Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የክርስቲያንና የሙስሊም ፍቅር በገለምሶ (አፈንዲ ሙተቂ)

$
0
0

ጸሓፊ፡-አፈንዲ ሙተቂ
——
gelemsoከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለገለምሶው መምሬ ሙላቱ የምትተርክ አንዲት ጽሑፍ ለጥፌ ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ግን ያቺ ጽሁፍ መሀል መንገድ ላይ ተቆርጣ የቀረች ሆና እየታየችኝ ነው
፡፡ ስለዚህ ለናንተም፤ ለወገንም፣ ለታሪክ ጸሓፊያንም እንዲጠቅም ይህችኛዋን ሐተታ እጨምርበት ዘንድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
——
በ1981 የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ይመስለኛል፡፡ ከትምህርት ቤት መልስ የጨዋታ ጓዶቼን ፍለጋ “ኒብራ” ከተሰኘው የገለምሶ ከተማ ዋነኛ ጎዳና ወረድኩ፡፡ ጓዶቼን ብዙም ርቀት ሳልሄድ ከትልቁ የጋሽ መሐመድ በከር መደብር በረንዳ ላይ አገኘኋቸው፡፡ እዚያም የኳስ ጨዋታ ሰዓታችን እስኪደርስ ድረስ በትረባና በፉገራ መናቆር ጀመርንና አንዱ ሌላውን ለማብሸቅ ይሞካክር ገባ (በጊዜው ትረባ፣ ፉገራና ለከፋ ጊዜያችንን የሚገፋልን ትልቅ መዝናኛችን ነበር)፡፡ እኛ የነበርንበትን በረንዳ በስተግራ በኩል ተጎራብቶ ወደ ታላቁ የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድና “ሐድራ” ወደሚባለው እስላማዊ ማዕከል (መስጊዱ የሐድራ አንድ ክፍል ነው) የሚያስወጣ መንገድ አለ፡፡ መንገዱ በወቅቱ በጎርፍ ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር ወደ አስር የሚደርሱ የቀን ሰራተኞች ድንጋይ እየቀጠቀጡ የተቦረቦረውን የመንገዱን የመሀለኛውን ክፍል ይሞሉትና በድንጋዩ ላይ አሸዋ እየመለሱ ይደመድሙት ነበር፡፡

ይህ የምላችሁ መንገድ በጎርፍ የተጠቃው በዚያን ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ዘወትር ክረምቱን ጠብቆ ከካምቦ ተራራ በሚወርደው ሀይለኛ ጎርፍ እየተደረመሰ አሳሩን ያያል፡፡ የከተማው ማዘጋጃ ቤት በመንገዱ ዳርና ዳር የፍሳሽ መውረጃ ቢሰራለትም ጎርፉ በጣም ከባድ በመሆኑ የተሰራለትን መውረጃ በመተው ወደ መሀል መንገድ ዘው ብሎ እየገባ መንገዱን ማበላሻሸቱ የየዓመቱ ትዕይንት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ መኪና ይቅርና ሰዎችና የጋማ ከብቶችም በዚያ ዳገታማ መንገድ ሲወጡና ሲወርዱ መከራቸውን ነው የሚያዩት፡፡

ክረምቱ ካለፈ በኋላ መንገዱ ይጠገናል፡፡ ጥገናው የሚከናወነው በአብዛኛው በነጋዴ ግለሰቦች እንጂ በማዘጋጃ ቤቱ አይደለም፡፡ ታዲያ ከላይ በጠቀስኩትና ወሩንና ቀኑን በዘነጋሁት የ1981 አንደኛው ዕለት መንገዱን የሚያስጠግነው ግለሰብ ከወትሮው የተለየ ሆነብኝና በደንብ አየሁት፡፡

ሰውየው ቄስ ነው፡፡ መንገዱ ደግሞ ወደ መስጊድ የሚያስወጣው ትልቁ መንገድ፡፡ ቄሱ ወደ መስጊድ የሚያስወጣውን ትልቁን መንገድ ያስጠግናል!! አጃዒብ! በልጅነት አዕምሮዬ ተገረምኩ፡፡ በጣም ተደመምኩ፡፡ እናም በአቅራቢያችን የነበሩትን ጋሽ መሐመድ በከርን ስለሰውየውና ስለመንገድ ጥገናው ጠየቅኳቸው፡፡

“ዛሬ መንገዱን የሚያስጠግነው ቄስ ነው እንዴ?”
“አይ ቄሱ ሳይሆን ቤተክርስቲያን ነው”
“የቱ ቤተክርስቲያን?”
“መድኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን ነዋ! በገለምሶ ስንት ቤተክርስቲያን ነው ያለው?”
“ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? የመስጊድን መንገድ ነው እንዴ ቤተክርስቲያን የሚያስጠግነው?”
“እንዴት ሊሆን አይችልም? እነርሱስ ቢሆኑ የኛ ሰዎች አይደሉም እንዴ? እኛስ ቤተ ክርስቲያናቸው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ቢጠቃ ዝም ብለን እናያለን እንዴ?”

