Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በወባ ከሚሞተው ይልቅ በፖለቲካ ጦስ እና ችግር የሚጎዳው በቁጥር ይልቃል›› ተመስገን ደሳለኝ – [ጋዜጠኛ]

$
0
0

ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት? በተሰኘውና በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ታትሞ በገበያ ላይ በዋለው መፅሀፍ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  የሰጠው ቃለ – ምልልስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ዘ-ሐበሻ ድረገጽ ለግንዛቤ በሚል ለአንባቢዎቹ እንደወረደ አቅርቦታል

 

 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

‹‹ተመስገን ደሳለኝ ጋዜጠኛ ሳይሆን የፀረ-ኢሕአዴግ ፖለቲካ አቀንቃኝ ነው›› ሲሉ ጋዜጠኛነቱ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል ከብዙ ፓርቲዎች በተሻለ ገዢው ፓርቲን በብዕሩ የታገለ፣ ጋዜጣ አንባቢው ኅብረተሰብ ከፖለቲካዊ ፍርሃት እንዲላቀቅ በጽናት የጣረ፣ የቁርጥ ቀን ጋዜጠኛ መሆኑን ምስክርነት የሚሰጡለትም አሉ። አራት ዓመት ገበያ ላይ በቆየችው ፍትሕ ጋዜጣ፣ ታይተው በጠፉት አዲስ ታይምስ መጽሔትና ልዕልና ጋዜጣ ላይ ባሰፈራቸው መጣጥፎቹ የመነጋገሪያ ርዕስ የነበረው ተመስገን ለእሱ በተሰጡ ቀጣይዎቹ ገጾች ላይ ከእዚህ መጽሐፍ አዘጋጆች የቀረቡለትን ሞጋች ጥያቄዎች በመመለስ የ‹‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?›› አካል ሆኗል።

 

በልጅነትህ ምን መሆን ትፈልጋለህ ስትባል ምላሽህ ምን ነበር?

ያደግኩት ፊት በር አካባቢ ነው። ይህ ሰፈር ደግሞ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ በርካታ የደሀ ሰፈሮች አንደኛው ነው። ያደግነውም ሆነ የምንጫወተው በቡድን ነበር። ልጅ ሆኜ ሁሌም ማታ ማታ አባቴ ጋዜጣ ገዝቶ ስለሚመጣ ቡና እየተፈላ ጋዜጣ እንዳነብላቸው ያበረታታኝ ነበር። ሁለተኛ እና ሦስተኛ ክፍል እያለሁ ለቤተሰቡ ጋዜጣ ማንበብ የዘወትር የማታ ተግባሬ ነበር። ታላቅ ወንድሜ ቢኖርም አባቴ የሚያስነብበኝ እኔን ነበር። ትምህርት ቤትም ክፍል ውስጥ አነብ ነበር።

አባትህ ማንበብ አይችሉም?

ይችላል። እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምሯል። በኃይለ ሥላሴ ጊዜ እስከ ዘጠነኛ ክፍል መማር ከአሁን ጋር ሲነፃፀር ያው እንደምታውቁት ነው። [ሳቅ]

ጋዜጣ ማንበቤ፣ ጋዜጠኛ እንድሆን አድርጎኛል እያልክ ነው?

አነብ ነበር እንጂ ጋዜጠኛ እሆናለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። አድጌ መሆን እፈልግ የነበረው መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ገብቼ እስከ ጄኔራል ማዕረግ መድረስ ነበር።

የሆንከው የማትፈልገውን ነው ማለት ነው?

ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ጋዜጠኛ በመሆኔ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ። ሁለትም፣ ሦስትም ሰዎች ቢሆኑ እኔ በምሠራው ሥራ ደስተኛ በመሆናቸው ደስ ይለኛል። በልጅነታቸው የተመኙትን ሲያድጉ የሚሆኑ ጥቂቶች ናቸው። የምንኖረው ደግሞ የተመኘነውን ሳይሆን የተጻፈልንን ነው። እናንተም ቢሆን ጋዜጠኛ እንሆናለን ብላችሁ ተመኝታችሁ እንደማታውቁ እገምታለሁ። [ጠያቂዎቹ የፈለጉትን እንደሆኑ ተናግረዋል።]

በልጅነትህ ቶሎ ደምህ የሚሞቅ፣ ከኪስህ ጩቤ የማይጠፋ የፍልውሃ እና የአራት ኪሎ የታወቅክ ተደባዳቢ መሆንህን ሰምተናል። ትክክል ነን?

[በጣም ሳቀ] አ… ማለት… እእእ… እንትን ነው… ወሬው ትንሽ ግነት አለው ብዬ አስባለሁ። እንደ ማንኛውም ልጅ ሰፈር ውስጥ ስትውል ‹‹ሰፈሬን አላስደፍርም›› ከሚል እሳቤ ፀብ አይጠፋም። በእኛ ጊዜ ደግሞ የቡድን ፀብ ፋሽን ነበር። ጩቤ ይዤ የምዞር ተደባዳቢ ግን አልነበርኩም።

ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጠሀቸው ቃለ-ምልልሶች ላይ እንደተናገርከው ወደ ጋዜጠኝነቱ ያመጣህ የሙያው ፍላጎት ሳይሆን ከ1997 ዓ.ም. በኋላ መንግሥትን የሚሞግቱ ጠንካራ ጋዜጦች አለመኖር አስቆጭቶህ እንደሆነ ገልጸሀል። አመጣጥህ መንግሥትን ለመቃወም ወይም ተቺ ፖለቲካዊ ሀሳቦችን ለማንሸራሸር ብቻ አይመስልም?

አይመስልም ሳይሆን ነውም፤ ይህ ግምት ሳይሆን እውነታ ነው። ቅድም እንዳልኩት ጋዜጠኛ የሆንኩት ተጽፎልኝ አይደለም። የጋዜጠኝነት ስሜቱም እንደነበረኝ እርግጠኛ አይደለሁም። ያመጣኝ ጎርፉ ነው። እንደ ማንኛውም ሰው አገሬን እወዳለሁ። በማንኛውም ቀዳዳ፣ በምችለው መልኩ ለአገሬ የሆነ ነገር ማበርከትን አስብ ነበር። 1997 ዓ.ም. የተፈጠረው ማዕበል፣ ያመጣበት ጎርፍ ያደናገጠው ኢሕአዴግ በርካታ ጋዜጦችን ከጥቅም ውጪ አደረጋቸው። ከዚያ በኋላ የተፈጠሩት ጥቂት ጋዜጦች ደጋግሜ እንደምለው አቅሙ ቢኖራቸውም ከኢሕአዴግ ባሕሪ አኳያ ‹‹ዶማን ዶማ፣ አካፋን አካፋ›› ከማለት ይልቅ ቅኔ ለበስ ያደርጉት ነበር። ስለዚህም ይህን የፍርሃት ቆፈን ለመግፈፍ መሞከር አለብኝ በሚል እንጂ ጋዜጠኛ ለመሆን ስወድቅ ስነሣ ቆይቼ አልመጣሁም። የ97 ጎርፍ ባይመጣ ኖሮ እሆን የነበረው ጋዜጠኛ ሳይሆን ኦዲተር ነበር፤ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ የውጪ ኦዲተር ነበርኩ።

ፍትሕ ምን ዓይነት ጋዜጣ ነበረች?

የፖለቲካ ጋዜጣ!

አንድ ጋዜጣ፣ ጋዜጣ ለመባል ሊያሟላቸው የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የዓምድ ስብጥር ነው። በሙሉ ወይም በከፊል ፍትሕ ይህን ይዛ ነበር ብለህ ታስባለህ?

አይ …. እንደሱ ብዬ ላስብ አልችልም። ምክንያቱም የአገራችን ሚዲያ ገና እያደገ ስለሆነ እኛም አንድ ጋዜጣ ሊያሟላ ያስፈልገዋል ወደሚባለው ደረጃ ለመድረስ ሌት ተቀን እየሠራን ባለንበት ሁኔታ ነው ጋዜጣዋ እንድትቆም የተደረገው እንጂ እጅግ በጣም ብዙ እንደሚቀረን እናውቃለን።

በአገራችን ያሉ ጋዜጦች አቋማቸው፣ የገጽ ብዛታቸውና የዓምድ መጠናቸው ቢለያይም የሚይዟቸው ነገሮች አሉ። ለምሣሌ ጤና የአገሪቷ ትልቅ ችግር ነው። በዚያ ዙሪያ የሚደረጉ ወንጀሎች፣ ሙስናዎች፣ በግል ሕክምና ተቋም የሚካሄዱ ሕጋዊ የሚመስሉ ዘረፋዎች… ብቻ ብዙ ናቸው። የምትሠሩት ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ በቀጥታ ከመንግሥት ጋር የተገናኘው ፖለቲካ ላይ ከማተኮር ባለፈ ሌሎች ችግሮችን ወደ ማጋለጥ ለምን አታተኩሩም?

