Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ቤተመንግስት እና የአላሙዲ ሸራተን አካባቢ የሚኖሩ የምስኪን ቤት አልባ ኢትዮጵያውያን አሳዛኝ ሕይወት

$
0
0

seharon
ናፍቆት ዮሴፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከጻፈችው የተወሰደ፦
“እናቴ የኤች አይቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ ይገኛል፤ እኔና እህቴ ከእናታችን ውጪ ማንም የለንም፡፡ ሰባት መፅሀፌን አቃጥለውብኛል፤ በዚህ የተነሳ በትምህርቴ ውጤት ላመጣ አልቻልኩም፣ ከምማርበት ይልቅ ከት/ቤት የምቀርበት ቀን ይበልጣል፣ እናቴ ቀበሌው ቤት ይፈልግልሻል ተብላ ነበር፤ በኋላ ተቀንሰሻል አሏት፡፡ ለምን ብላ ስትጠይቅ፣ አንቺ የኤች አይቪ ቫይረስ በደምሽ ውስጥ የለም፣ ውሸትሽን ነው ተባለች፡፡ እናንተ ግን እናቴን ሂዱና እይዋት፣ ፎቶም አንሷት፣ የምትወስደውንም መድሃኒት ተመልከቱ፡፡
”ይህ የ12 ዓመቷ ታዳጊ ቃልኪዳን ተመስገን በእንባ ጎርፍ የታጀበ ንግግር ነው፡፡ ቃልኪዳን በጆኔፍ ት/ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ አራት ኪሎ ቤተመንግስቱ ስር ባለውና በአረንጓዴና ቢጫ ቀለም ቅብ በታጠረው የቆርቆሮ አጥር ስር ከእናቷና ከታናሽ እህቷ ጋር በላስቲክ ቤት ውስጥ የወደቀባትን ሀላፊነት ለመወጣት የምትቃትት ህፃን ናት፡፡
አቶ ጀማል ሁሴን ለመልሶ ማልማት በፈረሰው የአራት ኪሎ መንደር ለ23 ዓመታት እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊት ትንሽ ብር እየከፈሉ ዘመድ ቤት በጥገኝነት ይኖሩ ነበር፡፡ ከዚያም ልጅ ወልደው እና አካባቢውን መስለው በሰላም ይኖሩ እንደነበር አጫውተውኛል፡፡ “ሙዘይን ጀማል የተባለ የ18 ዓመት ልጅ አለኝ፡፡ በችግር ምክንያት ትምህርቱን ባያቋርጥ ኖሮ አሁን ዩኒቨርስቲ መግቢያው ነበር” የሚሉት አቶ ጀማል፤ አሁን ግን የሚረዳው በማግኘቱ ያቋረጠውን ትምህርት መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ጀማልና ቀሪ ቤተሰቦቻቸው ያለ ስራ ያለመጠለያ፣ ያለመብራትና ውሀ ሙጃ ሳር በከበበው የአራት ኪሎ ሜዳ ላይ ከነልጆቻቸው ስድስት ሆነው በወጠሩት ላስቲክ ቤት ውስጥ የመከራ ኑሮ እየገፉ ይገኛሉ። አሊ ጀማል የተባለው ልጃቸው የሚለብሰውና የሚማርበት ቁሳቁስ እንዲሁም ምግብ በማጣቱ ትምህርቱን እንዳቋረጠም በእንባ ይናገራሉ፡፡
የ62 ዓመቱ ስመኝ ላቀውም ከ15 ዓመት በፊት ሸራተን ፊት ለፊት በነበረውና አሁን ለመልሶ ማልማት በፈረሰው መንደር ውስጥ በጥገኝነት ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ቀበሌው ላለፉት 15 ዓመታት በጥገኝነት መኖራቸውን እንደሚያውቅ በተደጋጋሚ ቤት እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውና አሁን ግን ጭራሽ ቤቶች ሲፈርሱና ያስጠጓቸው ሰዎች ቤት አግኝተው ሲሄዱ እነሱ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን ይገልፃሉ። በዚህ ኑሮ አራት አመት እንዳስቆጠሩ የሚናገሩት እኚህ አባት፤ ልጆቻቸውን ወደ ትውልድ አገራቸው ሀረር ልከው በየዘመድ ቤት እንዳስጠጓቸውም አውግተውኛል፡፡ “አሁን ያለነው ያለ ውሀ፣ ያለ ምግብና መጠለያ እዚህ ወንዝ ውስጥ ነው፡፡ ማታ ማታ ጅቦች እየመጡ በላያችን ላይ ሲሮጡብን ያድራሉ፤ ህፃናትን እንዳይበሉብን በርካታ ውሾችን አሠማርተን እኛም ተራ በተራ እየተከላከልን በስቃይ እንኖራለን” በማለትም ጨምረው ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ስመኝ ገለፃ፤ ችግራቸው ይሄ ብቻ አይደለም። ቦታው በቆርቆሮ ከመታጠሩም በተጨማሪ የበቀለበት ረጃጅም ሙጃ ለሌቦች መደበቂያ በመሆኑ ሌቦች ሰርቀው አጥር ውስጥ ሲገቡ ፖሊሶች መጥተው ሌቦቹን አውጡ በማለት እንግልት እንደሚፈፅሙባቸው በምሬት ይናገራሉ፡፡
አቶ ምትኩ ገብሬ የ75 ዓመት አዛውንት ናቸው። እርጅናና ጉስቁል የተጫናቸው አቶ ምትኩ፤ ጅማ ውስጥ ተወልደው ማደጋቸውን አጫውተውኛል። በደርግ ጊዜ ኢህአፓ እየተባለ ሰው ሲባረር በኢህአፓነት ተጠርጥረው ያለ ምንም ማስረጃ መታሠራቸውንና ከእስር ቤት አምልጠው ሱዳን መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከሱዳን ተመልሰው አዲስ አበባ መኖር የጀመሩት እዚሁ አራት ኪሎ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ምትኩ፤ ላለፉት 19 ዓመታት ሠው አስጠግቷቸው ይኖሩ እንደነበርም ያብራራሉ፡፡ ገና ከሱዳን እንደመጡ ጉልበታቸውም ሆነ ጤንነታቸው ደህና ስለነበር አነስተኛ ቤት ተከራይተውና ያገኙትን እየሠሩ ይኖሩ እንደነበር ገልፀው፤ እድሜና የጤና ችግር እየተጫናቸው ሲሄድ ያከራየቻቸው ሴት “ለፈጣሪ ይሆነኛል” በሚል ኪራዩን ትተው እንዳስጠጓቸው፣ አሁን ግን እዚህ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን የሞጨሞጩ አይኖቻቸው እንባ እየተሞሉ አጫውተውኛል፡፡ እኚህ አባት አሁን ጤናቸው ተቃውሷል፡፡ አይናቸውንም እንደሚጋርዳቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ ምትኩ በተለይም ኑሯቸውን የከፋ ያደረገው የአስም በሽታቸው ነው፡፡ ቅዝቃዜው ለአስም በሽታቸው መባባስ ምክንያት ሆኖ መተንፈስ እየተሳናቸው ነው ያነጋገሩኝ፡፡ “እኔ የምለብሰው ልብስ በቀበሌ ሹማምንቶች ተወስዷል፤ አሁን ገላዬ ላይ ጣል ያደረግኩትን አሮጌ ጨርቅ ለነፍሴ ያለ ነው ጣል ያደረገብኝ፤ ከዚህ በላይ ሞት የለም፣ ተስፋ ቆርጫለሁ” ሽማግሌው ሳግ እየተናነቃቸው ሀሳባቸውን ለማቋረጥ ተገድደዋል፡፡
አቶ ቱሉ በየነ ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው ምንጃር ነው፡፡ ከትውልድ ቀያቸው መቼ እንደወጡ ወሩንና ዓመቱን ባያውቁውም ከምንጃር ከወጡ በኋላ ደብረ ዘይት ለተወሠኑ ዓመታት መኖራቸውን ነግረውኛል፡፡ የደብረዘይት ኑሯቸው ስላልተመቻቸ የዛሬ 17 ዓመት አራት ኪሎ መጥተው መኖር ጀመሩ፡፡ “አሮጌው ቄራ አካባቢ ወ/ሮ አስካለ የተባለች ሴት ጋር በጥገኝነት ነው