Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ምርጫ መጣ፤ ምን ይመጣ ይሆን? (ታክሎ ተሾመ)

$
0
0

2007 election

 

መቼም ምርጫ ሲነሳ ብዙ ትዝታዎች መኖራቸው አይቀሬ ነው። በዚህች ምድር ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ጐጅና ጠቃሜ የሆኑ  ብዙ ውጣ ውረዶች ይስተናገዳሉ። ሁሉም እንደየስሜቱ  ክፉና ደጉን የመለየት ባህሪ አለው።  ምርጫ ማለት  ከሁለት ነገሮች አንዱን መምረጥ ማለት ይመስለኛል። አንድ ሰው ምግብና መጠጥ ሊመረጥ ይችላል። የወደፊት ፍቀረኛውን ሊመርጥ ይችላል፤ ሥራም ሊመርጥ ይችላል፤ የሚኖርበትን አገር ይመርጣል። ስለዚህ ምርጫ ሲባል ብዙ ነገሮችን  ይመለከታል።

 

ከላይ ይኽን ካልኩ ዘንዳ  ሕዝብ  ምርጫ  ለምን አስፈለገው  የሚለውን  በመጠኑ  መዳሰስ አስፈላጊ ነው። ሰው የሚለው ሥም  ጥቁር ቆዳ፤ ነጭና ቢጫ ቆዳ፤ የቀይ ዳማ ቆዳ  የሚመስል  መልክ አለው። በዚህ ሁኔታ ሰው የቆዳ  ልዩነት አለው። እንዲሁም ሰው የእምነት፤ የቋንቋ፤ የአመለካከት ልዩነት አለው። ነገር ግን ሰው የሚለው ሥም አንድ በመሆኑ የቆዳ ልዩነት ይታይበት  እንጂ  በሰብአዊ  መብት ዙሪያ ግን ሁሉም እኩል መብት ሊኖረው እንደሚገባ  መጠራጠር  አይቻልም።

 

ከኅብረተሰብ እስከ ግለሰብ የሚደርስ  ሰብአዊ መብቶቹን የሚደነግግ በተባበሩት መንግሥታት ዘንድ  በሕገ- የጸደቀ  መሆኑ አይታበልም። ሰዎች በፈለጉት መንግሥት መተዳደር  እንደሚችሉ ሕገ መንግሥቱ ያዛል። አገራዊ ምርጫ  ሲደረግ  ለአገርና ለሕዝብ  ሊጠቀም  የሚችል  ፓርቲ  ይመረጣል። ነገር ግን  ተግባርና አዋጅ ሥራቸው እየቅል እንዲሉ በአፍሪካ ነፃ ምርጫ  ብሎ ነገር የለም። ቢሆንም ምርጫው ፍትሃዊ ሆነም አልሆነ  የምርጫ  ሰዓት  ሲደርስ  እያንዳንዱ የሚመቸውን የመምረጥ መብት  ያለው  ይመስለኛል።

 

የሰው ልጅ ግን ከእንሰሳት በተሻለ ሁኔታ የማሰብ ችሎታው ከፍተኛ በመሆኑ መብቱን ከሚጨቁኑት፤ ከሚያስርቡት፤ ከሚያስሩት፤ ከሚገድሉትና ከሚያሰድዱት ጋር የሞት የሽረት ትግል እያደረገ ማንነቱን ያረጋግጣል። በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለመኖሩ ሰብአዊ መብቶች አልተከበሩም። ከአጼው እስከ ደርግ ድረስ የነበሩ የፍትህ-ሥርዓቶች የአገር ደህንነትን የተጠበቁ ቢሆንም ሕዝቡን ክፉኛ ያጐሳቆሉ ሥርዓቶች እንደነበሩ አይዘነጋም። ዛሬም ቢሆን ኢሕአዴግ በመጀመሪያዎች ዓመታት ብልጪ አድርጓቸው የነበሩትን የዴሞክራሲ ፍንጮች መልሶ አዳፍኗቸዋል።

 

በኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ አገራዊ ምርጫ ቢደረግም የፖለቲካው ድብብቆሽ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው። ድብብቆሹ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅቶችንም ይመለከታቸዋል። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ኖረም አልኖረ መንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች ምን ጊዜም ይኖራሉ። ነገር ግን ልዩነቶቻቸውን ለአገርና ለሕዝብ ሲሉ አቻችለው መሄድ የማይችሉ ከሆነ የሰው ሕይወትና የአገር ንብረት መውደሙ አይቀሬ ነው። በአገራችን እስከ ዛሬ ድረስ እየታየ ያለው ይህ  እውነታ  ነው።

 

ከላይ ይህን ካልኩ ዘንዳ ከዚህ በፊት በአገራችን የተካሄዱትን አገራዊ ምርጫዎች ምን ይመስሉ እንደነበር መዳሰስ አፈላጊነው። ቢሆንም ሁነቶች ፍትው ብለው ስለሚታወቁ ባለፈ ነገር  ጊዜ ማባከ ትክክል መስሎ ስላልታየኝ ቀጣዩ የ2007 ዓ.ም ብሄራዊ ምርጫ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በመጠኑ ማንሳት ይበጃል። የ2007 ዓ.ም ብሔራዊ  ምርጫ  በምን  መልክ  ይከናወን  ይሆን?  ፓርቲዎችስ ለዚህ ተዘጋጅተዋል ወይ? ሕዝቡስ ምን ሊያደርግ  አስቧል? መንግሥትስ  ቀጣዩን ምርጫ ፍትሃዊ ለማድረግ  ምን  አስቧል? የሚለው ቀጣይ  አጀንዳ ሆኖ ሁሉም ሊያስብበትና ሊመክርበት ይገባል። በየጊዜው የተደረጉ ምርጫዎች አስመሳይ መሆናቸው እርግጥ ነው። ምክኒያቱም መንግሥት ሥልጣኑን  ለሕዝብ  ለማስረገብ እየተቸገረ በሕገ-መንግሥት ያስቀመጣቸውን ሕግጋት ተግባር ላይ ለማዋል  አልደፍረምና።

 

ሙሽራ መጣ ቄጠማ እንዲሉ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ምርጫ መጣ ሲባል ካልሆነ በስተቀር  አስቀድመው ሲዘጋጁ አይስተዋሉም። አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ  ትግሉን እመራለሁ ከማለቱ በፊት ከራሱ ባሕሪ ጋር መጀመሪያ ሙግት መግጠም አለበት። ሙግቱ ትግሉን ለመምራት ብቃቱን፤ ጥንካሬውን፤ መስዋዕት ለመሆኑ ቁርጠነቱን፤ ከግል ዝና መጽዳቱን፤ እውነተኛ  ለሕዝብና ዴሞክራሲ  የቆመ ስለመሆኑ ከሕሊናው ጋር ሙግት መግጠብ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ የነደፈው ፕሮግራም ምን ያህል ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅማል? ሕዝቡስ ፕሮግራሙን ተቀብሎ  መሰረታዊ ሥር-ነቀል ለውጥ እስኪመጣ ድረስ  ከፓርቲው ጋር ይወግናል ወይ? ፓርቲው ከሰርጐ ገቦች የጸዳ መሆኑን  ወዘተ  ሊሟሉ የሚገባቸውን ነገሮች ቅድሚያ አስቀድሞ ማጤን ያስፈልጋል። ነገር ግን በይሁን ይሁን  የመሪነት ሥም በመያዝ ለምርጫ መቅረብ  መሰረታዊ ለውጥ ሊያስገኝ አይችልም።

 