ጋሽ መሐመድ የነገረኝ ነገር እውነት መሆኑን በደንብ ያረጋገጥኩት በአስር ሰዓት ገደማ ቄሱ ለሰራተኞቹ ክፍያ በፈጸሙበት ወቅት ነው፡፡ በነጋታውም እኒያ ቄስ ሰራተኞችን አሰማርተው መንገዱን ሲያስጠግኑ ነበር የዋሉት (እኚያ ቄስ የአካባቢያችን ተወላጅ አልነበሩም፤ ለዚህም ነው ስማቸውን ያልያዝኩት፡፡ ሆኖም ቀጠን ብሎ ዘለግ ያለው ሰውነታቸው፣ ጠይም መልካቸውና ሰልካካ አፍንጫቸው እስከ አሁን ድረስ ይታወሱኛል፤ ብዙ ጊዜም ሰማያዊ ቀለም ያለው ቆብ ነው በራሳቸው ላይ የሚያደርጉት)፡፡

ልብ ያለው ይበል! እንዲህ አይነት ታሪክ በገለምሶ ተፈጽሟል፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ወደ ሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ የሚያስወጣውን መንገድ በራሷ ገንዘብ አስጠግናለች፡፡ በገለምሶ የክርስቲያንና ሙስሊሙ ፍቅር እስከዚህ ድረስ ነበር፡፡ ዛሬ በአካል እዚያ ባልኖርም ይህ የጥንት ፍቅራችን አሁንም ድረስ እንዳልቀዘቀዘ ቤተሰቦቼ ያወጉኛል፡፡
***** ***** *****
“የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድስ ለክርስቲያኖችና ለቤተክርስቲያኒቷ ምን አድርጎ ያውቃል?” ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም መቼስ! እንዲያ ከሆነ የሚከተለውን ታሪክ ላጋራችሁ፡፡

የሼኽ ዑመር አሊዬ መስጊድ “ሐድራ” የሚባለው እስላማዊ ማዕከል አንዱ ክፍል ነው- ከላይ እንደጠቀስኩት፡፡ ይህ ሐድራ የሚባለው ማዕከል ከትልቁ መስጊድ ሌላ የቁርአን መማሪያ (ቁርአን ጌይ)፣ የዒልሚ መማሪያ (ቤይተል ዒልሚ)፣ የሴቶች መማሪያና መስገጃ፣ የዚክሪና አውራድ ማድረጊያ፣ የአዛውንቶችና የሽማግሌዎች መኖሪያና ሌሎች በርካታ ቤቶች አሉት፡፡ እንዲሁም “ቤይቱል ሐድራ” የሚባለውና የሁሉም እንግዶች ማረፊያ የሆነው ቤት (በስፋቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ልደት አዳራሽ የሚያክል) በዚሁ ሐድራ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ እነዚህ ቤቶች ሁሉ ከዓመት እስከ ዓመት ተመሳሳይ አገልግሎት ነው የሚሰጡት፡፡ በመውሊድ ጊዜ ግን አገልግሎታቸው ይቋረጥና በበዓሉ ለመታደም የሚመጡትን እንግዶች ያስተናግዳሉ፡፡ በየቤቶቹ ውስጥ ሰለዋትና መንዙማ ይደረጋል፡፡

በገለምሶ የሚከበረው መውሊድ ሞቅ ደመቅ ያለ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶች ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለሀገራት ይመጣሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ከጎረቤት ሀገራት ጭምር (ሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና የመን) በርካታ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን እንግዶች ለማስተናገድ በትንሹ አስራ አምስት በሬዎችና ሶስት ግመሎች ይታረዳሉ፡፡ ግመሎችና በሬዎቹን የሚገዙት ግን የሐድራው ሰዎች አይደሉም፡፡ ድሮ በሼኽ ዑመር አሊዬ እጅ የተማሩ ሼኮችና ሌሎች የሼኽ ዑመር ወዳጆች ናቸው ከብቶቹን የሚያመጡት፡፡

ታዲያ የሐድራው ሀላፊዎችና የመስተንግዶ መሪዎች ወደነርሱ የሚመጡትን ከብቶች በሙሉ አያርዷቸውም፡፡ በቅድሚያ አንድ ወይም ሁለት በሬ ለሴቶች ይሰጥና የከተማው ሴቶች ከልዩ ልዩ ክፍለ ሀገራት የሚመጡ ወይዛዝርትን እንዲያስተናግዱበት ይደረጋል (በሐድራ ውስጥ ሴትና ወንድ መቀላቀል ክልክል ነው፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ምግባቸውን ለየራሳቸው ነው የሚያዘጋጁት፤ ደግሞም የሁለቱም ጾታ ሰዎች ከተፈቀደላቸው ክልል ውጪ መውጣት የለባቸውም)፡፡