ኢትዮጵያ ውስጥ በወባ በሽታ ከሚሞተው ይልቅ በፖለቲካ ጦስና ችግር የሚጎዳው በቁጥር ይልቃል። ለዚህ ነው ከወባው ይልቅ ለፖለቲካው ቅድሚያ የሰጠነው።

[ሳቅ] ፍትሕ ጋዜጣ፣ አዲስ ታይምስ መጽሔት እና ልዕልና ጋዜጣ ላይ ከ12 ሰዎች በላይ የግል ሃሳባቸውን ይገልጹበታል፤ ከድርጅታችሁ ሠራተኞች ብዛት ይልቅ የዓምደኞቻችሁ ቁጥር ይልቃል። ይሄ ደግሞ የጋዜጣውን ኤዲቶርያል ሐሳብ ለማንሸራሸር ዕድል አይፈጥርም። ሁሉም አገሪቷ ላይ ያሉ ችግሮችን አስቦ መጥቶ ይተነፍሳል እንጂ ‹‹ሳምንታዊ አጀንዳችን እነዚህ ናቸው›› ተብለው የመሠራት ዕድላቸው አናሳ ነው።

ይሄ የሚታየው ከጋዜጣው አሠራር አኳያ ነው። ኤዲቶሪያላችን የሚያስቀምጠው ነገር አለ። ሃይማኖትን የተመለከቱ በጣም ስስ የሆኑ ነገሮች አሉ። ከዚያ በተረፈ ጋዜጣው ሙሉ በሙሉ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ስላልን ከርዕስ አንቀጻችን ውጪ ሁላችንም የተለያየ ሐሳብ የምናንፀባርቀው ከዚያ ተነሥተን ነው። ከላይ እንደገለጽኩት ፍትሕ የተመሠረተችው የጋዜጠኝነት ሙያ ባንገበገባቸው ወይም ባቃጠላቸው ሰዎች ሳይሆን ጭራሽ ጋዜጠኛ እንሆናለን ብለው ባላሰቡት ነው።

የሆነ ሆኖ ትልልቅ አገራዊ አጀንዳዎች ሲኖሩን ኤዲቶሪያል ቡድናችን ተነጋግሮ በጋራ የሚሠራበት አጋጣሚ አለ። አዲስ ታይምስ ላይ በ‹‹አባይ ግድብ›› ዙሪያ የሠራነውን መጥቀስ ይቻላል። ልዕልና ላይ ወቅታዊውን የሚዲያ ሁኔታ በተመለከተ ሠርተናል። ፍትሕ ላይም ደጋግመን ኤዲቶሪያላችን ወስኖ የሠራናቸው አጀንዳዎች አሉ። ስለዚህም ከሞላ ጎደል የጋዜጣዋን ኤዲቶሪያል ሐሳብ ማንሸራሸር ችለናል ብለን መናገር እንችላለን። አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት አናጣላም፤ በብሔርም እንደዚሁ ነው። ከእነዚያ ውጪ የሚከለክለን/የማይከለክለን ኤዲቶርያል አቋም አለን ብለን የምንራቀቅበት ሁኔታ የለም። የጋዜጣው ዋነኛ የማዕዘን ድንጋይ ፍርሃትን መግፈፍ ስለሆነ አሁን የምንከተለው ስልት ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ።

ይህ ምን ያህል ተሳክቶልናል ብለህ ታስባለህ?

ይሄንንም የምናገረው በግምት ነው እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ ወይም ያካሄድነው ጥናት የለም። ነገር ግን የተሻለ ነገር አምጥተናል ብዬ አስባለሁ። ሌላ ሰው መጥቶ ‹‹ይሄን … ይሄን ፍትሕ የፈጠረችው አይደለምን?›› እስከሚል ድረስ ማለት ነው። የመምህራን ተቃውሞ፣ የፀረ- መጅሊስ እንቅስቃሴ የመሳሰሉት ‹‹ስትነጠቅ እምቢ በል›› የሚለው ፍትሕ የፈጠረችው ለውጥ እና መነቃቃት ነው ብዬ አስባለሁ። በሁለቱም በኩል ፍትሕን እንደሞዴል አንሥተው በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጽፈው አይተናል።

ስትፅፍ ሐሳብን ገልጸህ መገላገልህን ነው ወይስ የሚያስከትለውን ውጤት (Consequence) ታሰላዋለህ?

ጋዜጠኝነት አርበኝነት አይደለም፤ ጦር ይዘህ ጠላትን ስታይ የምትወረውረውርበት/የምትሰካበት ተግባር አይደለም። ጋዜጠኛ ከሆንክ የምታነሣቸው ትችቶች እውነትን መሠረት ያደረጉ እና ሕዝብ ሊያውቃቸው ይገባል የምትላቸውን ነው። መፍትሄ ማግኘት አለባቸው ያልናቸውን ጉዳዮች እናነሣለን። ገዢው ፓርቲ እየሄደበት ያለውን ስሕተት መጠቆም እና የተሻለ መንገዶችን ማሳየት ላይ አተኩራለሁ። ኢሕአዴግ ብልጥ አምባገነን ነው። የእኛ ጋዜጣ (ፍትሕ) ታተኩር የነበረው የኢሕአዴግን የብልጠት ሴራዎችን ለሕዝብ በማሳየት እና በማጋለጥ ላይ ነው። የእኔም ጽሑፎች የሚቃኙት በዚሁ መልኩ ነው።

‹‹ተቃዋሚ›› ከሚባሉት ከአንዳንድ ፓርቲዎች በተሻለ መንግሥትን በጽሑፎችህ ለመገዳደር ትሞክራለህ። መጣጥፎችህም የጋዜጠኛ ሳይሆን የአርበኛ ወይም የተቃውሞ ፖለቲካ አቀንቃኝ ዓይነት ናቸው።

እንደምታውቁት አደባባያችን ጭር ብሏል። ጠንካራ ተቃዋሚ የለም፤ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት በዘለለ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ያሉ አማራጭ የትግል ስልቶችን አንዱንም አይጠቀሙም። ተቃዋሚዎች ትልቅ ነገር አደረጉ ከተባለ መግለጫ ማውጣት ነው። መሪያቸው ሲታሰር፣ አቧራ የሚያስነሣና ለትችት የሚዳርግ ፖሊሲ ሲወጣ የእነሱ ሥራ መግለጫ ማውጣት ነው እንጂ በሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ አማራጮችን አይጠቀሙም። ወደ እኛ ስትመጣ አንድ ጋዜጠኛ ሊያደርጋቸው የሚገቡ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀማችን ከፓርቲዎቹ የተሻለ ግምት አስይዞልን ‹‹አርበኛ›› ሊያስብለን ይችላል። ይህን የሚያመጣው የአርበኝነት ሚና መጫወት የነበረባቸው ፓርቲዎች ጭርታን በመፍጠራቸው እና አንተ የድርሻህን በመወጣትህ ነው። እኔ ግን ከጋዜጠኝነት የዘለለ ሚና አለኝ ብዬ አላስብም።

ፍትሕ ላይ አስፍረኸው የነበረውን ‹‹የፈራ ይመለስ›› የሚለውን ጽሑፍህን ለአብነት ማንሣት ይቻላል። [ጠያቂው ጋዜጣውን ገልጦ እያሳየው] በሰላማዊ መንገድ ቢሆንም ‹‹መብትህን ለማስከበር ውጣ፣ ተንቀሳቀስ›› የሚል ጥቅል ሐሳብ አለው። ይሄ የአንድ ጋዜጠኛ ተግባር ሊሆን ይገባዋል?

ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ አገር የሌለው ብቻ ነው። አገር የሌለው ደግሞ ማን አለ? ማንም የለም። ጋዜጠኛ ብሆንም የራሴ የሆነ የፖለቲካ አቋም አለኝ። ጽሑፎቼ ላይ አቋሞቼ ሊንፀባረቁ ይችላሉ። ሥርዓቱ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመተቸት ያልከውን ጽሑፍ ጽፌዋለሁ። አምስት ዓመት ያህል የጻፍኩት ግን ‹‹የፈራ ይመለስ›› ብቻ ብዬ አይደለም።

የአንድነት ፓርቲ ልሳን ከነበረችው እና ስትንፋስዋ ከተገታው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ፣ የፖለቲካ አቀንቃኝ (Political Activist) ስለ መሆንህ ጥያቄ ቀርቦልህ ‹‹አዝማሚያው ሊኖር ይችላል›› ብለህ ነበር። ታዲያ ይህ ከጋዜጠኝነት መርሕ ጋር በእጅጉ አይጋጭም?

‹‹የፖለቲካ አቀንቃኝ ነህ?›› ያለው ጠያቂው እንጂ እኔ አይደለሁም።

አንተም ግን ‹‹አክቲቪስት ነኝ ባልልም እስከ ዛሬ ፍትሕ ታደርግ የነበረው ከዚህ የዘለለ አይደለም›› ስትል ምላሽ ሰጥተሀል።

‹‹ጽሑፎቼ ያንን ስያሜ ለማሰጠት አጋድለው ሊሆን ይችላል›› ነው ያልኩት። አንባቢ ከጽሑፍህ ተነሥቶ አርበኛ ሊልህ፣ ፅንፈኛ ሊልህ፣ የተቃውሞ ፖለቲካ አቀንቃኝና ሌላም ሊልህ ይችላል። እነዚህ ሁሉ ምድቦች ግን እኔ ውስጥ የሉም። ራሴን የምቆጥረው በአገሩ ላይ የተሻለ ነገር እንዲፈጠር የሚጥር አንድ ጋዜጠኛ አድርጌ ነው።

ስለ ስደተኛ ጋዜጠኞች ያለህ አቋም ምንድን ነው?

ኧኧኧ… [ሳቅ… የቁጥብነት ስሜት እየታየበት] ማንም ሰው ‹‹ለምን የእኔን ፅዋ አልጠጣም?›› ብለህ ልትወቅሰው አይገባም። የራሱ መከራ የመቀበል አቅም የት ድረስ እንደሆነ ያውቀዋል። እዚያ ደረጃ ሲደርስ ማንም ሰው ይሰደዳል። ለእኔ ግን መሰደድ የሚወገዝ ተግባር ነው።

ጋዜጠኛ መፍራት/መሸሽ የለበትም እያልክ ነው?

የመፍራት ጉዳይ ብቻ ሆኖ ሳይሆን ችግሩ እኮ ያለ ነገር ነው። እናንተ ጋዜጣ ለመጀመር ፈቃድ ጠይቃችሁ የነበረው የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲተር ‹‹ልከሰስ ነው›› ብሎ በሸሸበት፣ አዲስ ነገሮች የተሰደዱበት ሁኔታን እያወቃችሁ ነው። እና ታዲያ ‹‹ይህ ጸበል ለእኛ አይደርሰንም›› ብላችሁ ታስባላችሁ? ታዲያ ልከሰስ ነው፣ ልታሰር ነውን ምን አመጣው?

ስለዚህ ለተሰደዱ ጋዜጦች ምንም ክሬዲት አትሰጥም ማለት ነው?