የኖርኩት” የሚሉት አቶ ቱሉ፤ አካል ጉዳተኛም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሶስት ልጆቻቸውና ባለቤታቸውን ይዘው በወጠሯት የላስቲክ ቤት ውስጥ አምስት ሆነው ዝናብና ብርድ በላያቸው ላይ እየወረደ ኑሮን ቀጥለዋል፡፡ “ቦታ ተመድቧል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠርተን እናስገባችኋለን ሲሉን ቆይተው፣ ምን አደረጋችሁልን ብለን ስንጠይቅ ለእናንተ የተመደበው በጀት ተቃጥሏል፤ አዲሱን ካቢኔ ጠይቁ አሉን” የሚሉት አቶ ቱሉ፤ ሹም ሽር እየተካሄደ አዳዲስ የወረዳ አስተዳዳሪዎች በመጡ ቁጥር የእነሱ ጉዳይ እየደበዘዘና እየተረሳ ከችግር የሚላቀቁበት ጊዜ እንደናፈቃቸው በምሬት ይናገራሉ፡፡ “ቤት ልንሠራላችሁ ነው ሲሉን እኛ ሌላ ነገር ባይኖረንም በአቅማችን በጉልበታችን እናግዛችሁ እስከማለት ደርሠን ነበር” የሚሉት አቶ ቱሉ፤ እንኳን አዲስ ቤት ሊገቡ ቀርቶ ጭራሽ ወንዝ ውስጥ ላስቲክ ወጥረው የሚኖሩበትን ቤት ከስምንት ጊዜ በላይ በእሳት እንዳጋዩት ይናገራሉ፡፡
“ከሌሊቱ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት እየመጡ ላስቲክ መጠለያችንን ሲያቃጥሉብን ወደ ሬዲዮ ጣቢያዎች ሄደን ብንናገርም ይህን ይፋ ያደረገ እና ጩኸታችንን የሠማ የለም” ትላለች፤ የሁለት ልጆች እናት የሆነችውና ስሟን መጥቀስ ያልፈለገች አንዲት እናት፡፡ “አሁን እዚህ ወንዝ ዳር ከመምጣታችን በፊት በሸራተን ሆቴል በኩል ከጭቃማው ቦታ የሚሻል ጠፈፍ ያለ ቦታ ላይ ነበርን፤ ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ የምስረታ በዓል እንግዶች ስለሚመጡ ከዚህ ልቀቁ ተብለን ወንዝ ውስጥ ደበቁን” የሚለው የሁሉም ችግረኞች ድምጽ ጆሮን ይሠቀጥጣል፡፡
አቶ አያሌው ነጋሽ የ53 ዓመት ጐልማሳ ናቸው። በቤት እጦት ምክንያት ልጆቻቸውን በተለያየ የዘመድ ቤት አስጠግተው፣ ከባለቤታቸው ጋር በላስቲክ ቤታቸው ውስጥ የችግር ኑሮ እየገፉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እኚህ ጎልማሳ አራት ኪሎ መኖር ከጀመሩ 18 ዓመታቸው ነው፡፡ አራት ኪሎ ከመምጣታቸው በፊት የነበራቸው ህይወት የውትድርና ነው፡፡ ኢህአዴግ ግንቦት ወር ላይ ሊገባ እርሳቸው መጋቢት ላይ በጦርነቱ ተመትተው ቦርድ ከወጡ በኋላ ወደ አራት ኪሎ እንደመጡ ይናገራሉ። “ቦታው ለልማት ይፈለጋል ተብሎ የአካባቢው ነዋሪ ስብሰባ ሲጠራ እኔም ቀበሌው ውስጥ እንደመኖሬና ተከራይ እንደመሆኔ በስብሰባው ላይ ተካፍዬ ነበር” የሚሉት አቶ አያሌው፤ የግል ይዞታና የቀበሌ ቤት ያላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እኛም ረጅም አመት በዚህ አካባቢ የኖርነው ጉዳይ ይታሰብበት የሚል ሀሳብ እንዳነሱም ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሀላፊዎቹ “ድሮም ተጠግታችሁ ነው የምትኖሩት አሁንም የሚያስጠጋችሁ ፈልጉ” የሚል ከአንድ ሀላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የማይጠበቅ ምላሽ ሰጡን ያሉት እኚህ ነዋሪ፤ “እኔ ሜዳ ላይ እንደምወድቅ ያወቅሁትና ተስፋ የቆረጥኩት ያን ጊዜ ነው” ይላሉ።
