Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ጎንደር –ክፍል ሦስት (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ክፍል ሦስት

ከሥርጉተ ሥላሴ 29.05.2014 (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)

Gondor„ለመደመጥ የጥሩ አድምጩን የጎንደርን ህዝብ ሥነ ልቦና በጥንቃቄ መርምሮ ማወቅ ይገባል፤ ጎንደር መሆን ነውና!“ ጓድ ገብረመድህን በርጋ የጎንደር ክፍለ ሀገር የኢሠፓ ዬድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ በአጽህኖት – በተደጋጋሚ የሚቃኙት ቅኔ ነበር። ሲገፉም አብሮ ለመሰለፍ ያስቻለው፤ ቋሚ ጽናት የመነጨው ከዚህ ንጹሕ ፍቅርና እርግጠኝነት እንዲሁም የበቃ አቅማቸው የተፈለፈለ ነበር። እስከ መጨረሻዋ ቀን ድርስ አብረን ነበርን። ማናቸውንም መስዋዕትነት ከፍለን። ጓድ ገዛህኝ ወርቄና ጓድ ገ/መድህን በርጋ አብረው የመሥራት አጋጣሚ ኖሯቸው ቢሆን ኖሮ ህዝበ – ጠቀም  ትዕይንቱ ጎንደር ላይ እጬጌ በሆነ ነበር። ሁለቱም በቂና ሙሉ የመምራት አቅምና ብቃት፤ የህዝብ የጸዳ ንዑድ ፍቅር፤ ከቶውንም ሊገለጽ የማይችል የሥራ ፍቅር ጉልታቸው ነበርና። ለእኔ ህሊናዎቼ ናቸው – ዬምኮራባቸው።

እጅግ የማከብራችሁ የሀገሬ ልጆች ባለፈው ጊዜ ክፍል ሁለትን በዚህ መልኩ ነበር የደመደምኩት። እንዲህ …

ክፍል ሁለት ማጠቃለያው — በዬዘመናቱ መበደሉን እያወቀ ግን በአርምሞና በትእግስት የላቀውን ዬእናት ሀገሩን ጉዳይ በማስቀደም በተደሞና በአርምሞ እንዲሁም በጭምትንት የተቀመጠን ህዝብ ሰብዕና፤ ከእኛም አልፎ ዬዐለም ሃብትና ቅርስ የሆኑ ውድ ጌጦቻችን ያበረከተ ንቁ ህዝብ፤ ለማንኛውም ቋያ ነክ ግዳጅ መቆስቆሻ የሆነውን ወርቅ ህዝብ ዛሬ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይብጠለጠላል በሦስት ተመድቦ …. ይከተከታል መረማመጃም ሆኗል። ግን ለምን?!!!

ጎንደር – ክፍል ሦስት።

እንደ መግቢያ – ጣዕሙን ስፈትሽው እኔን ውስጤን እንዲያሳይ እያስገደደ ነው። እሱን ስገለጥው እኔን እራሴን በሃቅ መተርጎም እችል ዘንድ ሚዛን ላይ አስቀምጦ እዬፈተሸኝ ነው። ስመሰክር ውስጤን አደባባይ አውጥቼ በእርግጠኝነት እንዳቀርብ እዬመከረና ቆሞም እዬጠበቀኝ ነው። የጎንደር እውነትነትና ትውፊትነት እንዲሁም የታሪክ ተመክሯዊ መስታውትነት፤ በተጨማሪም የባህል ልዕቅና ጉልበታምነት ሆነ፤ የተባ ዬተግባር ፍቅር ጉልህነትን፤ በአንክሮ ችዬ መግለፄን ፈተና ላይ አስቀምጦ ለማድመጥ በዝግጁነት ነው። እኔ ደግሞ ፈተናውን እንዳልወድቅ ቢያንስ 50% ቁንጥጧን ማግኘት እችል ዘንድ ጥሬ እዬታገልኩ ነው። ግን እችል ይሆን?

ውጪ ሀገር በምንኖረው በእኛም ብቻም ሳይሆን አፍ እላፊው ሆነ ቅጥዬለሹ ድልደላው እንዲሁም ምደባው በሽታሽቶ በዬዘመኑ የሚወቀጠው፤ በክፉ አይን የሚታዬው ያ መከረኛና አሳረኝ ሀገርቤት ያለውንም ህዝብንም – ረመጡ ይኽ ነው። ዘመንና እርግማን ….

ሀ. „የወያኔ ሙሉዕ ደጋፊነት፤“

ለ. „የአማራነት አክራሪነት፤“

ሐ. „ለነፃነት ደንታ ቢስነት“ አራተኛም አለ „መሃል ሰፋሪነት“ – ያንገሸግሻል – ለመስማትም- ምግለት።

በቅድሚያ ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት አንድም አካባቢ ተነቅሶ በተገኘው አጋጣሚ መጠቃጠቂያ የሆነ የለም። በጠላትም በወገንም በኩል አለመሰልጠኑ፤ ቁምጣ ለባሽነቱ፤ ደንታቢስነቱ፤ ባላገርነቱ፤ ውጪ እንኳን ወጥቶ ከታክሲ ሹፌርነት ውጪ ሥልጣኔ – ገብ አለመሆኑ በአነጋገር ዘይቤው ሁሉ ይወቀጣል – ጎንደር ብቻ። ኧረ ስንቱ?