በማስከተልም አንድ በሬ ለስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂዎች ይሰጣል፡፡ እንዲህ የሚደረግበትን ምክንያት በትክክል ባላውቅም በዘመኑ በነበረው ልማድ የተነሳ የበሽታው ተጠቂዎች መሸማቀቅ ሳይደርስባቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተናግዱ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይመስለኛል፡፡ በሬዎቹ ለሴቶችና ለስጋ ደዌ ህሙማኑ የሚላኩት ግን ለግብዣና ለፌሽታ ብቻ አይደለም፡፡ በመስተንግዶው የሚታደሙት ሰዎች ሰለዋት ስለሚያደርጉና የነቢዩን ገድል በመንዙማ ስለሚያወድሱ ነው፡፡ እንዲያ የማያደርግ ጀመዓ ለመውሊድ ከመጣው በሬ አንዳች ድርሻ የለውም፡፡

ነገር ግን ይህ መመሪያ የማይመለከተው አንድ ክፍል አለ፡፡ የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን! በዓሉን የማታከብር ሆኖም ከመውሊድ በሬዎች የራሷ ድርሻ የነበራት ብቸኛ አካል እርሷ ነበረች፡፡ ለዚያውም ለርሷ የሚደርሳት አንድ በሬ ብቻ አይምሰላችሁ! ሁለት በሬዎችን ነው በየዓመቱ የምታገኘው፡፡

የዚህ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ዕድሜዬ ከፍ ካለ በኋላ ግን ምክንያቱን የሐድራው መሪ የሆኑትን ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅን ጠይቄ ከአንደበታቸው ተረዳሁ (ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ የሐድራው መስራች የነበሩት የሼኽ ዑመር አሊዬ ልጅ ናቸው- አሁን ዕድሜአቸው ከዘጠናው ተሻግሮ ወደ መቶ ዓመት እየተጠጋ ነው)፡፡

ሼኽ ሙሐመድ ሲራጅ ሁለት በሬዎች በየዓመቱ ለቤተክርስቲያን የሚሰጥበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ነበር ያስረዱኝ፡፡

“እነዚህ ክርስቲያኖች ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እንደኛው የአዳም ልጆች ናቸው፡፡ በሀይማኖት ብንለያይም የአንድ ሀገር ሰዎች ነን፡፡ ከዚያም አልፎ የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ነን፡፡ በሬዎቹ ወደኛ የሚመጡት በዓላችንን በደስታ ለማክበር እንድንችል ነው፡፡ እኛ በሬዎቹን አርደን በዓላችንን በደስታ ስናከብር ክርስቲያን ወገኖቻችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ እስልምናችን ጎረቤቶቻችንንም ማስደሰት እንዳለብን ያዘናል፡፡ ስለዚህም ነው በሬዎቹን ወደ ቤተክርስቲያን የምንልከው”፡፡
***** ***** *****
እንዲህ ዓይነቱን ውብ ባህል ምንድነው የምትሉት? “መቻቻል” ነው የሚባለው ወይስ ሌላ ስም አለው? እኔ ግን “መቻቻል” አልለውም፡፡ ይህ በተመን የማይመነዘር ፍቅር ነው እንጂ “መቻቻል” የሚለው ዘመን ወለድ ታፔላ የሚለጠፍለት አይሆንም፡፡ “መቻቻል” ሲባል አንዱ ወገን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሌላውን የሚያስከፋ ድርጊት በሚፈጽምበት ጊዜ ሌላኛው ወገን በትዕግስት ችሎ ማለፍ ይገባዋል የሚል እድምታ ያለው ይመስለኛል፡፡ በኔ ከተማ ግን ፍቅር ሰባኪ የሆኑት ሼኮች እና ቄሶች ክፋት ሊፈጸም የሚችልባቸውን ሽንቁሮች ሁሉ ቀድመው የደፈኗቸው በመሆኑ “መቻቻል” የሚባለው አነጋገር እዚያ ዘንድ ተራ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ በዚያች እትብቴ በተቀበረባት መሬት ያየሁትና የሰማሁት “ፍቅር” ነው እንጂ “መቻቻል” አልነበረም፡፡

በኔዋ የገለምሶ ከተማ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ነበረን፡፡ በሌላው ኢትዮጵያስ ቢሆን? ዲግሪው (መጠኑ) ይለያይ ይሆናል እንጂ ተመሳሳይ ታሪኮች ሞልተዋል፡፡ እንዲህ በህብረት የኖረውንና ፍቅርን የተቋደሰውን ህዝብ የፖለቲከኞች ወሬ ሆድና ጀርባ ሊያደርገው ከቶ አይቻለውም፡፡ ፖለቲከኞች ይህንን በሌሎች ሀገራት በስለት እንኳ ተፈልጎ የማይገኝ ውብ ባህላችንን በዓለም ዙሪያ ቢያስተዋውቁልን ነው የሚያምርባቸው፡፡

እኛ አንድ ነን፡፡ ወንድማማቾች ነን፡፡ ፍቅር ነን፡፡ ክብር ነን፡፡ ህብር ነን፡፡ ሰሞነኛ ወሬ አያለያየንም፡፡
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 21/2005


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>