ከላይ የጠቀስነውን የስቃይ ኑሮ በላስቲክ ቤት የሚገፉትን 48 አባዎራዎች ሁኔታ ከርቀት ለመመልከት ከፒያሳ በአቋራጭ በሚጭነው ታክሲ ወደ ካሳንቺስ ሲመጡ አሻግረው ወደ ቤተመንግስቱ ይመልከቱ፡፡ የላስቲክ ቤት “መንደሮችን” ለመቃኘት አመቺው ሥፍራ ይሄ ነው፡፡ እነዚህ ቤት አልባ ዜጎች ትራሳቸው ቤተመንግስቱ ነው፤ ግርጌያቸው ደግሞ ባለ አምስት ኮከቡ ሸራተን አዲስ ሆቴል፡፡ የአገሪቱ አናት የሆነው ቤተመንግስት ስር በኩራዝ መብራት የሚኖሩ ስራ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት የማያገኙ ዜጎች “እየኖሩ” ነው፡፡ ጩኸታቸውን ቤተመንግስቱ እንዳይሰማ በቢጫና አረንጓዴ ቀለም ያጌጠው የቆርቀቆሮ አጥር የከለለው ይመስላል፡፡
48ቱ አባወራዎች እያንዳንዳቸው በአማካይ አምስት ቤተሰብ እንዳላቸው እነዚሁ ችግረኞች ይናገራሉ፡፡ በልመናና በጉልበት ስራ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ልጆቻቸው የምግብና መጠለያ እንዲሁም የመብራት እጦት ሰለባ በመሆናቸው ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ በርካታ የኤችአይቪኤድስ ታማሚዎች እንዳሉም ሰምተናል። ከነዚህም ውስጥ የህፃን ቃልኪዳን ተመስገን እናት ወ/ሮ መሰረት አንዷ ናት፡፡
ይሄውም ኑሮ ሆኖ የላስቲክ ቤታችንን ከስምንት ጊዜ በላይ አቃጥለውብናል” ይላሉ አቶ ጀማል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ የመምረጥ መመረጥ መብታቸው ተነፍጎ 48ቱም አባወራዎች የምርጫ ካርድ እንዳይወስዱ መከልከላቸውንም በእንባ እየታጠቡ አጫውተውናል፡፡ ወረዳውም ክ/ከተማውም የአካባቢው ነዋሪ መሆናችንን ያውቃል፤ ግማሾቻችን የቀበሌ መታወቂያ አለን፤ የግማሾቻችን የላስቲክ ቤታችንን ሲያቃጥሉ አብሮ ተቃጥሏል። እኛ እንደዜጋ አንቆጠርም፣ ቅኝ ግዛት ውስጥ ነው ያለነው” በማለት ይማረራሉ፡፡
ህገ ወጥ ናችሁ በሚል ልብሳቸው፣ የቤት እቃቸውና ንብረታቸው ተወስዶ በቀበሌው ግቢ ውስጥ በዝናብ እየበሰበሰ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ጀማል፤ አሁን ሻይ የሚጠጡበት ብርጭቆ እንኳን አጥተው አንዳንድ ሰዎች እያመጡ እንደሚረዷቸው ይናገራሉ፡፡ ”ከ10 ወር በፊት ቤት ተሰርቶ ሊሰጣችሁ ነው እያሉ ሲነግሩን ነበር፤ አሁን ግን የእናንተ በጀት ተቃጥሏል፤ ልንረዳችሁ አንችልም፤ እንደውም አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ” እያሉ እያንገላቱን ነው ብለዋል፡፡
