በቅርቡ አንዲት ታላቅ ጥቁር አሜሪካዊት የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ከዚህ አመት በሞት አልፈዋል። ማያ አንጀሎ ይባላሉ። እኝህ ታላቅ ሴት ጸሃፊ፣ ገጣሚም ነበሩ። አንድ ጊዜ ማያ አንጀሎ ሲናገሩ ፡ “We may encounter many defeats but we must not be defeated.” ብለው ነበር።
በዚህ አለም ስንኖር፣ በግለሰብ ደረጅ፣ በቤተሰብ፣ በአገር የተለያዩ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። ስህተቶች እንሰራለን። እንወድቃለን። ሽንፈቶች ያጋጥሙናል። የምናቀርቅርበት፣ የምናዝንበት፣ የምናለቅሰበት ጊዜ አለ። በአገር ጉዳይ ያለውን ሁኔታ እንኳን ስንመለከት፣ ከስድሳዎች የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ፣ በተለይም በአገራችን እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ የሕግ የበላይነትን በተመለከተ ፣ ከተገኙት ድሎች ይልቅ፣ ሽንፈቶቻችን በጣም ይበዛሉ። በስድሳዎቹ የነበረው የለዉጥ እንቅስቃሴ መስመር ስቶ ወደ ማይሆን ቦታ ወሰደን። በዚያ ጠባሳ ምክንያት ፖለቲክ እንደ ኮረንቲ ይፈራ ጀመር።ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሲተካ፣ «አዲስ ንጉስ እንጂ ለዉጥ መቼ መጣ» እንዳለው ዘፋኙ የታሰበለትም የተጠበቀው ሳይሆን ቀረ። በዘጠና ሰባት ታሪካዊ የሆነ የቅንጅት እንቅስቃሴ ታያ። የኢሕአዴግ ዱላ ተጨምሮበት፣ በመሪዎቹ መካከል የተፈጠረው ልዩነት የትግሉን ግለት አወረደው። እንደገና ሽንፈት አጋጠመን። እንደገና አምባገነኖች ለጊዜ ተሳካላቸው።
ላለፉት አንድ አመት፣ የሚሊዮኖች ንቅናቄ በሚል መርህ ፣ የወዳደቀዉን በማንሳት ፣ የተሰባበረዉን በመጠገን፣ ብዙዎች ለአሥርተ አመታት መስዋእትነት የተከፈለበትን ትግል ከግብ ለማድረስ፣ ተጨባጭ የሆኑ ሥራዎችን መታየት ጀምረዋል። ለዉጥ ሊያመጣ የሚችለው ኃይል የህዝብ ኃይል ብቻ ነው። ይህንን ኃይል ከማደራጀት፣ ከማንቃት፣ ከማሰባሰብ ዉጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለም። ሕዝብን ከጎኑ ያላደረገ ትግል ዋጋ የለውም። የሚሊዮኖች ንቅናቄ ሕዝብን ማእከል ያደረግ የሚሊዮኖች ንቅናቄ ነው።
ብዙዎች ከጊዜ ወደ ጎዜ ከሚሊዮኖች አንዱ ነን እያሉ ትግሉን እየተቀላቀሉ ነው። የሶሊዳሪቲ ንቅናቄ፣ የብዙ ደርጅቶች ስብስብ የሆነው ሸንጎ፣ የሽግግር ምክር ቤቱ እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች የሚሊዮሞች ንቅናቄ አካል ሆነው በጋራ እየሰሩ ነው። በሰላማዊና ሕዝባዊ ትግል ዙርያ መሰባሰቦች እየታዩ ነው። ይህም አስደሳች ዜና ነው።
ነገር ግን አሁንም ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆነ ወገኖቻችን ያለፉትን ጠባሳዎችን እየተመለከቱ፣ ተስፋ ቆርጠው፣ እጃቸውን ለፍርህትና ለባርነት አሳልፈው ሰጠው፣ ዝም ማለትን የመረጡ አሉ። ለነዚህ ወገኖቻችን የማያ አንጀሎ አባባል ልናካፍላቸው እንወዳለን። “We may encounter many defeats but we must not be defeated.” እንላቸዋለን። «ዝምታችን እስከመቼ ነው ?» እንላቸዋለን።
የሚሊዮኖች ንቅናቄ መጪው እንቅስቃሴዎች በአዳማ/ናዝሬት፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደብረ ታቦር ይሆናል። ከነዚህ ከሶስት ከተሞች በተጨማሪም፣ ከሃላፊዎች እውቅና ከተሰጠ ፣ በአርማጭሆ፣ በወገራ እና በቁጫ ሰላማዊ ሰልፎች ይደረጋሉ። ቢያንስ በአንድ ቀን ብቻ፣ ከሶስት እስከት ስድስት ባሉ ከተሞች የአንድነት ፓርቲ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው። ሕዝቡ ፍርሃትን አውልቆ፣ ያለፉት ሽንፈቶች ተስፋ ሳያስቆርጡት፣ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለፍትህ ፣ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ድምጹን ለማሰማት መዘጋጀቱ ትልቅ ድል ነው።
እንግዱህ ይሄንን ታሪካዊና አገራዊ እንቅስቃሴ እንቀላቀል። ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ። ነጻነት ዋጋ ያስከፍላል። ሌሎች ትልቅ ደረጃ የደረሱት ጥረው ግረው ነው። ሌሎች ነጻነታቸው ያገኙት መስዋእትነት እከፍለው ነው። እኛም እንደዚሁ ዋጋ ለመክፈል እንዘጋጅ። ለኛ መብት ሌሎች እንዲጮሑልን መጠበቅ የለብን። ለመብታችን እያንዳንዳችን እንነሳ ።ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን።