Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

(የሳዑዲ ጉዳይ) የማለዳ ወግ …በጭካኔ እየተገዳደልን ፣ ወዴት እየሔድን ነው ? –ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ አረቢያ

$
0
0

(ፎቶ ፋይል)

(ፎቶ ፋይል)

ከሳምንት በፊት እዚህ ጅዳ ሻረ ሄራ በሚባል አካባቢ የሃበሻን ዘር ያሳዘነ የግድያ ድርጊት መፈጸሙን ሰማሁ ። ትውውቅ ባይኖረንም በአይን የማውቀው ወንድም አብዱ ሁሴን ይማም በጭካኔ መገደሉን የሰማሁት ድርጊቱ በተፈጸመ ከሰአታት በኋላ ከአንድ ወዳጀ በኩል በደረሰኝ የስልክ መልዕክት ነበር። በቀጣይ ቀናት ወጣቱ አብዱ የተቀጠፈበትን የጭካኔ ድርጊት የሚያወግዙ በርካታ መልዕክቶች ማስተናገድ ጀመርኩ። በመካከላችን ባሉ ጥቂት የሰው አውሬዎች እየሆነ ያለው እና ስማችን የመክፋቱ ነገር ያሳሰባቸው በርካታ ወገኖች በግድያው ማዘናቸውን በመግለጽ በርካታ መልዕክቶችን ልከውልኛል። በጭካኔ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ዘልቆ ነፍሱን አስጨንቆ ያሳዘነው አንድ ወንድም የላከልኝ መልዕክት እንዲህ ይላል ….

” ጩኸት ሰሚ ሲያጣ እንዴት ያናዳል … ሀበሻ የድሮወቹ የሉም … ወድ የሆነውን የሰውን ደም በከንቱ የሚጠጡ እርኩስ መንፈስ የተጠናውታቸው ውሾች ናቸው .so ሰሞኑን በ ጅዳ አካባቢ ሸር ሄራ አካባቢ የተደረገውን ግፍ ልንገርክ …በሀበሾች ጭካኔ የተገደለውን ልጅ በአካል አውቀዋለሁ አብዱ ሁሴን ይማም ይባላል … በሳንጃ ገደሉት ! ልብ በል … የሳውድ መንግስት ታዲያ እንዴት አያሳድደን ! እንደነዚህ አይነት እርኩሶች እያሉ እኛ ቤተሰብ እንዴት እንርዳ? ልጅስ እንዴት እናስተምር? ..ነብዩ ሰው እንዴት …የሰውን ነፍስ ያጠፋል? ደግሞም ሳውዲ ውስጥ ? ከተሰራ ለሚገኝ ገንዘብ እጅግ ያሳዝናል ይጎመዝዛል ! ጌታ እውነቱን ይፍረድ ለሀበሻ ጩኸት በቃኝ እኔም ሀበሻ ነኝ!!! ” ይላል !

ሰሞኑን “ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ላይ በግፍ የግድያ ወንጀል ተፈጸመ !” የሚለው ወሬ ከጓዳ እስከ አደባባይ ሲናኝ አስከፊውን ሂደት የታዘቡ ወገኖች ኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበሩም። ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁና ከሚከታተሉ የሃገሩ ሰዎችም መልዕክቶችና አስተያየቶች ደርሰውኝ በሃፍረትም ቢሆን ለማስተናገድ ተገድጀም ነበር … የሟችን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ ፣ ኢትዮጵያን የሚወዱና ስለኢትዮጵያ የሚጽፉ ፣ አንድ ከፍ ያለ ሃላፊነት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያና ሃያሲ የሃገሩ ሰው አዝነውብን አግኝቻቸዋለሁ ። በቁም ነገር በቢሯች አስጠርተው ያሉኝ እንዲህ ነበር ” ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ምንድ ነው እንዲህ የመሰለ የዘቀጠ በሃበሾች ያልተለመደ ጉዳይ ተደጋገመሳ ? ሀበሾች ምን ገባባችሁ? ከአመታት በፊት በሪያድ መንፉሃ ፣ ከወራት በፊት በመዲና በአብሃ እና በዙሪያው ያን ሰሞን ደግሞ በኪሎ ተማንያ እና በዙሪያው በሃበሾች መካከል መጨካከን የተሞላበት ድርጊት ታይቷል። ከሁሉም የሚያሳዝነው የግድያ ምክንያቶቹ ጊዜያዊ ጸብን ፣ ጥቅምንና ጥቃቅን የሰው ህይዎትን በጭካኔ ሊያስጠፉ የማይገባቸው ምክንያቶች ናቸው ። ግን ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ወደ የትስ እየተኬደ ነው? ” ሲሉ በጥያቄ ላፋጠጡኝ ሳውዲ ወዳጀ የሚሆን መልስ ግን አልነበረኝም ! ብቻ የሆነው አሳዝኖ ፣ አሳፍሮ አንገቴን አሰበረኝ …