ምርጫው የተወሳሰበና ከአስመሳይነት ሊወጣ ያልቻለበትን  ምክኒያት ብዙ ነው።  ፍትሃዊ ምርጫ እንዳይካሄድ  መንግሥት የሚያደርገው ጫና ቀላል  አይደለም።  ከዚህ በፊት ተደጋግሞ እንደታየው መራጩ ሕዝብ  ነፃ ሆኖ የሚበጀውን እንዳይመርጥ መንሥግስት በግልጽና በጃዙር የሚያደርገው ተጽኖ አስከፊ መሆኑ አይካድም። ፓርቲዎች  ከሕዝባቸው ጋር በየጊዜው እንዳይወያዩ ነፃ ሚያዎችን ገዥው ፓርቲ ያፍናል። በመሆኑም በሚዲያ እጥረት ፓርቲዎች ሕዝቡን ከጫፍ እስከ መሃል መቅረብ  ይቸገራሉ።  የምርጫ አስፈፃሚው አካል ገለልተኛ ባለመሆኑ ተቃዋሚዎች ቢያሸንፉ እንኳን ምርጫ ቦርዱ ተሟሙቶ የድምጽ መስጫ  ሳጥኑ ተገልብጦ ወደ ገዥው ፓርቲ  የድምጽ መስጫ ሳጥን  እንዲገባ  ያደርጋል። ይህ ድርጊት  በተግባር የታየ  ሰለሆነ  ወደፊትም  እኩይ  ተግባሩ  ሊቀጥልበት  እንደሚችል  እገምታለሁ።

 

ባንፃሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ድክመት የለባቸውም ማለት አይቻልም። ምርጫ ሲነሳ ከብዙ ስዎች ጋር ያገነጋግራል። የአገራችን  ፖለቲካ  ድርጅቶች  ምን  ሊመስሉ እንደሚችሉ ከአገር ቤት አንድ ወዳጀ  እንዲህ ሲል ገልጾታል። ” በእኔ ግምትና  እምነት በአሁኑ ወቅት በአገራችን ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ሕዝቡ ሥር የሰደደ ጥላቻ  ባይኖረው  ደካማነታቸውን  ተቀብሎ  ተስፋ   ቆርጦባቸዋል።  ኢሕአዴግ ሕዝቡን  በማስገደድም ሆነ  በጥቅማጥቅም  በመያዙ  በእያንዳንዱ  ንቁጣ  መንደር ሁሉ ስለገባ ዙሪያ ገባው  ጨለማ  መስሎአቸው ፓርቲዎች ሕዝቡንም መፍራትና መጠራጠር  የጀመሩ ይመስላል።

 

ፓርቲዎች ለክፉ ቀን የሚሆን የረባና ጠንካራ መዋቅር የላቸውም። እንቅስቃሴያቸ ሁሉ ለሕልውና ያህል የሚደረግ መፍጨርጨር ሲሆን ብዙዎች ጊዜያቸውን የሚያባክኑት በውስጥ ጉዳይ በመሻኮትና ሌሎች ድርጅቶችን ጠልፎ ለመጣል  በመሮጥ ነው።” ከዚህ ሌላ የመንግሥት ችግር እንዳለ ሆኖ  የአገራችን ፖለቲካ ችግሩ  ውስብስብ ሊሆን  የቻለው  አብዛኛው  ቡድናዊ  ይዘት ሲኖረው እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ ሌላው ይከተል፤ ሃሳብ አይስጥ፤ እኔ ከመሪነት ከወረድኩ ትግሉ የደረቀ ሣር  ይሁን ባዮች በመብዛታቸው ነው። ይሁን እንጂ  አገር ቤት ውስጥ የሚቀሳቀሱ ድርጅቶች ይብዛም ይነስ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ነገር ግን በውጭ  የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ አገር በነፃነት መንቀሳቀስ እየቻሉ  በስሜት ብቻ መወሰናቸው አስገራሚ ነው። ይባስ ብለው  አንዳንዶች ወደ  ዘር  ፖለቲካ  የወረዱ  አሉ።

 

በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በየጊዜው አሸንፊያለሁ የሚለው ገዥው ፓርቲ ነው። ተቃዋሚዎች ለምን የማሸነፍ እድል አላጋጠማቸውም ብለን ብንጠይቅ  የሚሰጡን መልስ  መንግሥት  ሳጥን ገልብጦ  ውጤታችን  ስለቀማን  ነው  ይላሉ። ይህ  እውነት እንዳለ ሆኖ ግን ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ተጨባጭ ሆኔታ ተገንዝበው በጋራ መቆም  ባይችሉም  የየራሳቸውን  ፕሮግራም  ይዘው አንዱ ሌላውን ድርጅት  ሳይተነኩስ  በያሉበት ተቻችለው  ሕዝቡን አሰባስበው ለምርጫ  ማቅረብ አልቻሉም።

 

ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለምርጫ የተሳተፈበት ጊዜ  ቢኖር ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ ነው። የግንቦቱ 7 1997 ዓ.ም አገራዊ መርጫ ተካሂዶ በነበረበት ወቅት ተቃዋሚዎች የሕዝብ ድምጽ ማግኘታቸው  አይታበልም። ነገር ግን ያን ድምጽ ሊያገኙ የቻሉት ጥንካሬ ኖሮቸውና ሕዝብ  አምኖባቸው ሳይሆን አማራጭ  በማጣት እንደነበር  ብዙዎች  ይስማሙበታል። ቅንጅት ውስጥ የተሰባሰቡ ቀስተዳመና እዴፓ መኢአድ እውነት ልብ ለልብ ተገናኝተው ነበር ወይ? እውነት ለመስዋዕትነት ተዘጋጅተው  ነበር  ወይ?  እውነት 15 ቱ  አድርጅቶች  በኅብረት  የተሰባሰቡት ከልባቸው ነበር ወይ? ብለን ስንጠይቅ ከማስመሰያነት ውጭ በእውነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳልነበራቸው ብዙ የሚያመላክቱ ሁነቶች ነበሩ።

 

የኢደፓ ሊቀመንበር  የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው በሚፈጥሩ የማስመሰያ ቃላት በቅንጅት ውስጥ የሚደረጉ ስብሰባዎች የአንዳንዶችን ስሜት ማሻከሩ አልቀረም።  እንደምናስታውሰው በቅንጅት ውስጥ በተፈጠረው የእርስ በርስ ጥርጣሬ የቅንጅት ምስጢሮች እየሾለኩ ከመንግስት ጀሮ ይደርሱ ነበር። ፓርላ መግባት፤ አለመግባት የለም የተሰረቀውን ድምጽ ማስመለስ አለብን በሚለው ዙሪያ  ከቅንጅ ሰርገው የገቡ ሰዎች አመራሩን ውዥንብር  ፈጠሩበት። የመጣው ይምጣ የሕዝብ ድምጽ ተሰርቆ ፓርላማ አንገባም ብለው  በአቋማቸው የጸኑ አመራር አባላት ታሰሩ፤ ተንገላቱ፤ ቤተሰቦቻቸው ሳይቀሩ ችግር ላይ ወደቁ።

 

በዚህ ጊዜ ድምጽ ሰጥቶ የመረጣቸው ሕዝብ ከሞላ ጐደል የታሰሩትን ለማስፈታት ከጫፍ እስከ መሀል አገር ሕዝቡ ሆ ብሎ ሊነሳ አልቻለም። ዲያስፖራው ግን  ሰላማዊ ሰልፍ  በማድረግ በሃሳብ ከጐናቸው  እንደነበር አይዘነጋም። ለታሰሩ የቅንጅት አመራር አባላት ቤተሰቦች የተቻለውን ያህል የገንዘብ ድጐማ ማድረጉን አስታውሳለሁ። በጨረሻም የቅንጅት አባላት ብዙ መከራና እንግልት ከደረሰባቸው በኋላ  ለግንቦቱ 7 1997 ዓ.ም ምርጫ ሁከትና  እልቂት ጥፋተኛ ነን ብለው ይቅርታ ጠይቀው ከቃሊቲ መውጣታቸው የማይረሳ የትላንት ትዝታ ነው። በዚህ ጊዜ ለተነሱለትና  ለአመኑለት ዓላማ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ለምን አልቆሙም ያሉ ወገኖች ነበሩ።  በሌላ በኩል ፍርሃት ተሰምቷቸው ድፍረት እንኳን ቢያንሳቸው ያገኙትን  ወንበር  በመያዝ  አዲስ አበባን እያስተዳደሩ  ለለውጥ ተስፋ መሆን ነበረባቸው ያሉም ነበሩ።

 

ከዚህ ላይ አንድ እውነታ አለ። ለውጥ እንዲመጣ ቀስቃሽ ያስፈልጋል፤ የድርጅት መሪዎች ደግሞ ትግሉ ስኬት እንዲያመጣ የግድ የማያቋርጥ የሕዝብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ዴሞክራሲ ተጠማሁ ያለ ሕዝብ መሪዎቹ ሲታሰሩ እጁን አጣጥፎ  መቀመጥ የለበትም። ሕዝቡ የተሰረቀበትን  ድምጽ  ለማስመለስ ትግሉን ማቆም ያለበት አይመስለኝም። ስለዚህ ችግሩን የመሪዎች ብቻ ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም።

