Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የመስዋዕትነት ወንጌል –ከጸጋዬ ገ.መድኅን አርአያ

$
0
0
በአጤ ኀይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት (በ1960 አካባቢ) ኤድመንድ መሪ የተባለ አሜሪካዊ የዕለታዊው ኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጣ አማካሪ ሆኖ ይሰራ ነበር። እኛም እንጠረጥረው እንደነበረ ሁሉ የአሜሪካ ስለላ ድርጅት ሠራተኛ (ኮንታክት ማን) ነው። (እግዜሩ ይይላቸውና ለካ በእኛም መሐል ሰዋቸውን ይተክሉ ነበር) ኤድ መሪ የሥነ ጽሑፍ ሰው ስለሆነ በማስታወቂያ ሚኒስቴር “ተረፈ ዜና” የምንለውን – የማይታተመውንና የማይታወጀውን (በራዲዮና በቴሌቪዥን) በንጥረ ነገሩ መውሰጃ ሥፍራ የተነፈስነውን ሁሉ ሰብስቦ ካገጣጠመው በኋላ ወደ አሜሪካ ሲመለስ Kulubi የሚል መጽሐፍ አወጣ። እንግዲህ ተረፈ ዜና የገባችሁ ይመስልኛል። ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ብዙ ሳንርቅ- ጠባያችንን ወደማያውቁ ሰፈሮች በወረራ መልክ ሳንዘምት እዚያችው ከባዕታችን እንደልማዳችን እንቀማምስና (ከቢራ አያልፍም) ቶሎ ወደ ማተሚያ ቤት እንመለሳለን። እንግዲህ ደግሞ ወደ ማተሚያ ቤት እንመለሳለን። “ምሳችንን እንጠጣ” ይላሉ አንዳንዶቻችን። ቀስ ብሎ ሁላችንም እንዲህ እንደምንል ተደርጐ ተወርቶብናል።
Pen
 በምሽቱ የቢራ ታይም አውት ሰዓት እንደ ሚዚዬ (መክሰስ) ልትታተም ያልቻለችና የማትችል ወሬ ትቀርባለች። ድሮ ድሮ እኔ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ሪፖርተርነት ስሠራ አንዳንዶቹን ተረፈ- ዜና ውሃ እየጨመርሁባቸው “የአዲስ አበባ ሹክሹክታዎች” ብዬ ለማውጣት ሞክሬያለሁ። ያም ሆኖ “የማይታተሙና የማይታወጁ” “ተረፈ ዜና” ደኅና አድርገን ሰልቀን እንመለሳለን። አሉባልታ አልተከለከለም። የተከለከለው በጋዜጣና በራዲዮ ላይ ነው። የኤድመሪ “ቁልቢ” እንዲህ ያሉና የበለጠ በፖለቲካ ትካዜያችን ወቅት በብቅል የመጣ አሳብ ከእኛው ለቃቅሞ ጥሩ ውበትና ስላቅ ለብሶ የመጣ መጽሐፍ ነው። አይ የሰላይ ነገር! ( በኋላ ጊዜ- በ2006ዓ.ም ላይ ሰውየው ሲሞት ሰላይ እንደነበረ በኦፊሲያል ተነግሮናል። ያለፈ ነገር አንዳንድ ጊዜ ይጥመናል። ደራሲያችን አቤ ጉበኛ አንድ ጊዜ- በዚያው በአጤው ሥርዓት አሜሪካ ሄዶ ሲመለስ በመጀመሪያ ያወራልኝ ኤድመሪን በገዛ አገሩ እንደደበደበው ነው። እኔም “የእኔ ዘርዓይድረስ!” አልሁት።)
 አዎን ኤድ መሪ- በኋላ ጊዜ በዓሉ ግርማ ሲጽፍ በነበረበት ስታይል – የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንት አጣምሮ በአንድ ስም እያቀረበ በማናገር መጽሐፉን አጣፍጦታል። በዚያ ጽሑፍ ላይ በቅርብ የሚያውቀውን በመጨረሻው የአጤው ሥርዓት የኅትመቱ ፕሬስ ምክትል ሚኒስትር የነበረውን አቶ ተገኘ የተሻወርቅን “ተስፋዬ” ብሎ ዋናው ገጸ ባሕርይ ያደርገዋል። (የኅትመቱ ፕሬስ መምሪያ የመጨረሻው የደርግ ዘመን ኅላፊ ይህ ጸሐፊ ነበር።) (ተረፈ- ዜና ማቅረቤ ነው- ባያምርልኝም) ለቁም ነገሩ ኤድ መሪ ትንንሹንም (ለምሳሌ የትልልቆቹን ሰዎች የወሲብ ሕይወትና አንዳንድ ባለሥልጣኖች እጅግ ወራዳ በሆነ ሁኔታ ቆነጃጅት እየመረጡ ለትልልቆቹ (ስም አላነሳም) ስለሚያቀርቡበት ሁኔታ ይወሳል። አንዳንዶች ደግሞ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ምን አቅጣጫ እንደሚይዝ እየታያቸው የጭንቅ ሕይወት እያሳለፉ እንደሚገኙ ቃኝቶአል። እንዲያውም ዋና ገጸ- ባሕርይ አድርጐ የሳለው “ተስፋዬ” (ማለትም ተገኘ የተሻወርቅ) በዚህ ረገድ እየተቃጠለ- እየከሰለ እንደሚገኝ ያወሳል። የትዮጵያ ውድቀት፣ የክብርዋ ድቅት፣ -የአንድነትዋ መፍረስ- በአንድ ወቅት ደሀዋ ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ… ካሉ አገሮች እኩልና ከቶውንም ጐላ ብላ የመታየትዋን ሁኔታ..ወዘተ ይነግረናል። የፖለቲካውን ሁኔታ ይመረምራል። አዎን ተስፋዬ ከአንድ ትልቅ ተራራ ላይ ያቆመዋል። ኢትዮጵያን በሙሉ ያያል። የተስፋዬ አእምሮ በአንድ ሴኮንድ እይታ ሰማያት ሲደፉበት፣ ያታየዋል። አእምሮው ሮጠ። ሮጠ። እዚያ ተራራ ላይ ደራሲው ለምን ተስፋዬን አወጣው? ወደ ሲና ተራራ፣ ወደ ካርሜል ተራራ፣ ወደ ደብረዘይት ተራራ ሄደው ከአምላካቸው የሚቀበሉትን ቃልና መልእክት ስለተረከቡትና በነዚያው ተራሮችም (ለምሳሌ ጌታ ኢየሱስ በደብረዘይት ተራራ) ለሕዝቡ ሲያስተምሩ እናነብባለን። የግሪክ አማልክት መኖሪያ በሚባሉት በኦሊምፐስ፣ የሮማውያን አማልእክት ቤቶች መገኛ በሚባለው አልፕስ- በሒማላያስ ተራሮች የሕንድ ሺህ በሺህ አማልእክትና መልእክቶቻቸው ብዙ አንብበናል።
