ጠ/ሚ ኃይለማሪያም በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ
(በፋክት መጽሔት ቅጽ 2 ቁጥር 33 የካቲት 2006 ታትሞ የወጣ)
ሕፃን እዮሲያስ የጓደኛዬ ልጅ ነው። በሰባት ዓመቱ ሁለተኛ ክፍል ገብቷል። ፈጣንና መጠየቅ የሚወድ ታዳጊ ነው። ባገኘኝ ቁጥር በጥያቄ ልቤን ጥፍት ያደርገዋል። አብዛኛው ጥያቄዎቹ ትምሕርት ቤት ከጓደኞቹ ጋራ ከሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የሚመነጩ ናቸው። ባለፈው ሰሞን እንዲህ ብሎ በእንቆቅልሽ መልክ ጠየቀኝ። ለእኔም አጠያየቁ ልጅነቴን ስላስታወሰኝ በትዝታ ፈገግታ ታጅቤ “ምናውቅልህ” አልኩት። ”እ … ቢሄዱ፣ ቢሄዱ የማይሰለቻቸው?” አለኝ። ጥያቄውን እኔ ከለመድኩት የልጅነት የእንቆቅልሽ መልስ ጋራ ለማዛመድ የዱር አልቀረኝ የቤት መንገድ አይሰለቻቸውም ስል ያሰብኳቸውን እንስሳት ማሰላሰል ቀጠልኩ። የመሰሉኝንም ስማቸውን ደረደርኩለት፤ አልተሳካልኝም።
እዮሲያስ አገር ስጭኝ አለና በሰጠኹት አገር ላይ ፍልስስ ብሎ፤ ”ቢሄዱ፣ ቢሄዱ የማይሰለቻቸው … እ … ውሃ፣ መብራት እና የስልክ ኔትወርክ” ሲል ያልጠበኩትን ምላሽ ሰጥቶ በደንብ አስፈገገኝ። ዐዋቂን እንጂ ሕፃናትን የሚያሳስባቸው የማይመስለን የውሃ፣ የመብራት እና የስልክ አገልግሎት መጓደል ከማሳሰብ አልፎ በእንቆቅልሻቸው ውስጥ አስገብተው እንደ ሥነ-ቃል በየቦታው እንዲያዛምቱት እንዳስገደዳቸው ተገነዘብኩ። ቤት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚሰሙት “ውሃ ሄዳለች፣ መብራት ጠፍቷል፣ ኔትወርክ የለም” የሚለውን ነው፤ መሄድ፣ መጥፋት እና አለመኖር የሚዛመዱት ደግሞ ከመንገደኝነት ጋር ነውና ስለእንቆቅልሹ ለእዮሲያስ እና ለጓደኞቹ አጨበጨብኩላቸው።
ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ “አዲስ አበባ ውስጥ ሃያ አራት ሰዓታት ውሃ የሚያገኘው የከተማው ክፍል ሰባ አምስት በመቶ ነው” ብለው የሕፃን እዮሲያስ እንቆቅልሽ ፈገግ እንዳደረገኝ ሁሉ እርሳቸውም ፈገግ አሰኙኝ። እንደ እርሳቸው አባባል፤ ሰባ አምስት በመቶ የሚኾነው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ያለመቋረጥ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሲያገኝ ሃያ አምስት በመቶ የሚኾነው ነዋሪ ደግሞ በተለያየ ደረጃ ያገኛል።አንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ዐሥራ አምስት ቀን ቆይቶም ቢኾን ውሃ ያገኛል።
በውሃ እና በመብራት እጦት የአዲስ አበባ ሕዝብ እየተሰቃየ መኾኑን በመጥቀስ ጥያቄ ላነሱላቸው ጋዜጠኞችም ጥያቄው አጠቃላይ ስዕሉን የማያሳይ እና በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ መኾኑን በመጠቆም “አጠቃላይ ስዕሉን ካላየን በስተቀር የተሳሳተ ስዕል እንዳንሰጥ መጠንቀቅ አለብን” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ቢጤም ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኅብረተሰቡን ችግሩ ያጡታል ብሎ ግምታዊ መላምት ማስቀመጥ ቢከብድም ምናልባት በማስታወሻ መያዣቸው ላይ የተሰጣቸውን መረጃ ሲያሰፍሩ ቁጥሩ ተገላብጦባቸው ሊኾን ይችላል ብሎ መገመት ግን ትክክለኛነት ይመስለኛል።