እርግጥ ነው ፣ ባሳለፍናቸው አመታት በሪያድ መንፉአ አካባቢ አልፎ አልፎም በኢትዮጵያውያኑ መካከል በሚፈጠር ግጭት ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ዜጎች በሰላ ጩቤ አሰቃቂ ጥቃት ተፈጽሞባቸው የመቁሰልና የመገደል አደጋ ምክንያት እንደ ነበር የአይን እማኞች አጫውተውኝ ነበር ። በጩቤ ለመወጋጋቱ ዋንኛ ምክንያትም ደግሞ ተራ ከገንዘብና ከሴት ጋር የተያያዙ እዚህ ግቡ የማይባሉ መሆናቸው ማጤንና መገንዘብ ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል …በቀደሙት ጥቂት አመታት በሳውዲና የመን ድንበር ከተሞች ይህ መሰሉ ወንጀል የከፋ እንደ ነበር አውቃለሁ። በተለይም በጀዛን ፣ በአብሃና በከሚስ ምሽት በሚባሉ አካባቢዎች በዙሪያው ባሉ የከተማና የገጠር ከተሞች በከተሙ ኢትዮጵያውያን መካከል ተፈጸሞ የምንሰማው ግድያ ፍጹም ጭካኔ ያልተለየው መሆኑ ይጠቀሳል ! ወደ አብሃና ከሚስ ምሸት ለስራ ባቀናሁባቸው ቀናት በእኛ ዙሪያ እየሆነ ያለውን ለመስማት የከበደ መረጃ በእጀ መድረሱን አስታውሳለሁ። በህገ ወጥ መንገድ ዜጎቻችን ከየመን ሳውዲ በሚያመላልሱ ለገንዘብ በገንዘብ እየሸጡ የሚተዳደሩ ደላሎችና አቀባባዮች በጎሳ ተቧድነውና ብሔርን ለይተው የሚከሰተውን ግጭት ከጩቤ ያለፈ እንደ ነበርም በቦታው ተገኝቸ ታዝቤያለሁ። በተለይም በአብሃ አካባቢ በግጭቱ ስለተቀጠፈው ህይዎት ፣ ፍርድን ይጠባበቁ ስለነበሩ የእኛ ገዳዮችም የፍርድ ሂደት በቅርብ እከታተል ነበር ። ከሁሉም የሚያሳዝነው የሰውን ልጅ ያህል ታላቅ ፍጡር በስለት የሚጠፋበትን ምክንያት መስማት እንደ ነበርም ትዝ ይለኛል። ከሃገር ቤት ያለ የዘር ፣ የግል ጥላቻና ጸብን መሰረት ያደረገው የደም መቃባት ፣ በገንዘብ መካካድ ” ጓደኛየን ነጠቀኝ!” ፣ “የሰማንያ ሚስቴን ደፈረ !”፣ በሚሉትና በመሳሰሉት ክሶች የሚያጠነጥነው ብቀላ በፍትህ ሳይሆን በጭካኔ ለመወጣት የሚፈጸም ያረጀ ያፈጀ ይትበሃል ሳውዲ ተከትሎን መጥቶ ስማችን ማርከሱ ደግሞ ከሁሉም በላይ ያማል!

በያዝነው አመት ከጅዳ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው በሙስሊማን ቅዱስ ከተማ በመዲናም በዜጎቻች መካከል በተፈጠረ የቨዛ ሽያጭ እና ተጓዳኝ የገንዘብ መካካድ ያስከተለው አምባጓሮ በቅዱሷ ከተማ ቅዱስ የማይባል ግድያ ለመፈጸሙ ምክንያት ነበር ። ይህም የጭካኔ ወንጀል የተፈጸመበት ኢትዮጵያዊ ፣ ወንጀል ፈጻሚው ኢትዮጵያዊው መሆኑ ደግሞ ጉድ አሰኝቶ አሳፍሮን አልፏል። ከወራት በፊትም እዚሁ ጅዳ በተለያዩ አካባቢዎች በኢትዮጵያውያን መካከል የተነሱ አምባጓሮዎች በተመሳሳይ ጭካኔ በተሞላባቸው የግድያ ድርጊቶች የተከበቡ ወንጀሎች ምክንያት ነበሩ ማለት ይቻላል። እናም ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ….