 

ከዚህ በፊት እንዳልኩት ለውጥ ሊመጣ የሚችለው አገር ውስጥ በሚደረገው ሰላማዊ ሕዝባዊ  የተቃውሞ ትግል  በማድረግ  ነው። የአገር ቤት ተቃዋሚዎች ጥንካሬያቸው አስተማማኝ ባይሆንም በተቃውሞ ሥም እየተንቀሳቀሱ  ነው። እንደሚመስለኝ ከሆነ የፓርቲዎች ችግር አንደኛ የመንግሥት ሰርጐ ገቦች በሚያደርጉት የውስጥ አሻጥር  የድርጅቶች የውስጥ ጥንካሬ  ደህና አይደለም።  እንዲሁም  የውስጥ  ሽኩቻ  አለባቸው። የተለያዩ ፓርቲዎች ዓላማቸው በአገራቸው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ ሥልጣን የሕዝብ እንዲሆን የሁላቸውም  ፍላጐት  ይመስለኛል።

 

ነገር ግን አንድነት፤ ውህደት የምትለው ቃል ለምን  እንደምታስፈራቸው  በውል ይህ ነው ማለት ባይቻልም አንዳንዶች የፓርቲ መሪነትን ሥልጣን ማጣት ስለማይፈልጉ ይመስለኛል። ድርጅቶች እንደ ቁጥራቸው ብዛት ፕሮግራማቸውም የተለያየ ነው።  ስለሆነም የአመለካከት ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን  ለአገርና ለሕዝብ ሲባል መሰረታዊ ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት ለምን በጋራ ወይም በያሉበት ተከባብረው ጠንክረው መቆም አቃታቸው የሚለው አሳሳቢ ነው። ስለዚህ የድርጅቶችን አደረጃጀትና  ጥንካሬ ሲቃኝ እጅግ  ውስብስብ  ነው።

 

ተደጋግሞ እንደታየው ድርጅቶች በሥልጣን ይገባኛል በየመድረኩ እስጥ አገባ ሲሉ ይደመጣሉ።  የሚያስገርመውና  የውስጥ ችግሮቻቸውን በሰለጠነ  ሁኔታ ሳይፈቱ፤  ሕዝብ ሳያደራጁና በቂ አባላት ሳይኖራቸው  በብዙ ችግር የተወሳሰበቸውን አገርና  ሕዝብ መምራት  እንችላለን  እያሉ ሲናገሩ  መደመጣቸው ነው። ምኞታቸው ባልከፋ እስየው ያስብላቸዋል። ግን መጀመሪያ አገርና ሕዝብ መምራት እንችላለን ከማለታቸው በፊት ዴሞክራሲን መልመድ ግድ ይላቸዋል። ሌላው የድርጅቶች ድክመት ወይም ችግር ስለኅብረት ትግል በየጊዜው ያወራሉ። ነገር ግን ሌሎች ወደ እነሱ ተጠግተው  ኅብረት እንዳይፈጥሩና ሥልጣን  እንዳይጋሩ በብረት መጋረጃ  በማጠራቸው ኅብረት የሚባለው ከይስሙላ ባለፈ  ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ተሞክሮው ተጨምሮበት ማለቴ  ነው። ይህ ሲባል የማንንም ሞራል ለመንካትና ዝቅ ለማድረግ ሳይሆን  ከሚታየው እውነታ በመነሳት ነው።

