ከእውነት መስካሪ
የክርስትና ኃይማኖት ሰዎች በእምነት የማይታየውን አምላክ በማመን የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ፈጽመው በጌታ ጸጋና ቸርነት ለዘላለማዊ ሕይወት እንዲበቁ ማድረግ ነው። ይህም በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ለእብራውያን በጻፈው መልእክት ውስጥ ተካቶ እናገኘዋለን። ይህም እምነት ከላይ ከአምላክ የተሰጠ ሲሆን በምድርም ሰዎች በሥርአት እየተመሩ እንዲፈጽሙት የተገባ ነው። ነበር! ነበር ለዘመናችን የሚስማማ አገላለጽ ይመስላልና ነበር አልኩ። ለምን ቢሉ? ሕግና ሥርአት በዘመናችን አለ ተብሎ ሊነገር አያስደፍርምና ነው። ‘መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ‘ ያለው አርድእቱ ቅዱስ ሉቃስ በግብረ ሐዋርያት መልእክቱ ይህ የእኛ ዘመን እንደሚመጣ በገሃድ ታይቶት ስለመሆኑ የሚያጠራጠር አይደለም። ይህን ሁሉ ቅዱስ ቃል ያነሳሁበት ዋናው ጉዳይ ግን ሰባኬ ወንጌል ሆኜ ወይም ለመሆን ፈልጌ ሳይሆን እንዲያው የቤተክርስቲያናችን ነገር፣ ያለችበት ሁኔታ እጅጉን ቢያሳስበኝ፣ ቢያበሳጨኝ፣ቢያስቆጨኝ መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም ቢሆንብኝ ነው፤ የተሰማኝን ለመተንፈስ ። ለቤተክርስቲያን ጠበቃ ነን ከእኛ ወዲያ ስለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ላሳር እያሉ ሲያደነቁሩን የነበሩትም ‘ቅዱሳን’ እንኳንስ የቤተክርስቲያኗ ሕልውና ተደፍሮ ይቅርና ዳርዳሯ እንኳን ቢነካ እንደቅዱሳኑ አንገታችን ለሰይፍ ይላሉ ብለን ስንጠብቅ እንደዘመኑ ጎመን በጤና ማለታቸው እጅጉን ቢያስደምመኝ ትንሽ ነገር ለመጫር ተነሳሁ። እኔም በመደመም ብቻ ዝም ብል ከእነርሱ በምን እሻላለሁ? በማለት ውስጤን ቢያውከው ላልሰማ ለማሰማት ያህል።
ሰሞኑን የቅድት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተዘጋ ደግሞ ተከፈተ እየተባለ ሲነገር ስሰማ ምንድን ነው ነገሩ? ብዬ ወሬ አቀባይ የዜና አውታሮችን ሳስስ እውነትም ለካ ቤተክርስቲያንን እየመራት ያለው እንደ አባቶቻችን ዘመን ቀዳማዊና ዳሕራዊ የሌለው መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ለመንጋውና ለራሳቸውም ግድ የሌላቸው/የማይራሩ የአላውያን መሪዎች ጉዳይ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን በውል ተገነዘብኩ። ከ50 ሚሊዮን የማያንስ ምእመን ያላት ታላቅ ቤተክርስቲያን እንደምን እንዲህ መደፈሯ፣ ኮሌጇ በቀጭን ትእዛዝ ይዘጋ መባሉ፣ የገዳማቶቿ መቃጠል፣መታረስ፣የካኅናቶቿና ምእመናኖቿ መታረድ፣ሕጋዊ መብቷ መገፈፍ ወዘተ ባለቤት እንደሌላት የጠፍ በግ መሆኗ እጅጉን ያሳዝናል።
