Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

እራህብ!

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)
እርሃብ እያገላበጠ ይቆላናል። ሲያስፈልገውም ይፈጨናል። ሲያሰኘው እንደ ድልህ ይደቁሰናል። ሲያሰኘውም መለመላችን እንዲህ ይገርፈናል። ወህ! ገና ሳልጀምረው እንዲህ ድክምክም አለኝ። ታካች —
የእኛው ድንቁ ኢትዮ – አፍሪካዊ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በርትተው የታገሉበት። መንፈሳዊ ሃብታቸውን ሳይሰስቱ የገበሩለት። ሥልጡኑን ብቃታቸውን በገፍ የመገቡት፤ የነጭን የበላይነት በረቂቅ ብልሃዊ ስልት ታግለው ያሸነፉበት፤ ዬታላቁ ኢትዮ አፍሪካዊ ውለታን በስውር የሰነቀው ዬዐለሙ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ከፍ ካለ ደረጃ ደርሶ እንሆ በብራዚል የሚሊዮንን መንፈስ በቅርብም በሩቅም ከተሞ ሲያፍነከንክ፤ ሲያስጨፍር፤ ሲያስደንስ፤ ማጫ ሲያማታ፤ ምሾ ሲያስደርድርም፤ ወይንም መወድስ ሲደረደርለት፤ እንዲሁም በሰላ አንደበት ሲሳሳልም በቀለማምሙ ፍቅር በመስተዋድድ አጭቶ ሲያጋባ፤ ሲያጣምር …. ፍልቅልቅ …
ኮቢው- ብራናው ሲያሸበሽቡለት፤ እልልታው፤ ፉከራው፤ እልሁ፤ ቅጣቱ፤ ዳኝነቱ፤ የሜዳ ፍንጠዛ፤ የመረብ ኩልልታ፤ የድንብልብ ፍጥጫ፤ የአራጋቢ ሩጫ፤ የተፈጥሮ ኩልኩልታ፤ የሰንደቅዓለማ ሽለላ፤ የማህል ዳኛ ነጋሪት -ጉስምታው፤ የአሰልጣኙ ቁጭ ብድግ ቡረቃ፣ የእግረኛ ሰርገኛ – የቴስተኛው ቅልቅል፤ የበረኛ ፈረሰኛ፤ ውሃውም አድሎት ዘንድሮ በቸረቸራ ታድሟል። አቤት! ያቺ 90 ደቂቃ የሞት የሽረት ትግል፤ የውጭ ግቢ ነፍስ ስንደቃ። ግን የፍሰሃ አውደ ምህረት። እማማ አፍሪካ በመታደሟም የደም ህትምት ሂደቱ ሆነ ውስጣዊነቱ ከልብም ነበር ማለት ይቻላል – ለእኔ።
ነገር ግን ተሳታፊ ሃገሮች በቀረቡ ቁጥር ልቤ ቁስል – ክስል – እርር – ትክን – ቅስሜ ስብር ይላል። የተፈጥሮ መስኮቶቼ ተከፍተው ጠብታቸውን ያለ ይግባኝ በተፋሰሳቸው ይለቁታል። እኔም እንዳሻችሁ ብዬ ፈቀድኩላቸው። ፍል!
አንዲት ታላቅ ሀገር፤ የሰው ልጅ መፈጠሪያ ሀገር፤ የነጻነት የተግባር ትምህርት ቤት ሀገር ዛሬ አንድ መለያ ወላዊ የሆነ የጋራ መዝሙር የሌላት፤ በነፃነት የመኖሯ ትርጉም ተቀጥቅጦ መቅኖው የተዘረፈበት፤ ከአለም ማዕቀፍ ተነጥላ በበቀል የምትከተከት፣ በጠላቷ ሉዑላዊነቷን የተቀማች ሀገር፤ ለዛውም ከአብራኳ በበቀሉ ተወሳኮች – የምትቀጣ። ወያኔ እንዲህ አድርጎ ነው ኢትዮጵያዊነትን የተለተለው – በበቀል። ይህ ዘመን እንዴት ይነበብ? እንዴት ይደመጥ? ለመሆኑ ከልባችን ገብቷልን? ስርስር አድርጎ አጥንታችን ፈትሾታልን? እህህህ!
