በይበልጣል ጋሹ
ትውልዱ ከበፊቱ በበለጠ መሪ የሚፈልግበት ዘመን ነው። ጊዜውንና ዘመኑን የዋጀ ወላጅ፣ መሪና ህብረተሰብ ይፈልጋል። የዘመኑን ትውልድ በጥሩ ሥነ ምግባር፣ ለአገር ተቆርቁሪና በማንነቱ የሚኮራ አድርጎ ለማሳደግ ሃላፊነት ሊወስድ የሚችል አካል ያስፈልጋል። የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ግን ወደየት እሄደ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶችን መጥቀስ ይቻላል። የትናቱንና የበፊቱን ትውልድ በማነኛውም መልኩ በእጅጉ የሚያስመሰግን ከሆነ ውሎ አድሯል/የበፊቱን ስርዓት ናፋቂ ባትሉኝ ደስ ይለኛል/። ትውልዱ በአለማዊነት ተፅዕኖ ውስጥ ወድቆ ማንነቱን የረሳ ትውልድ እንደሆነ በመሰረተ ሃሳቡ የምንስማማ ይመስለኛል። ከተስማማን መንስኤውና መፍትሄው ምን ይሁን? የሁላችን መሰረታዊ ጥያቄ ይሆናል።
መንስኤው፦
- አለማዊነት፦ ትውልዱ አለማዊነት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በሚገባ ከአለማወቅ የመጣ ችግር ነው። ይህንን ሃላፊነት ወስዶ ሊያስገነዝበው የሚችል አካል በማጣቱ የመጣ ትልቅ ክስረት ነው። ወላጅ እንደ ወላጅ፣ መንግሥት እንደ መንግሥት፣ እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዜጋ ሃላፊነቱን በየደረጃው መወጣት ስላልቻለ አንድ ትውልድ በማጣት ላይ እንገኛለን። ይህን ደግሞ በአካባቢያችንና በሰፈራችን የምናያቸውን ነገሮች መጥቀስ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ናቸው። ልጅን በሃይማኖት ማሳደግ እንደኋላ ቀርነት ተቆጠረ፤ልጆችም ስለእምነትና ባህል መነጋገርንና መወያየትን ትተው ስለአለማዊነት “ስለ ግብረ ሰዶምና ሰይጣናዊነት” መነጋገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህንና መሰል አስነዋሪ ድርጊቶች ሲከናወኑ እያየን ዝም በማለታችን ለትውልዱ መጥፋት በየደረጃው ተጠያቂዎች ነን። የመጀመሪያዉና ትልቁ ለትውልዱ መጥፋት መንስኤው ይህ ነው።
- ትምህርት ቤቶች፦ ተማሪዎችን በጥሩ ሥነ ምግባርና ባህልን ከማሳዎቅ አንጻር አስተምሯቸው ዝቅተኛና ከዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ለትውልዱ መጥፋት ሌላው መንስኤ ነው። እንደሚታወቀው ትውልዱ ጥሩ ዜጋ እንዲሆንና እምነቱንና ባህሉን አክባሪ አድርጎ በማነጽ በኩል ት/ቤቶች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ዛሬ ግን ትምህርት ቤቶችን ስንመለከት ከተቀረጸላቸው ሥርዓተ ት/ት ጀምሮ ትውልድን ለመቅረጽ ቀርቶ በዜግነት ደረጃም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚናገር ትውልድ እንዳይጠፋ ስጋቴ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ባለፈም አንዳንድ ት/ቤቶች የብልግና ድርጊት ተባባሪዎች በመሆናቸው ለትውልዱ መጥፋት ተቆርቋሪ አካል መጥፋቱን ያመላክታል /በህጻናት ላይ ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ መምህራን የሚገኙበት ት/ትቤቶች/። ወላጅም ልጆቻቸውን የሃይማኖት ት/ት ቤት ልኮ ሥነ ምግባር እንዲማሩ የማድረጉ ተግባር አናሳ ነው። ከፍተኛ ት/ት ተቋማትም የተማረና አገርን ሊረከብ የሚችል ዜጋ ይፈራበታል ብሎ ማሰብ ቅዥት እየሆነ መጥቷል፤ የመጥፎ ሱስ ተገዥዎች ቁጥር በግቢ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ ነው፤ እንደ አንዳንድ ከተሞች በግቢ ውስጥም የዝሙት መፈጸሚያ ቦታውች ስም ተሰጥቷቸው እና እንስሳዊ ባህሪ ሲፈጸምባቸው እየታየ ችግሩን ለመቅረፍ ግን የሚወሰድ እርምጃ የለም።