 የኤድ መሪው “ተስፋዬ” ከእንጦጦ ተራራ ላይ ይቆምና ትልቂቱን ኢትዮጵያ ለማየት ይሞክራል። ትልቂቱ ኢትዮጵያ ለትናንሽ ዓይኖቹ ኮሳሳና ትንሽ ሆና ታየችው። የልጅ ኢያሱ ወዳጅና ባለሟል የነበሩት አባቱ በግዞት በነበሩበት ጊዜ ደሴ ተወልዶ ያደገበትና ከእሳቸውም ስለውብ አገሩ ሲሰማ ያደገበት ሁኔታ …ወደ ሐረር ሄዶ የልጅነት መንፈሱን ስለአገሪቱ ታላቅነት እየተረዳ የኖረበት፣ አብሮ አደጉ የለውጥ መንፈሱ የዳበረበትን ሁኔታ፣ በኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ…በዩኒቨርሲቲ ኰሌጅ ያሳለፈው የፖለቲካ ንቅናቄ ሕይወት፣ ከቦስተን ዩኒቨርሲቲ ሲመለስ ምን ለማድረግ፣ ምን ለመሆን የነበረው ህልም ግጥም አለበት። ለትናንሽ አይኖቹ፣ ለትንሽዋ ጭንቅላቱ ኢትዮጵያ ኮስሳና ኰስምና ታየችው። “ኢትዮጵያ! ወይ ኢትዮጵያ!” አለና ሲጨርስ ከእነዚያው ልም-ዓይኖቹ ውሃ ይቀዳ ገባ። አለቀሰ።
 እንዲህ ዓይነት ታሪክ ፍጻሜና የሌላ ታሪክ ጅማሬ ለትረካው ባለቤት (ኤድመሪ) እንዴትና ለምን እንደመጣበት አላውቅም። ለማንኛውም ግን “የሳይኪ ጉዳይ” እስካሁን በምንም ሁኔታ ተዘርዝሮ እንደማይነገር የታወቀ ነው። ብቻ በአገራችን የተከፋ ተደፋ – ይባላል። ተገኘ የተሻወርቅ ጥቅምት 13-1967 ሌሊት ላይ በጥይት ከተደበደቡት ስድሳዎቹ የአጤ ኅይለሥላሴ ባለስልጣኖች አንዱ ሆነ።
 እንደ ጥንቱ ነቢይ- እንደ ኤርምያስ እኔንም አልቃሻ ሳያደርገኝ አልቀረም። “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!..” እያሉ ሲያለቅሱ ከነበሩትና ትንሣዔዋን (እሱም ካለ) ሳያዩ ዓለምን ከተሰናበቱት ግዙፋን ኢትዮጵያውያን መካከል አለቃ አያሌው ታምሩም ትዝ ይሉኛል። አለቃ አያሌው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባዔ ፕሬዝዳንት ነበሩ። አዲስ አበባ በነበርሁበት ጊዜ እሳቸው የሚመሩት “ማኅበር በኩር” ከሚባለው በየሳምንቱ በሚሰበሰብ ጉባዔ ላይ ብዙ ጊዜ ተካፍያለሁ። ለመንፈሳዊ ልጆቻቸው “በኢትዮጵያ ቤተ መንግሥቱም ቤተክህነቱም ያለ መሪ የቀረውና መከራችሁ የበዛው በእኔ ምክንያት ነው። ኅጢያተኛው እኔ ነኝ።” እያሉ መንታ መንታ እንባ ሲያፈሱ አስታውሳለሁ። አለቃ አያሌው “የእኔ ኅጢያት..” ሲሉ የሃይማኖት አባቶችም እንደ ፖሊቲካ መሪዎች እልም ብለው የጠፉበትን ሁኔታ መግለጣቸው መሆኑ ይሰማኛል። በዚህም እምነት በመነሳት ከሩሲያ ዛሪና ጋር ተባብሮ በተራ ሴሰኝነት ተጠምዶ ክፉ እየመከረ፣ ሕዝብ እያስገደለ ለኮሚኒዝም መግቢያ አውራ ጐዳና ጠራጊ የነበረውን የውሸት መነኩሴ ራስ ፑቲንን (አቡኑን) ያወግዛሉ። የአባ ጴጥሮስን ፈለግ በመከተል እስከ ማዕዜኑ (እስከ ወዲያኛው) አትቀበሉት ብለዋል። ለነገሩ ከሞቱ ከአሥር ዓመት በኋላ የቤተክህነቱም የቤተ መንግሥቱም መሪዎች በጥቂት ቀናት ልዩነት ተያይዘው ሄዱ።” ባለፈው መጣጥፌ የጠቀስሁት ሥዩም ሐረጐት እንዲህ ዓይነት ፍጻሜን “የክብረ ነገሥት ፍጻሜ” ይለዋል። ይህ ፍጻሜ የአጤው ሥርዓት መደምደሚያ ብቻ አይደለም። ለራሳቸው አጤያዊ ሥርዓት የቆረቆሩትን ዘመናዊ አጤ በጉልበቱና ራስፑቲኖችን ፍጻሜ ይመለከታል። የሚገርመው ከእነሱ በኋላም ቢሆን የአለቃ አያሌው እንባ አልተገደበም። በሥጋ ረገድ ዓይነሥውር የነበሩት የእኒህ አባት እንባ ደግሞ ሕሙም ከነበረው አንጀታቸውና ልባቸው የሚቀዳ እንባ ነበር። “ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም ለራስሽ አልቅሺ!” ነበር ጌታ ኢየሱስ ያለው? ለራሳችን የማናለቅስ ነንን? አለቃ አያሌው እንደ ተገኘ የተሻወርቅ የታያቸው ገና ያልመጣ – እንደሚመጣ የተረጋገጠ- የኢትዮጵያ አደጋ አለ። ጠብቁ ልበል ወይስ ይበቃናል?