የዛሬዋ ብራዚል የፖርቹጋል ቅኝ ተገዢ ነበረች፤ በጠቅላላ የላቲን አሜሪካ ሀገሮችም፤ ዛሬ በ60 ዎቹ ነፃነታቸውን ያገኙት አፍሪካዊት ሀገራት ሳይቀር አንገታቸውን ቀና አድርገው ብሄራዊ መዝሙራቸውን በጉልበታማ የተመሰጠ መንፈስ በህብረት ይዘምሩታል፤ የአብነቷ ሀገር ኢትዮጵያ ልጆች ግን …. ተርጉሙት አቅም ካላችሁ … እባካችሁ?!
እያንዳንዱ ሀገር ከነደጋፊው ወደ ብራዚል ተጓጉዟል። ቤት ሆኖ የሚመለከተውም በመንፈሱ ከዛው ከደራው የኳስ ድለቃ ፌስታ ነው። እኛም እንደ ህዝብ እንደ ዓለም ታዳሚነታችን ከጥበቡ ፍቅር ጋር ያለን ሰወች በትጋት እንከታተላለን። ግን በሀዘን ድንኳናችነን ጥለን ትካዜን እዬዘገን።
የትካዜው ምንጭ የይድነቃቸው ልጆች ባለመሳተፋቸው አይደለም – በፍጹም። ያን የተከተረ በምናምን የተተበተበ ድሪቶ ጉድ ጥሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ማጣሪያው ላይ ነበሩ። በአፍሪካ ዋንጫም ላይ ታዳሚ ነበሩ። ላደረጉት መልካም ተሳትፎ ይመስገኑ። እኔ የሚያርመጠምጠኝ ግን ከጽንፍ አስከ ጽንፍ እያንዳንዱ ሀገር „አንድ ህዘብ አንድ ቡድን“ ብሎ ብሄራዊ መዝመሩን በህብርት ሲዘምርና በብሄራዊ ስሜት በፍቅር፣ በሲቃ ፍንድቅድቅ ብሎ እንደዛ ተመስጦ ወጥነቱ ሲያምርበት፤ ሲያለቅሱም ሳይ ሃዘኔን ለመግለጽ አቅም ያንሰኛል። እኛስ? ይህ ነው ኮረኮንቹ ህመም፤ ይህ ነው የቋቁሻማው ዘመን መርዝ፤ ይህ ነው የዚህ ጠቀራማ ዘመን ዬዞገኝነት ኪሳራ ሂደት? በአለም ተለይታ ህዝቦቿ የሚስማሙበት አንድ ብሄራዊ መዝሙር የሌለት ሀገር – ኢትዮጵያ!
ያ … ውስጥን ገልጦ፤ አኃታዊነትን በፍቅር ፈጥሮ፤ እናትና ልጅን የሚያገናኘው የጋራ ብሄራዊ ጸሎት – የጋራ ልዑቅ ዝማሬ – የወል መንፈሳዊ ቅኔዊ ሃዲድ የክብር – የሞገስ መግለጫ ስብርብር አደረገው – ወያኔ። እራሱ የመንፈሱን ቁመና መለመለው። የዚህ ውስጥን ትክን – ከእሳት እንደገባ ፕላስቲክ ከሙትርትር የሚያደርገው ደባ ሥሩን ስናገኘው፤ ልዕልት ኢትዮጵያ – እመቤት ኢትዮጵያ – ንግሥት ኢትዮጵያ በባዕድ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለዛውም በበቀል በመሸገ አኳኋን ታሽጋና ታፍና እዬተገዛች – እዬተገዘገዘች ያለች መሆኗን ያመሳጥርልናል።
ይህን ትውልዱ ከቶውንም መመዘኛ ከቶ ሊገኝለት የማይችለውን፤ የሞት ሞቱ ጥቃቱን ከውስጡ ሆኖ ውስጡን በመፈተሽ፤ መፍትሄውን በማያዳግም ሁኔታ ማመንጨት ያለበት ይመስለኛል። ከዚህ በላይ አንገት የሚያስደፋ ሥር ሰደደ ውርድት የለምና። እኔ የለሁም። አንተም የለህም። እርሶዎም የሉም። አንቺም የለሽም። ሃቁ ይህ ነው። በአጥንትና በደም የቆዬች፣ የኖረች ሀገር ብሄራዊ መዝሙር አልባ – በእኛ ዘመን።