ምናልባት በቅርቡም “እኔ ለማለት የፈለኩት በተለይ ባለሥልጣናት በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ ያሉትን ጨምሮ ሃያ አምስት በመቶ የሚኾነው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሃያ አራት ሰዓት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያገኛል። ሰባ አምስት በመቶ የሚኾነው ደግሞ በአጭር እና በረጅም ጊዜ ተራ ውሃ ያገኛል።” የሚል መግለጫን ይሰጡ ይኾናል ብሎ መጠበቅ ሳይሻል አይቀርም። ለነገሩ ይቺ የቁጥር ጨዋታ የገዢዎቹ የተለመደ የጋዜጣዊ መግለጫና የፓርላማ ሪፖርት ማዳመቂያ መኾን ከጀመረች ከራርማለች።
ባለፈው ጊዜ እንዲሁ የጋዜጣ ማተሚያ ቤትን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጋዜጣን በጥራት እና በብዛት የማተም አቅም ያለው ብቸኛ ማተሚያ ቤት “ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት” ነው። እንዲሁም በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን ጋዜጣ ማተም የሚችል ማሽን ያላቸው ማተሚያ ቤቶች ከሦስት አይበልጡም እነርሱም ቢሆኑ ከላይኛው አካል ፍቃድ ካላገኙ በስተቀር ለማተም ፍቃደኛ አይደሉም። ታዲያ እውነታውን ያጡታል ተብለው የማይታሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረሰኝና የአድራሻ መያዣ ካርድ የሚያትሙትን ጥቃቅን ማተሚያ ቤቶች ሳይቀር ተደምረው ሲሰጣቸው እንደወረደ ተቀብለው አገሪቱ ላይ ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ የሚጠጉ ማተሚያ ቤቶች እንዳሉ ጋዜጣ ማሳተም የሚፈልግ አካል ካለም ወደ እነዚህ ማተሚያ ቤቶች ሄዶ ማሳተም እንደሚችል ሲመክሩ ሰምቼ፤ ”የእነዚህ ማተሚያ ቤቶች አድራሻ የት ይኾን?” ስል ልጠይቃቸው ፈልጌ ነበር።
አሁን ደግሞ በእርሳቸው የመንግሥት አስተዳደር ሥር የሚተዳደሩ ብዙኀን መገናኛ ሳይቀሩ በየጊዜው የሚያነሱትን የአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ችግር በምን ስሌት እንደተሠራ በማይታወቅ መልኩ ሰባ አምስት በመቶው የከተማው ነዋሪ የተሟላ አገልግሎት እንደሚያገኝ ደምድመው ተናገሩ። እነ ሕፃን እዮሲያስ እንኳን “መንገደኛ” ያደረጉትን “ውሃ” እርሳቸው “የትም ንቅንቅ ብሎ አያውቅም” ሲሉ የቤት ልጅ አደረጉት። የአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ሽፋን በመቶኛ እያደገ መሄዱንማ አገልግሎቱን የሚሰጠው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣንን በየቤቱ በዘረጋው የውሃ መስመርና የቧንቧ ቆጣሪ ቁጥር ልክ ለክቶ ሁሌም በሚሰጠው መግለጫ ሲነግረን ቆይቷል። ከዛም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች የከፋ የውሃ እጥረት ሲያጋጥምም በውሃ ማከፋፈያ መኪና ውሃን ለኅብረተሰቡ የማድረስ አገልግሎት እንደሚጀምርም ጭምር ሲናገር ተሰምቶ ነበር። ጥያቄው “በየቤቱ ባሉት የውሃ ቧንቧዎች አማካኝት ሊወርድ የሚገባው ውሃ መቼ ነው ከሄደበት የሚመለሰው?” የሚለው ነው።
