Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የአማራ ጉዳይ፤ አለ? ወይስ የለም?

$
0
0

መስፍን ወልደ ማርያም

ግንቦት 2006

mesfinተናግሬ ነበር ማለት ዋጋ የሌለው የወሬ ማጌጫ ነው፤ እስቲ ፍቀዱልኝና ልጠቀምበት፤ ከወያኔ ዋና ምሁር፣ ከመለስ ጋር ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ፊት-ለፊት በቴሌቪዥን በተገኛኘን ጊዜ ‹‹አማራ የሚባል ጎሣ የለም፡›› በማለቴ መለስ ዜናዊና ጭፍሮቹ ብቻ ሳይሆኑ ‹‹አማራ-ነን ባዮች›› በቃልም፣ በጽሑፍም፣ በቴሌፎንም ልክ-ልኬን እየነገሩኝ አንጀታቸውን ቅቤ አጠጥተው ነበር፤ ‹አንዲት ሴት ደውለው እብድና ዘበናይ የልቡን ይናገራል፤› ብለውኛል፤ አንድ ሰው የተናገረው ስሕተት ከሆነ ስሕተቱን በማስረጃ ማጋለጥና የራስን ሀሳብ በማስረጃ መትከል ነው፤ እውቀት የሚዳብረው፣ ሰዎች የሚማሩትና በእድገት ጎዳና የሚጓዙት በተጨባጭ ማስረጃ መነጋገር ሲችሉ ብቻ ነው፤ እኔ አማራ የለም፣ ዜሮ (0) ነው፤ አልሁ፤ አማራ አለ፣ አንድ አለ፤ (1) ነው ያለ ሰው የአንድን ዋጋ ማሳየት አለበት፤ አማራ የለም የሚል ዜሮ ነው ማለቱ ስለሆነ ከሌለ ነገር ምንም አይጠብቅም፤ ከአለ ነገር (ከ1) ብዙ ነገሮችን መጠበቅ ይቻላል።

ዱሮ በልጅነታችን ጭራቅ የሚሉት ማስፈራሪያ ነበረ፤ በአለፉት ሃያ ሦስት ዓመታት አማራ የሚባል ጭራቅ ማስፈራሪያ፣ የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ቋት እንደሆነ ሲነገር ቆየ፤ መለስ ዜናዊም እየደጋገመ ‹አከርካሪቱን ሰብረን ሁለተኛ እንዳያንሰራራ› እናደርገዋለን እያለ እንደዛተ የተሰበረውን አከርካሪት ሳያይ ሞተ፤ በሕይወትም እያለ ቢሆን መለስ ዜናዊ አከርካሪቱን እሰብረዋለሁ የሚለውን አማራ የተባለ ስያሜ እንደሹመት ለነበረከት ስምዖንና ለነተፈራ ዋልዋ ይሰጥ ነበር፤ የክብር ጎሣ እንበለው! ራሱም ቢሆን ከዚህ የክብር ጎሣ ቤተሰብነት አልራቀም፤ አከርካሪቱ እንኳን ሊሰበር አልተገኘም!

ስንት ሺህ ሰዎች አማራ ናችሁ እየተባሉ ከስንት ስፍራ ተፈናቀሉ? አማራ ማለት እነዚሁ የተፈናቀሉት፣ በየጫካው የተገደሉትና የተሰደዱት ብቻ ናቸው? ሌሎችም ካሉ የጎሣ ዝምድና ሳይስባቸውና ከተፈናቀሉት ጋር አብሮ ለመቆም ለምን አልቻሉም? በጋምቤላ በደረገው ጭፍጨፋ የተጨፈጨፉት ጎሣዎች በጣም ትንሽም ቢሆኑ ከካናዳ እስከ አውስትራልያ ዓለምን ያዳራሱት የጎሣ ዝምድና ስሜት ለምን ለእነዚህ አማራ ለተባሉት ተፈናቃዮች አልሠራም? እንግዲህ አማራ እየተባሉ የሚፈናቀሉት፣ የሚገደሉትና የሚሰቃዩት ዘመድና ደጋፊ የሌላቸው ሰዎች ናቸው ማለት ነው፤ ሰውነታቸውም ቢሆን በሕግ ያልተረጋገጠላቸው፣ ሕግ የማይመክትላቸው ናቸው ማለት ነው፤ ይህንን ክርክር ከገፋንበት ዜግነታቸውንም የምንጠራጠርበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን፤ ደርግ በጎሣ ላይ የተመሠረተ የውትድርና ሥልጠና ያደረገ ይመስለኛልና በዚህ ጉዳይ ላይ የደርግ ባለሥልጣኖች፣ በተለይም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አንድ ቀን የሚነግሩን ይኖራል የሚል ግምት አለኝ።

