Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሰሚ ጆሮ ያጣ የሕዝብ እሮሮና ጩኸት እስከመቼ? (ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌይ ሌና)

$
0
0

ገዛኸኝ አበበ ከኖርዌይ ሌና

Gezahegn Abebeዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ ካለችበት የኢህአዲግ ስርአት ለመላቀቅ እና ከገባችበት ፖለቲካዊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሜያዊ ውድቀት ወጥታ ህዝቡም ከወያኔ ስርዓት ተላቋ ወደ ተሻለ እና ወደ ተረጋጋ ሕይወት ለመድረስ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እና በሁሉም አቅጣጫ እና በሚችለው መንገድ መታገል ይጠበቅበታል:: ዛሬ ላይ ወያኔ ኢህአዲግ የእምነታችንን ነጻነት እያሳጣን የዜጎቻችን ሰብዓዊ መብት እየረገጠ እና የዜግነት ክብራችንን እና ነፃነታችንን በመግፈፍ የባርነት ኑሮ እየኖርን እንገኛለን::  መቼም በአሁኑ ጊዜ በጨቋኙ የወያኔ ስርአት ያልተማረረ የህብረተሰብ ክፍል ያለ አይመስለኝም ስለሆነም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ሀይማኖት፣ ዘርና፣ቋንቋ ሳይዘው ሊጠይቀው የሚገባ የመብትና የነጻነት ጥያቄ ሊሆን የሚገባው  እስከ መቼ ? በወያኔ መንግስት የግፍ ስርዓት  እየተጨቆኑ መኖር ብለን እራሳችንን ልንጠይቅ ያስፈልጋል::

በርግጥ በአሁኑ ሰአት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀገር ቤትም የሚኖረው ከሀገር ውጭ ተሰዶ የሚኖረውም (ዲያስፖራ) ኢትዮጵያዊ በሚችለው መንገድ ሁሉ ወያኔንን በመቃወም እና በመፋለም የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውንም ግፍ እና በደል ለአለም ህዝብ እና መንግስታቶች ለማሳወቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ  እንዳለ ይታወቃል::በተለይም  በወያኔ መንግስት ጨቋኝ እና ዘረኛ አገዛዝ ተጠቂ የሆነው በሀገር ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሕዝባችን ከማንኛውም ጊዜ  በባሰ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ እና እየደረሰበት ካላው ችግር የተነሳ በየጊዜው ድምጹን እያሰማ እንዳለ ይታወቃል:: በሀገር ውስጥም ሆነው መሰዋህትነትን  እየከፈሉ ያሉ  በሰለማዊ ትግል የወያኔን አቅም ማሽመድመድ እና ከስልጣን ማስወገድ ይቻላል በማለት አምነው እና ቆርጠው የተነሱት እንደ ሰመያዊ ፓርቲ እና አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ የመሰሉ ፓርቲዎች ሕዝቡ ብሶቱን እና ምሪቱን በአደባባይ እንዲያሰማ  እያደረጉት ያለው ሰላማዊ ትግል የሚያስመሰግናቸው ነው :: እነዚህ ፓርቲዎችም  የኢትዮጵያ ሕዝብ ህገ መንግስታዊ መብቱን እንዲያስከብርና ለነጻነቱም እንዲታገል እያነቁት ሲሆን ፣ በአሁኑ ሰአት ለመብቱ እና ለነጻነቱ በየጊዜው ድምጹን እያሰማ እና በአደባባይ እየጮኸ  ይገኛል :: ቢሆንም ሀገርን እመራለው ሕዝብንም አስተዳድራለው ብሎ ከተመጠው መንግስት ነኝ ባይ አካል ግን ምንም አይነት የሕዝቡን እሮሮና ጩኸት አዳምጦ የሕዝብን ጥያቄ የመመለስ ነገር አይታይም::

