ከአቤ ቶክቻው
በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ እያሰማ ነው። መንግስትም በበኩሉ የፈሪ ዱላውን እያወረደው ይገኛል። እውነቱን ለመናገር መፍራት ተቃወሞ የሚያመጣ ተግባር ሲፈጽሙ ነበር እንጂ ተቃውሞውን አለነበረም።
ኢህአዴግዬ በክላሿ ተማምና ያላስቀየመችው የህብረተሰብ ክፍል ካለ እርሱ ኢህአዴግን እንደ ግል አዳኙ የተቀበለ ብቻ ነው። ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላየ እየተወሰደ ያለው ርምጃ በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል ጎንደርም እየተወሰደ ይገኛል ይሄው አይነት ከዚህ በፊት በጋምቤላ፣ በአዲሳባ፣ በደቡብ ብሄር በሄረሰቦች ክልል ሀዋሳ እና ተረጫ ወረዳ ላይ እንዲሁም በቅርብ ጊዜ በሀረሪ ከልል ሀረር ላይ ሲወሰድ ነበር። (እነዚህ በቀላሉ ያስታወስኳቸው ናቸው ማስታወሻ ብናገላብጥ ደግሞ ሌላም ሌላም ይገኛል)
በጥቅሉ እነደ ኢህአዴግ ያሉ ”ፋራ” አምባገነኖች ለሰላማዊ ተቃወሞ ሰላማዊ ምላሽ ሲሰጡ ታይቶም አይታወቅ። እኛ የምንጸለይ የነበረው ኢህአዴግ ገደላውን ትታ የምትጠየቀውን እንደ ዘመናዊ ገዢ ፓርቲ፤ በቅጡ ብትመልስ ነበር። ግን አልሆነም። በዚህም የተነሳ እስከ አሁንም ድረስ በኦሮሚያ ክልል ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ዜጎች በአልሞ ተኳሾች እና ሳያልሙ ተኳሾች ተገድለዋል ቆስለዋልም።
ይህ ህመም የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች እና ዘመዶቻቸው ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ነው። ሰለዚህም ሁሉም በያለበት እና በየ አቀሙ ጩኸቱን ሊቀባበል ይገባል የምለው።
“አንተ ውጪ ቁጭ ብለህ….”
ወጪ ሀገር የሚገኝ ሰው የሚገጠመው ትልቁ ፈተና ይሄኔ ነው። ጩኸቱ የጋራ ነው ብዬ ስናገር አንዳንድ ወዳጆች ገና አንብበው ሳይጨረሱት ሁላ “አንተ ውጪ ቁጭ ብለህ እኛን ልታስጭርስ” የሚል አስተያየት ለመጻፍ ሲያቆበቁቡ ይታየኛል። በተወሰነ ደረጃ እወነትም ውጪ ሃገር የሚገኝ ሰው “አይዟችሁ አትፍሩ በረቱ…” ብሎ ለማለት የሞራል የበላይነት እንደሌለው አምናለሁ።
ስለዚህም አትፍሩ ብዬ አልመክርም። ነገር ግን እየፈራንም ቢሆን፤ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ጩኸቱ የጋራችን እንደሆእነ ልናሳይ ይገባል፤ ይሄ ማለት የግድ አደባባይ ውጡ ብሎ ማደፋፍር አይደለም። ቢያንስ ግን ከገዳዮቹ ጋር ባለመተባበር ጩኸቱ እና ኡኡታው የእኛም መሆኑን ማሳየት እንችላለን ለማለት ነው።
በተጨማሪም በተለያዩ ሰለፎቻችን ላይ፤ ለምሳሌ ነገ በሚካሄደው የአንደነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የእሪታ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ከሚያሰማቸው እሪታዎች አንዱ በኦሮሚያ እንዲሁም በአማራ ክልል ጎንደር ላይ እየተደረገ ያለውን የሰላማዊ ዜጎች ጭፈጨፋ የሚያወግዝ ሊሆን ይገባዋል የሚል እምነቴን ለማካፈልም ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በጎንደርም ሆነ በኦሮሚያ አካባቢዎች እየተደረገ ያለውን ግድያ በሶሻል ሚዲያዎቻችን እና ባገኘነው አጋታሚ በማሰራጨት ጩኸቱ የጋራችን መሆኑን እናሳይ ለማለትም ነው። ምክንያቱም አንድም ዛሬ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየደረሰ ያለው ትላንት ብብዙዎች ላይ ደርሷል፤ ነገም በእያንዳንዳችን እንደማይደርስ ዋስትና የለንምና ነው!
በመጨረሻም
ህይወታችውን ላጡ ነፍስ ይማርልን!
ለቆሰሉት ምሀረትን ይስጥልን!
የሚገድሉትንም ክላሻቸውን ያክሽፍልን!
አሜን!