በየጊዜው  የተለያዩ  ሰላማዊ  ሕዝባዊ  የተቃውሞ ሰልፎች  ይደረጋሉ። ደም ያልፈሰሰበት ለውጥ ማምጣት ከሁሉም በላይ  ይመረጣል። ነገር ግን የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ግራ ማጋባታቸው አልቀረም። የአንድነት ፓርቲ  ስልፍ ሲጠራ ሌሎች ከጐኑ ቆመው ሰልፉን መቀላቀል ሲችሉ በርቀት ይመለከታሉ። አንድነት ፓርቲ ሰልፉን ካጠናቀቀ በኋላ  ወር ጠብቆ  ሌላው ፓርቲ  ወይም ድርጅት ሰላማዊ  ሰልፍ  ይጠራል። የዚህ ዓይነት የተሰበጣጠር ትግል የት ሊያደርስ እንደሚችል ግልጽ ነው። ስለዚህ የተቃዋሚዎችን እየርስ በርስ ፉክክር ማመላከት ብቻ ሳይሆን የእውነትን  መንገድ አለመከተል ቁልጭ አድርጐ  ያሳያል። “ለተቀማጭ  ሰማይ ቅርቡ” ካልተባልኩ የተናጥሉ ሰላማዊ  ሕዝባዊ  ሰልፍ  ውጤት አያመጣም።  ስለዚህ በተቻለ መጠን የፕሮግራም ልዩነት ቢኖርም እንኳን  አንዱ ፓርቲ የሚጠራው  ሰላማዊ  ሕዝባዊ የተቃውሞ  ሰልፍ  ሁሉን  ሊመለከታቸውና ሊተባበሩ ግድ እንደሚላቸው የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

 

እስከ ዛሬ  አንድነት፤ ኅብረት፤ ውኅደት እየተባለ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ተሞክሮ አልተሳካም። ወደፊትም ቢሆን በዚህ አካሄድ አይሳካም። ሥር ነቀል ለውጥ  እንዲመጣ  ከተፈለገ  እያንዳንዱ ፓርቲ የራሱን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ ድርጅቱ ከሰርጐ ገቦች ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ከዛም  ለአንዲት ኢትዮጵያ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ከሕዝቡ ጐን ሆኖ ከታገለ ስኬታማ ሊሆን ይችላል። ይህን ሲያደርግ ግን ሌሎች ድርጅቶችን በጥላቻ ዓይን መመልከት የለበትም።  የእያንዳንዱ ፓርቲ ማንነት የሚለካው  በሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው። ሥልጣን ሊይዝ የሚችለው የሕዝቡን አመኔታ ሲያገኝ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ፓርቲ   በምርጫ ተሳትፎ የሚያገኘው የሕዝብ ድምጽ ይወስነዋል ማለት ነው። ብዙ ድምጽ ያገኘ መንግሥት ሲሆን ትንሽ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎች እንዲሁ የያዙትን ወንበር ይዘው ወደፊት ፕሮግራማቸውን አሻሽለው ሕዝብ እያደራጁ ለቀጣዩ ምርጫ መዘጋጀት ይችላሉ። ስለዚህ ጨቋኙን ሥርዓት ለማስወገድ የግድ ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸው መጐሻሸም የለባቸውም። ነገር ግን ተቃዋሚ ሆነው እርስ በርሳቸው ፍክክርን ከመረጡ ተጠቃሚው መንግሥት መሆኑ አይቀሬ ነው።

 

ከላይ ይህን ካልኩ ዘንድ ዛሬ ማሰብ የሚገባን ካለፈው ስህተት እንዴት እንማር የሚለው  እንጅ  ያለፈ ታሪክ መውገጥ አያስፈልግም። ይህች ዓለም በሥልጣኔ  ወደፊት እየገሰገሰች ነው። ጊዜያችሁን ተጠቀሙብኝ እያለች ነው። በተለይ በዉጩ ዓለም የሚኖሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ደጋፊዎች በአጠቃላይ ዳያስፖራው  ከሰለጠነው ዓለም ብዙ ነገሮችን መቅሰም ይችላል። ከአገር ቤት አንድ ወዳጀ  እንዲህ ሲል ይመክረናል። “ ያለንበት ዘመን የሥልጣኔና  የእውቀት ዘመን ነው፤ እንደ ጥንቱ እንደ ጀግኖች አባቶቻችና እንደ አሁኖቹ ገዥዎቻችን  አገርን  በስሜትና በግምት  መምራትና ማሰልጠን  አይቻልም። በአገራችን  ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ጥርት ያለና ግልጽ አገራዊ ራዕይ ያላቸውና  የተለያየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠር አለባቸው። ወይም አሁን ያሉት በሀገራችን እናሰፍናለን የሚሉትን የሕገ የበላይነትና  ዴሞክራሲያዊ  አስራር  ቢያንስ  በራሳቸው  መካከል  በመለማመድ  መጠናከር  አለባቸው።

