(ከአሌክስ አብርሃም)
ዛሬ ማታ ማለትም በ 20 /07/ 2006 ዓ/ም በሰይፉ ፋንታሁን እየተዘጋጀ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በሚተላለፈው ሾው ላይ የተመለከትኩት አሳፋሪ ድርጊት ይህን እንድፅፍ አነሳስቶኛል !
የሰይፉ እንግዶች አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ፣ አርቲስት ግሩም ኤርሚያስና ኮሜዲያን ደረጀ ሃይሌ ነበሩ … (በዚህ አጋጣሚ ሶስቱንም እስከዚህ ጊዜ ድረስ የማከብራቸውና የማደንቃቸው አርቲስቶች መሆናቸውን እወቁልኝ ) እናም ሰይፉ ስለስራቸው ስለግል ሂወታቸው እየጠየቃቸው ውይይቱ ሞቅ ብሏል … (ወደ 33ኛው ደቂቃ አሳልፈው ያዳምጡት)
በመሃል ሰይፉ ቀለል አድርጎ አንድ ጥያቄ ለአርቲስት ግሩም ኤርሚያስ አቀረበ
‹‹ በቀረፃ ላይ ላለ ፊልም የአንድ ‹ድራግ› ተጠቃሚን ወጣት ገፀ – ባህሪ ተላብሰህ ስትጫወት ድራግ ወስደህ ነበር ይባላል ..እውነት ውሸት ?
ሚሊየን ኢትዮያዊያን ወጣቶች ታዳጊወችና ህፃናት የሚያውቁት አርቲስት ግሩም ሚሊየኖች በሚመለከቱት ፕሮግራም ላይ እንዲህ ሲል መለሰ
‹‹እውነት !! ››
‹‹እንዴት ነበር አጋጣሚው ምንስ ተሰማህ›› ሰይፉ ጠየቀ
‹‹ በትወና ላይ ማስመሰል ሳይሆን ሁኖ መስራት የሚባል ነገር አለ… መምህሬ አለማየሁ ሊረዳኝ ይችላል (አለማየሁ በመስማማት ራሱን ነቀነቀ ) እናም በጭስ ተከልየ (?) የሚል ፊልም እየሰራን ነው … ቀረፃው ላይ የወከልኩትን ገፀ ባህሪ ወክየ ሳይሆን ‹ ሁኘ › ለመስራት ሃሽሽ (ድራግ) ወሰድኩ ..በቃ ጉልበቴ ተንቀጠቀጠ ዞረብኝ …..›› ሲል ሰፊ ማብራሪያ ሰጠ …
ይህን ፀያፍ ድርጊት እንደትልቅ የጥበብ ክስተት ማውራቱ ሳያንስ ጭራሽ በሃሽሽ ደንዝዞ መናገር ሁሉ አቅቶት ቀረፃ ላይ ባጋጣሚ የተወሰደውን ምስል በመሃል አስገብተው ያሳዩት ጀመረ … ይህ አሳፋሪ ቪዲዮ ታይቶ ሲያበቃ በአዳራሹ የታደመው ሰው ሞቅ ያለ ጭብጨባ ‹በሃሽሽ ደንዝዞ› ለታየው ‹‹አርቲስት ›› ለገሰ …..ሰይፉን ጨምሮ ! አለማየሁ ታደሰና ደረጀ ሃይሌን ጨምሮ !
1ኛ . በኢትዮጲያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ (ኧረ በብዙ የአለማችን አገራት ጭምር) አደንዛዥ እፆችን መውሰድም ይሁን በማንኛውም መንገድ ማቀባበል ይዞ መገኘት ቁልጭ ብሎ የተቀመጠ ወንጀል እንደሆነ ሰምተናል ( በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ) ይህን ፀያፍ ድርጊት አደባባይ አውጥቶ በትወናም ይሁን በሌላ ተልካሻ ምክንያት በሚሊየን ለሚቆጠሩ ወጣቶች ማሳየት ምናይነት ሃላፊነት አለመሰማትና ስርአት አልበኝነት ነው ?
