ከአዲስ አበባ የደረሰን ጽሁፍ
እስካሁንም እንቆቅልሽ የሆነብኝ ነገር ቢኖር በምዕራቡ ዓለም የቁዩና የእነዚህን አገራት ነጻነት ያዩ፣ ከነጻነቱም የተቋደሱ፣ ስለ አገራችንም ሆነ ስለ ዓለም ፖለቲካ መረጃ የማግኘት እድል ያላቸው፣ ሆድ አደር ሳይሆኑ በራሳቸው የገንዘብ አቅም መኖር የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ስለምን በጭቁን ኢትዮጵያውያን መከራ ይቀልዳሉ? ስለምንስ ለአምባገነኖች መሳሪያ ይሆናሉ? ዲያስፖራ ደግሞም በጋዜጠኝት፣ አሊያም በምሁርነት በውጩ ዓለም አገልግሎ አሊያም አይቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አፋኝ ስርዓት በግልጽ ባይቃወም እንኳ በምን ህሌናው አብሮ ይጨቁናል? ያስጨቁናልስ? የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ይህን ጥያቄ እንድጠይቅ ከሚገፋፋኝ አንዱ የሚሚ ስብሃቱ ጉዳይ ነው፡፡ ሴትዮዋ ከአሜሪካን አገር ከተመለሰች ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች፣ ስርዓቱን በሰላ ብዕራቸው በሚተቹ ጋዜጠኞችና አጠቃላይ ህዝብ ላይ ከመቀለድም አልፋ አስተኳሽ ሆኖ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ከሳምንታት በፊት የትኛውም አእምሮ ያለው ሰው ሊያምነው በማይችል መልኩ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ፓስፖርታቸው የተቀደደው አፍጋኒስታን ሄደው ስለተመለሱ ነው ብላለች፡፡
በቅርቡ ደግሞ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችና ሶስት ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ‹‹አገሪቱን ሊያበጣብጡ፣ በህዝብ ላይ ችግር ሊፈጥሩ…….›› የሚሉ ክሶችን በመለጠፍ የመያዛቸውን አስፈላጊነት ልታስረዳ ስትሞክር ተሰምታለች፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም የአንድነትና ሰማያዊ ወጣቶች (የየልሳኖቹን ጋዜጠኞች ማለቷ ሳይሆን አይቀርም)፣ አዲሱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ…..ብቻ ለስርዓቱ ያላጎበደዱትን ሁሉ በህገወጥነት ፈርጃለች፡፡
አቤ ‹‹ባንኮኒ›› ብሎ የሚገባውን ስም ያወጣለት ‹‹ክብ ጠረጴዛው›› ላይ የሚነሱት ሀሳቦች በትዕዛዝ የሚሰሩ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ግን እንደ ሚዲያ የአየር ሰዓት ተወስዶ፣ እንደጋዜጠኛ ‹‹ተዘገበ፣ ተጠየቀ፣ ለህዝብ ተቆመ…..›› ተብሎ ቢዋሽ፣ አድሎዊነት ቢኖር ስልታዊ በመሆነ መልኩ ቢሆን ከማስተዛዘብ ውጭ ባላለፈ ነበር፡፡ የእነ ሚሚው ግን አቅሉን የልሳተ ሰው እንኳን ሊያቀርበው የማይችለው ነው፡፡ አሁን እንዴት አንድ ፖለቲከኛ ለአፍጋናዊያን ፖለቲከኞች እንኳ ለማትመቸው አፍጋኒስታን ሊሄድ ይችላል?
በምን ስሌት፣ እንዴትን (ከእሷም ታንሶ!) የአገርን ሉዓላዊነት አሳልፈው ሰጥተው ዞን ዘጠኞች፣ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ፣ ሰማያዊ፣ አንድነት ውስጥ ያሉ ወጣቶች ግብጽና ኤርትራ ሄደው ‹‹ተልዕኮ›› ይዘው ይመለሳሉ?
ይህን ሁሉ ሳየው ሴትዮዋ ጤነኛ አትመስለኝም? ሰው እያመመውም ይሰራል፡፡ አሊያም አርፎ ይቀመጣል፡፡ እሷ ግን የሌለ፣ ለመጋገር እንኳ የማያመች ፕሮፖጋንዳ እየነዛች ኢትዮጵያውያን ላይ ትቀልዳለች፡፡ ‹‹ጋዜጠኞች ነን፣ የጋዜጠኛ ማህበራት መሪዎች ነን›› ከሚሉት መሰሎቿ ጋር ሆና ታስተኩሳለች፡፡ እነዚህ ሰዎች ጤነኞች አይደሉም፡፡ ደግሞም እንደ በቀላሉ ህመምተኞች ናቸው የሚባሉም አይመስሉኝም፡፡ እናም ለዚህ መሳሪያነታቸው ውጫዊ ምክንያት መኖር አለበት፡፡ እኔ የምጠረጥረው አቤ ከሚለው በላይ ነው፡፡ ሰውኮ ባንኮኒም ላይ ሆኖ ስለ አገሩ፣ ስለ እውነት ይናገራል፡፡ እናም የሚያጨሱትን ነገር ጠረጠርኩ፡፡ ግን እነ ሚሚ ስብሃቱ ምኑን ነው የሚያጨሱት?