[እየሳቀ] ያው ገልጬዋለሁ ‹‹የተሰደዱ ጋዜጠኞች ለፍተዋል፣ ሠርተዋል›› ብዬ ላስተካክለው? [ሳቅ] የእውነት ሠርተዋል፤ ለፍተዋል። ሲሰደዱ መከራን የመቀበል አቅማችን እዚህ ድረስ ነው ብለው ነው። ባይሰደዱም ያሉት ነገር (እስር) ሊተገበርባቸው ይችል ነበር። የእኔ ቅሬታ ኢሕአዴግ የለየለት አፋኝ በመሆኑ የጋዜጣ ፈቃድ ሲወስዱ ይህ እንደሚሆን ስለሚያውቁት ከመሰደድ ይልቅ ፊት ለፊት መጋፈጡ የተሻለ ነው የሚል ነው። የምንፈልገውን ውጤት የምናመጣው መስዋዕትነት በመክፈል ነው። ጋዜጠኛ የሐሳብ ተዋጊ ነው፤ ምሽጉ ደግሞ ሚዲያው ነው። ስለዚህ መስዋዕትነቱን እየከፈለ ምሽጉን መልቀቅ አይገባውም። ከአገር የተሰደዱ ጋዜጠኞችን ግን በምንም መልኩ ጥፋተኛ ልናደርጋቸው አይገባም። የሸሹ ሰዎች ጥፋተኛ ናቸው አለማለቴ እንዲታወቅልኝ ግን እፈልጋለሁ።

አገር ውስጥ ሆነው የሰላ ትችት ለሚሰነዝሩት ክብር ሰጥቶ በተቃራኒው የተሰደዱትን ክሬዲት ማሳነስ ልክ ይሆናል? አገር ውስጥ ካሉት ከተሻለ በውጪ ወጥተውም አበርክቷቸው ያልተቋረጠ (እየሠሩ ያሉ ጋዜጠኞች) አሉ ብዬ ስለማስብ ነው። እንዳሉት የሚታሰሩ ከሆነስ ወጥተው የሚችሉትን ማበርከታቸው ተገቢ አይሆንም?

ግልፅ እንዲሆን የምሻው ስደተኛ ጋዜጠኞች ፈሪዎች፣ የማይሸሹ ጋዜጠኞች ደግሞ ደፋሮች ናቸው አላልኩም። ድፍረት እና ፍርሃትን ከዚህ ውስጥ እናውጣው! ነገር ግን የቁርጠኝነት ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። መከራ የመቀበል ደረጃ ልዩነት እና የስልት ጉዳይም ነው። እኛ (ፍትሖች) ‹‹እዚሁ ቆስለን፣ እዚሁ ደምተን እንሠራለን›› ስንል፣ ሌሎች ጋዜጠኞች ደግሞ ‹‹ከመታሰር ከአገር ውጪ ሆኖ አስተዋፅኦ ማድረግ የተሻለ ነው›› ይላሉ። ይሄ የምርጫ ጉዳይ ነው። በእኔ እምነት ግን ከአገር ውጪ ሆኖ መሥራት የተሻለ አይደለም፤ እዚህ ሆኖ የመጣውን በጸጋ መቀበሉ የለውጡን ቀን ያቀርበዋል። በተረፈ ትክክሉ ለየራሳችን የሚተው ነው።

የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን አስመልክቶ ‹‹ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ ነገር ይኖራል ጠብቁ›› ብለህ ፌስቡክ ላይ ገልጸህ ነበር። በሁለተኛው ቀን ማረፋቸው ተነገረ። የኢሕአዴግ የውስጥ ምንጮች አሉህ?

ምንም የማያከራክረው ፍትሕ በአገሪቷ ትልቅ ጋዜጣ ነበረች፤ ዋና መስፈርቱ የኅትመት ቁጥር በመሆኑ። የብዙ ሰዎችን ትኩረት ስለሚስብ መረጃዎች ወደ እኛ ይመጣሉ። ሥርዓቱ አገርን እየጎዳ እንደሆነ የሚገነዘቡ የሥርዓቱ ወሳኝ የሆኑም/ያልሆኑም ሰዎች አገርን ከማዳን አኳያ፣ እኛን በማመን አንዳንድ መረጃዎችን ያቀብሉናል።

ጽሑፎችህ ጥልቀት እንደሌላቸው እና ሰዉ ‹‹የእኔ›› ብሎ እንዲያነብ ሰሞነኛ ብሶታዊ ስሜትን ማንፀባረቅ ላይ እንደምታተኩር የሚተቹህ አሉ።

ሁሉም ጽሑፎቼ ላይ ባይሆንም ይሄ ዓይነት ነገር አለ ብዬ አስባለሁ። ፍርሃትን በመግፈፍ ሕዝብን ወደ አደባባይ መሰብሰብን ስለማልም፤ [አደባባይ ስል አብዮት አደባባይ አይደለም] ሕገ- ወጥነትን እምቢ እንዲል የማንቃት ባሕሪ ዋና ዓላማዬ ስለሆነ ሕዝባዊ እና ስሜታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩራለሁ። በአገራችን ላይ የጠፋው ነገር የርዕዮተ ዓለም ዳሰሳ እና ትንተናዎች ሳይሆን [ይሄን በቂ ምሁራን ብለውታል] ፍርሃትን ማሸነፍ ነው። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው አብዮታዊ ዲሞክራሲን ከሊበራል ዴሞክራሲ ጋር እያነፃፀርክ መተንተን አይደለም። የጠቀስካቸውን ጉዳዮች መዳሰስ ነው። ከዚህ አኳያ እንዳልከው ጥልቅ ትንታኔ ላይኖረኝ ይችላል። ‹‹የፈራ ይመለስ›› ለማለት ጥልቅ ትንታኔ አያስፈልግህም። አምስት ዓመት የተጻፉት ጽሑፎች ሁሉ ጥልቀት የሌላቸው ናቸው ብዬ ግን አላስብም።

ከሐሳብ ሙግት ይልቅ ግለሰቦችን ‹‹መጭረፍ›› ላይ ታተኩራለህ። መለስ ዜናዊ፣ ስብሀት ነጋ፣ ፕ/ር አንድሪያስ እሸቴ፣ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ ሬድዋን ሁሴን፣ ፋሲል ናሆምና ሌሎችም ላይ ግላዊ መሠረት ያለው ትችት አቅርበሀል። ችግሮች ያሉት ግለሰቦቹ ጋ ነው ወይስ ተቋማዊ አሠራሩጋ?

ገበያ ላይ ከዋሉ 197 የፍትሕ ኅትመቶች ውስጥ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጽሑፍ ላይ እኔ አለሁ። [በነገራችን ላይ የፍትሕ የመጀመሪያዎቹ ሕትመቶች ላይ ተመስገን በስሙም ሆነ በብዕር ስም የጋዜጣዋን ከግማሽ በላይ ገጾች ይሸፍን ነበር።] ከዚያ ውስጥ ግለሰብ ላይ ያተኮርኩት በጣም ጥቂት ጽሑፎች ላይ ነው። ግለሰቦች ላይ የጻፍኩት እኮ አምስት ጊዜ ብቻ ነው።

ልልህ የፈለግኩት ለውይይት የሚጋብዙ ሓሳቦች (Arguments) ላይ ከማተኮር ይልቅ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር መለስን ጨምሮ በርካቶች ግላዊ ኹነት ላይ ትንተራሳለህ ነው። [የተቋምም ሆነ የሲስተም ፈጣሪ ሰው መሆኑ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።]

በርዕዮተ ዓለሞች ላይ፣ በፍትሕ ሥርዓቱና በመሳሰሉት ላይ ለሁለት ዓመት ያህል ሀተታዎች (Features) ጽፌያለሁ። ስለዚህ ፍትሕ ከመግነኗም በፊት ያለውን ማሰብ/ማየት ያስፈልጋል።

‹‹እስኪ በስብሀት ሙድ እንያዝባቸው፣ ንዋይ ገብረ አምላክ በረሃ እንዳልገቡ አውቃለሁ ምናልባት ውቤ በረሃ ካልገቡ በስተቀር…›› መሰል ከሞራል እና መገናኛ ብዙኃን ከሚቀርብ ጽሑፍ አንፃር (በተለይ ኮስታራ ጽሑፍ ላይ) ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን ትጠቀማለህና ይህ ሐሳብህን ወደ ስድብ ደረጃ አያወርደውም?

ኧ… ኧ… ኦኬ! ቃላቶቹን የተጠቀምኩት ትንሽ ዘና ለማድረግ ያህል ነው። ለምሳሌ ንዋይ ገብረ አምላክ የኢሕአዴግ ታጋይ አይደሉም፣ የደርግ ባለሥልጣን ነበሩ። ያንን ይበልጥ ለመግለጽ ‹‹ንዋይ ገብረ አምላክ በረሃ አልገባም፤ ምናልባት ውቤ በረሃ ካልሆነ›› ብያለሁ። ስድብ ነው ብዬ አላስብም ነበር። በዚያ መልኩ ተተርጉሞ ከሆነ በጣም አዝናለሁ። ምናልባት ቃላቶቹ ወደ ስድብ ወርደው ከሆነ በእጅጉ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ለመሳደብ አልነበረም፤ ከባሕሪም አኳያ የመሳደብ ነገር የለብኝም።

አፍሮጋዳ የሚል መጽሐፍ አንብበሀል? ‹‹ዘመኑ የሚወደው ጥልቀትን አለዝበህ ስሜቱን እንድትነግረው ነው። ቴዲ አፍሮ እና ይስማዕከ ወርቁ (ዴርቶጋዳ) የተወደዱት ለዚህ ነው›› ይላል፤ ታሪክ ሠሪው ከግልቡ እኩል አይታወቅም የሚል ይዘት አለው ጽሑፉ። ይሄንን በአንተ ላይ እንዴት ታየዋለህ?

