ፋሽስታዊ ፕሮፖጋንዳው እና ምላሻችን!( pdf )
ሐምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዘረኛውና ፋሽስታዊ ወያኔ፣ የኢትዮጵያዊያንን የትግል መንፈስ ለመስበር እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነፃነትና ለፍትህ የሚያደርገውን ትግል ወኔ ለመስለብ ያቀደበትን የመጀመሪያውን ፕሮፖጋንዳ ለቀቀ። የህግ ልጓም የማያውቀው ፋሽስት በግፍ የያዛቸውን ሰዎችን እይስሙላው ፍርድ ቤት እንኳን ከመቅረባቸው በፊት “ወንጀለኛ” እያለ እንዲህ ዓይነቱ ፕሮፖጋንዳ እንደሚነዛባቸው ተደጋግሞ የታየ በመሆኑ ይህ ፕሮፖጋንዳ የሚጠበቅ ነበር። ሆኖም ግን ፕሮፖጋንዳው ያዘጋጁ ሰዎች ተስፋ ያደረጉትን ውጤት ያመጣ አልሆነም። ወደፊት ደግሞ ሌሎች ሙከራዎች ይደረጉ ይሆናል፤ ውጤታቸው ግን ከዚህኛው የተለየ እንደማይሆን ይገመታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢቲቪ የእውነት ጥፍጣፊ እንኳን እንደማይገኝ ያውቃል።
በአሁኑ ተቆራርጦ በተለጣጠፈ ፊልም በታጀበው ፕሮፖጋንዳ ውስጥ፣ መሪያችን አንዳርጋቸው ጽጌ በምግብና ውሀ እጦት ብቻ ሳይሆን በተፈጸመበት የተለያዩ የማሰቃያ ወንጀሎች ብዛት አካሉ መዳከሙ ይታያል። ያም ሆኖ ግን ከእሱ ወጥተው እንድንሰማቸው የተደረጉት ቃላት የመንፈሱን ጥንካሬ ገላጮች ናቸው። እሱ ሥራውን መጨረሱንና በዚህም ምክንያት ህሊናው የተረጋጋ መሆኑን ነው የሰማናቸው ቃላት የነገሩን። በዚህ አጭር አጋጣሚ እሱ ግዴታውን ማጠናቀቁ፤ ሀገራችን ከወያኔ ፋስሽቶች ነፃ የማውጣት ኃላፊነቱ በእኛ ትከሻ ላይ መውደቁን ነገረን። ለዜናው ማጀቢያነት የገቡት ፎቶግራፎችም መሪያችን ፈታኝ በሆነ የተፈጥሮ አካባቢ የከፈለውን መስዋዕትነት የሚመሰክሩ ሆነው ተገኙ።
ጀግናው አንዳርጋቸው ጽጌን በተጎሳቆለ ሁኔታ ማየት ስሜትን የሚጎዳ ቢሆንም የመጀመሪያው ስሜት ካለፈ በኋላ ከፊልሙ በአዕምሮዓችን የሚቀረው ከላይ በአጭሩ የተገለፁት ጥንካሬውና ኃላፊነትን ወደ እኛ በይፋ ያስተላለፈበት አጋጣሚ መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የተሠራው የመጀመሪያ በምስል የተደገፈ የወያኔ ፕሮፖጋንዳ ከታለበት ዓላማ በተፃራሪ የወያኔን ሹማምንት አውሬነትና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ትልቅነት አሳይቷል።
ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለፀው ይህ የመጀመሪያ የፕሮፖጋንዳ ሥራ እንጂ የመጨረሻው አይደለም። የማስተዋል ችሎታ ያነሳቸው የወያኔ ፕሮፖጋንዲስቶችም ፊልማቸው ቁጣን ማባባሱ ሲያዩ ፈጥነውም ይሁን ዘግይተው ከዚህ በተለየ አቀራረብ መመለሳቸው አይቀርም። ስለሆነም የኢትዮጵያን ሕዝብ ከወያኔ የጅል ፕሮፖጋንዳ መንፈሱን እንዲጠብቅ ማሳሰብ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል። የወያኔ ፕሮፖጋንዲስቶች አሁን የደረሰባቸውን ኪሳራ ለማካካስ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ያላለውን አለ ይሉን ይሆናል፤ ቃላትን ፈጥረው እሱ የተናገራቸው ያስመስሉም ይሆናል። የቻይና ቴክኖሎጂ ከወያኔ ድድብና ጋር ሲደባለቅ ምን እንደሚያመጣ አስቀድሞ መገመት ያዳግታል። ኢቲቪ ለዘመናት የተካነበትን ውሸት የመፈብረክ ክህሎትን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግያ አጋጣሚ አድርጎ ሊጠቀምበት ስለሚችል መንፈሳዊ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው።
ከዚህ በተረፈ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥብቅ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ አለ።
ጀግናው፣ ብልሁና አስታራቂው አንዳርጋቸው ጽጌ ኢትዮጵያን በማጥፋት ዓላማ ባበሩ፤ ዘርፈውና በልተው በማይጠግቡ፤ የንፁሃንን ደም መጠጣት በለመዱ ዘረኞችና ፋሽስቶች መዳፍ ውስጥ ነው። ለዚህ ምላሻችን ምንድነው? ገና ከአሁኑ እንደታየው በሰላማዊ መንገድ ሥርዓቱን ለመገዳደር የደፈሩ ወጣቶችን ለማሰር አንዳርጋቸው ጽጌን ሰበብ ሲያደርግ የኛ ምላሽ ምንድነው? አገራችን ያፈራቻቸው ምርጥ ዜጎች በሙሉ ወይ ታስረው አልያም ተሰደው ሲያልቁ እያየን ምን እየሠራን ነው? ነፃነታችንና አገራችን ለህወሓት ዘረኞች አስረክበን እንቀመጣለን? በጭራሽ!