የኢትዮጵያ ሕዝብም ሕገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ሀገርን እመራላው ብሎ ለተቀመጠው አካል ድምጹን ማሰመትና መብቱን መጠየቅ ሕገ መንግስታዊ መብቱ ቢሆንም ነገር ግን ይሄ መብቱ ሲከበርለት አይታይም :: በወያኔ መንግስት በኩል በተቃራኒው የሚሆነው ግን ሌላ ነው ሕዝቡ ብሶቱን ለማሰማት በተነሳ ጊዜ ዜጓችን ማዋከብ፣ ማስፈራራት፣ ማሰርና፣ የተለያዩ በደሎችን በዜጎቹ ላይ መፈጸመ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ አሳሳቢ የሆነና የወያኔ መንግስት የለመደው የእለት በእለት ተግባሩ ሆኖል::

በርግጥ በአሁኑ ጌዜ የምርጫም ጊዜም እየደረሰ ከመሆኑም የተነሳ ሕዝብን ለማታለልና በኢትዮጵያ ላይ ዲምክራሲ እንዳለ ለማስመሰል በምህራባውያን ዘንድ የፖለቲካ ቁማሩ እንዳይበላሽበት በፓርቲዎች ጥያቄ ሳይወድም ቢሆን በስንት መከራ ሰላማዊ ሰልፎችን የማድረግ መብትን የፈቀደ ቢመስልም  ሕዝብን እና የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችን ግን በአይነ ቁራኛ በመከታተል ፣ በማዋከብ፣በማሰር ላይ ይገኛል:: ሕዝቡ በተለያያ ጊዜ በሰላማዊ ሰልፎች በየጊዜው ጩኸቱን እያሰማ ቢሆንም የሕዝብ ጩኸት ግን  አዳማጭ ያገኘ አይመስልም:: በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች ሕዝቡ  እየጠየቀ ላለው ጥያቄ የወያኔ መንግስት የሕዝብን ጩኸት ሰምቶና አዳምጦ መልስ ይሰጣል ብሎ ማሰብ ሲበዛ እጅግ የዋህነት ይመስለኛል:: የወያኔ መንግስት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር፣ መከራ ምንም የማያሳስበው መንግስት እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ያየነውና የተረዳነው ነገር ሲሆን በአለም ላይ በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሮ ሕዝቦች መካካል በአሁኑ ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ እየተዋረደና መከራ እየደረሰበት የሚኖር ያለ ሕዝብ ያለ አይመስለኝም በቅርቡ እንኮን እንደምናስታውሰው በሳውድ አረቢያ በጨካኝ አረመኔ አረቦች ሕዝባችን በአደባባይ እንደ በግ ሲታረድ በአለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት በኢትዮጵያዊ ስሜት በጩኸት ድምጻቸውን ሲያሰሙ በጊዜው በወያኔ መንግስታቶች ዘንድ የሕዝባችን እንደ በግ በአደባባይ መገደል እንደ ምንም ነገር ቦታ ያልተሰጠው ጉዳይ እንደነበር እና የወያኔን መንግስት በብዙዎች ዘንድ ለትዝብት የዳረጋቸው ክስተት እንነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው ::

ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ላይም መኖር አቅቶታል ጮኸቱንም ያሰማል የሕዝቡም ጩኸት ማብቂያ ያለው አይመስልም ሰመያዊ ፓርቲም ቢሆን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በአሁን ሰአት ሕዝቡ ብሶቱንና በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ እንዲያሰማ በየጊዜው የሰለማዊ የተቀውሞ ሰልፎችን እያዘጋጁ እና በወያኔ መንግስት ላይ የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ቢሆኑም  የወያኔ መንግስት ግን የሕዝብን ጥያቄ የመመለስ አዝማሚያ አይታይበትም  ነገር ግን  በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሕዝብን እሮሮና ብሶት ማዳመጥ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታው ነው፡፡ እነ እስክንድር ፣ርዕዮትና ፣ አንዶለም ሌሎቹም የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች  በየእስር ቤቶች ውስጥ በእስር በማቀቅ ላይ ባሉበት ሁኔታ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የአለም የሰባሃዊ መብት ተከራካሪዎች ሳይቀሩ ያለበደላቸውና ያለሀጢያታቸው በግፍ በእስር ላይ ያሉ እስረኞች  ከእስር እንዲፈቱ በየጊዜው በመጠየቅና በውጭ ሀገርም በሀገር ውስም የሚኖሩ ኢትዮጵያ ዜጎች በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች በመሰብሰብ ስለወገኖቻችን ቢጮኽምጩኸቱም ሰሚ ጆሮ ያጣ እየሆነ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ሕዝብ በየጊዜው ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች ከእስር እንዲፈቱ በሰላማዊ ሰልፎች ይጮኻል ነገር ግን የወያኔ መንግስት ህገ መንግስቱን አክብሮና የሕዝብን ጩኸት ሰምቶ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት ሲገባው ያለምክንያት ያስራቸውን ዜጓች ከእስር ከመፍታት ይልቅ የሕዝብን ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ከቀን ወደ ቀን ሕዝብን በማተራማስና ሌሎች ንጹሃን ዜጎችንም እያደኑ በመያዝና በማሰር ስራ ላይ ተደምጦል::