የ‹‹ጥልቀት›› እና የ‹‹ግልብ›› መስፈርቱ ምንድን ነው? የሚለው አንድ ነገር አለ። በእኔ እምነት የቴዲ አፍሮም ሆነ የዴርቶጋዳ ሥራዎች ግልብ አይደሉም። እነዚህን ‹‹ግልብ›› እንበላቸውና የንዋይ ደበበን ወይም የሰለሞን ተካልኝን ሥራዎች ‹‹ጥልቀት›› አላቸው እንበል? [የአግራሞት ሳቅ] ጥያቄውን ለመመለስ ግን ምናልባት አገር እና ሕዝብን የመናቅ ነገር ይመስለኛል። ቴዲ አፍሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድማጮች አሉት እነዚህን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አብረህ መተቸት ነው። እነዚህ ኢትዮጵያኖች የወደዱትን ሥራ አናንቀን የተሻለው የትኛው ነው?

ሕዝብ የወደደው ነገር ሁሉ ትክክል ነው ማለት ይቻላል?

እንደ ሕዝብ ስሕተት አለው ብዬ አላስብም። አንድ መጽሐፍ ጥልቅም ይሁን ግልብ ሆኖ ይውጣ፣ ገበያ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥረው ጋዜጦች ላይ ከሚወጣው ማስታወቂያ ይልቅ ሕዝብ የሚያወራው ነው። የአንተን መጽሐፍ በጣም አሪፍ ነው እያለ የሚያወራው ከሆነ በቃ አከተመ፤ በጥሩ ሁኔታ ይሸጣል። ‹‹ኡ… የአቤል መጽሐፍ የሞተ ነው›› ብሎ ሕዝብ የሚያወራ ከሆነ ታቅፈኸው ትቀራለህ። ዴርቶጋዳ በእኔ እምነት ጥሩ መጽሐፍ ነው። ያንን ሁሉ ሰው ማሳማን የቻለ ሥራ ግልብ ነው? ይሄ ሁሉ ሰው ግልብ እና ጥልቀት መለየት አይችልም? የሚሉ ነገሮች አብሮ ሊታዩ ይገባል ባይ ነኝ።

ሁሌም መንግሥትን የሚያጠለሹ ጽሑፎችን ብቻ በመጻፍ ትተቻለህ። ይህ ሥርዓት ምንም አልሠራም ብለህ ታስባለህ?

ሩቅ ሳትሄድ ለምሳሌ አዲስ ነገር፣ አውራምባ ታይምስ፣ ፍትሕ ጥቂት ጊዜ ቢኖሩም የዚህ ሥርዓት ውጤት ናቸው፤ እንደ ድመት ራሱ ወልዶ በላቸው እንጂ። ምንም የምትክደው ነገር አይደለም። በደርግ ጊዜ ‹‹ሠርቶ አደር፣ አዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› እያልክ ትሄዳለህ እንጂ የግል ሚዲያ ሽታውም አልነበረም። በዚህ 22 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚመስሉ ነገሮች ብዙ አሉ። ለምሳሌ እናንተ የአውራምባ ታይምስ ባልደረቦች ነበራችሁ። ምንም ይሁን ምን አውራምባ ታይምስ የተዘጋው በኢሕአዴግ ጫና ነው። ስለዚህ ስለ ፕሬስ ነፃነት የሚኖራችሁ ግንዛቤ እዚያ ላይ መሠረት ያደረገ ነው። አውራምባ ታይምስ አራት ዓመት ያህል ለመሥራትዋም ቢሆን ምንም ሳያከራክር ክሬዲቱን መውሰድ ያለበት ኢሕአዴግ ነው። ‹‹ነፃ ፕሬስ›› ብሎ፣ አዋጅ አቋቁሞ፣ ፈቃድ የሰጠው ኢሕአዴግ ነው። ፍትሕ ተዘግታለች ነገር ግን እስከ ነበረችበት ጊዜ ድረስ ፈቃድ የሰጣት ኢሕአዴግ ነው። እነዚህ እነዚህ በጎ ጎኖች በትልልቅ ጥፋቶች፣ ውድመቶችና ኪሳራዎች ስለሚጋረዱ ያንን ማየት የማትችልባቸው ሁኔታዎች አሉ።

ፍትሕ ከተዘጋችና አዲስ ታይምስ መጽሔት ላይ ተሻግራችሁ ሥራ ከመጀመራችሁ በፊት 300 ሺህ ብር ወጪ እንዳወጣህ ፌስቡክ ላይ ጽፈህ አንብበናል። የማስታወቂያ ገቢ አልነበረህምና ጋዜጣ ሸጦ ይሄንን ሁሉ ወጪ መሸፈን ይቻላል?

ጋዜጣ እየሸጥክ እያለህ ድርጅትን ልታሻሽል ትችላለህ። አቁመህ ግን ይሄን ያህል ትርፍ ወጪ መሸፈን አትችልም። እንደምታውቁት ባለፈው ዓመት (2004 ዓ.ም.) ግንቦት ወር ላይ ከወጣው መጽሐፌ (የመለስ አምልኮ) ብዙ ብር አግኝቼበታለሁ። ንገረኝ ካልከኝ መጠኑን ልነግርህ እችላለሁ።

ይቻላል!

እስካሁን ባለው ሁኔታ ከስድስት መቶ ሺህ (600,000) ብር በላይ አግኝቼበታለሁ። ጋዜጣው ቢዘጋም የደጎመኝ ይሄ ብር ነው። ‹‹300 ሺህ አወጣሁ›› ያልኩት ፍትሕ ማተሚያ ቤት ስትያዝብን 84 ሺህ ብር ከፍለን ነበር። በተጨማሪም ጋዜጣውን ለማዘጋጀት የከፈልናቸው ወጪዎች ነበሩ። በአዲስ ታይምስ እስክንመለስ ድረስ ማንም ሠራተኛ ስላልተባረረ ደመወዝ እንከፍል ነበር። 300 ሺህ ብር የደረሱት እነዚህ ወጪዎች ተደማምረው ነው። መቆየት የቻልነውም በመጽሐፉ ገቢ ነው።

ፍትሕ እንደቆመች በተሻለ ፍጥነት በአዲስ ታይምስ መጽሔት ተመለሳችሁ፣ ለስምንት እትም የሄደችው አዲስ ታይምስ ስትቆምም አራት እትም በሄደችው ልዕልና›› ለሦስተኛ ጊዜ መጥታችሁ ነበር። በዋነኝት ኦርኬስትራውን የምትመራው አንተ ነህና ይህ ትጋትህ ለፕሬስ ነፃነት ነው ወይስ ለገንዘብ ነፃነት? [የንግድ ሱቁ የተዘጋበት ሰው ገቢው እንዳይቆም በፍጥነት ሱቅ አፈላልጎ እንደሚይዘው ሁሉ የእናንተም ወደ ሌላ ፕሬስ የምትጓዙት በፍጥነት ስለሆነ ጥርጣሬ በመፍጠሩ ነው።]

ትልቁ ስሕተትህ የሚጀምረው [ጠያቂው አቤልን ቆጣ ብሎ እያየ] በኢትዮጵያ የጋዜጣ ንግድ ለገንዘብ ነፃነት ያበቃል ብለህ መገመትህ ነው። ሐሳቡ የአንተ ካልሆነም ‹‹ሐሳባችሁ ስሕተት ነው›› በልልኝ። በኢትዮጵያ ፕሬስ ውስጥ ያለህን ይዘህ ገብተህ፣ ባዶ እጅህን ትወጣለህ እንጂ እውነት አትራፊ የምትሆንበት ነው?

ፍትሕ አትራፊ አልነበረችም?

ፍትሕ አትራፊ ነበረች። ለአራት ዓመት ያህል ርምጃዋን ጠብቃ መጓዝ በመቻልዋ በሂደት አትራፊ መሆን ችላለች። ነገር ግን አዲስ ታይምስን ስምንት ጊዜ ስናሳትም እና ልዕልናን በከፍተኛ (በተጋነነ) ወጪ ንግድ ፈቃድዋን ከግለሰብ ላይ ስንገዛው ቁማር እንደሆነ እናውቃለን። ከኢሕአዴግ አፋኝ ባሕሪ አንፃር አንድ እትምም ሳንሄድ ሊዘጋት እንደሚችል እናውቃለን። በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት በኋላ ሥርዓቱ ሆደ ባሻ በመሆኑ ያገኘውን ነገር ሁሉ መርገጥ እና ማፈን ጀምሯል። ይህ ባለበት ሁኔታ ብዙ ወጪ አውጥቶ፣ በኪሳራ ምክንያት የቆመን ጋዜጣ ከግለሰብ ላይ በተጋነነ ገንዘብ መግዛቱ ለገንዘብ ያለህን ሐሳብ በፍጹም አያሳይም። ልናተርፍ ይቅርና ያወጣነውን ገንዘብ እንኳን ለማስመለስ ዋስትና የለንም። የሚገርመው ደግሞ የቃለ-ምልልሱን ተከታይ ክፍል በምታደርጉበት በዚህ ወቅት ልዕልና መቆሟን የምነግራችሁ የመጀመሪያ ሰዎች ሆናችኋል። ስለዚህ፣ ያወጣነውን ወጪ እንኳን ማስመለስ አልቻልንም ማለት ነው። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ‹‹ለገንዘብ ነፃነት ነው የምትሠሩት›› መባል የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ አለማወቅ ይመስለኛል። ያለንን እያወጣን መቆመራችን፣ ለፕሬስ ነፃነት እንታገላለን ከሚል እሳቤ የመነጨ መሆኑን ያለጥርጥር እናገራለሁ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ራሳቸውን ሳያከብሩ ሌላውን ማክበር፣ ለራሳቸው አድናቆት ሳይኖራቸው ሌላውን ማድነቅና ጥቂት ግለሰቦች ላይ መንጠልጠል ይፈልጋሉ። መናገር እየቻሉ ‹‹ተመስገን በዚህ ጉዳይ ጻፍበት፣ ተችበት፣ ንገርልኝ›› ሲሉ በጎንዮሽ መልዕክት ማስተላለፍን ይመርጣሉ። ትቀበለዋለህ?