ነዋሪዎች በየመንደሩ ውሃ መጣ አልመጣ እያሉ፣ በርካቶች የሌሊት እንቅልፋቸውን መስዋዕት አድርገው ሲያገኙ እያጠራቀሙ ሲያጡ ደግሞ ከያለበት እያስቀዱ በሚኖሩባት ከተማ “ሰባ አምስት በመቶው በተሟላ ሁኔታ ውሃ ያገኛሉ” ማለት ተናጋሪውን ትዝብት ላይ ይጥላል። ይህን መግለጫ በየቤቱ ሆኖ የሚከታተለው “ውሃ አጥ” ነዋሪ ምናልባት በያለበት ሆኖ “ ውሃ የጠፋው እኛ አካባቢ ነው እንጂ ሌላ ቦታ ውሃ አለ ማለት ነው” በሚል ሊያስብ ስለሚችል ቁጥሩን አምኖ ይቀበላል በሚል ከኾነ ያስኬዳል። ነገር ግን እኔ እንኳን በግሌ ለማረጋገጥ ከሞከርኳቸው አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ፤ የረር ጎሮ፣ አያት፣ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ አስኮ፣ ዊንጌት፣ ኮተቤ፣ ፈረንሳይ፣ ሽሮሜዳ፣ ብስራተ ገብርኤል፣ ለቡ፣ መገናኛ፣ ሃያ ሁለት፣ በአብዛኛው የኮንደምኒየም ቤቶች እና ሌሎች ቦታዎች ያሉ ነዋሪዎች ውሃን በየተራ እንደሚጠቀሙ ነው። እነዚህ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በስንት በመቶ ታስበው ይኾን? ጠቅላይ ሚኒስትር።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እንደ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍ ቢያደርግለትና ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሃያ አራት ሰዓት ውሃ ቢያገኝ፤ እንዲሁም በከፊል የሚያገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ሃያ አምስት በመቶው ብቻ ቢኾን ኖሮ ችግርን በሂደት የመላመድ ባሕል ባለው በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ ፍጹም የውሃ እጥረት እንደ ችግር አይነሳም ነበር። ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት የአዲሱን ባቡሩን ቀለም ለመምረጥ በየቦታው እንደተቀመጡት መዝገቦች ዓይነት በየአካባቢው በማስቀመጥ መረጃን ለማሰብሰብ ቢሞክሩ የተገላበጠውን ቁጥር ያገኙታል ብዬ እገምታለሁ።
***********
በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የተንቀሳቃሽ ስልክ፣ የመደበኛ እና ኢንትርኔት አገልግሎት ተገቢ አገልግሎት አለመኖር እና ጥራት መጓደል ተጠቃሚውን እጅግ ካስመረሩት ጉዳዮች አንዱ ነው። “ኔትወርክ ተጨናንቋል፤ እባክዎትን ትንሽ ቆይተው ይደውሉ፤ የደወሉላቸው ደንበኛ መሥመሩን እየተነጋገሩበት ነው፣ እባክዎትን ደግመው ይሞክሩ፤ የኔትወርክ ሽፋን የለም” የሚሉት በኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎት ላይ የተለመዱ ምላሾች ናቸው። ስልክ ሲደወል ከስልኩ ውስጥ ድምጽ አለመስማት፤ ስልኩ ከተነሳ በኋላ የራስን ድምጽ መልሶ መስማት፣ እያወሩ የራስን ድምጽ እንደ ገደል ማሚቱ ከሥር መስማት የተለመዱ የአገልግሎቱ አካል ናቸው። ወደ ባንክ እና በኢንተርኔት አገልግሎት ወደሚሰጡ መሰል ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲኬድም “ኮኔክሽን የለም ትንሽ ጠብቁ “የሚሉት ምላሾች እንደተገቢ ምላሽ መቆጠር ከጀመሩ ሰንብተዋል።