 እነ አንዷለም አራጌ ፣እነ በቀለ ገርባ ፣ እና ናትናሄል እና ሌሎችም እስረኞች ከቃሊቲ እንዲወጡ ሕዝብ እየጮኸ ባለበት ሁኔታ ሌሎች በብዙዎች የሚቆጠሩ አንዷለሞች፣ ሌሎች በቀለዎች፣ ሌሎች ናትኖሄሎች ለእስር እየተዳረጉ ነው እነ ርዕዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸትንና ሌሎች በግፍ የታሰሩ ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ እየጮኽን ባለንበት ሁኔታ ሌሎች ርዕዮቶችና ሌሎች እስክንድሮች፣ ሌሎች ውብሸቶች ወያኔ በሚያቀርባቸው የሃሰት ውንጀላዎች እየተከሰሡ ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ ሲሆን  ሰሞኑንም እያየን ያለነው ያለነው ይኼንኑ ነው :: ሕዝብን አስሮ የማሰቃየት ሀባዜ የተጠናወጠው አንባ ገነኑ የወያኔ መንግስት በማን አለብኝነት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ሌሎች  ጋዜጠኞችን በማያዝ አስሯቸዋል::እነዚህ ወገኖቻችን  ምንም የተደበቀ አጀንዳ የሌላቸው ግን ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይከበር ያሉና በህገ መንግስቱ መስረት የሕገ መንግስቱን አንቀፅ እየጠቀሱ የሃሳብ የመግለፅ መብታቸውን የተጠቀሙ ሶስት ጋዜጠኞችን እና ስድስት ብሎገሮችን በተለያየ የሀሰት ወንጀል በመወንጀል ለእስር መዳረጉ ወያኔ ምን ያህል በእምቢርተኝነት ልቡን እያደነደነ ያለ አንባ ገነን መንግስት እንደሆነ በገሃድ ቁልጭ አድርጎ ያሳይ ሀቅ ነው::  ይህ ሁሉ ግን የሚያሳያው ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ዜጎችን በተለያየ የሀሰት ውንጀላ በመወንጀል ማሰረኑንና ሕዝብን ማሰቃየቱ እንደማይቀር የሕዝቡም ስቃይ፣ መከራ፣ እስራታ እና ግድያ እስከ መቼ እንደዚህ ይቀጥላል ? የእኔም ጥያቄ የብዙዎቻችን ጥያቄ የወያኔ አንባ ገነንተ እስከ መቼ ? ሰሚ ጆሮ ያጣው የሕዝብ ሮሮ እና  ጮኸትስ እስከ መቼ ?

እንደእኔ አመለካከት ህዝባችን በሚያደርገው ሰላማዊ ሰልፎች አረመኔው የወያኔ መንግስት ለሕዝቡ ጥያቄ  መቼም ቢሆን መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ  ይሆናል ብዪ አላስብም::ነገር ግን የወያኔን መንግስት ይበልጥ ሊያዳክሙ የሚችሉትን ስልቶችን ( strategy) በመንደፍ ትግላችንን ብንቀጥል ወያኔን ማንበርከክ ይችላል የሚል እምነት አለኝ:: ለነገ የሕዝብ እሮሮ እና ጩኸት ተሰምቶ ህገ መንግስቱ የሚከበርባትንና ዜጎች በነጻነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እየተመኛው ለዛሬ ጹሁፊን ላጠቃል ::

ውድቀት ለአንባ ገነኖች!!
  gezapower@gmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>