ባሳለፍነው ሳምንት በጭካኔ የተገደለው ወንድም ወንጀል ተጠርጣሪ ፣ ተጠያቂ የቅርብ ጓደኛ ወዳጁ እንደነበረና ከቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ሰማን ! አብዱ በማጣታቸው ትልቁ የሃዘን መርግ የወደቀባቸው፣ የሚይዙት የሚጨብጡ ያጡት ፣ ቤታቸው የጨለመባቸው አንዲት ሴት ልጂና የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ባለቤቱ ሃዘን የከበደ ነው…ስለአብዱን ቅንነት፣ ሰው አማኝ ፣ ትጉህና ታታሪነቱን የሚመሰክሩት ባልንጀሮቹም ሃዘናቸው መሪር ያደረገው የተፈጸመው የጭካኔ ወንጀል ብቻ ሳይሆን የወንጀሉ ቀዳሚ ተጠርጣሪ የቅርብ ወዳኛ መሆኑ ነበር ። በዚህም ሊያምኑት በከበደ ድርጊት እርር ድብን ብለው አዝነዋል! ዛሬ የማይሰማ የማያየን አብዱ ሁሴን በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል ይገኝ እንደነበር በቅርብ ጓኞቹ ጨምረው አጫውተውኛል ። የወንድም አብዱ ሁሴን ይማም የቀብር ስነ-ስርዓት ትናንት የካቲት 12 / 2006 ረቡዕ ከቀትር በኋላ በጅዳ ከተማ ተፈጽሟል ! አብዱ የሔደው ሁላችንም ወደ ማንቀርበት የላይኛው ቤት ነው ! ነፍሱን ይማረው ! ” አላህ ይርሃሙ !”

ወንጀሉን በትኩሱ ለማቅረብ በፖሊስ ክትትክ መሆኑና ተጠርጣሪ ወንጀለኛው ባለመያዙ የማለዳ ወጌን እንዳዘገየው ቢያስገድደኝም መረጃውን ባሳለፍናቸው ቀናት ከበርካታ ነዋሪዎች አስተያየቶችን ለመሰብሰብ ሞክሬ ነበር ። በዚህ መሰል ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ዙሪያ እየተነጋገረ የሚገኘውን አብዛኛው የጅዳ ነዋሪ ” ህጋዊ ህገ ወጥ ” ነገን ምን ይከተል ይሆን እያለ በጭንቀት በሰቀቀን እየጠበቀ ባለበት ሰአት የዚህ መሰሉ ድርጊት መፈጸም ” እንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ !” ሆኖበት ተመልክቻለሁ! ለእኔም የሆነብኝ እንዲያ ነው …

ድርጊቱ አሳዝኖኝ ለማውገዝ ያነሳሁት ብዕር መቋጫ የሚሆነው ሳውዲው ሃያሲ ወዳጄ ያጫወቱኝን ዘልቆ የሚሰማ ያልመለስኩት ጥያቄ ነው ። ሃያሲው ሃበሾች በዚህ መሰል ድርጊት እንደማንታወቅ ተንትነው ከቅርብ አመታት የሰበሰቧቸው መረጃዎች ቢያሳስቧቸው ቆጣ ብለው በንዴት ሲያጠይቁ “ግን ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ወደ የትስ እየተኬደ ነው? ” ነበር ያሉኝ …እኔም ተጠርተን የማናውቅበት ወንጀል ሲደጋገም አሞኛልና ድርጊቱን አወግዘዋለሁ! ወደ መጨረሻም አሳፍሮ መልስ ያጣሁለትን የሃያሲውን ወዳጀ ጥያቄ ላጠይቅ ግድ አለኝ … ግንስ … በጭካኔ እየተገዳደልን ፣ እየተጠላላን ወዴት እየሔድን ነው ? ምንድን ነው እየሆነ ያለው?
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>