 ከታገሳችሁ ሌላ አጋጣሚ ላውራችሁ። “የሸዋ ጠቅላይ ግዛት” እንደራሴ የነበሩትንና ከአውራ አርበኞቻችን አንዱ የሆኑትን ራስ መስፍን ስለሺን በ1966 መጋቢት ላይ አነጋግሬያቸው ነበር- ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ። የካቲት “ግም” ካለ በኋላ ስለ ለውጡ የተለያዩ የሕብረተሰቡ አባላትን “ስለ ለውጡ ምን ይሰማሃል? ወዴት የምጓዝ ይመስልዎታል? ከአድማስ ባሻገር ምን ችግር- አደጋ- ያታይዎታል? ወንድሜን ማን ልበል?..” የሚሉ ጥያቄዎችን ይዘን መዞራችን አልቀረምና ጌታ ራስ መስፍንን በቢሮአቸው አነጋግሬአቸዋለሁ- እንዲያውም የሾረ ጋዜጠኛ ከምለው ከሀብተ ዮሐንስ ዲሳሳ ጋር። በግልጽ እንደ ነገሩን የኢትዮጵያ ሰማያት ያረገዙት ዝናም የምሕረት አይመስልም። “አየኸው ጌታዬነህ! የኢትዮጵያውያን ደም የተከበረ ነው። በከንቱ መፍሰስ የለበትም። አንድ ጊዜ መፍሰስ ከጀመረ ማቆሚያ የለውም። ለውጥ አያስፈልግም አንልም። ያስፈልጋል። ደም በመፋሰስ የሚመጣ ለውጥ ለማን ሊጠቅም ይችላል?” ነበር ያሉኝ። ብዙ ጊዜ የምጠቅሰው የሼክስፒየር ቃል አለኝ። መጭ ሁኔታዎች አስቀድመው ጥላቸውን ያሳያሉ፤ Coming events cast their Shadow- አዎን ለራስ መስፍን እንደታያቸው ሁሉ በዚያ ወቅት የኢትዮጵያውያን ደም መፍሰስ የጀመረ እነሆ አርባ አመት ሆነው። ራስ መስፍን በዚያን ወቅት ለማልቀስ አልዳዳቸውም አይባልም። እንባቸውን ከመታገላቸው በስተቀር።
  ኔልሰን ማንዴላ በ Long Walk to Freedom ስለ ፍርሃትና ድፍረት የነገሩን ቁም ነገር አላቸው። በየሰው ልብ ውስጥ ፍርሃት አለ። የድፍረቱ መጠን (ዶዜች) ትንሽ ከፍ ያለውና ያንንም በተግባር የሚያውለው ጀግና ይባላል። ደፋር ይባላል። አለዚያ ሁላችንም በተፈጥሮአችን ውስጥ- ከተፈጥሮ የወረስነው ፍርሃት አለ። ጀግኖች ደግሞ ከፈሪ ሕዝብ አየፈጠሩም። አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ በኅብረተሰቡ መሐል ሲወጣ በአንድ እጁ ጐራዴ፣ በሌላ እጁ ሰነኔ ይዞ አይደለም። ጀግና የሚፈልግ ታላቅ ሕዝብ ፈልጐ ያገኘው ነበር። ድፍን በረንታ፣ ድፍን ሶማ፣ ድፍን የዳባት፣ ድፍን ብቸና…እቅፉን ዘርግቶ ባይቀበለው ኖሮ በላይ አልነበረም። ታሪክም ባልሆነ ነበር።
 ጉራ እንደማይሆንብኝና እናንተም በዚህ እንደማትጠረጥሩኝ ተስፋ አለኝ። በመሠረቱም በእውቀትም፣ በማሕበራዊ ደረጃም ማንንም ወደ ታች ለመመልከት የማልችል ምስኪን ዜጋ ነኝ። እንዲህ የምልበት ምክንያት አለኝ። ማንንም ወደ ታች መመልከት ኅጢያት ሆኖ ይበላሃል። ወንድምህን ወደ ታች የምትመለከተው መንጥቀህ ልታወጣው የምትችል ከሆነ ብቻ ነው። እንዲሁ አንዳንድ ማስታወሻዎች እያየሁ፣ ከአንዳንድ ታላላቅ ዜጐች (በየአጋጣሚው) ጋር በመገናኘት ትዝታቸው የእግር እሳት እየሆነ እንቅልፍ የሚነሳኝ ነኝ። የልጅ ልጆቼን (ስድስት ሆነዋል) እያጫወትሁ፣ ቁም ነገር እየነገርኋቸው በሚገባኝ የዕድሜ ርበት ላይ አገር አጥቼ ስኖር (እግዜር ይመስገን መንፈሳዊ አገር አላጣሁም) በየጊዜው በርበሬ እንደታጠነ ወጣት የሚነቀንቀኝ ነገር አልጠፋም። እንግዲህ “በወረቀት ማበላሸቱ ሥራ” (በጋዜጣ ሥራ እንዳልል ያበረከትሁት አስተዋጽዖ ያሳፍረኛል- ከልብ) ብዙ ዘመን ስላሳለፍሁ ብትፈቅዱልኝ አንድ ሌላ ትዝታ አየመጣብኝ ነው። እንደ መረማመጃ አሳብ ከሆነ ደስ ይለኛል።
 በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጊዜ እንደ መጀመሪያው ጋዜጠኛ ሲጠቀሱ የነበሩትን ጋዜጠኛ (ከንቲባ) ደስታ ምትኬን ከአንዴም ሁለት ሦስቴ አነጋግሬያቸዋለሁ። ደስታ ምትኬ ምኒልክን ተከትለውና እንዲያውም የእቴጌ ጣይቱን ቀሚስ እየጐተቱ ወደ አድዋ ጦር ግንባር ከዘለቁ ለጋ ወጣቶች አንዱ ነበሩ። ወደ አድዋ ስለተደረገው ጉዞ፣ ስለአገራቸው ሠራዊት ልበ-ሙሉነት፣ ስለ ጦርነቱ ውሎ ደኅና ሲያወሩላችሁ ቆይተው አፈፍ ብለው ቆመው እየየ ይላሉ። የወደቀው የአገራቸው አርበኛ ከፊታቸው ይመጣባቸዋል። ይሰለፋል። ታንክ በጐራዴ የተባለበትን እሾሁ እንኳ ስለማይወጋው ጦረኛ ያወጉአችኋል። እየየ ይላሉ። አንዳንድ ሰነፍ ተዋጊ ለመሸሽ ሲሞክር እቴጌይቱና ደንገጡሮቻቸው “አንተ ወዴት ነው የምትሸሸው- እያሸነፍህ? እየረፈረፍኸው? የምኒልክ ጮማ- የምኒልክ ጠጅ ይኽ ነው?” እያሉ የፈሪ ልብ ሆነው ሲያዋጉ የነበረበትን ሁኔታ ያነሡና ያለቅሳሉ።