አንዳርጋቸው ጽጌ የተመቻቸ ኑሮዉንና ልጆቹን ጥሎ ለነፃነቱና ለሀገሩ የዘመተ ጀግና ነው። ከእኛም የሚፈለገው ይህንኑ ነው። ጀግናችንን ብቻ ሳይሆን አገራችንም ጭምር ከታሰረችበት ማስፈታት የምንችለው አንዳርጋቸው ጽጌ በተጓዘበት መንገድ ስንጓዝ ነው። ለዚህ የተዘጋጀ ሁሉ “አለሁ!” ይበል።
ማንም ዝርዝር መመሪያ በሬድዮ ወይም በቴሌቪዥን እንዲነገረው አይጠብቅ። የቆረጠና የመረረው ጀግኖች የሚገኙበት ድረስ ሄዶ ይቀላቀል። ከልቡ የቆረጠና ጥቂት ፍለጋ ያደረገ ሁሉ መንገዱን አያጣም።
- ቀደም ሲል ንቅናቄዓችን – ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ – ያወጣውን የመጀመሪያ እርከን የትግል ጥሪ ተግባሪዊ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በቁርጠኝነት በተግባራዊ ትግልቶች ይመንዘሩት፤
- የተቆጣ፣ ጥቃት፤ ውርደት፤ ግፍ የመረረው ሁሉ፤ ለነፃነቱ ግድ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የስነ ልቦና ዝግጅት ያድርግ፤ ከወያኔ ሰላዮች ራሱን ተከላክሎ በያለበት በጥብቅ ከሚያምናቸው ጋር በመሆን በየአካባቢው በቡድን በቡድን ይደራጅ፤ በወያኔ ቀንደኛ ሹሞችና ወንጀለኞች ላይ ይሰልል፤ መረጃዎችን ለንቅናቄዓችን ይላክ።
- በየአካባቢያችን የወያኔን ፋሽስቶችን የሚያሸማቅቁ፣ በሁለተናዊ መልኩ (በስነልቦና፤ ማኅበራዊ ተጽዕኖ በመፍጠር፣ በኢኮኖሚ) ጉልበታቸውን የሚቦረቡሩ፣ የሚያድክማቸው፣ ውስጣቸውን የሚሸረሽራቸው ሥራዎችን በቁጭትና በእልህ ሳናሰልስ ተግባራዊ እናድርግ።
- በሕዝብ ጎራ ሳይሆን በጥቂቶቹ በወያኔ ፋሽስቶች ጎራ ፍርሃትና ብርክ የሚፈጥሩ የጀግንነት ሥራዎችን በቡድን በመደራጀት በመላው ዓለምና በኢትዮጵያ ውስጥ በብልሃት፣ በጥናትና በስልት በመተግበር ሕዝባዊ እምቢተኝነት እሁን እናድርግ፡፡
- ሁሉም ኢትዮጵያዊን የሚቻለውን ሁሉ ትንሿንም ጠጠር ብትሆን ወያኔና ጭፍሮቹ ላይ እንወርውር።
- በደጀን የተሰለፈው ኃይል ደግሞ የዘማቹን ስንቅ በማዘጋጀት በገንዘቡ፤ በጉልበቱ፤ በመረጃ ይተባበር።
የአገር ማዳን የክተት ዘመቻ ላይ ነንና በእያንዳንዱ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሳንጠብቅ ቀበቶዓችንን አጠባብቀን እንነሳ። ድል እናደርጋለን!! አገራችን ከዘረኞችና ፋሽስቶች መንጋጋ መንጭቀን እናወጣታለን!!
ድል ለኢትጵያ ሕዝብ !!
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