ከዳኛቸው ቢያድግልኝ
የእለት እለቱን የትግራይ ውሎ የሚያበስረን እውነትን ምርኩዝ አድርጎ አረናን ወግኖ የትግራይ ነፃ አውጪዎችን ነፃነት ሳይሆን ሙልቅ ነው ያወጣችሁን ዲሞክራሲን ሳይሆን ሀፍረትን አከናነባችሁን ብሎ በመሞገቱ ከጠላት ተፈረጀ። ሴት ወይም ህፃን ልጅን እንደመከላከያ ከፊቱ አድርጎ ማምለጫ እንደሚፈልግ ዘራፊ የትግራይን ሕዝብ መሸሸጊያ ነው ያደረጋችሁት በወገኑ ማስጠላትና ያለናንተ ሕልውና የሌለው እንዲመስለው ማድረግን ነው የያዛችሁት። መበለጥ በቃን መሳርያ መሆን በቃን። በመቀሌ የገነባችሁት የአፓርታይድ መንደር የትግል መነሻችሁ የዝቅተኝነት ስሜት ግባችሁ ደግሞ ሁሉን ማግበስበስ መሆኑን ያሳያል በማለቱ ዳግማይ ጭፍጨፋ በሀውዜን ብሎ በመመስከሩ አሸበራቸውና በመጨረሻ ከለመዱት እስርቤት ጨመሩት።
አብርሃ አሁን ያለበትም አይታወቅምና የሚደርስበትን በደልና ጭካኔም አናውቀውም። ስለሁኔታውም የሚነግረን መኖሩን ገና አናውቅም። ኢትዮጵያን የምንል፣ ነፃነትና ፍትህ ለሁሉም የምንል ግን ስለ አብርሃ ይጨንቀናል። ከመንደርና ከጎጥ በላይ በመሆን ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ ደግሞ ይበልጥ ያስተሳስረናል የጠላቶቻችንን መንደርም ያሸብራል። የመከራው መብዛት፣ የስቃያችን መጨረሻ ማጣት ዋናው ምክንያት የጠላት አፈራረጃችንና መፍትሄ አፈላለጋችን የሩቁንና የቅርቡና ያላገናዘበ በመሆኑ ነጣጥለው ለሚመቱን ደካሞች እንዲመቻቸው ሆነ። ከዚህ አዙሪት በራሳችን እውቀትና አቅም በጊዜው መውጣት አልቻልንም።
አሁን ግን በግድ ወደ አንድ ጎራ እንድንመጣ እየተገፋን ነው ይህንንም አውቀን በደል ለደረሰባቸው ሁሉ በጋራ የምንጮህ ልንሆን ይገባል። ደቡብ ሱዳንን አስጨንቀን፣ ጅቡቲንና የኬንያ መንግስትን አውግዘን ቢሆን ኖሮ ምናልባት የመንም ባልተጨመረች ነበር። በደሎች ሁሉ እንዲያስቆጡን ወደ ውጤትም እንድንሄድ አንድ መሆን ቢያቅተን የጋራ ስምምነት ያሻናል። ከጊዳሚ እስከ ወሎንኮሚ ከመቀሌ እስከ ባሌ ከሀረር እስከ ጎንደር ኢትዮጵያን ያሉ ነፃነት እንሻለን ያሉ ሁሉ በየጉሮኖው ተጥለዋል። ወያኔ ይቅር ብላ ያለፈቺው ይሁን ብላ የተወቺው አንዳችም ሰው የለም። አድፍጣ ለማደን የማትደክም አድና በልታም ለመጥገብ ያልታደለች የእርጉማን ጥርቅም ነች። ቁጣችን ግን ወደ ወያኔ ብቻ ሳይሆን ወደራሳችንም ሊሆን ይገባል። ያሳበጥናት ያደለብናት አውሬነቷን እያደነቅን እስክትበላን እስር አስሯ የሄድን እኛው ነን። ጉልበት የሆናት መንገድም ያሳየናት እኛው ነን። እስኪበቃን አቅምሳናለችና በቃን ማለት ደግሞ የኛው ስራ ነው። አስጥሉን ብለን ብንጮህ የሚደርስልን የለምና
የኛ ነፃነት በኛው እጅ ናት።
እንደ አብርሃ ያሉ እውነትን የሚደፍሩ ኢትዮጵያዊነትን የሚያከብሩ እንዲበዙልን ምኞቴ ነው። አብርሃ ለእውነት እስከቆምክ፣ ለነፃነት እስከታገልክ ድረስ ከጎንህ የማይቆም የለምና ጽናትና መበረታታት እንዲኖርህ እመኛለሁ። በርካቶች ዝም ባሉበት ሰዐት ዘራቸውን ከሀገራቸው አስበልጠው ለጥቅማቸው በቆሙበት አስቸጋሪ ቦታና ሁኔታ ብቅ ያልክ ብርቱ ነህና ከትንሿ እስር ቤት ወደ ትልቁ መጥተህ ያንን እስር ቤት እንድናፈርሰው ምኞቴ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!