-       ለዛውና ዘይቤዊ አነጋገሩ ሆኑ ልዩ ግርማ ያላቸው ሙሽራ ቃላቶቹ በቋሚነት በኤሎትሪክስ ሚዲያ ሆነ በፕሬስ እንዲሁም በመጸሐፍት ህትምት ተጠናክሮ ይቀጥላል። እራስን ተበድሮ ወይንም ተውሶ መኖር ተፈጥሮው ስላልሆነ።

-       በኢትዮጵያዊነቱ የመኖር አቅሙ ዛሬ ሳይሆን፤ አርቲፊሻል ሳይሆን ሆኖ የኖረበት አብነት ስለሆነ ንቅንቅ አይልም። ተፈጥሯውን አይዘልም ወይንም አይደፈጥጥም።

-       ቁምጣ ለባሽነቱ የአርበኝነት መለያ ምልክቱ ስለሆነ ትውፊቱን አበልጽጎ ይቀጥልበታል – አጉልቶ።

-       ባለገርነቱ – አዎን ሀገር አልባ አይደለም በነፃነት የኖረች እናት ሀገር አለች – ፈተናን እንደአመጣጡ እያሸነፈች የኖረች ገናና – ኢትዮጵያን የመሰለ የሰው ልጆች መፈጠሪያ አለችው – ይኮራባታል ቃናውም ቅኔውም – ዜማውም – መዝሙሩም -ማዕዛውም ናት።

-      አለመሰልጠኑ ቅርሶቹ ለዓለም አቀፍ ውርስና ቅርስ መብቃታቸው ህሊናን ሚዛን ላይ ያሰቀምጣል። ከዚህም ባለፈ ከዬትኛውም አካባቢ ከሚመጡት ወገኖቹ የሚመጥን የሥልጣኔ አቅም አለው። የቀለም – የዘር – የሃይማኖት ልዩነት በሌለበት ሁኔታ ሰልጥነዋል ከሚባሉት ሀገሮች ህዝቦች ጋር በተሻለ አቀራረብ መስሎ ሳይሆን መጥኖ የመኖር መክሊቱ ትርፋማ ነው። ይህም ተጨባጭ ነው።መረጃው መዳፍ ላይ ይገኛል።

እርግጥ ነው የወያኔ አሙካዎች የወጣላቸው የወያኔ ሃርነት ትግራይ አባላት ፓልቶክ ላይ ሥማቸውን ብታዩት „ማይዘጎንደር፤ በለሳ፤ አርማጭሆ፤ ጎንደር፤ አመድወንዝ፤ አንገረብ፤ አንባጊዮርጊስ“ ወዘተ ነው። ይህ ምክንያታዊ ነው። በሁለት የሚሰነጥቅ። አንደኛው ጎንደር አረሙን ወያኔን ከልቡ ተቀብሏል – ደጋፊ ነው ለማሰኘት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የነፃነት ትግሉ ቤተሰብ ጥርጣሬ እንዲሰፍንበት ሆን ተብሎ የተሸረበ ሴራ ነው። የሆነ ሆኖ መሆንን ለሚያውቅ ቅን ዜጋ መንፈሱ የረጋ፤ የብረት ማገር ነውና ከፍላጎቱ ሆነ፤ ከአንጡራ የመንፈስ ቅርሰ – ሃብቱ ጭብጦ መስረቅ  ጠላት አይችልም። እኔ የምታዘበው በሁሉም አቅጣጫ ተነጥሎና ተለይቶ በይፋም ሆነ በሽምቅ ጎንደር ሲነሳ መታመስን ነው፤ ይህ ለእኔ የሚሰጠኝ ጉልህ ምላሽ የበታችነት ስሜት የወጠነው ወይንም ያስታጠቀው እራሱን መሸከም ያልቻለ ለጋ ስሜት ይመስለኛል – ብዕር የሚያነሳውም፤ የማይክ ተጠቃሚውም – ሽምቅ ተዋጊውም፤ ይህ የበለጠ ለጥንካሬ የሚጋብዝ እንጂ ጉልበትን የሚያሞሽሽ፤ ወይንም ጥንካሬን የሚሸበሽብ ሊሆን አይችልም። በጠራ ቋንቋ ምን እንዳለን – ምን እንደምንፈልግ – ምን እንደምንችልና ምን እንደተፊቀደልንም በሚገባ እናውቃለን።     

