይማኖት ካቶሊካዊነት እንዲሆን ተደረገ። ቫቲካንም የፋሺሽቶቹ ዋና ደጋፊ፤ አጋር ሆነች፤
“The church rejoiced. On February 13, 1929, the pope once again praised Mussolini as the man
“who was sent to us by Providence” and shortly after ordered the clergy to say prayer “for the
King and the Duce” (“Pro Rege et Duce”) at the end of daily mass.” (p. 36) (ትርጉም፤ ቤተ
ክርስቲያኗ (ቫቲካን) ፈነደቀች። እ.አ.አ. የካቲት 13 ቀን 1929 ፖፑ (ፖፕ ፓየስ 11ኛ) ሙሶሊኒን አመሥግነው
“በፀጋ የተላከ ሰው” መሆኑን እንደ ገና ገልጸው፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ካሕናቱ ለንጉሡና ለዱቼ (ለሙሶሊኒ) በየእለቱ
ሥርዓት እንዲጸልዩ አዘዙ።) (ገጽ 36፤ ምንጭ፤ Tondi, Die geheime Machr [The Secret Power], 34,
and Die Jesuiten [The Jesuits], 73, Manhattan, 118)
7ኛ/ የሙሶሊኒና የፖፕ ፓየስ 11ኛ ጠንካራ ሕብረት የተንጸባረቀበት ከባድ ክስተት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው
የጦር ወንጀል ነበር። በቫቲካን በኩል፤ እነካርዲናል ኢልዲፎንሶ ሹስተር (ሚላን) (Cardinal Ildefonso Schuster of
Milan) ኢትዮጵያን የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ለማድረግና የኢጣልያን ግዛት ለማስፋፋት ወረራውን በይፋ ሲደግፉ
በፋሺሽቶቹ በኩል ደግሞ ቁጥሩ እየጨመረ ለሔደው ለኢጣልያ ሕዝብ የቅኝ ግዛት ማስፈለጉን እንደ በቂ ምክንያት
በማቅረብ ጦርነቱ እንዲከናወን ገፉበት። ፖፕ ፓየስ 11ኛ የፋሺሽቱን ወረራ በሚቀጥለው ቋንቋ ደገፉት፤
“On August 27 (1935), when the Italian war preparations were running at full speed, the
Pope announced-interwoven in many calls for reason and peace-that a defensive war (!) for
the purposes of the expansion (!) of a growing population could be just and right.”
(ትርጉም፤ እ.አ.አ. ነሐሴ 27 (1935) የኢጣልያ የጦርነት ዝግጅት እየተጧጧፈ ሳለ፤ ፖፑ (ፖፕ ፓየስ 11ኛ)-
ከተገቢነትና ከሰላም ጥያቄዎች ጋር እያወሳሰቡ፤ ታዳጊ ለሆነው የሕዝብ ብዛት ግዛትን ለማስፋፋት (!) የመከላከያ
ጦርነት (!) ማከናወን ተገቢና ትክክል መሆኑን ገለጹ።” (ገጽ 43፤ ምንጭ፤ Manhattan, 121 ff. The speech is
Printed in Reichspost, Vienna, August 30, 1935)
ፖፕ ፓየስ 11ኛ የፋሺሽቱን የኢትዮጵያ ወረራ የደገፉት ከላይ በተጠቀሰው መግለጫ ብቻ አልነበረም። ብዙ ሌሎች
ተጨባጭ እርምጃዎች ወስደው ነበር። ከነዚህ ውስጥ፤ (ገጽ 41-49)
(ሀ) ጳጳሶቹ የወርቅ መስቀሎቻቸውንና የአንገት ሰንሰሎቻቸውን እንዲያስረክቡ አዘዙ። በተጨማሪም፤ ጳጳሶቹና
ካሕኖቹም የካቶሊክ ምእመናን ወርቆቻቸውንና ጌጦቻቸውን ለፋሺሽቱ መንግሥት ጦርነት እንዲያበረክቱ
አደረጉ።
“According to Professor Salvemini from Harvard University, at least seven Italian
