Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሐረርነት እና ጎንደርነት!

$
0
0

በሰሎሞን ተሰማ ጂ

አዳላህ እንዳልባል እንጂ፣ የዚህ መጣጥፍ ርዕስ “ጎንደርነት እና ሐረርነት”ም ቢባል አያወዛግብም፡፡ ነገር ግን፣ ሐረር ከጎንደር በምስረታዋም ሆነ በቀደምትነቷ የታወቀች ስለሆነ ነው ርዕሳችንን ሐረርነት እና ጎንደርነት ያልነው፡፡ እንደምታውቁት ስለሐረርነት እና ስለጎንደርነት ማውራት ማለት፣ ስለሐረሬዎች ወይም ስለሐረሪዎች ማውራት አይደለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም፣ ስለጎንደርነት ማውራት ማለት፣ ስለጎንደሬዎች ማውራት ማለት አይደለም፡፡ የዛሬዎቹ ሐረሬዎችም ሆኑ የዛሬዎቹ ጎንደሬዎች ከመፈጠራቸው ብዙ መቶ አመታት በፊትም ሐረርነት እና ጎንደርነት ነበሩ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ልናወሳው የፈለግነው ስለሁለቱ ከተሞች ሳይሆን ስለታሪካቸው፣ ስለስነ-ሰብዓቸው፣ ስለሃይማኖታቸው፣ ስለፖለቲካቸው፣ ኤኮኖሚያቸውና ስለባሕላቸው ነው፡፡ በጥቅሉ ይህ፣ ጽሑፍ የሐረር እና የጎንደር (ወይም አዳላችሁ እንዳንባል የጎንደር እና የሐረር) ፖለቲካዊ ፍልስፍናን በደሕና መስኮት ወደውስጣቸው ለማሳየት የሚጥር ይሆናል፡፡ (በበሩ ገብቶ ሐረርነትን እና ጎንደርነትን በቅጡ ማወቅ የሚፈልግ ካለ፣ ጠቀም ያለ ገንዘብ ቆጥቦ/ቋጥሮ ለቀናት ወይም ለወራት ያህል ቢጎበኛቸውና ቢያጠናቸው ይበጃል፡፡) ሐረርነት እና ጎንደርነት ብዙ-ብዙ ምስጢራትን የተሸከሙ ጽንሰ-ሃሳቦች ናቸው፡፡
ይህንን ጽሑፍ ጽሁፍ ስጽፍ በማናነት ያነበብቸውንና ያዳመጥኳቸውን መጽሐፍትና የሬዲዮ ንግግሮች ለአንባቢያን ማውሳት አሻለሁ፡፡ በመጀመሪያ የሚመጣው በ1867 ወይም በ1868 እ.አ.አ. ተጽፏል ተብሎ የሚገመተው የእንግሊዛዊው ደራሲና ገጣሚ አርኖልድ ማቲው ሥራ ነው፤ “Hebraism and Hellenism” ይሰኛል፡፡ ይህ ደራሲ በሁለት ጽንሰ-ሃሳቦች መካከል ያለውን ልዩነት ለመተንተን ያደረገው ቁዘማ ተንተርሶ፣ በ20ኛው ክ/ዘመን የመንትዮች ተቃርኖ (Binary Opposition) የተባለ ኃይለ-ሃሳብ በቋንቋ፣ በስነ-ጽሑፍ፣ በፍልስፍና፣ በሂሳብና በኮምፒውተር ሳይንስ እንዲሁም በሌሎች የጥናት መስኮች ውስጥ ተሰራጭቷል፡፡ ማቲው ጥልቅ ቁዘማ ነበር የደረገው፡፡
harar
ከአርኖልድ ማቲው ለጥቆም በ1964 እ.አ.አ የተጻፈውን የሊዮ ስትራውስ (Leo Strauss) “Athens and Jerusalem” የተሰኘ ጥናታዊ ጽሑፍ ለማንበብ ጥረት አድረጌያለሁ፡፡ የሊዮ ስትራውስ ጽሑፍ፣ በተለይም በፖለቲካዊ ፍልስፍና አተያዮች በኩል ያለኝን ግንዛቤ እንዳሻሽል ጥሩ የአይን መግለጫ ሆኖኛል፡፡ በመጨረሻም፣ በሬዲዮ ንግግሮቹና አስተማሪ ጽሑፎቹ የሚታወቀው፣ የዶክተር ዳኛቸው አሰፋን “አክሱማዊነት እና ላሊበላዊነት” የተሰኘ ገለጻ ደጋግሜ ያዳመጥኩ መሆኔን ለአንባቢያን መግለጽ እወዳለሁ፡፡
የዶ/ር ዳኛቸውንና የአርኖልድ ማቲውን ፈለግ ተከትዬ፣ የጽሑፌን ርዕስ “ሐረርአዊነት እና ጎንደርአዊነት” ልለው አልፈለኩም፡፡ የመጀመሪያው ምክንያቴ፣ በሀገራችን ውስጥ ያለውን የዘርና የመንደርተኝነት/የጎጠኝነት ፖለቲካ የማልደግፍ በመሆኔ ሲሆን፤ ምናልባትም “-አዊነት” የሚለው ታካይ ምዕላድ ሌላ አይነት የፖለቲካ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ስለገመትኩ ነው፡፡ ሁለተኛውም ምክንያቴ ደግሞ፣ የአርኖልድ ማቲውንና የዶ/ር ዳኛቸውን ምዕላድ ከመጠቀም ይልቅ፣ የሊዮ ስትራውስ “Athens and Jerusalem” የሚለውን አካኼድ መከተሉ የሁለቱን አካባቢዎች ታሪክ፣ ባሕል፣ ፖለቲካ፣ ኤኮኖሚ፣ ሃይማኖትና ፍልስፍና ለመግለጽ የተመቸ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ ስለሆነም፣ ርዕሴን “ሐረርአዊነት እና ጎንደርአዊነት” በማለት ፈንታ፣ “ሐረርነት እና ጎንደርነት” ብዬዋለሁ፡፡ አንባቢያንም፣ በዚህ “ትርጉሙ ብቻ” እንድትወስዱልኝ ስል በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ወደዋናው ርዕሰ ጉዳያችን እንመለስ፤ ሐረርና ጎንደር 1101 ኪሎ ሜትር ያህል ይራራቃሉ፡፡ አመሠራረታቸውም ቢሆን በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ሐረር በ1248 ከአረብ ፔኑዜላ በመጡ 405 ሼኰች ተመሰረተች ተብሎ ይታመናል፡፡ በአቅሪያዋ (የዛሬን አያድርገውና) 18 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን ምዕራብ በኩል የሐሮማያ (አለም ማያ) ሀይቅ ነበር፤ ምንም ደሴት አልነበረውም፡፡ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ደርቋል፡፡ ከዚህም ሌላ፣ ሐረር አምስት ሆስፒታሎችና አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አንድ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ፣ አንድ የጤና ሳይንስ ት/ቤት (በተለምዶ Nursing School) አንድ የአውሮፕላን ማረፊያ (ድሬ-ጠያራ ይባላል፤ 12 ኪሎ ሜትር በስተሰሜን በኩል) ይገኝ ነበር፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያው አገልግሎት መስጠት ካቆመ የአንድ አዛውንት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ አንድ የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍ አላት፡፡ ብቸኛው የከተማዋ ሲኒማ ቤት (ሐጂ ቦምባ-እየተባለ ይጠራል፣ በጣሊያን ጊዜ የተሰራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ፣ ሐረር የታወቀው የሦስተኛው ክፍለ ጦር መቀመጫ ነበረች፡፡ የዛሬን አያድርገውና፣ የታወቀው የሐረር ጦር አካዳሚም እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በርካታ የወታደራዊ ክሕሎት ያዳበሩ ወጣት መኮንኖችን አስተምሯል፡፡ ከሁሉም-ከሁሉም፣ የማይረሳኝ የሐረር ጀጎል (በግንብ አጥር የተከለሉት ሰባት ቀበሌዎችና ቤቶቹ ሲሆኑ)፣ ከተማዋ በ1998 ዓ.ም የዓለም ቅርስ ሆና ተመዝግባለች፡፡ ጀጎል ውስጥ የሐረር ገዢዎች (አሚሮችና ሕዝቡ በአንድ ግንብ አጥር ስር በጋራ ኖረዋል፡፡ ሐረር ከአዲስ አበባ 520 ኪሎ ሜትር በስተምስራቅ ትርቃለች፡፡