እነሕፃን እዮሲያስ “መንገድ የማይሰለቻቸው” ሲሉ በእንቆቅልሽ መልክ ካስቀመጧቸው ውስጥም የቴሌኮም አገልግሎትን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሲናገሩ፤ በቴሌኮም አገልግሎት ሥር ያሉት የተንቀሳቃሽ፣ የኢንተርኔት እና የመደበኛ አገልግሎት መቆራረጥ የተከሰተው አሠራሩን ዘመናዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመሳሪያ ለውጥ ሂደት አገልግሎት መዛነፍ መኖሩን ገልጸው ይህ መዛነፍ በተቀመጠለት የስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚስተካከል እርግጠኛ ሆነው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት “ከስድስት ወራት በኋላ” ሲሉ ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ የኢትዮ – ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ አብዱራሂም አሕመድ፤ ችግሩን ለማስወገድ መሠረተ ልማት ለመቀየር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን እና በጥቂት ወራት ውስጥ በጣም በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ለዚህ ሲባልም የቅድሚያ ቅድሚያ ተሠጥቶት ዝርጋታውን የማቀላጠፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ከተናገሩ ስምንት ወይም ዘጠኝ ወራት መቆጠሩን አስታውሳለሁ። ባለሥልጣናቱ በቁጥር እየተጫወቱ የሚዘልቁት እስከመቼ ይኾን?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ ኢትዮጵያ የመረጠችው የቴክኖሎጂ ኩባንያ፤ ”ዴንማርክ”፣ “ኖርዌይ”፣ እና “እንግሊዝ” የሚጠቀሙበት “ሁዋዌ” የተሰኘውን ኩባንያ መሆኑን በኩራት ሲናገሩ ተሰምተዋል። ሌላውን ቁሳቁስ ቢሆን እነ “ዴንማርክ”፣ “ኖርዌይ”፣ እና “እንግሊዝ” እና የመሳሰሉት አገራት ኢትዮጵያ ከምታመጣበት “ቻይና” አይደል እንዴ የሚያስመጡት? ዋናው ጥያቄ የሚነሳው ለእነዚህ አገራት የሚገባው ዕቃ ጥራት እና ኢትዮጵያ የሚገባው ዕቃ ጥራት አንድ ዓይነት መሆን አለመሆኑ ላይ ነው። እነዚህ አገራት ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቁጥጥር አንድ መሆን አለመሆኑ ላይ ነው። በእነዚህ አገራት ያለው ሙስና እና በኢትዮጵያ ያለው ሙስና አንድነት እና ልዩነት ላይ ነው።
ጥያቄው መሆን ያለበት “ሁዋዌ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘረዘሯቸው አገራት ካሉት አስተዳዳሪዎች ጋራ ያለው የሥራ ግንኙነት እና ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት አስተዳዳሪዎች ጋራ ያለው የሥራ ግንኙነት ምን አንድነት አለው የሚለው ላይ ነው። ሌላው ጥያቄ ደግሞ የእነዚህ አገራት ገዢዎች ለሕዝባቸው ያለባቸው ተጠያቂነት እና የኢትዮጵያ ገዢዎች ያለባቸው ተጠያቂነት ነው። የ”ዴንማርክ”፣ የ”ኖርዌይ”፣ እና የ”እንግሊዝ” ገዢዎች በየስምንት ወሩ እየመጡ “ጥቂት ወራት ታገሱ፣ ከስድስት ወራት በኋላ ይጠናቀቃል፣ ዕድገቱ የፈጠረው ችግር ነው” የሚሉ ምክንያቶችን እየደረደሩ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም እንደማይሞክሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያጡታል ብዬ አላስብም። ለማንኛውም ስድስት ዓመት መታገስ ለለመደ ሕዝብ ስድስት ወር እሩቅ አይደለምና “ኔትወርኩ አያሰማማም፣ ኢንትርኔቱ ኮኔክሽን የለውም፣ የቤቱ እና የቢሮው ስልክ አይሠራም” እየተባባሉ ስድስት ወር መጠበቅ ብዙ የሚከብድ አይመስለኝም።