“አሁን ገጠር አካባቢ ሁሉ መብራት ገብቷል እየተባለ እንሰማለን፤ እኛ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት ስር ቁጭ ብለን ኩራዝ እንጠቀማለን” ያሉት ችግረኞቹ፣ እዚህ መንደር ውስጥ የግልም የመንግስትም ጋዜጠኞች መግባት እንደወንጀል እንደሚቆጠር ይናገራሉ፡፡ “ለመሆኑ እንዴት ልትመጪ ቻልሽ? እዚህ እኮ መግባት የተከለከለ ነው” አሉኝ በግርምት፡፡ ከጭቃውና ከረጃጅሙ ሙጃ ሳር ጋር እየታገልንና ጫማችንን ጭቃ እያወለቀው የላስቲክ መንደሮቹ ጋር ስንደርስ፡፡ ከየትና ለምን እንደመጣን ጠየቁን፡፡ ነገርናቸው፤ ማመን አልቻሉም፡፡ “እኛ በማንም ሳይሆን በፈጣሪ እርዳታ ነው የምንኖረው፤ ለስንቱ ጮህን ግን ጩኸታችንን ወፍ ነው የለቀመው፤ አሁንም ምንም አትፈይዱልንም አንናገርም” አሉ አንድ ጎልማሳ፡፡ ሌላው ደግሞ “በጋዜጣ ብታወጡትም ባታወጡትም ጉዳዩን ጉዳያችሁ አድርጋችሁ ይህን ያህል ብሶታችንን እንድንተነፍስ በማድረጋችሁ እናመሰግናለን” አሉ፡፡ ሌላዋ ወ/ሮ ደግሞ “ሄዳችሁ ለፈለጋችሁት ተናገራችሁ፤ የነገራችኋቸው ቤት ይስጧችሁ” እየተባልን ከዚህም ብሶ ችግር እየፈጠሩብን ተቸግረናል፡፡” እኛ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለነው” ሲሉም ተናገሩ፡፡ መረጃውን እንስጥ አንስጥ በሚል በሀሳብ የተከፋፈሉት እኚህ ቅሬታ አቅራቢዎች ከዚህ በፊት መረጃ በመስጠታቸው የደረሰባቸውን ዛቻና ማስፈራራት ይጠቅሳሉ፡፡
እየጮኸች ብሶቷን በለቅሶ የነገረችኝ ህፃን ቃልኪዳን፤ “እኛ ነገ አድገን አገር እንረከባለን፤ እድል ከተሰጠን ብዙ መስራት እንችላለን፡፡ እዛ ደረጃ ለመድረስ ዛሬ ከለላና እንክብካቤ እንሻለን” በማለት አልቅሳለች፡፡ አቶ ጀማል በበኩላቸው፤ “ሚስቶቻችን እሰው ቤት ልብስ አጥበው፣ እንጀራ ጋግረው የገዛነው የቤት እቃችን በቀበሌው ግቢ ውስጥ በዝናብ እየበሰበሰ ነው፣ የልጆቻችን ልብስ ተወስዶ ህፃናት በብርድ ሊያልቁ ነው፤ ልብስና ንብረታችን እንዲመለስልን መንግስትን እንጠይቃለን” ብለዋል።
አቶ ቱሉ የተባሉት አዛውንት “እኛ እድሜያችን ገፍቷል፤ የልጆቻችን መጨረሻ ይናፍቀናል፤ አሁን መብራት ስለሌላቸው አይማሩም፤ ወደ ቀን ስራና ልመና ተሰማርተዋል፤ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጠን እንማፀናለን” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
“የእናንተ በጀት ተቃጥሏል” አዲሱን ካቢኔ ጠይቁ የሚሉን እኛ አዲስ ካቢኔ ፣በጀት መቃጠል የሚባል ነገር እንዴት እናውቃለን? መንግስት የሚያውቀን የአካባቢው ነዋሪ ነን፤ እንደዜጋ መፍትሄ ይሰጠን፤ እዚህ ወንዝ ውስጥ ተቀምጠን ጅብ ቢበላን ለመንግስት ለራሱ ስምም ጥሩ አይደለም” በማለት ተማፅነዋል፡፡
ስሟን መጥቀስ ያልፈለገች አንዲት ሴትም፤ “ለ18 እና 20 ዓመት በቀበሌ ጉዳዮች ስንሳተፍ በእድር ተካተን ወልደንና ከብደን በኖርንበት አካባቢ መንግስት አላውቃችሁም ማለቱ አሳፋሪ ነው፤ በመንግስት ተስፋ ቆርጠናል፤ አሁን ፈጣሪን የሚፈሩ ባለሀብቶች እንዲታደጉን እንጠይቃለን” ብላለች፡፡ ጉዳዩ የሚገኝበት ወረዳ ሄደን ለማጣራት ሙከራ ያደረግን ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀላፊ በዚህ ሳምንት አይገኙም የሚል ምላሽ በማግኘታችን የወረዳውን ምላሽ ማካተት አልቻልንም፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>