በተመሳሳይ መልኩም፣ ጎንደር ከአዲስ አበባ 748 ኪሎ ሜትር ያህል ስትርቅ፣ በ1626/7 ዓ.ም ገደማ በአፄ ፋሲል ተመስርታለች ተብሎ ይገመታል፡፡ መስራቿ አፄ ፋሲልም ሆኑ ወታደሮቻቸው፣ እንዲሁም ካህናቱና የእደ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ከዚሁ፣ ከኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ወይም የኢትዮጵያን አየርና እህል፣ ማርና ወተት እየተመገቡ ያደጉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ (እያወራን ያለነው፣ ከተማዋ በምትቆረቆርበት ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ከጎንደር 60 ኪሎ ሜትር በስተደቡብ በኩል የጣና ሐይቅ አለ፤ ከሠላሳ ሰባት (37) በላይ ደሴቶች አሉት፡፡ ልክ እንደ ሐረር ሁሉ፣ አምስት ሆስፒታሎች፣ እንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አንድ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ፣ አንድ የጤና ሳይንስ ት/ቤት፣ አንድ የአውሮፕላን ማረፊያ (አዘዞ አካባቢ ወይም 10 ኪሎ ሜትር በስተደቡብ በኩል) ይገኛል፡፡ አሁንም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ እንደ ሐረር ሁሉ፣ አንድ የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍ አላት፡፡ ብቸኛው የከተማዋ ሲኒማ ቤት በጣሊያን ጊዜ የተሰራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ፣ ጎንደር የምትታወቀው በወታደራዊ ከተማነቷ ነው፡፡ ጎንደርን የጎበኘ ሰው፣ ከሁሉም-ከሁሉም የማይረሳው የጎንደር አብያተ-ነገስታት ግንብ ነው፡፡ በርካታ ነገስታትም በዚህ ቅጥር ግቢ ውስጥ ኖረው አልፈዋል፡፡ ሕዝቡ ግን ከግንቡ አጥር ውጭ ነበር የሰፈረው፤ አሁንም ሰፍሮ ያለው፡፡ ይህም የነገስታት ቅጥር/ግንብ፣ እ.አ.አ በ1979 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡

የሐረርነት ጉዳይ ከእስልምና ጋር በቀጥታ ይያያዛል፡፡ በጀጎል ውስጥ ብቻ እንኳን 44 መስኪዶች ሲኖሩ፣ ከጀጎል ውጭ ደግሞ 38 መስኪዶች ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ መሰኪዶችም የቅዱሳንን መቃብር በውስጣቸው ይዘዋል፡፡ መስኪዶቹ ውስጥ ለመቀበር ቅዱስ መሆን ወይም መሪ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌም ያህል፣ የአው አባዲሪን፣ የአው ዜይንን፣ የአው ዶቢርን፣ የአው ሐኪምን፣ የአው ወሪቃን፣ አው ኡመርንና የሌሎችንም መቃብር ስፍራዎች ብንመለከታቸው መስኪዶችም ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ “አው” ማለት “ቅዱስ” ማለት ነው በአካባቢው ቋንቋ፡፡) ከመሪዎቹም ውስጥ አሚር ኑር ኢብን ሙጃህድ መቃብር መስጂድ ውስጥ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ሐረርነት አስክሬንን በማድረቂያ አማካይነት አድርቆ አያስቀምጥም፡፡ በሐረርነት እና በእስልምናም ሃይማኖት አስከሬን ማድረቅ “ሀራም” ነው፡፡ ሐረርን የሚጎበኝ ሰው፣ ከራስ መኮንን (ደርግ የምስራቅ አርበኞች) ሆስፒታል ብሎት ነበር፣ አጠገብ ያለውን የአሚር ኑር መቃብር ቢጎበኝ፣ እውነትነቱን ያረጋግጣል፡፡ ከዚህም ሌላ፣ በሐረር ከረመዳን ጾም አንድ ሳምንት በኋላ የሚከበረው የሸዋል ኢድ በዓል፣ ለሐረር ወጣቶች የመተጫጫና የፍቅር ቄጠማ የመቁረጫ ጊዜ ነው፡፡ ጎረምሶቹና ልጃገረዶቹ፣ ደማቅና ብርቅርቅ ልብሶችን ለብሰው ለክብረ በዓሉ ፈላና በር አጠገብ ድንኳን ተደኩኖ ለስድስት ቀናት ያህል ይታደማሉ፡፡ ያልቀናውም ለከርሞ እድሉን ይሞክራል፡፡
Gonder
በአንጻሩ፣ ጎንደርነት በእጅጉ ከክርስትና ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ብቻ እንኳን 44 አብያተ-ክርስቲያናት አሉ፡፡ አብዛኞቹ አብያተ-ክርስቲያነትም በዙሪያቸው የመቃብር ስፍራዎች አሏቸው፡፡ የተለየ ቅድስና ያለው ሰው ካልሆነ፣ ወይም ከነገስታቱ ወገን ካልሆነ በስተቀር ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የሚቀበር ሰው የለም፡፡ ካለም አሰክሬኑ/አጽሙ በማድረቂያ እንዲደርቅ ተደርጎ ይቀመጣል፡፡ አስከሬንን ገንዞና አሽሞንሙኖ መሸኘት የጎንደርነት ክብር ነው፡፡ ከዚህም ሌላ፣ በጎንደር ለጥምቀት በዓል አምሮና ተውቦ ለመተጫጨት መውጣት አግባብ ነው፡፡ ባሕል ነው፤ ወግም ነው፡፡ ጎረምሶቹና ልጃገረዶቹ፣ አዲስና የክት ልብሳቸውን ለብሰው ለክብረ በዓሉ ፋሲል መዋኛ እየተባለ በሚጠራው፣ የጥምቀተ-ባሕር ተገኝተው ያከብሩታል፡፡ የቀናው ይተጫጫል፡፡ ያልቀናውም ለከርሞ እድሉን ይሞክራል፡፡