cardinals, twenty-nine archbishops, and sixty-one bishops supported the Fascist
raid (on Ethiopia) immediately,….) (p. 46) (ትርጉም፤ የሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር
ሳልቬሚኒ (እንዳቀረቡት) ቢያንስ 7 (የካቶሊክ) ካርዲናሎች፣ 29 ሊቀ-ጳጳሶች እና 61 ጳጳሶች ወረራውን
(በኢትዮጵያ ላይ) ወዲያውኑ ደገፉ።” (ገጽ 46፤ ምንጭ Manhattan, 123)
(ለ) ጀርመን ሐገር የነበረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንብረት ለሙሶሊኒ እንዲዛወርና ለጦርነቱ የሚያስፈልገው
እንዲገዛበት አደረጉ፤
(ሐ) ሌሎች ሐገሮች የሚገኙ ካቶሊኮች የኢጣልያን ወረራ እንዲደግፉ አደረጉ፤
(መ) የካቶሊክ ካሕናትና ሰባኪዎች ለኢጣልያ ጦር ድል እንዲጸልዩ ተደረገ፤
(ሠ) የፋሺሽት ወታደሮች፤ መድፍና የመርዝ ጋዝ በተጋዘበት መርከብ የቅድስት ማርያም ምስሎችም አብረው
እንዲጓዙ ተደረገ፤
“…..Abyssinians, who had neither gas masks nor shelters, unsuspectingly fell victim to the
dangers of Catholic culture. After the so-called Battle of Amba Aradam, an Italian
captain counted more than sixteen thousand butchered “enemies” (Ethiopians). They lay
there, dead or half-dead, where the skin-burning, lung-tearing gas that was sprayed
from the air had reached them, and they were all eliminated in the most hygienic
possible way – that is, by flamethrowers. (p. 49) (ትርጉም፤ ጭንብልና መጠለያ
የሌላቸው ያልጠረጠሩ ሐበሾች (ኢትዮጵያውያን) የካቶሊክ ባህል ሰለባ ሆኑ። አምባ አራዶም
ከተሰኘው ጦርነት በኋላ አንድ የኢጣልያ ካፕቴን በቆጠረው መሠረት ከ16 000 “ጠላቶች”
(ኢትዮጵያውያን) በላይ ከአየር በተነሰነሰባቸው የመርዝ ጋዝ ቆዳቸው ተቃጥሎ፤ ሳምባቸው ተበጣጥሶ
የሞቱ ወይም በመሞት ላይ የሚገኙ ነበሩ። ሁሉም በተወረወረባቸው የእሳት ቃጠሎ በቅልጥፍና
ተወገዱ። (ገጽ 49፤ ምንጭ፤ Borgese, 400)
(ረ) የፋሺሽቱ ጦር ኢትዮጵያን 90% ሲቆጣጠር፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ የደስታ መግለጫ አሰምተው ነበር፤
“And the Pope also shared in the “triumphant joy of the truly great and good people
about the peace, which,” he said on May 12, 1936, “as one may hope and agree, will be
an effective contribution, a prelude to true peace in Europe and the whole world”. (p 49)
(ትርጉም፤ እ.አ.አ. ግንቦት 12 ቀን 1936 ፖፑ (ፖፕ ፓየስ 11ኛ) የደስታ ተካፋይነታቸውን ሲገልጹ፤
“ለአውሮፓና ለመላው ዓለም እውነተኛ ሰላም አስተዋጽኦ የሚኖረው ለታላቅና ግሩም ሕዝብ (የኢጣልያ)
ታላቅ ድል መሆኑ እንደሚታወቅ ተስፋ ይደረጋል።” (ገጽ 49፤ ምንጭ፤ Manhattan, German edition,