ሀ. „የወያኔ ደጋፊነት“ … ወይንም የባንዳ ደጋፊነት። ቃሉ እንዳይጠጋኝ በጥቅስ ውስጥ ይቀመጥ። ብራናዬም ይቀፋታል። ከምን አንፃር? ከዚህ በላይ ምን በደል አለና? ከአፈር – ከመሬት፤ ከድንበር በላይ ምን ጥቃት አለና? ወልቃይትና ጠገዴ – አዲረመጽና አዳርቃይ – ሰቲትና አብደራፊ አሁን ደግሞ ድንቁ ዋልድባ ገዳምን፣ ስሜን ፓርክንም ጨምሯል መሬቱ መወሰዱ ብቻ መሰላችሁ። በዬዕለቱ በነዋሪዎች መንፈስ ላይ የሚጫነው በበቀል የጨቀዬ ድቀት ቅጣቱ፣ ውርድቱ፣ ግልምጫው፣ የበታችነቱ፤ በስላቅ መገፋቱ – መገፍተሩ፤ የአጽም – ፍልሰቱ፤ የአዛውንታት አፈናውና – ድራሻቸው ጥፋቱ፤ የአንስት እህቶች ከፍቃድ ውጪ መደፈሩ፤ የነፍስ ልግጫው፤ በእርስታቸው ላይ ባይታዋርነቱ፣ በህዝብ ማህል መሳቂያነቱ ይህ ክብር ነውን? ይህ ደስታን ያመነጫልን? ዕድሜ ዘለቅ ቅርሶች መዘረፋቸው – መቃጠላቸው፤ ታሪካዊ ዝክሮች በስውር መጥፋታቸው፤ ይህ መንፈስን ለጠላት ይሸልማልን? በፍጹም! ውርደትን ተቀብሎ ድጋፍን ከመሰጠት አፈር መልበስ ይበልጣል። በብረት ብቻ ሳይሆን በብረትና በድንጋይ መዶሻ ተቀጥቅጦ መሞት ይሻላል – ሙጃን ከመደገፍ። እንተዋወቃለን እኮ ጫካ ላይ ምን እና ምን እንደ ነበሩ – እርቃኑን የቀረ ደመ – ነፍስ መንፈስ እንዴት ተብሎ ይደገፋል?! በምን ስሌት?! ህልም ነው።

አንድ የወልቃይት የጠገዴ ኗሪ ከተማ መኖር ቢያምረው በመንፈሱም አያስበውም ትግራይ ሄዶ መኖርን፤ እንኳንስ ገንዘቡን ሆጭ አድርጎ ቤት ሊገዛና ሊሠራ ቀርቶ። ፈጽሞ! ባዕቱን ፈልጎ ሄዶ ጎንደር ላይ ይሠራል – ይኖራልም ደስ ብሎት። የትግራይን ህዝብ ጠልቶ አይደለም፤  አንድ ጊዜ ስለ አይሁዲት ጋዜጠኛ አብርሃም ደስታ ከሀገርቤት ፕሬስ ጋር በነበረው ቆይታ „አዜብ አጀንዳችን“ አይደለችም ብሎን ነበር። እንደዛ ነው ነገሩ። ጠረኑም አይጠጋም። የፈለገ ቢበደል ወይ ወደ ማህል ሀገር በስተቀር እርግጫውን ቀምሶ ይኖራል እንጂ ፍትህ ፍለጋ „ትግራይ“ አይታሰብም። ቅርጥምጣሚዎች አሉ ውጪ ሀገር የሚኖሩ እነሱ እንኳን ወደ ሀገር ሲሄዱ ትኬታቸው ጎንደር ይላል። በጎንደር አድርገው ሰቲት እንጂ በትግራይ እእ፤ ለወላጆቻቸው የሚያደርጉት ነገር ካለም ጎንደር ላይ። በመንፈስ ፈቃድ መገዛትና በመንፈስ  ሽፍትንት መገዛት በጣም የተለያዩ ናቸው። ሊቀራረቡም የማይችሉ የሩቅ ገደል ግልም – ጎርማዳና የዶዶሙ ዕይታዎች ናቸው። አይታሰብም።

ነገር ግን በአብሮነት ሂደት ውስጥ ያለው አምክንዮ ደግሞ ሌላ ውብ እርእስ ነው። አፈሩ መርግ ሆኖ ይክበዳቸውና ሄሮድስ መለስ በቦታው ተገኝተው ጠይቀው ነበር  „ሊጠይቁን የሚፈልጉትን ነገር አናውቀውም ነበር ያላቸው“  ማናቸውም ኢትዮጵያዊ  ጎንደር ላይ ሲኖር ደንበር አልቦሽ ሆኖ ነው። ተግባር ይመሰክረዋል። ጎንደር ላይ እኮ „የቴወድሮስ ከተማ የለም“ ዬየኋንስ ከተማ እንጂ። አብዛኛውን የጎንደር ሰው ከፋሲል ይልቅ ምርጫው የኋንስ ነው። ከአንድ ቤተሰብ በጣምራ የኋንስን ይጠሩበታል – ከፍቅሩ ከአክብሮቱ የተነሳ። በሃዘን ተፍሰኃው፤ በቤተ እግዚአብሄር ውሎም ቢሆን የመንፈስ አባቶቻቸውን አክብረውና አቅርበው እንጂ አጋ ለይተው አይደለም – አብረው ናቸው። ነገር ግን ጠላቱ ማን እንደ ሆን? ስለምንስ እንደ ሆነ? አስተርጓሚ አያስፈልገውም – ወይንም ቀስቃሽ። አሳምሮ ጠፈፍ አድርጎ ጎንደር ያውቀዋል።