 ጦርነቱ አልቆ በምኒልክ ድንኳን ውስጥ ከነበሩት መሳፍንት መካከል ራስ መኰንን የተናገሩትን ያስታውሳሉ። ደስታ ምትኬ እንድሚሉት ራስ መኰንን “ግርማዊ ጃንሆይ! እናቴ እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር በዚች ዕለት ወደፊት በሚነሡ የኢትዮጵያ ትውልዶች ላይ የሚያመጣውን ጦርነት ሁሉ እኛው እንድንገላገለው ቢሰጠን ምንኛ መታደል ነበር?” እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ይህን ትዝታ ያወርዱና ከንቲባ ደስታ እየየ ይላሉ። በእንባ ይጠመቃሉ። ራስ መኰንን ከእነሱ በኋላ የሚበቅለውን ትውልድ የተጠራጠሩ ይመስላል። ለአገር አንድነት የሚኖረውን እሴት፣ የወገንን ሉዓላዊነትና ክብር በማስጠበቁ በኩል የሚያድርበት የውጊያ መንፈስ፣ “የኢትዮጵያ እና የመስዋዕትነት ፋይዳ ምን ያህል ለትውልዶች ሊወርድ እንደሚችል ጠርጥረዋል። በእኛ ላይ ተስፋ የቆረጡ ነበር…ልበል? ” ደስታ ምትኬ አለቀሱ። አለቀሱብኝ። መላልሼ አነጋግሬያቸዋለሁ። ደጋግመው አለቀሱብኝ። ደስታ የሉም። እኔ ቀርቻለሁ። አላቅሱኝ ልበል ወይ? ወይስ የደስታ ምትኬ ስሜት ያላችሁን ሁሉ እናላቅሳችሁ ወይ? (በነገራችን ላይ ከንቲባ ደስታ ምትኬ የኮሎኔል መንግሥቱን ሥርዓት ለመለወጥ ተነሥተው ከተሰውት ጄኔራል መኰንኖች የአንደኛው የጄኔራል አምሐ ደስታ አባት ነበሩ። የጀግና ልጅ ጀግና)  - በተጨማሪ ሊነሳ የሚችለው የጋዜጠኝነቱ ጉዳይ ሲወሳ ደግሞ ኤርትራ በወቅቱ በኢጣልያ ሥር ስለነበረች እንጂ በጋዜጣ ባለሙያነት ረገድ ምጽዋ ውስጥ ይታተሙ የነበሩት ጋዜጦች አዘጋጅ የነበሩት ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላይ ይጠቀሳሉ። እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ደግሞ በጋዜጣቸውና በሌሎችም ጽሑፎቻቸው ቅኝ ገዥውን አምርረው የታገሉ አርበኛ ናቸው። የብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላይ There is no medicine fot the bite of the White Snake ዋናው ነው። የስካንዲኔቪያው ምሁር የፕሮፌስር ተከስተ ነጋሽ ሥራዎች ለዚህ ምስክር ናቸው።
 ያ ሁሉ የአርበኝነትና የጀግንነት እሴት አንድ ጊዜ ሟሽሾና ከውስጣችን እንደ ፈጣን ወፍ ሸሽቶ ከላይ የጠቀስኋቸው ሰዎች ሁሉ የፈሩት እየደረሰ መጣ። እኛው በእኛው፣ እኛው ከእኛ ጋር ጠላትነት አበቀልንና እኛንም አገሪቱንም የሚያድን ጠፋ። በአገሪቱ ጀግኖቻችንና ዋናው የሃይማኖት አባት ላይ ሳይቀር ሞት ስናስተላልፍ ተገኘን። በፋሺስቶች ዘመን፣ ሚስት በባልዋ፣ አባት በልጁ፣ ኦሮሞው በኦሮሞው፣ አማራው በአማራው፣ ትግሬው በትግሬው ላይ ጦር የሚመዝበት፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ “ይሙት በቃ” የሚልበት፣ የሚጠቁምበትና የሚተኩስበት አሳዛኝ ገድል አየን። የምታውቁት ታውቁታላችሁ…ለማታውቁትም እንደ መርዶና የታሪካችን ቆሻሻ ምዕራፍ ላነሣ እችላለሁ። አንዱንና ጉልሑን ማለቴ ነው። የሰማያዊው ንጉሥ አገልጋይና የኢትዮጵያ የቃልኪዳን ልጅ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ግንባራቸውን ሳያጥፉና የሞት ፍርሃት ሳያስደነግጣቸው በፋሺስቶች ጥይት መደብደባቸውን ታውቃላችሁ። እውን ጣልያን ብቻ ነው ይሙት በቃ ያላቸው? አንድ የመሐል ዳኛው ነው ጣልያን የነበረው። የቀኝና የግራ ዳኞች ተብለው የተሰየሙት ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ብላታ አየለ ገብሬና ነጋድራስ ወዳጆ አሊ። “በጥይት ይደበደቡ ዘንድ ፈርደናል። ከማንዳንቴ ባሪሴሮ፣ ብላታ አየለ ገብሬ፣ ነጋድራስ ወዳጆ አሊ!” አቤት ጭካኔ! አቤት ጭካኔ! ከዚያ በኋላ የነበሩትን ብዙ ብዙ ክህደቶች ላጫውታችሁ እችላለሁ።
  ክህደቶቹ የባሰ የሆኑት “ጨው አልጫ ሆነ” ብሎ የክርስትና መሥራች ራሱ የሚመሰክርባቸው ካሕናትና መነኰሳት ሲሆኑስ? አቡነ ጳውሎስ (ራስ ፑቲን) እና አያሌ መነኮሳት ሲሆኑስ? አዎን አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል በክርስቲያናዊ አርበኝነትና ለአገርም ለሕዝብም ሰማዕታት ሲሆኑ አቡነ ገብርኤልና ሌሎችም የፋሺስቶች አስተናጋጆች እንደነበሩ ሌላው የታሪካችን ገጽታ ነው። ጄኔራል ቦዳልድ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ነው ሲባል ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ካሕናትና መዘምራን ሰላሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘው ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው፣ ከበሮአቸውን እየደበደቡ፣ ጸናጽሉን እያንጻለሉ…ተቀበሉት ይባላል። በጽሑፍ ጭምር ቆይቶልናል።…ቆይ ቆይ እንጂ ወዳጄ ዶክተር አረጋዊ በርሔ የሚነግረን ምሥጢር አለው። ወያኔ ሥልጣን ከመያዙ በፊት – ጫካ በነበረበት ዘመን ከአንድ ሺህ በላይ ካህናትና መነኮሳት ካድሬዎች ነበሩት። ስለ አስቆሮቱ ይሑዳ ማውራት የማይሰለቻቸው ከሐድያን ደባትር! ሃይማኖቱ በዚህ የተነሳ ሊወቀስ አይገባውም። ቆቡን ያጠለቁ ደካሞች፣ ጸናጽሉን የሚያንሹዋሹ ሰነፎች እንጂ። ራስ መኰንን እንዲህ ያሉ ሰዎችን እያሰላሰሉ፣ ራስ መስፍን የሚመጣውን የደም ጐርፍ እያሰቡ፣ የኤድመሪ “ተስፋዬ” የአገር መቅለጥ ትካዜ እያስጨነቀው ቢያለቅስ- ቢያለቅሱ- ይብዛባቸው?
                                የሚሰውት አለቁ?
ቀደም ሲል ለጠቀስኋቸው ጋዜጠኛ (ደስታ ምትኬ) ሁለት ጥያቄዎችን አንስቼባቸው ነበር። አንደኛው ጥያቄ “ለመሆኑ የአርበኝነቱ ዘመን- የጀግንነቱ ፍጻሜ” አድዋ ነው ብለው ያምናሉ?” ሁለተኛው ጥያቄ “እቴጌይቱ የምኒልክ ጮማ- የምኒልክ ጠጅ እንዲህ ነው ወይ? ሲሉ ለመሆኑ ያ ሁሉ ሠራዊት የምኒልክን ጠጅና ጮማ ያውቅ ነበር ማለት ነው?” አልኳቸው። አረጋዊው ከንቲባ የምኒልክ ጮማና ጠጅ ይትበሐል ነው። በምኒልክ ጊዜ ሕዝቡ ሰላም ነግሦለት፣ ፍትሕ አግኝቶ ያለሥጋት የሚኖርበት መሆኑን በሙሉ እርግጠኝነት ይናገራሉ። አገር የመጠበቅን እሴት አንሥተው በዚያ መንፈስ ሕዝቡ በአንድነት እየተመመ ወደ ጦር ሜዳ በደስታ እንደ ዘመተ ያወሳሉ። ኢትዮጵያን የጠበቀ ይህ መንፈስ ነው። ይህ እምነት ነው። ያ ወኔ ነው። የእነዚህ የሦስቱ ባሕርያት ውህደት እየተሸረሸረ መምጣቱን ደግሞ በዓይናቸው በብረቱ አይተውታል። በፋሺስቱ ወረራ ወቅትና በኋላም። በኋላም እስከ እኛ ድረስ! አዎን እንደሚባለው ምኒልክና ጣይቱ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ ወዘተ ያሉትም በማዕዳቸው ከበርካታ ሕዝብ ጋር ይመገቡ እንደነበረ ይታወቃል።
 እነዚህ የጠቃቀስኋቸውና እንደ ነብዩ ኤርምያስ ባለሙያ አልቃሽ የሚመስሉት አባቶች ፍርሃት ሊሰመርበት የሚገባ መሆኑን እረዳለሁ። ወርቁም ሚዛኑም በጠፋበት በዚህ ሰዓት ለአገሪቱ ጥሪ ማነው “እነሆኝ እኔ” የሚል? እኔም እንደነሱ በተራዬ እጠይቃለሁ። በግፈኞች አማካይነት ወደ ግፈኞች የስቅላት “ስካፎልድ” ሲወሰዱ ቀጥ ብለው በኩራት የሚራመዱ ሰዎች አሉን? አዎ…አዎ…አዎ…ቁጥራቸው አነሰ እንጂ!