116)
8ኛ/ ፖፕ ፓየስ 11ኛን የበታቾቻቸው ከሆኑት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተግባሮች ነጻ ለማድረግ
የሚደረገው ሙከራ ሁሉ መሠረተ ቢስ ነው።
“….But all attempts to exculpate the pope are in vain because his own words are a testament
to the contrary. Quite apart from the fact that the bishops can do only what he wants. Or
should they collect gold, bless weapons, and give martial speeches to Italy, of all places, if
the pope has banned it? If he really desires peace? (p. 44) (ትርጉም፤ የራሳቸው ቃላት
ተቃራኒውን ስለሚያረጋግጡ፤ ፖፑን ከኃላፊነት ለማዳን የሚደረገው ሙከራ ዋጋ ቢስ ነው። ተጨባጩ ጉዳይ
ጳጳሶቹ ሊያከናውኑ የሚችሉት ፖፑ የፈቀዱትን ብቻ ነው። ፖፑ ከልክለው ቢሆን ኖሮ (ጳጳሶቹ) ወርቅ
መሰብሰቡን፤ የጦር መሣሪያ መባረኩንና ቀስቃሽ የሚሊታሪ ንግግሮችን፤ ሌላ ሐገር ሳይሆን በኢጣልያ ማከናወን
ይችሉ ነበር?(ፖፑ) ሰላም ቢፈልጉ ኖሮ? (ገጽ፤ 44)
መደምደሚያ፤
በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው አሰቃቂ ግፍና የጦር ወንጀል፤ በሙሶሊኒና በፖፕ ፓየስ 11ኛ መሀል ስለ ነበረው የጠበቀ
ግንኙነትና ሕብረት፤ ብዙ አስተማማኝ ማስረጃ በማቅረብ ግንዛቤያችንን ስላጠናከረልን፤ ደራሲውን ዴሽነርን
አመሠግናለሁ። ስለዚህ ጉዳይ፤ ተቃራኒውን በመጻፍ የማያስፈልግ ውዥንብር የፈጠሩ ጸሐፊዎችም፤ በተለይ
ኢትዮጵያውያን፤ ተገቢውን እርምት በማከናወን ለውድ ሐገራችን ለኢትዮጵያ የሚገባትን ፍትሕና ክብር ለማስገኘት
እንዲተባበሩ በዚህ አጋጣሚ አደራ እላለሁ።
በተጨማሪም፤ ዓለም-አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global Alliance for Justice – The Ethiopian
Cause) የተሰኘው ድርጅት በኢትዮጵያ ለደረሰው የፋሺሽት ግፍ ተገቢው ፍትሕ እንዲገኝ ለሚከተሉት ዓላማዎች እየጣረ
ነው፤
(ሀ) ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤
(ለ) የኢጣልያ መንግሥት ተገቢውን ካሣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲከፍል፤
(ሐ) ቫቲካንና የኢጣልያ መንግሥት ከኢትዮጵያ የተዘረፉትን ንብረቶች እንዲመልሱ፤
(መ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤የፋሺሽቱን ጦር ወንጀል በመዝገቡ እንዲያውል፤ እና
(ሠ) በቅርቡ፤ የቫቲካን ተወካይ በተገኙበት፤ አፊሌ (ኢጣልያ) ለፋሺሽቱ ወንጀለኛ የተመረቀው ኃውልት
እንዲወገድ።
ባሁኑ ጊዜ፤ ከላይ የተጠቀሰው ድርጅትና ደጋፊዎቹ በመተባበር፤ የዚህ ዓመት የካቲት 12 የሰማእታት ቀን በዓለም ዙሪያ በ30
ከተሞች እንዲከበር ጥረት እየተደረገ ነው።
ለበለጠ ዝርዝር የድርጅቱን ድረገጽ፤ www.globalallianceforethiopia.org መመልከት ይቻላል። በዚያውም፤ ኢጣልያኖች
ጭምር የፈረሙት አንድ ዓለም-አቀፍ አቤቱታ ስለሚገኝ አንባቢዎች በፊርማችሁ ድጋፋችሁን እንድትገልጹ በትሕትና
ተጋብዛችኋል።
ለኢትዮጵያ ክብርና ፍትሕ እንታገል!
↧
“እግዚአብሔርና ፋሺሽቶቹ”
↧