ከዚህ በላይ በዬዘመኑ ማገዶነት – የግንባር ሥጋነት የማን መለያ እንደሆን ታሪክ ቆሞ ይመሰክራል። የሀገርን ልዑላዊነትን ለማስከበር ከሁለቱ የጫካ አራዊቶች ጋር በነበረው ፍልሚያ እሳትን እዬቀደመ ይረመጠመጥ የነበረው ማን እንደ ነበር በህይወት ያሉ የሠራዊታችን ከፍተኛ መኮንኖችም ሆኑ ባልደረባዎቻቸው ሀቁን መናገር ይችላሉ። ግንባር ላይ የሚሸሽ አንድም የጎንደር እትብት ኖሮም አያውቅም። እንዲህ ዓይነት ወንድ ልጅ የጎንደር እናት አምጣ አትወልድም – በፍጹም።  እስቲ ከቻላችሁ የድንቁን ጸሐፊ የአቶ ገሪማ ታፈረን „ጎንደሬ በጋሻውን“ አንብቡት። ሴቶች ሳይቀሩ ሥማቸው ተዘርዝሯል የጣሊያንን መሪዎችን አንገት እንዴት እንደቅል ይሰዬፉ እንደ ነበር። መርምሩ – በውስጡ መኖር ያስችላችኋል። የአርበኝነት እውነት በልጽጎ የአልገዛም ባይነት ብርታት ፈክቶ ፈልቆም ጎንደር ላይ እትብት

ለ.የአማራነት አክራሪነት፤“ „አማራነት“ የሚለውን እራሴን ነው ለናሙና ዬማቀርበው። ሲዊዝ እራሱ ቅርበቴ ከእነማን ጋር እንደሆነ የሚያውቀው ያውቀዋል። ለመንፈሴ የሚመች የሀገሬ የኢትዮጵያ ልጅ ዬልቤ ነው። ከዚህም ባለፈ ገደብ አልቦሽ የበዙ ሲዊዞችን ጨምሮ በርካታ ግንኙነት፣ ጠንካራም ትስስር ከሌሎች ሀገር ዜጎችም ጋር ነው ያለኝ። ባይኮራበትም በእርግጠኝነት ሙሉዑነት መግለጽ ያስችላል።። በቃ! ስለ „አማራነት“ እኔ እራሴ አላውቀውም። ቤተሰቦቼ እራሳቸው የሚያውቁት ስላልነበረ፤ ቤተሰቦቼ „አማራ“ ነሽ ብለው አላሳደጉኝም። ቤተሰቦቼ የማያዋቁትን እኔ ዬት አባቴ አምጥቼ ላውቀው እችላለሁ? ለዚህም ነው ብዙ ነገሮች የማይመቹኝ። እምወደው ፓርቲዬ ኢሠፓ ቆርጦ በሚገስጻቸው ወይንም በዲፕሎማሲ ቋንቋ ከቦታ ወር በሚያደርጋቸው ጓዶቼ ጎን እስከመጨረሻው ነበር እምሰለፈው። በድፍረት። ያላደኩበትን ዬት አባቴ አምጥቼ እሆነዋለሁ። ጓድ ወንደወስን ኃይሉ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሜቴ ተለዋጭ አባል የቺኮዝላባኪያና የሀንጋሪ አንባሳደር ሲሆኑ ከሥርጉተ ጋር በማናቸውም ሁኔታ ይገናኙ ነበር። ጓድ ገ/ መድህን በርጋ ጎንደርን እንዲለቁ ሲወሰን አብራቸው ሥርጉተ ነበረች፤ የሚዛን ተፈሪ ክ/ ሀገር አንደኛ ጸሐፊ ሆነው ከፓርቲያቸው ያፈነገጠ አንጃ ፈጥረዋል ተብለው ማዕከላዊ ሲታሰሩ በግልጽ ደብዳቤ ፈቃድ ጠይቃ እሳቸውንም ቤተሰባቸውን ሄዳ ጠይቃላች – ሥርጉተ፤ ጄ/ አሰፋ ሞሲሳ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲገጥማቸው ሆለታ ገነት ድረስ ሄዳ አይታቸዋለች፤ አሁንም ሌትና ቀን የምትባትለው ስለ ታላቁ ኢትዮ – አፍሪካዊ የቅኔ ንጉሥ ስለ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ድህን ነው። የምትከሰበት፤ የተገለለችበት አምክንዮ አንዱም ይሄው ነው። ሲዊዝ ውስጥ አንድ ቀን ከአንድ ጎንደሬ ጋር ቡና ጠጥታ አታውቅም፣ ወይንም ስትጓተት አትገኝም። ሃጢያት ሆኖ ግን አይደለም። ቀድሞ ነገር ጎንደር እትብታቸው የተቀበረ ወገኖቼ ከዚህ ሲዊዘርላንድ ምን ያህሉ ይኑሩ አይኑሩ አላውቅም። ስለምን? አላደገችበትም። እነሱም አይፈልጓትም። ያለደጉበትን ከዬት አምጥተው። እንዲህ ቢሆኖ ስንቱን መከራ አብረዋት በታገሱ ነበር …..

ሐ. „ለነፃነት ደንታ ቢስነት።“ ማን እዬከፈለን ይሆን እንዲህ መቆስቆሻ የምንሆነው? ስንት ባውንድ ይሆን በዬወሩ የተቆረጠልን?! በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ጎንደሬን ዘጭ ያደረገ ንግግር በተደጋጋሚ በጆሮዬ አድምጫለሁ። አላዝንም። ስለምን? እራሳችን እናውቃለን። የበታችነትም ፈጽሞ አይሰማንም። ያጣነው ነገር የለም። ማለት የመንፈስ ደሃዎች አይደለንም። የትም ቦታ የሚመጥን አቅም እንዳለን አሳምረን እናውቃለን። ከሁሉ በላይ „ሙያ በልብ ነው“ መርኃችን። ብዙ ነገሮች ድከምቶች በሉት ወቀሳዎች ተነቅሰው ተሸከም ይባላል – ህዝቡና ልጆቹ።  በድንበሩ ጉዳይ „ሰማያዊ ፓርቲ“ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅቶ ብዙ ሰው አለውጣም ተብሎ ጎንደር እስኪበቃው ሲከተከት ነበር። ቃሉን ብገልጸው እራስን መስደብ ይሆናል። ግን ስለምን? ብሎ መጠዬቅ መልካም ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ጉዳዩን በቅርበት አድምጦ እርምጃ መውሰዱ ፍጥነቱ አንቱ ነው። ነገር ግን መሬት ላይ የሰከነ የሚሠራ ነገር ካልኖረ በጥድፊያ ጎንደር ላይ  ምንም ነገር መከወን አይቻልም። ሥልጣን ያለው አካልም ቢሆን በፈለገው ነገር ላይ ይመካ – አይችልም። አቅም ሆነ ጉልበት ይኖረው እማይቻለው ነገር ጎንደር ላይ አይቻልም። ሥጋን መግዛት እንጂ መንፈስን መግዛት አይቻልም። አንድ ምሳሌ እንዳነሳ ይፈቀድልኝ። እትብቴ በተቀበረበት ተወልጄ ሳድግ፣ ስኖርና ሥሰራ በውጩ ሆኜ ሳይሆን በውስጡ ስለነበርኩ ደልዳላ መረጃዎች አሉኝና።

በደረግ ጊዜ መንደር ምስረታ ለማስፈጸም ከፍተኛ ችግር ነበር። እኔ ጋይንት ዞን ነበርኩኝ። የጋይንት ህዝብ ጥንካሬ ብርታት ታታሪነት መግለጽ አልችልም። ስለምን? ከአቅሜ በላይ ነውና። ቤታቸው ጅብ ገል ይባላል። ክዳኑ በእሳር የሚሠራ ሆኖ፤  ግማሹ ግድግዳ በድንጋይ ወጥ ሆኖ ይሠራል፤ በሌላ በኩል ሥራ ወዳዶችም ስለሆኑ የተሻለ ኑሮ ያላቸው ቤታቸው ደርብና ምድርም ነው። በጣውላና በድንጋይ የተሠራ። ይህን አስፈርሶ መንደር ለመመስረት እጅግ – እጅግ ከባድ ዳገት ነበር። ከባድ የጦር መሣሪያ ለአስፈፃሚነት ነበር የተሰናዳው። መሣሪያ ቢጠመድ ግን የጋይንት ህዝብ – ይስቃል። እንደሚያሸንፍ ያውቀዋል። ልበ ሙሉ ነው። ደፋርም ነው። የዬትኛውንም ህዝብ ሥነ – ልቦናውን ስታውቁት መፍትሄው ከቅርብ ነው። 14 ቃላት በሁለት ዐረፍተ ነገር ግን ደንዳናውን ልቦናቸውን አራርቶ አሸነፈ። እንዲያውም እኛ እንበልጥ እኛ እንበልጥ ውድድር ጀምረው ካለምንም ብጥብጥ፤ ከመንግሥት ጋርም ሳይጋጩ ቡድኑም ሳይተዋክ በለሰለሰ ሁኔታ፤ ትህትናን በሰነቀ አኳኋን መርኃ ግበሩ ተፈፃሚ መሆን ቻለ። የተጠመደው መድፍና መትረዬስ አልነበረም ያሸነፋቸው። ከልባቸው ጠብ ያሉ ሁለት ስንኛት ነፍሳቸውን ገዝተው ፈቀዱ – በደስታ።