 አቶ ተፈራ ደግፌ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሥርዓት በማስያዝ፣ የባንክን አገልግሎት ለማስተዋወቅና ራሳቸውም በንጽሕናና በሕጋዊነት በመኖር የተደነቁ አገር ወዳድ ሰው ናቸው። አቶ ተፈራ በደርግ ጊዜ በግፍ ከታሰሩ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። ከእሥራት ከተፈቱ በኋላ Tipping Points የሚል የትዝታ መጽሐፍ አውጥተዋል። ለመድገም ያህል አቶ ተፈራን በንቅዘት፣ በቅብጠትና በውስልትና መጽሐፉ አይጠራቸውም። ታዲያ አቶ ተፈራ በጠቀስሁት መጽሐፋቸው ላይ መላልሰው የሚጠይቁት ጥያቄ አለ። “ለምን እኔ?” Why me? Why me? Why me? ለምን እኔ? ሌሎችም ሰዎች ሁሉ ይህን ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ። የሞቱት ስድሳ ጓደኞቻቸው- በኋላም በሰማዕትነት የወደቁት እነ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ቄስ ጉዲና ቱምሳ፣ ደጃች ካሣ ወልደማርያም- አበበ ከበደ- ሐረጐት ዓባይ…ከመቃብርም ሆነው ለምን እኔ? ሊሉ ይችላሉ። አባ ኮስትር በላይ ዘለቀ…አፈ ንጉሥ ታከለ ወልደ ሐዋርያት…አቶ ፈጠነ…ራስ አበበ…ሙሉጌታ ቡሊ…ለምን እኔ? የሚል ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል። ባልፈው መጣጥፌ ቅጥፈትና ወንጀል ወደ ቤተ መንግሥት…ንጽሕናና መስዋዕትነት ወደ ቀራንዮ እንደሚሄዱ – አድራሳቸው ያ መሆኑን ለማመልከት ሞክሬያለሁ። በእምነታቸው የሚያመነዝሩ፣ አደራ የተሰጣቸውን የሚዘርፉ ቤተ መንግሥቱ ይመቻቸዋል። የየዘመኑን የአገራቸውን ጥሪ ለመስማት የሚችሉት ደግሞ የጽጌረዳ ፍራሽና የወርቅ አልጋ አይደለም የሚጠብቃቸው። “እንዲህ ዓይነቱን” የጊዜ ድምፅ- የእናት አገር ጥሪ የሚሰሙ ሰዎች በምንም ዓይነት ለምን እኔ” አይሉም። ልጆቼ እነ እስክንድር፣ በቀለ፣ አንዱዓለም…ርእዮት ይህን ጥያቄ አያነሡም። መስዋዕት መሆንኮ የታሪክ ዕጣና ዕድል ነው። ኩራት!
  አዎን ምኒልክም፣ ጐበናም፣ በላይም፣ አበበም፣ አብዲሳም..በሌሉበትና የኢትዮጵያን ጥሪና የጊዜ ድምፅ ( The Voice of Time) ለመስማት የቻሉ ጥቂቶች በሚመስሉባት አገር በከፍተኛ ደረጃ ሊሰበክ የሚገባው የመስዋዕትነት ወንጌል (The Gospel of Sacrifice) ነው። The Gospel of Sacrifice የአሜሪካ ጥቁሮች በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ያነሡት የእኩልነት መታገያ ዓርማቸው ነበር። የሥልጣኔ ምሥጢር፣ የባላአገርነት ትርጉም፣ የሰለጠነ ሕዝብ የሕልውና ዋስትና ከዚህ ሰፊ ውቅያኖስ (ከመስዋዕትነት ወንጌል) ውስጥ ለመቅዳት እንችላለን።
 ስለ ልቅሶና አልቃሽ ግለሰቦች ነበር በሰፊው ለማስረዳት ወዲያ ወዲህ ስረግጥ የቆየሁት። ለአገራችን ማልቀሱ፣ ስለተረጋገጠው ሰብእናችን መተከዙ፣ ስለተሸነሸነው አንድነታችን መቆዘሙ አንድ ነገር ነው። አልቃሽና አልቃሽ ሕዝብ ሆነንና ወሬ ስንሰልቅ መኖርም አይገባንም። ወንዶችም- አዎን ሴቶችም ሆኖ መነሳቱ ነው መድኅኒቱ። ጠላቶቻችን እስከታወቁ ድረስ በገቡበት ዱር ለመግባት፣ በቆሙበት ሥፍራ ደርሶ መገኘት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ከቶውንም ከምር አምኜበታለሁ። የእነሱ እጅ የሚተኩስ፣ የእኛ ፈንታ መገደል ብቻ ከሆነ ፍልስፍና ራስዋ ማደሪያ አጣች ለማለት ይቻላል። ስለ መስዋዕትነት ነው የማወሳው። ለመሆኑ መስዋዕትነት መገደል ማለት ነው ያለው ፈላስማ ማነው? ከዚያ የተሻለ ማሰብና ማቀድ እንዴት አንችልም? ለመሆኑስ ሰላማዊ ትግል ማለት “ያውልህ ግደለኝ! ዋጋውን በመንግሥተ ሰማያት አገኘዋለሁ” ማለት ነውን? የዚህ ዓይነቱ ሰው ሥፍራ ገዳም ነው። እኔ የማነሳው ስለ ምድራዊት ኢትዮጵያ ነው።