ስለባሕላዊ ጉዳዮች እናንሳ፡፡ ሐረርነት የሚመነጨው ፊት ለፊት ከመናገር ነው፡፡ ቂም መያዝም ሆነ ማኩረፍ የተለመደ አይደለም፡፡ በንግግሮቻቸው ጣልቃ “አቦ ተወኝ! አቦ ተይኝ!” ይላሉ፡፡ ከተገረሙ ደግሞ፣ “ወለበል!” ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ ያቺ የሚታወቁባትም ስድባቸው አለች፤ “እናትክ……!” ይላሉ፡፡ “አሚር” የሚለውን ስም ሐረርነት ለወንድ ልጁ በብዛት ይሰጣል፡፡ “(ገዢ! መስፍን!” እንደማለት ነው፡፡) ሐረርነት እነዚህ መሰል መገለጫዎች አሉት፡፡ በአንጻሩ ጎንደርነት ደግሞ፣ በፈሊጥ መናገርን ይወዳል፡፡ በቀጥታ ልጥፍ አድርጎ አይናገርም፡፡ በገደምዳሜ ወይም በምሳሌና በተረት መናገር ጨዋነት ነው፡፡ በጎንደርነት ውስጥ “ኧረ ባባጃሌው!” ማለት መገረም ነው፡፡ አልፎ አልፎም “ኦረ! ኦረ!” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የሚታወቁባት ስድብ የለቻቸውም፡፡ ፋሲል፣ ግዛቸው እና ቴዎድሮስ የጎንደርነት ተወዳጅ ስሞች ናቸው፡፡

ሐረርነት ውስጥ ኦሮምኛ ተናጋሪነት፣ የሐረሪ ቋንቋ ተናጋሪነት፣ የሶማሌኛ ተናጋሪነት፣ አርጎቢኛ ተናጋሪነት፣ አማርኛ ተናጋሪነት፣ ጉራጌኛ ተናጋሪነት፣ አረቢኛ ተናጋሪነት አሉ፡፡ የወደቀን ማንሳት፣ የሞተንም መቅበር የሐረርነት መለያ ባሕሪ ነው፡፡ ድንበር አሳብሮ ነግዶና ሸቅሎ ወደሀገር መግባት በሐረርነት ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ በሐረርነት ውስጥ መሸፈት ወይም “ጥራኝ ዱሩ፣ ጥራኝ ደኑ” እየተባለ አይዜምም፡፡ አይፎከርምም፡፡ ጠዋት ተጣልቶ፣ ከሰዓት አብሮ “በርጫ” ላይ መጫወት የተለመደም ነው፡፡ ሽፍታ ወይም ወንበዴ ወይም ደግሞ ምቀኛ ፈጽሞ አይፈራም ነበር፡፡ እንኳን ሰውንና ጅቡንም “አባድር ጦም አያሳድረውም” ነበር፡፡ “አባድር! አባድር! ጦም አታሳድር!” ሲሉት የሚሰማ ቅዱስ ነበር-ሐረርነት ውስጥ!” (“ነበር!” ያልኩት ሆን ብዬ ነው፤ ዛሬ እነዚህ ሁሉ እሴቶች ላይኖሩ እንደሚችሉ ስለምገምት ነው፡፡ ያው እንግዲህ የግምት ጉዳይ ነው፡፡)