ሌላም – ጎንደር እንደ ሻ/ መላኩ ተፈራ የበደለ ልጅ የለውም። አይናቸው ደስ ብሎት እንኳን የሚመሩትን ህዝብ የማዬት አቅም አልነበራቸውም። እንዲህ ብዬ ልለፈው። በኋላ ጓድ ገዛህኝ ወርቄን ሰጥቶ በትህትና ሁለት ሦስት ሰዓት ነበር ቢሮቸው መግቢያ ላይ ቀጥ ብለው የተበደለን በማዳመጥ፤ ከዛው በዘቦች ስልክ ደውለው ጉዳዩን ለሚመለከተው ክፍል እራሳቸው በባለቤትነት ስሜት በመከወን፤ ሁሉም ይቅር ያ የሚበራ ግንባራቸው ብቻ ይበቃ ነበር አይደለም ሌላው። „ከፍትፍቱ ፊቱ“ ይላል ጎንደሬ – ለማንኛውም ወያኔ በስሱ ገብቶ ፍርደ – ህዝብ፣ ድምጽ – ህዝብ በሻ/ መላኩ ተፋራ ላይ ለማሰጠት ሞክሮ ስብሰባ አብዮት አደባባይ ላይ ጠራ፤ ቻለን አረሙ ወያኔ? እእ! አልቻለም። የጎንደር ህዝብ የበቃ መንፈሱን ከሱቅ ተሂዶ የሚገዛ ደጋፊነት ሆነ ተቃዋሚነት የለም። በመንፈሱ ዲታ ነው ሃብታም። በራስ የመተማማን ብቃቱ ያጠግባል – ጉልበታምም ነው። ድፍረቱ ከብረት ቁርጥራጭ የተሠራ – የሚመክት ነው። ውሳኔው ህይው፣ ውበታማ ጸዳሉ ቆሻሻን የመርገጥ አቅሙ – አንቱ ነው። ለማናቸውም ፍላጎቱና እምነቱ ጽናቱ የማይበገር ማገር ነው። በሃይማኖቱ ያለው ፍቅር ከእንቁላል ውሃ የተገነባ ነው። አሁን በሥርጉተ ልብ ውስጥ ልቡን ገጥሞ እንደ ቦይ ውሃ ሊያፈስ የቻለ ማን ነው? ይቻላል? ማንም አይችልም። አይታሰብም። እንደ ተፈጥሮዬ – እንደ መንገዴና እንደ መርሄ ነው የምኖረው። ይህ ከታሪካዊው እትብቴ አፈር የተቀመመ የውስጤ መልክ ነው። ሳምንና ሲገባኝ ብቻ ነው መገኘት የምችለው።ነገር ቀድሞ ይገባናል እንደዛ ነው ….

ጎንደር ለረጅም ጊዜ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ መዲና መሆኗ፤ በዬጊዜው በሚቀሰቀሱ ጦርነቶች የሚቀሩ የበቁ ማህበራዊ ህሊናዊ ዕሴቶች፤  ኢሠፓም ሆነ ኢህአፓ የፈጠረው ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ታክሎ፤ ከሁሉም በላይ የሃይማኖታዊ የቀደመ የሚስጥራት ጥልቅና የዳጎሰ ዕድምታ – ትርጓሜ፤ በተፈጥሮ የሚገኙ የትውልድ ውርርስ ጸጋዎች ተዳምረው የዳበረና የሰከነ፣ የሠለጠነ ብጡል ብቃት በመንፈስ ላይ አጽንተው ገንብተዋል። በቀለሉ የማይናድ – በቀላሉ የማይገባበት። ይህ በድንገተኛ አቀራረብና አያያዝ የሚደፈር አይደለም ወይንም በታንኳ እንደ አሻው የሚቀዝፍበት አይደለም። የእንቁላል ግንብ ነው። ወያኔን እኮ ዬትኛው አካባቢ ነው ሽንጡን ገትሮ የተዋጋው ከአንቦ በስተቀር ጎንደር ነው ፊት ለፊት በጣም ለርጅም ጊዜ የታገለው፤ ወያኔንም  የተረፈረፈው።

ያው ይታወቃል ጎንደር ሲባል ብዙ ሰው መስጥሮ ዓይኑ ይቀላል። ጸጉሩ ይቆማል፤  የንጉሦችን ንጉሥ ዐፄ ሚኒልክን አትንኩ የሚል አርበኛ የንጉሦችን ንጉሥ ዐፄ ቴወድሮስን ቀጥቅጡ ሲል ትሰማላችሁ። የጓጎለ ያልጠና የመንፈስ ድህነት። የጸሎት መጸሐፍት የሚጽፉት እንኳን „ታምረ ማርያምን“ እስኪ አንብቡት በሞቴ ሁለቱም የንጉሦች ንጉሥ ዘመናቸው የፈቀደላቸውን ከውነዋል። እንዲያውም ከዘመኑም የቀደሙ ነብይም ነበሩ – ሁለቱም። ይህ ሃቅ ለእኔ የሚሰጠኝን የዳበረ ትርጉም ያህል ለሌላው አይሰጠውም። ስለምን? የነፃነት ቃናን፣ የኢትዮጵያዊነት ህግጋትን የመተርጎም ሆነ፣ ጥልቅ የማንበብ አቅምን ይጠይቃል። አንድ ኢትዮጵያዊ ዐፄ ቴወድሮስን አልቆ ዐፄ የኋንስን ወይንም ባልቻ አባነፍሶን ቢያል ለእኔ መራራ ነው። ጎንደርም ሥርጉተን መታዘብ አይደለም ድቅቅ እንድል ይረግመኛል