 መለስ ዜናዊ ከመሞቱ አንድ ዓመት በፊት “መለስ ዜናዊ ከምርጫ ሳጥን ይልቅ የሬሳ ሳጥን መርጦአል” በሚል ርእስ የጻፍሁትን መጣጥፍ አስታውሳለሁ። ሰፊና የተንዛዛው መጣጥፌ እንደ መለስ ያሉትን ግፈኞች አምባገነኖች መታገል እንደ ጽድቅ ሊታይ እንደሚችል ገልጫለሁ። ለዚህም ስለ Just war, Holy war ወዘተ የሰበኩትን ታላላቅ የክርስትና መሪዎች አሳቦች አንስቻለሁ። ዛሬ ራሴን ለመጥቀስ አልወድድም። ብቻ ልደግም የምፈልገው ግፈኞችን ማስወገድ፣ አለዚያም መቃወምና መቋቋም እግዜርን መታዘዝ መሆኑን ላሰምርበት እሻለሁ።
 ግፍና ጭቆና በደም ሥሮቹ ውስጥ “ቁጡ ቀይ ደም ያለውን” ግለሰብ ያሳብዳል። ወላጆቻችሁ በአብዛኛው ይህ ቀይ ደም በሥራሥሮቻቸው ውስጥ ነበራቸው። ይህ ግፍና ጭቆና ደግሞ ዛሬ ባለበት ሁኔታ፣ ሥፍራና ጊዜ (ታይም ኤንድ ስፔስ) ሊሽር- ሊድን -አይችልም። ጠንካራ ዜጐች ካሉን መድኅኒቱ ቅርብና ቀላል ነው። ጠላቶቻችን በእኛ ላይ የደገኑትን መሣሪያ ጭምር አስጥለን ወደነሱ ማዞር በዓለማዊውም ሕግ ወንጀል፣ በመንፈሳዊውም ዓለም ኅጢያት አይደለም።  ከማንም ጋር ለመከራከር እችላለሁ። ቶማስ አኳይነስን፣ አቡነ አትናትዮስን፣ የንጽሕና ማስረጃ የሆነውን ፍራንሲስ ኦፍ አሲሲን፣ የላዮላ ዩኒቨርሲቲ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን መነኰሳትን ምስክርነት አቀርባለሁ። ሒትለርን ለመግደል ስንት ፓስተሮች የየራሳቸው እንቅስቃሴ አድርገዋል? በአመጽ ላይ አመጽ በተካሄደበት ወቅት እንደ ፓስተር ዎልፍጋንግ ያሉ ሰባክያን ያካሄዱአቸውን ትግሎች ያጤኑአል። የእኛንም አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤልን እንደገና እጠቅሳለሁ። ስለዚህ የጊዜን ድምጽና የአገርን ጥሪ የማይሰማና የማይቀበል ትውልድ ርጉም ስለሚባል ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበት የትግል አስተዋጽዖ አለ። ወጣቱ ተባባሪ ፓይለት ምን የመሰለ አኤሮፕላን ይዞ ወደ ስዊትዘርላንድ በመሄዱ አንድ የትግል ግንባር ወይም አስተዋጽዎ አበርክቶአል። አንድ የወያኔ ሹመኛ ቀጣሪዎቹን በአደባባይ ቢያጋልጣቸው (በተወከለበት ሁነኛ መድረክ) አንድ ሌላ ጠንካራ ተጋድሎ ነው። ዋነኞቹ ወሳኝ ገዥዎች በአንድ አካባቢ ሲያድሙ (መቸም ለእድገትና ልማት ተሰበሰቡ አይባልም) በቁጥጥር ሥር ማዋል…ወዘተ ከፍ ያለ የትግል እድገት ይመስለኛል። ማዕከላዊ መንግሥቱን መገላገል በእርግጥ መስዋዕትነትን ይጠይቃል። ለሚፈለገው ውጤትም አስተማማኝ ርምጃ ይመስለኛል።
 እንደልባቸው በመናገር የታወቁ አንድ የድሮ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር በስልክ ከመከላከያ አቻቸው ጋር ሲነጋገሩ በሠራዊቱም በወጣቱም ተስፋ የቆረጡበትን ሁኔታ መፈንጠቃቸውን አስታወሳለሁ። “ስማ ጄኔራል! የአንተም ወታደሮች የደሀ ጐተራ የሚገለብጡ እንጂ መንግሥት መገልበጥ የሚባል ቋንቋ ሰምተው የማያውቁ ናቸው። እነዚህ ምላሰኛ ተማሪዎች ደግሞ የሚያደርጉትን የማያውቁ፣ ያልተረዱትን የሚያነግሱ ናቸው። ትውልዱን በአጭሩ በፋንድያ ላይ የበቀለ እንጉዳይ ልለው እፈልጋለሁ” ይላሉ። አነጋገሩ ጭካኔ የበዛበት ቢመስልም መሠረቱ ያልጠበቀ፣ በብስለት ያልታነፀና፣ ለመስዋዕትነት ያልተዘጋጀ መሆኑን እያጉረመረምንም ቢሆን እንቀበለዋለን። እግረመንገዳችንን ለዚህ አደጋ ተጠያቂ የምንሆንበትም መጠን ማመን አለብን።
 አዎን ሁላችሁም ቆም ብላችሁ እስኪ የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የአመራር፣ የሚሊተሪ ሥዕል እናሰላስል። የአገር አንድነት ፈረሰ ብለን ልቅሶአችንን ሳንጨርስ በየክልሉ ያሉ “በፋንድያ ላይ የበቀሉ እንጉዳዮች” ከቶውንም ገና ምኑ ታየና በማለት በመጨረሻ ትንፋሻቸውን እያጮኹ ናቸው። ከዚህ የባሰ ምን ሊያደርጉን ፈልገዋል? በሥልጣን ላይ ያለው አፍራሽ ኅይል ራሱ የትውልድ ትውልድ ብሔራዊ ወንጀል እየፈጸመ- ሕዝባችንን እያረደ፣ የአገሪቱን ሀብቶች እየዘረፈ፣ የሞራል ድቀት እያስፋፋ- ባሕልና እምነትን እያጎደፈ-ይገኛል።