ጎንደርነትም ውስጥ አማርኛ ተናጋሪነት፣ ኦሮሚኛ ተናጋሪነት፣ ትግርኛ ተናጋሪነት፣ ግዕዝንም ተናጋሪነት አለ፡፡ ቅማንትኛ ተናጋሪነት፣ ጭልግኛ ተናጋሪነት፣ አገውኛና ወይጦኛ ተናጋሪነቶች ነበሩ፡፡ ዛሬ፣ እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሰዎች በብዛት ጎንደር ውስጥ የሉም፡፡ በጎንደርነት ውስጥ ለመረዳዳትና ለመተባበር አጥቢያና እድር መቋጠር ተዘውትሮ ይስተዋላል፡፡ የከፋው እና የከረፋው፣ “ኧረ ጥራኝ ዱሩ፣ ኧረ ጥራኝ ደኑ፤ ላንተም ይሻልኃል ብቻ ከማደሩ!” ብሎ ዱር ይገባል፡፡ ከቻለም፣ እንደመይሳው ካሳ፣ ሃምሳ ሰው ይዞ ወደ ቋራ ወይም ዘመዶቹ ዘንድ ይሸፍታል፡፡ አርባ አራቱ ታቦት ላጣና ለነጣ ነዳይ የእለት እንጀራውን አይነፍጉትም፡፡ የቆሎ ተማሪና የዜማ ተማሪ፣ ጎንደር መጥቶ፣ የመጣበትንም ትምሕርት አጠናቆ እስኪሔድ ድረስ ረሃብ አይለመጥጠውም፡፡

በሐረርነት እና በጎንደርነት ውስጥ ያሉት ትምህርቶች ከሃይማኖት ጋር የተጋቡ ነበሩ፡፡ ሐረርነት “ጌይ መድረሳ” ውስጥ የአረቢኛ ፊደላትን አስቆጥሮ ቁራን ሲያስቀራ፤ ጎንደርነት ውስጥ ያለው የሃይማኖት ትምህርት በበኩሉ፣ ከአቡጊዳ ጀምሮ መልዕክተንና ዳዊትን አስጠንቶ ወደ ዜማና ቅኔ ቤት ያስገባል፡፡ ሁለቱም ቢሆኑ፣ የሊቃውንትን ቋንቋ ከተራው ሕዝብ ቋንቋ ለይተው ይጠቀማሉ፡፡ ተራው ሕዝብ ወደ ሕዝባዊው ኪነጥበብና የምርት ስራ ተግባር ላይ ሲሰማራ፤ ልሒቃኑ ግን በቤተ-መንግስትና በቤተ-ሃይማኖት ተግባራት ላይ እንዲተጉ ተደርገው በሃይማኖት ትምህርት ቤቶቹ አማካኝነት ይዘጋጃሉ፡፡

በጎንደርነት ውስጥ ከሕፃንነት ጊዜ ጀምሮ የሚደረግ የወታደራዊ ስልትና ታክቲክ ልምምድ/ጨዋታ አለ፤ አካንዱራ ይባላል፡፡ ሕጻናቱ ወንዝ ዳር ሔደው በቡድን ተመራርጠው የለየለት የዱላ ምክቶሽና ድብድብ ያካሂዳሉ፡፡ ፈሪነትና ቦቅቧቃነት ክብረ-ቢስ ያደርጋል፡፡ ወንዝን በዋና ማቋረጥም ሆነ፣ ከፈረስኛና ደራሽ ወንዝ ጋር መገዳደር የተወደደ ጎንደርነት ነው፡፡ “የትም ፍጪው፣ ስልጣኑን አምጭው!” የሚል ተረት ከተተረተ፣ ያ ተረት ያለ ጥርጥር ለጎንደርነት የተተረተ ነው፡፡ በአንጻሩ፣ በያመቱ ከሚመጣውና ፈረስ መጋላ ላይ ከሚከናወነው የወንዶች ልጆች ቅል ሰበራ በዓል ውጭ ወታደራዊ ልምምድ የማድረጊያ ጨዋታ በሐረርነት ውስጥ እምባዛም አይስተዋልም፡፡ በሐረርነት ውስጥ መፍራት “የእናቱ ልጅ!” ያሰኛል፡፡ ሐረርነት የገንዘብና የወርቅ ባለቤትነት ስለሆነ እረኝነትም ሆነ እርሻ ማረስ ለዋቶዎች የተተወ ነው፡፡ “የትም ፍጪው፣ ገንዘቡን አምጭው!” የሚለው ተረት ካለ፣ የተተረተው እዚህ ነው፡፡ (ክፍል ሁለት ይቀጥላል፡፡ የሳምንት ሰዎች ይበለን!)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>