2ኛ . አንድ ትልቅ እውቅና ያለው አርቲስት በርካታ ኢትዮጲያዊያን ተመልካቾች ባሉት ሾው ላይ በሃሽሽ ደንዝዞ ሲቀባጥር የሚታይበትን ቪዲዮ ማሳየት (ያውም እንደታላቅ ክብር በጭብጨባ ታጅቦ )የብሮድካስት ባለስልጣን መስሪያቤት …የኢቢኤስ ቴሌቪዥን አስተዳዳሪወች እንዲሁም የሾው ባለቤት ሰይፉ ፋንታሁንን የሚያስወቅስ (ጠያቂ ቢኖር በህግም የሚያስጠይቅ) ፀያፍ ተግባር ነው ! ምስሉን ካሳዩ በኋላ ‹‹ድራግ አይጠቅምም ጎጅ ነው ምናምን እያሉ ማውራቱም ቢሆን ከድርጊቱ በላይ ተፅእኖ የሚያሳድር ምክር አይደለም ) እዚች አገር ላይ ለትውልድ የሚገደው ማነው …የሚዲያወቻችን ስርአት አልበኝነትስ ሃይ የሚባለው በምን መንገድ ይሆን ?
3ኛ. በትወና ሰበብ ስክርቢቱ ላይ ድራግ መውሰድ ስለተፃፈ ስሜቱን ለመሞከር እና ‹‹መስሎ ሳይሆን ሁኖ›› ለመስራት ይህን ማድረጉ እንደአንድ የጥበብ መንገድ ከተወሰደ ( መምህሩ አለማየሁ ታደሰም ስላረጋገጠ) ወሲብ ነክ ስክርቢቶች ላይም ወሲብ መፈፀም ሙያዊ ፈቃድ ሁኖ ሊታይ ነው ማለት ነው ?
በዚህ አይነት አገራችን ላይ ከስር እንደአሸን የሚፈላው ፊልም ሰሪ ወጣት ሁሉ ‹‹መስሎ ሳይሆን ሁኖ›› ለመስራት በሚል ሰበብ ‹‹ወደ ፊልም ኢንዳስትሪ›› ሳይሆን ‹‹ወደብልግና ኢንዳስትሪ›› እንዲጎርፍ አንጋፋወቹ መንገድ እየከፈቱለት መሆኑን መታዘብ ይቻላል (አውቀውም ይሁን ሳያውቁ )
በአጠቃላይ ይህን ፀያፍ ድርጊት ለፈፀመው ግለሰብ …ምስሉን እንደደህና ነገር በጭብጨባ አሳጅቦ ላቀረበው የዝግጅቱ ባለቤት እንዲሁም ለህዝብ እንዲደርስ ላደረገው የቴሌቪዥን ጣቢያ ድርጊቱ ከእናተ የማይጠበቅ እጅግ የወረደና በ ሱስ አፋፍ ላይ የቆመውን በርካታ ወጣት ወደሱስ አዘቅት የሚገፋ ድርጊት መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም እላለሁ !
ከፍ ያለ አደራ የተጣለበት የጥበብ ሰው እንኳን በአደባባይ በጓዳውም ቢሆን ትውልድን የሚያንፅ ወደበጎ ነገር የሚመራ ድርጊት ይፈፅም ዘንድ የሙያው ድስፕሊን በራሱ ያስገድደዋል ! መንግስትም ይሁን የሚመለከተው አካል ይህን ጉዳይ ዝም ቢልም በበኩሌ ይህን የአርቲስቱን ድርጊት በፅኑ እቃወመዋለሁ ! አጥፊና ፀያፍ ድርጊት ነው ግሩም ኤርሚያስ አዝናለሁ !!