እንደሚታወቀው ሃይማኖታዊ ዶግማዎች ብጥብጦች ከተነሱ ለማስከን እጅግ ከባድ ነው። ያን የታመሰ ዬኦርቶዶክስ ተዋህዶ የዶግማ ሆነ የቅኖና ውቂያ ዬት ላይ ነበር በዴሞክራሲያዊ መፍትሄ አምንጭነት ለዛውም በዛ በጥንት ዘመን መልክ ያዬዘው? የዘመኑ ልዩ ሥጦታ በነበሩት በዐፄ ፋሲል ዘመን።  ሊቃውነተ – ቤተክርስትያናት ካራ – ጸጋ – ቅባት በሚባል ሃይማኖታዊ ዶግማ ሲከታከቱ ኖረዋል። ወደዛ መግባት ጸጋዬ ስላልሆነ ዘልዬ ጦር አማዞ፣ አጋ አስለይቶ ሲያፋልጥ የኖረውን እንዴት እንደ ነበር? እንዲህ ይሉናል አራት ዓይናማው ሊቅ ሊቃውንቱ ጸሐፊ ተክለፃድቅ መኩሪያ

„ ከሦስቱ ወገኖች ማናቸው እውነትን ዬያዙ እንደሆነ ለማረጋገጥ ዬአውራጃ ሊቃውንት በሻና በአንጎ ላይ ተስብስበው እንዲከራከሩ ንጉሥ ዐፄ ፋሲልና ጳጳሱ አቡነ ማርቆስ አዘው ነበር። ከጎጃም ከቅባቶች ወገን ዋናው ተከራካሪ ዘእያሱ የሚባለው ነው። ከደብረ ሊባኖስ ተዋህዶዎች ወገን አዳም ዘእምፍራዝ የሚባለው ሆኖ ብዙ ጥቅስ እያጣቀሱ ተከራከሩ። በመጨረሻም አዳም እምፍራዝ ተዋህዶ አሸነፈ። ዘእዬሱስ ቅብዕት ተሸነፈ ተብሎ ጉባኤው ተፈታ። የቅባቶች ወገን ከጎጃም በተለይ ደብረ ወርቆች ናቸው። ተዋህዶ ግን በደብረ ሊባኖስ፣ በሽዋ፣ በጎንደር፣ በትግሬ ነው። ጸጋዎች ግን ይበልጥ የሚገኙት በሽዋ ነው ይባላል“ ገጽ (ገፅ 148-149 )* በዚህ መልክ በተለይ በተዋህዶዎችና በቅባቶች መሃከል ተነስቶ የነበረውን እሳት የሚያጠፋ ፍጥጫን ከሥሩ የነቀለ፤ የዳበረ ሥልጡን የዴሞክራሲ ያደገ ልምድ ፤ በመንፈስ የዳጎሰ መረቅ ቅርሱ በትውልድ ውስጥ ገንብቶ በትውፊት ማብቀሉ መንፈስን ልምድ ጠገብ አንዲሆን አድርጎታል – ፍሬ ዘሩ ዲታ እንዲሆን አግዞታል። ይህ እንግዲህ የፈረንሳይ አብዮት ተነስቶ „ነፃነት፤ እኩልነት፤ ወንድማማችነት“ የሚል ዓለምዓቀፍ ዴሞክራሲያዊ መንፈስ ከመፍጠሩ በፊት ቀድሞ እጅግም በጣም ቀድሞ ዕውን ሆኗል።

ይህ በራሱ አቅም ያለው የመንፈስ ውርስ ነው – ትውፊት። ትውልድ ከቶውን ሊተካቸው የማይችሉት ኢትዮ አፍሪካዊ የጥበብ ቅርስ ህይወትም የነበሩት ሰአሊ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የማስተር ፒሳቸው  „እናት“ ነፍስ የዘራች – መንፈሳዊት፤ ወጥ ሀገር በቀል ልዑቅ ተግባር ቀልብ ያረፈው ከአዲስ ዘምን ሊቦ ወደ ጎንደር ሲኬድ ያለ ዬሜሮናዊ ተራራ ትርጉም ነው። ተራራውን እንዲሁ ስታዩት ያቺ ቀደም በሰው እጅ ያልተሰመረችውን ወ/ሮ ኢትዮጵያን ቁጭ። እንደ ግሼ! ኢትዮ አፍሪካዊው የቅኔው ንጉሥም የሎሬት ዕዝለ መንፈስ ያረፈበትን „ሊማሊሞን“ እንዲህ ይለዋል በጥቂቱ ከአባቴ – ጽዑም ቅኝት እንሆ -

„ሊማሊሞ“

„ ….. ክንፉ ከነካስማው ዘሞ

ከጽንፍ ጽንፍ አርምሞ

ከደበራቅ እስከ አዲ አርቃይ

አለት ከደመና በላይ

አዘንብሎ እንደ ሰማይ

እንደጠፈር ሽቅብ ሲታይ፤

ጉም አጥልቆ እንደቀሚሱ

ፀሐዩን እንዳንገት ልብሱ

ተከናንቦ ተሸላልሞ

ተንደላቆ ሊማ – ሊሞ  /// ///

የቅኔው ንጉሥ ዝቅ ብሎ ደግሞ ወደ ማጠቃለያው …. እንዲህ ለዛዊ ተፈጥሮውን ከሰማዬ ሰማያት ይቀዳዋል …..

