ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
ኢህአዴግ የሚባል ገዢ በሄድንበት ሁሉ ለትዝብት የሚሆኑ ነገሮችን ማስቀመጥ አይተውም እኛም አንጀታችን ማረሩ ይቀጥላል፡፡ አንዳንዶቻችን ለአንጀታችን ማረር መፍትሔ ብለን በፅሁፍ አስፍረን እንገላገላለን ያለበለዚያ ለስንቱ አውርተን እንዘልቃለን፡፡ የሚያነብ ካለ ደግሞ ማስተካከያ ይወስዳል፡፡ ለሚስተካከሉት ማለት ነው፡፡ ተጠያቂ ካለ ደግሞ እንዲጠየቅ ማድረግ የእርምጃው አንድ አካል ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ ግን አፍ እንጂ ጆሮ የለውም ሰለሚባል ተጠያቂነት ያሰፍናል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ አባላቶቹ ሲያጠፉ ለአሽከርነት ቀብድ እንደከፈሉ ተቆጥሮ ይመዘገብና ሲፈለግ ይመዘዛል እንጂ በወቅቱ እርምጃ አይወስድም፡፡
አንድ ሰሞን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ የነበረ አስቻለው የሚባል ጓደኛዬ በከተማው ውስጥ መንገድ ዘግተው አጥር የሚያጥሩ ባለስልጣናትን ማሾር ጀምሮ ነበር፡፡ በዚያ መነሻ ብዙ የከተማ መንገዶች ተከፍተው መተንፈሻ አግኝተን ነበር፡፡ ባላስልጣናቱ በመንግሰት ገንዘብ ህገወጥ ግንባታ ማካሄዳቸው ከተጠያቂነት እንደማያድናቸው አስረግጦ ሲነገራቸው ማፍረስ ጀመሩ፡፡ እኛም ጉድ ተሰኝተን በቀጣይ መከላከያም ሆነ ቤተ መንግሰት የእግረኛ መንገድ እየዘጉ ማለፍ ክልክል ነው ማለት አይቻሉም ጥበቃቸውን ውስጥ ግቢያቸው ያደርጋሉ ብሎን በቴሌቪዥን መስኮት ተመለከትነው፤ ይህም ሳይተገበር እርሱም ተገፍቶ ከሀገር ወጥቶ ይኖራል፡፡ ይህን ጉድ ያስታወሰኝ በቅርቡ ቂሊንጡ እስር ቤት ሄጄ ያየሁት ጉድ ነው፡፡ አቶ አስራት ጣሴን በገደብ ከተጣለበት እስር የሚታሰብ ይሁን አይሁን ባይታወቅም በጣቢያ ለሶሰት ቀን እና በቂሊንጡ ለሰባት ቀን ቆይቶዋል፡፡ እንዳሰቡት አስራት ጣሴን አንገት ያስደፉት አልመሰለኝም ይልቁንም ውስጥ ገብቶ ተምሮ የወጣ ይመስለኛል፡፡ ብዙ ወዳጆች እንዳፈራ ነው የነገረኝ፡፡ አቶ አስራትን ለማውጣት እንደ ማስገባት ቀላል አልነበረም፡፡ የማውጣት ሂደቱም ግምገማ/ቢ.ፒ.አር ሊሰራለት እንደሚገባ የሚያሳብቅ ነው፡፡ ውስጥ ገብቼ ምን ያህል ደቂቃ እንጠብቅ ብዬ ሰሟገት ከ20 -30 ደቂቃ ቢሆን ነው ውጪ ጠብቁ ተብለን ወጥተን አላፊ አግዳሚ መታዘብ ጀመርን የተባለው ደቂቃ አለፈ ከሁለት ሰዓት በላይም ሆነ፡፡ ከቅጥር ጊቢ ውጭ ያለስራ መቀመጣችን አንድ ነገር ይዞ ብቅ አለ፤ ወዲህ ወዲያ ማየት እና መንቀሳቀስ፡፡ እየተንቀሳቀስን እያለ የጊቢው አጥር በግምት ርዝመቱ ከሁለት መቶ ሜትር እና ቁመቱ ከሁለት ሜትር በላይ የሚሆን ነው፡፡ ይህ አጥር ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ወደ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚሄደውን አዲስ መንገድ ዘግቶ ተገትሮዋል፡፡ የመንገድ ሰራውን አስቁሞታል፡፡ ይህ አጥር የተሰራው በቅርብ ሲሆን ለምን 12 ሜትር ከፕላን ወጥቶ እንደ ተሰራ ግርምት ፈጠረብኝ፡፡ ይሄኔ ነው አሰቻለው ትዝ ያለኝ መፍትሔውን ሳሰብ አጥሩ መፍረስ አለበት ግን ይህ የሚፈርስ አጥር የተገነባው በህዝብ ሀብት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መፍትሔው መፍረስ ብቻ ነው፡፡ ይህ አጥር በዚህ ሁኔታ ከፕላን ወጥቶ እንዲሰራ ያደረገ መጠየቅ አለበት፡፡ ከፕላን አልወጣንም የሚል መከራከሪያ ካላ ይህን ፕላን አዘጋጅቶ የሰጠ መሃንዲስ መንገድ መኖሩን አላውቅም ነበር ሊለን ስለማይችል ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል፡፡ በማነኛውም ሁኔታ ግን የተጠያቂ ያለ ብለን እንድንጮህ ይህን ሀሳብ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ከአጥሩ ጋር ተያይዘው የሚፈርሱ ብዙ የመብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ለማነኛውም ይህን ፅሁፍ ያነበበ ጋዜጠኛ የእስር ቤቱንም ሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሰዎቹን አነጋግሮ ለህዝብ ይፋ ያድርግልን፡፡ አንገታችን ታንቆ በምንከፍለው ግብር የሚሰራ መንገድም ሆነ አጥር እንደፈለገ የሚፈርስ መሆን የለበትም፡፡
ሌላው ሰሞነኛ ጉዳይ ደግሞ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወንበራቸውን በቅጡ ሳያደላድሉ ፈተና የበዛባቸው መሆኑ ነው፡፡ አንዱ የፈተናቸው ምንጭ ደግሞ አቶ አለምነው መኮንን የተባለ ካድሬ ነው፡፡ አቶ አለምነውን አንተ ያልኩት ከተመስገን ደሳለኝ ተውሼ ነው፡፡ አምባገነን ሰርዓትን የሚመሩ ሰዎች አንተም ሲበዛባቸው ነው ሰለሚል ማለቴ ነው፡፡ ለነገሩ እኛም ሰፈር ቢሆን አንቱ ብሎ ስድብ የለም፡፡ አቶ አለምነው ደግሞ ሰድበውናል ስለዚህ መሰዳደብ ሊጀመር ከሆነ አንቱታው አይገባቸውም፡፡ ብአዴን ለአማራ ህዝብ ክብር ሲል ይህን ካድሬ ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ ከኃላፊነቱ ማንሳት ሲገባው በየቦታው እየዞረ ማስተባበሉን ቢያቆም ጥሩ ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ዓይነት አካሄድ በኢህአዴግ መንደር የተለመደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናው በምክር ቤት ቀርበው ይሁን በጋዜጣው መግለጫ አንድ ፋውል መስራታቸው የተለመደ ነበር፡፡ ታዋቂዎቹ ፋውሎች ባንዲራ ጨርቅ ነው፣ የአክስሙ ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው? የመሳሰሉት አሁንም ትዝ ይሉናል፡፡ በዚህ ጊዜ በህዝቡ ዘንድ ጫጫታ ሲነሳ እርሳቸው ማለት የፈለጉት የግል ሚዲያ፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች፣ ኒዎሊብራሎች እንደሚሉት ሳይሆን ይህን ለማለት ነው በማለት እንደምታ ትርጉም ይስጠው ነበር፡፡ አለቆቻቸው ውሃ እየተጎነጩ የፈለጉትን ይናገራሉ፤ ካድሬዎች ምራቃቸው እስኪደርቅ በውሃ ጥም እየተሰቃዩ ለማስተባበል ይሞክራሉ፡፡ ይህ የማስተባበል ዘመቻ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ቢሆን በማስተባበል ጫወታው የገቡ ይመስላል፡፡ አቶ አለምነው መኮንን ፀያፍ ስድብ ተሳድቦዋል፡፡ ድምፁ የእኔ ነው ሰድቡ ግን የእኔ አይደለም የሚለውን ቀልድ ትቶ ማሰተባበል ካልቻለ ይቅርታ ይጠይቅ፣ ብሎም ከሃላፊነቱ ይነሳ፡፡ የአቶ ገዱ “አቶ አለምነው ለአማራ ሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሰሩ ናቸው” የሚለው ምስክርነት እውነት ከሆነ ጥፋት ማቅለያ እንጂ ከጥፋተኝነት መዳኛ አይደለም፡፡ በፍርድ ቤት ጥፋት አጥፈተሃል አላጠፋህም ተብሎ ሲጠየቅ የቤተሰብ ሃላፊ ነኝ ብሎ እንደ መመለስ ነው፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሁን የያዙት ተግባር ደረጃቸውን አይመጥንም የሚጠበቅባቸው ለተሰደበው ህዝብ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ነው፡፡ እኔ አቶ አለምነው ይሰቀል አላልኩም፤ ይውረድ ነው፡፡