የአሁኑም የቀድሞውም ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሲሉ እንደተሰሙት፤ መንግሥት የቴሌኮምን አገልግሎት ወደ ግሉ ዘርፍ ማስተላለፍ የየማይፈልገው፤ ቴሌ ገንዘብ የሚታለብበት ተቋም በመኾኑ ነው። ምናልባት ለኅብረተሰቡ የሚከብደው ስድስት ወር መጠበቁ ብቻ ሳይሆን ባልተገኘ አገልግሎት መታለቡ ሊኾን ይችላል። በአሁኑ ወቅት ባለው አገልግሎት በአብዛኛው አንድ ሰው ወደ ሚፈልገው ሰው ስልክ ደውሎ ለማግኘት ከአምስት እና ከስድስት ጊዜ በላይ ደውሎ የራሱን ድምጽ እየሰማ ለመዝጋት የሚገደድ ሲኾን ለዚህም ቴሌ የአገልግሎት ክፍያውን ያገኛል። እንደጠቅላይ ሚኒስትሮቹ አገላላጽ፤ ቴሌ ባልሰጠው አገልግሎት ኅብረተሰቡን ያልባል ማለት ነው። ስለዚህም ከባድ የሚመስለው ስድስት ወር መጠበቁ ሳይሆን ባልበላ አንጀት መታለቡ ነው።
የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ቁጥርን በሚመለከት በ2003 እና በ2004 ዓ.ም. ከዕቅዱ በላይ ማሳካቱን የገለጸው ኢትዮ-ቴሌኮም ለ22 ሚሊዮን ሕዝብ ተንቀሳቃሽ ስልክ በመስጠት በሞባይል አገልግሎት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ስድስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሲናገር ተሰምቷል። የተለመደው የቁጥር ጨዋታ ኾኖ ነው እንጂ፤ ደረጃው የአገልግሎት ጥራትን መሠረት አድርጎ የወጣ ቢኾን ኖሮ አገሪቷ ከአፍሪካ የመጨረሻው ተርታ ላይ ትሰለፍ ነበር።
***********
ሕፃን እዮሲያስ “ቢሄድ፣ ቢሄድ የማይሰለቸው” ካላቸው መንገደኞች ውስጥ አንዱ የመብራት አገልግሎት ነው። የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሠራተኛ የኾነ ታማኝ ምንጭ በአንድ ወቅት፤ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ድርጅት ውስጥ የምትሠራ ነገር ግን ልዩ ልዩ የጥቅማ ጥቅም ድጋፍ ይደረግላት የነበረች አንዲት ጋዜጠኛ ለኮርፖሬሽኑ በርካታና አስቸኳይ የኾኑ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች እንዳለባትና ለዚህም አገልግሎት መብራት እየጠፋ ስለሚያስቸግራት የግል ትራንስፎርመር እንዲገጠምላት መጠየቋን ይነግረኛል። እርሱን ያስገረመው እርሷ ምን ዓይነት ኃላፊነት ላይ ብትኾን ለግሏ ትራንስፎርመር መጠየቋ ነበር። እኔ ደግሞ ምን ዓይነት ምላሽ እንደተሰጣት ጓጉቼ ጠየኩት። “ከአንቺ በፊት በጣም በርካታ ባለሥልጣናት ስለጠየቁ፤ ተራ ጠብቂ “ተባለች አለኝ። ምናልባት የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለኅብረተሰቡ ችግር ቦታ ሳይሰጡ በቁጥር የሚጫወቱት፤ የውሃ፣ የመብራት እና የስልክ አገልግሎት ተራ እየጠበቁ በየግላቸው ስለሚያገኙ ይኾን?
tsiongir@gmail.com