የወያኔ መዝሙር ለእኔ ምኔም ነው። እንዲያውም አላውቀውም። ማወቅም አልፈልግም – ማድመጥም። ኢትዮጵያዊነትን ለረገጠ ለጎሳ ነጋዴ መንፈሴን አልፈቅድለትምና። ይህን ረመጥ ለመታደግ – በምን ቋንቋ? በምን ፍልስፍና? በምን ዶግማ? ያን የቀደመ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለምን በውስጥነት የሚያውለበለበውን ሞገዳማ ንጹህ መንፈስ የሚፈጥር፤ ውስጥን ፈንቅሎ የሚወጣውን የቃል ኪዳን ማደሻ ሥርዓተ – መወደስ መፍጥር ይቻላል? መቼስ? እንዴትስ?! አቅም ይገዛል ወይንስ ይወለዳል? መልሱ የቤት ሥራ – ለእኔዎቹ። ጌጦቼ የሐገሬ ልጆች – ያጣነው ብዙ ክብር ነው። የተራቆትነው ከመጠነ ሰፊ የእኛነት ረቂቅ ንጥረ ቅማማት ነው። የተነጠልነው ከደማቁ ውበታችን ነው።
አለሁልሽ እናቴ! ከአንቺ በፊት እኔ! ቃሌ ይታደስ – በፊትሽ! እኔነቴን እንሆ ተቀበይኝ! ውሉ እንዴት ይታሰር ….?! እንዴት? እንዴት? እንዴት? መከራዋን በአብሮነት ለመታገስ፤ ሐሤቷን ለመታደም – ፍላጎቷን ለመከወን፤ ትእዛዟን ለመቀበል እንዴት ይቻል? ይህ አኮ በጋለ ማረሻ ልብን የመተርተር ያህል ነው – ህመሙ ከተሰማን? ? ?
ህቃታ ተሸክሞ
መንፈስሽ እንዲህ ተሰንጎ – ታርሶ – ታሞ
ታወከ በግርግር – በአታሞ!
መወድስሽ አለቀሰ
እንደራበው – በቋሳ ተጠበሰ – ተበጠሰ። አለቀሰ – አስለቀሰ!
የጠብታ ስብስብ -
ኤሉሄን ይሰብስብ!
ነገን አምጦ ይውለድ
እንዲወለድ!
የእኔ ውቦች የሐገሬ ልጆች አለመሸነፋችን የሚረጋገጠው ወያኔ ባሰናዳው መጠራቅቅ ገብተን አለመቀርቀራችን ስናረጋግጥ ብቻ ነው። መርዝነቱን በአትኩሮትና በማስተዋል መርምረን ከራሳችን ጋር መታረቅ ስንችል ብቻ ነው። ማሸነፍ! አዎን – እራስን ማሸነፍ ግማሹ የመፍትሄ ድላችን ነው። በማሸነፍ ሙቀት እኛን ከነተፍጥሯችን ማግኘት ይቻላል። በስተቀር ግን – እም!
እንዳመመኝ = እንደ ተከዝኩ = አንገቴን እንደ ደደፋሁ ልሰናበት። ጊዜው ከኖራችሁ በዚህ ሊንክ Radio Tsegaye ወይንም www.tsegaye.ethio.info Aktuell Sendung „የተሰፋ ናፋቂን ግጥም“ አዳምጡ ትእዛዝ አይደለም ትሁት አስተያዬት እንጂ። የ19.06.2014ን ፕሮግራም። አመሰግንኳችሁ ከልብ – በፍቅር። ቸር እንሰንብት – ቸር ያሰማን። አሜን!

የራበው ዕህል ፍለጋ ይማስን – ነገን ማኖር እንዲችል!
የጎጥ ጋጥ – ማጥ!

እግዚአብሄርይስጥልኝ!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>