 ቀደም ሲል የጠቀስሁት ቁጡ ቀይ ደም በውስጣችን መኖሩን መጠራጠር አይገባንም? በዚህ ዕድሜዬ ማሰብ የማይገባኝ (ምናልባት) አሳብ ድቅን ይልብኛል። በአንድ በኩል ኢሕአፓ ትናፍቀኝ ጀምራለች። ቆራጥነት ማለት በራስም በጠላትም ሕይወት ላይ ውሳኔ ለመውሰድ መወሰን ነው። ኢሕአፓ ናፈቀችኝ። የአባቶቻችን አዋራጆች- ልጆቻችንን በጠራራ ፀሐይ የሚረሽኑ፣ አገራችንን በግላጭ የሚሸጡ ወንበዴዎች በየአደባባዩ ሲጐማለሉ ሁላችንም ሊያቃጥለን አይገባም? ኢሕአፓ እንደ ሞተ ዘመድ ናፈቀችኝ። ኢሕአፓ ብትኖር ይኸ ሁሉ ሽፍታ መሪ መንፈሱ አርፎ ከመሸታ ቤት መሸታ ቤት እየዞረ- ሽጉጡን መሬት ለመሬት እየጐተተ- የፈገውን እያሰረና እያስገደለ፣ በእብሪት ይንቀባረርብን ነበርን? ኢሕአፓን እንዳላማኋት ዛሬ ሙት መንፈስዋን መቀደስ ይዣለሁ።
  ቁጥራችንን- ንዴታችንን- በደላችንና የተዋለብንን ሁሉ ሳስብ ለመሆኑ የአዲስ አበባ ሲሦ ሕዝብ አንድ ማለዳ ላይ በእነዚህ ሰዎች ላይ ቢንቀሳቀስ ለወሬ ነጋሪ የሚተርፍ ይኖር ይሆን? ብዬም ራሴን እጠይቃለሁ። በውስጤ ውስጥ ያለው የሕሊና ድምፅ ደግሞ የሚነግረኝ ሌላ ሐቅ አለ። ወደ ሚዲየቫል እንግሊዝ ልውሰዳችሁ። ከሀብታም ቀምቶ ደሀ የሚቀልበው Robin Hood ከአሥር የማይበልጡ Mery men ) ይዞ አይደለም ወይ ለንደንን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገው? እንኪያስ አሥር የቄራ ቦምባርዶች አዲስ አበባን በቁጥጥራቸው ውስጥ ሊያደርጉ አይችሉም? ይኸ ሁሉ ባለሙሉ ገላ ወጣት- ይኸ ሁሉ አንጀቱ የተኮማተረ ጐረምሳ በቡድን ተከፋፍሎ አንዱ ዘርፍ አጥቂ፣ ሌላው ዘርፍ ደጀን ሆኖ አዲስ አበባንና – ባለሥልጣኖችዋን በቁጥጥር ሥር ሊያደርግ- የተወሰኑ ግለሰቦችን መፋረድ አይችልምን? ሞት አይኖርም አይባልም። ጦርነት ታውጆ የለምን? ይህ መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት ማወጁን አልሰማንም የሚል ማነው? ዋናው ነገር ከውሳኔ ላይ ነው። ዋናው ነገር እንዲህ ላለው ጦርነት መዘጋጀትና ለመስዋዕትነት የተቆጣ ወኔ፣ የገነፈለ ቀይ ደም መኖር ነው። ቀደም ሲል ያነሣሁትን የመስዋዕትነት ወንጌልን መቀበል ነው። The Gospel of Sacrifice
  የጀርመንን ፍልስፍናና ሥነ ጽሕፈት ያነበቡ (በጀርመንኛው) ሰዎች Goe the የገቴ ስም ሲጠራ ልዩ ስሜት ይፈጥርባቸዋል። እኔ ገቴን ልጠቅሰው የምወድደው (ፋውስት ክፍል አንድ ..Faust Part One ላይ በተጠቀሰው ፍልስፍናው ነው። የገቴ ፍልስፍና በአጭሩ እንዲህ ይጠቀሳል። “ራስህን ካድ- ራስህን መካድ ይገባሃል- Deny yourself, you must deny yourself) አዎን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የደመደመው ነው- የሚከተለኝ ቢኖር ራሱን ይካድ- የሚከተለኝ ቢኖር ግማደ መስቀሉን ይሸከም! ኢትዮጵያን ያለ ዛሬ ጥሪው ይኸ ነው። የጊዜ ድምፅ!
 ጠላትን ሲሆን ከያዘው መሣሪያ በበለጠ ትጥቅ- አለዚያም በተስተካከለ መሣሪያ- በተሻለ ወኔ ለመግጠም ማመንታት የአገርን ዕድሜና ዕድል ማበላሸት – ማሰናከል ነው። ከፊት ለፊታችሁ ያማረ ሸለቆ የለም። ከፊት ለፊታችሁ ማለፊያ ድልድይ የለም። ከዚያ ማዶ ከሚታየው ተራራ ላይ ወጥተህ ከአምላክህና ከአገርህ ጋር ቃልኪዳን ትገባለህ። ከተራራው ላይ ሆነህ ከአምላክህ ጋር በቅርበት ትነጋገራለህ። ከኢትዮጵያ ጋር በመንፈስ ትነጋገራለህ። ለመሞት ብቻ ሳይሆን ለመግደልም ቃል ትገባለህ። ከአሥርቱ ትእዛዛት ስድስተኛውን መጣስህ ሊሰማህ አይገባም። ከሕጉ ባለቤት ጋር ተነጋግረሃል።
 ወደፊት የመስዋዕትነቱን ወንጌል ቃል አስፋፍተን እናቀርባለን።

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>