የጉም ክናዱን እንደጣር፣ ወደ ምድር ማኀፀን ልሞ

እንደባቢሎን ግንብ አጥር፣ ቋንቋ ለቋንቋ አሳድ

አልበገር አልደፈር፣ አልሰበር ያለን ከርሞ …….“  ( እሳት ወይ አበባ ከ114- 115)

አቤት! ዜማ አቤት! ውበት አቤት! ጣዕም …. አዬ ሊቁ አንተም በሥጋ ትሞትን?! ጌታዬ ተራቆትን አንተን በማጣታችን።

ሊማ – ሊሞን … ገታ ላድርግና ሌላ ማከያ አለኝ ከዚህ ንዑድ ጥልቅ መንፈስ ሳንወጣ። የሥነ – ጥበብ ዓራት ዓይናማ ሊቀ – ሊቃናት እንዴት ጎንደር ላይ ቅዱስ መንፈሳቸው ያርፍበት እንደ ነበር ለማጠዬቅ የእሳት ወይ አበባ መድበል ግጥም „ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ“ መግቢያው በጎንደር በር ተሟሸ። ሥጦታውም እዛው አረገ። እኔ እላለሁ ጋሼ ጸጋዬ አንድ ሰው አልነበረም ህዝብ እንጂ።

„ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ „

„ ….ርቀህ ተብርህ ሰንብተህ

የቱሪስት ካርድ የሳበህ

አንተ ማነህ?

እኮ ማነህ ወንድምዬ፣ ደራሲ የሚቃኘው

ሣአሊ የሚነድፍብህ

ቀሲስ የሚቀስብህ

የቱሪስት የጋዜጠኛ፣ ካሜራ እሚጋብዝህ

የሚተች የሚተረጉም፤ የሚነድፍህ የማንም እጅ

የማነህ ደም የማነህ ቅጅ?

አንተ የእማማ ኢትዮጵያ ልጅ  (ገጽ 26)

ያ የሚስጥራት የዜማ ጣዝማ የነበረው የቅዱሱ መንፈስ ያሬድስ የመክሊቱ መና አህዱነት – ያው ጎንደር።

እንደ መሰብሰቢያ — ሌላው ቀርቶ የታሪካችን አካል የሆነው የግራኝ መሐመድ እረፍት እኮ ጎንደር ነበር። ደንቢያ ላይ የግራኝ በር ይባላል። በነገራችን ላይ በዛ ዘመን የትግራዩ እንደርታና የጎንደሩ ደንቢያ በከንቲባ የሚተዳደሩ ዕውቅና የነበራቸው ከተሞች ነበሩ። ዛሬ ግን የእንደርታን ባላውቅም፤ አይደለም ደንቢያ ጎንደር አንዲት መንደር ናት በጨለማው ዘመነ በወያኔ – የታሪክ ረግረግ። ታሪክ ማለት እንደ ሥርጉተ ዕይታ – የህዝብ ወላዊ አዎንታዊና አሉታዊ አምክኖዊ፣ ክስተታዊ ክንውኖች ዕደሜ ጠገብ ሲሆኑ ታሪክ ይባላል። ይህን መክፈል ወይንም እንደ ዶሮ መበለት አይቻልም። ታሪክ ከአንገት በላይና በታች፤ ወይንም ሲሶና እርቦ ተብሎ ሊከፈል ከቶውንም አይችልም። አሉታዊም ሆነ አዎንታዊው ክንውኖች ለታሪክ ወጥ ገፀ – ባህሪው ወይንም ሙሉ ቁመናና መልኩ ነው፤ ታሪክ የትርጉም ሥራ አይደለምና።

ውዶቼ ዘመን ጠገብ ተመክሮ፤ ወገን ጠቀም የበቃ ተሳትፎ፤ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ይፈጥራል። ምንጮቹ በሥርዓት ሲፈተሹ የማንነት መነሻ ይታወቃል። የመነሻው ነፍስ ውስጥን ይሠራል። ሥራው ደግሞ ጥልፍ ነው – ውጽፈተ ወርቅ – ዬትውልድ የዕንቁ  ልቅ፤ ቀጥ ያለ ዓዕማደ የምሰሶ – ዓውድ! ስለነበረን መልካም ጊዜ ውስጤን ለውበቶቼ ለእናንተ ሸልሜ ክፍል አራትን በቀጠሮ አሳድሬ አክብሬና ወድጄ ልሰናበት ነው፤ አኔው ሎሌያችሁ ሥርጉተ ሥላሴ። ቸር ያገናኘን – አምላካችን በፋቃዱ።

ክፍል አንድ http://en.wikipedia.org/wiki/User:Aatebeje

ክፍል ሁለት http://www.zehabesha.com/amharic/archives/30526#respond ንባቡ ተከታታይ ይሆንላችሁ ዘንድ ሊንኮቹ እነዚህ ሲሆኑ ኮከብ ያለበት – ምንጭ ከዐጼ ልብነ ድንግል እስከ ዐጼ ቴውደርሱ ከሊቁ የተወሰደ ነው – በትህትና።

ትውልዳዊ ድርሻችን በህብረትና በአንድነት እንወጣ!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>