እንዳልኳችሁ እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች እና ሁኔታ አገራችን ላይ በመኖሩ ነው እኔ ጋዜጠኛ የሆንኩት እንጂ ፍላጎቱ ኖሮኝ ከየትኛውም የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ተመርቄ አይደለም። እንደዚህ ዓይነት ድባብና ፍርሃት ስላለ የግድ የተወሰንን ሰዎች ሰንደቅ ማንሳት አለብን፤ ሰዎቹ ቢሉም ትክክል ናቸው። የምንሠራው ለእነሱ፣ ለሌላው ሕዝባችንና ለአገራችን ነው። በዚህ ላይ ደግሞ ለአንድ አገር መስዋዕት ሊሆኑ የሚገቡት ጥቂት ሰዎች ናቸው እንጂ 80 ሚሊዮን ሕዝብ መስዋዕት ከሆነ ታዲያ ማን ነው በመስዋዕትነት በተገኘ ድል ላይ የሚረማመደው? የአረብ ዓለም አብዮት በተነሣ ጊዜ ሆን ብለው የመንግሥት የፀጥታ ሠራተኞች ‹‹ይሄ ሕዝብ አንተ ሞተህለት እንዲያልፍለት ነው የሚፈልገው›› የሚል አፍራሽ ቅስቀሳ ጀምረው ነበር። አገራችን የተሻለች ልትሆን የምትችለው፣ የተወሰንን ሰዎች መከራውን ከተቀብለን ነው። ፈረንጆቹ ‹‹ነጻ ምሳ የለም›› እንደሚሉት ሕዝቡ በሙሉ መከራና ችግር የሚቀበል እና የሚቸነከር ከሆነ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ያመዝናል። ስለዚህ በጥቂቶች ላይ ቢንጠለጠሉም ተገቢ ነው።

ዱላውን የሚቀበል በሌለበት፣ ለእውነት መታገል እና መስዋዕትነት መክፈል ኪሳራ አይሆንም?

ፍትሕን የመሠረትኩትና እኔ ጋዜጠኛ የሆንኩበት ምክንያት የዚህ ዓይነት ዱላ የሚቀበሉ ዜጎችን ለማፍራት ነው። እቅዴ ፍርሃትን አሸንፈው እና ከቀንድ አውጣ ዛጎላቸው ውስጥ ወጥተው ዱላ ሊቀበሉ የሚችሉ የፍትሕ ቤተሰቦችን ማፍራት ነው።

ዱላ ተቀባይ ከሌለስ?

ማፍራት አለብን። እስኪፈራ ድረስ አቅም እስካለ እንሠራለን። እኛ ብናልፍ በርካታ ሰዎች ይቀጥሉታል። ቢያንስ በዚህ አራት ዓመታት ውስጥ ሁለትና ሦስት ማፍራት እንችላለን ብዬ አስባለሁ። በሂደት እንዲህ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እየተባለ ይቀጥላል።

‹‹ዱላ ተቀባዮችን በሂደት እናመጣለን›› ብለሀልና አሁን ዱላ ተቀባዮች ከሌሉ፣ ብዙዎች በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ከባተቱ፣ አንተ ወይም ጥቂቶች ጠንካራ እና ሞጋች ሐሳቦችን መሰንዘራችሁ እናንተን እያገነነ ወደ ጀብደኝነት ደረጃ ከፍ ያደርጋችኋል እንጂ ተከታዮችን ለማግኘት ያስችላችኋል?

‹‹ተመስገን አርአያዬ ነው›› የሚሉ ሰዎች አሉ። እንዲህ ካሉ እኔ አናጢ፣ ግምበኛ ወይም አስተማሪ አይደለሁም። አርአያነቴ በጋዜጠኝነት ሥራዬ ነው። ስለዚህ ይህንን አርአያ ይከተላሉ ማለት ነው።

የሠራህባቸው የኅትመት ውጤቶች ከተቋማዊ አሠራር ይልቅ በአንተ ትከሻ ላይ መንጠልጠል ይታይባቸዋል። ጥናት ባንሠራም፣ ባለን መረጃ መሠረት ከጋዜጣችሁም ጥቅል ፍሬ ነገር ይልቅ አንተ ርዕስ ነህ። በሆነ አጋጣሚ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንታት ተመስገን ባይጽፍ የጋዜጣችሁ ሽያጭ አደጋ ውስጥ የሚወድቅ አይመስልህም? [የፍትሕ/አዲስ ታይምስ/ልዕልና አንባቢያን ማዳመጥ የሚፈልጉት ያንተን ትኩሳት ነው ብዬ ነው።]

ይሄ ሁኔታ ተቋማዊ ሁኔታን ካለመገንባት የሚመጣ ሳይሆን ጋዜጣው ለረዥም ዓመት እንደ አሁኑ ‹‹በድል ጎዳና›› መራመድ ሳይጀምርና በቂ የሠራተኛ ኃይል ሳይኖረው፣ ለረዥም ዓመት በችግርና በብድር [አራጣ እስከ መበደር ደርሼ] ጋዜጣውን ይዤ የተጓዝኩት እኔ ስለሆንኩ ነው። በ2004 ዓ.ም. ሙሉ ዓመት ግን ጋዜጣው ተቋማዊ ሰውነት ይዞ እየተጓዘ ነበር። በእኔ እምነት ፍትሕ የተለያዩ ሐሳቦችን ታነሣለች፣ ታስተናግዳለች። አቅም ኖሮንም መክፈል ችለናል። ይሄ ጋዜጣዋ በድል ጎዳና መጓዝ ከጀመረች በኋላ የመጡ ለውጦች ናቸው። ይሄ ጥያቄ የተነሣው 2004 ዓ.ም. ሳይገባ በፊት ቢሆን ትክክል ነበር። ከስሜ ውጪ በብዕር ስም ስድስትና ሰባት ጽሑፍ በሳምንት የምጽፍበት ጊዜ ነበር።

‹‹ፍትሕ በድል ጎዳና…›› ካልከው ጋር ልንተራስና፣ በተደጋጋሚ ጊዜ በኅትመት መጠን ቀዳሚ መሆንን እንደ ብቃት ጥግ ማሳያ ትመለከተዋለህ። ፍትሕ ታብሎይድ ስለሆነች እና ስሜት ቀስቃሽ (Sensational) ጉዳዮችን ስለምታንፀባርቅ (ስለምታነሣ) እንጂ የጋዜጣዋን በደረጃ ቀዳሚነት እና ጥልቀት፣ ተነባቢነቷን ፈጽሞ አይገልጽም ብልህ ተሳስቻለሁ?

አዎን! ሙሉ በሙሉ ተሳስተሃል። ምክንያቱም ምንም የማያከራክረው ነገር 2004 ዓ.ም. ሙሉ ፍትሕ በኅትመት መጠን ቀዳሚ ነበረች። በታብሎይድ ስታይል ብትሄድ፤ አንድ ሳምንት ስሜት ቀስቃሽ ርዕሰ ጉዳይ ስታገኝ ሊሳካልህ፣ ሳታገኝ ደግሞ ላይሳካልህ ነው። ከሳምንት ሳምንት በቋሚነት አንባቢ አፍርተህ መጓዝ ማለት ግን የተሻለ አማራጭ ይዘህ መጥተሃል ማለት ነው። ስሜት ቀስቃሽ ነገሮች በጣም ውስን እና ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚያያዙ ናቸው። ለምሳሌ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት ስሜት ቀስቃሽ አጀንዳ ሊሆን ይችላል። ጥሩ አድርገህ ልትሠራበት ትችላለህ። ሁልጊዜ ግን እሳቸው አይሞቱም። ዓመቱን ሙሉ በቀዳሚነት መጓዛችን የሚያሳየው ቋሚና ታማኝ አንባቢ ማግኘታችንን ነው። ታማኝ አንባቢ ማግኘት ደግሞ ቀዳሚ መሆን ማለት ነው።

በአገራችን ነፃ ፕሬስ ስሙ ነው እንጂ በአሁን ወቅት አለ ብለህ ታምናለህ?

የለም ብዬ አምናለሁ።

ማሳያህ ምንድን ነው?

ጋዜጠኛው በራሱ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቱ ምን ያህል ተከብሯል? እስክንድር ነጋ፣ መስፍን ነጋሽ፣ ዳዊት ከበደ፤ አቤል፣ ኤልያስ፣ ውብሸት ወይም አቤ ቶኪቻውን ምን ያህል ነፃ አድርገዋቸዋል? በሚል ነው የሚለካው እንጂ ‹‹ኢሕአዴግ አምባገነን ነው›› ብቻ ብሎ በመጻፍ የጋዜጣህ ነፃነት ወይም ነፃ ጋዜጠኝነት አይለካም። ከዚህ አኳያ አሁን ወዳሉት የኅትመት ውጤቶች ስትመጣ ‹‹ነፃ ጋዜጣ አለ›› ለማለት ይከብደኛል። [የቃለ ምልልሱን የመጀመሪያ ክፍል ያደረግነው ፍትሕ ጋዜጣ ከቆመች በኋላ በነሐሴ 2004 ዓ.ም. እንደነበር ልብ ይሏል።] ‹‹ከዚህ በኋላ በዚህ ርዕስ ላይ እንዳትሠራ›› የሚሉ የጋዜጣ ባለቤቶች ናቸው ያሉት። ዋና አዘጋጆቹም የባልደረቦቻቸውን ሸክም (መስቀል) መሸከም የማይችሉ ናቸው። በአገሪቱ የፕሬስ ሕግ መሠረት የሚጠየቀው ዋና አዘጋጁ ነው። ፍትሕ ላይ ሁሉም በሚጽፉት ጽሑፍ አንዳች ነገር እንደማይደርስባቸው ያውቁታል። ስለዚህ እነዚያ ጋዜጠኞች እንዳሻቸው በነፃ ሜዳ ላይ ይቦርቁበታል ማለት ነው። ማንኛውም ዋና አዘጋጅ ለባልደረቦቹ ያንን ያህል ኃላፊነት መውሰድ አለበት። በዋነኛነት ‹‹ነፃ ጋዜጣ የለም›› የምልህ አፈናው የሚጀምረው ከውስጥ፤ ከባለቤቱና ከዋና አዘጋጁ በመሆኑ ነው። ጋዜጦቹን በደንብ ተከታተሏቸው፤ የሚጮሁበትና የማይጮሁባቸው ጉዳዮች አሉ። የሚሠሩት ‹‹ይሄ ኢሕአዴግን ያስቆጣዋል/አያስቆጣውም›› እያሉ በማማረጥ ነው።

ነፃ ሚዲያ አለ ብለህ አታምንም ነገር ግን የኅትመት ውጤቶችህ/ቻችሁ ሲዘጉ እነዚህኑ የፕሬስ አካላት ሁኔታውን ይፋ እንዲያደርጉ እና አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ትጠይቃለህ። አይጣረስም?