- መንግሥት፦ ትውልዱ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን የማድረግ ሃላፊነትም ግዴታም ያለበት መንግሥት ነው። አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው እርሱ እስከሆነ ድረስ አገር ተረካቢ ዜጋ የመፍጠሩ ስራ በዋናነት የመንግሥት ነው፤ ምንአልባት “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ካልሆነ ነገሩ። ሃገራዊ ስሜት ያለው ዜጋ ለመፍጠር ይህን ስሜት ሊፈጥር የሚችል ሥርዓተ ት/ት፣ ሊተገብሩ የሚችሉ ትምህርት ቤቶችንና የማስተማር ብቃት ያላቸው መምህራንን ማደራጀት እንዲሁም ለተማሪዎች ከምረቃ በኋላ የሥራ ዕድል ማመቻቸት የመንግሥት ግዴታ ነው። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ለትውልዱ መጥፋት የመንግሥት ተቆርቋሪነት ጎልቶ የሚታይበት አጋጣሚዎች ባለመኖሩ ችግሩ ሥር መስደዱና በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን እንመለከታለን። መንግሥት ግን ትውልዱ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን ራዕይ የለውም? የዘወትር ጥያቄዬ ነው።
- ወጣቶችን ወደ አልተፈለገ ህይወት የሚመሩ ነገሮችን ቸል ማለት፦ በት/ት ቤቶችና ወጣቶች በሚያዘወትሩበት አካባቢ የሥነ ምግባር ብልሹነት ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮችን ተቆጣጣሪ አካል በመጥፋቱ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎቷል። ለምሳሌ ጫት ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ አሽሽ ቤቶችና የሴተኛ አዳሪ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ መጨመሩና ወደ እነዚህ ቦታወች መሄድ ከነውርነት አልፎ እንደ ዘመናዊነት በመቆጠሩ ትውልዱ በግልጽና በድፍረት የድርጊቱ ተሳታፊ ሁኗል።
- ማህበራዊ መገናኛዎች/ social medias/፦ ማህበራዊ መገናኛዎች ትውልዱን የማዳንም የመግደልም አቅም አላቸው። ይህን ተገንዝቦ ለትውልዱ መዳን የሚሰሩ መገናኛዎች ግን ጎልተው አይታዩም። በተለይ የዘመኑ መገናኛ ዜዴ በእጅጉ ትውልዱን ሰነፍና በአለማዊነት ተጽኖ ውስጥ እንዲገባ አድርጎቷል። ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንገባ ደግሞ ጥበብ የሞላበት አጠቃቀም አይደለም የምንጠቀምው ከጊዜ ማጥፋት ጀምሮ እስከ አጉል ሱስነት ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። የፌስ ቡክና ትዊተር ተጠቃሚዎች በእጅጉ ታውቁታላችሁ። ትውልዱ ወደ አልተፈለገ ህይወት ውስጥ እንዳይገባ በማህበራዊ መገናኛ ዙርያም ትልቅ ሥራ ሊሰራ ይገባል።
መፍትሔው፦ በአጠቃላይ ከላይ በጥቂቱ የተዘረዘሩትን ችግሮች በሚገባ ማጤንና አገራዊ ጉዳቱን በመረዳት ትውልዱን ለማዳን ከቤተሰብ፣ ከጎረቤትና አካባቢ በመጀመር ግዴታችንን መወጣት መቻል ነው። ልጆቻችንን ዘመኑን በዋጀ መልኩ ማሳደግ፣ መከታተልና በመንከባከብ በጊዜ ሂደት ችግሩን ልንቀንሰው እንችላለን፤ ፈጽሞ ማጥፋት ግን የሚታሰብ አይሆንም። ምክንያቱም ዓለም ሰይጣናዊነትን አሜን ብላ ስለተቀበለችሁ የዛ ነጸብራቅ ወደ ልጆቻችን መድረሱ አይቀርምና። ቢሆንም ግን ወላጆች ልጆቻችንን የት፣ ከማን ጋር እና በምን መልኩ መሄድ እንዳለባቸው ቀስ አድርገን በሚገባቸው መልኩ በማስረዳት በጥሩ ሥነ ምግባር ማሳደግ ይቻላል። ችግሩ ግን እኛስ ማን ነንና ለልጆቻችን አርያ የሚሆን ህይወት አለን? በፍቅርና ግልጽ በሆነ መልኩ ልጆቻችንን እያሳደግን ነው? ፍቅር የሞላበት የትዳር ህይወት፣ የጸሎት ህይወት አለን?