ሌላኛው አስገራሚ ዜና ደግሞ ፖሊሶች ማን ፍርድ ቤት እንደደፈረ አላወቅንም አሉ፡፡ ኮምሽነር ጄነራሉም ማወቅ አልቻልምን አሉ፡፡ አሰቂኝ ዜና ነው፡፡ እኔ የገባኝ ግን ፍርድ ቤት በመድፈር ከተጠረጠሩት ውስጥ ባለ ከፍተኛ ማዕረጎች ፍርድ ቤቱን እንደደፈሩ የሚያሳይ ነው ፍንጭ ነው፡፡ ተራው ወታደር ቢሆን ኖሮ ታንቆ ይስጥ ነበር፡፡ ተራ ወታደሩ አለቆቹ እንዳጠፉ አውቆ ቢናገር ደግሞ የሚከተለውን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ዝም ማለት መርጠዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ በእለቱ ተረኛ የነበሩት አስራ አምስቱም በጋራ ተባብረው ነው ያጠፉት ማለት ነው፡፡ ለጥፋታቸው የሚመጥን ቅጣት ይገባቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ ፍርድ ቤት ባይደፍሩም ጥፋተኛ እንዲታወቅ ትብብር ባለማድረጋቸው ሁሉም ጥፋተኞች ናቸው፡፡ ዳሬክተር ጄነራሉ እንደሚሉት ጉዳዩን ወደ እኛ መልሱትና እኛ በተቋም ደረጃ እርምጃ እንውሰድ የምትለውም ፌዝ ቢጤ ነች፡፡ ለማነኛውም ግን ፍርድ ቤቱ አስተማሪ የሆነ ነገር ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ይህ ጉዳይ በህዝብ ዓይን እና ጆሮ ሰር ገብቶዋል፡፡ ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ለሚደርስ ጥፋት መርምሮ እንዲይዝ የተቀመጠ አካል ከአስራ አምስት ሰዎች ውስጥ ጥፋተኛ መለየት አልቻልኩም ሲል ግን ትዝብት ውስጥ እንደሚገባ ያለማወቁ ያስተዛዝባል፡፡
በመጨረሻም ለመሰናበቻ የሚሆን ሰለ የካቲት 11 ክብረ በዓል እናንሳ፡፡ ይህ በዓል በየአምሰት ዓመት በሰፊው ይከበር የነበረ ሲሆን አሁን ግን በተለየ ሁኔታ እንደተከበረ አብርሃ ደስታ ነግሮናል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ምን አልባት በቀጣይ ዓመት በምርጫ ውጥረት ምክንያት ሊሆን ቢችል ብሎ መጠርጠር የአባት ነው፡፡ ግን ምን ችግር አለው በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ከዚህ በበለጠ ቢያከብሩት ገንዘቡ እንደሆነ የፓርቲ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እኔ ግን ግርምት የፈጠረብኝ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ከፍተኛ አመራሮችን(እነ ተፈራ ዋልዋን ጨምሮ) ይዞ ወደ አዲስ አበባ ሊመጣ ሲል ችግር ገጥሞት የነበረው የሱዳን አውሮፕላን ለምን ለህውሓት ብቻ መታሰቢያ እንዲሆነ ተፈለገ የሚለው ነው፡፡ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ይህን አሮጌ አውሮፕላን አይደለም አዲስ ጀት ገዝተው ቢሰጡን የሚበዛብን አይደለም፡፡ ምክንያቱም በነብሰ ገዳይነት ለእስር የሚፈለጉ ሰውዬ እንደፈለጉ የሚወጡበትና የሚገቡበት ሀገር ከዚያም አልፎ ክሳቸው ይነሳላቸው ብሎ የሚከራር መንግሰት ይህ ስጦታ ቢያንስ እንጂ አይበዛም፡፡ የእነ ተፈራም ነብስ የህውሓት ነብስ ነች እንዴ እረ እየተስተዋለ፡፡