ግልፅ እንዲሆን የምፈልገው ነገር… የሕወሃትን አጀንዳ የሚያራምዱ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉ አምናለሁ። ሌሎቹ ግን ራሳቸው ላይ ቅድመ ቁጥጥር እያደረጉ ራሳቸውን በራሳቸው አዳክመዋል። አንድ ሚዲያ ራሱን ከገደበ፣ ኤዲቶሪያል ነፃነቱ ላይ ከተደራደረ፣ ‹‹ይዘጉብኛል›› ብሎ ራሱን ከቆጠበ ደካማ ነው። በርግጥ ይህ የሆነው በሥርዓቱ ጫና ፈጣሪነት ነው። ይህ ማለት ግን ሕወሃት ጠፍጥፎ ሠርቷቸዋል ማለቴ አይደለም። ስሕተታችንን ነግረኸናል በሚል ቅር ተሰኝተው፣ ከእናንተ ጎን አንቆምም የሚሉ ካሉ የአቶ መለስን አባባል ልዋስና [አቶ መለስ የሚነሡለት በጎ ነገር ባይኖርም፣ ተረቶቹ ይነሣሉ] ‹‹በሊማሊሞ ማቋረጥ ትችላላችሁ›› እላቸዋለሁ።

እኛ አገር ባለው ሁኔታ አሳታሚዎች ወይም ጋዜጠኞች የጋራ ችግር ሲመጣ፣ የማተሚያ ቤት ዋጋ ሲወደድና መሰል ችግሮች ሲፈጠሩ ለይምሰል ማኅበር ይቋቋማል፣ ‹‹ኅብረት›› ለመፍጠር ይጥራሉ እንጂ በጥቅሉ አጋርነት (Solidarity) አለ ለማለት ይቻላል?

እንዳልኳችሁ ምን ያህል ጋዜጦች ነፃ ናቸው? ከ2003 ዓ.ም. በኋላ ገበያ ላይ እስከነበርንብት ጊዜ ድረስ ከአውራምባ ታይምስ ውጪ ነፃና በራሱ ቆሟል ብዬ የማምነው ሌላ ጋዜጣ አልነበረም። ይሄ የአደባባይ ሃቅ ነው። ሌሎቹ የየራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ናቸው። ራሳቸውን ነፃ ካላወጡ ሰዎች ጋር አብሬ፤ ነፃ ማኅበር መስርቼ እንቀሳቀሳለሁ፣ የፕሬስ ካውንስል መስርቼ እንቀሳቀሳለሁ ብትል አያስኬድም። የፕሬስ ካውንስል በየትኛውም አገር የሚታየው ከሥነ-ምግባር አኳያ ነው። አፍሪካ ውስጥ ትልቅ የፕሬስ ካውንስል ያለበት የመጀመሪያ አገር ዛምቢያ ትመስለኛለች። እዚያ ፕሬዝዳቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፍተኛ ባለስልጣናት በአንድ ጋዜጣ የወጣ ዘገባ በደለን፣ ጎዳን፣ ስማችንን አጠፋው ብለው ሲያስቡ ወደ ፍ/ቤት አይሄዱም። ፕሬስ ካውንስሉ ጋ ሄደው መርምሮ የሥነ-ምግባር ጉድለት ካለበት ቅጣት ይወስናል። ‹‹ለሦስት ወር አትዘግብ›› ሊል ይችላል። ፕሬስ ካውንስል ይሄንን የሚያደርግ ትልቅ ኃላፊነት የተሸከመ ድርጅት ነው። ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ካውንስል አደራጅ ሊቀ-መንበር ሚሚ ስብሐቱ ትባላለች። የምናወራው ስለ ስነ-ምግባር ነው፤ ከግለሰቧ ጋር ምንም ችግር የለብኝም። አንዳንዴ ትራንስፖርት ውስጥ ድምጿን በሬድዮ ከመስማት ውጪ ስለእሷ ብዙም መረጃ የለኝም። በአካልም ተገናኝተን አናውቅም። ነገር ግን ከአሜሪካ ሬድዮ ጣቢያ በሥነ-ምግባር ጉድለት የተባረረች፣ በ1998 ዓ.ም. ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ‹‹እነዚህ ጋዜጠኞች ሞት ሊፈረድባቸው ይገባል›› ብላ ስትከራከር የነበረች፣ ጋዜጠኞች በተሰደዱ ቁጥር ‹‹ከሥረው ነው፣ አሸባሪዎች ናቸው›› የምትል፣ ፍትሕ ሲዘጋም ‹‹መንግስት ዘገየ›› ያለች ሴትዮ ሌላውን ጋዜጠኛ እንዴት አድርጋ እንደ ምታስተምር እግዚአብሔር ነው የሚ ያውቀው።

እንደዚህ አይነት ካውንስልን ስለማታምነው እና ነፃነት እንደሌለው ስለምታውቅ አብረኸው ልትሠራ አትችልም። በሙሉ መልዕክተኞች ናቸው። በአብዛኛው የመንግሥት አስፈጻሚዎች ናቸው። እነሱ ነፃ መሆን ቢፈልጉም ኢሕአዴግ በባህሪው ምንም ነገር ነፃ እንዲሆን አይፈልግም። እነዚህ ሠዎች ደግሞ የሥርዓቱ ቀንደኛ አገልጋዮች እና ዋና ተጠሪዎች ናቸው። ስለዚህ ከእነዚህ ጋር ልትሠራ አትችልም። ይሄ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ አጋርነት እንዳይኖር ያደረገው።

ከመንግሥት ትዕግስት አልባነት አንፃር ብዙዎች ጋዜጣ ለመጀመር ፈቃድ ማግኘት ባልቻሉበት አገር እናንተ ሦስት ‹‹መለያ›› ቀያይራችሁ [አዲስ ታይምስ እና ልዕልና ላይ የቆያችሁት ለአጭር ጊዜም ቢሆን] ስትጫወቱ መታየቱ ጥርጣሬ የጫረባቸው ወገኖች አሉ። ‹‹የኢሕአዴግ አንድ ክንፍ “ነጻ ሚዲያ አለ” ለማስባል ከጀርባቸው ሆኖ ያግዛቸዋል›› የሚሉ ድምጾችም ይሰማሉና ምን ትላለህ?

እንዲህ እያሉ የሚያራግቡት ሕሊናቸው በጥቅም የታወሩ ሠዎች ናቸው። ምክንያቱም እኛ በ‹‹አዲስ ታይምስ››ም ሆነ በ‹‹ልዕልና›› ስንመለስ በሥርዓቱ (በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን) ፈቃድ አይደለም። ሁለቱንም ከባለቤቶቹ ጋር ተደራድረን ገዝተን ወደ እኛ ከዞረ በኋላ የአንድ ዓመት ፈቃድ ስለነበራቸው በሕጉ መሠረት ለብሮድካስት ባለስልጣን ያደረግነው ‹‹ዋና አዘጋጅ እና ሥራ አስኪያጅ መቀየራችንን ማስታወቅ እንጂ ማስፈቀድ አይደለም። በማስታወቅ እና በማስፈቀድ መሀከል ሰፊ ድልድይ አለ።

ስታሳውቁ እናንተ መሆናችሁን ሲረዱ እንዳትንቀሳቀሱ እንዴት አላደረጓችሁም?

ያው ዘጉት እኮ። ከታኅሳስ 30 በኋላ የሥራው ፈቃድ ስለሚቃጠል የአዲስ ታይምስን ፈቃድ ልናድስ ስንል ‹‹ሥም ያዞራችሁት በሕገ-ወጥ መንገድ ስለሆነ አናድስም›› ብለው ዘጉት። ልዕልናንም የጀመርነው አዲስ ፈቃድ አውጥተን አይደለም በውልና ማስረጃ ማድረግ የሚገባንን ከጨረስን በኋላ ጋዜጣው ነገ ሊወጣ እንደዛሬ ባለቀ ሰዓት ዋና አዘጋጅ መቀየራችንን በደብዳቤ አሳወቅን። ሦስት ዕትም ከሄድን በኋላ ብሮድካስት ላይ ያሉ የሥርዓቱ ሎሌዎች ‹‹በሕገ ወጥ መንገድ ነው ጋዜጣውን ወደ እናንተ ያዞራችሁት›› ብለው ደብዳቤ ጻፉልን። በጣም የሚገርመው ግን ከልዕልና ባለቤት ጋር ስምምነት ነው እንጂ የፈጸምነው ገና ሥም ወደ እኛ አልዞረም ነበር። አራተኛውን ዕትም ካወጣን በኋላ በንግድ ሚኒስቴር በኩል ‹‹የንግድ ፈቃዳችሁ ተሰርዟል›› የሚል ደብዳቤ ላኩልን።

እውነታው ይህ ስለሆነ የሚወራውን በማስተባበል ራሴን አላደክምም። እንዲህ ብለው የሚጽፉትም እውነታውን ያውቁታል። በሦስቱም የኅትመት ውጤቶች ላይ እኛ የምናነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች የእውነት ሥርዓቱ የሚፈልጋቸው ወይም ለማስተንፈሻነት የሚጠቀምባቸው ናቸው? አንባቢ ስለሚፈርድ ይህን በማስተባበል ጉልበቴን አላደክምም።

በነገራችን ላይ… ልዕልና ላይ ባሰፈርካቸው መጣጥፎች ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን  አንቱታን ትተህ ሁለተኛ መደብ ነጠላ ስም በመጠቀም ‹‹አንተ›› እያልክ ትገልፃቸው ነበር። ይህ ተገቢ ነው?