 

ሁሉም ወይም  አብዛኛው አገር  ወዳድ  ወገን ሁሉ አሁን የሚታየው  ግዴለሽነና  ራስ  ወዳድነት  ተወግዶ  በሀገሩ ጉዳይ ያገባኛል የሚል አስተሳሰብ  እንዲኖረው  በማድረግ በኩል የፓርቲዎች  ዋነኛ  የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል። ጠቅለል ባለ መልኩ የጠንካራ ድርጅቶች ጥያቄ ምላሽ ከአገኘና ችግሮቻችን ላይ በጥሞና መነጋገር፤ መግባባትና  መተባበር  ከተቻለ  የምንፈልገውን ሁሉ  ለውጥ ማምጣት  እንችላለን።”

 

ቀደም ሲል እንዳልኩት ተበላሸም አልተበላሸ  የ2007 ዓ.ም  አገራዊ ምርጫ መካሄዱ አይቀሬ  ነው። በመሆኑም  አገር ቤትና ውጭ  የሚገኙ  ፓርቲዎች ለመጭው ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ  ስለመሆኑ መረጃ የለኝም። ቢሆንም  እየተዘጋጁ  ይሆናል  የሚል ግምት መስጠት ይቻላል። ምርጫው ሁሉን የሚያሳትፍ ቢሆንም የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ውስብስብ በመሆኑ ለፓርቲዎችም ሆነ ለመራጩ ከፍተኛ ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል  እገምታለሁ።  መንግሥት  የፓርቲዎችን  መኖር  ስለማይፈልግ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ መንገዱን ሁሉ  ዘግቶባቸዋል። ጋዜጦችም ቢሆኑ  መንግሥትን  የሚያወድሱ  ካልሆኑ  የተቃዋሚዎችን ሃሳብ የሚያንጸባርቁ ጋዜጦች ታግደዋል። ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቶች የበጀት እጥረት ሊኖርባቸው እንደሚችል እገምታለሁ። ሕዝቡም ቢሆን ከዚህ ቀደም በምርጫ ተሳትፎ  ተደጋጋሚ ጊዜ ሽንፈት ስለደረሰበት ተስፋ የቆረጠ ይመስላል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙን ከሆነ  መንግሥት የምረጡኝ ቅስቀሳ ጀምሯል። ባንፃሩ በተቃዋሚዎች በኩል የምረጡኝ ዘመቻ በሁሉም ክፍላተ-ሀግራት  መጀመር  አለባቸው። ሕዝቡም ከተቃዋሚዎች ጐን በመሰለፍ የማቲሪያል የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግላቸው  ግድ ይላል። “የተሳለ ካራ” የእግር ኮቴ አቸውን  እየተከተላቸው የሕዝብ ደሮ ድምጽ የሆኑ ጀግና ጋዜጠኞች የሕዝብ  ድጋፍ  ያስፈልጋቸዋል።  ነገር ግን አብዛኛው ሕዝብ እሩቅ ሆኖ ተቃዋሚዎች  ለውጥ ያመጣሉ ብሎ  የሚገምት ከሆነ  ስሌቱ የተዛባ ይሆናል። በ2007 ዓ.ም ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ገዥው ፓርቲ አሸነፍኩ ለማለት የተለያዩ ዘዴዎች እየተጠቀመ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

የአዲስ አበባ መስተዳደር ከሕዝቡ ጋር በተለያየ መንገድ ግንኙነት እንዳለው አይታበልም። በየጊዜው ነዋሪውን እየሰበሰበ ስለ መልካም አስተዳደር መስበክ ከጀመረ ሰነባብቷል። የትራንስፖርት ችግር፤ የውሃ፤ የመብራት አገልግሎት ይሟላል፤ ሥራ አስጥነት ይወገዳል፤ ወደፊት ኅብረተሰቡ በኢኮኖሚ በትምህርት በልማት፤ የባቡር አገልግሎት ተጠቃሚ  እንዲሆን ሌት ተቀን እየሰራን ነው ማለቱን በወቅቱ ስብሰባ ላይ ከነበሩ አንድ አዛውንት አረጋግጫለሁ።

