Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ከሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ለሚዲያ ማህበረሰቡ የተላለፈ ጥሪ

$
0
0
     ቀን 18/08/ 2006 ዓ.ም
ethiopia-blue-party-300x164ውድ የሚዲያ ማህበረሰብ አባላት፡- ባለፉት 23 ዓመታት ህወሓት/ኢህአዴግ በህገ መንግስቱ የሚዲያ ነጻነት እንደሚፈቀድ ቢደነግግም በተግባር ግን የራሱን ፕሮፖጋንዳ ከሚነዛባቸው ሚዲያዎች ውጭ ሌሎቹን ሲዘጋና ሲያሸማቅቅ ኖሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ህዝባችን ከገዥው ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ ውጭ አማራጭ መረጃ ማግኘት አልቻለም፡፡ ጋዜጠኞች እየታሰሩ፣ እየተሰደዱ፣ ሚዲያዎች እየተዘጉም ቢሆን የተቻላችሁን ያህል ለህዝብ መረጃ ለማድረስ የሚዲያው ማህበረሰብ አባላት ለምታደርጉት ሁሉ ከፍ ያለ ክብር አለን፡፡ የታፈነውን የህዝብ ድምጽ ለማሰማት የምታደርጉትን ጥረትም እናበረታታለን፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን በገዥው ፓርቲ አፋኝነት ምክንያት ህዝባችን የሚገባውን መረጃ እያገኘ አይደለም፡፡ እናንተም በሰበብ አስባቡ ጫና እየደረሰባችሁ እንደሆነ ፓርቲያችን ይገነዘባል፡፡
ገዥው ፓርቲ ላይ የሰላ ትችት የሚያደርሱ ጋዜጠኞች ‹‹አሸባሪ›› ተብለው ታስረዋል፡፡ ጋዜጦችና መጽሄቶች በስርዓቱ ተዘግተዋል፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ድብደባ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ደርሶባቸዋል፡፡ እየደረሰባቸውም ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በሚያደርስባቸው ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ጫና ከገበያ ወጥተዋል፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ለህዝባችን አማራጭ መረጃ የሚያደርሱ ሚዲያዎችና የሚዲያው ማህበረሰብ መብቶቻቸውን ተነጥቀው አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡
አማራጭ መረጃ ለዴሞክራሲና ለልማት ቀዳሚውን ሚና እንደሚጫወት የሚያምነው ፓርቲያችን ይህን የመብት ረገጣና አፈና ሲቃወምና ሲታገል ቆይቷል፡፡ አሁንም በጠነከረ መልኩ ይቃወማል፡፡
ፓርቲያችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽን ጨምሮ የተነጠቁትን መብቶቻችን ለማስመለስ በመጣሩ አመራሮቹና አባላቱ በህገ ወጥ መንገደ እስር ቤት በሚገኙበት ተመሳሳይ ወቅት የዞን ዘጠኝ ወጣቶች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ከመቸውም ጊዜ በላይ ጭቆናው እንደመረረ እና ሁሉን ማህበረሰብ ያቀፈ ትግል እንደሚያስፈልግ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ የመረረ ጭቆና ህዝባችንን ነጻ ማውጣት የምንችለው እኛ ህዝቡን ማደራጀትና ማንቀሳቀስ የሚዲያ ማህበረሰቡም መደረጃውን ለህዝባችን ማድረስ ሲችል ብቻ ነው፡፡
ፓርቲያችን ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ጨምሮ ገዥው ፓርቲ ከኢትዮጵያውያን የነጠቃቸውን መብቶች ለማስመለስ ተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል፡፡ የሚዲያው ማህበረሰብ ይህን የተቃውሞ ሰልፍ ሂደት ለህዝብ በማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የታመነ ነው፡፡ በመሆኑም መብቶቻችን በህዝብ ትግል ይመለሱ ዘንድ እናንተም የተለመደው የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
መረጃ ኃይል ነውና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ የህትመትም ሆነ የብሮድካስት ውጤቶች የተነጠቁትን መብቶቻችን፣ የሰላማዊ ሰልፉን ሂደት፣ በሂደቱ በፓርቲያችንና በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን በደል እና ሰላማዊ ሰልፉን ለህዝብ በማድረስ ግዴታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡ በተለይ ሌሎች ሚደያዎች በታፈኑበት በአንጻራዊነት የህዝብ ድምጽ በመሆን ላይ በሚገኘው ፌስ ቡክ በኩል መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ቀላል የማይባል ጫና መፍጠር የሚቻል በመሆኑ አጋጣሚውን በመጠቀም መብታችን ለማስመለስ እንድንታገልና በሰልፉም እንድንገኝ አደራችን እናስተላልፋለን፡፡
ኑ ራሳችን ነጻ በማውጣት የአገራችን እጣ ፈንታ እንወስን!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>