ተሳስቼ ሳይሆን ሆን ብዬ ያደረግኩት ነው። ፍትሕ ላይ እያለን ሥርዓቱ በተወሰነ መልኩ ሕግ እንደሚያከብር የማስመሰል አካሄድ ስለነበረው ለዚያች እውቅና ሰጥቼ ‹‹አንቱ›› እላቸው ነበር። አሁን የተፈጠረው ግን ጭልጥ ያለ አፈና እና ጉልበተኛነት ስለሆነ እነዚህን ሰዎች አንቱ ማለቱ አግባብ አይደለም ብዬ ስለማስብ ነው። የምታከብረው እኮ የሚከበርን ሠው ነው። አፋኝ፣ ሕገ ወጥና ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ ጭፍን አምባገነን ስለሆኑ ‹‹አንተ›› ከማለት ባለፈ በአፋጣኝ ከሥልጣናቸው እንዲለቁም እፈልጋለሁ። ‹‹ከሥልጣንህ ውረድ›› እንጂ ‹‹ከሥልጣንዎ ይውረዱ›› አትልም። ጋዳፊ፣ ሙባረክ ‹‹ውረድ›› ነው የተባሉት።

ጋዜጠኛ ከሥልጣን ሲወርዱ ይዘግባል እንጂ ‹‹ከሥልጣን ውረድ›› ማለት ይገባዋል?

ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ የጋዜጠኝነትን መርህ አክብረህ የምትሠራበት ስላልሆነ ነው። ጋዜጠኝነት መታየት ያለበት ከአውዱ አኳያ ነው ብዬ አስባለሁ።

ባለፈው ነሐሴ 2004 ዓ.ም. በጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ላይ አንተ፣ አቶ አማረ አረጋዊ [የሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ ባለድርሻ እና ሥራ አስኪያጅ] እና ዶ/ር መሠረት ቸኮል [በዊስኮንሲን ሪቨር ፎልስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ፕሮፌሰር የነበሩና በሕዳር/2005 ዓ.ም. በጉበት ካንሰር ሕይወታቸው ያለፈ] ለቃለ ምልልስ ቀርባችሁ ነበር። አቶ አማረ ‹‹ሚዲያ ካውንስሉ የፕሬስ ነፃነትን እየታገለ ነው መጓዝ ያለበት›› ሲሉ አንተ እና ዶ/ር መሠረት ደግሞ ‹‹መጀመሪያ የፕሬስ ነፃነቱ መቅደም አለበት›› ስትሉ ነበር።

ጋዜጠኞች ናችሁና ብዙ መረጃ አላችሁ። ለረዥም ጊዜያት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ‹‹አገሪቱ ላይ የቀሩት ሁለት ነፃ ጋዜጦች ናቸው›› ይሉ ነበር። አውራምባ ታይምስ ከተዘጋች በኋላ ደግሞ አንድ ጋዜጣ ብቻ መቅረቱን ተናግረዋል። አሁን ደግሞ ‹‹የቀረችው አንድ ጋዜጣ ተዘጋች›› ብለዋል፤ ፍትሕን። ስለዚህ መጀመሪያ የሚያስፈልገው ሚዲያው ነው። ካውንስሉ የሚያስፈልገው ሚዲያ ሲኖር ነው፤ ሚዲያ ከሌለ ደግሞ ካውንስሉ ምንም አይሠራም። ሚዲያ የሚኖረው ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሲረጋገጥ በመሆኑ፣ መጀመሪያ መታገል ያለብን ሚዲያ እንዲኖር ነው። እናንተ የጋዜጣ ፍቃድ ተከልክላችኋል። ታዲያ እንዴት ስለ ካውንስል ይወራል? ማውራት ያለብን [ቆጣ ብሎ] ፍቃድ ስለ መከልከል/አለመከልከል ነው። ፍቃድ ተከልክለህ ካውንስሉ ምን ያደርግልሀል? ካውንስሉ የሚያያዘው ከሥራ ጋር ነው፤ ስትሠራ፣ ስታጠፋ ካውንስሉ ያስፈልጋል። ‹‹የዐይንህ ቀለም አላማረኝም›› ተብለህ ፍቃድ በምትከለከልበት አገር ላይ እንዴት ስለ ካውንስል እናወራለን? ካውንስሉ አያስፈልግም ሳይሆን በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣ ነው። መጀመሪያ ሚዲያው በእግሩ መቆም አለበት። የእነ አማረ አረጋዊና የእነ ሚሚ ስብሐቱ የሚዲያ ካውንስል ዕቅድ ዝም ብሎ ተራ ቅዠት ነው። ዝም ብለው ድርጅት አቋቋምን ብለው መንፏለል ካልሆነ በስተቀር ግብዝነት ነው። እኔ አማረ አረጋዊን ከሚሚ ስብሐቱ ጋር አንድ ላይ ደርቤ አላየውም። አማረ የራሱ ፍላጎት ቢኖረውም፣ የራሱ ኤዲቶሪያል ነፃነት ያለው ጋዜጠኛ አለው። ሚሚን ግን እንደ ጋዜጠኛ ልወስዳት አልችልም፤ ጋዜጠኛ አይደለችምም። ‹‹ጋዜጠኛ አይደለሽም፤ አትችይም›› ተብላ የተባረረች ነች፤ እየሠራች ያለውንም የምታዩት ነገር ነው። ‹‹ካውንስል መሠረትን›› ብለው በየመድረኩ ለታይታ ለመቅረብ ካልሆነ በስተቀር የትም ሊደርስ እንደማይችል ከእኔ የበለጠ እነሱ ያውቁታል።

በአንድ ወቅት ላይ ከአንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋር ፖርላማ ስብሰባ ላይ ተገናኝተን ስናወራ ‹‹ተመስገንን አስረን አናጀግነውም›› ብለውኝ የነበረ ቢሆንም ለስድስት ቀንም ቢሆን መታሰርህ አልቀረም። ታስረህ ‹‹መጀገን››፣ መሸለም እንደምትፈልግ፣ ለመታሠር ጉጉ እንደሆንክ የሚደመጡ አስተያየቶች አሉ። ምን መልስ አለህ?

ይሄ እንደ ሰውየው የማሰብ መጠን ይወሰናል። ሲ.ፒ.ጄ. ከሸለማቸው ሰዎች ውስጥ [ከዳዊት ውጪ ያሉት] አብዛኛዎቹ ታስረው የማያውቁ ናቸው፣ እስር ቤት ሆነው የተሸለሙ በጣም ጥቂቶች ናቸው። በሲ.ፒ.ጄ ለመሸለም ትልቁ መስፈርቱ በአምባገነን መንግሥት ውስጥ ሳትሸሽ፣ በድፍረት መሥራት ብቻ ነው እንጂ ‹‹መታሰር›› የሚል ቅድመ ሁኔታ የለውም። ምናልባት መታሰርን እንደ ሁለተኛ መስፈርት ሊወስዱት ይችላሉ። አቶ ሽመልስ ከማል አንተ [ኤልያስ] በጥያቄህ ላይ እንዳነሳኸው ሁሉ እኔንም ቢሯቸው ጠርተው ‹‹የዳዊት ሽልማት አማልሎህ ከሆነ በጣም ተሳሰተሃል›› ብለውኛል። ንግግራቸው እና ከንግግራቸው ጀርባ ያለው እውነታ የሚያሳየው ‹‹አሳሪ፣ ጨፍላቂ፣ ደምሳሽ ነን›› የሚል ነው እንጂ አንድ ጋዜጠኛን ጠርተህ ‹‹ለመታሰር ፈልገሃል›› የምትልበት ምንም ምክንያት የለም። ጋዜጠኛ ካጠፋ መታሰር አለበት። ወንጀል የሠራ ሰው መመከር ሳይሆን መታሰር ነው ያለበት። የአቶ ሽመልስ ንግግር የሚገልጸው እሳቸው የሚያገለግሉት ሥርዓት ምን ያህል ጨቋኝ፣ አፋኝና የነፃውን ፕሬስ ምኅዳር አጥባቢ መሆኑን ነው።

… ታስሬ ጀግና መሆን የምፈልገው መቼ ስፈታ ነው? ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ውሰደው! 18 ዓመት ተፈርዶበታል። ከእነዚህ ዓመታት በኋላ 60 ዓመት ሲሆነው [አሁን አርባ ሁለት ዓመቱ ነው] ወጥቶ የሚያገኘውን የጀግንነት ክብር ፈልጎ ይታሰራል? ‹‹የማገኘው ክብር አለ›› ብለህ መታሰር፣ ሕይወትህን ልትበላበት የምትችለው ቁማር ነው። አሁን 34 ዓመቴ ነው። 15 ዓመት ቢፈረድብኝ ከእስር ቤት የምወጣው በ50 ዓመቴ ነው። በዚያ 15 ዓመታት ውስጥ የማጣቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የማገኘው ክብር ምንድን ነው? ሁሉንም ነገር ከዜሮና ከአዲስ ነው የምትጀምረው። አቶ ሽመልስ የሚያንፀባርቁት ነፍሳቸውን ይማረውና የሟች ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጉልበታም ሐሳብ ነው። ይሄ የአምባገነኖች ባሕሪ ነው።

(ዘ-ሐበሻ ድረገጽን በየቀኑ በማንበብ ራስዎን በመረጃ ከሰው እኩል ያድርጉ)
በቃሊቲ የስድስት ቀን አክራሞትህ እነማንን አገኘህ? ምንስ ተማርክ?