ሕዝቡ የትራንስፖርት፤ የውሃ፤ የመብራት ችግር እንዳለበት አይካድም። ከንቲባውና ሽማምታቱ ችግሩን እንቀርፋለ ማለታቸው መቼስ ተስፋ ጥሩ ነውና አባባላቸው አይጠላም። ግን  የገዥውን  ፓርቲ  ባህሪ አተኩረን ስንመለከት ዴሞክራሲያዊ  እንዳልሆነ ነው። ምርጫ ሲቃረብ የኅብረተሰቡን ችግር እቀርፋለሁ፤ ኢኮኖሚ ያድጋል፤ ዴሞክራሲ  በሽበሽብ  ይሆናል  ይላል። ነገር  ግን  ከምርጫ በኋላ የውሃና የመብራት ችግር  አይኖርም፤ የዋጋ ውድነት፤ የህክምና አገልግሎት እጥረት ይወገዳል ግድ የላችሁም “በኢሕአዴግ ይሁንባችሁ”ማለቱ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ተደጋግሞ እንደታየው ተግባር ላይ ይውላል ብሎ መገመት ጉም መጨበት ይሆናል።

 

ለማጠቃለል ያህል፦ ያለፈው አልፎ  ወደፊት ለዜጐች እኩልነት፤ ለዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አንድነት  እንታገላለን የሚሉ ሁሉም ዜጋ በቋንቋ፤  በዘር፤  በሃይማኖት ልዩነት ሳይወሰኑ ስፋ አድርገው እየተመለከቱ በአንዲት ኢትዮጵያ ላይ ማተኮር  ይጠበቅባቸዋል። ይህ  የተሰበጣጠረ  ውጥንቅጡ  የወጣ  በቡድንና  በአካባቢ መደራጀት የትም ስለማያደርስ መቆም አለበት። የእከሌ ዘር ጨቋኝ፤ የእከሌ ዘር ተጨቋኝ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ኦሮሞ፤ አገው፤ ጉራጌ ወዘተ እያሉ መከፋፈሉ አገራችን  እየጐዳ  ነው። መጭውን  ትውልድ፤ አገርና ታሪክ አልባ እንዳይሆን ከወዲሁ መጠንቀቅ ተገቢ ይመስለኛል።

 

እያንዳንዱ ሊያስብበትና ሊጠነቀቅበት የሚገባ የዘር ፖለቲካን  እያወገዝ  እግረመንገዳችን  በዘርና  በቋንቋ  መደራጀትን  ከመረጥን  እንዴት ሕወሃትን  ዘረኛ ልንለው  ህሊናችን  ሊፈቅድ  ይችላል የሚለው ነው። ምክኒያቱም መጀመሪያ ዘረኛ ከሚባለው ተሽሎ መገኘት አዋቂነት ብቻ ሳይሆን ግዴታ ሊሆን ይገባል።  በዘር መደራጀት ካንሰር ነው። በዘር መደራጀት  ያለፈ ታሪካና  መውጭውን  ትውልድ  ያረክሳል። ስለዚህ አንዳንዶች  ለእለት ፍጆታ ብለው ውጭ ሆነው መደበሪያና  የገንዘብ ማግኛ  ዘዴ ለማድረግ ሲባል ከዚህ በፊት ያልታየ ዘር ቆጠራ የትም አያደርስ።  ስለዚህ ዘርን  ያማከለ  ቅስቀሳ የሚያካሂዱትን በቃችሁ መስመር  አልፋችኋል ብለን  ፌሽካ ነፍተን  ልናስደነግጣቸው ይገባል። ይህች አገር የሁሉም ናት፤ ማንም ተነስቶ በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ወሳኝ ሊሆን  አይፈቀድለትም። ድብብቆሹ  በዚህ ከቀጠለ  አደጋው ሊከፋ እንደሚችል መጠርጠር ቢያንስ ነው። የፉክክር ቤት  ሳይዘጋ  ያድራል  እንዲሉ  ቆም ብለን  መዝጊያ  ልናበጅለት  ግድ  ይላል።

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>