በመንፈስ ቅዱስ አደራ የተሰጣቸው የቤተክርስቲያኗና የመንጋዋ ጠባቂዎች የት ሔዱ? ለነገሩ እግዚአብሔር ከሁሉ አስቀድሞ ሰላምንና እርቅን ለማይከተል እንኳን መንፈስ ቅዱስን መስጠት ይቅርና መባን እንኳን እንደማይቀበል አስረግጦ አስተምሮናል። ስለሆነም በዚህ ዘመን መንፈስ ቅዱስ ከአባቶች ዘንድ ተሰቋል የሚሉትን ባሕታውያንና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን ትክክለኛነት መጠራጠር አይገባም ባይ ነኝ። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የተሰጠው ሰው/አባት ከስራ መታገድና ደመወዝ መከልከል ይቅርና የተሳለ ሰይፍ ፣የፈላ ውኃ ወይም ያገጠጠ መጋዝ እንኳን በፊቱ ቢቀርብ ፍርሃት የሚባል ነገር ስለማያገኘው፤ ለኃይማቱ፤ ለቤተክርስቲያኑና ለቅድስት ሃገሩም እንኳን ቢሆን የሚሰየፍ፣የሚቀላና የሚሰነጠቅ ይሆናልና ነው። እንደ እውነተኞቹ ቅዱሳን! ዛሬ ሳይገባቸው ወይንም ሳይገባቸው ‘ቅዱሳን እየተባሉ የሚጠሩ ማኅበራትና ጥቁር ለባሾች ቤተክርስቲያንና ሃገርን ሲያጠፉና ሲያስጠፋ ማየት እጅጉን የሚያሳዝን የዘመን መጨረሻ ምልክት መሆኑ አያጠያይቅም። የእሳት ልጅ አመድ እንዲሉ የቅዱሳንና የጀግኖች ሀብታም የሆኑት ቅድስት ቤተክርስቲያንና ቅድስት ሃገር ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት የዘመን አልጫ ላይ መድረሳቸው ለሁሉም ሊያስቆጭ የሚገባው አብይ ጉዳይ መሆን ይገባዋል ባይ ነኝ። ከእኔ ጀምሮ! መሆን የሚገባው ይህን አይነት ቤተክርስቲያንና ሃርን የመታደግ ውሳኔ ማሳለፍ ሆኖ ሳለ አንዳንዶች ግን እዚህ ባለንበት በባእድ ሃገር ሆነው እዛ ቤተክርስቲያንና ሃገርን ለሚያጠፉ ‘አባቶች’ እና አለቆቻቸው መናፍቃንና አላውያን እንገዛ እያሉ ባንድነትን መናፈቃቸው ከሁሉም ያስደመመኝ ክስተት ነው። ዛሮ ወያኔ ኢህአድግ በታላቂቱ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በስውር ባሰማራቸው መነኩሴ መሳይ ካህናት መሳት ጳጳሳት መሳይ ምእመናን መሳይ ሰርጎገቦች ይኽ ነው የማይባል ምዝበራና ጥፋት እያደረሰ ይገኛል። ፓትርያርክ ብሎ ያስቀመጣቸው አባትም አጠገባቸው ስላለው መንፈሳዊ ኮሌጅ እንኳን የማውቀው የለም በማለት ለምን አገልግሎት እንደተመደቡ እንኳን የማያውቁ ናቸው። እግዚአብሔር ግን በጊዜው ፍርዱን የሚሰጥ ቢሆንም ሰዎችም የራሳችንን ድርሻ መወጣት ግዴታችን ነው። ስለዚህም በያለንበት ቤተክርስቲያኖቻችንን ጉባዔዎቻችንን ነቅተን ከወያኔ ሾልኮ ገብ ጉዳይ አስፈጻሚዋች መጠበቅ ይገባናል።
ባለፈው ሰሞን በሚኔሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ያሉ አንዳንድ ምእመናን ኢትዮጵያ ባሉት አባቶች እንመራ አሉ ሲባል ሰምቼ አይ መካሪ ማጣት! የቀድሞ ትውልዶች ለጽድቅና ለሰማእትነት ሲሯሯጡ ምነው በዚህ ዘመን ባርነት፣ ባንድነት ናፈቀን ማለታቸው ብዬ እንደገና ተደመምኩ። በርግጥ በተዋሕዶ እምነትና በዚያች ቅድስት ሃገር ላይ የሆነውንና የተደረገውን ለሚያስብ ሕሊና ላለው ሰው ከበደሉና ከጥፋቱ እኛም እንዳያመልጠን ብሎ መነሳት በርግጥም
የጉግ ማንጉግ ዘመን ላይ ለመሆናችን አመልካች ብቻ ሳይሆን ማረጋገጫም ጭምር ነው። እኔ በቅርብ እንደማውቀው የሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በውጪው ዓለም ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ነች። ይኸውም ዝናዋ በመላው ዓለም የተኛኘ መሆኑን በበቂ መረጃ ለመገንዘብ ችያለሁ። በተለይም መንፈሳዊ አገልግሎቶቿ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቁ ከመሆናቸው አኳያ ሲታይ ምን ጎደለና ነው በቀውጢ ቀን ቤተክርስቲያንን ከሚያጠፉ ጎን እንቁም እየተባለ ያለው? ለሚለው ጥያቁዬ መልሱን ማን ይሰጠኝ ይሆን ብዬ አልጠየኩም፤ በተለያዩ አካባቢዎች ከተካሄዱትን አስነዋሪ ድርጊቶች ስላገኘሁት።