የታሰርኩት የቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናት ታስረው በነበረበት ‹‹ዞን አራት›› ነው። ዋና ዋናዎቹ ተፈትተዋል፣ ጥቂት ሚኒስትሮች ነበሩ። ለምሳሌ የኢኮኖሚ እና የጡረታ ዋስትና ሚኒስትር የነበሩት ኮሚሽነር ገሠሠ ወልደኪዳን ነበሩ። ሻለቃ መላኩ ተፈራ [የጎንደር አስተዳዳሪ] እነ ሻምበል በጋሻው አታላይ [የወሎ አስተዳዳሪ] ነበሩ። በርካታ እስረኞች አሉ። ዶ/ር ተስፋዬ ብሩ፣ የአዋሽ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ለይኩን ነበሩ፤ ብዙ ብትቆይ ከእነሱ ብዙ ትማራለህ።

የቀድሞ የቤንሻንጉል ጉምዝ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ያረጋል አይሸሹምን አግኝቻቸዋለሁ። ከእሳቸው የምትማረው ነገር አለ ብዬ አላስብም፤ ሙስናን ካልተማርክ በስተቀር። [ሳቁ መጣበት] ከብዙዎቹ ጋር አውርተናል፤ ግን ለጊዜው ባልገልጻቸው ጥሩ ነው። የእስር ዘመንና ሰቆቃቸውን ማበርታት ይሆናል። ብዙዎቹ ከእኔ ጋር የሚያወሩት ስለ ዕድርና ዕቁብ አይደለም። አስቀድመው የፖለቲካ ጋዜጣ አዘጋጅ መሆኔን ስላወቁ፣ ያወጋነው ፖለቲካዊ ወሬ ስለሆነ፣ ይሄንን መናገር አስቸጋሪ ነው።

‹‹ለምን እንዳሰሩኝ፣ ለምን እንደፈቱኝ›› አላውቅም ብለህ ከወጣህ በኋላ ጽፈሀል። ዞን 4 ተስማምቶህ ነበር እንዴ?

[ከሳቀ በኋላ] አይደለም። በጥፊ አጩዬህ ይቅርታ መጠየቅ የለብኝም። ሲጀመር መማታት የለብኝም። ዝም ብለህ ማንንም ሰው እየጠራህ፣ ከቤቱ እየወሰድክ፣ እስር ቤት እየከተትክ፣ የምትፈታበት ሁኔታ መቆም አለበት። መብቴ ሊከበር ይገባል። የተለቀቅኩት ስድስት ቀን ያለአግባብ ታስረሀል ተብዬ አይደል? ለዚህ ካሳ ማግኘት ነበረብኝ፤ መንግሥትም በይፋ ይቅርታ ሊጠይቀኝ ይገባ ነበር።

ዳግመኛ ወደ እስር ቤት የምትመለስ አይመስልህም? [ይህ ጥያቄ የቀረበለት በድጋሚ በዚህ ጉዳይ ከመከሰሱ በፊት ነበር።]

በዚህ ጉዳይ ተመልሼ እገባለሁ ብዬ አላስብም።

በድህረ መለስ ኢትዮጵያ ምን ገጽታ የሚኖራት ይመስልሀል? ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ማን እና ምንድን ነው ብለህስ ታስባለህ?

ከፋፍለን እንየው፣ መጀመሪያ ከእውነታው እንነሣ። ስገምት ‹‹ድህረ-መለስ›› አስቸጋሪ ሁኔታ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። አራቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ሲይዙ ባልተመጣጠነ ጉልበት ነው። ሕወሃት አስኳል ነው። ወሳኝ ወሳኝ ነገሮችን ይዟል። የመሪነት ባሕሪ አለው። ልክ በደርግ ጊዜ ስትመጣ መፈክሩ ሁሉ ‹‹በጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ማዕከላዊነቱ ኢሠፓን እንመሠርታለን…›› ነበር የሚሉት። ኢሕአዴግም ሲመሠረት በሕወሃት ማዕከላዊነት ነው። ከ1993 ከሕወሃት መሰንጠቅ በኋላ ግለሰብ (አቶ መለስ) ማዕከላዊ ሆነዋል። ይሄ ሁኔታ ጉዳቱን በግልጽ ያመጣዋል። በተለይ ደግሞ አማራንና ኦሮሞን የሚወክሉ ሁለት ድርጅቶች አሉ። ኦሕዴድ እና ብአዴን ወክለውት ወደ ግንባር የመጡት የሕዝብ ቁጥር አለ። ከፍተኛ ሥልጣን ይዞ የነበረው ሕወሃት ይዞ የመጣው የሕዝብ ቁጥር አለው። ምናልባት አሁን የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ‹‹በቁመታችን ልክ ግንባሩ (ኢሕአዴግ) ውስጥ ቦታ ልናገኝ ይገባል።›› የሚል ጥያቄ ያነሣሉ ብዬ አስባለሁ። አሁን የሥልጣን ትግል (Power Struggle) ይፈጠራልም፤ ተፈጥሯልም። በተለይ ደግሞ በትግሉ ላይ ተቀራራቢ ዕድሜ ያስቆጠሩ ፓርቲዎች አሉ፤ ሕወሃትና ብአዴን። ኦሕዴድ ከ1981፣ ደኢሕዴን ከ1983 ወዲህ ስለሆኑ፣ በዚሁ ልክ ነው ግንባሩ ውስጥም የእኔነት ስሜትና የበላይነት ቁመት የሚኖራቸው። አሁን ያለው የድህረ መለስ ክፍፍል በብአዴንና በሕወሃት መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ ፈጥሯል። ይሄ ትንቅንቅ የቱ ጋር ሄዶ ሄዶ ያቆማል ሌላ ጉዳይ ነው። ወይ ደግሞ ትንቅንቁ ወደ አደባባይ በወጣ ጊዜ የሥርዓቱ መጨረሻ ይሆናል። ጉልበት መለካካቱ አይቀርም።

በምኞት ደረጃ የምትለኝ ከሆነ፣ መንግሥት ብሔራዊ ዕርቅ መፍጠር አለበት። ለደርግ ባለሥልጣናት የተሰጠው ምሕረት ጥሩ ነው። ኢሕአዴግ ብዙውን ጊዜ ፈልጎ፣ የተወሰነ ጊዜ ደግሞ በስሕተት በርካታ ዜጎችን አሰቀይሟል፣ አስኮርፏል፣ በድሏል፣ ለስደት ዳርጓል። እነዚያን ለማምጣት ዕርቁ ያስፈልጋል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች [ኦነግ እና ግንቦት 7ን ጨምሮ] ጋር ምሕረት ነግሦ፣ ‹‹አሸባሪ›› ለሚሉት ምሕረት አውርደው፣ የምርጫ ጊዜ ከመድረሱ በፊት ሁሉም ፓርቲዎች ፓርላማውን አፍርሠው፣ በእኩል ምኅዳር፣ በእኩል የሚዲያ አጠቃቀም የሚወዳደሩበትን ዕድል መንግሥት ፈጥሮ፣ ምርጫ እንዲደረግ ቢያደርግ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለ አንገት ልብስዋ እናውራ። ፍትሕ ላይ ፎቶህን ለጥፈህ መጻፍ ከጀመርክበት ጊዜ ጀምሮ አንገትህ ላይ የምትታየው የአንገት ልብስ (Scarf ) በተለያየ አጋጣሚ ስናገኝህም ወልቃ ተመልክተን አናውቅም። አንተ ብቻ ሳትሆን ባልደረቦችህና የፍትሕ ቤተሰቦችም የአንገት ልብስ አይለያቸውም። የአንገት ልብስዋ መልዕክት ምንድን ነው?

ሻርፑ ራሱን የቻለ መልዕክት አለው።

ልትነግረን ትችላለህ?

ጊዜው ገና በመሆኑ አሁን ልናገረው አልችልም።

‹‹የአንገት ልብስ አብዮት›› የማስነሳት ዓላማ አላችሁ?

በአገራችን ላይ ማንም የማይፈቅድልን፣ ማንም የማይነሳን የፈለግነውን ሕጋዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ሙሉ መብት አለን። ይሄ ጥያቄ ከላይኛው ጋር ስለሚያያዝ ለጥቂት ወራት ቢቆይ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን፣ የአንገት ልብሱ ለብርድ ወይም ለጌጥ የሚደረግ አለመሆኑን መናገር እችላለሁ።

ከዚህ በኋላ በሌላ የፕሬስ ውጤት ትመለሳለህ?

CNNን እንደ ሞዴል ወስደን ከሰዎች ጋር በሽርክና ግዙፍ የሆነ የኦን ላይን ሚዲያ (ድረ-ገጽ) ለመመሥረት ብዙ መንገዶችን ተጉዘናል። አራት የኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ቢሮዎች ይኖሩናል። የምንመለሰው በዚህ መንገድ ነው።

ከመሰናበታችን በፊት በኪስህ ስንት ብር እንደያዝክ ልታሳየን ትችላለህ?

አደጋ ይደርስብኛል፣ አንድ ነገር ያጋጥመኛል ብዬ ስለማስብ ከአምስት ሺህ ብር በታች አልይዝም። ብሩን ላሳያችሁ እችላለሁ፤ ግን አንድ ነገር ላይ መግባባት አለብን። [ሳቅ] ‹‹አበድረን›› የሚል ነገር አልፈልግም። [ስድስት ሺህ አራት መቶ (6,400) ብር የታሰረ፣ ሦስት ሺህ (3,000) ብር ያልታሰረ መያዙን ፊታችን ቆጥሮ አረጋግጠናል] የሥርዓቱ ባሕሪ በፈጠረው የተለያዩ ምክንያቶች ከቤቴ ስወጣ ቀና ነገር ይገጥመኛል ብዬ አስቤ አላውቅም። በተወሰነ መልኩ ገንዘብ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ።

ጨርሰናል። ስለ አብሮ ቆይታችን ከልብ እናመሰግናለን። መልካሙን ሁሉ እንመኝልሀለን።

እኔም አመሰግናለሁ። በእውነቱ ብዙ ጊዜ መናገር የማልፈልጋቸውን ነገሮች እንድናገር ስትገፋፉኝ ስታስገድዱኝ ነበር፤ አስገድዳችሁኛልም። ‹‹Hard Talk›› እንደማለት ነው። ቢሆንም እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጨለማ በነገሠባቸው አገራት፣ ሕዝብ እንዲያውቅ የመረጣችሁበት መንገድ በእጅጉ የሚያስመሰግን እና ፈር ቀዳጅ ነው ብዬ አስባለሁ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>