አጥቂና ጨቋኝ ነፍጠኛ የሚባለው ሕዝብ ሲጠቃና ሲበደል ከኡኡታ በቀር ድምጹ የማይሰማው ትርጉሙ የህልውና ነው? ወይስ የወኔ? በሌላ አነጋገር አማራ የሚባል ጎሣ በእርግጥ አለ? ወይስ የለም? ከአለ የሚወራለትን ነፍጠኛነትና ወኔ ምን ዓይነት ብል በላው? ይህ ክርክር ከሃያ ሦስት ዓመታት በፊት አማራ የሚባል ጎሣ አለ ብለው የሞገቱኝን ሰዎች (የሞተውን መለስንና ያሉትን ጓደኞቹን ጭምር)፣ የመላው አማራ ይባል የነበረውን ድርጅት፣ ብአዴን የሚባለውን የወያኔ ድርጅት መሠረተ-አልባነት ለማሳየት እንጂ የሌለውንና ከዚህ በፊት ተቆስቁሶ ያልተነሣውን ጎሣ ለማነሣሣት አይደለም፤ የሌለ ነገር ቢቆሰቁሱት አይነሣም,

በአለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ውስጥ እነዚህን አማራ እየተባሉ የሚፈናቀሉትን፣ የሚገደሉትን፣ የሚሰቃዩትን ሁሉ ‹‹ሰዎች›› ብናደርጋቸውና ሰዎች ብንላቸውስ? ሰው መሆን የተፈጥሮ ነው፤ ልለውጥህ ቢሉት አይለወጥም፤ ሰው ሆኖ ተወልዶ ሰው ሆኖ ይሞታል፤ ሰው መሆናቸውን ወንጀል የማድረግ ዝንባሌ የሚኖረው ሰይጣን ብቻ ይመስለኛል።

ወይም አማራ የክርስቲያን ሃይማኖትን ተከታይነት የሚገልጽ ስያሜ አድርገን ብንወስደው የእነዚህ ሰዎች መፈናቀል፣ መገደል፣ መሰቃየትና መሰደድ ክርስቲያኖች እንዲጠፉ ለማድረግ ነው? ይህ ከሆነ አንድ ጸረ-ክርስቲያን ኃይል አለ ማለት ይመስለኛል፤ ይህ መደምደሚያ ችግር አለበት፤ ፓትርያርክና ሊቃነ ጳጳሳት ሰይሞ ጸረ-ክርስቲያን ተግባር ነጋ-ጠባ ማከሄድ አታላዩንና ተታላዩን ለመለየት ያስቸግራል።

እነዚህን አማራ እየተባሉ የሚፈናቀሉትን ‹‹ኢትዮጵያውያን›› ብንላቸውስ? ኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ ዜግነት ነው፤ ዜግነት አንድ ሕዝብ በደሙና በአጥንቱ የሚገነባው ነው፤ ዜግነት የሕግ ከለላ አለው፤ ይህንን የሕግ ከላላ ተነፍገው በኢትዮጵያ ምድር ከያለበት የሚፈናቀሉት፣ የሚገደሉት፣ የሚሰቃዩትና የሚሰደዱት ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ለማጥፋት የተደራጀ ኃይል አለ ማለት ነው።

አንግዲህ አማራ የሚባሉት ነፍጥ የሌላቸው ነፍጠኞች በምድረ ኢትዮጵያ ሰዎችም ሆነው፣ ክርስቲያኖችም ሆነው፣ ኢትዮጵያውያንም ሆነው መኖር አይፈቀድላቸውም ማለት ነው ወደሚል መደምደሚያ በግድ መድረሳችን ነው፤ ያዋጣል ወይ?

ግራም ነፈሰ ቀኝ አማራ የሚባል ጎሣ እንደሌላ በስያሜው ላይ የሚደርስበትን ጥቃት ለመመከት እንኳን ባለመቻሉ አስመስክሯል፤ በሕይወት ላለ በህልውና ላይ የሚደርስበትን ጥቃት መመከትና መከላከል የተፈጥሮ ነው፤ ይህ ሳይሆን ሲቀር ህልውና የለም።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>