ሁላችሁም እንደምታውቁት በቅርቡ በእህት ቤተክርስቲያናችን በሎንዶን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ሁኔታ በቅርብ ተከታትየዋለሁ። በውስጠደንብ እናሻሽል ሰበብ የተጀመረው አለመግባበት ቤተክርስቲአኗን ለሁለት መክፈሉ ምስጢሩ በርግጥም የውስጥ ደንብ ማሻሻል ጉዳይ ሳይሆን ማን የት እንደነበረና አላማውም ምን እንደነበረ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ታሪክ ነው። የጵጵስና ሹመት አንድም በረብጣ አልያም ቤተክርስቲያናትንና ምእመናንን አሳልፎ በመስጠት በሆነበት ዘመን የተፈጸመ ወንጀል ስለሆነ የዚህ አይነቱ ሃሳብ መፍለቂያ ያው የመለያየትን ጦስ ያመጣብን አካል መሆኑን በሚገባ ስለተረዳሁት ማለቴ ነው።
ከላይ ለመንጋው የማይራሩ ብዬ በታላቁን መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈረውን ቃል መጥቀሴ በለንደን ከተፈጸውና በሚኒሶታ ደብረሰላም ቤተክርስቲያን ላይ ለመፈጸም ከታሰበው እኩይ ሴራ ጋር ስለተመሳሰለብኝ ነው። በታላቁ አብይ ጾም በግቢያ/ቅበላ/ እለት ጀምሮ የተዘጋው የሎንዶን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በአለ ትንሳዔንና እርገትን በአለ ልደተ ቤተክርስቲያንንን/ጰራቅሊጦስን/ ጨምሮ ምእመኑ በተቀደሰው ቤቱ /ቤተክርስቲያኑ/ ሆኖ እንዳያከብር ከማድረግ የበለጠ አውሬነት ወይም ርኅራኄ አልባነት የለምና ነው። የቤተክርስቲያኗ አለቃ ተብዬው ሰው ሹመት ፈልገው ያን የመሰለ ታላቅ ደብር ያለምንም ርኅራኄ እንዲዘጋ ማድረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? ለመንጋው የማይራሩ እረኞች የተባለላቸው ካልሆኑ በስተቀር! አሁን እኔ እንደምመለከተውም በሚኒሶታ ደብረሰላም ቤተክርስቲያን ያለው ሁኔታ ይኸው ነው። ይህችን ታላቅ ደብር የመበጥበጥና ምእመናኑን የመከፋፈል አካሔድ አሁን ያለውን የቤተክርስቲያን ችግር ወይንም የጳጳሳት መለያየት ይፈታል ተብሎ የመጣ ሳይሆን በዚያች ቅድስት ሃገር ላይና በኅዝቧ መካከል መለያየትን ያመጣው ቡድን /ርኩስ መንፈስም በሉት/ ጥንስስና ሴራ ነው። የሎንዶኑ የቀበሮ ባሕታዊ ‘መነኩሴ’ ሰላምንና እርቅን እምቢ ብለው ጥረቱን ሁሉ ካመከኑ ጉያ ለመግባት መወሰኑ ህያው ምስክር ነውና!
ስለሆነም በታላቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችን ውስጥ እየተደረገ ያለው አጠቃላይ ሁኔታና መሪዋም መንፈስ ቅዱስ መሆኑ ቀርቶ መናፍቃንና እምነት የሌላቸው …የኦርቶዶክስን አከርካሪ ሰብረነዋል….የሚሉ ግለሰቦች መሆናቸውን አውቀን በዚህ በሚኒሶታ አካባቢ የምንገኝ ምእመናን ሁሉ አንድነታችንንና ቤተክርስቲያናችንን ነቅተን መጠበቅ ይገባናል እላለሁ።
በዚህ አጋጣሚም ስለቤተክርስቲያንና ስለቅድስት ሃገር ኢይዮጵያ ድምጻቸውን ከሚያሰሙ ወገኖች ጋር ሁሉ በአንድነት በመቆም የትውልድ ድርሻችንን መወጣትን አንርሳ። ለሁሉም የእውነተኞቹ ቅዱሳንና የደጋጎቹ አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!